Saturday, April 29, 2017

ኦባንግ ሜቶ ከከፋ አደጋ ተረፉ!

April 29, 2017

  • “ዳግም የመኖር እድል ተሰጠኝ፤ ተማርኩበት፤ እናንተም ተማሩ”
“ጥቁሩ ሰው” ኦባንግ ሜቶ በሁሉም ስፍራ፣ በየትኛውም አጋጣሚ ለሚፈልጋቸው ሁሉ “አለሁ” የሚሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው። ዘረኝነትን፥ ዘውገኝነትን፥ ጎሠኝነትን አጥብቀው ይዋጋሉ። ይጸየፉታል። ከዘር ቆጠራና ከቂም የጸዳች ኢትዮጵያን ማየት ህልማቸውና የመጨረሻ ግባቸው ነው።
ሰብዓዊነት ለአፍታም ከአንደበታቸው የማይለይ፣ በሚያውቋቸው ሰዎች ሁሉ የሚወደዱ፣ ግልጽ ተናጋሪነታቸው ልዩ የሚያደርጋቸው ኦባንግ በዚሁ ባህሪያቸው “አባ ነቅንቅ” የሚል ስም ተሰጥቷቸዋል። በስደት ለሚሰቃዩ የኢትዮጵያ ልጆች /እሳቸው ቤተሰቦቼ የሚሏቸው/ በጠሯቸው ቦታና ሁሉ በመገኘት ለሚያሳዩት ትጋት አቻ የላቸውም። ኢትዮጵያን በመወከል በከፍተኛ ቦታዎች የሚሟገቱ፣ ያዘነውን የሚጎበኙ፣ ለሴት እህቶቻችን ቀድመው የሚደርሱ እኚህ ውድ ሰው በድንገተኛ የመኪና አደጋ ተዓምር ሊባል በሚችል አጋጣሚ ከሞት የመትረፋቸው ዜና ስንሰማ ደንገጠናል። እርሳቸው ብቻ ሳይሆኑ አብሯቸው የነበረ ባልደረባቸውም ከዚህ ዘግናኝ አደጋ አምልጧል።
ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ሚያዚያ 14 2009ዓም /22.04.2017 ከዋሽንግተን ዲሲ ወጣ ብሎ የደረሰባቸውን የመኪና አደጋ አስመልክቶ “ዳግም የመኖር ዕድል ተሰጠኝ፤ ተማርኩበት፤ እናንተም ተማሩበት። ዜናው የእኔ ከአደጋ መትረፍ ሳይሆን በቅጽበት የምትሰናበተውን ህይወታችንን በሚገባ ልንጠቀምበት እንደሚገባ መማሩ ላይ ነው” ሲሉ ነበር የገለጹት።
“አዎ” አሉ ጥቁሩ ሰው። “አዎ! ሞትን ለቅጽበት አየሁት። እንዳልወሰደኝ ስረዳ ሰዎች በቅጽበት ታሪክ እንደሚሆኑ በመረዳት በህይወት ዘመናቸው ደግ ለመስራት ለራሳቸው አለመማላቸው አሰብኩ” ሲሉ መልዕክታቸውን የጀመሩት ኦባንግ “እንኳን ነገ፣ በደቂቃዎች ምን እንደምንሆን ማስተማመኛ በሌለበት ሁኔታ ሰዎች ስለበቀልና ሌላውን ስለማጥፋት ስልት እየነደፉ ለመኖር መምረጣቸው አሳዘነኝ”።
ይህንን ሲናገሩ “የሚጸጽተዎ ነገር አለ እንዴ?” የሚል ጥያቄ ሰንዝረን ነበር። ኦባንግ ግን መልሳቸው ሌላ ነው። “እኔ ጸጸት ብሎ ነገር አላውቅም። የምጸጸትበት ነገርም ስለመፈጸሜ አስቤ አላውቅም። ነገር ግን ለወገኖቼ መሥራት የሚገባኝን እንዳልሰራሁ አስባለሁ። በተለያዩ ምክንያቶች ያስብኩትን ያህል አልተጓዝኩም። ይህ ከጸጸትም በላይ ነው። ምክንያቱም ዘረኝነትን ረግጠንና ቀብረን መጓዝ አለመቻላችን መድሃኒት የሌለው የቅዠት ተስቦ በሽተኛ አድርጎናል” ብለዋል። በውል የማይታወቅ ዘመን ወደኋላ በመሄድ ለአሁኑ ትውልድና ለአገራችን በማይጠቅም ጉዳይ ላይ ጉልበት፣ ሃብትና ጊዜ እየባከነ መሆኑንን የጠቆሙት ጥቁሩ ሰው “ከዚህ አዙሪት ሳንወጣ ሞት ይወስደናል፥ ለትውልድ የማይድን ቁስል ትተን፥ ትውልዱን መርዝ ወግተን እናልፋለን” ይላሉ።
ተፈጥሮ በጥድፊያ ወደ ሞት እየገፋችን ባለበት ሰዓት ሰው ሌላውን ስለመበቀልና ስለማጥፋት ዕቅድ ይዞ መስራቱ ከምንም ነገር በላይ ልብ የሚሰብር እንደሆነ ኦባንግ በሃዘኔታ ነው የገለጹት። “የማውቃቸውም ሆነ የማላውቃቸው በርካታ ወዳጅ ቤተሰቦች እንዳፈራሁ አውቃለሁ። ይህን ዜና ሲሰሙ እንደሚያዝኑ እረዳለሁ። ከዜናው በላይ ግን ለሚሰሙ ትምህርት እንዲሆን ይህንን መልዕክት ለማስተላለፍ ስል መናገርን መርጫለሁ። ዳግም የመኖር ዕድል ስለተሰጠኝ የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ስል ከሞት መልስ የተማርኩትን አካፍያለሁ። ለሚሰማ ትልቅ ጉዳይ ነው” ሲሉ ማሳሰቢያ አዘል መልክታቸውን ኦባንግ አስተላልፈዋል።
ከዘርና ከዘረኛነት ቋት ወጥተው “ከጎሳ በፊት ሰብዓዊነት” በሚል አዲሲቷ ኢትዮጵያ ልትተከልበት የሚገባውን መርህ የሚያቀነቅኑት ኦባንግ “መለስ ሲነገረው ቢሰማና ለአንድ ቀን ቀና ሰው ስለመሆን ቢያስብ፣ ብለን ብንመኝ ቢያንስ በቅርቡ ያለቁትን በሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን ነፍስ ማትረፍ፣ እየሰፋ የመጣውን የጎሳ በሽታ መቀነስ በቻልን ነበር። ግን ያሳዝናል በተቃራኒው ነው የሆነው። ያለመውንና ያሰበውን ሳያይ ህይወቱ በጥላቻና በዘረኝነት እንደመረረች ሄደ” ሲሉ የቀናነት እጥረት በሽታ ክፋት ያስረዳሉ።
የኮምፒውተር እቃ ለመግዛት አንድ መደብር ደረሰው ሲመለሱ የ18 ዓመት ወጣት ሴት በፍጥነት እያሽከረከች ሊያመለጡት በማይችሉበት ሁኔታ ተምዘግዝጋ ኦባንግ የሚያሽከረክሩትን መኪና በሳቸው በኩል ጎኑንን መታችው። ወጣቷ በከፍተኛ ፍጥነት ላይ ስለነበረች የኦባንግ መኪና ምቱ እንዳረፈባት ወደ ጎን ተገለበጠች። በመጨረሻም የአውራ ጎዳናው ጠርዝ መኪናዋን ያዛትና በቋፍ ተደግፋ እግሯን ሰቅላ ተገልብጣ ቆመች። የመውጫ በሮቹ በሙሉ ተቀርቅረውና ተጨረማምተው ስለነበር ዕርዳታ ሰጪዎች ባደረጉት ድጋፍ ኦባንግና ባልደረባቸው በኋለኛው በኩል ባለው የእቃ መጫኛ በር ሾልከው እንዲወጡ ተደረገ።
አደጋው ከደረሰ በኋላ አካባቢው ላይ የነበሩ ሰዎች እያነቡ ውስጥ የነበሩት እነ ኦባንግ ሲወጡ ሰላም መሆናቸውን ሲመለከቱ መገረማቸውን መስክረዋል። ፖሊስም ያለ አንዳች ጭረት፣ ደም፣ ስብራት፣ … ኦባንግና ባልደረባቸው መትረፋቸው “ድንቅ” ተብሎ ሊገለጽ እንደሚችል ሁኔታዎች ከተረጋጉ በኋላ ተናግሯል። እንደ ፖሊስ ገለጻ መኪናዋ ከተመታቸበት ቦታ ትንሽ ወደ አሽከርካሪው ተጠግቶ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ኦባንግ “ከሞት መልስ ተማርኩ” ለማለት እንደማይበቁ ይሆኑ ነበር። ይህንኑ አስመልክቶ ጥቁሩ ሰው “በፈጣሪ ኃይል ከሞት ተረፍኩ፣ ዳግም የመኖር ዕድል ተሰጠኝ ያልኩት ለዚህ ነው” ብለዋል።
አያይዘውም በቀናነት፣ በታማኝነት፣ በጸዳ ህሊና፣ በሃቅ፣ በመታመን፣ ለአገርና ለህዝብ ከመስራት የበለጠ የሚያኮራ ነገር እንደሌለ ተናገረዋል። በዘርና በጎሳ ተቧድነው፣ ጥላቻን መነሻ መሠረታቸው አድርገው፣ ሌላውን ለማጥፋትና ለመበቀል ዝግጅት እያደረጉ ላሉ፣ ዘመኑ በውል በማይታወቅ ጊዜ ወደኋላ ተመልሰው ቂምን የሚያራግቡና የክፋት ዘርን የሚረጩ ሁሉም ቆም ብለው በማሰብ ራሳቸውን ወደ መግዛት ብልኃትና ጥበብ እንዲመለሱ ጥሪ አስተላልፈዋል።
እሳቸው ከሞት አፋፍ መልስ የተማሩት ይህንን ነውና በግላቸው ከቀድሞው በላይ ራሳቸውን ለህዝብ እንደሚያስረክቡም ቃል ገብተዋል። ዜናውን አስቀድማ የነገረችን ምስክር “ኦባንግን ማጣት እንደ አገር ክስረት ነበር የሚሆነው። ኦባንግ ጀርባቸው የጸዳ፣ ለሚፈለገው ዓይነት ኃላፊነት የሚታመኑ፣ ታላቅ ራዕይ ያላቸው፣ ከነፈሰው ጋር የማይነፍሱ፣ ራሳቸውን ሆነው በነጻነት የሚኖሩ፣ የአንደበት ሳይሆን የተግባር ሰው የሆኑ … ኢትዮጵያዊ” ስትል ገልጻቸዋለች። አያይዛም “ከሚሠሩት ከፍተኛ ሥራ 10 በመቶውን ብቻ አደባባይ የሚያወጡ፣ ጊዜና ትውልድ በሰዓቱ ክብር የሚሰጣቸው ሰው እንደሆኑ አምናለሁ። የተረፉትም ለዚሁ ዓላማ ነው” ስትል ይህንን የተናገረችው የሚሰሩትን ሥራ ሁሉ በቅርብ ጠንቅቃ ስለምታውቅ መሆኑንንም አመልክታለች።
ኢትዮጵያን አስመልክቶ በከፍተኛ ቦታዎች በዝግ ስለሚሠሩት ሥራ ለምን በአደባባይ እንደማይገልጹ በተደጋጋሚ ኦባንግ ተጠይቀው “ገና ምን ሰራን፣ ሥራው ራሱ ሲገልጸው ማየት ይሻላል” የሚል መልስ በዚሁ ገጽ ላይ መመለሳቸው አይዘነጋም።
የመኪናውን አደጋ ያደረሰችው የ18 ዓመት ወጣት ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባት ለመረዳት ተችሏል። የመኪና አደጋ ሲደርስ ሰዎች በአብዛኛው እርስበርስ ሲካሰሱና ሲሰዳደቡ በተደጋጋሚ የታየ ቢሆንም በዚህ አደጋ ወቅት ኦባንግ ልጅቷን በማረጋጋትና በማጽናናት የፈጸሙት ተግባር የልጅቷን ቤተሰቦችና ባካባቢው የነበሩትን ሁሉ ያስደመመ እንደነበር በቦታው የነበሩ የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
የዝግጅት ክፍላችን ለአቶ ኦባንግ፣ ለባልደረባቸውና ለልጅቷ፣ እንዲሁም ለወዳጆቻቸው ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ ይላል።
ከጎልጉል የድረ ገጵ ጋዜጣ የተወሰደ

No comments: