Monday, February 4, 2013

በደብረብርሃን ነዋሪዎች በፖሊሶች የተፈፀመን የመብት ጥሰት አጋለጡ

  • digg

በአማራ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ በሆነው ደብረብርሃን ከተማ ፖሊስ በነዋሪዎች ላይ የመብት ጥሰት እየፈፀመ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ዝግጅት ክፍላችን ድረስ በመምጣት በሰጡት መረጃ ፖሊስ በፀጥታ ማስከበር ስም በወንጀል ድርጊት ላይ መሰማራቱን አጋልጠዋል፡፡
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ፖሊስ ራሱን ከህግ በላይ አድርጐ ስለሚቆጥር የዜጐችን ህገመንግስታዊ መብት በሚጥስ አሰራር ላይ ተሰማርቷል፡፡ ነዋሪዎቹ ጨምረው እንደሚያስረዱት “ፖሊሶች ከካድሬና ከደህንነት በሚሰጣቸው ትዕዛዝ ንፁሐን ዜጐችን በፖለቲካ አመለካከታቸው እያስጠሩ ያሸማቅቃሉ፣ ያስፈራራሉ፣ ይደበድባሉ፣ ያስራሉ፡፡” ነዋሪዎቹ በምሳሌነት ሲገልፁም “የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀበሌው ኮሚኒቲ ፖሊስ፣ ከወረዳው ፖሊስ፣ ከክልሉ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ እና ከፌዴራል ፖሊስ የተውጣጣ ቡድን ከለሊቱ 8 ሰዓት ቀበሌ 06 ቀጠና 4 ውስጥ የጌታ ወ/ሚካኤል የተባሉን ግለሰብን ግቢ ከበቡ፡፡ የግቢው ነዋሪዎች ለአካባቢው ነዋሪ በስልክ በማሳወቃቸው የአካባቢው ህዝብ ወጥቶ ምንድነው? ብሎ ጠየቀ፡፡ እዚህ ግቢ የሚኖር አቶ አበበ በቀለ የተባለ ግለሰብ አካባቢውን በጥብጧል የሚል መረጃ ደርሶን ነው ብለው መለሱ፡፡ የመላው አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ የሰሜን ሸዋ ተጠሪ የሆኑት አቶ አበበ ከነጐረቤቶቹ በሠላም ተኝቷል፡፡ በአካባቢው የተፈጠረም የፀጥታ መጓደል የለም፡፡ ማነው እንዲህ ብሎ የነገራችሁ በዚህን ሰዓት ከተለያየ ቦታ የተውጣጣ ፀጥታ አስከባሪዎችስ እንዴት ተቀናጅታችሁ ልትመጡ ቻላችሁ ብለን ብንጠይቃቸው መልስ ሳይሰጡ አቶ አበበንና ለፖሊሶቹ ጥያቄ ያቀረቡትን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱ፡፡ የፍ/ቤት ትዕዛዝን ብንጠይቅ ምን አገባችሁ፡፡ የመጠየቅ መብት የላችሁም አሉን፡፡ ለሊቱኑ ለተለያየ ሚዲያ ደውለን በማሳወቃችን ንጋት ላይ በ12 ሰዓት ስትጠሩ ትመጣላችሁ ብለው ታሳሪዎቹ ለቀዋቸዋል” ብለዋል፡፡ ታሳሪዎቹ “የታሠርንበት ወንጀል ይነገረን፤ የከሰሰን ሰው ማነው” ብለው ቢጠይቁም መልስ እናዳለገኙ መረጃ ሰጪዎቻችን ጠቁመውናል፡፡ ያለ አንድ ምክንያት ዜጐችን በአመለካከታቸው ለማዋከብና በሐሰት ለመወንጀል ሲባል የአካባቢው ህዝብ ሠላም ማጣቱም እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ የቀበሌው ኮሚኒቲ ፖሊስ አስተያየት እንዲሰጥበት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ ይሁን እንጂ የወረዳውን ፖሊስ አዛዥ ኢ/ር ምንውዬለትን በስልክ አግኝተን ጠይቀናቸው ጉዳዩን አጣርተው እንደሚደውሉ ቢነግሩንም ዜናው እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ምላሽ አልሰጡንም፡፡


No comments: