Thursday, July 27, 2017

በሙስና ከታሰሩ ባለስልጣናት መካከል የተወሰኑት ስም ዝርዝር ታወቀ | ይዘነዋል

July 27,2017

በአዲስ አበባ ታትሞ የሚወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ እንደዘገበውና ዜና አቅራቢው ፋኑኤል ክንፉ እንዳጠናቀረው  በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 34 ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ባለሀብቶችና ደላሎች፤ በትላንትናው ዕለት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢፌዴሪ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አስታወቀ::
የጽ/ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ትላንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ 34 የሚሆኑ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ባለሀብቶችና ደላሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ኃላፊዎቹ ተጠርጥረው የተያዙት “በፖሊስ፣ ዐቃቤ ህግና በፌደራልና አዲስ አበባ ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች በተደረገ የማጣራት ስራ የሙስና ተግባር ውስጥ ተሳትፈው በመገኘታቸው መንግስት ሙስናን ለመከላከል በያዘው ቁርጠኛ አቋም ነው፤” ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል::
በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ  ኃላፊዎች ከተገኙባቸው የመንግስት  ተቋማት መካከል፤ የፌደራል መንገዶች ባለስልጣን፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ ስኳር ኮርፖሬሽን እና የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መስሪያቤቶች ጋር ይገኙበታል፡፡
የሰንደቅ ምንጮች እንደገለጽት፣ በስኳር ኮርፖሬሽ በኩል ተጠርጥረው ከተያዙ መካከል  የቀድሞው የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ አበበ ተስፋዬ እና የቀድሞው የተንዳሆ የፋይናንስ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ድምፁ እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡ እንዲሁም፣ አቶ በኃይሉ ገበየሁ የኮርፖሬሽኑ ንብረት አስተዳደር ዳሬክተር እና አቶ ኤፍሬም አለማየሁ የቀድሞ የኮርፖሬሽኑ፣ ግዢና ንብረት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዳሬክተር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ግዢ ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ግርማ፤ እንዲሁም ወ/ሮ ሠናይት ወርቁ እና አቶ ኃየሎም ከበደ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ማዋላቸው ታውቋል፡፡
አንድ የቀድሞ ሚኒስትር እና አንድ ሚኒስትር ዴኤታም ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ምንጮቻች የጠቆሙን ቢሆንም፣ ከሚመለከታቸው አካላት ለማረጋገጥ አልቻልንም፡

No comments: