Friday, February 15, 2013

ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ በጀርመን ተካሄደ

Dawit Fanta
የኢትዮጵያውያን የፖለቲካና ሲቪክ ማህበር አባላት አንድነት ድርጅት በፌብሯሪ 09, 2013 ዓ.ም. ያዘጋጀው ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ በታሪካዊቷ የኑረንበርግ ከተማ ተካሄደ።
ከመላው ጀርመን የተሰባሰቡ ቁጥራቸው ከ350 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በታደሙበት በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ከተለያዩ ድርጅቶት ተወካዮች የተገኙ ሲሆን የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሲቪክ ማህበሩ መስራችና ሊቀ መንበር አቶ በላይነህ ወንዳፍራሽ ነበሩ።
clip_image002አቶ በላይነህ በመክፈቻ ንግግራቸው ሲገልፁ የዚህ አይነቱ መድረክ መዘጋጀት የፖለቲካ ድርጅቶች ከህዝባችን ጋር ገጽ ለገጽ በመገናኘት አላማና ፕሮግራማቸውን ለማስረዳት ከመጥቀሙም በላይ ከህዝብ ጋር በሚኖራቸው የቀጥታ ግንኙነት መሠረት ሀገራዊ ፋይዳ እና ራዕይ ያለው የትግል አጋር የሆነ ተረካቢ ወጣት ትውልድ ለማፍራት ይረዳል ብለዋል።
”በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ አራት አይነት ዜጎች አሉ” በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት ተወካይ ኢንጂነር ስለሺ በዚያች ሀገር በተጠቃሚነት ደረጃ የህወሃት አባላት የመጀመሪያ እና ትልቁ ሲሆኑ፤ሁለተኛ ዜጋ የሚባሉት የወያኔ ተለጣፊ ድርጅት አባላት ናቸው።እንዲሁም በሦስተኛ ዜግነት የሚፈረጁት በወያኔ 5ለ1 አደረጃጀት ለመኖር፣ለመስራትና ለመማር ሲሉ በኢህአዴግነት የታቀፉ ሲሆን ከነዚህ ውጪ የሚገኘው አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በአራተኛ ደረጃ የዜግነት እርከን ላይ ይገኛል ብለዋል።
ኢንጂነር ስለሺ በመቀጠለም በኢትዮጵያ አምስት አይነት የሽግግር አማራጮች እንዳሉ ሲዘረዝሩ 1ኛ ሥርዓቱ ከውስጥ በሚነሳ መሰነጣጠቅና በመዳከም ይወድቃል ብሎ በተስፋ መጠበቅ ሲሆን ይህም የመሆን ዕድሉ የጠበበና ”የስንፍና” አስተሳሰብ ነው ብለዋል።2ኛ የወያኔን ህገ-መንግስት ተቀብሎ በምርጫ ማሸነፍ የሚል ሲሆን ይህም በምርጫ 97 ተሞክሮ እንደታየው ተግባራዊ ሊሆን አይችልም ብለዋል።3ኛ. አንድ ጠንካራ ፓርቲ በኃይል ጠንክሮ ወጥቶ ወያኔን በመጣል ሥልጣን መያዝ የሚለው ሲሆን ይህም በኢትዮጵያ እየታየ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ለሀገራችን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች ዘለቄታ ያለው መፍትሔን የማያመጣ ይልቁንም ልክ እንደወያኔ ሁሉ ለማሸነፍ ብዙ መስዋዕት የከፈልኩት እኔ ነኝ ከሚል ዕሳቤ በመነሳት አምባገነናዊ ስርዐት የሚገነባበት ዕድል የሰፋ ይሆናል ሲሉ ይህንንም አማራጭ አጣጥለውታል።4ኛ. ብሔራዊ እርቅ ማድረግና የሽግግር መንግስት መመስረት የሚለው ሲሆን ብሔራዊ እርቅ የሚለውን ሀሳብ የወያኔ መንግስት ለዘመናት በማጣጣል ወደጎን ሲገፋው የኖረ ሀሳብ በመሆኑ ይህንንም አማራጭ በተጨባጭ ወደ ተግባር ለመተርጎም የማይቻል ሲሉ ገልፀውታል።5ኛ ሁሉን አቀፍ በሆነ ትግል የወያኔን ሥርዓት ማስወገድ እና የሽግግር መንግስት ማቋቋም ሲሆን ይህን ሀሳብ ድርጅታቸው እንደሚያምንበት ገልፀው የዚህን አማራጭ አዋጭነትም ሲያስረዱ የወያኔ ስርዓት መወገድ አለበት የሚለው የአብዛኛው ህብረተሰብ ጥያቄ መሆኑ፣”ትግሉም የጋራ፥ድሉም የጋራ” ከሚል መንፈስ በመነሳት እንዲሁም በግብፅ የተከሰተው አይነት ሁኔታ እንዳይፈጠር ከለውጡ በኋላ የሚኖረውን ክፍተት ለመዝጋትና ሁሉም ዴሞክራሲዊ ኃይሎች ያለቅድመ ሁኔታ ለመስራት ስለሚረዳ ሲሉ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
በሌላ በኩል የነፃውን ፕሬስ ወክለው ንግግር ያደረጉት የጥላ መጽሔትና ዌብ ሳይት ዋና አዘጋጅ አቶ ዳዊት ፋንታ ሲሆኑ ዛሬ የወያኔ መንግስት ከጦር መሣሪያ ይልቅ ብዕርን አጥብቆ እንደሚፈራ ገልፀው ሥርዓቱ በፈጠረው አፋኝና ዘረኛ አስተዳደር ምክንያት ብዕር የሚያነሱ እጆች አንድም ለስደት አልያም ለሰንሰለት ተዳርገዋል በማለት ተናግረዋል።
clip_image002

የወያኔ መንግስት የፕሬስ ነፃነትን በአዋጅ አፅድቄአለሁ እያለ ቢመፃደቅም በተግባር እንደሚታየው ግን ይህ አዋጅ ለፕሬስ ነፃነት መከበር ዋስትና የማይሰጥ ይልቁንም ወያኔን በውጪው አለም ዴሞክራሲያዊ መንግስት አስመስሎ ለማሳየት የተዘጋጀ የወረቀት ላይ ነብር ነው በማለት አክለው ተናግረዋል።እንደ አቶ ዳዊት ገለፃ የወያኔ አስተዳደር በየጊዜው የሚያወጣቸው ህጎች ማለትም እንደ አዋጅ ቁጥር 652/2009 የመሣሠሉ ጋዜጠኞችን በአሸባሪነት የሚፈርጁ አሻሚ የህግ አንቀፆች የነፃውን ፕሬስ እጅ ተወርች ጠፍንገውት ይገኛል ሲሉ ሃሳባቸውን አጠቃለዋለዋል።
በሌላ በኩል የአማራው ነገድ ራሱን ከጥፋት ለመከላከል የመደራጀት አስፈላጊነትና አስገዳጅነት ነጥቦችን በመዘርዘር ንግግራቸውን የጀመሩት የሞረሽ ወገኔ የአማራ ድርጅት ተወካይ ዶ/ር አፈወርቅ ተሾመ ሲሆኑ ለሞረሽ ወገኔ የአማራ ድርጅት መመስረት ምክንያት ነው ያሉትን ነጥብ እንደሚከተለው አቅርበዋል፦
  • ”የአማራው ነገድ ከመቼው ጊዜ በከፋ መልኩ ህልውናው በከፍተኛ አደጋ ላይ የወደቀ መሆኑን እንገነዘባለን።አማራው በሆደ ሰፊነት፣በትዕግስትና በአርቆ ተመልካችነት ወያኔ በአማራው ላይ የሰነቀውን የዘር ጥላቻ እያረገበ ወደ መቻቻልነትና ወደ አብሮነት ይመለሳል፤ሥልጣናቸውን ሲያረግጡና ሲረጋጉ ወደ እውነተኛ ኅሊናቸው ይመለሳሉ በማለት በከፍተኛ ተስፋ ቢጠብቅም የጠበቀው ተስፋ እውን ሊሆን ካለመቻሉም በላይ በአማራው ላይ የከፋና የከረረ የዘር ማፅዳት ዘመቻ ተጠናክሮ በመቀጠሉ አማራው ባለፉት 22 ዓመታት ያሳየው ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት ተፈላጊውን ውጤት ያላስገኘ በመሆኑ ትውልዱ ፈፅሞ ከመጥፋቱ በፊት ሌላ አማራጭ መከተል ግድ ብሎታል።ይህም አማራጭ አማራው በዜግነት ሲቪክ ድርጅት ተደራጅቶ ራሱን ከፈፅሞ ጥፋት መታደግ ነው።” በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ፣የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ዘብ እና የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር በጀርመን የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተወካዮች የድርጅቶቻቸውን አላማና ፕሮግራም ለተሰብሳቢው ያቀረቡ ሲሆን በውይይቱ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ከድርጅት ተወካዮች ምላሽ ተሰጥቷል።
በሁለት ክፍለ ጊዜ ተከፍሎ በተዘጋጀው በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የተለያዩ ወቅታዊ የሆኑ ግጥሞችና መጣጥፎች በየመሀሉ የቀረቡ ሲሆን መድረኩን በብቃት በመምራት የሴቶች ተሳትፎ ጎልቶ የወጣበት ሁኔታም ተስተውሏል።
በመጨረሻም ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ባለ ሦስት ነጥብ የጋራ የአቋም መግለጫ በማውጣት ውይይቱ ተጠናቋል።
  1. የወያኔ መንግስት በሃይማኖት ውስጥ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት እናወግዛለን፤በሃገራችንም የሃይማኖት ነፃነት እስኪረጋገጥ ትግላችንን አጠንክረን እንቀጥላለን።በቅርሶቻችን እና ጥንታዊ እና ታሪካዊ ገዳማት ላይ የሚደርሰውን ጥፋት አጥብቀን የምንቃወም ሲሆን በቅርቡ ”ጂሃዳዊ ሓረካት” በማለት በወያኔ የፕሮፖጋንዳ ማሽን የተላለፈው ድራማ የወያኔን ፖለቲካዊ ኪሣራ የሚያመላክት እንዲሁም የሙስሊም ወንድሞቻችንን የድምፃችን ይሰማ ጥያቄ አቅጣጫ ፖለቲካዊ መልክ ለማስያዝ የተደረገ ከንቱ እና ያልተሳካ ሩጫ ነው።
  2. ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ቃልኪዳናችን ነው፥በመሆኑም በዘር፣በሃይማኖትና በብሔር ሳንከፋፈል በህዝባችን ላይ በኃይል የተጫነውን ሥርዓት ለማስወገድ ብሎም ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መምጣት በሚደረገው ትግል ያለመታከት በሙሉ አቅማችን እንሳተፋለን።ለለውጥ ያለንን ቁርጠኝነትም በተግባር ለማሳየት ቃል እንገባለን።
  3. በወያኔ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ያሉ የነፃነት ታጋዮችን፣የኅሊና እስረኞችንና የፖለቲካ አመራሮችን ሁልጊዜም የምንዘክራቸው ሲሆን ከምናደርገው የፖለቲካ ትግል ጎን ለጎን በነዚህ ጀግኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ሰቆቃ ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ በሰላማዊ ሰልፎች፣በዲፕሎማሲ ጥረት እና በግልጽ ደብዳቤዎች የምናጋልጥ ይሆናል።ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

No comments: