ግልጽ ደብዳቤ ለህወሃት!
“ጊዜ መልኩን ሳይቀይር አሁን ባላችሁ ዕድል ተጠቀሙ!
… ቀናነት ነጻ ያወጣችኋል!”
አባይ ወልዱ
የህወሃት ሊቀመንበር
መቀሌ፤ ትግራይ
አቶ አባይና መላው የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፤
ይህንን ደብዳቤ የምጽፍላችሁ ከተለያዩ ኢትዮጵያውያን በተውጣጣው የማኅበራዊ ፍትሕ እንቅስቃሴ ከሚመራው በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ስም ቢሆንም በተለይ ግን ሁላችንም የኢትዮጵያ ልጆች እንደመሆናችን እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ አባል የላኩላችሁ ደብዳቤ መሆኑን እንድታውቁልኝ እወዳለሁ። በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አለመግባባት ሲከሰት ሁኔታውን ማብረድና ወደ መልካም ማምጣት የቤተሰቡ አባላትና ስለቤተሰቡ በጥልቀት የሚያስቡ ሽማግሌዎች ዋንኛ ተግባር ነው። ታዲያ እኛም አንድ አገርና አንድ ተስፋ በፊታችን ያለ እንደመሆኑ በመካከላችን ያለውን ችግርና ግጭት በእውነትና በታማኝነት ልንነጋገር ይገባል ብዬ ከማመን ነው ይህንን የምጽፍላችሁ።
የዚህ ደብዳቤ ዋና ዓላማ የህወሃትን ሊቀመንበር፣ የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም የትግራይ ተወላጅ ወንድምና እህቶቻችንን በሙሉ፤ ስለ እያንዳንዳችን ጣት እንድንጠቋቆም ሳይሆን እርስበርሳችን መነጋገር እንችል ዘንድ ለመጋበዝ ነው። ይህም ንግግርና ውይይት ከፍ ብሎ ወደ ብሔራዊ ዕርቅ እንዲያመራ ለማድረግ ነው። ከዚህ አንጻር ይህንን ደብዳቤ በምጽፍበት ጊዜ ህወሃትን ከትግራይ ሕዝብ በመለየት ለማስቀመጥ ያደረኩትን ሙከራዎች በሙሉ ልብ እንድትሏቸው እሻለሁ። የዚህ ደብዳቤ አግባብ በሥልጣን ላይ ላሉቱና ላጋዦቻቸው ነው እንጂ ብዙውን ጊዜ አለአግባብ ከህወሃት ጋር አብረው የሚወቀጡት የትግራይ ወገኖችን ደርቤ እየተናገርኩ አለመሆኑን እንድታስተውሉልኝ ይሁን።
ይህንን ደብዳቤ የምጽፍላችሁ በጥላቻ በመነሳሳት ሳይሆን በፍቅርና መልካምን ሁሉ በማሰብ እንደሆነ እንድታውቁልኝ እፈልጋለሁ። ምክንያቱም የህወሃት ዘረኛ ፖሊሲ ከህዝቡ ጋር ተቆራኝቶ በአገራችን በቂ ምሬትና ጥላቻ በትግራይ ወንድሞችና እህቶቻችን ላይ እንዲኖር በማድረጉ እኔ በዚያ ላይ ሌላ ጥላቻ የመጨመር ምንም ፍላጎት የለኝም። እንዲያውም ከአምስት ዓመት በፊት የአደባባይ ምስጢር የሆነውን እውነታ በማፍረጥረጥ በህወሃት እየተገበረ ያለው የዘር መድሎና አፓርታይድ ሥርዓት እያደረሰ ያለውን በግልጽ አስረድቼ ነበር። የዚያን ጊዜ የጻፍኩት ደብዳቤ እዚህ ላይ ይገኛል። (
http://www.solidaritymovement.org/090611OpenLetterToMyFellowTigrayans.php)
ይህ የአሁኑ ደብዳቤ ከዚያ የቀጠለ ሲሆን የዚያን ጊዜ እንዳልኩት ጉዳዩን እያቀረብኩት ያለሁት እንደ አንድ ባለሙያ ሳይሆን እንደ አንድ ተራ ሰው ለማኅበረሰቤ መልካም በማሰብ ማበርከት የሚገባኝን ከመጠቆምና ለወደፊቱ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ለእናንተ ለራሳችሁ የሚጠቅም ነገር ከማሳየት አኳያ ነው። ስለሆነም በዚህ ደብዳቤ ውስጥ እናንተ ለመስማት የምትፈልጉትንና ለጆሯችሁ የሚጥም ነገር የምዳስስ ሳይሆን እውነትን ቁልጭ አድርጌ ነው የማቀርበው። “እውነትን ተናግሮ የመሸበት ማደር” እንደሚባለው ውሸትን ተናግሬ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነትን ከማግኘት ይልቅ እውነትን ተናግሬ ብጠላና ብገለል እመርጣለሁ። ምክንያቱም ያለንበት የአገራችን ሁኔታ በውሸት እንድንነጋገር አይፈቅድልንም። እኔ እዚህ ደብዳቤ ላይ እውነቱን አሰፍራለሁ ብልም በተጻፈው ነገር ሁሉ ከኔ ጋር ትስማማላችሁ ብዬ አልጠብቅም፤ ነገር ግን ሁለታችንንም የሚያስማማ አንዳንድ ነጥቦችን እናገኛለን ብዬ አምናለሁ።
እኛ ማነን?
ኢትዮጵያ በምትባለው አገር በመወለዳችን ወይም በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት ያለን በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ነን።በውጭ አገር ያሉትም ከዚህ የተለዩ አይደሉም፤ ምክንያቱም በውጭ አገር ቢኖሩም ወይም አስተዳደጋቸው በውጭ ቢሆንም የቤተሰባቸው የዘር ሃረግና ማንነት ከኢትዮጵያ ባሕል ጋር የተሳሰረ ነው። በመሆኑም ማንም ሰው ከዚህኛው አካባቢ ወይም ዘር ወይም ጎሣ ልወለድ ብሎ ሳይሆን በፈጣሪ ፈቃድ በዚህ አገር ላይ ተወልዷል፤ ዕድሉም ከኢትዮጵያ አገር ጋር ተሳስሯል። ከሚታወቀው ፍጥረተ-ዓለም ውስጥ የሰው ልጅ በሚኖርባት በዚህች ምድር፤ ሁላችንም በውቅያኖስ፣ በአህጉር፣ በተራራ፣ በአገራትና ሰው ሰራሽ በሆኑ ድንበሮች ተከልለን እንገኛለን። በዚህ ውስጥ ሁሉ በልዩነታችን የምንከፋፈል ሰዎችም ነን።
በኢትዮጵያ ውስጥ የራሳቸው ቋንቋ፣ ባሕልና ልዩ አኗኗር ያላቸው ከ80 በላይ የጎሣ ቡድኖች ይገኛሉ። በእርግጥ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት እነዚህን ቡድኖች “ብሔር ብሔረሰቦች” ተብለው ይጠራሉ። የዚህ ዓይነቱ የመንግሥት አስተዳደር በተለያዩ ቡድኖች መካከል እኩልነት እንዲኖር ማድረግ ሲገባው እውነታው ግን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የተገፋና የተተወ መሆኑን ነው የሚያሳየው። በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሊኖር የሚገባው ጤናማ መተሳሰብና መረዳዳት በኢትዮጵያችን ውስጥ በሚገኙ “የብሔር ቤተሰቦች” ሲከሰት አይታይም። ከዚህ ይልቅ ለሕዝብ የቆመ ሆኖ እንደተመሠረተ የሚናገረው የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ እንደ ብርቅያ ልጆች ለሚያያቸው ትግሬዎችና ህወሃት የቆመ መንግሥት መሆኑ በግልጽ የሚታይ ሐቅ ነው፤ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ ውጭ ተደርጓል።
በአሁኑ ጊዜ አንዳንዶች ከዚህ “የብርቅየ ልጅነት” ጎራ ለመመደብ በመፈለግ ደፋ ቀና ይላሉ፤ ሌሎች ደግሞ እንደ እውነተኛ ኢትዮጵያውያን ባለመቆጠራቸው ምክንያት አሁን አለ የሚባለውን ግንኙነት “መቁረጥ” ይፈልጋሉ። የእነዚህኛዎቹ አቋም ጠንከር ያለ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንዶቹ እናንተ ህወሃቶችን ሥልጣን እንድትለቁ የሚጠይቁ ሲሆኑ ከዚያ ጋር አብሮ ለራሳችሁ ያጋበሳችሁትን ልዩ መብትና ጥቅማጥቅም አብራችሁ እንድትሰጡ ይጠብቁባችኋል። ይህ አስቸጋሪ እንደሚሆን አጠያያቂ አይደለም፤ ሆኖም እናንት ህወሃቶች በማታለል፣ በሙስና እና በጠብመንጃ በማስገደድ የራሳችሁን ጥቅም ስታስከብሩ የቆያችሁ በመሆናችሁ የፈጸማችሁት ነገር ስህተት ብቻ ሳይሆን ህጋዊ፣ ማኅበራዊ እና ግብረገባዊ መብታቸውን በጣሳችሁት ወገኖች ዘንድ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንድትገቡ አድርጓችኋል።
እናንት ህወሃቶች የራሳችሁን ጥቅም ለማስከበር ስትሉ ፍትህን እንዴት እንዳጣመማችሁ፣ ፍርድ ቤቶችን የፖለቲካ መጠቀሚያ እንዳደረጋችሁ፣ መብቶችን እንዴት እንደረገጣችሁ፣ የኢኮኖሚና ንግድ ክፍሉን እንዴት እንደተቆጣጠራችሁ፣ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ እንዴት ስትነፉ እንደኖራችሁ፣ የማኅበረሰቡን ዘርፎች (የሃይማኖት ድርጅቶችን፣ ማኅበራዊ ስብስቦችን፣ ወዘተ) በሙሉ እንዴት እንደተቆጣጠራችሁ እና የራሳችሁን ሰዎች (ማለትም ትግሬዎችን) በወታደራዊ፣ በደኅንነትና በሌሎች ቁልፍ ቦታዎች እንዴት እንደሰገሰጋችሁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳያውቅ የቀረ እንዳይመስላችሁ!
እንደዚህ ወገናዊ እና ሁሉንም እኩል በማይመለከት ቤት ውስጥ እንዴት ነው ሌሎች ኢትዮጵያውያን መኖር የሚችሉት? እንዴትስ ነው በእንደዚህች ዓይነት ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር የሚመኙት? እስካሁን እየታየ ያለው ተቃውሞ እና ንቅናቄ እናንተ ህወሃቶች በአንድም ይሁን በሌላ ሁኔታ መላ እንድትፈልጉ እያስገደዳችሁ ያለ ሁኔታ ነው። ስለዚህ የወቅቱ ጥያቄ ጊዜው እስኪያልፍባችሁ ነው የምትጠብቁት ወይስ ከዚህ በላይ የሆነውንና የመንፈስ ልዕልና የሚጠይቀውን የዕርቅና የተግባራዊ ተሃድሶ መንገድን በመከተል ፍትህን እንደገና ታሰፍናላችሁ? ይህንን መንገድ የምትከተሉት ግን በዕርቅና ተሃድሶ ስም ከዚህ በፊት እንዳደረጋችሁት በሥልጣናችሁ ለመቆየት የምታደርጉት ብልጣብልጥ አካሄድ ሳይሆን መደረግ ያለበት አስፈላጊና እውነተኛ ነገር በመሆኑ ልትፈጽሙት የሚገባ ስለሆነ ነው።
ፈጣሪ የሰጠውን ዓለምአቀፋዊ ሕግ መከተል ሰላምን ያወርዳል!
ፈጣሪ ኃያሉ አምላክ ለማንም አያዳላም፤ እኛንም እንዲሁ እንድንሆን ይመክረናል። ፍትሕን ለታናናሾችም ሆነ ለታላላቆች እንዲሁም ከእኛ ጋር ላሉትም ሆነ ከእኛ ውጭ ለሆኑት እንድናሰፍን ይጠበቅብናል። ሌሎችን ስንንቅ፣ ከሰው በታች ስናደርግ፣ ስናገልል፣ ስናጣጥል፣ ስንበድል ወይም ስናጎሳቁል ይህንን ሁሉ ቆጥሮ በእኛ ላይ ተመልሶ መምጣቱ የማይቀር ሐቅ ነው። እኛ እንደ ኢትዮጵያዊ የሌሎችን መብት ስንጠብቅ፣ ማንነታቸውን ስናከብር ፈጣሪ የለገሳቸውን መብት ሁሉ በግልም ሆነ በጋራ ስናከብር የሥራችንን መልካም ውጤት እናገኛለን። ይህንን ሳንፈጽም ከቀረን ግን የዘራነውን ማጨዳችን የማይቀር ነው። ከዚህ አንጻር እናንት ህወሃቶች ባለፉት ሁለት ዓስርተ ዓመታት ስትዘሩ የኖራችሁትን የምታጭዱበት ቀን ሲመጣ እንዴት ልትሆኑ እንደምትችሉ አስባችሁበታል?
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ሁሉም በራሱ ንዑስ ማንነት ላይ በማተኮር በሌሎች ላይ የሚደረገውን ኢሰብዓዊ ድርጊት ትክክለኛነት ለማስረዳት ሲጠቀምበት ይስተዋላል። ይህም ኃያሉ ፈጣሪ በሌሎች ወንድሞችና እህቶቻችን (ሌሎች ብሔረሰቦች/ጎሣዎች) ላይ ያስቀመጠውን የራሱን ምስል ለማየት ካለመቻል የመነጨ ነው። አኢጋን የተቋቋመውም ይህንን የተሳሳተ አመለካከት ለመቀየርና “ሌሎች” እያልን የምንጠራቸውን የራሳችን አድርገን እንድንወስድና ከፈጣሪ ጋር ስምምነት እንዲኖር ለማድረግ ነው። እንደው እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ኃያሉ ፈጣሪ አንድ ሰው እንደ “እኛ ካልተናገረ” ወይም “እኛን ካልመሰለ” ወይም “የእኛን ዓይነት” ሃይማኖት ከሌለው ወይም “ከእኛ ጎሣ/ብሔር” ውጭ ከሆነ ወዘተ ለይቶ የሚያየው ይመስለናል? ወይም ይህ ሰው “የእኛን ዓይነት” የፖለቲካ አመለካከት ከሌለው ወይም በጣም ዝቅተኛና የተዋረዱ ከሚባሉ ጎሣዎች የመጣ በመሆኑ አምላክ ከእኛ አሳንሶ ይመለከተዋል ብለን እናስባለን እንዴ?
“ልዩነታችን ውበታችን” በማለት ትልልቅ ማስታወቂያ (ቢልቦርድ) መለጠፍ ብቻ አይደለም የሚያዋጣው። ከዚህ በማለፍ ፈጣሪ ለጎረቤታችን እንድንሰጥ የጠየቀንን ፍቅር፣ መልካምነትና ፍትሕ በተግባር ማስፈን ይገባናል። ልናስታውስ የሚገባን ነገር ቢኖር ከአካል ሰውነታችን አንዲቷም ክፍል ብትሆን ከታመመች ሌላው የአካል ክፍላችን በጠና ይታመማል፤ ሰላም አይኖረውም። ታዲያ ህወሃት በኢትዮጵያችን ውስጥ ያሰራጨው የዘርና የጎሣ ፖለቲካ ያመረቀዘው ቁስል ህመም እናንተንስ ተሰምቷችሁ ያውቅ ይሆን?
በዘር ላይ የተመሠረተ ፌዴራላዊ አወቃቀር የጎጠኝነት፣ የፊውዳላዊነትና የማርክሲስታዊነት ጣምራ ውጤት ነው።
ህወሃት/ኢህአዴግ የሚከተለው በዘር ላይ የተመሠረተው ፌዴራላዊ አወቃቀር በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ቡድኖች በሙሉ የሚያቅፍና የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት የሚያጎናጽፍ ነው እያለ ቢናገርም በተግባር ግን ይህ አዲስ ያልሆነና ከቁሻሻ ወጥቶ እንደገና በተግባር የዋለ የጎጠኝነት፣ የፊውዳላዊነትና የማርክሲስታዊነት የወረደ ጣምራ ውጤት ነው።
- ጎጠኝነት – አንድን ጎሣ ወይም ጎጥ (የትግሬን) ከፍ በማድረግ በአፓርታይዳዊ አሠራር “አንዱ ጎሣ/ጎጥ ሁሉንም ነገር ለራሱ ማድረግ አለበት” ወይም “የመብላት ተራው የእኛ ነው” በሚል ከፋፋይነት ላይ የተመሠረተ ነው።
- ፊውዳላዊነት – አንድን ቡድን ወይም ጎሣ ወይም ወገን ከሌላው የተለየ፣ የተሻለ፣ የተመረጠ፣ የበቃ፣ ስለሆነ የመግዛት/የመምራት መብት አለው፤ “ወርቃማ ዘር” ስለሆነ ትርፉንም ለራሱ የማድረግ ሥልጣን ተሰጥቶታል፤ ሌሎች ዕድለቢሶች በሥሩ የመሆን ግዴታ አለባቸው የሚል ነው።
- ማርክሲስታዊነት – የሚቃወሙትን ሁሉ – ትግሬዎችንም ጭምር – የመርገጥ ባህርይ ሲሆን ከፊውዳላዊነት በተለየ መልኩ ህወሃት በማርክሲስታዊ አስተሳሰብ “ሰፊውን ሕዝብ” እየጠቀምኩ ነው ቢልም በተግባር ግን “በጭቁኑ ሕዝብ” ስም የራሱን ሥልጣን ያመቻቸ ሆኗል። ይህ ዓይነቱ አታላይ ስልት ብዙሃኑን የአገራችንን ሕዝብ ከሌላው እንዲከፋፈል ያደረገ ብቻ ሳይሆን ብዙሃኑ ያልተማረ፣ በድህነት ላይ የሚገኝና ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና የሚለውን በልዩ ሁኔታ በቁጥጥር ሥር ለማዋል የተደረገ ነው።
ማርክሲስታዊነት በውስጡ ካሉት መርኾዎች አንዱ ሕዝብን መከፋፈል ነው። ይህ ዓይነቱ መርህ ተግባራዊ በመሆኑ ስንቱ የአገራችን ሕዝብ ተከፋፍሎ ቀረ? ስንቱስ “እርስ በርሱ በጠላትነት” እየተያየ ያለፈውንና አዲስ ግጭቶችን እያጎላ “ሰፊውን ሕዝብ” ለራሱ መጠቀሚያነት ያዋለው ስንቱ ነው? ህወሃት ይህንን መሠሪ ስልት በመጠቀም ተዋደውና ተከባብረው የኖሩትን፣ ለምሳሌ አማራና ኦሮሞዎችን፣ እርስበርስ በማጋጨት ክፉ ተግባር ላይ አውሎታል። በገሃድ ሲነገር ባንሰማውም፤ ዋንኛው ምክንያት የእነዚህ ሁለት ወገኖች መተባበርና መስማማት የሚያመጣው ታላቅ ለውጥ ምን ሊሆን ይችላል በሚል ፍርሃቻ እንደሆነ ብዙዎች ያውቁታል።
ይህ ከሆነ ዘንዳ ታዲያ በግማሽ ኦሮሞ እና በግማሽ አማራ የሆኑ ወይም ሌላ ተመሳሳይ ዓይነት ጥምረት ውልድ የሆኑ የት ይድረሱ? የእንደነዚህ ዓይነት ኢትዮጵያውያን እርስበርስ ግጭትና አለመግባባት በእናንተ ህወሃቶች እየዳበረና እየተደጎመ ቆይቶ እዚህ ደርሰናል። ለመሆኑ እናንተ ባመጣችሁት በዘር ላይ የተመሠረተ የጥላቻ ፖሊሲዎች ምክንያት ምን ያህል ግጭቶች እንደተከሰቱና ምን ያህል ሕዝብ እንዳለቀ ታውቁታላችሁ?በዋንኛነትና በዓላማ ስታራምዱት የቆያችሁበት ስለሆነ እያንዳንዷ መረጃ ከእናንተ የተሰወረች ልትሆን አትችልም።
ይህ ብቻ አይደለም፤ እናንተ ህወሃቶች ለአገሪቷ እጅግ የሚጠቅሙ የተማሩ ሰዎችን አሁን እናንተ ለምታራምዱት ፖሊሲ ተቃዋሚ በመሆናቸው ብቻ አስወግዳችኋል፤ እስካሁንም ጥቃት እያደረሳችሁባቸው ይገኛል። እነዚህ በምሁራን ብቻ የሚወሰኑ ሳይሆኑ የእናንተ ጥቃት የደረሰባቸው በኅብረተሰቡ ዘንድ በፖለቲካ፣ በሃይማኖት፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ጉዳይ፣ ተቀባይነት ያላቸውን ግለሰቦች፤ እንዲሁም ከእናንተ ውሸትና በሃሰት ለፈጠራችኋትና የጥቂቶች ብቻ ላደረጋችኋት ኢትዮጵያ አልገዛም የሚል ሁሉ በሁሉም ብሔር የሚገኝ የእናንተ የጥቃት ሰላባ ሆኗል። እናንተ ብትክዱትም ግፉን የተቀበሉትና ታሪክ ግን ፈጽሞ ሊረሳቸው አይችልም።
ሌላው በእኩል ደረጃ ሊጠቀስ የሚገባው ነገር ቢኖር ያለማቋረጥ የሚለፈፈው ውሸት ነው። ዓይን ያወጣው ውሸት እንዳለ ሆኖ በማርክሲስታዊ ርዕዮት መልክ የሚቀርበው “የአገም ጠቀም” እና መልካም የሚመስለውን ብቻ ለይቶ በማቅረብ ሕዝቡ እንዲወናበድ የሚደረገው አካሄድ በአጸያፊነቱና በአሳፋሪነቱ የሚጠቀስ ነው። ይህንን በማድረጋችሁ ሕዝብን ሳያውቅ በጭፍን ለመምራት ያስቻላችሁ ቢመስላችሁም በምላሹ ግን በሕዝቡ ዘንድ ውሸት፣ አለመተማመን እንዲሁም እናንተኑ መልሶ የሚያወድም ስትራቴጂ መሆኑን የተረዳችሁት አይመስልም። እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው ከትግሬ ሌላ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን በሥልጣን እርከን ላይ በማስቀመጥ ሕዝቡ ሁሉም ተወክሏል ብሎ እንዲያምን የምትጠቀሙበት ወራዳ አካሄድ ነው። የዚህ ማታለያ ሰለባ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተቀመጡት ኃይለማርያም ደሳለኝና ሌሎች እንደ እርሳቸው የተመደቡ ተጠቃሾች ናቸው። በኢትዮጵያ ሰላም እንዲኖር ካስፈለገ ይህ ዓይነቱ አጸያፊና እጅግ ነውረኛ አካሄድ መቆም አለበት።
ህወሃት የተለየ ሊሆን ይችል ነበር! ዕድሎች ነበሯችሁ ግን አልተጠቀማችሁበትም!
ህወሃት በተመሠረተበት ወቅት እንደ ምክንያት አድርጎ ያቀረበው ትግሬዎች በደርግ አገዛዝ በደል ደርሶባቸዋል፣ ተገልለዋል፣ … የሚል እንደነበረና ይህም በረሃ እንዳስገባችሁ ራሳችሁ የምትመሰክሩት ነው። ሆኖም የሥልጣን መንበሩን በተቆጣጠራችሁበት ጊዜ ለውጥ የማምጣት ምርጫ ነበራችሁ። ከፊውዳላዊውም ሆነ ከደርግ አገዛዝ የተለያችሁ መሆን ትችሉ ነበር። በርግጥ የተለያችሁ ሆናችኋል፤ የሚያሳዝነው የተለያችሁት በመልካም ሳይሆን በክፉ፣ በዘረኝነት፣ በስግብግብነት፣ በወገናዊነት፣ በሙስና፣ በራስ ወዳድነት፣ ብዙሃኑን በመበደል፣ ለራሳችሁ ሃብትና ንብረት በማከማቸት፣ በጭቆና፣ በግፍ፣ … ከበፊቶቹ እጅግ በከፋና አጸያፊ በሆነ መንገድ የተለያችሁ ሆናችኋል።
ህወሃት እንደ ማርክሲስታዊው ደርግ የተቃወሙትን ሁሉ በማፈን እና ጦርነት በማወጅ “ገርስሼዋለሁ” የሚለው የደርግ ውላጅ ሆኗል።በሥልጣን በቆየ መጠንም ከደርግ እጅግ እያስከፋና እያስመረረ መጥቷል። ነጻ አውጪ ግምባራችሁ “ለውጥ አመጣለሁ” በማለት ሥልጣን የተረከበ ቢሆንም በጨበጠውን ሥልጣን በመጠቀም የራሱን ጦር ሠራዊት መሥርቷል፤ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሃብት ንብረት በራሳችሁ ስምና በህወሃት ቁጥጥር ሥር አደረጋችሁ፤ የቀረውንም የአገራችን ሃብት ለቤተሰቦቻችሁና ለዋና የጥቅም ተካፋዮቻችሁ አከፋፍላችኋል፤ ዋንኞቹ የጥቅም ተካፋዮችም ትግሬዎች ናቸው!!
በአገራችን የተለያዩ ክፍሎች በጋምቤላ፣ በኦጋዴን፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል፣ በአማራ እና በአዲስ አበባ ሕዝቡ ተቃውሞውን ሲያሰማ በእናንተ ቁጥጥር ሥር ያለው የጦር ሠራዊትና ፖሊስ ተቃውሞ የሚያሰሙትን ወይ ያስወግዳቸዋል ወይም በግድ ዝም እንዲሉ ያደርጋል። ይህ የሚፈጸመው ደግሞ በመግደል፣ በማሰር፣ የሰብዓዊ መብት በመርገጥ፣ ሕዝብን በማሸበር፣ ወደ ሌላ አገር እንዲሰደድ በማድረግ፣ ወዘተ ሲሆን አገር ቤት የሚቀረው ደግሞ በግድ ጸጥ ይደረጋል፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን እናንተም ሆነ ህወሃት ምንም ነገር እንዳልተከሰተ ነው የምታስመስሉት።ወጥታችሁ መግለጫ ስትሰጡም ሆነ ስለ ልማት ስታወሩ ይህ ሁሉ ግፍ በአገራችን ላይ እንዳልተፈጸመ ስታስመስሉ ሁለት ዓስርተ ዓመታትን አሳልፋችኋል። “ለብሔር ብሔረሰቦች” መብት መከበር በሚል ራሳችሁ ያቋቋማችሁት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል የሚል ቢሆንም በተቃራኒው የኢትዮጵያን ሕዝብ እስከ ቀበሌና ቤተሰብ ድረስ በራሳችሁ ቁጥጥር (ጥርነፋ) ሥር በማዋል እኩይም ቢሆን ራሳችሁ ላወጣችሁት መመሪያ እንኳን የማትገዙ መሆናችሁን በተደጋጋሚ አስመስክራችኋል።
አገራችንን ላለፉት 23ዓመታት ስታልቧት ከቆያችሁ በኋላ በረሃ በነበራችሁበት ወቅት እና እስካሁን ድረስ “ነፍጠኛ አማራ” እያላችሁ ስታማርሩት የነበረው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እናንተ በደርግ ላይ ከነበራችሁ መራርነት ባለፈ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል። ይህ ሁኔታ ነው ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መመሥረት አንዱ ምክንያት። እናንተ እስካሁን ስታደርጉት የቆያችሁት ፍጹም የተሳሳተና መሰሪ ነው። በዚህ ምክንያት ሕዝብ ቢማረርባችሁና ግፉ አንገቱ ቢደርስ ልትደነቁ አይገባችሁም፤ ምክንያቱም ሕዝቡ በቅቶታል፤ አንገፍግፎታል። ላለፉት ዓመታት ሕዝቡን አንድ የማድረግና ለውጥ የማምጣት ዕድል ነበራችሁ። ከዚህ ይልቅ ግን በአገሪቷና በሕዝቡ ላይ መከፋፈልን እንዲሁም መተላለቅን የሚፈቅድ ወራዳ ሥርዓት ነው የፈጠራችሁት። ታዲያ በራሳችሁ ያመጣችሁትን ይህንን ሁሉ ችግር እንዴት ነው ልትጋፈጡት የምትችሉት?
ይህ ብቻ አይደለም እውነትን እጅግ በጣም የምትፈሩት ነገር ነው። “ብሔር ብሔረሰቦች” በሚል ቅዠት ኢትዮጵያን መሠረትን አላችሁ። ይህ ትክክል እንዳልሆነ በማስረዳት እውነቱን የተናገሩትን ሁሉ በመግደል፣ በማሰር፣ በማስወገድ፣ ደብዛቸውን በማጥፋት፣ ወዘተ ህወሃት ከእውነት ጋር በሚጋፈጥበት ጊዜ የሚያሳየውን አሳፋሪ ገጽታ ቁልጭ አድጋችሁ በገሃድ አሳያችሁ። ይህ ድርጊት እናንተን ለኅሊና ወቀሳና ውርደት የሚያጋልጣችሁ ብቻ ሳይሆን መቅኒያችሁን የሚመጥ፤ ነፍሳችሁን ቅርጥፍ አድርጎ የሚበላ ቅንቅን ነው። ከእናንተ መካከል አንዳንዶች አሁንም እልኸኛና እብሪተኛ በመሆን ልባቸውን አደንድነው ሊሆን ይችላል፤ ለብዙዎች ግን ሐቅን መካድ ለእብደትና ለሞት የሚያደርስ እንደሆነ እሙን ነው።
ህወሃት የሚዲያውን መስክ ለራሱ ጥቅም እንደተቆጣጠረው የተመሰከረ ቢሆንም በተለይ ሰሞኑን የወጣ መረጃ እንዳመለከተው በየድረገጹ ለሚወጡ ጦማሮች እና አስተያየቶች እናንተ በገንዘብ የገዛችኋቸው ቅጥረኞች ማንነታቸውን በመደበቅ ምላሽ እየሰጡ የህወሃትን መልካምነት እንደሚሰብኩና የአጸፋ ፕሮፓጋንዳ እንደሚነዙ የተደረሰባቸው መሆኑ ታውቋል። አገር እንመራለን ብላችሁ ተቀምጣችሁ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ስታስደርጉ ኅሊናችን ነጻ ነው ብትሉ ማን ሊያምናችሁ ይችላል? በአገራችን “መከበር በከንፈር” እንደሚባል ይህንን ሁሉ ግፍ ስትፈጽሙ ቆይታችሁ በሕዝቡ ለመከበር መፈለጋችሁ ለራሳችሁ ሊገርማችሁ ይገባ ነበር። የፈለጋችሁትን ዓይነት መሸፋፈን ብታደርጉ፤ አሳምራችሁ ብታቀርቡት፣ የሕዝቡን ምሬት ግን በምንም ልታፍኑት አትችሉም!
ለተሻለ ወደፊት አማራጩ እውነተኛ ለውጥ ብቻ ነው! የይስሙላ ተሃድሶ ተቀባይነት የለውም!
ሁኔታዎች አሁን ባሉበት ዓይነት እንደማይቀጥሉ እሙን ነው፤ መጨረሻው ይመጣል። አገሪቷ ወደ ሁከትና ቀውስ ውስጥ ከገባች እጅግ ከፍ ያለውን ክፍያ የምትከፍሉት እናንተና ልጆቻችሁ እንዲሁም ዝርያችሁ ነው። ሆኖም ማናችንም ብንሆን ይህ ሲከሰት ማየት አንፈልግም። ስለዚህ የዚህ ደብዳቤ ዋንኛ ዓላማም እናንተ ይህንን እንድትረዱ ለማድረግና ሁኔታው እንዳይከሰት ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ለማሳወቅ ነው።
እናንተ አሁን ድረስ የምትከተሉት ፖሊሲዎች ሁሉ ሲወጡና ሲቀምሙ የኖሩት በቀድሞው ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ነበር። ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳውን ፈንጂ ለእናንተ አውርሰው እርሳቸው አልፈዋል። እናንተስ ምንድነው የምታደርጉት? ከአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግሬዎች 6በመቶ ናችሁ። ይህ ሲነገራችሁ ምንም እንዳልሆነ እና እንደማይሆን ለማስመሰል አትሞክሩ። ቁጥራችሁ ትንሽ ሆኖ ያደረሳችሁት በደል እጅግ ግዙፍና ፈጽሞ የማይረሳ ነው። በአንድ አገር ላይ አንድ ቡድን ለብቻው ሁሉንም ነገር ሲቆጣጠር የሚከሰተውን ለማወቅ ሩቅ መሄድ አያስፈልግም – ሩዋንዳ ቅርባችን ናት። መለስ ሲቀምሙት ከቆዩት የማታለያና ብልጣብልጥ ታክቲክ ጋር ተደምሮ የኢትዮጵያ ሁኔታ ከሩዋንዳም የባሰ ይሆናል ብሎ መናገር ይቻላል። መለስ ጥሎት የሄደውን እሣት በጉያችሁ አቅፋችሁ ነው ያላችሁት።
በመጋቢት ወር 1988ዓም በሩዋንዳ የሆነው አሳዛኝና ሰቅጣጭ ድርጊት የተጀመረው በዚያው በመጋቢት ወር አይደለም። ይልቁንም ለዓመታት የወሰደ አፓርታይዳዊ የዘር ፖሊሲ አንዱን ዘር የበላይ በማድረግ፣ ሥልጣን ለራስ ወገን ብቻ በማድረግ፣ ኃብትን ለራስ ወገን በማግበስበስ፣ ሌሎችን በማሰር፣ በመግደል፣ በማሰቃየት፣ … ዓመታት ካለፉ በኋላ ነበር። በወቅቱ የተጮኹ የማስጠንቀቂያ ደወሎች ነበሩ፤ የሰማቸው ግን አልነበረም።አሁን ግን ከ20 ዓመታት በኋላ ሩዋንዳውያን እስካሁን ቁስላቸውን ለማሻር አልቻሉም፤ ለውጦች ቢኖሩም የቁስሉ ጥልቀት እና የፈሰሰው ደም ያረጠበው መሬትና የሞላው ወንዝ አለመተማመንን ቢያሰፍንም ዕርቅን ብቸኛ አማራጭ በማድረግ በፈውስ ሂደት ውስጥ ይገኛሉ። ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ግን የተሰጡት ማስጠንቀቂያዎች አድማጭ ሊኖራቸው ይገባ ነበር።
ብዙዎች በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ቀጣይ ሩዋንዳ ልትሆን ትችላለች እያሉ ነው። በ1997 ምርጫ መለስና የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ የቅንጅት አመራሮችን በትግሬዎች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል ብላችሁ የፈጠራ ክስ መስርታችሁ ነበር። የቅንጅት አመራሮች ይህንን በጭራሽ ያደረጉት ባይሆንም እናንተ ግን በአገሪቷ ላይ ያለውን አደጋ ለራሳችሁ የፖለቲካ መጠቀሚያ በማድረግ በራሳችሁ ሕዝብ ላይ ፈርዳችሁበታል፤ ሁኔታው ባይከሰተም በሰው አእምሮ ውስጥ ይህ ክፉ አሳብ እንዲገባ በማድረግ እንወክለዋለን የምትሉትን የትግራይ ሕዝብ ለዕልቂት ዳረጋችሁታል። በወቅቱ በሥልጣን ለመቆየት ስትሉ እና ተቃዋሚዎቻችሁን ለማክሸፍ ብትጠቀሙበትም ተክላችሁ የሄዳችሁት ግን በአገራችን የዘር እልቂት እንዲነሳ የሚያደርግ ፈንጂ እንደሆነ ራሳችሁ ምስክርና ተጠያቂ ናችሁ።
እኔ በግሌም ሆነ የጋራ ንቅናቄያችን በድርጅት ደረጃ ይህ በጭራሽ እንዲከሰት የማንፈልገው ቢሆንም ፍርሃቻው ግን አለ። ባልነደደበት እንደማይጨስ ሁሉ ፍርሃትና ስጋት ደግሞ እንዲሁ ያለምክንያት አይከሰትም። ሕዝቡ ያለውን ፍርሃቻ እኔ በግሌም ሆነ የጋራ ንቅናቄያችን ባለው የመገናኛ መስመር አገር ቤት ጎብኝተው ከሚመጡም ሆነ እዚያው ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉትና ሌሎች ሰፋ ያለ ጥናት ከሚያካሂዱ በየጊዜው የምንሰማው ነው። ከእነዚህ ሁሉ የምናገኘው መረጃ የሚያመለክተው ሕዝቡ ምን ያህል በህወሃትና በትግሬዎች ላይ እያመረረ መምጣቱን ነው።ሁኔታው ያሳሰባቸው ኢትዮጵያውያን ለአገሪቷም ሆነ ለቤተሰቦቻቸው በማሰብ አንድ መላ መፈለግ እንዳለበት ይወተውታሉ።
“ልማት፣ ህዳሴ፣ …” እያላችሁ እውነታውን ለመደበቅ ብትሞክሩም ውጥረት ከነገሠ ግን ቆይቷል። በትግሬዎችና በሌሎች ኢትዮጵያውያን መካከል ያለው ልዩነት በተለይ ከውጭ ለሚመጡ ኢትዮጵያውያንም ሆነ ሌሎች በግልጽ የሚታይ ነው፤ ልዩነቱ የሚታየውም ከቦሌ ኤርፖርት ጀምሮ ነው። ወደ አገር ሲገቡ ትግሬ በመሆናቸው ብቻ የተለየ መስተንግዶና አገልግሎት ሲሰጣቸው ማየት ለብዙዎች አዲስ አይደለም። በኤርፖርቱ ውስጥ ያሉት የጉምሩክ ሠራተኞች ትግሬዎች መሆናቸው አንዱ ማረጋገጫ ነው። (በነገራችን ላይ ይህ በራሱ ወደ አገር ውስጥ ማን እንደሚገባ ማን ከአገር እንደሚወጣ በታማኞች ለመቆጣጠር ሆን ተብሎ የተደረገ ነው።)
ከበርካታ ክስተቶች መካከል አንድ የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ልጥቀስ፤ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች የያዘ አንድ ኢትዮጵያዊ ወደ አገሩ በቦሌ በሚገባበት ወቅት የጉምሩክ ሠራተኛው እጅግ ከፍተኛ የሆነ ቀረጥ ይጭንበታል (በብዙ ሺዎች የሚቆጠር)። ግለሰቡም ይህንን ያህል ለመክፈል እንደማይችል ይናገራል። ይህን ጊዜ የጉምሩክ ሠራተኛው ዕቃው እንደሚወረስ (ወደ ጉምሩክ እንደሚገባ) ይነግረዋል። በመጨረሻ ላይ በአማርኛ ይናገር የነበረው የዕቃዎቹ ባለቤት የቋንቋ ማርሹን በመቀየር በትግሪኛ መናገር ይጀምራል። የጉምሩክ ሠራተኛውም በመደነቅ ለግለሰቡ በሰጠው ምላሽ አስቀድሞ ለምን ትግሬ መሆኑን እንዳልተናገረ የሚጠይቅ ነበር። በጉዳዩ ላይ ገብቶበት የነበረው ሱፐርቫይዘርም ዕቃዎቹን ወደ ሻንጣው መልሶ ያለ አንዳች ክፍያ እንዲሰናበት አድርጎታል። ሲሰናበትም ሱፐርቫይዘሩ ግለሰቡን እንዲህ ይለዋል፤ “አንተ የኛ ነህ እንዴ!? – እኛ እኮ የታገልነው፤ ወደ በረሃ የሄድነው ላንተ ነው – በል እቃህን ያዝና ወደ ቤትህ ሂድ” በማለት አሰናብቶታል። እውነቱ ግን ግለሰቡ ትግሬ ሳይሆን አብሮ በማደጉ ቋንቋውን አቀላጥፎ የሚናገር ነበር። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱና ከዚህም ያለፈ የረቀቀ ስንት ኢፍትሃዊነት ይፈጸም ይሆን? ለዚህም ነው በአሁኑ ጊዜ ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ዓይነት ሕግጋት ናቸው ያሉት የሚሉት፤ አንዱ ለትግሬዎች የሚሠራ ሌላው ደግሞ ለተቀረው ኢትዮጵያዊ!
በርካታ ኢትዮጵያውያን እኔንም ጨምሮ ለአገራችን ሰላማዊና ዘላቂ ፍትህ እንዲሁም ሕጋዊ መንገድ የሚከናወን ዕርቅ እንጂ የሩዋንዳ ዓይነት ወይም በጎረቤት ደቡብ ሱዳን የሆነውን ዓይነት መተላለቅና ውድመት በጭራሽ አንመኝም። በአሁኑ ወቅት ባለው ሁኔታ ለበርካታ መቶሺዎች ለሚሆኑት ደቡብ ሱዳናውያን ስደተኞች ዕርዳታ ለማደረግ የማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል። አስቀድሞ መፍትሔ ካልተፈለገ በኢትዮጵያስ ይህ ከመሆን የሚከለክለው ምን አለ? ጥፋቱ ሲመጣስ እናንተን የሚታደግ ማን ይሆን? ከዚህስ የምታመልጡ ይመስላችኋል?
ባለፉት ቅርብ ዘመናት በአገራችን ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ሳንችል ቀርተናል – መንግሥቱ አልሆነለትም፣ መለስ አላደረገውም፣ አሁን ደግሞ የተተካችሁት እናንተ ህወሃት/ኢህአዴጎች እየከሰራችሁ ነው። ከደገማችሁት ሁላችንም እንደገና አብረን እንወድቃለን። አወዳደቁ የሚከፋው ግን ለእናንተ ነው፤ እጅግ ብዙ የምታጡት አላችሁና፤ ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ 23ዓመታት ሲያጣ ስለኖረ የቀረው ነገር ስለሌለ የሚያጣው እንደ እናንተ አይከፋም። ስለዚህ ዕርቅ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው፤ ይህ ግን ጭፍን “አንተም ተው፤ አንቺም ተው” ዓይነት ጭፍን ዕርቅ ሳይሆን ጥፋትን ማመን፣ እውነትን መቀበል፣ በደልን ማመን፣ እውነተኛ ተሃድሶ ማምጣትና ፍትሕን ማስፈን የሚጠይቅ ነው። እንዲህ ዓይነት እውነተኛ ለውጥ ካልመጣ ህወሃት ለቀጣዩ ትውልድ ጥላቻና ቂም በቀል ነው የሚያስተላልፈው። ይህ ደግሞ በህወሃትና በአመራር ላይ ባላችሁት ብቻ የሚያነጣጥር ሳይሆን በትግሬዎች ስም አገር ስትገዙ እንደመኖራችሁ አደጋው የትግሬዎች በሙሉ ይሆናል። ከመለስ ጋር ተደምሮ የእናንተም እውነተኛ ውርስ/ሌጋሲ ይህ ይሆናል።
ስለዚህ ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ ያላችሁን ፈቃደኛነት በግልጽ አሳዩ። ወደ ድርድሩ ጠረጴዛ ኑ! የፖለቲካ እስረኞችን፣ ጋዜጠኞችን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን፣ የሃይማኖት መሪዎችን እና የተቀናቃኝ ፓርቲ መሪዎችን ከእስር በመፍታት ፈቃደኛነታችሁን አሳዩ። ከእናንተ ጋር ሚቃወመውን ሁሉ “አሸባሪ” በማለት ማሰራችሁን አቁሙ! ኃይልን ወይም ጉልበትን በመጠቀም እስከመጨረሻው በሥልጣን አትቆዩም! በዓለም ታሪክ ያልተከሰ ስለሆነ እናንተ ልትከውኑት አትችሉም። እናንተ አለን ከምትሉት ጉልበት በብዙ እጥፍ የሚበልጥ የነበራቸውም ተንኮታኩተዋል። ስለዚህ ከትዕቢታችሁ ተንፍሱ፤ ትህትና አሳዩ፤ ከፍ ብላችሁ የተሰቀላችሁበት ከመሰላችሁ “ፎቅ” ውረዱ! ለለውጥ ያላችሁን ግልጽነት አሳዩ! ለዓመታት ሳታቋርጡ ስታወሩ የነበራችሁትን ውሸት አቁሙ፤ እውነትን መናገር ተለማመዱ። የሃሰትን መንገድ ሳይሆን ትክክለኛውን በመከተል በዜጎች መካከል መተማመን እንዲፈጠር የሚያስችል ሥራ ማከናወን ጀምሩ!
ይህንን ወርቃማ ዕድል አታባክኑት!
ባለፉት 60ዓመታት በላይ ኢትዮጵያ በአምባገነናዊ ሥርዓት ሥር ስትገዛ ኖራለች። ከዚህ አንጻር ሕዝባችን በቂ ግፍ፣ መከራ፣ ስቃይ፣ ደም መፍሰስ፣ ሰቆቃ፣ … አልተቀበለም ትላላችሁ? የብዙዎች ቤት ፈርሷል፣ የበርካታዎች ንጹህ ደም ፈሷል፣ የብዙዎች ልብ ደግሞ በቂም፣ በበቀል፣ በጥላቻ፣ በምሬት ተወጥሯል። ተራው ደርሶ እነርሱም ደም እስኪያፈሱና የተቀማባቸውን መልሰው እስኪዘርፉ ቀናቸውን የሚጠብቁ ጥቂቶች አይደሉም።
እስቲ ለጥቂት ጊዜ ቆም ብለን እናስብ፤ እናንተም ለበርካታ ዓመታት ከተጠመቃችሁበትና ከተዘፈቃችሁበት የማርክሳዊና ሌኒናዊ አመለካከት ትንሽ ቆም ብላችሁ ሁላችንም ወደ ፈጣሪ አምላክ እንመልከት። ማን እንደነበርን እና አምላክ የሰጠንን ሰብዓዊነት ለጥቂት ጊዜ እናጢን። እጅግ በጣም ወድቀናል፤ ከመስመሩ ርቀን ሄደናል፤ ስህተታችንን እንቀበል። ነገር ግን በፈጣሪ ኃይል ከወደቅንበት እንነሳለን፤ እንደገናም እንደ አንድ ሕዝብ እርስበርስ መዋደድም እንችላለን።
የሰዎች ስግብግብነት በመንግሥታት ሕግ ውስጥ እየተሰነቀረ ለሕዝባችንና ለመጪው ትውልድ እርግማን አትርፈናል። ከራስ ወዳድነት እና ለራስ ወገን ወይም ዘር ብቻ ከማሰብና ከመሥራት ይልቅ በአገራችን በበርካታ ወገኖች ዘንድ እንደሚታወቀው ያለውን ማካፈል የተለመደና የተቀደሰ ተግባር እንደገና የምንፈጽምበት ጊዜ አሁን ነው። ይህንን አምላካዊ የሆነ ነገር ትተን ከወዴት ይሆን ለራሴ ወገን፣ ለራሴ ሕዝብ፣ ለራሴ ዘር፣ … የሚል አጥፊ ነቀርሳ ውስጥ የገባነው? በተለይ እናንተ በህወሃት/ኢህአዴግ አማካኝነት ሥልጣን ከጨበጣችሁ በኋላ የራስ ወዳድነቱና ወገናዊነቱ መጠን እየከፋ ከመሄዱ የተነሳ ባሁኑ ወቅት ሲከሰት ማየት ምንም የማይገርም ነገር ሆኗል።
በአገራችን የተለመደው አብሮ የመካፈል ባህል የግራው አስተሳሰብ አቀንቃኞች እንደሚሉት ሃብትን ማሰራጨት አይደለም። የአንዱን ሃብት ወስዶ ለሌላው መስጠት በፍጹም ትክክለኛ ተግባር አይደለም፤ ሌላው ዓይነት ሌብነት ነው። የአገራችን ባህል ግን አብሮ መካፈልን ከፍቅር፣ ከለጋስነት፣ ከመተሳሰብ የመነጨና ወገናዊነትን የሚጻረር ነው። ኢትዮጵያችን አንዲህ ዓይነት ነበረች፤ አሁንም ተመልሳ እንዲህ መሆን ትችላለች። እንዲህ ዓይነቷን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር እኔም ሆንኩ ሌሎች የማይፈልጉበት ምንም ምክንያት የለም። ለመጪው ትውልድም ማውረስ የምፈልገው ይህንኑ ነው። እናንተስ? እውነትን መካድ ማንም አይችልም! ሥልጣን በወሰዳችሁበት ጊዜ አንድ ወርቃማ ዕድል አመለጣችሁ። ሌሎችን ሁሉ ማስተባበር ስትችሉ አሻፈረኝ አላችሁ። ደርግንም እንኳን ቢሆን ጨምሮ ለሁሉም መንገዱን መክፈት ስትችሉ የራሳችሁን ነጻ አውጪ ድርጅትና ዘር ብቻ ይዛችሁ ሁሉንም ከህወሃት እና ከትግሬ በታች ማድረጉን ተያያዛችሁበት። ብዙዎችን አስመረራችሁ፤ አስከፋችሁ። እናንተ በበረሃ ተሰማን ያላችሁትን ስሜት ባሁኑ ጊዜ በሚሊዮኖች በናንተ ላይ እየተሰማቸው ነው። “ብሶት የሚወልደው” እናንተን ብቻ እንዳልሆነ ታውቁታላችሁ፤ አገሪቷን ከሰሜንና ደቡብ እንዲሁም ከምስራቅና ምዕራብ በማጠርና በመድፈን “የማንበገር ሆነናል” ብትሉም “ብሶት የሚወልደው” እዚያው አራት ኪሎ አፍንጫችሁ ሥር ስላለመኖሩ አንዳች ማረጋገጫ ሊኖራችሁ አይችልም። ስለዚህ ቀን ሳለ፤ ጊዜ መልኩን ሳይቀይር አሁን ባላችሁ ዕድል ተጠቀሙ! ይህ ሳይሆን ቀርቶ እናንተ በሥልጣን ላይ ባላችሁበት ባሁኑ ወቅት ያልዘረጋችሁት ዕድል ዘመን ፊቱን ሲቀይር ለእናንተ የሚዘረጋላችሁ ይመሰልላችኋል?
እናንተ ለበቀል የነበራችሁ ዓይነት ምርጫ እኔ ሳይኖረኝ የቀረ አይምሰላችሁ! በእናንተ በህወሃት ታጣቂዎች የቅርብ ወገኖቼና ዘመዶቼ በጋምቤላ ተጨፍጭፈዋል፤ ደማቸው ፈሷል፤ ካገር ተሰድደዋል። ነገር ግን ከእኔ ብቀላና ጥላቻ በላይ የሆነችና የወደፊቱ ትውልድ በኔ የደረሰው ዓይነት እንዳይደርስባት የምመኛት ኢትዮጵያ በውስጤ ስላለችና ያችንም ኢትዮጵያ ለማየት ስለምመኝ የይቅርታ እና የዕርቅን አማራጭ መንገድ ተከትያለሁ። ለዚህም ነበር ለቀድሞው መሪያችሁ መለስ፣ ለትግሬዎችና ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ከዚህ በፊት በላኩት ደብዳቤ ሁኔታዎችን ሁሉ ዘርዝሬ ለማስረዳት የሞከርኩት። ያንን በጻፍኩበት ወቅት በአገሪቷ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የተዛባ የሃብት ስርጭት መኖሩንና በተለይ የዚህ ዋንኛ ተጠቃሚ ትግሬዎች መሆናቸውን ጠቅሼ ነበር። ይህንን ከጻፍኩ በኋላ በርካታ የተለያዩ ምላሾችን ከትግሬዎች ያገኘሁ ሲሆን በዚህ አግባብነት በሌለው የሃብት ስርጭት ዙሪያ ትግሬዎች ስለመጠቀማቸው የሰበሰብኩትን ምላሽ በዚህ መልኩ ጠቅለል አድርጌ አቅርቤዋለሁ።
1. ሁሉም ትግሬ እኩል አልተጠቀመም፤ ብዙዎች ድሆች ናቸው እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ዕርዳታ ይሻሉ፤
ይህ አስተሳሰብ እውነተኛ ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። ብዙዎቻችን ስለ ትግራይ ስናስብ ትግሬ የሆነ ሁሉ ደልቶታል፣ ተጠቀሟል በሚል ማጠቃለያ ሁሉንም በአንድ በመፈረጅ ስህተት እንፈጽማለን። በትግራይ የሚገኙትን ድሆች ለመርዳት ትልልቅ ፕሮጀክቶች ይካሄዳሉ፤ ይህ በመሠረቱ መልካም ነገር ነው፤ እንደ ዜጋ ቢረዱ ልንደሰት ይገባናል። ችግር የሚሆነው ግን “ትግራይ በጦርነት ተጎድቷል” እየተባለ ከሌሎች ክልሎች በተለየመልኩ ትግራይን ብቻ ለማልማት የሚደረገው አሰራር ፍጹም ኢፍትሃዊና ዘረኛ ነው። ለምሳሌ እኔ ራሴ በ1993ዓም በጋምቤላ የልማት ፕሮጀክት ለማቋቋም በምንቀሳቀስበት ጊዜ ወደ ትግራይ እንድሄድና እዚያ ኢንቨስት እንዳደርግ ግፊት ተደርጎብኝ ነበር። የተሰጠኝም ምክንያት “እዚያ በርካታ መረዳት ያለባቸው አሉ” የሚል ነበር። ባላውቅ ኖሮ እታለል ነበር፤ ነገር ግን ጥያቄውን ውድቅ አደረኩት።
ህወሃት ሥልጣን በመቆጣጠሩ ሁሉም ትግሬ ደልቶታል ማለት አይቻልም። ፕ/ር መስፍን ወልደ-ማርያም “የወያኔ ጥላቻ ፍሬ” በሚል ርዕስ በቅርቡ በጻፉት ጦማር እንዲህ ይላሉ፡- “የትግራይ ሕዝብ መደህየቱ አልበቃ ብሎት ሲለምንም እየተሳቀቀ ነው፤ የሚለምነው ትግሬ ለብዙ ሰዎች ትግሬና ወያኔ አንድ መስሎ እንደሚታየው ያውቃል፤ አብዛኛው ሰው በወያኔ ላይ ያለውን ስሜት ያውቃል፤ ስለዚህም ሲለምን ሰዎች በወያኔ ላይ ያላቸውን ስሜት ስለሚያራግፉበት እየተሸማቀቀ ነው፤ አንድ የትግራይ ቄስ ከአርሲ ነኝ አሉኝና ለምን እውነቱን አይናገሩም ስላቸው እውነቱን ስናገር የማገኘው ስድብ ብቻ ነው አሉኝ፤ እኒህ ሰው ምን በወጣቸው የወያኔን ኃጢአት ተሸካሚ ይሆናሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በትግሬነቱ የተጠቀመ አለ፤ እኔ የማውቀው የደርግ ወታደር የነበረ ትግሬ ቆስሎ ከውትድርና ወጣና በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የጥበቃ ሥራ ላይ ነበር፤ በጣም ይቸግረው ነበር፤ ሚስቱ ሕመምተኛ ነበረች፤ የቤት ኪራይ መክፈል ይቸገር ነበር፤ ዛሬ ግን የሚለብሰው ልብስ ሌላ ነው፤ ከኑሮውም ተርፎ ለሲጃራና ለጫት እያወጣ ነው፤ ወይም ሌሎች እያወጡለት ነው፤ ትግሬነታቸው ብቻ እንዲህ የደላቸው በጣም፣ በጣም ጥቂቶች ናቸው፤ ስለዚህም በወያኔ አገዛዝ ትግሬ ሁሉ ተጠቅሞአል ማለት ከጉልሁ እውነት ጋር የሚጋጭ ስሕተት ነው፤ አብርሃ ሰዎች ትግሬ ሁሉ ተጠቃሚ ሆኗል ሲሉ “ያመኛል” ማለቱ ይገባኛል።”
ከዚህ አንጻር ሁሉም ተጠቃሚ እንዳልሆነና የትግራይ ሰዎች የተገለሉ መሆናቸው ግልጽ ነው። ይህም የሆነው አፓርታይዳዊውን ሥርዓት በመቃወማቸው ሲሆን የተቀሩት ግን ከትክክለኛው ዘር – ከአድዋ – ባለመሆናቸው ነው።
2. ህወሃት ደርግን አሸንፏል ስለዚህ ሽልማቱ ይገባናል፤
ይህንን አስተሳሰብ ከሚያራምዱት መካከል አንዱ ወገን በትግራይ ልማቱ እየተካሄደ መሆኑን እና ለትግራይ ሰዎችም የተሻለ ዕድል እንደተሰጣቸው ያምንና ይህ ሁሉ መሆን ያስፈለገው ትግሬዎች ይህ ስለሚገባቸው ነው የሚል ነው። ደርግን የተፋለሙት ሌሎቹስ? በእርግጥ ትግሬዎች ብቻ ናቸው ደርግን ያስወገዱት? ትልቁን ድርሻ ተወጥተው ይሆናል፤ ግን ሌሎችም በዘር ተደራጅተው ሲፋለሙ እንደነበር ታሪካቸው ይመሰክራል። ከእነዚህ መካከል የኦሮሞ፣ የኦጋዴን፣ የጋምቤላ፣ የሲዳሞ፣ የአፋር፣ የቤንሻንጉል፣ … አርነት ንቅናቄዎች ተጠቃሽ ናቸው። ሌሎች አናሳ ናቸው በሚል ቅድሚያ እንዳይኖራቸው ለማድረግ በምን ያህል ማነስ አለባቸው? ሌሎችን በኢትዮጵያዊነት ተጠቃሚ ላለማድረግ ምን ያህል በቁጥርና በመስዋዕትነት መብለጥ ይገባቸዋል? እናንተስ በምን ያህል መስዋዕትነት በልጣችሁ ነው የበላይነቱን ለመውሰድ የቻላችሁ? ወይስ በትጥቅ ትግሉ ዘመን የእናንተ የህይወት መስዋዕትነት ሌላው ከከፈለው ይበልጣል? መለስ እንዳለው “የወርቅ ዘር” ደም ከሌላው ስለሚበልጥ የማሸነፉ “ሽልማት” ይገባችኋል?
3. አማራዎች ተመሳሳይ ነገር ፈጽመውብናል፤ በሥልጣን ካልቀጠልን ሌላው ተመሳሳይ ያደርግብናል፤
ይህ መከራከሪያ የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን ከሞራልም አኳያ ውዳቂ ነው። በፈጣሪ ዘንድ እናንተ አደረጋችሁትም ሌሎችም በናንተ ላይ አደረጉት የሚለወጥ ነገር የለም፤ የሁሉንም በደል የሚመለከት ነውና። ይልቅ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ሌሎችን ለመጉዳት ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ሴራ ነው። እንዲህ ያለው በራስ ወዳድነት የታጠረ አስተሳሰብ ነው ለዘመናት የአገራችንን ሕዝብ ሲያንገላታና ሲያሰቃይ የኖረው።
በቅድሚያ በአማራ ስም በደሉን የፈጸመና ኃላፊነት የወሰደ የለም። ሲቀጥል የቅርብ ታሪካችን ስንመለከት እናንተ በትግሬ ስም አገር አየገዛችሁት እንዳላችሁት እንደ እናንተ በአማራ ስም ድርጅትና ፓርቲ አቋቁሞ አገር የገዛ የለም። ለመሆኑ አማራ ብላችሁ የምትጠሩት የትኛውን ነው? ወይስ እናንተ እንደምትሉትና ከሟቹ መሪያችሁ አንደበት ሲነገር እንደሰማነው “የአማራ አስተሳሰብ” ነው? ይህ ሁሉ ይሁን እንበልና “አማራ ገዝቷልና … ” በሚለው ሃሳብ እንኳን ብንሄድ አሁን እናንተ እንዲህ አድርጋችሁ ስላፈናችሁት ወደፊት ጊዜውን ጠብቆ የጠጣውን ፍዳ የማያስከፍላችሁ ይመስላችኋል? ለዚህ ነው ይህ አስተሳሰብ ከሞራል አኳያ የዘቀጠ ነው ያልኩት።
ይልቁንም ባልንጀራህን/ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ በሚለው የላቀ መመሪያ መሠረት ሌሎች ለእናንተ ጊዜውን ጠብቀው እንዲቆሙላችሁ እናንተ አሁን ለሌሎች ልትቆሙ ይገባችኋል። ከዘራችሁ ሳጥን ወጥታችሁ፤ ይህ ተደርጎብናልና ይህንን እናደርጋለን ከሚል ጠባብነት ተላቅቃችሁ ለሰብዓዊነት መቆም ዋንኛ መመሪያችሁ ብታደርጉ ራሳችሁንና መጪውን ትውልድ ታተርፋላችሁ። እናንተም ብቻ ሳትሆኑም ሌሎችም በዘርና በጎሣ የጠበቡ ሁሉ ይህንን ሊያስተውሉትና ሊገነዘቡት ይገባል።
4. ህወሃት ለወገኖቹ፣ ለዘሩ እና ለክልሉ የሚያደርገውን አድሎአዊነት በጭፍን የሚክዱ፤
በዚህ ሥር የሚጠቀሱት በአገሪቷ የሚካሄደውን አድሏዊነት ሽምጥጥ አድርገው የሚክዱ ናቸው። እስቲ በየክልሉ ያለውን ልዩነት እንመልከትና ራሳችሁ ፍርድ ስጡ። እጅግ በጣም ጥቂቱን ልጥቀስ።
የትግራይ ክልል
- ዓለምአቀፋዊ የልማት ፕሮጀክቶች በቅድሚያ እንዲሄዱ የሚደረግበት
- የኤፈርት ዋና ጽ/ቤት የሚገኝበትና በቅርቡ ዊኪሊክስ (ሹልክዓምድ) እንዳጋለጠው ለኢትዮጵያ ተብለው ለሚሰጡ ዓለምአቀፋዊ ዕርዳታዎችንና ድጎማዎችን ኤፈርት ለትግራይና ለህወሃት እንዲውሉ ያደረገበትና በሥሩ ያሉት ድርጅቶች በህወሃት ቁልፍ ሰዎችና ተባባሪዎቻቸው ቁጥጥር ሥር በመሆኑ ለትግራይ ክልል የተለየ እንክብካቤ የሚከናወንበት
- የኢትዮጵያ ወታደራዊ ሥልጣን ዘጠና ስድስት በመቶ የሚሆነው በትግሬዎች ከመያዙ በላይ ወታደራዊ ተቋማት ዋና መሥሪያ ቤታቸው ያደረጉበት
- ትግሬዎች ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስድስት በመቶ አካባቢ ሆነው ክልሉ ግን ከየትኛውም ክልል በበለጠ ሁኔታ ሆስፒታሎች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት የተከማቹበት መሆኑ
- በአገሪቷ ብቸኛ የቴክኖሎጂ ተቋም ያለበት፤ ከሚወጡ መረጃዎች ለመረዳት እንደሚቻለው በዚህ ተቋም ለመግባት ትግሬ መሆን ወሳኝነት ያለው እንዲሁም በሌሎቹ የኢትዮጵያ ክልሎች ያለውን አሠራር ለመቆጣጠር ተማሪዎቹ ከትግሪኛ በተጨማሪ ኦሮምኛ፣ አማርኛ እና እንግሊዝኛ የሚናገሩ እንዲሆን መደረጉ እንዲሁም የተቋሙ በር ጠባቂዎች የቀድሞ ተመራቂዎች እንዲሆኑ በማድረግ በአገሪቷ ውስጥ ምንም ዓይነት ተቋም ተፎካካሪው እንዳይሆን የተደረገበት ክልል መሆኑ
- በመንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ ያሉት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከዚሁ ክልል የመጡበት መሆኑ
- ኢህአዴግ ብላችሁ በፈጠራችሁት ድርጅት ውስጥ የትግራይ ክልል ሕዝብ ከበርካታዎቹ ጋር ሲነጻጸር አናሳ ሆኖ ሳለ ከአማራውና ከኦሮሞው ድርጅት ጋር በመሆን በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ትግራይ ብቸኛ ተወካይነት እንዲኖረው የተደረገበትና ሌሎቹ በደቡብ ስም የተጠቃለሉበት የተቀሩት አምስት ክልሎች ከነጭራሹም ያልተወከሉበት አድሏዊነት በግልጽ የሚታይበት ክልል ነው።
ለመሆኑ ህወሃት/ኢህአዴግ በዘር ላይ የተመሠረ አፓርታይዳዊ ሥርዓት ነውን?
ይህንን ጥያቄ ለመመለስ በኢትዮጵያ ያሉትን ዋንኛ ተቋማት ማን እንደሚቆጣጠር መመልከቱ በቂ ይመስለኛል። ዝርዝሩ እዚህ ላይ ይገኛል (
http://www.solidaritymovement.org/downloads/140731-leaders-key-institutions-in-Ethiopia.pdf) እስቲ ተመልከቱትና ለራሳችሁ ወስኑ! እንደምትሉት በእውነት ኢትዮጵያ “የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት የተረጋገጠባት” ነች ወይስ የ-ተ-ረ-ጋ-ገ-ጠ-ባ-ት ነች?
የፌዴራል ጉዳዮች ሚ/ር፣ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ የፍትሕ ሚ/ር፣ የብሔራዊ ደኅንነት አገልግሎት (NISS)፣ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚ/ር (MCIT)፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ የመከላከያ ሚ/ር፣ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ሚ/ር፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የሬዲዮና ዜና አገልግሎት – እነዚህ ሁሉ ታላላቅ ተቋማት የአገሪቱን ስድስት በመቶ በሚወክሉ ትግሬዎችና የህወሃት አባላት ቁጥጥር ሥር ያሉ ናቸው።
ከእነዚህም ሌላ ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማኅበረሰቦች፣ … በትግሬዎች፣ በህወሃት አባላት፣ በህወሃት ደጋፊዎች፣ … በሞኖፖል የተያዙ ናቸው።
እንደ ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሌላ ዓይነት ወገን የሆኑ ሰዎች ሥልጣኑን በሚይዙበት ጊዜ አቅራቢያቸውን በሙሉ በትግሬዎች በማጠር እውነተኛውን ሥልጣን በእናንተ እጅ ይወድቃል።
እንደሚታወቀው ነጻ የሆኑ ተቋማት በአንድ ነጻና የተረጋጋ ማኅበረሰብ ውስጥ ወሳኝነት ያላቸው ናቸው። ከዚህ አንጻር እንደነዚህ ያሉ ድርጅቶች ብቃት ባላቸውና ነጻ በሆኑ ግለሰቦች መመራታቸው ከአድልዖ የጸዱ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። በአምባገነን ሥርዓቶች ግን እንዲህ ያሉትን ተቋማት በሥልጣን ባሉት ጥቂት ግለሰቦች ወይም በተላላኪዎቻቸው እንዲያዙ በማድረግ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማስረዘም የሚጠቀሙበት ዓይነተኛ መሣሪያ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሙስና፣ ወገናዊነት፣ ኢፍትሐዊነት፣ ጭቆና፣ … እየተስፋፋ እንዲሄድ የሚያደርግ ከመሆኑ ኅብረተሰቡ በተቋማቱም ሆነ በመሪዎቹ ላይ ያለው እምነት እየተመናመነ ይሄዳል።
በዘር ላይ የተመሠረተ አፓርታይዳዊ ሥርዓት የሚያራምዱ ሁሉ ቁልፍ የሆኑ የሥልጣን ቦታዎችን በአንድ ዘር ወይም ጎሣ አባላት ወይም የአንድ ዘር አባላት በመሠረቱት ፓርቲ ወይም ድርጅት አባላት ብቻ እንዲያዙ ያደርጋሉ። እንዲህ ያሉት ዘረኛ ጥቅመኞች ለሚከፍሉት ታማኝነት በምላሹ ከፍተኛ ሥልጣን፣ ሹመት፣ ዕድልና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች እንዲያገኙ ይደረጋሉ።
ይህ ሲሆን ያላቸው ታማኝነት በየጊዜው እየተለካ የሚያገኙት ጥቅም በዚሁ መልኩ እየጨመረ እንዲሄድ ይደረጋል። ከዚህ አንጻር ህወሃት/ኢህአዴግ በዘር ላይ የተመሠረተ አፓርታይዳዊ ሥርዓት የሚከተል ለመሆኑ ራሳችሁ ፍርዱን እንድትሰጡ እጠይቃችኋለሁ። ይህንን ጽሁፍ (
http://www.solidaritymovement.org/downloads/140731-leaders-key-institutions-in-Ethiopia.pdf) ብትመለከቱ በአገሪቷ ውስጥ ያሉትን ተቋማት ማን እየመራቸው እንደሆነና ከየትኛው ዘር እንደሆነ በግልጽ ልትመለከቱት ትችላላችሁ።
ይህ ሕዝብ የሚያውቀው መረጃ ነው፤ የፈለገውን የብሔር ብሔረሰቦች መብት ተከብሯል ብትሉም ኢትዮጵያን በአፓርታይዳዊ የዘር ሥርዓት እየገዛችሁ መሆኑን ልትሸሽጉ ከቶውንም አትችሉም።
እነዚህን ሁሉ ማስረጃዎች እየዘረዘርኩ ለመናገር የሞከርኩት ከተያዛችሁበት የዘረኝነት፣ የወገናዊነት፣ የጠባብነት፣ የጎጠኝነት እና ሁሉን ለኔ ወይም ለዘሬ ከሚል ስግብግብነት በሽታዎች እንድትላቀቁ ነው። በዚህ ነጥብ ላይ የምለምናችሁ ነገር የለም። ከእነዚህ የዘመናት በሽታዎች ብትላቀቁ ራሳችሁንና መጪውን ትውልዳችሁን ታድናላችሁ። ከኅሊና ፍርድ ነጻ ትሆናላችሁ። ተዋግተንለታል የምትሉት ዘራችሁን በጭፍን ከመፈረጅ አድናችሁ አንገት ከመድፋትና በእናንተ ግፍ መላውን የትግራይ ሕዝብ ከማስወንጀልና ይህንን ተከትሎ ሊነሳ ከሚችል በቀል ትታደጉታላችሁ።የኢትዮጵያ ሕዝብ ለ23 ዓመታት መከራውን ስታበሉት ስለኖራችሁ ከዚህ በኋላ የሚያጣው ብዙም ነገር አይኖርም። ለእናንተና ለዘራችሁ ግን ብዙ እጅግ ብዙ የምታጡት አለ። መጠኑ የማይለካ ፍዳ ቁጭ ብሎ እየጠበቃችሁ ነው። ከሰው ብታመልጡ ከፈጣሪ ፍርድ አንዳች የሚያመልጥ የለምና ጊዜ ፊቷን ያዞረችባችሁ ቀን እንዲህ ዓይነቱን የምህረት ተግሳጽ የትም ብትፈልጉት አታገኙትም።
ከዚህ መሰሉ መቅሰፍት ለማምለጥ እንድትችሉ በዋንኛ ኃላፊነት ላይ የምትገኙት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ቀዳሚው ስትሆኑ እናንተን የሚደግፉት የትግራይ ተወላጆች በሙሉ ቀጣዩ ኃላፊነት የወደቀባቸው ናቸው። በሦስተኛነት በኢህአዴግ ስም ከእናንተ ጋር ተቀላቅለው የሚሰሩት – የኦሮሞ፣ የአማራና የደቡብ ሰዎች – እንዲሁም ሌሎች ለጥቅም ያደሩ፣ ኅሊናቸውን የሸጡ ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት ነው።
ከዚህ ሌላ በፍጹም መዘንጋት የሌለባቸው አሉ። ከእነዚህም መካከል ጋሻ ለኢትዮጵያ ያለውን ችግር በግልጽ ከመናገር አኳያ ቀዳሚው ነው። በግለሰብ ደረጃ ቀድሞ የህወሃት አባል የነበሩትና የህወሃትን አደገኛ አካሄድ ካወቁበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን አቅጣጫውን እንዲቀይር በአደባባይ የሚመሰክሩት አቶ ገብረመድኅን አርአያ፣ ከአገር ውስጥ ሆነው በብዙ መከራና ስቃይ ውስጥ እንኳን እውነትን ከመናገር ወደኋላ የማይሉት፣ እሳቸውና ልጆቻቸው ቢታሰሩም፣ ስቃይ ቢቀበሉም በዓላማቸው የጸኑት አዛውንት አቶ አሰግደ ገብረሥላሴ፣ ደፋሩና አስተዋዩ ወጣት የኮሌጅ መምህር በዘር መጠጥ ያልሰከረውና እናንተን ህወሃቶች በትግራይ ሕዝብ ስም የምታደርጉትን በመቃወም ሌሎቹን ትግሬዎችን “ይህ በኔ ስም መደረግ የለበትም” ብለው እንዲሟገቱ በድፍረት በመናገሩ በግፍ ያሰራችሁት አብርሃ ደስታ ለብዙዎች መዳኛ ይሆኑ ዘንድ የሚጠቀሱ ናቸው።ፕ/ር መስፍን ወልደ-ማርያም እንዳሉት እኔም “አሥር ቢሞሉልኝ ደስ ይለኝ ነበር!” ጥቂትም ቢሆኑ የራሳችሁ ወገኖች የሆኑ እና ከራሳችሁ ድርጅት ጋር ሲሰሩ የነበሩ ምስጢራችሁን ሁሉ የሚያውቁት በግልጽ እየተናገሩ ከጥፋት መንገዳችሁ እንድትመለሱ ሲመክሯችሁ እምቢ በማለት ለእስር ስትዳርጉ ከቶውንም አታፍሩም?! ወዮ የምትሉበት ጊዜ አሁን ነው። ጊዜ ሳያልፍ፤ ቀን ሳይጨልም!
ከትግራይ ማኅበረሰብ በርካታዎች እናንተ የምታደርጉትን አፓርታይዳዊ የዘር ፖሊሲ እንደሚቃወሙ አምናለሁ፤ ነገር ግን በገሃድ ወጥተው ለመቃወም እንደሚፈሩ አስተውላቸኋለሁ። የሌሎች ፍርሃቻ ደግሞ ህወሃት ከሥልጣን ከወረደ ማን ይተካዋል የሚል ነው። ለዚህም ነው የትግሬዎች በይፋ መውጣትና ኃላፊነት በመውሰድ ለመፍትሔ መነሳት አስፈላጊ የሆነው። ዝምታው ድጋፍ ከመስጠት ተለይቶ አይታይምና።
እንዲሁም ከተለያዩ ክፍሎች የሆናችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ራሳቸውን በማነጽ ለልጆቻቸውና ለመጪው ትውልድ መልካም ለማድረግ የሚነሱትን ትግሬዎች መደገፍ እንደሚገባችሁ ላሳስብ እወዳለሁ። ስለሌሎች “እነሱ” እያሉ ከማውራት ይልቅ “እኛ” እያላችሁ ለሁሉም የሚሆን መፍትሔ እንዲመጣ እንድትወያዩና እንድትቀራረቡ ይሁን። ከፈጣሪ የተሰጠንን ልዩ መብት የምታከብር አገር ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያ እንድትኖረን ውይይቱ ይጀመር። የአንዱ ጉዳት የሁላችንም ሆኖ ይሰማን፤ በ“እኔ ከሞትኩ …” ጭፍን አስተሳሰብ አንታወር፤ መልሶ የራሳችንን የአስተሳሰብ ዓይን ያጠፋዋል። ስለዚህ ሁላችንም እንደ አንድ ትልቅ ቤተሰብ ተከባብረንና ተሳስበን ለመኖር የምንችልባት አገር ለመሥራት እንትጋ።
የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ እነዚህን ሁሉ ችግሮች የማያርም ከሆነ ጉዳዩ በርትቶ ወደ ዓመጽ ተቀይሮ ከፈነዳ በኃላፊነት የምትጠየቁት ራሳችሁ ናችሁ። ፍርዳችሁንም ከሁሉም መስመር ትቀበላላችሁ። ይህንን ዓይነቱን ማስጠንቀቂያ ደቡብ አፍሪካውያን አሻግረው ተመለከቱትና በተግባር አዋሉት፤ ሩዋንዳውያን ግን ሰምተው ዝም አሉ። ውሳኔ አለመስጠት በራሱ ውሳኔ ነው። ስለዚህ እናንተም በህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ያላችሁ ይህንን ማስጠንቀቂያ ችላ ልትሉት ትችላላችሁ፤ አላወቅንም ማለት ግን በጭራሽ አትችሉም። ሁሉ ይቅርና ይህ ደብዳቤ ራሱ በበቂ ማስረጃነት ይቀርብባችኋል፤ ለዚህም እንዲያግዝ የእንግሊዝኛውም ሆነ ይህ ትርጉም ለመንግሥታት፣ ለሚዲያ ተቋማት፣ ለዓለምአቀፍ ድርጅቶች፣ … በግልባጭ እንዲደርስ ተደርጎ በሰነድነት ተቀምጧል፤ በጊዜው እንዲወጣ ይደረጋል። የዚያን ጊዜ የት ትሸሸጋላችሁ?
ህወሃትን ለምትቃወሙ የትግራይ ወንድሞችና እህቶቻችን፤
ለስኬት ለመብቃት እና ህወሃት ለ23 ዓመታት የመሠረተውን የጥላቻና የዘር ግምብ ለማፍረስ ጠለቅ ያለ ከልብ የሆነ መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልጋል። ህወሃት በሚለው መጠሪያ ውስጥ “ትግራይ” ተጠቅሷል። ይህ ደግሞ እናንተን ሁሉ የሚጠቀልል ነው። ስለዚህ ይህንን የህወሃት ፖሊሲ የማትደግፉ ከሆነ ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ “ይህ በኔ ስም አይሆንም” ማለት አለባችሁ።
እውነትን በቤታችሁንና በትናንሽ ቡድኖቻችሁ ውስጥ ሳይሆን በገሃድ የምትናገሩበት ጊዜ አሁን ነው። ሊፈነዳ ደቂቃውን እየቆጠረ ያለውን ቦምብ ማክሸፍ የሚቻለው “ቦምብ የለም” ብሎ በማስመሰል፤ ወይም “ሁሉም ሰላም ነው” በማለት አይደለም። ለጥፋታችን ሌላውን በመወንጀል ብቻ እውነትን ሳንናገር ተሸሽገን እንዴት ነው ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያ መመሥረት የምንችለው? “አልሰማም” ብለን ጆሮአችንን ከመስማት ብናርቅ እውነትን ልናመልጥ እንዴት እንችላለን? ልባችንን ብናደነድን፣ ብናሳብጥ፣ ስህተታችን ከማረም ብንታቀብ፣ ጥለን ብንሄድ፣ እውነትን በተጋፈጥን ቁጥር በንዴትና በቁጣ ምላሽ ብንሰጥ፣ … ምን ይረባል? ከእውነት እውነተኛነትስ እንዴት መሸሽ ይቻላል? በህወሃት ሲደሰኮር የቆየውና በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያችን የሚታየው “ቅድሚያ ለዘሬ” የሚለው አመለካከት ሌላው የመጥበብ ፖለቲካ ውጤት ነውና የትም አያደርስም። በወቅቱ የንዴት ማብረጃና የበቀል መወጫ መስሎ ቢወሰድም ለመጪው ትውልድ ግን የማይጠፋ እሣት ነው የሚለኩሰው።
ስለዚህ በትግራይ ማኅበረሰብ ውስጥ ያላችሁትን ሁሉ የአንድ ዘር የበላይነትን የማትደግፉ የለውጥ ሐዋሪያት በመሆን ለእርቅ እና ለፍትሕ እንዲሁም ለእውነተኛ ተሃድሶ ፈርቀዳጅ እንድትሆኑ ላደፋፍራችሁ እፈልጋለሁ። የዘር በሽታውን ለማምከን የመጀመሪያው ሥራ መሥራት የሚገባችሁ እናንተ ናችሁ። ልትግባቡና ልትተማመኑ በምትችሉበት መንገድ በመነጋገር አንድ አቋም ላይ መድረስ አለባችሁ። ማኅበራሰባችሁን ማነጋገርና ማሳመን የእናንተ ቀዳሚ ኃላፊነት መሆን ይገባዋል። መተማመንን ማዳበር የምትችሉት እናንተ ናችሁ። ከዚያም ከሌሎች ጋር ለመነጋገርና ለመወያየት በር እየተከፈተ ይሄዳል። የዕርቅ መሠረትንም መዘርጋት የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስችላል። ራሳችሁን ነጻ አውጥታችሁ ለሌሎች ነጻነት በጽናት የምትቆሙበት ወቅት ቢኖር አሁን ነው፤ ይህንን አዲስ ዓመት ለዚህ ዓላማ ተጠቀሙበት።
ሌሎችም በዘር ላይ የተመረኮዘ እንቅስቃሴ የምታደርጉ ራዕያችሁን በማስፋት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻ እስካልወጣ ድረስ የራሳችሁን ዘር ብቻ ነጻ ማውጣት እንደማትችሉ መገንዘብ ይኖርባችኋል። ስለዚህ ከእናንተም የሚጠበቀው ከትግራይ ወገኖች ከሚጠበቀው ያነሰ አይደለም።
በህወሃት አመራር ያላችሁ በሙሉ፤ ይህንን ግልጽ ደብዳቤ በራሴና በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ስም ልኬላችኋለሁ። ከሰከራችሁበት የዘር ፖለቲካ የምትነቁ ከሆነ በጣም ጥቂት የሆነውን በዚህ ደብዳቤ ለማስፈር ሞክሬአለሁ። ለመንቃት ለሚፈልግ ከበቂ በላይ ነው። አንገት በማደንደን፣ ልብ በማሳበጥና በትዕቢት በመወጠር የጀመርነውን እንቀጥላለን የምትሉ ከሆነ ውሳኔው የራሳችሁ ነው። ሁሉም ነገር ግን ጊዜውን ጠብቆ ለፍርድ ይቀርባል። “ነጻ አውጪ” ነን በሚል ድንፋታ ብትቀጥሉ ከሁሉ የሚበልጠው የነፍስ ነጻነት እንደሆነ ልታውቁ ይገባችኋል። ይህ ደግሞ በነጻ አውጪ ግምባር የሚመጣ አይደለም።
ከዚህ ሁሉ በላይ በደልን የሚቆጥርና ግፍን የሚመልስ ፈጣሪ አለ። የበቀል ሰይፍ ከመመዘዙ በፊት አምላክ ለሁላችንም የማስተዋል አእምሮ ይስጠን። እውነትን በድፍረት የምንናገር፣ የዘር ቦምብ የምናከሽፍ፣ ለጎረቤታችን የምንራራ፣ በፍቅርና በትህትና የምንመራ፣ ለፍትሕ፣ ለይቅርታና ለዕርቅ የምንሰራ፣ ከጥላቻ ይልቅ የመቻቻልን መንፈስ የምናራምድ ያድርገን። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ለሁላችንም እና ለመጪው ትውልድ የምትሆን አዲስ ኢትዮጵያ የምትኖረን። ልቦና ይስጠን!
መልሳችሁን እጠብቃለሁ።
አክባሪ ወንድማችሁ፤
ይህ ደብዳቤ ለሚከተሉት ግልባጭ ተደርጓል፡- ለጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ለኢህአዴግ፣ ለኦህዴድ፣ ለብአዴን፣ ለደኢህአዴን እና ለህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ ለኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለኢትዮጵውያን የሲቪክና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ ለሃይማኖት መሪዎች፣ በዳያስፖራ ለሚገኙ ድርጅቶች፣ የእንግሊዝኛው ቅጂ ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ ለውጭ ጉዳይ ሚ/ር ጆን ኬሪ፣ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሱዛን ራይስ፣ ምክትል የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ በስትራቴጂክ ግንኙነት ዘርግ ቤን ሮድስ፣ በውጭ ጉዳይ ሚ/ር የዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብትና ሠራተኞች ጉዳይ ረዳት ጸሃፊ ቶም ማሊኖውስኪ፣ በብሔራዊ ደኅንነት ም/ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ዳይሬክተር ግራንት ሃሪስ፣ በብሔራዊ ደኅንነት ም/ቤት የልማትና የዴሞክራሲ ከፍተኛ ዳይሬክተር ጌይል ስሚዝ፣ በውጭ ጉዳይ ሚ/ር የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ረዳት ጸሃፊ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ፣ ለዩኤስ ኤይድ ረዳት አስተዳዳሪ ኧርል ጋስት፣ በአሜሪካ ሕግመወሰኛ ምክርቤት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር ሮበርት ሜኔንዴዝ፣ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ከፍተኛ አባል ቦብ ክሮከር፣ በሕግ መወሰኛ ም/ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ክሪስቶፈር ኩንስ፣ ለሌሎች የሕግ መወሰኛ ም/ቤት ከፍተኛ አባላት (ሴናተሮች) ሚች ማኮኔል፣ ዳያን ፋይንስታይን፣ ጆን ማኬይን፣ ሪቻርድ ደርቢን፣ ኤድዋርድ ሮይስ፣ በእንደራሴዎች ም/ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የአፍሪካ ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ክሪስቶፈር ስሚዝ፤ ለእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ ለአውሮጳ ማህበር የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀመንበር፣ ለጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ ለኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር፣ ለአፍሪካ ኅብረት፣ ለአውሮጳ ኅብረት፣ ለአውሮጳ ኮሚሲዮን፣ ለካናዳ መንግሥት፣ ለታላቋ ብሪታኒያ መንግሥት፣ ለካናዳ ዓለምአቀፍ ተራድዖ ድርጅት (ሲዳ)፣ ለአሜሪካ የዓለም አቀፍ ልማት ተቋም (ዩኤስኤይድ)፣ ለእንግሊዝ ዓለምአቀፍ ልማት መምሪያ፣ ለጃፓን የዓለምአቀፍ ትብብር ባንክ፣ ለጃፓን ዓለምአቀፍ ትብብር ኤጀንሲ፣ ለቻይና ዓለምአቀፍ ትብብር ካውንስል፣ ለህንድ ዓለምአቀፍ ልማት ትብብር ኤጀንሲ፣ ለህንድ ኤግዚም ባንክ፣ ለቻይና ኤግዚም ባንክ፣ ለዳኒሽ ዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዳኒዳ)፣ ለፊንላንድ ዓለምአቀፍ ልማት ትብብር (ፊኒዳ)፣ ለፈረንሣይ ዓለምአቀፍ ትብብር መምሪያ፣ ለፈረንሣይ ልማት ኤጀንሲ፣ ለጀርመን ዓለምአቀፍ ልማት፣ ለኔዘርላንድስ የልማት ትብበር ሚ/ር፣ ለኖርዌይ ዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ኖራድ)፣ ለስዊድን ዓለምአቀፍ ልማት ትብብር (ሲዳ)፣ ለስዊዝ ዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ፣ ለቱርክ ዓለምአቀፍ ልማት ትብብር ኤጀንሲ (ቲካ)፣
ለሚከተሉት የተለያዩ ድርጅቶችና መ/ቤቶች ግልባጩ ተልኳል፡- Amnesty International, Human Rights Watch, International Commission of Jurists (ICJ), Physicians for Human Rights, The International Justice Resource Center (IJRC), The African Court of Justice and Human Rights, International Criminal Court (ICC), International Justice Project, United to End Genocide, Humanity United, Never Again Coalition, GlobalSolutions.org, The World Council of Churches (WCC), ACTION AID, AFRICA HERITAGE FOUNDATION, AFRICA LEGAL AID, AFRICAN DEVELOPMENT ASSOCIATION, ALLIANCE FOR FINANCIAL INCLUSION, BUSINESS ACTION AGAINST CORRUPTION, CARE INTERNATIONAL, CATHOLIC AGENCY FOR OVERSEAS DEVELOPMENT, CENTER FOR INTERNATIONAL PRIVATE ENTERPRISE, CORRUPTION WATCH, COUNCIL ON FOREIGN RELATIONS, CREATE TRUST, DEMOCRACY WATCH, FORD FOUNDATION, FREEDOM NOW, Free Africa Foundation, GENOCIDE WATCH, Global Advice Network, GLOBAL HUMAN RIGHTS DEFENSE, Global Integrity, INTERNATIONAL CRISIS GROUP, INTERNATIONAL LEGAL ALLIEANCE, Least Developed Countries Watch (LDC Watch), MELINDA & GATES FOUNDATION, Development Research Institute NYU, THE AFRICAN CHAMBER OF COMMERCE IN THE US, THE AFRICAN INSTITUTE OF CORPORATE CITIZENSHIP, The Bertelsmann Foundation, THE COMMONWEALTH BUSINESS COUNCIL, THE CORPORATE COUNCIL ON AFRICA, THE FINANCIAL ACTION TASK FORCE (FATF), THE GLOBAL CLEARINGHOUSE FOR DEVELOPMENT FINANCE, TRANSPARENCY INTERNATIONAL, TRUST Africa, U.K. Anti-Corruption Forum, Overseas Development Institute UK, OXFAM, PARTNERSHIP AFRICA CANADA, PAC, World Vision International, World Accord, HOPE International Development Agency, CARE- Cooperative for Assistance and Relief, Africa Governance Monitoring and Advocacy Project (AfriMAP), AFRICAN DEVELOPMENT BANK, AFRICAN UNION, The African Economic Community (AEC)-AU, Common Market for Eastern and Southern Africa (COMESA), East African Court of Justice (EAC), BANK FOR INTERNATIONAL SETTLEMENTS,ECONOMIC COMMISSION FOR AFRICA (ECA), INTERNATIONAL FUND FOR AGRICULTURAL DEVELOPMENT (IFAD), INSTITUTE FOR INTERNATIONAL COOPERATION AND DEVELOPMENT (IICD), Multilateral Investment Guarantee Agency-World Bank, INTERNATIONAL BANK FOR RECONSTRUCTION AND DEVELOPMENT WORLD BANK, International Monitory Fund (IMF), INTERNATIONAL LABOUR ORGANIZATION, Investment Climate Facilities for Africa Trust (ICF), ORGANIZATION FOR ECONOMIC CO-OPERATION AND DEVELOPMENT, Development Assistance Group (DAG), United Nations (UN)-Sectary, United Nations Human Rights Council, United Nations Development Programme (UNDP), United Nations Conference on Trade and Development (UNCTAD), Multilateral Investment Guarantee Agency, United Nations Industrial Development Organization UNIDO, Jeffrey Sachs (earth institute), Kofi Annan (Africa progress panel)
የደብዳቤው ግልባጭ ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት በአዲስ አበባ ለሚገኙት ኤምባሲዎች አምባሳደሮች በስማቸው ተልኳል፡- ለአሜሪካ፣ ለታላቋ ብሪታኒያ፣ ለስዊድን፣ ለፈረንሣይ፣ ለእስራኤል፣ ለዴንማርክ፣ ለፊንላንድ፣ ለሩዋንዳ፣ ለካናዳ፣ ለብራዚል፣ ለሕንድ፣ ለኬኒያ፣ ለጀርመን፣ ለጣሊያን፣ ለአውሮጳ ኅብረት፣ ለአውስትራሊያ፣ ለቱርክ፣ ለስዊትዘርላንድ፣ ለጃፓን፣ ለዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮሪያ፣ ለኢንዶኔዢያ፣ ለሳውዲ አረቢያ፣ ለሩሲያ ፌዴሬሽን፣ ለኖርዌይ፣ ለታንዛኒያ፣ ለግብጽ፣ ለቤልጂየም፣ ለጅቡቲ፣ ለሱዳን፣ ለቻይና ፣ ለደቡብ አፍሪካ እና ለኔዘርላንድስ ኤምባሲ አምባሳደሮች።
ለአገር ውስጥና ለውጭ የሚዲያ ተቋማት እንደ ቋንቋው ተጠቃሚነታቸው ተልኳል። እነዚህም፡ Africa Confidential, Al Jazeera, BBC, the Guardian, New York Times, Washington Post, Wall Street Journal, Bloomberg News, MSNBC, CNN, INDIAN OCEAN NEWSLETTER, REUTERS AFRICA, The East Africa, Business Daily, African Review, Deutsche Welle Radio, VOA Amharic, VOA-English, ESAT, Addis Fortune, ለሪፖርተርና ለሌሎች በአገር ውስጥ እና በዳያስፖራ ለሚገኙ ድረገጾች፣ የራዲዮ ፕሮግራሞች፣ መጦመሪያዎች፣ ወዘተ።