Monday, February 25, 2013

መንግስት ሕገ መንግስቱን ንዶ እየጨረሰው ነው!
ድምፃችን ይሰማ
‹‹የያዛቸው የፖሊስ መኮንን ወይም የሕግ አስከባሪ በጊዜው ገደብ ፍርድ ቤት በማቅረብ የተያዙበትን ምክንያት ካላስረዳ፣ ፍርድ ቤቱ የአካል ነጻነታቸውን እንዲያስከብርላቸው የመጠየቅ ሊጣስ የማይችል መብት አላቸው፡፡››
ሕገ መንግስት አንቀጽ አንቀጽ 19መንግስት ሕገ መንግስቱን ንዶ እየጨረሰው ነው!
ለ200 ቀናት ያለ ክስ የታሰሩ ሙስሊሞች በኢትዮጵያ ምድር
የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብት ያስከብራል ብለን ተስፋ የጣልንበት ሕገ መንግስት በመንግስት አስፈጻሚዎች እየተጣሰ መብታችንም ፈጽሞ በማይነጻጸር መልኩ እየተመዘበረ ነው፡፡ የእምነት ነጻነታችን፣ የአምልኮ መብታችን፣ ሃይማኖታችንን በነጻናት የመተግበር ተፈጥሮአዊ መብታችን፣ የእምነት ተቋማትን የማቋቋም መብታችን፣ የሃይማት መሪዎችን በነጻነት የመምረጥ መብታችንና መሰል መብቶች ሕገ መንግስታዊ እውቅና የተሰጣቸው ነገር ግን በመንግስት ባለፉት አመታት እንደዘበት እየተወረሱብን የሄዱ መብቶቻችን ናቸው፡፡ ለእነዚህ ሕገ መንግስታዊ መርሆች መከበር ሁለመናችንን አሳልፈን ሰጥተን ሰላማዊ ትግል እያደረግን ነው፡፡
ሆኖም የመንግስት የህገ መንግስት እና የመብት ጥሰት ድንበር የለሽ እየሆነ መጥቷል፡፡ መንግስት ሕገ መንግስቱን አስጠብቃለሁ በሚል የለበጣ ምክንያት ሕገ መንግስቱን እየናደው ነው፡፡ የዜግነት ሕገ መንግስታዊ መብቶቻችን ሁሉ ውሃ እየበላቸው ነው፡፡ ከቀናት በፊት ገልጸነው እንደነበረው መንግስት የህግ ጥሰቱን ለመደበቅ እንኳ የማይጨነቅበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በአገሪቱ በሁሉም አቅጣጫዎች የመብት ጥሰቱ ያለ መስፈሪያ.. ያለ ከልካይ እየተሳለጠ ነው፡፡ ሕገ መንግስቱን ማስጠበቅ የሚገባቸው አካላት ዝምታን መርጠዋል፤ እንዲያውም በሌላ አቅጣጫ የመብት ጥሰቱ አቢይ ተዋናይ እየሆኑ ነው፡፡
ፍ/ቤቶችን ተመልከቷቸው – ሕግ ከማስከበር ይልክ ከጸጥታ አስከባሪዎች ጋር በመተባበር የዜጎችን መብት እየጣሱ ነው፡፡ ሕገ መንግስቱ በአንቀጽ 19 የተያዙ ሰዎች መብት በሚል ርእስ በሁለቱ የመጀመሪያ አንቀጾች የታሰሩ ሰዎች ያላቸውን መብቶች ይጠቅሳል፡፡ ‹‹የተያዙ ሰዎች በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አላቸው፡፡ ይህም ጊዜ ሰዎቹ ከተያዙበት ቦታ ወደ ፍርድ ቤት ለመምጣት አግባብ ባለው ግምት የሚጠይቀውን ጊዜ አይጨምርም፡፡ ወዲያውኑ ፍርድ ቤት እንደቀረቡ በተጠረጠሩበት ወንጀል ለመታሰር የሚያበቃ ምክንያት ያለ መሆኑ ተለይቶ አንዲገለጽላቸው መብት አላቸው፡፡›› እንዲሁም ሌላኛው ንኡስ አንቀጽ ‹‹የያዛቸው የፖሊስ መኮንን ወይም የሕግ አስከባሪ በጊዜው ገደብ ፍርድ ቤት በማቅረብ የተያዙበትን ምክንያት ካላስረዳ፣ ፍርድ ቤቱ የአካል ነጻነታቸውን እንዲያስከብርላቸው የመጠየቅ ሊጣስ የማይችል መብት አላቸው፡፡›› ይላል ሕገ መንግስቱ፡፡ መሬት ላይ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡
ዛሬ ግን በኢትዮጵያ ምድር ከ190 በላይ ቀናት ያለ ክስ በእስር ላይ የሚገኙና የሚንገላቱ ዜጎች አሉ፡፡ በተለይም በአማራ ክልል ጥቂት በማይባሉ ከተሞች ኢማሞች፣ የሃይማኖት አዋቂዎች፣ አረጋውያንና ወጣቶች ያለ ክስ ከ6 ወራት በላይ በእስር ላይገኛሉ፡፡ ከሕገ መንግስቱ ይጋጫል የተባለው የጸረ ሽብር ሕጉ አንኳ በ4 ወራት ውስጥ ክስ እንዲመሰረት ያዛል – ያ ካልሆነ ታሳሪዎቹ እንዲለቀቁ ያዛል፡፡ ነሀሴ አራት በደሴ ፖሊስ ባስነሳው ግርግር የተያዙት ሸኽ ሀሰን ሀሚዲን፣ ሸኽ ጀማል እና ኡስታዝ ባህረዲን 195 ቀናት ያለምንም ክስ በወህኒ ይገኛሉ፡፡ በሰሜን ወሎ መርሳ ከተማ ያለው ደግሞ ከዚህ እጅግ የከፋ ነው፡፡ ከረመዳን ወር ጀምሮ ማለትም ከባለፈው ሐምሌ ወር 2004 ጀምሮ ያለ ክስ በእስር ላይ የሚገኙ በርካታ ሙስሊሞች አሉ፡፡ የመርሳው ታሳሪዎች ከ200 በላይ ቀናት በእስር ቤት ያለ ምንም ክስ ታጉረዋል፡፡ በወልዲያ፣ በኮምቦልቻ፣ በከሚሴ እና በሌሎችም አቅራቢያ ከተሞች በርካታ ሙስሊሞች ያለ ክስ ያለ ፍርድ በወህኒ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ዜጎች ዳኞች በነጻ ሊያሰናብቷቸው ቢገባም ይህ አልሆነም፡፡ እነዚህ ዜጎች የተከሰሱበት የተጠረጠሩበት ወንጀል አልተነገራቸውም – ፖሊስ ይህን እንዲያደርግ ሕጉ ቢያስገድደውም አላደረገውም፡፡ ሌላዉ ቢቀር መንግስት በራሱ ፍ/ቤቶች እንኳ አስቀርቦ ሊያቀርብባቸው የሚችለው ክስ የለውም፡፡ ንጹሀን ዜጎች ሙስሊም በመሆናቸው ብቻ፣ በሃይማኖታቸው ምክንያት ብቻ በእስር እና ስቃይ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ይህ ሁለ ሲደረግ የፍትህ አካላት፣ ለሕገ መንግስቱ ዘብ ነን የሚሉ ዜጎች እና ተቋማት፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ስለ ሕግ የበላይነት የሚጨነቁ ዜጎች የት ናቸው? ሕገ መንግስቱ ጠባቂ እና አስከባሪ አጣ እኮ፡፡ ዜጎች ሕገ መንግስታዊ መብታቸው ተደፈጠጠ እኮ፡፡ ሕገ መንግስታዊ ዋስትናችን ተገሰሰ እኮ!
መንግስት ሕገ መንግስቱን ንዶ እየጨረሰው ነው! ክፍል ሁለት ይቀጥላል…
አላሁ አክበር!

No comments: