November 10,2014
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
ባለፈው ሳምንት ባቀረብኩት ትችቴ (እ.ኤ.አ በ1984 የተከሰተው የኢትዮጵያ ታላቁ ረኃብ ሲታወስ፡ ክፍል1)፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት ረኃብን በማስመልከት ሳቀርባቸው በነበሩት ትችቶች የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ እና አሁን በህይወት የሌለው መሪው መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ ከ1991 ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት ረኃብ የለም በማለት ሙልጭ አድርገው በመካድ ሲያደርጉት የነበረውን ተራ ቅጥፈት በማጋለጥ በተጨባጭ መረጃዎች ላይ በመመስረት ስሞግት የቆየሁባቸውን ዋና ዋና ጭብጦች በማካተት ክለሳ ማድረጌ ይታወሳል፡፡ መለስ እና ጓደኞቹ ከዓለም አቀፍ ለጋሾች እና አበዳሪ ድርጅቶች ጋር በመሞዳሞድ ለረኃብ ስያሜ የተለያዩ የማስመሰያ እና የማደናገሪያ ስሞችን በመስጠት በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ተንሰራፍቶ ህዝብን ሲፈጅ እና ሲያሰቃይ የቆየውን ረኃብ በመደበቅ በሀገሪቱ ውስጥ በየትኛውም ቦታ ቢሆን እንደሌለ አድርገው በረኃብ ሲሰቃዩ በቆዩት እና በረኃቡ ምክንያት ባለቁት ወገኖቻችን ላይ ሸፍጥ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ለዚህም አጽንኦ በመስጠት በኢትዮጵያ ያለው ረኃብ የፈለገውን ያህል በማስመሰያ እና በማደናገሪያ ቃላት እና ሀረጎች ተሸፋፍኖ እና ታጅቦ ቢቀርብም ያው አሁንም ቢሆን ረኃብ ነው! በማለት ማጠቃለያ መስጠቴ የሚታወስ ነው፡፡
በዚህ በክፍል ሁለት ትችቴ ደግሞ እ.ኤ.አ ከ1984 – 85 ድረስ ህወሀት በተከሰተው በታላቁ ረኃብ ምክንያት የረኃብ ሰለባ ለሆኑት ወገኖች ነብስ ማዳኛ ለሰብአዊ እርዳታ የመጣውን እርዳታ ለጦር መሳሪያ ግዥ እና ለግል ጥቅም ለማዋል ሲያደርገው የነበረውን የዥዋዥዌ ጨዋታ ለመዳሰስ ሞክሪያለሁ፡፡ በመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ ሜይ 2011 በሁፊንግተን ፖስት “ለመስረቅ ፈቃድ ማግኘት” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት የመጀመሪያ ትችት ህወሀት የሰረቀ መሆኑን ከሁለት የቀድሞ የህወሀት የአመራር አባላት ጋር የተደረገን ቃለ መጠይቅ ዋቢ በማድረግ ለሰብአዊ እርዳታ ተብሎ የመጣን የእርዳታ እህል ከታለመለት ዓላማ ውጭ ህወሀት ለመሳሪያ መግዣ እና ለሌላ ለግል ጥቅሙ ያዋለ መሆኑን በማጋለጥ ትችት አቅርቤ ነበር፡፡ ይህ ቡድን እ.ኤ.አ በ1984 ጫካ በነበረበት ጊዜ የጀመረው የዓለም አቀፍ የእርዳታ ስርቆት፣ ዘረፋ እና ሙስና የማይላቀቁት መናጢ አመል ሆኖበት አሁንም እስካለንበት ጊዜ እስከ 2014 ድረስ በተለያየ እና በተወሳሰበ መልኩ ቀጥሎ ይገኛል፡፡
“አሊ ባባ”፣ መለስ እና 40 የህወሀት/ማረት (TPLF/REST) የ1984- 85 የእርዳታ እህል እና ዶላር ሌቦች እና ዘራፊዎች፣
እ.ኤ.አ በ1984 – 85 በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው አስከፊ እና አሰቃቂ ረኃብ ምክንያት የረኃቡ ሰለባ ለሆኑ ህዝቦች በሚል ከዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ሩብ ሚሊዮን ዶላር ተሰብስቦ ነበር፡፡ ያ ረኃብ እጅግ በጣም አስከፊ ገጽታ ያለው እና ባልተጠበቀ መልኩ የተከሰተ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ1984 የትግራይን አካባቢ የጎበኘው የቢቢሲው ጋዜጠኛ ሚካኤል ቡርክ የረኃቡን አስከፊነት እንደሚከተለው ገልጾት ነበር፣ “የ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ረኃብ“ እና “በመሬት ላይ ለሲኦል የቀረበ ነገር“፡፡
እ.ኤ.አ በ1984 – 85 በአማጺያን ኃይሎች እንቅስቃሴ እና በደርግ ወታደራዊ አምባገነን መንግስት የአውሮፕላን ድብደባ ምክንያት በትግራይ ክልል እና በሌሎች የሰሜን ኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታን በተለመደው የእርዳታ አሰጣጥ ሁኔታ ማቅረብ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ በርካታ የዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ለጋሽ ድርጅቶች እርዳታውን አማጺያን ቡድኖች በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች በአስከፊው ረኃብ የጥቃት ሰለባ ለሆኑት ወገኖች ፈጣን በሆነ መልኩ የህይወት አድን እርዳታውን ለማድረስ ሌሎች ተለዋጭ መንገዶችን እና ዘዴዎችን ማግኘት ነበረባቸው፡፡
እንደ አማራጭ በመውሰድ በርካታዎቹ መንግስታዊ ያልሆኑ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ለረኃብ ጥቃት ሰለባ ለሆኑ ወገኖች በቀላሉ ምግብ ማድረስ እንዲቻል በማሰብ በምስራቃዊ የሱዳን ጠረፍ በትግራይ ወሰን አካባቢ የማከፋፈያ ጣቢያ ከፈቱ፡፡ በሱዳን ወሰን አካባቢ በርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች በብዛት መከማቸት እና ገንዘብ በማዋጣት እረገድ ይደረጉ በነበሩት የህዝብ ግንኙነት ጥረቶች ምክንያት ለህወሀት አመራሮች እና ለአማጺያኑ ወታደሮቻቸው ትርፋማ የሆነ የንግድ አጋጣሚ ፈጠረላቸው፡፡ አማጺያኑ እነርሱ በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ጥሩ የእርዳታ ማስተላለፊያ መንገዶች እንዳሉ በማሳወቅ እና የእርዳታ እህሉንም ሆነ ሌላ ማንኛውንም ዓይነት ቁሳቁስ እነርሱ ማከፋፈል ቢችሉ ስራው የተሳካ እንደሚሆን እና ለዘለቄታው ውጤታማ እንደሚሆኑ መንግስታዊ ላልሆኑ ለጋሽ ድርጅቶች ሀሳብ አቀረቡ፡፡
የቀድሞው የህወሀት የገንዘብ ግምጃ ቤት ኃላፊ የነበሩት እንደ ገብረመድህን አርአያ እና የአማጺያኑ መስራች የነበሩት እንደ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ገለጻ ከሆነ የህወሀት ቁልፍ መሪዎች መለስ ዜናዊን ጨምሮ በዓለም አቀፍ የረኃብ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች አማካይነት በረኃቡ ሰለባ ለሆኑት ተብሎ የተመደበውን በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር የእርዳታ እህል የማጭበርበሪያ ስልት ነድፈው ከተያዘለት ዓላማ ውጭ ለጦር መሳሪያ መግዣ እና ለግል ጥቅማቸው አዋሉ፡፡ ገብረ መድህን እና አረጋዊ ግልጽ እንዳደረጉት መለስ እና ቁንጮ ካድሬዎቹ አንድ የማጭበርበሪያ ዕቅድ በመንደፍ የሰብአዊ እርዳታ የሚያቀርብ ድርጅት በሚል ማህበረ ረዲኤት ትግራይ/ማረት (Relief Society of Tigray/REST) ተብሎ የሚጠራ የማስመሰያ እርዳታ ሰጭ ድርጅት አቋቋሙ፡፡ ውስጡ ለቄስ ነው እና በአንድ ወቅት አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ እንዳለው የዚህ ድርጅት ልብ እንደ ፈጣን ሎተሪ ተፍቆ ቢታይ እንደ ስሙ እርዳታ ሰጭ ድርጅት እንዲሁም ለሰው ልጆች ክብር በፍቅር ተቃጥሎ ህይወትን ለማዳን ከልቡ የሚሰራ ርህራሄን የተላበሰ እውነተኛ ሰብአዊ ድርጅት ሳይሆን ሌባ፣ ዘራፊ እና በቅጥፈት የተሞላ የማፊያ ድርጅት ሆኖ ይገኛል፡፡ በዚያን ወቅት የህወሀት አመራሮች ማረት ከህወሀት ወታደራዊ ክንፍ ጋር ፈጽሞ ግንኙነት የሌለው እና የተለዬ ሀቀኛ የእርዳታ ሰጭ/አከፋፋይ ለጋሽ ድርጅት እንደሆነ በማስመሰል የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶችን ለማሳመን ሌት ከቀን ጥረት አደረጉ፡፡ እውነታው እንደሚያሳየው በእርግጥ ማረት እና ህወሀት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በስደት በውጭ ሀገር የሚኖሩት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ የህወሀትን የረቀቀ የእርዳታ ማጭበርበር ባህሪ ለቢቢሲ ጋዜጠኛ ለማርቲን ፕላውት እንዲህ በማለት ገልጸው ነበር፣
“… አንዳንድ ጊዜ የእርዳታን ገንዘብ እንደ ሁለተኛ አማራጭ በመውሰድ የጦር መሳሪያ እንገዛበት ነበር፡፡ ገንዘቡ ካለህ መካከለኛው ምስራቅ በመምጣት መሳሪያ መግዛት ትችላለህ፡፡ ስለሆነም የተወሰነውን ገንዘብ ለመሳሪያ ግዥ በማዋል እንጠቀምበት ነበር፡፡ ይህንን ማረት እየተባለ በአህጽሮ ቃል የሚጠራውን ድርጅት ታውቀዋለህ፣ ሲተነተን ማህበረ ረድኤት ትግራይ ማለት ነው፡፡ የህወሀት የሰብአዊ እርዳታ ክንፍ ነው፣ እና በማረት ስም የእርዳታ ገንዘብ ወደ ህወሀት ይመጣ ነበር፡፡ ከዚያ ይህንን የእርዳታ ገንዘብ ካገኘህ በኋላ ለእርዳታ፣ ለጦር ግንባር ወይም ደግሞ ለጦር መሳሪያ ግዥ፣ ለመድኃኒት፣ ወዘተ በሚል በጀት ታዘጋጃለህ፡፡ የእርዳታን ገንዘብ ትግሉን ለማስቀጠል እንጠቀምበት ነበር ለማለት እችላለሁ፡፡
ከዚህም በላይ በብዙ ሚሊዮን ስለሚቆጠር ዶላር ጉዳይ እንነጋገር ነበር፡፡ ለዚህ አንድ ተጨባጭነት ያለው ምሳሌ ልነግርህ እችላለሁ፡፡ እ.ኤ.አ በ1985 ትግራይ አሰቃቂ በሆነ ረኃብ በተጠቃች ጊዜ የእርዳታ ገንዘብ በማረት በኩል አድርጎ ወደ ህወሀት ይጎርፍ ነበር፡፡ ስለሆነም ከሞላ ጎደል አንድ ዓይነት ዓላማ ያላቸው እና ምንም ዓይነት ልዩነት የሌላቸው ማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ትግራይ/ ማሌሊት/Marxist Leninist League of Tigrai (MLLT) እና የህወሀት አመራሮች 100 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለተለያዩ ተግባራት እንዲውል መመደብ ነበረባቸው፡፡ በዚህም መሰረት መለስ ዜናዊ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነው ለህወሀት እንቅስቃሴዎች፣ 45 በመቶ የሚሆነው ለማሌሊት ማደራጃ እና 5 በመቶ የሚሆነው ብቻ በረኃብ ሰለባ ለወደቁት ተረጅዎች መዋል አለበት የሚል ሀሳብ አቅርቦ እንደነበር አስታውሳለሁ…እነዚህን ሁለት ሰዎች (አርዓያ ገብረመድህን እና ተክለወይነ አሰፋ) አውቃቸዋለሁ፡፡ የህወሀት ተዋጊዎች ናቸው፡፡ አንዱ እራሱን ነጋዴ በማስመሰል ይቀርባል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከነጋዴው ማሽላ የሚገዛ በመምሰል ይቀርባል፡፡ ሁለቱም የህወሀት ነባር ካድሬዎች ናቸው፣ እናም ነጋዴ ለመምሰል ትወና በመተወን ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሚተወኑት ገንዘቡን ለማግኘት ሲባል ነው፡፡ [በፎቶግራፉ ላይ ከላይ የሚታዩት የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካይ የነበረው ፔርቤዲ ከመካከል ሆኖ የታሰረ ረብጣ ብር ለተወካይ ተብዬዎች ሲያስታቅፍ ነበር] እናም ይህ ዜጋ መቶ በመቶ ተታሏል፡፡”
ገብረ መድህን የዓረጋዊንን ሀሳብ ትክክለኛነት አረጋግጠዋል፡፡ ገብረ መድህን (ከላይ በስዕሉ ላይ በስተግራ በኩል ሆነው ገንዘብ ሲቆጥሩ የሚታዩት) እራሳቸው በግንባር በመቅረብ በመቶዎች እና በሺዎች የሚቆጠር ዶላር ለመለስ ዜናዊ እና እንደ እባብ ተስለክላኪው እና የህወሀት የክርስትና አባት ለሆነው ለስብሀት ነጋ በወቅቱ በእጃቸው ያስረከቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሁለቱ የህወሀት አድራጊ ፈጣሪዎች መለስ እና ስብሀት የህወሀትን የገንዘብ ፍሰት ይቆጣጠሩ ነበር፡፡ ገብረመድህን የህወሀት ዋና የገንዘብ ኃላፊ ሹም የነበረ ቢሆንም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በእርዳታ ስም የሚመጣውን ገንዘብ ለመለስ እና ለስብሀት ካስረከበ በኋላ ስለገንዘቡ አወጣጥ እና ከጥቅም ላይ እንዴት ሆኖ እንደሚውል እንዲያውቅ አይደረግም ነበር፡፡ ያም ሆነ ይህ ገብረመድህን ገንዘቡ በትክክል ለታለመለት ዓላማ ጉዳይ ስለመዋሉ እና አለመዋሉ ጥርጣሬ ነበረው፡፡ ሆኖም ግን የጥፋተኝነት ማስረጃው (ሁለቱን የህወሀት ካድሬዎች እና ማክስ ፔርቤዲ የተባለውን ከእንግሊዝ መንግስታዊ ያልሆኑ የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች መካከል ታላቅ ከሆነው የክርስቲያን እርዳታ/Christian Aid ተብሎ ከሚጠራው ተወካይ እጅ እየቆጠሩ በመረከብ በወለሉ ላይ በትልቅ ቦርሳ ውስጥ በርካታ ገንዘብ ሲያጭቁ የሚያሳየው ፎቶግራፍ) በምንም ዓይነት መልኩ ማስተባበያ ሊቀርብበት የማይችል አስደንጋጭ ነገር ነው፡፡
የችግሩን ስፋት እና ጥልቀት እንዲሁም የረኃቡን አስከፊነት እና አሳሳቢነት መንግስታዊ ላልሆኑት እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች በውሸት በትወና መልክ ለማሳየት ሲባል የህወሀት አመራሮች እጅግ ብዛት ያለውን የረኃብ ሰለባ ህዝብ ከትግራይ ወደ ሱዳን በማምጣት በኢትዮ-ሱዳን ሰሜናዊ የድንበር አካባቢዎች ላይ በአንድ ጀንበር ምሽት እንደ አሸን የፈሉ የእርዳታ መስጫ ጣቢያዎችን በማዘጋጀት የተረጅዎችን ቁጥር ከመጠን በላይ አበዙት፡፡ የተለያዩ ዘዴዎችን እና ስልቶችን በመጠቀም የህወሀት አመራሮች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በትግራይ ውስጥ በረኃብ ለተጠቃው ህዝብ የእርዳታ እጃቸውን እንዲሰነዝሩ ለማስቻል ዝርዝር የሆነ የገበያ ተውኔት በማዘጋጀት ለመድረክ እይታ አበቁ፡፡ ይህ የተደረገው ለእነርሱ በጣም ታማኝ የሆኑ የድርጅቱን ጥቂት የውስጥ አባላት በመምረጥ እና በማደራጀት የእህል ነጋዴ ሆነው እንዲቀርቡ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እርዳታ የማሰባሰብ ንግድን ማጧጧፍ ነበር፡፡
መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የማታለሉ ጨዋታዎች ወይም ደግሞ የበለጠ ግልጽ ለማድረግ የምዕራቡን ዓለም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የረኃብ እርዳታ የማታለል ዕቅድ የተለያዩ መገለጫዎችን ያካተተ ነበር፡፡ በማጭበርበሩ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ የህወሀት አመራሮች ሶስት ደረጃዎችን ያካተተ ሂደትን ተጠቅመዋል፡፡ በመጀመሪያው ደረጃ አንድ የህወሀት/ማረት የባለስልጣኖች ቡድን ህጋዊ የእህል ነጋዴዎች በመምሰል በርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ይቀርባሉ፣ እናም በረኃብ ለተጠቃው ህዝብ እርዳታ በፍጥነት እንዲደርስ በርካታ ብዛት ያለው እህል እንዲሸጥላቸው ይጠይቃሉ፡፡ በዚያን ጊዜ የህወሀት አታላዮች በመቶዎች የሚቆጠሩ ከባድ የጭነት ማምላለሻ መኪናዎች ያገኙ እና በጣም ሚስጥራዊ በሆነ መልኩ ከመሬት ውስጥ በተዘጋጀ ሰፊ ማጠራቀሚያ ከተለያዩ ምንጮች ያገኗቸውን የእርዳታ እህሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ጨምሮ ለእራሳቸው ተዋጊዎች መጠቀሚያ በሚል ያጭቁታል፡፡ እነዚህ በከባድ ሚስጥር ከመሬት ውስጥ ታጭቀው የሚገኙ የእህል ቁልሎች በእርግጠኝነት ዓላማው መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ለመሸጥ ነው፡፡ የህወሀት/ማረት እህል አዳዮች መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር እህልን ለመሸጥ ይደራደራሉ፣ ከዚያም ሽያጩን ያጠናቅቁ እና ከሽያጩ ያገኙትን በርካታ ገንዘብ ተሸክመው እህሉን ወደ ደበቁበት ቦታ ይመለሳሉ፡፡ ገብረመድህን እራሳቸው በዚህ እህል የመግዛት እና የመሸጥ ትወና ላይ የእህል ማደል ቀጥተኛ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ከዚህ አንጻር የእርሳቸውን ሚና እንዲህ በማለት በግልጽ አስቀምተውታል፣
የሙስሊም ነጋዴ እንድመስል የሙስልም ልብሶች እንድለብስ ይሰጡኝ ነበር፡፡ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እኔን አያውቁኝም ምክንያቱም የእኔ ስም መሀመድ ነበር፡፡ ይኸ ስም የመቀየር የማጭበርበር ስራ የተደረገው መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለማታለል በህወሀት የበላይ አመራሮች የተዘየደ የማጭበርበሪያ ስልት ነበር፡፡ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በርካታ የሆነ ገንዘብ እቀበል ነበር፣ እናም የተቀበልኩት ገንዘብ ወዲያውኑ በህወሀት መሪዎች ይወሰድ ነበር፡፡ ከወሰዱት ገንዘብ ውስጥ በርካታውን የህወሀት አመራሮች በግል የሂሳብ ቁጥራቸው በምዕራብ አውሮፓ ባንኮች ያስቀምጡ ነበር፡፡ ከዚህ ገንዘብ ጥቂቱ ደግሞ ለመሳሪያ መግዣ ያውሉት ነበር፡፡ የአስከፊው ረኃብ የጥቃት ሰለባ የሆነው ተረጅው ህዝብ ግማሽ ኪሎ ግራም ያህል በቆሎ እንኳ አያገኝም ነበር፡፡ አንድ ጊዜ የእህል መግዛቱ ስራ ከተከናወነ በኋላ ሌላው የህወሀት/ማረት ቡድን ደግሞ የተገኘውን የእርዳታ እህል በትግራይ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች በመሄድ የማከፋፈሉን ስራ ይሰራል፡፡
በሁለተኛው ደረጃ የተዋቀረው የህወሀት/ማረት ባለስልጣኖች በሚስጥር ከመሬት ውስጥ ያከማቹትን የእህል ክምችት ድንገተኛ ፍተሻ በማድረግ ስራውን ያቀላጥፋሉ፡፡ ሆኖም ግን የእህል ማስቀመጫ መጋዘኑ በሌላ ማሳሳቻ ነገር ተሞልቶ ይቀመጣል፡፡ ገብረመድህን እንዲህ ብለው ነበር፣ “እዚያ ብትሄድ ግማሽ የሚሆነው የመጋዘኑ የእህል መያዣ ጆንያ በአሸዋ ተሞልቶ ነው የሚገኘው“ ገብረመድህን እንዳሉት ከሆነ የመንግስታዊ ያልሆኑ የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ተወካይ ወደ መጋዘኑ ከመጣ በኋላ በችኮላ እና በዓይን ውጫዊ የገረፍ ገረፍ እይታ ብቻ በመመልከት የእራሱን መተማመኛ ይሰጣል፣ ከዚያም ክፍያ ፈጽሞ ወደ ሱዳን ተመልሶ በመሄድ ሌላ ተጨማሪ እህል ለመግዛት ዝግጅቱን ያደርጋል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ የተመደበው አንድ ዓይነት ወይም ደግሞ ሌላ የህወሀት/ማረት ቡድን ወደ መንግስታዊ ያልሆኑ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ይሄድ እና ወደተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች በመውሰድ ለህዝቡ ማደል እንድንችል ሌላ ተጨማሪ እህል እንዲሸጥልን በማለት ሌላ የውሸት ማታለያ መጫወቻ ሜዳ በማዘጋጀት ጥያቄውን ለእርዳታ ሰጭ ደርጅቶቹ ያቀርባል፡፡ በዚህን ጊዜ ከእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች የተገኘው አዲስ የእርዳታ እህል ወደተባለው ህዝብ እንዲሄድ አይደረግም፡፡ ይልቁንም ከመሬት ውስጥ ባለው መጋዘን ውስጥ ታጭቆ የሚገኘው እህል ወደ ሌሎች የትግራይ የተለያዩ ክፍሎች እንዲሄድ በማድረግ መንግስታዊ ላልሆኑት የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ግን አዲሱ እና ከዚያ ተገዝቶ እንዲሰጥ የተባለውን እህል ያሰራጩ እና ያከፋፈሉ በማስመሰል የማታለል ስራቸውን በስፋት ይቀጥላሉ፡፡ የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ነጻ በሆነ መልኩ የተሰጠው እርዳታ ወደ እርዳታ ፈላጊው ህዝብ ሄዶ በትክክል መከፋፈሉን የሚያረጋግጡበት ምንም ዓይነት መንገድ ስለሌላቸው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለሚጓጓዘው ተመሳሳይ የማደናገሪያ እህል ሁሉ ይከፍላሉ፡፡ በዚያ መልኩ የረቀቀ የማታለል ዘዴን በመጠቀም ህወሀት/ማረት ቀደም ሲል የነበራቸውን የእህል እና የአሸዋ ክምችት ብዙ ጊዜ መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ደጋግመው በመሸጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር በገቢነት ይሰበስባሉ፡፡
ማርቲን ፕላውት ከቢቢሲ በሰሜን ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ ተከስቶ የነበረውን ረኃብ እ.ኤ.አ ማርች 2010 ባወጣው ዘገባው እ.ኤ.አ በ1985 የሲአይኤ መረጃ ያወጣውን ዋቢ በማድረግ እንዲህ የሚል መደምደሚያ ሰጥቶ ነበር፣ “ለተራቡት ወገኖች እርዳታ በሚል የሽምቅ ተዋጊዎች የሚያሰባስቡትን እርዳታ ዓለም በስፋት እያወቀው ሲመጣ እና የእርዳታው መጠንም እየጨመረ ሲመጣ ለእርዳታው ተብሎ የሚመጣው ሁሉ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ለጦር መሳሪያ መግዣ ይውል ጀመር፡፡“ በ1980ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ሮበርት ሁደክ የተባሉ በኢትዮጵያ የዩኤስ አሜሪካ ነባር ዲፕሎማት የህወሀት አባላት በዚያን ወቅት ለእርዳታ የሚሰጣቸውን እህል ለመሳሪያ መግዣ ያውሉ ነበር በማለት የተናገሩትን ቢቢሲ እንዳለ ቃላቸውን ወስዶ እንዲህ በማለት ዘግቦ ነበር፡፡ “አንድ ማክስ ፔቤርዲ የሚባል የእርዳታ ሰራተኛ በግንባር በመገኘት ለህወሀት/ማረት ባለስልጣኖች 500,000 ዶላር በኢትዮጵያ ገንዘብ ተቀይሮ እህል እንዲገዙበት በእጃቸው የሰጣቸው መሆኑን ተናግሯል“ በማለት ገልጸው ነበር፡፡
ገብረመድህን በጽሁፋቸው በዝርዝር ግልጽ እንዳደረጉት እ.ኤ.አ በ1984 – 85 ተከስቶ የነበረውን ታላቁን ረኃብ ሰበብ በማድረግ ህወሀት አብዛኛውን እርዳታ ለመሳሪያ መግዣ እና ለአመራሩ አባላት የግል ጥቅም አውለውታል የሚለው የመጀመሪያ ማስረጃ አሳማኝ ይመስላል (የገብረመድህንን ክፍል አንድ የአማርኛ ጽሁፍ እዚህ ጋ ይጫኑ፡፡ ለክፍል ሁለት ደግሞ እዚህ ይጫኑ)
የህወሀት የእርዳታ ስርቆት እና እርዳታውን ለሌላ ዓላማ ማዋል የሚለውን ፕሮፌሰር ሀሰን ሰይድ “መንግስታዊ ጥቃት በኢትዮጵያ፡ ሰብአዊ እርዳታ እና ሙስና“ (መነበብ ያለበት ጽሁፍ) በሚል ርዕስ ባዘጋጁት ዝርዝር እና ጥልቀት ባለው ጥናታዊ ጽሁፋቸው ውስጥ እንዲህ የሚል ማጠቃለያ ሰጥተዋል፣ “በጥናቴ ውስጥ የመረመርኳቸው ሰነዶች እና ያደርግኋቸው ቃለ መጠይቆች እንዲሁም የሰበሰብኳቸው የምስክርነት ማስረጃዎች እንደሚያረጋግጡት ለጋሽ እና እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ማህበረ ረድኤት ትግራይ/ማረት ከህወሀት ጋር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን እንደሚያውቁ የሚጠቁሙ መሆናቸው፣ እንደዚሁም ደግሞ የህወሀት እና የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ሰራተኛ ለሰብአዊ እርዳታ ተብሎ የሚመጣ እርዳታ ለመሳሪያ ግዥ እና ለጦር ግንባር ዓላማ ይውል እንደነበር ያውቁ ነበር…“
በዚህ አሳፋሪ እና የወረደ ድርጊት ስህተት ውስጥ ተሳትፈው የነበሩት መቅንየለሾች ማስረጃዎችን ቆሻሻ በማለት ዘለፋ ከማቅረብ ውጭ በእውነተኛ መረጃ ላይ በተመሰረተ መልኩ አጣሪ እና እውነታ አፈላላጊ ኮሚቴ በማቋቋም ማስተባበል እና እራሳቸውን ከዚህ ከባድ እና ጠንካራ ክስ ነጻ ማድረግ ተስኗቸው ቀርቷል፡፡ እውነት በሀሰት ተቀብራ አትቀርማ! እንደዚህ ያለ ምርመራ እስከሚካሄድ ድረስ የእርዳታ ምንተፋ ስግብግብነት እና ሌብነት የማይደፈር እና ሊስተባበል የማይችል መደበኛ ዘረፋ ሆኖ የቆያል፡፡ ቦብ ጌልዶፍ እ.ኤ.አ በ1984 የሙዚቃ ባንድ በማስተባበር በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለእርዳታው እንዲሰበሰብ አድርጓል፣ የረኃብ እርዳታው በተሳሳተ መልኩ ለጦር መሳሪያ መግዣ ውሏል እየተባለ የሚሰማውን ውንጀላ ምክንያት በማድረግ እንዲህ ብሎ ነበር፣ “ምንም ዓይነት ገንዘብ ያለአግባብ የጠፋ ካለ የኢትዮጵያን መንግስት በህግ እጠይቃለሁ፡፡“
እ.ኤ.አ በ1980ዎቹ አጋማሽ (እንዲሁም ባለፉት 23 ዓመታት) መንግስታዊ ካልሆኑ የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች በአስር ሚሊዮኖች የሚሆን ለእርዳታ የተመደበ ዶላር የህወሀት አታላዮች ለራሳቸው ተራ ተስፈኝነት፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር በብልጣብልጥነት እየዘረፉ ለግል ጥቅማቸው እና ለመሳሪያ መግዣ ያዋሉትን ሰው ዝም ብሎ በዘፈቀደ ሊያደንቅ ይችላል፡፡ እውነት ለመናገር አሊ ባባ እና የእርሱ 40 የወያኔ ሌቦች እንደዚህ ዓይነት ብልጣብልጥነት የተሞላበት የማጭበርበር ዕቅድ በመጠቀም መንግስታዊ ላልሆኑ የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች እራሳቸው እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች የለገሱትን እህል እና አሸዋ የተሞላባቸውን ጆንያዎች እየደጋገሙ መሸጥ አልነበረባቸውም፡፡ የግሪክ የሌቦች አምላክ የነበረው ሄርምስ እንኳ እንደዚህ ያለ በጣም የሚያስገርም ዕንከንየለሽ የሸፍጥ ዕቅድ በማውጣት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለመውሰድ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለማታለል እና በቀላሉ ለማሞኘት አልቻለም ነበር፡፡ የህወሀት አመራሮች “አዲስ የአፍሪካ የሌቦች ዝርያ” የሚለው ስም የሚገባቸው ነው፡፡
ማረት የህወሀት ባተሌ ፍጹም አያውቅ እረፍት፣
በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ የምግብ እርዳታ በሶስት የውጭ መንግስታዊ ያልሆኑ የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች በብቸኝነት ይተዳደራል፡፡ እነርሱም ምግብ ለተራቡ/Food for the Hungry (FH) (እራሱን የክርስቲያን ድርጅት/Christian Organization እያለ የሚጠራ እና እ.ኤ.አ ከ1971 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ድሆችን በመርዳት ላይ ያለ)፣ የህጻናት አድን ድርጅት/Save the Children (እራሱን የዓለም የተቸገሩ ህጻናት ቁንጮ እርዳታ ሰጭ ድርጅት እያለ የሚጠራ)፣ የካቶሊክ እርዳታ አገልግሎት/Catholic Relief Services (CRS) (በዩናይትድ ስቴትስ ለካቶሊክ ማህበረሰብ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅት) እና ማህበረ ረድኤት ትግራይ/ማረት የሚባል አንድ የሀገር ውስጥ መንግስታዊ ያልሆነ እርዳታ ሰጭ ድርጅት ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ1984 – 86 የረሀብ ሰለባ ለነበሩ ወገኖቻችን ከእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ቀርቦ የነበረውን የምግብ እርዳታ ያለምንም ይሉኝታ በረሀብተኞች ጉሮሮ ላይ በመቆም የተለያዩ ሸፍጦችን እና የማታለያ ዘዴዎችን እየፈበረከ ሙልጭ አድርጎ የበላ እና ለእራሱ የውንብድና ሀራራው የመሳሪያ ግዥ ያዋለ ማህበረ ረድኤት ትግራይ/ማረት የተባለው ያው ድርጅት አሁንም በ2014 በኢትዮጵያ ለተከሰተው ረሀብ ዓይን ባወጣ መልኩ እርዳታ አከፋፋይ ሆኖ ቀርቧል፡፡ የሌባ ዓይነደረቅ መልሶ ልብ ያወልቅ እንዲሉ!
እ.ኤ.አ በ2010 እና በ2014 (እንዲሁም ከ2010 በፊት) ማረት ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆን የምግብ እርዳታ ተቀብሎ በማከፋፈል ስራው ላይ ተሳታፊ የነበረ ብቸኛው የሀገር ውስጥ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ እ.ኤ.አ ኦገስት 15/2014 ዩኤስኤአይዲ/USAID እንዳወጣው ዘገባ ከሆነ ዩኤኤአይዲ በእራሱ ምግብ ለሰላም ጽ/ቤት/Office of Food for Peace እያለ በሚጠራው ጽ/ቤቱ በኩል እ.ኤ.አ በ2014 ለማረት እና ለሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች 237 ሚሊዮን ዶላር፣ እ.ኤ.አ በ2013 ደግሞ 236 ሚሊዮን ዶላር፣ እ.ኤ.አ በ2012 ደግሞ 307 ሚሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ በ2011 ሌላ 313 ሚሊዮን ዶላር እና እ.ኤ.አ በ2010 ደግሞ 452 ሚሊዮን ዶላር አድሏል፡፡
ማረት እስከ አሁንም ድረስ እራሱን “የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ/ህወሀት የሰብአዊ እርዳታ ክንፍ” አድርጎ ይቆጥራል፡፡ በእርግጥ ማረት እ.ኤ.አ በ2014 በሞኖፖል የያዘ መንግስታዊ ያልሆነ የሀገር ውስጥ ድርጅት እና ልክ እ.ኤ.አ በ1984 ሲያደርግ እንደነበረው ሁሉ በኢትዮጵያ ይህንን ግዙፍ የሆነ ዓለም አቀፍ እርዳታን በማጭበርበር በእራሱ የማስተላለፊያ ቱቦ ለህወሀት የሚያስተላልፍ በእርዳታ ሰጭ ድርጅት ስም የሀሰት ጭምብላ ያጠለቀ መንታፊ ድርጅት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ዓለም አቀፋዊ እርዳታን ለማከፋፈል የሚወዳደሩ ሌሎች ሀገር በቀል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሉም፡፡ በእርግጥ የበጎ አድራጎት እና ማህበራት አዋጅ እየተባለ የሚጠራው መንግስታዊ ተቋም በኢትዮጵያ ያሉትን ሁሉንም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሲያከስም (እ.ኤ.አ በ2010 አዋጁ ከወጣ በኋላ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ብዛት በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከ4,600 ወደ 1,400 ወርደዋል) ለማረት ጥሩ እድል በመፍጠር ምንም ዓይነት ተቀናቃኝ የሌለው ብቸኛው የሀገር ውስጥ ጠቅላይ ለመሆን በቅቷል፡፡
እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ምሁር ዘገባ ከሆነ ማረት የህወሀት የገንዘብ እና ቁሳቁስ ማስተላለፊያ ቱቦ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የህወሀት የንግድ ግዛት የመነሻ ካፒታል ከተለያዩ ምንጮች ይመጣል፡፡ አንዱ እና ዋናው የማስተላለፊያ ምንጩ የረኃብ እርዳታ የህወሀት ክንፍ የሆነው ማህበረ ረድኤት ትግራይ (ማረት) ነው፡፡ ማረት የእርዳታ ገንዘብን እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ካልተጠበቁ እና በፈቃዳቸው ከሚሰጡ የውጭ የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች በመቀበል ገንዘብ እና ቁሳቁሶችን ወደ ህወሀት የገንዘብ ሳጥን ውስጥ የሚያስተላልፍ ድርጅት መሆኑ በስፋት ይታወቃል፡፡
የበጎ አድራጎት ድርጅት አዋጅ እየተባለ የሚጠራው መንግስታዊ ተቋም የሚያሳየው እውነታ አገር በቀል የሆኑ እና በሀገር ውስጥ መንቀሳቀስ የሚችሉት በህወሀት ስር ተጠቃለው የተያዙ ወይም ደግሞ ሌሎች ከህወሀት ጋር ወይም እርሱ ከሚፈልግላቸው ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመንቀሳቀስ የሚችሉ ድርጅቶች ብቻ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ1984 ህወሀት በማረት በኩል ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ እርዳታን ለመሳሪያ መግዣ እና ለግል ጥቅሙ አውሏል፡፡ እ.ኤ.አ በ2014 ህወሀት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታን በማረት በኩል በመጠቀም አሁንም ለግል ጥቅሙ በማዋል ላይ ይገኛል፡፡ ምን ያህል! ነገሮች የበለጠ በተለዋወጡ ቁጥር የበለጠ አንድ ዓይነት እየሆኑ ይሄዳሉ!
ከመላ አፍሪካ ዩኤስኤአይዲ ትልቅ የእርዳታ ፕሮግራም ያለው በኢትዮጵያ ነው፡፡ ባለፉት 23 ዓመታት ብቻ በአስር ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ለህወሀት በእርዳታ ስም የተሰጠው ገንዘብ ከምን ላይ ዋለ? ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ እዕምሮን የሚበጠብጥ አስቸጋሪ ይሆናል! ማንም ሊያውቅ አይችልም፡፡ ዩኤስኤአይዲ/USAID እራሱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወደ ህወሀት የገንዘብ ካዝና ውስጥ የሚረጨው እንኳ አያውቀውም! ለዚያም ነበር የዩናይትድ ስቴትስ የመንግስት መምሪያ ጽ/ቤት ኢንስፔክተር በዘገባቸው ላይ እንዲህ የሚል መደምደሚያ የሰጡት፣ “የዩኤስኤአይዲ ኦዲት የምርመራ አገልግሎት የኢትዮጵያን የግብርና ምርታማነት ተግባራት (የኦዲት ዘገባ ቁጥር 4-6663-10-003-P (እ.ኤ.አ ማርች 30, 2010)“ በሚከተለው መልክ አስቀምጦታል፡
….የኦዲት ኢንስፔክተር [የግብርና ዘርፍ ምርታማነት] ፕሮግራም የገበያ መር የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣቱን እና ገበሬዎች፣ አርብቶ አደሮች፣ እና ሌሎች በኢትዮጵያ የሚገኙት ተጠቃሚዎች ሁሉ መሻሻል እያሳዩ መሆናቸውን በጥናቱ አግኝቷል፡፡ ሆኖም ግን ያ የተገኘው ውጤት ምን ያህል እንደሆነ በአፈጻጸም አያያዝ እና የስራ አፈጻጸም ዘገባ ማቅረብ ደካማነት ምክንያት መወሰን አይቻልም፡፡ በተለይም ድርጅቱ በተለያዩ አካባቢዎች የስራውን ሂደት እና አፈጻጸሙን ለመከታተል እንዲቻል በሚል የስራ አፈጻጸም መለኪያ አመልካቾች እና ግቦችን በማስቀመጥ የሚጠቀም ቢሆንም… ለአብዛኞቹ መለኪያ አመልካቾች በዘገባ የቀረበው ውጤት ግን በግብነት ከተያዙት ጋር አልተነጻጸረም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቀረበው የኦዲት ዘገባ በዩኤስኤአይዲ/ኢትዮጵያ የቀረቡት የአፈጻጸም ውጤቶች ተይዞ ከነበረው ዕቅድ ጋር መነጻጸር መቻል አለመቻላቸውን ለመወሰን አይቻልም ምክንያቱም የድርጅቱ ሰራተኞች እነዚህ ውጤቶች እንዴት እንደተገኙ መግለጽ አይችሉም ወይም ደግሞ ለእነዚያ ተገኙ ለተባሉት የስራ ውጤቶች ድጋፍ አይሰጡም፡፡ በእርግጥ የኦዲት ቡድኑ በዘገባው የቀረቡ የአፈጻጸም ውጤቶችን ተገቢነት ያላቸው እንዲሆኑ ለማድረግ ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም ይህንን ለመስራት በድርጅቱ ወይም ደግሞ የድርጅቱ ተባባሪ አስፈጻሚዎች ሳይቻል ቀርቷል (ከገጽ 6 – 12)…
እ.ኤ.አ ኦክቶበር 2010 ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በኢትዮጵያ እርዳታ ከዓላማው ውጭ ለሌላ ጉዳይ መዋሉን አስመልከቶ መግለጫ አውጥቶ ለህዝብ ከመልቀቁ ከጥቂት ቀናት በፊት ዩኤስኤአይዲ/USAID እና የልማት እርዳታ ቡድን/Development Assistance Group (ለኢትዮጵያ እርዳታ የሚሰጡ 27ቱ የሁለትዮሽ እና በይነ መንግስታት የልማት ድርጅቶች (አንዳንድ ጊዜም በጥቅሉ ዓለም አቀፍ የድህነት ወትዋቾች/አቃጣሪዎች እየተባሉ የሚጠሩት) በኢትዮጵያ የልማት እርዳታ ላይ መጠነ ሰፊ እና ስልታዊ የሆነ ገንዘቡን ከታለመለት ዓላማ ውጭ የዋለ የለም ብለዋል፡፡ የእኛ ጥናት ስልታዊ የሆነ የእርዳታ ገንዘብ የጠፋ ወይም ደግሞ ለሌላ ዓላማ የዋለ ለመሆኑ ያገኘው ማስረጃ የለም ብለዋል፡፡ የወፍ ምስክሯ ድንቢጥ እንደሚባለው! ዳምቢሳ ሞዮ አሳማኝ በሆነ መልኩ እንደምትሞግተው ሁሉ ዓለም አቀፍ እርዳታ ለኢትዮጵያ እና ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ወጥመድ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁንም ወጥመድ ነው፡፡ የዓለም አቀፉ የእርዳታ ምጽዋት ለኢትዮጵያ የጥገኝነት አዙሪትን፣ የተንሰራፋ ሙስናን፣ የገበያ መመሰቃቀልን፣ ስር የሰደደ ድህነት ማስፋፋትን እና ዘላለማዊ የእርዳታ ሱስ ውስጥ የሚያስገባ አደገኛ መርዝ ነው፡፡
ድህረ ጽሑፍ፣
በኢትዮጵያ ለበርካታ አስርት ዓመታት ሲከሰት በቆየው ረኃብ ላይ ጥናት በማካሄድ ዘገባ በማቅረብ ጠቃሚ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ የቆዩ ሁለት ያልተዘመረላቸው ጀግኖች አሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ1984 ተከስቶ ለነበረው በኢትዮጵያ ታላቁ ረኃብ 30ኛ ዓመት በሚታወስበት ዕለት እኔ በግሌ እንግሊዛዊውን ጋዜጠኛው ሚካኤል ቡርክን ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ ይህ ጀግና ጋዜጠኛ የኢትዮጵያን የ1984 ረኃብ በመዘገብ ሙዚቀኛ ቦብ ጌልዶፍን በማነሳሳት በቀጥታ በሚተላለፍ የእርዳታ ማሰባሰቢያ ኮንሰርት በመጠቀም ግዙፍ የሆነ ገንዘብ እንዲሰበሰብ በማድረጉ ብቻ አይደለም ሆኖም ግን በአስከፊው ረኃብ ምክንያት በመርገፍ እና በመሰቃየት ላይ የሚገኙትን የኢትዮጵያን ህዝቦች ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስተዋወቅ በፈጠረው ከፍተኛ የሆነ ግንዛቤ ጭምር እንጅ፡፡ እንደዚሁም ደግሞ የቢቢሲ ዘጋቢ እና በኋላም የአፍሪካ አርታኢ ሆኖ ሲሰራ የነበረውን እና እ.ኤ.አ በ1984 – 85 በተከሰተው ረኃብ ሰበብ ከምዕራቡ ዓለም ለተራቡት ወገኖቻችን የመጣውን በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠረውን እርዳታ በአቋራጭ ለመሳሪያ መግዣ እና ለግል ጥቅም ውሎ የነበረበትን እኩይ ምግባር ያጋለጠውን ጀግና ጋዜጠኛ ማርቲን ፕላውትን ከልብ ለማመስገን እወዳለሁ፡፡
የጋዜጠኝነትን ክቡር ሙያ በማስመልከት ታዋቂው የአሜሪካ ጸሐፊ፣ ዘጋቢ እና የፖለቲካ ተንታኝ የሚከተለውን አስፍሮ ነበር፣ “በጋዜጠኝነት ሙያ እውነታውን ከመናገር እና ሰይጣናዊ ድርጊትን ከማሳፈር እና ከማጋለጥ የበለጠ ትልቅ ህግ የለም፡፡“ እውነታን አፍርጦ በመናገር እና ሰይጣናዊ ድርጊትን በማሳፈር እና በማጋለጥ የ1984-85ን የኢትዮጵያን ታላቅ ረኃብ የዘገበ ከቡርክ እና ፕላውት ውጭ ማንም ጋዜጠኛ ይኖራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ኢትዮጵያዊ/ት የሆን ሁሉ እነዚህን ጀግኖች የማመስገን ዕዳ አለብን፡፡
ዓለም አቀፋዊ እርዳታ ለኢትዮጵያውያን/ት የድህነት አዙሪት ቀለበት ወጥመድ ሲሆን ለህወሀት ግን የመስረቅ እና የመዝረፍ ፈቃድ ነው!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም