Saturday, July 15, 2017

የአዲስ አበባ አስተዳደር መሬት አጥረው ባስቀመጡ ኤምባሲዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ መቸገሩ ተገለጸ

July 15,2017
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአዲስ አበባ መሬት አጥረው ባስቀመጡ የተለያዩ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ መቸገሩን መረጃዎች ጠቆሙ፡፡ በከተማዋ ለረዥም ጊዜ መሬት አጥረው ካስቀመጡ አካላት መካከል፣ የውጭ ሀገር ኤምባሲዎች፣ የሼህ ሁሰይን አሊ አላሙዲን ንብረት የሆነው ሚድሮክ ኢትዮጵያ፣ የመንግስት ተቋማት እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ እነዚህ አካላት የከተማዋን አንድ ሶስተኛ ሊያክል ምንም ያልቀረው መሬት በመውረር ያለ ምንም ስራ አጥረው አስቀምጠዋል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብለት የቆየው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ አሁንም ምንም ዐይነት እርምጃ አለመውሰዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በከንቲባ ድሪባ ኩማ የሚመራው የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ መሬት አጥረው ከያዙ አካላት ጋር ለውይይት ተቀምጦ እንደነበር ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወቃል፡፡ ሆኖም መረጃዎች እንደጠቆሙት ከሆነ፣ በወቅቱ የተደረገው ውይይት ምንም ዓይነት ውጤት አላመጣም፡፡ በዚህም የተነሳ ስማቸው የተጠቀሱት አካላት እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የከተማዋን መሬት እንደወረሩ ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡ በዚህ ሳምንት ስብሰባውን ያካሔደው የከተማዋ አስተዳደር፣ በጉዳዩ ላይ ውይይት እንዳደረገ ቢገለጽም፣ መሬት አጥረው የያዙ አካላትን በተመለከተ የረባ ሪፖርት አላቀረበም፡፡
አስተዳደሩ ሰፋፊ መሬት አጥረው ከያዙ ኤምባሲዎች እና ሚድሮክ ኢትዮጵያ ይልቅ በትናንሽ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መውሰዱን ነው የገለጸው፡፡ ለረዥም ጊዜ መሬት አጥረው ለያዙት ኤምባሰዎች እና ሚድሮክ ኢትዮጵያ ግን ወደ ስራ እንዲገቡ በድጋሚ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ብቻ ተሰጥቷቸው ታልፈዋል፡፡ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው ሲባል ይህ ለበርካታ ጊዜ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ህጋዊ ባለ ይዞታ የሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ድንገት ተነስቶ በማፈናቀል እና ቤት በማፍረስ የሚታወቀው የከተማዋ አስተዳደር፣ ኤምባሲዎች እና ሚድሮክ ኢትዮጵያ ላይ ሲደርስ አቅም እንደሚያጥረው ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ 

በከተማዋ 138 አካላት 150 ሄክታር መሬት አጥረው የያዙ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ሰፊውን ድርሻ የሚወስዱት የውጭ ኤምባሲዎች፣ ሚድሮክ ኢትዮጵያ እና የመንግስት ተቋማት ናቸው፡፡ ሆኖ,ም አስተዳደሩ እርምጃ ወሰድኩኝ ያለው ግንባታ ባልጀመሩ ትናንሽ ባለሀብቶች ላይ ብቻ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በ13 ባለይዞታዎች ላይ ክሰ መሰረትኩኝ ያለው የድሪባ ኩማ አስተዳደር፣ ከ43 ባለሀብቶች ጋር ደግሞ ያለውን ውል በማቋረጥ መሬታቸውን መንጠቁን አስታውቋል፡፡

Source: BBN News July 13, 2017

No comments: