Sunday, December 7, 2014

የ72 አመቱ አዛውንት በወያኔ መንግስት በአሸባሪነት ተከሰሱ

December 7,2014

ነገረ ኢትዮጵያ
የ72 አመቱ አቶ ቀኖ አባጆቢር የሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ውስጥ የጥበቃ ሰራተኛ ናቸው፡፡ የሚኖሩት ከ10 አመት ልቻቸው ጋር ነው፡፡ ይህን ልጅ እሳቸው ብቻ ነው የሚያሳድጉት፡፡ ትናንት ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ከታፈሱ ከሰዓታት በኋላ ስራ ውለው ወደ ቤታቸው ሲሄዱ በደህንነቶች ታፈኑ፡፡ አቶ ቀኖ የጥበቃ ስራ ከመስራት ውጭ ሰልፉ አስተባባሪም ተሳታፊም አልነበሩም፡፡ ግን ታጥሮ ከሰነበተው የሰማያዊ ቢሮ የወጣ ሁሉ ሲለቀም ነበርና እሳቸውንም አፈኗቸው፡፡ ምን አልባትም ተደብድበው ይሆናል፡፡
ይህ ስርዓት እነ ይልቃልን፣ ብርሃኑን፣ አቤልን፣ በላይን፣ ጣይቱዎቹን....ሰማያዊን ብቻ አይደለም የሚፈራው፣ የሚያፍነው፣ የሚያፍሰው፣ የሚደበድበው፡፡ አቶ ቀኖንም የሆነ ነገር ያደርጋሉ ወይንም አድርገዋል በሚል (በራሱ ትርጉም) አፍኖ አስሯቸዋል፡፡ አሁን አቶ ቀኖ አዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ ይገኛሉ፡፡ አይጠየቁም፡፡ ምን አልባትም ጨለማ ቤት ውስጥ ከታሰሩት መካከል ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡
ኢቲቪ ትናንት ታፍሰው የታሰሩትንም ሆነ የታፈኑትን ‹‹ከአሸባሪ ድርጅት ጋር በመስራት›› ሲል የተለመደ ፍረጃውን አሽጎድጉዷል፡፡ እንግዲህ ለስርዓቱ የ72 አመቱ አቶ ቀኖም ከ‹‹አሸባሪዎች›› ጋር አሲረዋል ማለት ነው፡፡
የአቶ ቀኖ መታፈን የስርዓቱን ቅጥ ያጣ ፍርሃት ደግሞም አረመኔነት የሚያሳይ ነው፡፡ ቀጣዩን ትውልድ ብቻ ሳይሆን አዛውንቶችንም ለማጥፋት እንደቆመ፣ ጥላውንም ማመን እንዳቃተው የሚያመለክት የእውር ድንበር እርምጃ ነው፡፡ ፍትህ፣ ሞራል፣ ምክንያታዊነት፣ ህግ፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ሰብአዊነት ጨርሶ ከስርዓቱ ጋር እንደሌለ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
ትናንት ሴቶች፣ እናቶች፣ ወጣቶች፣ እንደ አቶ ቀኖ ያሉ አዛውንቶች ታፍነዋል፣ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ይህን የሚመስል፣ ለሰሚው ግራ የሚያጋባ፣ ደግሞም የሚያሳፍር፣ የሚያበግን ጭቆና ውስጥ ነች፡፡ እህቶቻችን፣ ወንድሞቻችን፣ እናቶቻችንና አባቶቻችን እያነቡ ነው፡፡ ይህን የህዝብ እንባ ልናብስ የምንችለው በቆራጥነት ደግሞም ተባብረን ስንታገል ነው፡፡
ያለ መስዋዕትነት ድል የለም!

No comments: