Thursday, November 2, 2017

የህውሃት የዘረኝነት ፓለቲካና መዘዙ ( ገዛኸኝ አበበ )

 November 2,2017


ወያኔ (ኢህአዲግ)የስልጣን እድሜውን ለማራዘም ትልቁ የፖለቲካ አጀንዳ አድርጎ የተነሳው ሕዝብን ከሕዝብ ጎሳን ከጎሳ ሀይማኖትን ከሀይማኖት የፖለቲካ ድርጅትን ከፖለቲካ ድርጅት  በማጋጨትና በማጣላት ላይ ሲሆን ህሕዋት እያራመደ ባለው የዘርና የጎሳ ፖለቲካ የተነሳ በኢትዮጵያ ታሪክ ከመቸውም ጊዜ በላቀ እና ታይቶ በመይታወቅ ሁኔታ የወያኔ መንግስት አሁን የኢትዮጵያን ህዝብ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልልና አካባቢ  ሕዝቡ ኢትዮጵያዊነቱን እንዳያይ በዘር እየከፋፈለው ነው:: የህውሃ/ኢህአዴግ ገና ወደ ስልጣን ብቅ ሲል በጦርነት ከደርግ የሚረከባቸውን ቦታዎች ፣ዳገትና ቀበሌዎች ሁሉ በቤተሰብ ሳይቀር እየከፋፈለ በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች እያሰረ ልዩነታቸውን ብቻ እያሳየ ሌላ አማራጭ ያልነበረው ህዝብ ሲቀበለው ቆይቶ አሁን በክልል በዞን በወረዳ በቀበሌ እና ሰፈር ድረስ በዘርና በጎሳ ከፋፍሎ ይህ ወያኔ ከደደቤት በረሃ ይዞት የመጣው የዘረኝነት ፖለቲካ መዘዝ  ዘሬም በኢትዮጵያ ውስጥ ተንሰራፍቶ  በየሰፈሩ አሁን የእንትን ሰፈር ልጅ ከእንትን ሰፈር ልጅ ጋር በጩቤ በድንጋይ ሲፈነካከት ሲተራረድ ማየት ምንም አዲስ ነገር አይደለም፡፡

የአንዱን ወረዳ ነዋሪ ከሌላኛው ወረዳ ነዋሪ ጋር በሆነ ባልሆነው ሲኮራረፍ ሲገዳደል ሲቀጣቀጥ ማየት ምንም አዲስ አደለም፡፡ አንዱ ዞን ከሌላኛው ዞን ጋር በስራቸው በሚያስተዳድሩት ህዝብ ስም ጥቅም እየነገዱ አንዱን ከአንዱ አባትን ከልጁ እናትን ከልጇ ወንድምን ከወንድሙ ምን አለፋችሁ በቃ በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ ውስጥ እንደምታዩት ጠላቶች ሆነን ስንጨራራስ ስንተራረድ እንገኛለን፡፡ሰው ከሰው ጋር ለምን ይጋጫል ለምን ይገዳደላል የሚለው እውነተ ውስጥ አልገባሁም እርሱ ራሱን የቻለ ተፈጥሯዊ ክስተት ስለሆነ፡፡በዛም አለ በዚህ የመከፋፈላችን የመጨረሻ ውጤትና ምክንያት ፍጅት ነው፡፡ ሆኖም ፍጅት ሲባል ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ሊነሳ የሚችለው ፍጅት እንደሁቱና ቱትሲ ይሆናል ብላችሁ ግን አታስቡት፡፡ መቸም ቢሆን ይህ ጉዳይ ሊከሰት አይችልም፡፡ በብሄር ግጭት ተነስቶ ኢትዮጵያ ሃገራችን ትጠፋለች አንድ ዘር ይጠፋል ማለት አይቻልም፡፡ ለዚህ ራሱን የቻሉ እውነተኛ ምክንያቶች አሉ፡፡ ሌላው ዓለም ላይ የሌሉ ሃገራችን ውስጥ ግን እንደ ዕድል ብቻ ሆኖ ያሉ ነገሮች ሕዝባችን ሳይማር ተፈጥሮ ብቻ አስተምራ ያኖረችው ትውልድና ትስስር በመሆኑ ብቻ አብረውን የሚኖሩ እውነቶች አሉ፡፡

ወያኔ ኢህአዴግ ግን ከዞን እና ቀበሌ ባለፈ የመጨረሻ ሴራውን በክልል በቋንቋ፣ ዘር ፣ቀለም ወዘተ እያለ በባህል፣ በእምነት እያለ የሚታዩና የማይታንን ልዩነቶች እየፈጠረ በመካከላችን ምንም አይነት ችግርና  ሳይኖር በፍቅር የኖረን ሆነን ሳለን ህህዋት ከጅምሩ ይዞ የተነሳውን  በቋንቋና በዘር ልዩነት ላይ የተመሰረተው የፌደራል ሥርአትና ኢትዮጵያን የመሰነጣጠቅ ሴራው  አሁን ላይ ስር እየሰደደ መጥቶ በኦህዴድ፣ ብአዴንና ደህዴድን የመሳሰሉ የመሳሰሉ የወያኔ አለቅላቂዎችና  አሽከሩች ተጨምረውበት በእነዚህ የኢትዮያን ሕዝብ ደም መጣጭ ድርጅቶች በኩል እየተገበረ ያለውን ኢትዮጵያን የመሰነጣጠቅ እና ለአስተዳደር ለማመቻቸት በመሰለ ሴራና ተንኮል ህዝባችን አንድነቱ ፍርሶ አሞቱ ፈሶ ኢትዮጵያዊው ወኔ እንዲደርቅ በማድረግ ለራሳቸውየሚጠቅማቸውን ለህዝባችን እና ሃገራችን ግን ትልቅ የአንድነት ነቀርሳን ተክለውብን ምኞታቸውን እያሳኩ ይገኛሉ፡:

ይህ የወያኔ የዘረኝነት ፖለቲካ መዘዝ ስር እየሰደደ በጣም በአሳሳቢ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ አስከፊና አሳዛኝ የሆኑ የተለያዩ ችግሮች እየወለደ፤ ጸብና ግጭቶችን እያበራከተ የዜጎችን ሕይወት በቀላሉ እየቀጠፈና የሕዝቦችን ሀብት በማውደም፣ቤቶችን በማቃጠል መጥፎ ክስተት  እየተከሰተ ይገኛል። ከዚህ በፊት እንደምናስታውሰው  በምሥራቅ ኢትዮጵያ ደገሃቡርና ጅጅጋ፤ በምሥራቅ ሀረርጌ ጋራሙለታ፤ በደኖ አንስቶ በባሌና በአርሲ በሚገኙ አካባቢዎች በዘር ላይ የተመሰረቱ ግጭቶችና የሰው ሕይወትና ንብረት የወደሙበት በምሳሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው። በምዕራብ ኢትዮጵያም ቢሆን በተለያዩ ወቅቶች በአሶሳ በባምባሲ፤ በሰሪ፤ በጋምቤላ በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ፤ ነቀምት፤ አምቦም ለዚሁ አስከፊ ሁናቴ የሚጠቀሱ ናቸው። በአርሲ ክፍለ ሀገር በአርባጉጉ አውራጃ ውስጥ በሚገኙ ጎሎልቻ፤ ጨሌ፤ ጃጁ፡ መርቂ በተሰኙ ወረዳዎችና አካባቢዎች በርካታ መኖሪያ ቤቶች የወደሙበት፤ ሕይወት የጠፋበት፤ የሰው ልጅ እንድ ከብት አንገትና ጡቶች የተቆረጡበት አሰቃቂና አሳዛኝ በድሎች ተካሂደዋል። በሌላ ቦታ ደግሞ ከነ ነፍሰሕይወታቸው ወደገደል ተውርውረው እንዲፈጠፈጡ የተደረጉም እንዳሉ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ሲሆን ከሰሞኑ ደግሞ እንዳየነው ለሳምንታት በዘለቀው በኦሮሚያ እና በሱማሌ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት እንዲሁም በኢሊባቡር በአማራና በኦሮሞ ዜጎቻችን መካከል በተከሰተው ግጭት ለብዙ ሰዎችን መፈናቀልና ህይወት መጥፍት ምክንያት መሆኑ ይታወሳል በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ያለው  የእርስ በእርስ ግጭት ሆነ ተብሎ በህውሃት የበላይነት የሚመራው መንግስት በስልጣን ለመቆየት የሚጠቀምባቸው ስልቶች እንደሆኑ ሁላችንም ጠንቅቀን ልናውቅ ይገባል

በምንም መንገድ ከታሪካዊ አመጣጡም ቢሆን እንደተረዳነው ወያኔ ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ አንድነት ሳይሆን የታገለው አሁንም የሚሮጠው ለእነዚህ አላማዎች ብቻ ነው፡፡ አንድም ታላቋ ትግራይን መመስረትና የአማራውን  ተሰሚነት አኮላሽቶ መቅበር ነው፡፡ለዚህም አማራውን ዝም ካልነው አያስቀምጠንምየሚለው የመለስ መፈክር በቂ ምስክር ሲሆን ይህንን የሚያረጋግጡም በርካታ የምስልና የድምፅ ቅጅዎች በተለያዩ ነፃነት ናፋቂ የየትኛውም ብሄር ታጋዮች እጅ ይገኛል፡ከዚህ በፊት ኢትዮጵያን ሲመሩ የነበሩት መሪዎች ሁሉ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በማስከበረ ሕዝቡም አንድነቱን ጠብቆ እንዲኖር ብዙ መስዋትነትን  ከፍለዋል በወያኔ መንግስት እንደ አውሪ የሚቆጠረው ደርግ ሳይቀር ለኢትዮጵያ አንድነት ምሳሌ ናቸው ::ደርግ በርካታ አንቱ የሚያስብሉት ትግባራትን ፈፅሟል፡፡ በኋላም ለውድቀት የዳረገው በትክክል ደርግን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠልቶት ሳይሆን በመካከላቸው በነበረው ተራ የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት በነበራቸው የሃሳብ  መለያየት፣ ውስጣዊ ሴራ እና አማራጭ በማጣት አንድን የደርግ ወታደር በሁለት ብር ሂሳብ ለወያኔ በሰጡ ባስጨረሱ ጀኔራሎች ሴራ እንጅ በወያኔ ጥንካሬ እንዳልሆነ እውን ነው፡፡

የሚገርመው ግን የኢትዮጵያን አንድነት ለማጥፋት አላማ ይዞ የመጣው ወያኔ ስልጣን እንደያዘ የጀመረው የደርግን ጅማሮዎችን በሙሉ ከምድረ ኢትዮጵያ ማጥፋት እና ማቃጠል አንድነቷና ዳር ድንበሯ ተከብሮ የቆየውን ሀገሪቷን መሸጥና መቆራራጥ ሀገሪቷን ወደብ አልባ በማድረግ ለታሪክ መጥፎ የሆነ ጠባሳ ማስቀመጥ ነበር ይህንንም  ከሻቢያ ጋር በመሰማማት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ አድርጎታል:: ወያኔ ኢህአዴግ አሁን የያዘው ስትራቴጅ ደግሞ የማያዋጣው ማጥ ውስጥ ስለከተተው የሚከተለው እንደ ትግሉ በግልፅ ራሱን በመገንጠል አላማ ማለትም የመሄድ ዓላማ ሳይሆን ተቃራኒውን ነው፡፡ ይህም ማለት አሁን በምኑም በምኑም ምንያት የከፋፈለውን ህዝብ የበለጠ በመከፋፈልና የመለያያ ታሪኮችን እንደመልካም አስተማሪ ታሪክ በመምዘዝ እና አደባባይ በማውጣት /ሆኑ አልሆኑ የሚለው ባይታወቅም ምንጭ ባይኖረውም/ አንዱን ከአንዱ በማፋጀት እራሱ መሄዱን ሳይጀምር ሌሎች በየአቅጣጫው እንዲሄዱ በማድረግ የተዳከመች ኢትዮጵያ የተፈረካከሰች ኢትዮጵያ ስትቀርበሉ እኔም የድርሻየን እናንተ ከሄዳችሁማብሎ ለመነሳት ነው ያሰበው፡፡ አንድ ልናውቀው የሚገባ  እውነት  ይህች ሃገር በፍጹም ልትበታተንና ልትጠፋ አትችልም:: ይህንም ውሃቶችና የወያኔ ተላላኪ፣ተለጣፊዎቹ ኦህዴድ፣ ብአዴንና ደህዴድ ያወቁት አይመስለኝም  ፡፡ ይህ ህዝብ አንድ ሆኗል በወያኔ ተንኳልና ሴራ አሁን ላይ በተለያዩ ነገሮች ቢጋጭም የተጋባ፣ የተዋለደ፣አብሮ የበላና ፣የጠጣ አብሮ ለኢትዮጵያ አንድነት ሲል የታዋጋ የደማና የቆሰለ ሕዝብ ነው :: ይህ እውነታና ሚስጥር ያልገባቸው አንዳንድ የወያኔ ኢህአዴግ ሴራ ማስፈጸሚያና መጠቀሚያ መሆናቸውን ያላወቁ በስሜት የሚነዱ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ናቸው፡፡ስለሆነም የኦሮሞው፣የአማራው፣የአፋሩ፣የትግራዩ፣የጋምቢላው ........ሕዝብ የወያኔ የዘር ፖለቲካ ማስፈጸሚያ እንዳይሆን ሊጠነቀቅ ይገባል እያልኩኝ እዚህ ላይ ላጠቃልል:: ውድቀት ለዘረኛው የወያኔ አገዛዝ !!

የኢትዮጵያ አንድነት ለዘላለም ተጠብቆ ይኖራል!!

gezapower@gmail.com

Monday, October 16, 2017

አቶ በረከት ስምኦን ሃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው ለመልቀቅ ጥያቄ አቀረቡ።


October 16,2017

በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ምርምር ማዕከል የኢንዱስትሪ ዘርፍ መሪ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን ሃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው ለመልቀቅ ጥያቄ አቀረቡ።
ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት አቶ በረከት የሥራ መልቀቂያ ጥያቄያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ አስገብተዋል።
አቶ በረከት ስምኦን ለበርካታ ዓመታት በቦርድ ሰብሳቢነት ሲመሩት ከነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ሊለቁ እንደሆነ ባለፈው ሳምንት ተነግሯል።
አቶ በረከት ባለፈው ሳምንት የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስገባታቸው የተነገረ ሲሆን፤ ለመጨረሻ ጊዜ በቢሮአቸው ተገኝተው የነበሩት ሀሙስ ዕለት ነበር።
አቶ በረከት በተመሳሳይ ጊዜ ከሁለት የሃላፊነት ቦታቸው የተነሱ ሲሆን ለሥራ መልቀቃቸው ግልፅ ያለ ምክንያት አልቀረበም።
ነገር ግን በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ምርምር ማዕከል ውስጥ በነበራቸው ቆይታ ብዙም ደስታኛ እንዳልነበሩ በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገራሉ።
በተለይ ማዕከሉ በተለያዩ ጊዜያት የሚያቀርባቸው ሃገር አቀፍ የፖሊሲና የአስተዳደር ጥናቶች በጠቅላይ ሚኒስትሩና በመንግሥት ከፍተኛ ሃላፊዎች ዘንድ ብዙም ተቀባይነት አግኝተው ተግባራዊ አለመደረጋቸው ለቅሬታቸው ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።
ቢሆንም ግን በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ምርምር ማዕከል ያላቸውን ሃላፊነት ለመልቀቅ ሌላ ተጨማሪ ምክንያት እንዳላቸው ማረጋገጥ አልተቻለም።
የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ምርምር ማዕከል በአቶ አባይ ፀሐዬ ዋና ዳይሬክተርነት የሚመራ ተቋም ነው።
አቶ በረከት ስምኦን ከቀደምት የኢህአዴግ አመራሮች መካከል የሚመደቡ ሲሆን የገዢው ፓርቲ አንድ አካል የሆነው የብአዴን አመራር አባል ናቸው።
አቶ በረከት ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ሃላፊነቶች ላይ የቆዩ ሲሆን፤ የማስታወቂያ ሚኒስትርና የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል

Friday, August 4, 2017

(ሰበር ዜና ፓርላማ) ያለመከሰስ መብታቸው በፓርላማ የተነሳው የገንዘብ እና የኢኮኖሚ ትብብር ሚንስትር ዴኤታ በፖሊስ ቁጥጥር ዋሉ

Augest 4,2017
በሙስና ወንጀል ጠረጠርናቸው የሚሉአቸውን ባለስልጣናት እና ነጋዴ ማህበረሰብን ማደን ከተያዘ ሦስተኛ ሳምንቱን መያዙ የተገለፀ ነው ። በአሁን ሰአት የህወሀት መንግስት ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ነው በተባለበት በዚህ ጊዜ ፣በስሩ የነበሩትን የከፈተኛ ባለሥልጣን አመራሮችን ከቦታቸው አንስቶአል ፣ የድርጅቱ ሚስጥር ጠባቂ ተብለው በሙስና ውስጥ የተዘፈቁትን በአምባሳደርነት ሹመት ወደ ተለያዩ ቦታዎች አሸጋሽጎአቸዋል።
ሆኖም ግን በመንግስት እና በውጭ አገራት የተመሰረቱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን የሙስና መንሰራፋት መንግስት በይፋ እያወቀ  በሌሎች ትንንሽ ገዳዮ ላይ ትኩረቱን መጣሉ የሃገሪቱን ደህነንት የማይፈልግ መንግስት መሆኑን ያሳያል ሲሉ አንድ የመንግስቱ ባለስልጣን ለማለዳ ታይምስ የፃፉት ደብዳቤ ይገልጣል ።
በተለይም ይላሉ እኝሁ ባለስልጣን በዩኤስ አይድ እና በህወሃት መንግስት ባለስልጣን የተካሄደው ስምምነት የሀገሪቱን ውስጣዊ ደህንነት አሳልፎ የሚሰጥ በመሆኑ የተነሳ የሀገርና የአካባቢ ጥበቃ ተብሎ የተመደበውን ገንዘብ ቢመለስም ሆነ ይህነኑ ጉዳይ ለማስፈፀም ተብሎ ከውጭ ጉዳይ መስሪያቤት ዋና ሚንስትር ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ምንስትር መስሪያ ቤቱ ድርስ የዩኤስ ኤይድ ድርጅት ለስራ ማስሌጃቸው ይሆን ዘንድ ለሚንስትሮቹ በግላቸው  የሰጠውን ገንዝብ እንዲመረምር እና ሚንስትሮችም ከፍተኛውን ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉ ጠቁመዋል ።
ሀገሪቱን የውስጥ ችግሮቿን እያዩ ችግር ፈጣሪ አካላትን በበጎ አድራጎት በኩል መፍቀድ አሳፋሪ ቢሆንም ፣በአሁን ሰአት ሀገሪቱን ለማፍረስ እና የእር በእርስ ግጭት ለመቀስቀስ ቀላል እንደሆነ በደንብ አጥንተውበት ስር የሰደደ ሂደት ውስጥ መሆናቸውን እና በየክልሉ የአካባቢ ጥበቃ ተብሎ የተመሰረተው ይህንን አሜሪካ ድርጅት ጥናት በአስቸኳይ መንግስት ስራውን ማስቆም አለበት አለበለዚያ ግን ህዝቡን ለማጫረስ በዝግጅት ላይ መሆኑን ያመላክታል በማለት ስጋታቸውን ገልፀዋል።
ይሄው የአሜሪካ ድርጅት የኢትዮጵያ ችግሮች የቱ ጋር እንደሆነ የትኛው ቦታ ላይ የብሄሮች ግጭት እንዳለ ፣መንግስት ከየትኛው ማህበረሰብ ጋር አየተፋለመ እንዳለ ጠንቅቆ በጥናቱ ላይ ያወቀው ሲሆን ካለበት መንበረ ስልጣን ለማውረድም ይሁን ህዝቡን እርስ በእር ለማጫረስ ከፍተኛ የሆነ አማራጭ ያለው ስልት መሆኑን አውቆታል።
በመቀጠል ለዚህም ላካሄዱበት እያካሄዱበት ላለውም ጥናት ከሚንስትር መስሪያቤቶችም ሆነ ጠቅላይ ሚንስትሩ መስሪያቤት እስከ ታች ድረስ በሙስና ተጨማልቀው ሀገሪቱን ለውጭ ድርጅት ወስጣዊ ደህንነቷን አሳልፈው ሰጥተዋል ሲሉ ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
ፖሊስ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ዛይድ ወልደገብርኤልንና ያለመከሰስ መብታቸው በዛሬው እለት በፓርላማ የተነሳው የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አለማየሁ ጎጆን በዛሬው እለት በቁጥጥር ስር አዋለ።
ዛይድ ወልደገብርኤል ከሁለት አመት በፊት ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርነት ተነስተው ዋና ጽህፈት ቤቱን ሞንትሪያል ካናዳ ባደረገው አለም አቀፍ የስቪል አቬሽን ድርጅት; የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወሳል።
ማለዳ ታይምስ

Thursday, August 3, 2017

የህወሓት “መከላከያ ሰራዊት” በበቃኝ ጥያቄ ተወጥሯል፤ ጄኔራሎች አሉበት!

July 3, 2017

ኢትዮጵያን እየገዛ ያለው ህወሓት የሚመካበትን የታጠቀ ሰራዊት የሚመሩ ከፍተኛ መኮንኖችና ጄኔራሎች በጡረታ ለመሰናበት ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰማ። የአስቸኳይ አዋጁ ሲነሳ መልስ እንደሚያገኙ ቃል የተገባላቸው እንዳሉም ታውቋል።
የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ለደህንነት ሲባል መረጃውን ያገኘበትን ሳይገለጽ እንደጠቆመው “መከላከያ ሰራዊት” የሚባለውን የህወሓት ሥልጣን አስጠባቂ የታጠቀ ኃይል ከሚመሩት ጄኔራሎች መካከል “በቃኝ” ያሉት ጄኔራሎች ከሰባት በላይ ሲሆኑ፣ በከፍተኛ መኮንን ደረጃ ያሉት ግን ቁጥራቸው በርከት ያለ ነው።
ጄኔራሎቹ ሰራዊቱን ለመሰናበት ያቀረቡትን ዋና ምክንያት የመረጃ ሰዎቹ ቃል በቃል ይፋ ባያደርጉም፣ ከሰራዊቱ ጋር ላለመቀጠል ዕድሜ፣ ጤና፣ ጋብቻና ተያያዥነት ያላቸው ጥያቄዎችን እንደ ምክንያት አቅርበዋል። መልቀቂያ ያስገቡት ብቻ ሳይሆኑ በርካቶች ተመሳሳይ ፍላጎት እንዳላቸውም ጠቁመዋል። የዚህም ምክንያቱ ሥርዓቱ አያያዙና አሁን የደረሰበት ደረጃ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ሰላም አስጊ በመሆኑ ነው።
በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ውስጥ ባለው የኃይል አሰላለፍ ስጋት ውስጥ የገቡና ችግሩ ሊወሳሰብ እንደሚችል በማሰብ አድፍጠው በመጠባበቅ ላይ ያሉ ከፍተኛ የሰራዊቱ አመራሮች ሲሰናበቱ አገር ውስጥ የመኖር ዕቅድ እንደሌላቸውና ለዚሁም አስቀድመው የጉዞ ዝግጅት ያደረጉ እንዳሉም ተጠቁሟል።
ጥያቄውን የተቀበለው ውሳኔ ሰጪ አካል ለጊዜው የሰጠው ቁርጥ ያለ መልስ የለም። በአስቸኳይ አዋጁ ምክንያት ሰራዊቱን የመልቀቅ ጥያቄ በመመሪያ በመታገዱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መነሳት ተከትሎ ውሳኔ ሰጪዎች ምን እንደሚመለሱ ሊታወቅ እንደሚችል የመረጃው ሰዎች ለጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ነገረዋል።
በሰራዊቱ ውስጥ በሚታየው መረን የወጣ አድልዎ የተማረሩና የተሰላቹ ከፍተኛና መካከለኛ የመስመር መኮንኖችን ጨምሮ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሰራዊቱ አባላት ስንብት እንደሚፈልጉ በመረጋገጡ በወታደራዊ ውሳኔ ሰጪዎችና ፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ስጋት ፈጥሯል
በዚህም የተነሳ የአገልግሎት ጊዜያቸውን ጠቅሰው ስንብት የጠየቁ በከፍተኛ ደረጃ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑ ታውቋል። “አገሪቱ አሁን ባለችበት ችግር ውስጥ፣ አስቸኳይ ጊዜ ላይ እያለን እንዴት ስንብት ለመጠየቅ አሰብህ” በሚል እንደሚገመገሙም ከመረጃው ሰዎች ለመረዳት ተችሏል።
በሰራዊቱ ውስጥ ያለውን የ“በቃኝ” ህገ መንግስታዊ ጥያቄ በአስቸኳይ አዋጁ ስም አንቀው የያዙት ወሳኔ ሰጪዎች፣ ሰራዊቱን ፍልሰት እንዳያርደው ፍርሃቻ ስለገባቸው ከወዲሁ የአዳዲስ ሃይል ምልመላ ሲያካሂዱ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል። ከዚህም በላይ በየክልሉ ያለውን የልዩ ሃይል ከአስችኳይ ጊዜ መነሳት በኋላም በአንድ ዕዝ ውስጥ የማስገባት ስራ እንደሚሰራ ታውቋል።
እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሰራዊቱ አባላት የመሰናበት ፍላጎታቸውን አፍኖ መዝለቅ ስለማይቻል “ከጥልቅ ተሃድሶ በኋላ” በየክልሉ አዳዲስ ታጣቂ የማስፈለፈሉ ስራ እየተሰራ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል። አሁን ባለው አሰራር ከመከላከያ መሰናበት የሚችለው በጋብቻ ወደ ውጪ አገር የሚሄድ ወይም ቀደም ሲል በማመልከት የትምህርት ዕድል ያገኘ ብቻ እንደሆነና ይህ መመሪያ መቼ እንደሚነሳ በግልጽ የተቀመጠ ነገር እንደሌለ የመረጃው ምንጮች ተናገረዋል።
የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን አገዛዝ ወደ ፍጻሜው ለማምጣት እንዲረዳ “በመፈንቅለ መንግሥት” ሙከራ ሳቢያ በርካታ ጄኔራሎች ከሠራዊቱ ተወግደው ነበር። ይህ የተቀነባበረ ድርጊት ለህወሓት ወደ አዲስ አበባ መግባት ዕንቅፋት ይሆናሉ ተብለው የታሰቡን በቀላሉ “ከመንገድ የጠረገ” እንደነበር የሚታወስ ነው። አገር ውስጥ ባሉ የውስጥ አርበኞችና በውጭ አገራት የለውጥ ፈላጊ ሆነው በቀረቡ “ከሃዲዎች” ቅንብር ሳይካሄድ የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት የሚጠርገውን ጠራርጎ ካለፈ በኋላ ኮ/ሎ መንግሥቱ ከሥልጣን የመወገዳቸው ጉዳይ “የቀናት” ብቻ እንደሆነ “ያበሰረ” እንደነበር ብዙዎች የሚያስታውሱት ነው።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሰበብ አድርጎ የታፈነው የህወሓት ጄኔራሎች “የበቃኝ” ጥያቄ አስቀድሞ ከሥልጣናቸው የተለዩትን፣ በተለያዩ የሃብት መሰብሰብ ተግባራት የተሰማሩትንና ወደፊታቸውን የሰበሰቡትን ሃብት እየበሉ ለመኖር ባሰቡት ዘንድ እንዲሁም በሥልጣን ለመቆየት በሚያስቡት ጭምር የተደበላለቀ ስሜትን ፈጥሯል። ሆኖም የጄኔራሎቹ “የበቃኝ” ጥያቄ መነሻ ምክንያት ከላይ የተጠቀሱት ብቻ ይሁኑ ወይም ሌሎች ያልተጠቀሱ መነሾዎች ይኑራቸው ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም። (ፎቶው “የበቃኝ” ጥያቄ ካቀረቡት ጋር ግንኙንት የለውም)
ከጎልጉል ድህረ ገጽ የተወሰደ

Thursday, July 27, 2017

በሙስና ከታሰሩ ባለስልጣናት መካከል የተወሰኑት ስም ዝርዝር ታወቀ | ይዘነዋል

July 27,2017

በአዲስ አበባ ታትሞ የሚወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ እንደዘገበውና ዜና አቅራቢው ፋኑኤል ክንፉ እንዳጠናቀረው  በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 34 ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ባለሀብቶችና ደላሎች፤ በትላንትናው ዕለት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢፌዴሪ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አስታወቀ::
የጽ/ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ትላንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ 34 የሚሆኑ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ባለሀብቶችና ደላሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ኃላፊዎቹ ተጠርጥረው የተያዙት “በፖሊስ፣ ዐቃቤ ህግና በፌደራልና አዲስ አበባ ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች በተደረገ የማጣራት ስራ የሙስና ተግባር ውስጥ ተሳትፈው በመገኘታቸው መንግስት ሙስናን ለመከላከል በያዘው ቁርጠኛ አቋም ነው፤” ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል::
በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ  ኃላፊዎች ከተገኙባቸው የመንግስት  ተቋማት መካከል፤ የፌደራል መንገዶች ባለስልጣን፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ ስኳር ኮርፖሬሽን እና የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መስሪያቤቶች ጋር ይገኙበታል፡፡
የሰንደቅ ምንጮች እንደገለጽት፣ በስኳር ኮርፖሬሽ በኩል ተጠርጥረው ከተያዙ መካከል  የቀድሞው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ አበበ ተስፋዬ እና የቀድሞው የተንዳሆ የፋይናንስ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ድምፁ እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡ እንዲሁም፣ አቶ በኃይሉ ገበየሁ የኮርፖሬሽኑ ንብረት አስተዳደር ዳሬክተር እና አቶ ኤፍሬም አለማየሁ የቀድሞ የኮርፖሬሽኑ፣ ግዢና ንብረት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዳሬክተር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ግዢ ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ግርማ፤ እንዲሁም ወ/ሮ ሠናይት ወርቁ እና አቶ ኃየሎም ከበደ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ማዋላቸው ታውቋል፡፡
አንድ የቀድሞ ሚኒስትር እና አንድ ሚኒስትር ዴኤታም ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ምንጮቻች የጠቆሙን ቢሆንም፣ ከሚመለከታቸው አካላት ለማረጋገጥ አልቻልንም፡

Sunday, July 23, 2017

የግብሩ አመጽ – የፍጻሜው ጦርነት

July 23,2017
ክንፉ አሰፋ
የአስቸኳይ (የአፈና) ግዜ  አዋጁ ገና አልተነሳም። በአዲሱ የግብር ትመና ሳብያ ከዳር እስከዳር የተነሳው ሕዝባዊ አድማ እና አመጽ ግን አዋጁን ውድቅ ያደረገው ይመስላል። አንድ ስርዓት ራሱ ያወጣው ህግ በህዝብ ሲሻርበት - ያኔ ነው ያበቃለት!
        ከቶውን "የአለምን  ኢኮኖሚ እየመራች ያለች ሃገር" የበጀት ሸክሟን ለምን በህዝብ ላይ መጣል እንዳለባት ግልጽ አልሆነም። እውነታው ከነዚህ ሁለት እይታዎች ውጭ አይሆንም።  ይነፋ የነበረው የእድገት ቀረርቶ እና ይነገር የነበር ሁለት ዲጅት እድገት ቁጥር ሁሉ ውሸት ነበር፣  ወይንም ደግሞ የሃገሪቱ ሃብት በጥቂቶች እየተዘረፈ ነው።
        ጆሮን ያሰለቸው የ"እድገት እና ትራንስፎርሜሽኑ" ዘፈን ቀዝቀዝ ማለት ሲጀምር የ "ደብል ድጅቱ" የፈጠራ ተረት እንደ በረዶ እየነጻ መሄዱ አልቀረም። እድገቱ የህዝቡን  ህይወት አልለወጠም። ተጀምሮ ከሚቋረጥ ህንጻ እና መንገድ ውጭ ትራንስፎርሜሽኑም በተግባር አልታየም።  ይልቁንም ተሸፍኖ የነበረው ችግር አሁን ፈጥጦ ወጥቶ በህዝብ ጫንቃ ላይ ጉብ ሊል ዳዳው፣ ገበሬውን መሬት በመንጠቅ፣ ነጋዴው ላይ ደግሞ ሚዛናዊ ባልሆነ የገቢ ግምት - ከፍተኛ ግብር በመጫን።   ምላሹንም እንደምናየው ነው።  አድማ፡ ህዝባዊ አመጽ፣... ተቃውሞ!
        በዘንድሮው የበጀት አመት የህወሃት መንግስት 320 ቢሊዮን ብር ማጽደቁን አብስሮን ነበር።  ይህ በጀት የ100 ቢሊዮን ብር  (1/3ኛ) የበጀት ጉድልት ነበረበት። ይህ የ100 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ከብድር እና እርዳታ ይሸፈናል ተብሎ  ነበር የተጠበቀው። የ11 በመቶው እድገት ተረት - ተረት  ውስጥ የእርዳታው እና የብድሩ መጠን ተገልጾ አያውቅም። ሃገሪቱ በደፈናው እያደገች ነው አሉን። በፈጣን እድገት የአለምን ኢኮኖሚ የምትመራ ሃገር ተባለ።  ፈረንጆቹም አመኑ።
        እርዳታን  እንደ ስትራቴጂ የቀመሩት የህወሃት ጠበብቶች፣ ፈረንጆች ፊታቸውን ማዞር እንደማይሳናቸው እንኳን አላሰቡትም። በሶማሊያ ውስጥ የነሱን ቆሻሻ ጦርነት ስለተረከቡ ብቻ ጉዳዩን እንደ ይገባኛል መብት (for granted) አዩት። የሶማልያ ጉዳይ፣ የአልሻባብ ፖለቲካ ዲስኩር፣ የጸረ-ሽብር እንቶፈንቶ አሁን የለም። አሜሪካም ሆነች የአውሮፓ ህብረት ዜጎችን በአዋጅ እና በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አፍኖ የያዘው ስርዓት ጋር በረጅሙ እንደማይዘልቁ ግልጽ ነው። ታዲያ ከቻይናው የእድሜ-ልክ የእዳ ቁልል ውጭ የታሰበው የውጭ ገቢ ጠፋ። ማጠፍያው አጠረ። ለሰራዊቱና ለደህንነቱም ደሞዝ መከፈል አለበት።  ...ቀሪው ገንዘብ ከግብር እና ከሃገር ውስጥ የሚሰበሰብ ገንዘብ ብቻ ነው።
        እናም እዳው ሕዝብ  ላይ ተቆለለ። የቀን ገቢ በግምት እየታየ ተጫነ። በገቢና ወጪ ሳይሆን፣  በህዝብ ላይ በግምት ግብር ሲጫን በታሪክ የመጀመርያው ሳይሆን አይቀርም። አዲሱ የግብር ትመና በንግዱ ህብረተሰብድ ከባድ ቁጣ ቀስቅሷል። ከጫፍ እስከጫፍ የተነሳው የሥራ ማቆም አድማ የት ላይ እንደሚቆም አይታወቅም። በአስቸኳይ ግዜ በምትተዳደር ሃገር የተነሳው ይህ አድማ ቀድሞ የተጀመረው የመብት እና የነጻነት ትግል ቅጣይ ይመስላል። ቀድሞ የተነሳው የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።  የህወሃት የአፈና ሰንሰለትም እንደቀጠለ ነው። ዛሬ ነጋዴው ህብረተሰብ የሰለባው ባለሳምንት ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሰረታዊ ችግር ኢ-ፍትሃዊ የሆነ የግብር ፖሊሲ አይደለም። ችግሩ ስርዓቱ ራሱ ነው። ዛሬ የንግድ ቤቶች ቢዘጉ ሌላ የንግድ ቤቶችን የመክፈት አቅም ያላቸው የህወሃት ሰዎች በደስታ መፈንጠዛቸው አይቀርም። ...አሜካላው ሳይነሳ መፍትሄ አይታሰብም።
        ዋናው ነገር ወዲህ ነው። ግብር ለመክፈልም እኮ የህዝብ ውክልና ያለው ስርዓት መኖር ግድ ይላል። የሀዝቡን ይሁንታ ያላገኘ መንግስት፣ በሕዝብ ያልተመረጠ መንግሥት ግብር የማስከፈል መብት የለውም፣ ሕዝቡም ላልወከለው መንግስት ግብር ለመክፈል አይገደድም።    
        እ.ኤ.አ. በ1750ቹ እና 1760ቹ አስራ ሶስቱ የአሜሪካ ቅኝ ግዛቶች ይዘውት የተነሱት መፈክርን ያስተውሏል። "No Taxation Without Representation" ይላል። "ውክልና ከሌለ ግብር አይኖርም" እንደማለት ነው።  አሜሪካኖች በዚያ የነጻነት ትግላቸው ወቅት አቋማቸውን ለመግለጽ የተጠቀሙበት መሪ ቃል ነበር።  አመሪካውያኑ ይህንን መፈክር ይዘው በማመጽ የብሪትሽን ኤምፓየር እንዳናፈጡት የታሪክ ማህደር ያወሳናል።
         ህወሃት የህዝብ ይሁንታም የለው፣ መረጃም የለው። ሃይለማርያም ደሳለኝ በብሄራዊ ቴሌቭዥን ለይ ወጥተው እንዲህ አሉ። ስራችንን የምንሰራው፣ ውሳኔም የምንወስነው መረጃ ሳንይዝ እንዲሁ በግምት ነው። "መረጃ የሚጠናከርበት ስርዓት የለም።" አሉ።  እኚህ ሰው አንዳንዴ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ  እውነትን ይለቁልናል። ንግግራቸው እኝህ ሰው ነጻ ያለመሆናቸውን ይጠቁመናል።   ሃገሪቱ ነጻ መውጣት ካለባት በመጀመርያ ነጻነትን ማወጅ ያለበቸው እሳቸው ናቸው። እውነት ነው።  ህወሃት እየመራ ያለው በግምት እና በጥይት ነው።
        የሃይለማርያም ንግግር አጉልቶ የሚያሳየን ነገር አለ። ስርዓቱ ችግር ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን፣ ስርዓቱ ራሱ ችግር መሆኑን ግልጽ ያደርግልናል።
        ትግራይ "ክልል" ፕሬዝዳንት እና የመቐሌ ከንቲባ ላይ ከሰሞኑ የተፈጠረው ሕዝባዊ ተቃውሞ የሚሰብቀን ነገር ይኖራል። ከሰሞኑ በመቀሌ ስታድዮም የገባው ህዝብ በዝግጅቱላይ በተገኙ የህወሓት አመራሮችን "ሌባ ሌባ ሌባ .. ሃሳዊ (ውሸታም) መሲህ ሲሉ ተደምጠዋል። እንግዲህ የትግራይ ህዝብ ራሱ ተወክያለው ያለውን አመራር "ሌባ ሌባ " ካለ ምን ቀረ?... እንደኔ ግምት የቀረ የለም። ሃገር እየተመራች ያለችው መረጃ በሌላቸው፣ ራዕይ በሌላቸውና የህዝብ ይሁንታ ባላገኙ ሌቦች ነው።
        ከትግራይ ውጭ ያለውም ሕዝብ እንዲህ ነው የሚለው። "ወያኔ ሌባ ነው! ለሌባ ግብር አንከፍልም!"  
        "ኢትዮጵያንና ህዝቧን በጉልበት አፍኖ ለያዘ ዘራፊ ቡድን አንገብርም!!" ብለዋል ጊንጪዎች። ይህ የግብር አመጽ የፍጻሜው ጦርነት ይሆን? እድሜ ከሰጠን እናየዋለን።
        ለዛሬ በዚህ ላብቃ በመጪው ጽሁፌ ስለ "ኳስ እና ፖለቲካ" የምለው አለኝ።

Saturday, July 22, 2017

በአዲስ አበባ ሳሪስ፣ ኮልፌ፣ ቡራዩ፣ ደምቢዶሎ፣ ነጆ፣ ነቀምቴ በሥራ ማቆም አድማ ላይ ናቸው | ወደ ሰሜን ለሚሄዱ ተሽከርካሪዎች ማስጠንቀቂያ ተላለፈ!!

July 22,2017

( ዘ - ሐበሻ) ሕወሓት መራሹ መንግስት የጣለውን አግባብ ያልሆነ ግብር በመቃወም የተጀመረው የሥራ ማቆም አድማ በተለያዩ ቦታዎች እየተስፋፋ ነው:: በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ሳሪስ እና ኮልፌ አካባቢ ንግድ ሱቆች መዘጋጋታቸው ታውቋል::
ሳሪስ ሙሉ በሙሉ ዝግ ስትሆን በኮልፌ አካባቢ ግን አንዳንድ ነጋዴዎች የመንግስትን ማስፈራሪያ ተቀብለው መክፈታቸው ተሰምቷል:: ለነዚህ ሱቃቸውን በመክፈት መንግስትን ለተባበሩት ነጋዴዎች ከአካባቢው ነዋሪዎች ማስጠንቀቂያ እንደተላለፈላቸው ለማወቅ ተችሏል::
በደምቢዶሎ ከተማ ትንስፖርት ቆሞ ሱቆች ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ተቃውሞው የቀጠለ ሲሆን ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚታይባት ቡራዩ ከተማም ዛሬ ጭር ብላ መዋሏን የአካባቢው የህቡዕ ታጋዮች በፎቶ ግራፍና ቭድዮ አስታከው ከላኩት መረጃ ሌረዳት ተችሏል::
ነጆ ከተማም እንዲሁ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን ዘጋግተው ቤት ቁጭ ያለ ሲሆን የመንግስት ኃይሎች ሱቆቻቸውን እንዲከፍቱ ከፍተኛ ግፊት እያደረጉባቸው እንደሆነ ከሥፍራው የተገኙ መረጃዎች ጠቁመዋል::
በሌላ በኩል በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ በሰነበተችው ነቀምቴ ከተማ መንግስት የባጃጅ ሹፌሮችን ስራ አስፈትቶ ሥብሰባ እንዲቀመጡ ማድረጉ ታውቋል::
በሕዝባዊ እምቢተኝነቱ የቀጠለችው ነቀምቴ ከተማ የንግድ እንቅስቃሴዋ እጅጉን መዳከሙን የሚገልጹት የአካባቢው ነዋሪዎች መንግስት የባጃጅ ሹፌሮችን በስብሰባ ላይ የማትገኙ ከሆነ ታርጋችሁን እቀማለሁ በሚል አስፈራርቶ እንደሰበሰባቸውና በታክስ ስም ፕሮፓጋንዳውን እያስተማራቸው መሆኑን ከስፍራው የተገኘው ዜና ይገልጻል::
ይህ በ እንዲህ እንዳለ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የሚጓጓዙ መኪኖች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ት ዕዛዝ ተላለፈ:: በሕቡዕ ጉዳዩን እያደራጁ የሚገኙት ወጣቶች (ቄሮዎች) ያሰራጩት ማስጠንቀቂያ እንደሚከተለው ቀርቧል::
“ማስጠንቀቂያ… ማስጠንቂያ… ዛሬ በሱልታ፣ በጫንጮ፣ በጎርፎ፣ በዱበር፣ በሙከ ጡሪ፣ በደብረ ፅጌ፣ በፊቼና በገርባ ጉራቸው ከተሞች ውስጥ ማንኛውም የንግድ እንቅስቃሴ ለ3 ተከታታይ ቀናት የማቆም አድማ ይደረጋል። ሱቆች፣ሆቴሎችና የሸቀጣሸቀጥ መደብሮች በሙሉ ተዘግተው ይውላሉ። በመሆኑም ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልልና ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ ማንኛውም የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ይቋረጣሉ። ይህን ህዝባዊ ጥሪ አልፎ የሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪ ወይም የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርግ አካል ካለ ለሚወሰድበት እርምጃ ተጠያቂ ራሱ ይሆናል።”
ወጣቶች (ቄሮዎች) ካስተላለፉት መልዕክት የተወሰደ

Saturday, July 15, 2017

የአዲስ አበባ አስተዳደር መሬት አጥረው ባስቀመጡ ኤምባሲዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ መቸገሩ ተገለጸ

July 15,2017
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዲስ አበባ መሬት አጥረው ባስቀመጡ የተለያዩ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ መቸገሩን መረጃዎች ጠቆሙ፡፡ በከተማዋ ለረዥም ጊዜ መሬት አጥረው ካስቀመጡ አካላት መካከል፣ የውጭ ሀገር ኤምባሲዎች፣ የሼህ ሁሰይን አሊ አላሙዲን ንብረት የሆነው ሚድሮክ ኢትዮጵያ፣ የመንግስት ተቋማት እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ እነዚህ አካላት የከተማዋን አንድ ሶስተኛ ሊያክል ምንም ያልቀረው መሬት በመውረር ያለ ምንም ስራ አጥረው አስቀምጠዋል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብለት የቆየው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ አሁንም ምንም ዐይነት እርምጃ አለመውሰዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በከንቲባ ድሪባ ኩማ የሚመራው የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ መሬት አጥረው ከያዙ አካላት ጋር ለውይይት ተቀምጦ እንደነበር ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወቃል፡፡ ሆኖም መረጃዎች እንደጠቆሙት ከሆነ፣ በወቅቱ የተደረገው ውይይት ምንም ዓይነት ውጤት አላመጣም፡፡ በዚህም የተነሳ ስማቸው የተጠቀሱት አካላት እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የከተማዋን መሬት እንደወረሩ ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ሳምንት ስብሰባውን ያካሔደው የከተማዋ አስተዳደር፣ በጉዳዩ ላይ ውይይት እንዳደረገ ቢገለጽም፣ መሬት አጥረው የያዙ አካላትን በተመለከተ የረባ ሪፖርት አላቀረበም፡፡
አስተዳደሩ ሰፋፊ መሬት አጥረው ከያዙ ኤምባሲዎች እና ሚድሮክ ኢትዮጵያ ይልቅ በትናንሽ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መውሰዱን ነው የገለጸው፡፡ ለረዥም ጊዜ መሬት አጥረው ለያዙት ኤምባሰዎች እና ሚድሮክ ኢትዮጵያ ግን ወደ ስራ እንዲገቡ በድጋሚ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ብቻ ተሰጥቷቸው ታልፈዋል፡፡ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው ሲባል ይህ ለበርካታ ጊዜ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ህጋዊ ባለ ይዞታ የሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ድንገት ተነስቶ በማፈናቀል እና ቤት በማፍረስ የሚታወቀው የከተማዋ አስተዳደር፣ ኤምባሲዎች እና ሚድሮክ ኢትዮጵያ ላይ ሲደርስ አቅም እንደሚያጥረው ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ 

በከተማዋ 138 አካላት 150 ሄክታር መሬት አጥረው የያዙ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ሰፊውን ድርሻ የሚወስዱት የውጭ ኤምባሲዎች፣ ሚድሮክ ኢትዮጵያ እና የመንግስት ተቋማት ናቸው፡፡ ሆኖ,ም አስተዳደሩ እርምጃ ወሰድኩኝ ያለው ግንባታ ባልጀመሩ ትናንሽ ባለሀብቶች ላይ ብቻ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በ13 ባለይዞታዎች ላይ ክሰ መሰረትኩኝ ያለው የድሪባ ኩማ አስተዳደር፣ ከ43 ባለሀብቶች ጋር ደግሞ ያለውን ውል በማቋረጥ መሬታቸውን መንጠቁን አስታውቋል፡፡

Source: BBN News July 13, 2017

Thursday, July 13, 2017

አምቦ ውጥረት ላይ ትገኛለች ነጋዴው ህብረተሰብ ጩኸቱን እያሰማ ነው

July 13, 2017
የአዲስ አበባ የግብር መክፈያ ቦታዎችም በአቤቱታ አቅራቢዎች እየተጨናነቁ ነው
የእለታዊ ገቢ ግብር አሰራርን በመቃወም በአምቦ ከተማ ዛሬ ተቃውሞ ሲካሄድ የዋለ ሲሆን፣ አንድ የፌደራል ፖሊስ መኪና ሲቃጠል ፣ አንድ አውቶቡስና ሌሎች የመስሪያ ቤት መኪኖችም ተሰባብረዋል። ይህን ዜና እስካጠናከርንበት በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር እስከ 11 ሰአት ድረስ በከተማዋ ተኩስ ይሰማ ነበር። ወደ ወለጋ የሚወስደው መንገድም በድንጋይ ተዘጋግቷል። በከተማዋ ያሉ አገልግሎት መስጫ ተቋማትና የንግድ ቤቶችም ተዘግተዋል። 
በአዲስ አበባ ደግሞ የግብር መክፈያ ቤቶች በአቤቱታ አቅራቢዎች ተጨናንቀው ታይተዋል። የወያኔ ህወሃት መንግስት በነጋዴው ህብረተሰብ ላይ የጣለው የግብር ጫና ነጋዴው ከሚሰራው ሁለት እጥፍ በላይ ከመሆኑ ባሻገር ምንም ጥናትን የያዘ እን የነጋዴ ማህበረሰቡን ገቢ ያላገናዘበ መሆኑን ነጋዴዎች ይገልጣሉ ። የተለያዩ የመረጃ ማእከሎችም ከስፍራው እንደገለጹ በአዲስ አበባም ሆነ አምቦ አለበለዚያም በሌላ ክልሎች ከፍተኛ ውጥረት መነሳቱ፣ የሃገሪቱን መንግስት ቢያስጨንቅም ጠንካራ እና ለሃገር እና ለህዝብ የሚያስብ አማራጭ የፖለቲካ ባለመኖሩ ህዝቡን ይበልጥ ከኪሳራ ውስጥ ጥⶀል ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
በየወረዳው የሚገኙ ጽ/ቤቶች በአቤቱታ አቅራቢዎች በመጨናነቃቸው ፣ ባለስልጣናቱ “የምትችሉትን ክፈሉና ሌላውን ቀስ ብላችሁ ትከፍላላችሁ” በማለት ለማረጋጋት ሙከራ ሲያደርጉ ታይተዋል። ነጋዴዎች ግን በባለስልጣኖች በኩል የሚሰጠውን መልስ የሚቀበሉት አልሆነም።
በዲላ ነጋዴዎች ግብር አንከፍልም በማለት በአንድ ድምጽ እየተናገሩ ሲሆን፣ ድምጻቸውን ለማሰማት የተቃውሞ ሰልፍ ለማዘጋጀት የሚያደርጉትን ሙከራ ከንቲባው ለማጨናገፍ እየተሯሯጠ መሆኑን ወኪላችን ገልጿል።

Friday, June 23, 2017

ሰራዊቱን ዝም ለማሰኘት የታቀደ የመጀመሪያ ዙር ስራ የተቃዋሚ ደጋፊ የተባሉ ወታደሮችን ለማጥቃት የታቀደ ግምገማ ሊደረግ መሆኑ ታውቋል

Juni 23,2017
ከጦር ሃይሎች የተገኘው መረጃ እንደተመለከተው በመከላከያ ሰራዊቱ ሁሉም እዞች በወታደሮች ላይ ግምገማ ሊደረግ መሆኑ ታውቋል::የግምገማው ዋናው ሂደት በሰራዊቱ ውስጥ የተገኘው የኢሕአዴግ ድምጽ አነስተኛ መሆኑ እና ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ከሚል አንጻር ተጠርጣሪ የተቃዋሚ ደጋፊ የተባሉ ወታደሮችን ለማጥቃት የታቀደ ግምገማ ሲሆን በግምገማው ላይ ሞባይሎች እንደሚፈተሹ እና ተቃዋሚዎችን በተመለከት ውስጥ ለውስጥ ፕሮፓጋንዳ ያራግባሉ እንዲሁም አለማቀፍ ጉዳዮችን በተመለከተ ከሚዲያ መረጃዎችን ይዘው መተው ያወራሉ የሚባሉ ወታደሮች የግምገማው ሰለባ እንደሚሆኑ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ተናግረዋል::የመከላከያ ሰራዊቱ ከሲቭል ደህንነት እና ከኢንሳ በተመደቡ እና የወታደሩን ካኪ ለብሰው በመመሳሰል በሚሰልሉ የሕወሓት አባላት አቅራቢነት ወንጀሎች ተቀነባብረው ግምገማውን እንደሚያጦዙት ይጠበቃል ሲሉ ምንጮቹ አክለው ገልጸዋል::
የለውጥ ፈላጊ ሃይሎችን ደግፋችሁሃል በሚል ለጥቃት የተዘጋጀው ይህ ግምገማ አለመተማመን እና ጥርጣሬ በሞላው የመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ልዩነቶችን በማስፋት በአንድ ብሄር የበላይነት የሚተዳደረውን አምባገነን ወታደራዊ አመራርን በማጠናከር ሌሎች ብሄሮች በፍርሃት እና በስጋት እንዲኖሩ ለማሸማቀቅ የሚያደርግ እንዲሁም ሰራዊቱን ለለውጥ ያነሳሳሉ የሚባሉ መኮንኖችን እና ወታደሮችን ሰብስቦ ለማሰር እና ደብዛቸውን ለማጥፋት የታቀደ እንደሆነ ታውቋል:ግምገማው የሚመራው በተለያዩ እና በጄነራልነት ማእረግ ባላቸው የሕወሓት መኮንኖች ሲሆን ሰራዊቱን ዝም ለማሰኘት የታቀደ የመጀመሪያ ዙር ስራ መሆኑን ምንጮቹ ገልጸዋል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ 450 የሕወሓት አባላት ተመልምለው ለወታደራዊ ስልጠኛ በሚል በተለያዩ የምስራቅ አውሮፓ አገሮች ለትምሕርት ሊላኩ መሆኑ ሲታወቅ ከአንድ ብሄር ብቻ ለምን/እንዴት ይህ ሆነ የሚል ጥያቄ መነሳቱን እና ምንም አይነት ምላሽ እንዳልተሰጠው ታውቋል::ምንጮቹ አያይዘው እንዳሉት ልሰላም አስከባሪ ሃይል ከፍተኛ አመራር እንዲሆኑ ለስልጠና የታጩት የሕወሃት አባላት ጉዟቸው እንደማይሰረዝ እና ጉዞውን ለተቃወሙት መኮንኖች ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ገልጸዋል::
ቆንጂት ስጦታውm

Saturday, April 29, 2017

ባሕር ዳር ኮንሠርት ላይ በፈነዳ ቦንብን ምክንያት በማድረግ በርካታ ወጣቶች ታሠሩ፤

April 29,2017
ባሕር ዳር ኮንሠርት ላይ በፈነዳ ቦንብን ምክንያት በማድረግ በርካታ ወጣቶች ታሠሩ፤
ባሕር ዳር ኮንሠርት ላይ በፈነዳ ቦንብን ምክንያት በማድረግ በርካታ ወጣቶች ታሠሩ፤
ሚያዚያ 21 ቀን 2009 ዓ.ም፤ በባሕር ዳር የመስቀል አደባባይ በነበረ የዘፈን ኮንሠርት ላይ ምሽት 1፡30 አካባቢ በፈነዳ ቦንብ ዝግጅቱ ተቋርጦ የመከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ፖሊሶች ጥይት ይተኩሱ እንደነበር የመረጃ ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
የዳሽን ቢራ ስሙን ወደ ባላገሩ መቀየሩን ተከተሎ በባሕር ዳር ከተማ የዘፈን ኮንሠርት በማዘጋጀት ለሕዝብ የማስተዋወቅ የመጀመሪያ ሙከራው ሲሆን ኩኩ ሰብሰቤና አረጋኸኝ ወራሽ ነበሩ፡፡ ወንድሞቻችን እየተገደሉና እየታሰሩ ምንም ዓይነት ዘፈንና ጭፈራ አንፈልግም በሚል የባሕር ዳር ከተማ ሕዝብ ወደ ኮንሠርቱ እንዳልሄደ ነው የነገሩን፡፡ የሥርዓቱ ደጋፊዎች የሆኑ ጥቂት ሰዎች በታደሙበት በዚህ ኮንሠርት ኩኩ ሰብስቤ ‹‹ቻልኩበት›› እያለች በመዝፈን ላይ ሳለች ድንገት ከፍተኛ የቦንብ ፍንዳታ ተሰማ፡፡ በዚህም አደባባዩ ውስጥ የነበሩ ቁጥራቸውና የጉዳት መጠኑ በውል ያልታወቁ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡
ኩኩ ዘፈኗን አቋርጣ መጠጊያ ፍለጋ ለመሸሽ ተገዳለች፡፡ መድረኩ ላይ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ዘፈኑን አቋርጠው የሸሹ ሲሆን ከፌደራል ፖሊስና ከመከላከያ ከፍተኛ ተኩስ ተከትሏል ብለውናል መረጃዎቻችን፡፡ አስተያየቱ የሠጡን ሰዎች ‹‹እኛ አገር አጥተን የምን ‹ባላገሩ› የሚል አተላ ሹፈት ነው›› ብለውናል፡፡ ይህን ተከትሎ ባለፉት ጥቂት ሰዐታት ብቻ ከመቶ ያላነሱ ወጣቶች በገፍ ታሥረዋል ብለውናል፡፡ በቀበሌ 15፣ 04፤03፣ 05፣ 06 አካባቢዎች የተገኘ ማንኛውም ሰው እየታሠረ እንደሆነ የመረጃ ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ከአዲስ ዘመን እስከ አምባጊወርጊስና ትክል ድንጋይ ድረስ ከፍተኛ ውጥረት እንዳለ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ኦባንግ ሜቶ ከከፋ አደጋ ተረፉ!

April 29, 2017

  • “ዳግም የመኖር እድል ተሰጠኝ፤ ተማርኩበት፤ እናንተም ተማሩ”
“ጥቁሩ ሰው” ኦባንግ ሜቶ በሁሉም ስፍራ፣ በየትኛውም አጋጣሚ ለሚፈልጋቸው ሁሉ “አለሁ” የሚሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው። ዘረኝነትን፥ ዘውገኝነትን፥ ጎሠኝነትን አጥብቀው ይዋጋሉ። ይጸየፉታል። ከዘር ቆጠራና ከቂም የጸዳች ኢትዮጵያን ማየት ህልማቸውና የመጨረሻ ግባቸው ነው።
ሰብዓዊነት ለአፍታም ከአንደበታቸው የማይለይ፣ በሚያውቋቸው ሰዎች ሁሉ የሚወደዱ፣ ግልጽ ተናጋሪነታቸው ልዩ የሚያደርጋቸው ኦባንግ በዚሁ ባህሪያቸው “አባ ነቅንቅ” የሚል ስም ተሰጥቷቸዋል። በስደት ለሚሰቃዩ የኢትዮጵያ ልጆች /እሳቸው ቤተሰቦቼ የሚሏቸው/ በጠሯቸው ቦታና ሁሉ በመገኘት ለሚያሳዩት ትጋት አቻ የላቸውም። ኢትዮጵያን በመወከል በከፍተኛ ቦታዎች የሚሟገቱ፣ ያዘነውን የሚጎበኙ፣ ለሴት እህቶቻችን ቀድመው የሚደርሱ እኚህ ውድ ሰው በድንገተኛ የመኪና አደጋ ተዓምር ሊባል በሚችል አጋጣሚ ከሞት የመትረፋቸው ዜና ስንሰማ ደንገጠናል። እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ አብሯቸው የነበረ ባልደረባቸውም ከዚህ ዘግናኝ አደጋ አምልጧል።
ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ሚያዚያ 14 2009ዓም /22.04.2017 ከዋሽንግተን ዲሲ ወጣ ብሎ የደረሰባቸውን የመኪና አደጋ አስመልክቶ “ዳግም የመኖር ዕድል ተሰጠኝ፤ ተማርኩበት፤ እናንተም ተማሩበት። ዜናው የእኔ ከአደጋ መትረፍ ሳይሆን በቅጽበት የምትሰናበተውን ህይወታችንን በሚገባ ልንጠቀምበት እንደሚገባ መማሩ ላይ ነው” ሲሉ ነበር የገለጹት።
“አዎ” አሉ ጥቁሩ ሰው። “አዎ! ሞትን ለቅጽበት አየሁት። እንዳልወሰደኝ ስረዳ ሰዎች በቅጽበት ታሪክ እንደሚሆኑ በመረዳት በህይወት ዘመናቸው ደግ ለመስራት ለራሳቸው አለመማላቸው አሰብኩ” ሲሉ መልዕክታቸውን የጀመሩት ኦባንግ “እንኳን ነገ፣ በደቂቃዎች ምን እንደምንሆን ማስተማመኛ በሌለበት ሁኔታ ሰዎች ስለበቀልና ሌላውን ስለማጥፋት ስልት እየነደፉ ለመኖር መምረጣቸው አሳዘነኝ”።
ይህንን ሲናገሩ “የሚጸጽተዎ ነገር አለ እንዴ?” የሚል ጥያቄ ሰንዝረን ነበር። ኦባንግ ግን መልሳቸው ሌላ ነው። “እኔ ጸጸት ብሎ ነገር አላውቅም። የምጸጸትበት ነገርም ስለመፈጸሜ አስቤ አላውቅም። ነገር ግን ለወገኖቼ መሥራት የሚገባኝን እንዳልሰራሁ አስባለሁ። በተለያዩ ምክንያቶች ያስብኩትን ያህል አልተጓዝኩም። ይህ ከጸጸትም በላይ ነው። ምክንያቱም ዘረኝነትን ረግጠንና ቀብረን መጓዝ አለመቻላችን መድሃኒት የሌለው የቅዠት ተስቦ በሽተኛ አድርጎናል” ብለዋል። በውል የማይታወቅ ዘመን ወደኋላ በመሄድ ለአሁኑ ትውልድና ለአገራችን በማይጠቅም ጉዳይ ላይ ጉልበት፣ ሃብትና ጊዜ እየባከነ መሆኑንን የጠቆሙት ጥቁሩ ሰው “ከዚህ አዙሪት ሳንወጣ ሞት ይወስደናል፥ ለትውልድ የማይድን ቁስል ትተን፥ ትውልዱን መርዝ ወግተን እናልፋለን” ይላሉ።
ተፈጥሮ በጥድፊያ ወደ ሞት እየገፋችን ባለበት ሰዓት ሰው ሌላውን ስለመበቀልና ስለማጥፋት ዕቅድ ይዞ መስራቱ ከምንም ነገር በላይ ልብ የሚሰብር እንደሆነ ኦባንግ በሃዘኔታ ነው የገለጹት። “የማውቃቸውም ሆነ የማላውቃቸው በርካታ ወዳጅ ቤተሰቦች እንዳፈራሁ አውቃለሁ። ይህን ዜና ሲሰሙ እንደሚያዝኑ እረዳለሁ። ከዜናው በላይ ግን ለሚሰሙ ትምህርት እንዲሆን ይህንን መልዕክት ለማስተላለፍ ስል መናገርን መርጫለሁ። ዳግም የመኖር ዕድል ስለተሰጠኝ የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ስል ከሞት መልስ የተማርኩትን አካፍያለሁ። ለሚሰማ ትልቅ ጉዳይ ነው” ሲሉ ማሳሰቢያ አዘል መልክታቸውን ኦባንግ አስተላልፈዋል።
ከዘርና ከዘረኛነት ቋት ወጥተው “ከጎሳ በፊት ሰብዓዊነት” በሚል አዲሲቷ ኢትዮጵያ ልትተከልበት የሚገባውን መርህ የሚያቀነቅኑት ኦባንግ “መለስ ሲነገረው ቢሰማና ለአንድ ቀን ቀና ሰው ስለመሆን ቢያስብ፣ ብለን ብንመኝ ቢያንስ በቅርቡ ያለቁትን በሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን ነፍስ ማትረፍ፣ እየሰፋ የመጣውን የጎሳ በሽታ መቀነስ በቻልን ነበር። ግን ያሳዝናል በተቃራኒው ነው የሆነው። ያለመውንና ያሰበውን ሳያይ ህይወቱ በጥላቻና በዘረኝነት እንደመረረች ሄደ” ሲሉ የቀናነት እጥረት በሽታ ክፋት ያስረዳሉ።
የኮምፒውተር እቃ ለመግዛት አንድ መደብር ደረሰው ሲመለሱ የ18 ዓመት ወጣት ሴት በፍጥነት እያሽከረከች ሊያመለጡት በማይችሉበት ሁኔታ ተምዘግዝጋ ኦባንግ የሚያሽከረክሩትን መኪና በሳቸው በኩል ጎኑንን መታችው። ወጣቷ በከፍተኛ ፍጥነት ላይ ስለነበረች የኦባንግ መኪና ምቱ እንዳረፈባት ወደ ጎን ተገለበጠች። በመጨረሻም የአውራ ጎዳናው ጠርዝ መኪናዋን ያዛትና በቋፍ ተደግፋ እግሯን ሰቅላ ተገልብጣ ቆመች። የመውጫ በሮቹ በሙሉ ተቀርቅረውና ተጨረማምተው ስለነበር ዕርዳታ ሰጪዎች ባደረጉት ድጋፍ ኦባንግና ባልደረባቸው በኋለኛው በኩል ባለው የእቃ መጫኛ በር ሾልከው እንዲወጡ ተደረገ።
አደጋው ከደረሰ በኋላ አካባቢው ላይ የነበሩ ሰዎች እያነቡ ውስጥ የነበሩት እነ ኦባንግ ሲወጡ ሰላም መሆናቸውን ሲመለከቱ መገረማቸውን መስክረዋል። ፖሊስም ያለ አንዳች ጭረት፣ ደም፣ ስብራት፣ … ኦባንግና ባልደረባቸው መትረፋቸው “ድንቅ” ተብሎ ሊገለጽ እንደሚችል ሁኔታዎች ከተረጋጉ በኋላ ተናግሯል። እንደ ፖሊስ ገለጻ መኪናዋ ከተመታቸበት ቦታ ትንሽ ወደ አሽከርካሪው ተጠግቶ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ኦባንግ “ከሞት መልስ ተማርኩ” ለማለት እንደማይበቁ ይሆኑ ነበር። ይህንኑ አስመልክቶ ጥቁሩ ሰው “በፈጣሪ ኃይል ከሞት ተረፍኩ፣ ዳግም የመኖር ዕድል ተሰጠኝ ያልኩት ለዚህ ነው” ብለዋል።
አያይዘውም በቀናነት፣ በታማኝነት፣ በጸዳ ህሊና፣ በሃቅ፣ በመታመን፣ ለአገርና ለህዝብ ከመስራት የበለጠ የሚያኮራ ነገር እንደሌለ ተናገረዋል። በዘርና በጎሳ ተቧድነው፣ ጥላቻን መነሻ መሠረታቸው አድርገው፣ ሌላውን ለማጥፋትና ለመበቀል ዝግጅት እያደረጉ ላሉ፣ ዘመኑ በውል በማይታወቅ ጊዜ ወደኋላ ተመልሰው ቂምን የሚያራግቡና የክፋት ዘርን የሚረጩ ሁሉም ቆም ብለው በማሰብ ራሳቸውን ወደ መግዛት ብልኃትና ጥበብ እንዲመለሱ ጥሪ አስተላልፈዋል።
እሳቸው ከሞት አፋፍ መልስ የተማሩት ይህንን ነውና በግላቸው ከቀድሞው በላይ ራሳቸውን ለህዝብ እንደሚያስረክቡም ቃል ገብተዋል። ዜናውን አስቀድማ የነገረችን ምስክር “ኦባንግን ማጣት እንደ አገር ክስረት ነበር የሚሆነው። ኦባንግ ጀርባቸው የጸዳ፣ ለሚፈለገው ዓይነት ኃላፊነት የሚታመኑ፣ ታላቅ ራዕይ ያላቸው፣ ከነፈሰው ጋር የማይነፍሱ፣ ራሳቸውን ሆነው በነጻነት የሚኖሩ፣ የአንደበት ሳይሆን የተግባር ሰው የሆኑ … ኢትዮጵያዊ” ስትል ገልጻቸዋለች። አያይዛም “ከሚሠሩት ከፍተኛ ሥራ 10 በመቶውን ብቻ አደባባይ የሚያወጡ፣ ጊዜና ትውልድ በሰዓቱ ክብር የሚሰጣቸው ሰው እንደሆኑ አምናለሁ። የተረፉትም ለዚሁ ዓላማ ነው” ስትል ይህንን የተናገረችው የሚሰሩትን ሥራ ሁሉ በቅርብ ጠንቅቃ ስለምታውቅ መሆኑንንም አመልክታለች።
ኢትዮጵያን አስመልክቶ በከፍተኛ ቦታዎች በዝግ ስለሚሠሩት ሥራ ለምን በአደባባይ እንደማይገልጹ በተደጋጋሚ ኦባንግ ተጠይቀው “ገና ምን ሰራን፣ ሥራው ራሱ ሲገልጸው ማየት ይሻላል” የሚል መልስ በዚሁ ገጽ ላይ መመለሳቸው አይዘነጋም።
የመኪናውን አደጋ ያደረሰችው የ18 ዓመት ወጣት ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባት ለመረዳት ተችሏል። የመኪና አደጋ ሲደርስ ሰዎች በአብዛኛው እርስበርስ ሲካሰሱና ሲሰዳደቡ በተደጋጋሚ የታየ ቢሆንም በዚህ አደጋ ወቅት ኦባንግ ልጅቷን በማረጋጋትና በማጽናናት የፈጸሙት ተግባር የልጅቷን ቤተሰቦችና ባካባቢው የነበሩትን ሁሉ ያስደመመ እንደነበር በቦታው የነበሩ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
የዝግጅት ክፍላችን ለአቶ ኦባንግ፣ ለባልደረባቸውና ለልጅቷ፣ እንዲሁም ለወዳጆቻቸው ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ ይላል።
ከጎልጉል የድረ ገጵ ጋዜጣ የተወሰደ

Thursday, April 20, 2017

የአማራ ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን እንዳስታወቀው በክልሉ 66 ሽህ 102 ዜጎች በፍርድ እና ያለፍርድ እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ።

Aptil 20,2017

ሚያዝያ ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የክልሉ ማረሚያ ቤት ኮሚሽን እንዳስታወቀው በክልሉ 66 ሽህ 102 ዜጎች በፍርድ እና ያለፍርድ እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ።

በክልሉ የእስረኛው ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ በመሄዱ የክልሉ ባለስልጣናት መፍትሄ እንዲሰጡበት ጠይቋል። እስረኞቹን ለማስተናገድ የተበጀተው በጀት ማለቁንም ኮሚሽኑ አስታውቋል። እስረኞቹ በአማካኝ ከ5 እስከ 10 ዓመታት በፍርድ ወይም ያለፍርድ በእስር እንደሚማቅቁ የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ክልሉ ለ 22 ሺ 26 እስረኞች በቀን 9 ብር በድምሩ 203 ሺ 139 ብር፣ በአመት ደግሞ 73 ሚሊዮን 130 ሺ 40 ብር ወጪ ቢያደርግም፣ አሁን የእስረኞች ቁጥር በ3 እጥፍ በመጨመሩ ለማስተናገድ አለመቻሉን የክልሉ የማረሚያ ቤት ኮሚሽን ገልጿል፡፡

 የክልሉ ማረሚያ ቤት ለእስረኞች ህክምና ያወጣውን 2 ሚሊዮን 246 ሺ ብር ለመክፈል አልቻለም። የሁለት አመት ውዝፍ የህክምና ወጪ ለመክፈል ባለመቻሉም የጤና ተቋማት ለማስተናገድ ፈቃደኛ አንሆንም እያሉት መሆኑንም ገልጿል። እያንዳንዱ እስረኛ በአማካኝ 5 ዓመት በእስር ቤት ቢቆይ በጠቅላላው 1 ቢሊዮን 365 ሚሊዮን ፣ 200 ሺ ብር ምንም እሴት በማይጨምር ነገር ላይ ወጪ የደረጋል በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ገልጿል።

የእስረኞች ቁጥር በአንዴ ያሻቀበው በ2008 ዓም የታየውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ ያለምንም የፍርድ ውሳኔ የታሰሩ ወጣቶች መበራከታቸውን ተከትሎ ነው። ይህ አሃዝ በማረሚያ ቤት አስተዳደር ስር የሚገኙ እስረኞችን እንጅ በየወረዳው እና በየቀበሌው ታስረው የሚገኙትን ዜጎች ቁጥር አያካትትም። በክልሉ በሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ለአመት፣ ለወራት ወይም ለሳምንታት የሚታሰሩት እስረኞች ቁጥር ቢደመር በክልሉ የሚገኘው እስረኛ ቁጥር ከተጠቀሰው በብዙ እጅ ይልቃል። በአማራ ክልል ያለውን የእስረኞች ቁጥር ግምት ውስጥ በማስገባት በመላ አገሪቱ በሚገኙ ህጋዊ በሚባሉ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች እንደሚኖሩ ዘጋቢያችን አስተያየቱን አሰፍሯል።

ህዝብ ተፈናቅሎ እያለቀሰ ባለበት ሰአት የመሰረት ድንጋይ አላስቀምጥም

April 20,2017
ሚያዝያ ፲፪ (አሥራ ሁለት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 9 የሚገኝ 10 ሺህ ካሬ/አንድ ሄክታር/ ለሆቴል ግንባታ በካሬ 650 ሺህ ብር ሊዝ የገዙት የኳታሩ ባለሃብት ፣ አገዛዙ ቦታው ላይ የሰፈሩትን ነዋሪዎች በሙሉ አንስቶ ቦታውን አጽድቶ መጨረሱን በመግለጽ የመሰረት ድንጋይ እንዲያስቀምጡ ቢጋብዝም፣ ባለሃብቱ ግን ‹‹ህዝብ ተፈናቅሎ እያለቀሰ ባለበት ሰአት የመሰረት ድንጋይ አላስቀምጥም›› ማለታቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል። የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት ባለሃብቱን ለማግባባት ተደጋጋሚ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን፣ የኳታሩ መሪን የኢትዮጵያ ጉብኝት አስታኮ የመሰረት ድንጋይ ለማስቀመጥ ቀይ አሸዋ አፍስሰው የተጠረበ ድንጋይና ስሚንቶ አዘጋጅተው ቢጠብቁም፣ ባለሀብቱ ባለመቀበላቸው ድንጋይ የማስቀመጥ ስነስርዓቱ አልተከናወነም። የአካባቢው ነዋሪዎች መረጃውን ከክፍለ-ከተማውና የወረዳው መስተዳድር አካላት ማግኘታቸውን ተናግረዋል። የኳታሩ ባለሃብት ያነሱትን ጥያቄ ተከትሎ የአዲስ አበባ መስተዳድር “ከዚህ በፊት የቤት ግምቱ ይሻሻላል፣ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ምትክ ቦታ በስምምነታችሁ መሰረት ይሰጣችኋል ፣ ይህ እስኪፈጸም በግዳጅ መፈናቀል አይኖርም” በማለት ለህዝቡ በአደባባይ የገባውን ቃል አጥፎ፣ ህዝብን በመከፋፈል፣ የተሳሳተ መረጃ በመስጠትና አፍራሽ ወጣቶችን አሰማርቶ በግዳጅ ለማፍረስ ከጀመረው ድርጊት አለመቆጠቡን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። መስተዳድሩ ለተፈናቃዮች የተሰጠው ቤት ይህ ነው በማለት ለባለሃብቱ የልደታ ኮንዶሚንየምን ማሳየቱን የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ “ከእኛ መንግስት ይልቅ የኳታሩ ባለሃብት ያሳዩት ‹ሰብዓዊነት› በልጦ መገኘቱ፣ ይህ መንግስት እንደ ዜጋው እየተመለከተን ነው ብለን ለመቀበል አስቸግሮናል ›› በማለት ያሉበትን አሰቃቂ ሁኔታ ገልጸዋል። ተከራይ የቀበሌ ቤት ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ፣ ባለይዞታዎች ደግሞ በአብዛኛው ቤታቸውን በላያቸው ላይ አፍርሰው የግንባታ እቃዎችን በነጻ እንዲወስዱ በተፈቀደላቸው ‹አፍራሽ ወጣቶች› ፈርሶ ከአካባቢው እንዲለቁ የተደረጉ ሲሆን፣ በተለያየ ምክንያት ያለቀቁ ባለይዞታዎች የትንሣኤ በዓልን ‹‹ሌባ ሲጠብቁ ›› ማሰለፋቸውን በምሬት ገልጸዋል፡፡ እነዚሁ ባለይዞታ ነዋሪዎች — ያሉበትን አደገኛ ሁኔታ ቀኑን በሙሉ እዚያው ለሚውሉ የፖሊስ አባላት ቢያስረዱም ‹‹ እኛ ከዋናው መንገድ ወደ ውስጥ ለመግባት አንችልም፣ እኛም ለራሳችን እንፈራለን፣ አልታዘዝንም ›› በማለት መልስ መስጠታቸውን፣ ‹‹አፍራሽ ወጣቶችም ፖሊሶችን አፍርሰው ከሚያገኙት የጥቅም ተጋሪዎች እንዳደረጓቸውና ምንም እንደማይደረጉ በድፍረት የሚናገሩ መሆኑን፣ በሌላ በኩል አንዳንድ ፖሊሶች ‹‹ ይህ ወጣት የተወለደበትንና ያደገበትን ሠፈር ከማፍረስ መከላከል ሲገባው፣ ይህን ዓይነት ድርጊት ሲፈጽም እያያችሁ እኛን ምን አድርጉ ትላላችሁ›› ሲሉ በወጣቶቹ ሁኔታ ማዘናቸውን እንደገለጹላቸው አስረድተዋል፡፡

Saturday, February 18, 2017

በኢትዮጵያዊነትና በኢትዮጵያ ሀገራዊ ኣንድነት ላይ የተቃጣው ጦርነትና የአርበኞች ግንቦት 7 ሀገር ኣድን ትግል

February 18,2017

ነዓምን ዘለቀ
ራሱን ህዝባዊ ወይኔ ሃርነት ትግራይ  በማለት  በሚጠራው የጸረ-ኢትዮጵያ መሰሪዎች አምባገነናዊ አገዛዝ ላለፉት ሃያ አምስት አመታት  የዘለቀ  ስቃይ እና ጥቃት ኢላማዎች የነበሩት የኢትዮጵያ አንድነትና ኢትዮያዊነት ብቻ ሳይሆኑ  የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችም በተናጠል እና በየተራ ግፍ እና ስቃይ ሲቀበሉ ቆይተዋል ፣ አሁንም በከፋ መልኩ ስቃዩ ቀጥሏል። ጸረ ኢትዮጵያዊው ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በተደራጀ መልኩ  የጥፋት ሰይፉን በዋናነት የመዘዘበት  ኢትዮጵያዊነት ደግሞ አንዳንዶች እንደሚያምኑት የብሄር ብሄረስቦች ማለትም የኦሮሞው፣የአማራው ፣ የትግሬው፣የሶማሌው ፣የሲዳማው፣የጉራጌው ፣ የአፋሩ፣የከምባታው  እንዲሁም የሌሎች ብሄረሰቦች  ድምር ማንነት ብቻ ሳይሆን  ኢትዮጵያዊነት ከብሄሮች ድምር (The sum of its parts) በላይ ነው።  ኢትዮጵያዊነት ለዘመናት የተገነባ ማንነት ነው። የየትኛውም ብሄር ወይም ነገድ ባህልና ቋንቋ ብቻውን ኢትዮጵያዊነትን አይገልጸውም፣ አይበቃውም፣  አይተረጉመውም።
Neamin Zeleke a member of Patriotic Ginbot 7
ነዓምን ዘለቀ
ኢትዮጵያዊነት ሚሊዮኖች በጋራ የምንጋራው ውስጣዊ ማነትታችን ነው። ስነ-ልቦናዊም ህሊናዊ ባህሪያት ያሉት  ልንገልጸው ከምንችለው በላይ ረቂቅ ነው ፡፡ ለዘመናት የተገነባውና ሚሊዮንኖች በጋራ የሚጋሩት ይህ ማነንታችን መሰረታችን ከሆነው ብሄር ማንነት በላይ ሁለመናችንን የሚገዛን  መንፈስ  ነው።ድሃ ብንሆንም፣ በጨቋኝ ስርዓቶች ወስጥ ብናልፍም  የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎችን አሳፍሮ  በደም የተከበረው፣በማህበራዊ ትስስር የተገመደው ኢትዮጵያዊ ማንነታችን ያረካናል፣ ያጠግበናል። ከሁለት ብሄር  እና ከዚያ በላይ ቤተሰብ የተገኙ ሚሊዮኖች  ኢትዮጵያዊነትን በብሄር አጥር እንደማናቆመው  ህያው ማሳያዎች ናቸው። በአዲስ አበባ፡ በአዳማ ፣በደሴ፡ በሃረር፣ በድሬዳዋ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር፡ ጅማ፣ አዋሳ  በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ዋና ዋና ከተሞች  ተወልደው ያደጉ ሚሊዮን ከተሜዎች  (Cosmopolitans) በመሆናቸው ራሳቸውን ከተወለዱበት ብሄር/ዘውግ ማነንት ጋር የሚያቆራኙበት ሁኔታ ባለመኖሩም፣ ማንነታቸው ኢትዮጵያዊነት ነው።
ዘውግ ሳይለይ ከሁሉም ማህበረስቦች መሰረታቸው  የሆነ እንዲሁም  ከእያንዳንዱ የዘውግ ማህበረስብ የተወለዱ/ወይንም መሰረታቸው የሆኑ ሚልዮኖች በቀዳሚነት  የማንነታቸው መገለጫ ያደርጉት ኢትዮጵያዊነት በሂደት በህልቆ መሳፍርት ውስብስብ የረጅም ዘመናት ታሪካችንን የሚመግቡ ብዙ የታሪክ  ጅረቶች የተገነባ ነው። ኢትዮጵያዊነት ረጅም የዘመናት ጉዞ ውጤት ነው። ውድቅት፣ ማንሰራራት፣ መነሳት፣ መስፋትና መጥበብ በተፈራረቁባት ጥንታዊት  የሆንችው ኢትዮጵያ   ምድር ደቡብ የነበረው ማህበረስብ ወደ ሰሜን ሲፈልስ፡ የሰሜኑ  ህዝብ ወደ ድቡብ ሂዶ ሲሰፍር ፡ ምስራቅ የነበረው ወደ ምእራብ ፣ ከመሃል ወደ ደቡብ ፣ከደቡብ ወድ ምስራቅ፣ ከሰሜን ወደ መሃል  ወዘተ፡ ለስራ፣ ለግጦሽ፣ ለግብርና፣ ለንግድ ልውውጥ፣ የቋንቋና የባህል መወራረሶች፡ በመዋለድ፡ በመዛመድ፡ በግጭትም ሆነ በሰላም  ማህበረስቦችን ያገናኘ፣ ያስተሳስረ ፡ በረጅም ዘመናት ግንኙነቶች ውርርሶች የተገመደ ፣ የተገነባም   ሀገራዊና ብሄራዊ ማንነት ነው ኢትጵያዊነት ።
ኢትዮጵያዊነት ዛሬ በምትገኘው ኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ ማህበርሰቦች ሀገራዊ መጠሪያ ብቻ ሳይሆን  በብዙ ሚልዮኖች የሚቆጠሩ  የኢትዮጳያ ልጆች  የህልውናቸው፣ የማንነታቸው መገለጻጫ ነው።  ኢትዮጵያዊነት በልዩ ልዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሚልዮኖችን ያስተሳሰረ ማንነት ነው። ኢትዮጵያዊነት በጸረ-ኢትዮጵያዊ የትግራይ ነጻ አውጭ አገዛዝና በተባባሪዎቹ በተቃጣበት የሰነልቦና የታሪክ ክህደት፣ የታሪክ ብረዛ፣ የባህልና የሞራል ሽርሸራ፣ ጦርነት  ብዙ ቢደማም፣  ብዙ ቢቆስልም ማንም ምድራዊ ሀይል ሊበጣጥሰው ያልቻለ ውስብስብ እና ረቂቀ ሆኖ ቀጥሏል። አሁንም  ለህልውናው እየተጋደለ ሲሆን፣ኝ በአንጻሩ የኢትዮጵያዊነት ጠላቶቹ እየተዳከሙ የመጡበት ውቅት ላይ  እንገኛለን።
የዚህ ትውልድ አባቶች፣ አያቶች ፣ቅድም አያቶች የሰሩዋቸው ታሪኮች በረጂም ዘመናት ሂደት የተገነባው የኢትዮጵያዊ ማንነት ግንባታ አካል ብቻ ሳይሆኑ እነዚህ አያት ፣ ቅድማያቶቻችን ደማቸውን አፍሰሰው ፣አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ህይወታቸውን ገብረው ኢትዮጵያዊነትን አለምልመውታል። በአለም ታሪክ በብቸኝነት የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎችን ተቋቁማ፣ ሀገራዊ ነጻነትዋን ጠብቃ የኖረች ኢትዮጵያ የምትባለውን ወብ አገር አውርሰውን አልፈዋል።  የአውሮፓ ወራሪ  ጣልያኖች ላይ በኢትዮጵያውያን መስዋእትነት የተገኘው ታላቁ የአድዋ ድል የዚህ ትውልድ  ቅድመ አያቶች መስዋአትነት ስለከፈሉ፣ ህይወት ሰለገበሩለት ነበር።  በባርነትና በቅኝ ተጘዥነት ሲማቅቁ ለነበሩ በአለም ዙሪያ ለሚገኙ የጥቁርና የአፍሪካ  ህዝቦች ትልቅ የሞራልና የስነልቦና መነቃቃትን የፈጠረው አንጸባራቂው የአድዋ ድል የአማራ፡ የኦሮሞ፡ የወላይታ ፡የትግሬ፡ የጉራጌ የከንባታና ሌሎች የጦር ኣበጋዞችና ከእነዚህ ማህበረስቦች የሄዱ ሰራዊቶች ለኢትዮጵያ አንድነትና ነጻነት ኢትዮጵያዊነትን በመገንባት የጋራ መስዋትንነት የተከፈለበት የድል ታሪክ እንጂ የአንድ ብቸኛ ዘውግ ወይንም ብሄር ብቻ የተገኘ ድል አይደለም። በኣድዋ ከዘመቱት የኢትዮጵያ የሰራዊት ኣባላት መካከል የዚህ ጸሃፊ በኣባቱ በኩል ቅደመ ኣያቱ የሆኑትንና ከትውልድ ቀዬቸው ከጌጃ ፡ ሸዋ  ተነስተው ከራስ መኮንን ጉዲሳ ሰራዊት ጋር በመዝመት ሀረርጌ  የሰፈሩትን የሸዋ ኦሮሞ  ኣቶ  ጃቶ ወለገራን ይጨምራል።
በሁለተኛውና 5 አመታት የቆየው የጣልያን ፋሽቶች የወራራ ዘመን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘን ያሳዩት  የአርበኝነት  ተጋድሎ፡ አኩሪ ጀግንነት ኣና  መስዋእትነት  ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ነጻነትና አንድነት የተደረገ፣ ለኢትዮጵያዊነት  የተከፈለ ዋጋ ነበር። ራስ አበበ አረጋይ በቸሬ በሸዋ ፣ኮ/ል አብዲሳ አጋ በጣልያን በረሃዎች፡ እንዲሁም ከወጣቱ ኣርበኛ ደጃዝማች አብቹ አስከ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ በጎጃም ፣ ከራስ አሞራው ውብነህ በጎንደር አስከ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፡ ከልጅ ሀይለማርያም ማሞ አስከ ሻለቃ በቀለ ወያ ፣ከጀ/ል ጃጋማ ኬሎ በሸዋ አስከ ኡመር ሰመተር የኢትዮጵያ አርበኞች የጀግነት ታሪክ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ነጻነት በኢትዮጳዊት የጋራ ብሄራዊ ማንነት ስር የሚገኝ ታሪክ እንጂ የአንድ ዘውግ ወይንም የአንድ ነገድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ብቻ ሊሆን አይችልም። እነዚህ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አርበኞ ያፈሰሱት ደም፡ የከስከሱት አጥንት ፡ የገበሩት ኣይተኬ የህይወት መስዋእትነት  የጋራች የሆነውን ኢትዮጵያውነትን ለማለምለም ግዙፍ አሰተዋጾ አድርጓል። በኣምስቱ ኣመት የፋሽስት የጣሊያን ወረራ ዘመን መስዋእትነት ከከፈሉትና ከኣርበኝነት ትግሉ በሁዋላ በህይወት ከተረፉት ኣርበኞች መካከል የዚህ ጸሃፊ በእናቱ እናት በኩል የወንድ ቅድመ ኣያቱ ባላምበራስ እሻግሬ ተሰማ በፋሽስቶች ጋር በተደርግው የኣርበኝነት ተጋድሎ የተሰዉ ፡ ባላንበራስ ደምሴ ተሰማ ታላቅ ወንድማችው እንደዚሁ የተስው፡ እናም በህይወት የተረፉትን ፊታውራሪ ተገኔ ተሰማ፡ ቀኛዛች ጥላሁን ተስማን ፡ “አጥሬ ተሰማ የባህር አዞ ጠላቱን ገዳይ ኣናዞ ኣናዞ” ተብሎ የተገጠመላቸውን ሻምበል ኣጥሬ ተሰማን ፡ የኣርበኝነት ገድላቸ የተጻፈላቸውንና ከመሰረታቸው ከሰሜን ሸዋ ኣማራ የሆኑትን ስባቱን ወንድማማች የባሌና የሀረር ኣርበኞች ይጨምራል።
ከሰባት ወራት በፊት ጀግናው የጎንደር ህዝብ  በጎንደር ከተማ ላይ ባቀጣጠለው ታላቅ ህዝባዊ የእቢተኝነት ተቃውሞ ሰልፍ የወያኔው መንጋ ለ25 ኣመታት የኦሮሞና የአማራን ነገዶች ለመነጣጠል ያንሰራፋውን የከፋፍለህ ግዛ ሴራ የበጣጠሰ ብቻ ሳይሆን፣ በአማራው ህዝብ ዘንድ የሚገኘውን ከአንድ ብሄር በላይ የሆነውን፤ ከሌሎቹ ብሄሮች ጋር የሚጋራውን ኢትዮጵያዊነት ያረጋገጠ ጭምር ነው፣ የወያኔ ስርአት በዘርጋው ክልላዊነት ለሃያ አምስት አመታት ሲሰብክ የኖረውን ብሄርተኝነትንም ሰብሮ የወጣ፣  መቋቋም የሚችል (Resilient)  ክስተት ሆኖም አይተናል።
ላለፉት 25 አመታት የተሰበከውን የኢትዮጰያን  የመቶ አመት ታሪክ ተረትነትም አጋልጧል። የአክሱም ሀውልት ለወላይታው   ምኑም  አይደለም በማለት  ለብዙ ዘመናት የተገነባውን ኢትዮጵያዊነትን በማሳነስ፡ በማንኳሰስ  ዓመታት ያስቆጠሩት የትግራይ ነጻ አውጪ ነን ባዮች ዛሬ  የኢትዮጵያዊነት፣ ሀገራዊ ማንነት ካባ በማጥለቅ እንደለመዱት ህዝብን ለማጭበርበር እየሞከሩ ይገኛሉ። እነዚሁ በጭካኔ የተካኑ መሰሪ ወያኔዎች ላለፉት 25 አመታት እንዳደርጉት ሁሉ አሁንም ኢትዮጵያና ህዝቦችዋ፣ ዜጎቹዋን ከዳር እስከዳር በጭካኔያዊ አርምጃዎቻቸው የማጥቃትና የማድማት ተግባራቸው ተጠናክሮ እንደቀጠለ ሁላችንም በየእለቱ የሚያመንና  የሚያንገበግበን እውነታ ቢሆንም፣  ኢትዮጵያውያንን በጅምላ እየፈጁ፣ ከዚያው 40 ዓመት ካረጁበት  የዘር ከረጢታቸውም ሳይወጡ የኢትዮጵያዊነት ሰባኪ  ሆነው ብቅ ብለዋል።  ።
በቅርቡም ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያውያንን ቤት አልባዎች በሚል  ከጥበትና የከድንቁርና ብቻ በሚመንጭ ድፍረት የተናገሩም ሰምተናል፡፡ ኢትዮጵያዊነት  ሁሉ ቤቱ ነው፡ የኢትዮጵያዊነት  ቤት ከሀረር እስከ ጎንደር  ፡ ከእንድብር እስከ ኢሉባቡር፣ ከጂማ እስከ መተማ ፣ ከወሎ እስከ ያቤሎ፡ ከወላቃይት አስከ ወልቂጤ ከኦሮሞ የቅደመ ኣያቴ ትውልድ ቦታ ከጌጃ፡ ሸዋ እስከ ጅጅጋ፡ ሀረር፡ ኣማራ ቅድሜ ኣያቶቼ መሰረታቸው ከሆነው ከቡልጋ ፡ ሸዋ እስከ ባሌ ጎባ  የኢትዮያውያና የኢትዮጵያዊነት ቤቱ ነው። ይህን  መብት የሚነቀንቅ ምድራዊ ሃይል አይኖርም። አራቱም የሀገሪቱ ማእዘናት  የኢትዮጵያዊነት ቤቶች ናቸው።
በዚህ ረጅም ዘመና ሂደት እንደማንኛውም ሌሎች ሀገሮች ታሪክ ታሪካችን ብዙ በጎ ጎኖች የነበሩት ቢሆንም  አሉታዊ ጎኖችም ነበሩት ፣ ታሪካችን አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ በእነዚህ አሉታዊ የታሪካችን ጎኖች ሳቢያ ኢትዮጵያዊነት ሁሉም የቋንቋና የባህል ማህበረሰቦች  በእኩልነት የኔም ነው የሚሉት፣ ባለቤትነት፣ ባለድርሻነት የሚሰማቸው የእድገት ደረጃ አልደረሰም ለማለት ይቻላል።  ምክነያቱም አድጎ ለምልሞ  አላለቀም ፣ ሂደት ነው።  ሁሉም አገሮች የተጓዙበት ሂደት የተለየ አይደም። ከእንግሊዝ ኣስከ ቻይና ከሩስያ እስከ ህንድ ገና ኣላለቁም። የሁለት መቶ ኣመት ታሪክ ያላት ዲሞክራሲያዊ ሰረት ከባርሪያ ኣሳዳሪ ኢኮኖሚ ጋር ተጣምሮ፣ የጡቁሮች፡ የሴቶችና ከኣንግሎ ሳክስን ውጭ የነበሩ ማህበረሰኖች ሲብደሉ የነበሩባት ሃያልዋ አሜሪካም ፡ የጎደሉ መብቶች፡ ነጻነችን በህገ መንግስታዊ አርምጃዎችና በህዝብ ትግል እያስተካከልች መጥታለች። ሂደቱዋን ግን ኣልጨረስችም።
ከላይ እንደተጠቀሱትና እንዳልተጠቀሱትን  የኣለም ሀገሮችና ህዝቦች የኛም ሂደት ወደ ሚቀጥለው እድገቱ የሚሸጋገረው ወያኔዎች እንደሞከሩት ኣሁንም በሁልም ጎራ የሚገኙ ጽንፈጮች እንደሚሞክሩት ያለፈውን በማፍረስ ወይንም በብሄር  ማንነቶች ብቻ እንዲተካ፣ እንዲሳሳ በማድረግ ሳይሆን ሁሉን አቃፊ ሁሉንም የቁዋንቋና ባህል ማህበረሰቦች እኩልት፡ የሚረጋገጥበት፣ አሳታፊ የሆነ ዲሞክራስያዊ  የፓለቲካ ስርአት  እውን ማደረግ ስንችል ነው። በቀላል ቋንቋ ኢትዮጵያ የሁሉም የጋራ እናት እንጂ እንጀራ እናት ያለመሆንዋን የሚያረጋግጡ ሁኔታዎች መፍጠር ሲቻል ነው። እስካሁን ይህን ማድረግ አልቻልንም,። በጥቁሩ ዓለም  ብቸኛው ሀገራዊ ነጻነት የነበራትን ሃገር ለህዝቧ፣ ለማህበርስቦቿ እኩልነት፣  ነጻነት የሰፈነባት ሀገር  ማድረግ ይገባናል።በዚህም ነው  ኢትዮጵያዊነትን ወደ ሚቀጥለው የእድገት ደረጃ ማሸጋገር የሚቻለው።
ኢትዮጵያዊነት ወደ ሚቅጥለው የእድገት ደረጃ ሊሸጋገር የሚችል ሁሉን አሰባሳቢ፣ ሁሉን አቃፊና አሳታፊ ዲሞክራሲ የፖለቲካ ስርአት በትግላችን መመስረት ሲቻል ብቻ ነው። ይህን ማድረግ ካልተቻለ እስከአሁን የነበው የጋራ ብሄራዊ ማንነት — ኢትዮጳያዊነት– እንዲሁም የኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነትም አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ ። በዚህ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን  ፊት የተደቀነው ትልቁ ፈተናም  የጋራ ቤታችን የሆነችው ኢትዮጵያን  የተጋረጠባት  አደጋ ነው፡፡ዛሬ ላይ የምንገኝ የዚህ ትውልድ ኢትዮጵያውያንም  እረፍት የነሳን ፣ እንቅልፍ ያሳጣን ይህ በኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነትና በኢትዮጵያዊነት ላይ የተቃጣው አደጋ ነው።
ስለዚህ ነው የጋራ ትግላችን ዋና ተልእኮ ይህን  አደጋ መመከትንና  መቀልበስ  ይሆናል።የሀገር  አደጋውን ልንቋቋም የምንችለው፣ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነት፣ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ማንነት ልምላሜና መጠናከር ዋስትና የሚሆነው ‘ ለሁሉም እኩል የሆነች፣ ሁሉም ዘውጎች፡ ሁልም ማህበረሰቦች የእኔም ናት የሚልዋት፤ መገለል፣ መገፋት፣ መረገጥ ያከተሙባት፤ ህዝቧ የስልጣን ባለቤት፣  ዜጎቿ ነጻ የሆኑባት፣ ባይተዋር ያልሆኑባት፣ ባለቤት የሚሆኑባት፣ የበይ ተመልካች ያልሆኑባት፣ ፍትሃዊ የስልጣንና የሀብት ክፍፍል የሰፈነባት፣ ሁሉም ተጠቃሚ ሁሉም የአገሪቱን ጸጋዎች፣ እሴቶች ባለድርሻ የሚሆኑባት፣ ሁሉም ማህበረስቦች/ በጠቅሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤትነቱ የተረጋገገጠበት ሀገረ መንግስት (state) ስንመሰርት  እና ይህ የሚገለጽበት ህገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት እውን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው። ይህን ሁኔታ በመፍጠር ብቻ ነው አገራችንን ከጥፋት ማዳን የሚቻለው።

የኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ነገዶች የቋንቋና የባህል ማህበርስቦች ሙሉ ክብርና እኩልነት የሚጎናጸፉባት ፣ ሀገራዊ ማነንታቸው ለዘመናት ሁለንተናዊ ግንኙነች የገነቡት ትስስርና ውርርስ እንዲጠናከር በባለቤትነት፣ በዜግነት መብቶቻቸው  ሀገራዊ የጋራ ብሄርተኝነት – ኢትዮጵያዊንትን የሚያዳብሩባት፡ በእኩልነት የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያ – የአማራው የኦሮሞው ፣ ጉራጌው፣ የከምባታው፣  የአፋሩ፣ የሶማሌው፣የኣንዋኩ  ወዘተ የሆነች ኢትዮጵያ – የሰው ልጅ በዘውግ ማንነቱ ብቻ ሳይሆን በቀዳሚነት ሰው በሰውነቱ ፡ በስብእናው በተፈጥሮና በፈጣሪ የተሰጡት ሁለንተናዊ ነጻነቶችና መብቶች  ከፍተኛ ክብርና ሞገስ የሚጎናጸፍባት ኢትዮጵያ ፡ የሰው ልጅ፡ የማናቸውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ መብት፡ ነጻነትና  ክብር የነገሰባት፣ እንክባብካቤ የሚደረግባት፡የሚነገሱባት፡ የሚንስራፉባት ኢትዮጵያን እውን ስናደርግ ነው።
ኢትዮጵያዊነት የጋራ ብሄራዊ ማንነት  የሚጠናከረውና የሚያብበው የተገፉ፡ በታሪክ ሂደት  ተገቢ የስልጣን ውክልና ያልተጎናጸፉ  ማህበረሰቦች በእኩልነት  በፖለትካ ስርአቱ በፍትሀዊ የስልጣንና  የሀብት ክፍፍል ባለድርሻ የሚሆኑበት ስርዓት ሲዘረጋ ነው፣በዲሞክራሲያዊ ህገ-መንግስታዊ ስራአት የተረጋገጡ መብቶች ሲሟሉ ብቻ ነው። ያኔ ሁሉም የኔም ነው የሚለው  ከቨርዥን 1.0 ወደ ቨርዥን 2.0 ( የኮምፑተር ሶፍት ዋር አናሎጂ ለመጠቀም) የተሸጋገረ የሁሉም የጋራ ማንነት የሆነ ኢትዮጵያዊነት ያብባል። የሚያድጉ የሚዳብሩ እርምጃዎችንና ግንባታዎች በማድረግ የኢትዮጵያ ጸጋና ውበት የሆኑትን ልዩ ልዪ ባህሎችና ቋንቋዎች የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሀበቶች ጭምር መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል። ይህ ሁሉ ዕውን የሚሆነው የ በዙሃን (pluralism in all its manifestations) ህብረ ቀለምን በአንድነት(unity with diversity) ማሰተናገድና ማቻቻል  የሚችል ዲሞክራሲያዊ የፖለካ ስራአት  ስንመሰርት ነው። ይህን የፖለቲካ መሰረት ስንጥል ነው በሙሉ ትኩረትና በሙሉ ጉልበት አገራችን ኢኮኖሚያዊ አድገትና የቴክኖሎጂ ምጥቀት ተጠቃሚ እንድትንሆን፡ እንዲሁም ሁለንተናዊ ልማትና የተፈጥሮ ሀብታችን እንክብካቤ  ላይ በማተኮር ከድህነትና ጠኔ ነጻ የወጣ ጤናማ ኩሩ ህዝብ ለመሆን  የምንችለው ።
ከማንም የአለም ሕዝቦች በላይ የኢትዮጵያ ህዝብና በውስጡ የሚገኙ ማህበርሰቦች  ጥንታውያን ናቸው። ጥንታዊ ግሪካዊያን የታሪክ ጸሀፊዎች  ኣንዱ የሆነው ሄሮዶተስ የታወቀውና ጥንታዊ ኢትዮጵያውያንን ኣስመልክቶ የሚጠቀሰው “the blameless Ethiopians where the Gods love to feast with” ኣማልክት ከኢትዮጵያውን ጋር ድግስ መብላት ይወዳሉ ብሎ ነበር የጻፈው። ነብዪ መሐመድ- ለአደጋ ተጋለጡ የእስልም ተከታዮችን  ፍትህ ወደ ማያጉዋድለው   ወደ ኢትዮጵያ ንጉስ ሂዱ በለው ነበር  የላኩዋቸው። ሌሎች በታሪክ የተመዘገቡና ኢትዮጵያን የሚያሳዩት በጥንት ዘመን  ብዙ ብጎ ምግባሮችና ጻጋዎች ማማ የነበረች ምድርም እንደነበረች ይገልጻሉ። አሁንም ኢትዮጵያዊያን የዚያን የሩቅ ዘመን ከፍተኛ ስብዕናና የፍትህ እሴቶች የሚበልጡ የፍትህ፡ እኩልነት፡ የሰው ልጆች  ነጻነት የነገሰባት ዘመናዊ ሀገር መገንባት የማንችልበት ምክንያት የለም።ለዘመናት የኖረውን ከኣለም ሀገሮች ብቸኛው ሀገራዊ ነጻነት የነበረን ህዝቦች የማህበርስቦች እኩልነት፣ የዚጎች ነጻነት የሰፈነባት ሀገር እንድትሆን ማሸጋገር ፡ስንችል ነው ኢትዮጵያዊነት ወደ ሚቀጥለው የእድገት ደረጃ የሚሸጋገረው። ሀገራዊ የነጻነት የዘመናዊ ታሪካችን በዜጎች ነጻነትና ፍትህ  መመንዘር፡ ለሁሉም ማህበሰቦች እኩልነትን ማሟላት ስንችል ነው።
ስለዚህ ትግላችን ይህን የጋራ ቤታችን የሆነችዋን ኢትዮጵያ አገራችንን የማዳን ትግል ነው፡፡ ትግላችን  ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያዊት ቤት የሆነችውን ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ማዳን ነው። ለኢትዩጵያዊነትና ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መታገል የንቅናቄያችን መብትም በውዴታ የገባንበትም ግዴታ ነው። ከወያኔ ፋሽስታዊ የጨካኞች ስርአት ጋር የመረረ የከረረ ሁለገብ/ሁለንተናዊ ትግል ማድረግ ያለብንም ይህን የተሻለ የህዝብና የዜጎች መብቶችና ነጻነቶች የሚረጋገጡባት የፓለቲካ ስርአት እውን ለማድርግ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ህልውና   አደጋ ውስጥ በመሆናቸውም ጭምር  ነው።
ይህንን ኢትዮጵያን  የማዳን ሀገር አድን ታላቅ ራዕይና ተልዕኮ ቃል ኪዳን የሚመጥን ቃልን ወደ ተግባር ፡ ዲስኩርን ወደ ተግባር የሚተረጉም እንቅስቃሴዎችን ከከፍተኛ አመራሮቹና  በሺ የሚቆጠሩ  አባላቱ እያደረገ ይገኛል። አመራሮቹ  ታጋዮቹ  ሆነው ሲገኙ፣ መስዋዕትነት ሲከፍሉ ሲያታግሉና ሲታገሉ ቆይተዋል።የአርበኞች ግንቦት 7 ሀገራዊ  ራዕይና ተልዕኮ ለትልቅ ሀገር ለመቶ ሚሊዮን ህዝባችንን የሚመጥነውን ዲሞክራሲዊ ስራአት እውን  ማድረግ ነው። ንቅናቄችን ብዙ መስዋትነት እየከፈለም ነው። ወድፊትም ይከፍላል። ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያን ለማዳን ለህዝብ ነጻነትና ለሁሉም ዜግጎች መሰረታዊ መብቶች ለሁልም ዘውጎችና ማህበረሰቦች እኩልነት መታገል ብሎም ምስዋዕትነት መክፈል አጅግ የምንኮራበት እንጂ የምናፍረብት፣ ግንባራችንንም የምናጥፍበት በፍጹም አይሆንም።
አርበኞች ግንቦት 7 ውስት የሚገኙ አባላት የተሰባሰቡት በኢትዮጵያዊነት ነጻነትና ፍትህ የጠማቸው ስለሆኑ እንጂ ዘር እየተቋጠሩ አይደለም። ንቅናቄያችን የልዩ ልዩ  ዘውጎችና ብሄሮች ተወላጅ የሆኑ አባላት ቢኖሩትም ራዕይው ሀገራዊ፣ ኢትዮጵያዊ ነው። የጋራቸው የሚያስተሳስራቸው ያሰባሰባቸው ለዘመናት የተገነባው  ከሁሉም ብሄሮች ማንነት በላይ  የሆነው ኢትዮጵያዊነታቸው ነው። የንቅናቄው አርማ የኢትዮጵያ አንድነት ነው። ኢትዮጵያዊነት ነው።  ግባችን ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርአት ነው።  ስለዚህም ነው አርበኛች ግንቦት 7 የወደፊትዋ ኢትዮጵያ በዜግነት እኩልነትና ነጻነት ላይ የተመሰረተ ሀቀኛ የዲሞክራሲያዊ ስርአት ለኢትዮጵያ አንድነትና በአገራችን ለሚገኙ ዘርፈ ብዙ ውስብስብ ችግሮች ብቸኛ አገር አድን የፓለቲካ መፍትሄ ነው ብሎ በጽኑ የሚያምነው የሚያቀነቅነው። መስዋእትነት በመክፈል  ላይ የሚገኘው።
ጥሪያችን ኢትዮጵዊነትና ኢትዮጵያ ሀገራችንን በትግችን ለማዳን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቆርጦ ለተግባራዊ ትግልና ኣስተዋጻኦ እንዲነሳ ነው!!
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት  ለዘላለም ይኖራሉ!! ፡በትግላችን መስዋእትነት  አንድነቱዋ የተጠብቀ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን!!

ኑው ዮርክ፡ ፊብሩዋሪ 17፡ 2017

Saturday, January 21, 2017

ሳይጀመር የተጨረሰው የኢህአዴግ ውይይትና ድራማው!!! | የኢ/ር ይልቃል ተወካዮች ለምን ከእረፍት በኋላ ተባረሩ?

January 21,2017
ይድነቃቸው አዲስ

ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አድርጋለው ካለበት ቀን ጀምሮ ስለ ጉዳዩ ያለኝን መረጃ ለጠየቃችሁኝ በሙሉ ነገሩን ከፈረሱ አፍ እንዲሉ እንደሚከተለው ላካፍላችሁ ወድጃለው።
ድራማው የሚጀምረው ጥር 9 2009 ዓ.ም ወደ 10፡55 አካባቢ ለኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በተንቀሳቃሽ ስልኩ ከኢህአዴግ ፅ/ቤት ስልክ የተደወለለት ዕለት ነበር። ደዋይዋ ስሟን ከተናገረች በኃላ የደውለችበትን ምክንያት ተናገረች። እንዲህ በማለት ” ኢህአዴግ ባዘጋጀውና ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ሊያደርግ ባሰበው ውይይት ላይ እርስዎ በሊቀመንበርነት የሚመሩትን ሰማያዊ ፓርቲን የጋበዝን ቢሆንም እስካሁን ድረስ በፓርቲው በኩል የሚሳተፉትን ሰዎች ስም ዝርዝር አላሳወቃችሁንም ስለሆነም ከውይይቱ በፊት መታወቅ ስላለበት ስም ዝርዝራቸውን ሊነግሩን ይችላሉ? ” ስትል አክብሮት በተላበሰበት ንግግር የደወለችበትን ምክንያት ገለፀች። በስልክ መልዕክቱ ግራ የተጋባው ይልቃል ጌትነትም ፓርቲው የደረሰው ምንም ዓይነት የተፃፈ ደብዳቤ እንደሌለ ገልፃ ለነገ ለሚደረግ ውይይት በዚህ ሰዓት መደወል አግባብ አለመሆኑን ይናገራል። ከኢህአዴግ ፅ/ቤት የደወለችው ሴትዮ “ምናልባት ደብዳቤው በስህተት ሌሎች እጅ ገብቶ ሊሆን እንደሚችልና ማንም እጅ ቢገባም እርስዎ የሚሰጡኝን ሁለት ተሳታፊ ሰዎችን ስም ልመዘግብ። እውነተኛ አመራሩን ከምርጫ ቦርድ አረጋግጬ ነው የደውልኩት ” ስትል ይቅርታ በሚጠይቅ ቅላፄ ዳግም ጥያቄዋን አቀረበች። የድምፅ ምልልሱ የይልቃል ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ይገኛል።
የእኔን እና የቀድሞው የፓርቲው ም/ሊቀመንበር እና የምርጫ ጉዳይ ሃላፊ የነበሩትን አቶ ስለሺ ፈይሳን እያቅማማ ቢሆንም አስመዘገባትና ንግግራቸው አለቀ። ወዲያው ተነጋግረን ከመቅረት ሄዶ አቋምን ማሳወቅ ተገቢ ነው የሚል መተማመን ላይ ደረስን። በማግስቱ ጥር 10 /2009 ዓ.ም የፓርቲያችንን አቋም ለማሳወቅ እኔ ይድነቃቸው አዲስ እና አቶ ስለሺ ፈይሣ ከጠዋቱ 2፡50 አካባቢ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቅጥር ግቢ በር ተገኘን። ከመግባታችን በፊት አቶ የሺዋስ አሰፋ ከመኢአድ አመራሮች ጋር በሩ ላይ ተገኝቶ ስሙ እንደሌለና የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ያስመዘገቡት የሁለት ሰዎች ስም ዝርዝር ተነገረው። “የፓርቲው ሊቀመንበር እኔ ነኝ እዚህ ስማቸው ያሉ ሰዎች የተባረሩና የዲሲፒሊን ግድፈት ያለባቸው ሰዎች ናቸው” በማለት ተከራከረ። በሩ ላይ በፌደራል ፓሊሶች ተከቦ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን መታወቂያ እያየና ከተመዘገበው ሥም ዝርዝር ጋር እያመሳከረ መግቢያና ማለፊያ ባጅ የሚሰጠው ግለሰብ ምንም ማድረግ እንደማይችል በቁጣ ተናገረና፤ ምንም ማድረግ በማይችለው ጉዳይ ላይ ባይጨቀጭቀው መልካም መሆኑን በመናገር ወደ ኃላ ገሸሽ እንዲል አሳሰበው።
(ፎቶ መፍቻ) ከሕወሓት ጋር ድርድር ተቀምጠው የነበሩት ‘ተቃዋሚዎች’::

ይህ ሲሆን እነ ፕሮፌሠር በየነ ጴጥሮስ እና ፣ ከመንግስት ቀለብ እየተሰፈረላቸው የሚኖሩ የውሸት ፓርቲ ባለቤቶች አጠገባችን ነበሩ። ዘወትር ሳያቸው በስሙ የሚነግዱባት ህዝብ ፍዳ ፊቴ ድግን ስለሚል ደሜ ይፈላል። ስለሆነም አተኩሬ ማየት እንኳን አልፈልግም። በሰዓቱ አንድ ስሙን የዘነጋሁት የፎርቹን መፅሄት ጋዜጠኛ መግባት ተከልክሎ ፓርቲያችን ውስጥ ስለተፈጠረው ጉዳይ ጠይቆኝ እያወጋን ነበር። በስተመጫረሻም መግቢያ በሩ ላይ ስማችን እንደተመዘገበና መግባት እንደምንችል ተነግሮን እኔና ስለሺ ፈይሳ ወደ ውስጥ ዘለቅን። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኘው መለስተኛ አዳራሽ ታደምን። ውይይቱ በግምት 3፡35 አካባቢ ይመስለኛል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ በሆኑት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ እና አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ መድረክ መሪነት ተጀመረ። አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የመክፈቻ ንግግር አደረጉ። ውይይት መልካም መሆኑን እና መንግስት በሠላማዊ መንገድ ተደራጅተው ካሉ ሃያ ሁለት አገራዊ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆኑን ገለፁ። ወደ ዝርዝር አጀንዳ ከመግባታችን በፊት በቀጣይ ስለሚኖረው ውይይት አካሄድ ምን መምሰል አለበት በሚለው ላይ ለመወያየት መድረኩን ክፍት አደረጉት። የመጀመሪያው ተናጋሪ ፕሮሬሠር በየነ ጴጥሮስ ነበሩ። ዘወትር በሚናገሩበት የቀዘቀዘ የድምፅ ቃና መድረኩን ኢህአዴግ መምራት እንደሌለበትና ባለፉት ወራቶች የሞቱት ወገኖቻችንን በማሰብ ውይይቱ ከመጀመሩ በፊት የህሊና ፀሎት ቢደረግ መልካም ነው በማለት ሃሣባቸውን ገለፁ። የመድረክ መሪው አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ባይፈቅዱም የውይይቱ ተሳታፊዎች በከፊል የፕሮፌሠር በየነ ጴጥሮስን አባታዊ ምክር ተቀብለን በራሳችን ፍቃድ ተነስተን ላተወሰኑ ሰኮንዶች ቆመን የህሊና ፀሎት አድርሠን ተቀመጥን።
በቀጣይ ስላለው አጠቃላይ አገራዊ ሁኔታና ስለ ውይይቱ ከተሣታፊዎች ሃሣብ ተሠነዘረ። ብዙዎቹ አሠለቺና ተደጋጋሚ ነበሩ። መንግስት ለሚዲያ ፍጆታ ብቻ ለማዋል መጥራቱን ገና ከጅምሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለእነ አየለ ጫሚሶ ፣ ትዕግስቱ አወሉ እና መሠሎቻቸው ደጋግመው ዕድል ቸሩ። እነርሱም መንግስት በአገሪቱ ላይ አስከፊ ችግር ከመከሰቱ በፊት የማረጋጋት ስራ መስራቱን አደነቁ። የኢዴፓው ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ ትንሽ የተሻለ ነገር መናገራቸውን አስታውሳለው። አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በመጀመሪያው ዙር እጅ አውጥተን ዕድል የሰጡን ቢሆንም አውቀው ይሁን ሳያውቁት ዘለሉን። ሁለተኛው ዙር ላይ እንደምንም ብለን ዕድሉን አገኘን። ከውይይቱ በፊት የተስማማንበት ሃሣብ ተናገረን እንዲህ በማለት ” በመጀመሪያ ደረጃ ውይይት መልካም ነው ብላችሁ ከልባችሁ አምናችሁ ከሆነ የጠራችሁትን እኛም የምንፈለገው ነገር ስለሆነ ጥሩ ነው። ፓለቲከኛ ሆኖ ውይይትን መግፋት አይቻልም። ግን አይመስለንም! እኛም እንሁን ፓርቲያችን ኢህአዴግን የሚያየው በጥራጣሬ መነፀር ነው። ይሁን ተጠራጥረን የትም ስለማንደረስ የምናምነውን ለመናገር እዚህ ተገኝተናል። ፓርቲያችን በመጀመሪያ እራሱ ገዳይና ችግር ፈጣሪ ሆኖ መታደስ አለበኝ ያለ ድርጅት መድረክ ይዞ እራሱ አወያይ ሆኖ መቅረቡን አይደግፍም። ይህም ውይይት የጥልቅ ተሃድሶ አካል አድርጎ ድርጅታችሁ ኢህአዴግ የሚያየው ከሆነ መታደሱ ለእናንተ እንጂ ለእኛ አያስፈልገንም። ሲቀጥል መንግስት እውነተኛ መፍትፍሄ ጠቋሚ ውይይት ከፈለገ ውይይቱ ውጭ ከሚገኙ ጠብመንጃ ካነሱትም ጋር ሆነ በሠላማዊ መንገድ የሚታገሉ ድርጅቶችን አጠቃሎ ማካሄድ አለበት። ውይይት በአገር ደረጃ ውጤት የሚያመጣው ስርዓቱ ትክክል አይደለም ብለው በምናምንበት መንገድ ለውጥ እናመጣለን ብለው እየሠሩ ያሉ ድርጅቶችን በሙሉ መሰብሰብ ሲችል ነው።
እንደ 1997ቱ ከፀሃይ በታች በማንኛውም ነገር ላይ እንወያየለን ተብሎ ጊዜ እንደተገዛበት አይነት መሆን የለበትም። ይህ አለመሆኑን በቀጣይነት ለህዝባችን የሚታይና የሚዳሠስ ማረጋገጫ መሠጠት አለበት። ካልሆነ የህዝብ ውክልና የሌላቸው ፓርቲዎች እንደ አሸን በፈሉበት ሁኔታ በህዝብ ስም መወያየትና በአብላጫ ድምፅ አቋም መያዝ ቀልድ ካልሆነ በቀር ተገቢ አይሆንም። መንግስት አስከፊ ደረጃ ከመድረሱ መታደሡ ተገቢ ነው የሚሉትንና ማህተማቸውን በኪሳቸው እየያዙ የሚዞሩትንም ትንሽ ሸንቆጥ አደረግናቻው። አንድ ቀን ዋጋ እንደሚያስከፍላቸውም ጭምር። የሚል የመጀመሪያ የሰማያዊ ፓርቲ ሃሣብ ተነገረ። ውይይቱ ከዛ በኃላ ብዙም ሳይቆይ የመድረኩ መሪ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የሻይ ሰዓት አልፎ ወደ አምስት ሰዓት እየተጠጋ ስለሆነ ለሻይ ሰዓት እንውጣ በማለት የመጀመሪያ ዙር ውይይቱ በሻይ ሰበብ እንዲቆም ሆነ። የሻይ ሰዓት ላይ ከእነ ፕሮፌሠር በየነ ጴጥሮስ ፣ የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ፣ አቶ ገብሩ ገብረማርያም ጋር ውይይቱ ቀጠለ። እኛ ሰሚ ነበርን። ፕሮፌሠር በየነ በሽግግሩ ጊዜ የነበራቸውን የፓለቲካ ታሪክና የኢህአዴግ አታላይናትን አካፈሉን። በሰማያዊ ፓርቲ የቀረበውን ሃሣብም እንደሚደግፉት ለእኔና ለስለሺ ነገሩን። እንደውም በአራዳ ቋንቋ ህዝቡ በአሁን ሰዓት እኛን ከመንግስት ጋር እየተሞዳሞድን አድርጎ እንዳይስለን ስጋታቸውን አካፈሉን።

ትንሽ ፈገግ እንድንልም አደረጉን። ሻይ ቡናው ላይ ቆፍጠን ብለው ታዩኝ። ምናል መድረኩ ላይም እንዲህ ቢሆኑ ብዬ ተመኘሁ። የሻይ ሰዓቱ ስላለቀ በግምት ወደ አምስት ከሩብ አካባቢ ወደ አዳራሹ ገባን። ከመንግስት ሚዲያዎች በቀር የግል ህትመት ሚዲያዎች እንዲገኙ ስላልተፈለገ ይመስለኛል አልተጋበዙም። ለሁለተኛው ዙር ውይይት የቀድሞው ቦታችንን ያዝን። ድንገት በመሃል ከፍ ባለ ድምፅ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ሰማያዊን ወክላችሁ የመጣችሁ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች አንድ ጊዜ ወደ ውጭ ኑልን” አሉን። የውይይቱ ተሣታፊዎች ትኩረት በሙሉ ወደ እኛ ሆነ፤ ዝምታ ቤቱን ዋጠው። በነገሩ ግራ የተጋባነው እኔ እና ስለሺ ምን አስበው ይሆን ? በሚል መንፈስ ከአዳራሹ በራፍ ተገኘን።
አቶ ሽፈራው ራቅ ብለው ከቆሙ ሶስት ጋርዶች ጋር ጠበቁን። እንደወጣን ለምን እንደተጠራን አቶ ሽፈራውን ጠየቅናቻው ። አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ድምፃቸውን ቀንሰው “እናንተ እውነተኛው የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች አይደላችሁም የሚል መረጃ ደርሶኝ ነው። ስለሆነም ከአሁን በኃላ በስብስባው መካፈል አትችሉም” አሉን። እኛም የመጣነው ለይልቃል ተደውሎላት እንደሆነና እኛም የፓርቲው የማዕከላዊው ኮሚቴ አባል እንደሆንን ገለፅንላቸው። “እሱ ስህተት ነው አሁን ከምርጫ ቦርድ ፅ/ቤት ሃላፊ ድውዬ እንዳረጋገጥኩት እናንተ እውነተኛ አመራሮች አለመሆናችሁ ተነግሮኛል” በማለት እንድንወጣ አሳሰቡን። አርግ የተባሉትን ከሚያደርጉ ግለሠብ ጋር ብዙም ጊዜ ማጥፋቱ መፍትሄ እንደሌለው በመረዳታችን የግቢውን ቅጥር ግቢ ለቀን ወደ 5፡35 ወጣን። ይሁን እንጂ አቶ የሺዋሥ አሠፋና ግብረአብሮቹ ከወጣን በኃላ ተደውሎላቸው በጓሮ በር ገብተው መሣተፋቸውን አውቀናል። ህዝብ ምንግዜም አሸናፊ ነውና ህዝብን ማዕከል ያላደረገ ውይይት መጨረሻው ሽንፈትና ቅሌት ብቻ ይሆናል ብዬ አምናለው። የውይይቱም የመጨረሻ ገጽ ከቀድሞ የውይይት ታሪኮች የተለየ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ድል የህዝብ ነው! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች !!