January5/2014
መግቢያ፣
በመጀመሪያ ደረጃ ውድ አቶ ካሳሁን ነገዎ ታዋቂ ሰዎችን ወይም ምሁሮችን ለቃለ-መጠይቅ እያቀረበ አስተያየታቸውንና አመለካከታቸውን እንድናዳምጥና ትምህርት እንድንቀምስ የሚያደርገው ጥረት የሚያስመሰግነው ነው። በዚህም መሰረት በአ.አ በ23.12.2013 ዓ.ም ዶክተር ብርሃኑ ነጋን በቅርቡ ለዕትመትና ለንባብ ባበቃው፣ „ዲሞክራሲና ሁለንታዊ ልማት“ በተባለው መጽሀፉ ዙሪያ ምን ማለቱ እንደሆነ ለቃለ-መጠይቅ ጋብዞት አንዳንዶቻችን ለማዳመጥ ችለናል። የቃለ-መጠይቁን ምልልስ በጥሞና ላዳመጠ የዶክተር ብርሃኑ ነጋ መልስ ግልጽና ብዙም የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም።
እንደ ዕውነቱ ከሆነ አዲሱን የዶክተር ብርሃኑ ነጋን መጽሀፍ ለማግኘት ስላልቻልኩና ስላላነበብኩት ስለመጽሀፉ ጥሩና መስተካከል ይገባቸዋል ብዬ በማምነው ላይ ገንቢ ትችት መስጠት አልቻልኩም። መጽሀፉን አግኝቼ ከአነበብኩት በኋላ አስተያየቴን ለመስጠት እሞክራለሁ። ወደ ቃለ-መጠይቁና ምልልሱ ጋ ስንመጣ ከጠያቂው በቀረበለት ጥያቄ ዙሪያ የህብረተሰብአችንን ችግሮች በአጠቃላይ ሲዳስስ፣ መጽሀፉን በመመርኮዝ በተለይም በሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ እንዳተኮረ ተናግሯል። እነዚህም፣ 1ኛ) የፖለቲካ ችግሮች፣ 2ኛ) የኢኮኖሚ ችግሮችና፣ 3ኛ) የአካባቢ ችግሮች በሚሉት ዙሪያዎች ሰፊ ማብራሪያ ለመስጠት ሞክሯል። በተለይም ለቃለ-መጠይቁ ክብደት የሰጠው የፖለቲካው ላይ ስለሆነ በዚህ ላይ እሱ በሚመስለው መንገድ ለማብራራት ጥሯል። በእርግጥ ዶክተር ብርሃኑ በትክክል እንዳስቀመጠውና እኛም መቀበል ያለብን፣ እሱ ለንባብ ያቀረበው መጽሀፍ ለውይይት የቀረበና፣ ሰፋ ያሉትን የህብረተሰብአችንን ችግሮች በውይይትና በሂደት ለመፍታት በማመን ብቻ ነው። በእርግጥም የሚያስመሰግነው ነው ። ምክንያቱም ማንኛውም ምሁር አንድ ህብረተሰብን የሚመለከት መጽሀፍ በሚጽፍበትና ለንባብ በሚያቀርብበት ጊዜ፣ ለንባብ የሚቀርበው መጽሀፍ መወያያ እንጂ ያለቀለትና የደቀቀለት፣ የአንድም ህብረተሰብ ችግር በአንድ መጽሀፍ ላይ በቀረበ ሀተታ ሊፈታ ይችላል ብሎ በማመን አይደለም። በዚህ መልክ ከተለያየ አቅጣጫ ተመሳሳይ አመለካከትም ሆነ የተለየ አስተሳሰብ ያላቸው ቢጽፉና ቢያስነብቡን የመጨረሻ መጨረሻ የተወሳሰበውን የአገራችንን ችግሮች ለመፍታት ወደሚያስችለው አቅጣጫ ለመምጣት እንችል ይሆናል። በሌላ ወገን ግን ይህ ነው ትክክለኛው መንገድ ብሎ አንድ የጠራ መጽሀፍ ጽፎ አንባቢያን እንዲረዱትና እንዲገነዘብት የሚያደርግ መቶ በመቶ የተረጋገጠ አስተያየት ባይኖርም፣ ለህብረተሰብአችንም ሆነ ለሌሎች ደሀ አገሮች የሚስማማ አጠቃላይ መልስ መስጠት ይቻላል። በሌላ አነጋገር በሊትሬቸርም ሆነ በሳይንስ ታሪክ ውስጥ በተለያዩ አገሮች አንዳንድ የተገለጸላቸው ምሁራን ብቅ ሲሉና የህብረተሰብአቸውን ችግሮች ለመረዳት ሲጥሩ የሚመሩበት ፍልስፍና ወይም ርዕይ ነበራቸው። ይህ ባይሆን ኖሮ ከረዥም ጊዜ የርስ በርስ ትርምስና ጦርነት በኋላ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ካፒታሊዝም ባሸናፊነት ባልወጣ ነበር። የሳይንስና የፍልስፋና ጠቢባን በቀደዱት መንገድና ባስተማሩት መመሪያ መሰረት ብቻ ነው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገትና ምጥቀት ሊታይ የቻለው። አሁን ባለንበት ዓለም ግን የሌሎችንም ሆነ የኛን አገር የፖለቲካም ሆነ ሌሎች ችግሮች ለመረዳት ያለው ከባድ ነገር፣ በሳይንስና በፍልስፍናዊ ክርክር ዓለም ውስጥ ያለን ሳይሆን በኢንፎርሜሽን ዓለም ውስጥ ስለሆን ሁሉም እንደፈለገው የየአገሩን ችግር ለመረዳትና ለመተንተን ይፈልጋል። ይህ ዐይነቱ የተሰበጣጠረ አቀራረብ ደግሞ ችግሮችን በጥልቀት ተረድቶ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ በውዥንብር ዓለም ውስጥ እንድንኖር አድርጎናል።
እንደሚታወቀው ዶክተር ብርሃኑም ሆነ እኔና ሌሎች የዛሬው ዓለም ውጤቶች(Zeit Geist) ስለሆን፣ ዛሬ አገራችንም ሆነች ሌሎች አገሮች ያሉበትን ችግሮች ለመረዳት የምንጥረው ዛሬ በሚነፍሰው የአመለካከት ዘዴ ነው። በሌላ አነጋገር በዛሬው ዓለም የተለያዩ አገሮችን ችግር በሳይንስና በፍልስፍና መነጽር ለመገምገምና ለመረዳት የማይሞከርበት ዓለም ውስጥ ነው ያለነው። ስለሆነም አስተሳሰባችንና ሁኔታዎችና ማንበብ እንዲሁም ደግሞ ትንተና መስጠት የምንችለው በኢምፔሪሲስታዊ የሳይንስ መነጽር ብቻ ነው።
የዚህ ጽሁፍ ዓላማ የዶክተር ብርሃኑ ነጋን የቃለ-መጠይቅ ምልልስ ለመተቸት አይደለም። ቃለ-መጠይቁን ሁለቴ ካዳመጥኩኝ በኋላ ያልገባኛና ሌሎችንም ግራ የሚያጋባ በአገራችን ምሁራን ዘንድ የተለመደ የአቀራረብ ስልት አለ ብዬ ስላመንኩ፣ በሱ ዙሪያ አስተያየቴን ለመስጠትና ለመወያየት ነው። እነዚህም ምክንያታዊ፣ ስሜታዊና ፅንፈኛ የሚባሉ ጽንሰ-ሃሳቦች ሲሆኑ፣ ዶክተር ብርሃኑ በነዚህ ዙሪያ በተደጋጋሚ ገለጻ ስጥቷል። በተለይም ያተኮረው ምክንያታዊ በሚለው ፅንሰ-ሃሳብ ዙሪያ ሲሆን ፓለቲኛ ነን ባዮችም ችግር የህብረተሰብአችንን ችግር ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመረዳት ያለመቻልና፣ ምክንያታዊ በሆነ ዘዴም ለችግራችን መፍትሄ ለመስጠት ያለመቻል ነው የሚል ነው። ባጭሩ የችግራችን ዋና ችግር ችግሮቻችንን በምክንያታዊ መንገድ ያለመረዳትና ለመተንተን ያለመቻል ነው። ችግሬም በተለይም ምክንያታዊ ሲል ምን ለማለት እንደፈለገ ስላልገባኝ ከህብረተሰብ ችግር አንፃር እንዴት መረዳት ይቻላል ብዬ የራሴን አስተያየት ለመስጠት ነው ይህችን ጽሁፍ ለመጻፍ የተገደድኩት።
የህብረተሰብን ችግር ምክንያታዊ ወይስ ሳይንሳዊ በሆነ ዘዴ መረዳት!
ለምሳሌ በአቶ ዳንኤል ወርቁ ካሳ የታተመውን የእንግሊዝኛ- አማርኛ መዝገበ-ቃላትን ወስደን ስንመለከት ምክንያታዊ የሚለውን ጽንሰ-ሃብ በእንግሊዘኛው ሪዝን(Reason) ከሚለው ትርጉም ጋር የሚመሳሰል ነው። በመዝገበ- ቃላቱም መሰረት፣ ሪዝን የማሰብና የመረዳት ችሎታንም ያጠቃልላል። ይህም ማለት ሶስት ትርጉሞች ሲኖሩት፣ ሶስቱም የተያያዙ ናቸው። በሌላ ወገን ግን ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ምክንያታዊ በሚለው ጽንሰ-ሃሳብ ላይ ብቻ ያተኮረ በመሆኑ እሱ በተነተነው መልክ የሀብረተሰብአችንን ችግር ለመረዳት የተሟላ የመተንተኛና የመረዳት ዘዴ ሊሆን ይችላል ብዬ አልገምትም። ስለዚህም የሱን አገላለጽ ብቻ ብነወስድና የህብረተሰብ ችግርን እንደመገንዘቢያ ዘዴ ብንጠቀምበት፣ እያንዳንዱ ምሁር የየራሱን ምክንያት ስለሚደረድር ይህ ዐይነቱ ችግርን የመረዳት ዘዴ የህብረተሰባችንን የተወሳሰበ ችግር ጠለቅ ባለ መልኩ እንድንረዳው የሚያስችለን አይመስለኝም።
በአቶ ዳንኤል ወርቁ የተደረሰው የእንግሊዘኛና የአማርኛ መዝገበ-ቃላትም ሆነ የዶክተር ብርሃኑን ትርጓሜ ስንመለከት በአውሮፓ የፍልስፍና ታሪክ ውስጥ ምክንያታዊ ከሚለው አነጋገር ይልቅ አርቆ-ማሰብ ወይም ራሺናል(Rational) የሚለውን ጽንሰ-ሃሳብ ብንጠቀም ችግራችንን ለመረዳት አንድ ርምጃ ተራመድን ማለት ነው። በፍልስፍና ትምህርት ወይም ክርክር ውስጥ አርቆ-አስተዋይነት ወይም ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ምክንያታዊ የሚለውን መንገድ መከተሉ ብቻ የአንድን ህብረተስብ ችግር ለመረዳት በቂ እንዳልሆነ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች ይስማማሉ። ፈላሳፍዎች ኢንተሌክት ወይም ምሁራዊና ኢንተለጀንስ የሚሏቸው ነገሮች አሉ። ይህም ማለት አርቆ-አሳቢነት ወይም ምክንያታዊነት የተሟላ የህብረተሰብ ችግርን መረዳት ዘዴ ሊሆኑ የሚችሉት በኢንተሌክትና በኢንተለጀንት የጭንቅላት ክፍል ሲታገዙ ብቻ ነው። ይሁንና ግን በአንድ ህብረትሰብ ውስጥ ኢንተለጀንት ስዎች ቢኖሩም ችግሩን በተለያየ መልክ ስለሚተረጉሙት፣ በእነ ፕላቶን መሰረት ማንኛውም ዕውቀት ከሃሳብ መፍለቅና በሃሳብ መታገዝ እንዳለበት ይጠቁመናል። በፕላቶንም መሰረትና፣ በኋላም የሱን ፈለግ ይዘው ማሰተማር በጀመሩት ምሁራን አመለካከት የሰው ልጅ ችግር ሁሉ የተፈጥሮንና የሀብረተሰብን ትርጉም የመረዳት ችግር ነው። በፕላቶንም ዕምነት የሰው ልጅ ሁሉ ችግር የዕውቀት ወይም የአስተሳሰብ ችግር( Problem of Thought) ነው። ይህም ማለት በፕላቶን ዕምነት ዕውቀት በቀጥታ ከምናየው የሚፈልቅና የሚገኝ ሳይሆን ከሚታየውና ከሚጨበጠው አልፈን ሄደን የአንድን ነገር አፈጣጠር ምንነት ስንረዳ ብቻ ነው። ስለሆነም በሱ ዕምነት ወደ ዕውነተኛ ዕውቀት ጋ ለመድረስ ሃይፖቴስስንና ዲያሌክቲክን የመመራመሪያ ዘዴ ማድረግ መቻል አለብን። ይህም ማለት የአንድን ህብረተስብ ችግር ለመረዳትም ሆነ የተፈጥሮን ህግ ለመገንዘብ እየመላለስን መጠየቅ መቻል አለብን። ለምሳሌ የምንጠጣው ውሃ ለምን ከሃይድሮጅንና ከኦክስጂን ቅልቅል ብቻ መገኘት ወይም መፈጠር ቻለ? ለምን ሌሎች ንጥረ-ነገሮች የውሃ ምንጭ ወይም መሰረት ሊሆኑ አልቻሉም ? በዚህ መልክ ጥያቄን በጥያቄ ብናነሳ የመጨረሻ መጨረሻ ተቀራራቢ መልስ ለማግኘት እንችላለን። በሌላ ወገን ግን ምክንያታዊ የሚለውን ፅንሰ-ሃሳብ ብቻ ወሰደን የአገራችንን ችግር ለማንበብና ለመተንተን የምንሞክር ከሆነ ችግር ውስጥ ልንገባ እንችላለን። ይኸውም ሁሉም በፈለገው መልክ ቀደም ብሎም ሆነ ዛሬ ያለውን የህብረተሰብአችንን ችግር ለመተርጎም ስለሚፈልግ ይህንን አካሄድ እንደሳይንሳዊ ችግርን የመረዳትና የመተንተኛው ዘዴ አድርገን ለመጠቀም ያዳግታል። መፍትሄም ለመፈለግም አይጠቅመንም። በእኔ ዕምነትና በሳይንስ ዓለም ውስጥ የተለመደውን የተለያዩ አንድን ሁኔታ የማንበብ፣ የመረዳትና የመተንተኛ ዘዴዎች ብንጠቀም የችግሩንም ምንጭ ወይም ዋና ምክንያት ለመረዳት ብቻ ሳይሆን መፍትሄም ለመፈለግ ይረዳናል። እነዚህ ደግሞ ከአመለካከት ወይም ከተወሰነ ህብረተሰብአዊ ዕሴት ጋር የተያያዙ ናቸው። 1ኛ)በሃሳብ ላይ የተመረኮዘው ዲያሊሌክቲካዊው የፕላቶን መመርመሪያ ዘዴ፣ 2ኛ) በቀጥታ በሚታዩ ነገሮች ላይ ተመርኩዞ የሚደረግ የመመርመሪያ ዘዴ ወይም ኢምፔሪሲስታዊው መንገድ፣ 3ኛ) በማቴሪያሊስት ላይ የተመሰረተ የምርምር ዘዴ ወይም ማርክሲስታዊው የምርምር ዘዴ፣ 4ኛ) ከላይ በተጠቀሱት ውስጥ የሚጠቃለሉ የዱርክ ሃይምና የማክስ ቬበር የአገዛዝና የሶሻል ቲዎሪ የምርምር ዘዴዎች።
ዶክተር ብርሃኑ ነጋ በኢትዮጵያ ያለውን የተወሳሰበ ችግር ከብቃት ማነስ ጋርም ለማያያዝ ሞክሯል። ይህ ችግር በመንግስትም ሆነ በተቃዋሚዎች መሀከል ሲንፀባርቅ ሲታይ፣ ችግሩ በተለያዩ ኃይሎች ዘንድ የተለያየ ግንዛቤ እንዳለ ይጠቁማል። በተለይም በተቃዋሚው መሀከል ያለውን ችግር ሲያብራራ፣ የተወሰነው ኃይል የአገራችንን ችግር `በጥልቀት` ሲመለከትና `ለመፍታት` ሲጥር፣ ሌላው ደግሞ የራሱን አጀንዳ ይዞ በመምጣትና ስሜታዊ ቅስቀሳ በማድረግ የፓለቲካውን መድረክ እንደሚያደፈርሰውና፣ ይህም ዐይነቱም አካሄድ ለተወሳሰበው የአገራችን ችግር ተደራቢ ችግር እንደፈጠረለት ይጠቁማል። እዚህ ላይ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ የብቃትን ማነስ ከዕውቀት ጋር መያያዝ እንደሌለበት ለማብራራት ሞክሯል። በእኔ ግምት ግን ብቃት ማነስ የሚለው አባባል በቀጥታ ከዕውቀትና ከልምድ ማነስ ጋር የሚያያዝ ስለሆነ፣ ብቃት ማነስ በሚለው ፈንታ የንቃተ-ህሊና ማነስ የሚለው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ላነሳው ጥያቄና የህብረተሰብአችንን ችግር ለመረዳትና መፍትሄም ለመፈለግ የተሻለ አካሄድ ይመስለኛል።
በአውሮፓው የፍልስፍና ታሪክ ውስጥ ንቃተ-ህሊና(Consciousness) ከፍተኛ ቦታን የሚይዝ ሲሆን፣ ብዙ ነገሮችን የሚያጠቃልል ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የንቃተ-ህሊና መዳበር እንድናመዛዝን ይረዳናል። ንቃተ-ህሊናችን በዳበረ ቁጥር፣ 1ኛ) ያለፈውን ታሪካችንንም የመረዳት ኃይላችን ከፍ ይላል። ይህም ማለት ያለፈውን ታሪክ በጥቁርና በነጭ እየጻፉ አንዱን ከመፈረጅና ሌላውን ከማወደስ ይልቅ፣ ታሪካዊ ሂደት የቱን ኃህል አስቸጋሪና፣ አንድን ህብረተሰብ ለመሰብሰብና ለመገንባት ምን ምን ደንቃሮች እንቅፋት እንደሚሆኑ መገንዝበ ያስችለናል። 2ኛ) ከዚህ ስንነሳ የንቃተ-ህሊና መዳበር ህብረተሰብአዊ ኃላፊነት እንዲኖረንና፣ የምናደርጋቸውን ድርጊቶች በሙሉ ከህብረተሰብ ጥቅም ጋር መያያዝና አለመያያዛቸውን እንድንገዘብ ያግዘናል። 3ኛ) የንቃተ-ህሊናችን ሲዳብር ጥሩ ጥሩ ባህሎችን መንከባከብና፣ ከውጭ የሚመጡትን ባሀል ነከ ነገሮች በመለያየትና ጥሩውን መርጦ በማውጣት ካለን ጥሩ ባህል ጋር በማዋሃድ ውስጠ-ኃይሉ ከፍ ያለና የህዝቡን የማሰብ ኃይል የሚያዳብር ባህል እንዲገነባ ማድረግ ይቻላል። 4ኛ) የአንድ ህዝብ፣ በተለይም የምሁር ንቃተ-ህሊና መዳበር ሞራልንና ስነ-ምግባርን እንድናስቀድም ያግዘናል። መናናቅንና ትዕቢትነትን አሽቀንጥረን ጥለን ራስን ዝቅ በማድረግ አንድ ህብረተሰብ እጅ ለእጅ ተያይዞ አገርን ለመገንባት መንገዱን ለማመቻቸት ይረዳናል። 5ኛ)የንቃተ-ህሊና መዳበር በተለይም በዚህ በተወሳሰበ ዓለም ውስጥ የሚናፈሰውን ዕውቀት መሰል ነገር፣ ግን ደግሞ አገርን የሚያፈራርስና ማህበራዊ አሴትን የሚያበላሽውን በዕውቀት ስም ገብቶ የሰውን ጭንቅላት የሚያዛንፈውንና ዕውነትን ከውሸት ለመለየት የማያስችለውን ኢንፎርሚሽንና ዓለም አቀፋዊ ስምምነትን በደንብ እንድንገነዝብ ይረዳናል። በተለይም በዛሬው ወቅት የምዕራቡ ካፒታሊዝም በሁሉም ዘርፍ ቀዳሚነት አለኝ ብሎ በሚመጻደቅበት ዓለም ውስጥና ብዙ አገሮችን እያሳሳተ ወደ ማህበራዊና የኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ ዘፍቀው ከዘለዓለማዊ ባርነት እንዳይወጡ በሚያደረግበት ዘመን የንቃተ-ህሊና ማደግ ከፍተኛ ቦታን ይይዛል። ዞሮ ዞሮ የንቃተ-ህሊና መዳበር ከጥሩ ዕውቀት ጋር የሚያያዝ ነው። ዕውቀት ደግሞ ለዳቦ ተብሎ በአራት ዐመት የኮሌጅ ዲግሪ ወይም በአንድ የዶክትሬት ቴሲስ የሚጠናቀቅ ሳይሆን ከዚያ በላይ እንድንሄድ የሚያደርገንና፣ ትላንታና የተማርነውን እየደጋገምን በመጠየቅ ወደ ሀቀኛው መንገድ ለማምራት የሚያስችለንን መፈለጊያ ዘዴ ነው።
ከዚህ ስንነሳ በአገራችን የፖለቲካ ተዋናዮች ዘንድ አገዛዙንም ጨምሮ ከፍተኛ የሆነ የንቃተ-ህሊና ማነስ ክፍተት እንዳለ መገንዘብ እንችላለን። ይህም ስለሆነ ነው በተለይም ባለፉት 22 ዐመታት አገራችን በሁሉም አቅጣጫ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ስትቦረቦር፣ የህብረተስብአችን ባህላዊ እሴቶች እንዳሉ ሲበጣጠሱና ማንም እየመጣ እንዲጨፍርባቸው ሲደረግ፣ በዕድገትም ስም አገራችን ስትፈራርስና ህዝባችንም ከቤቱ እየተፈናቀለ ሜዳ ላይ እንዲወድቅ ሲደረግ ራሱ ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል ዝም ብሎ እንዲመለከት የተገደደው። በቁጭት እየተነሳ ጥያቄ በመጠየቅ ሲመራመርና መፍትሄ ሲፈልግ አይታይም።ሲታገልና ሲያታግል አናይም። ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በሚሉት አዲሱ የፈሊጥ አነጋገር እያየ ዝም ብሎ ተቀምጧል።
እንደሚታወቀው በፍልስፍናና በሳይንስ ዓለም ውስጥ አንድን ነገር ለመረዳት አንድ መንገድ ብቻ እንደሌለ በፈላስፋዎች መሀከል ክርክር ነበር። ዛሬም ቢሆን በመጠኑ አለ። ለምሳሌ ኢምፔሪሲስታዊው መንገድ በተለይም ሶፊስቶች ያፈለቁትና፣ ከአስራስድስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የእንግሊዝ ሊበራል ፈላስፎች ያስፋፉትና ዛሬ የዓለም ማህበረሰብ በሙሉ አውቆም ሆነ ሳያውቅ የሚመራበትና የሚደናበርበት ዘዴ ነው። ይኸኛው መንገድ ከተፈጥሮ ሳይንስ አልፎ ወደ ህብረተስብ ሳይንስና ወደ ፖለቲካ ሳይንስ ድረስ በመዛመት ዓለም ዛሬ ላለችበት የተመሰቃቀለ ችግር ዋናው ምክንያት እንደሆነ ብዙ ፈላስፎችና ሳይንስቲስቶች ይስማማሉ። በተለይም ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የብዙ አገሮች ዕድል በካፒታሊዝም መስፋፋት እየተወሰነ በመምጣቱ ፍልስፍናን የሰው ልጅ ኑሮ መመሪያና የጥበብ መፈለጊያ መሆኑ ሊያከትም በቃ። ስለሆነም የእንግሊዝ ሊበራሎች ፍልስፍና በአሸፋኒት ከወጣ ወዲህ ክስተት ዋናው መመሪያ በመሆን ዕውነትን ለመፈለግ የሚደረገው ጥረት ቆመ። ይህም ማለት ኒውትራል ወይም ገለልተኛ የነበረው የእነ ፕላቶን ፍልስፍና በመገፍተር የመጨረሻ መጨረሻ ርዕዮተ-ዓለምን ተገን ያደረገው ወይም ለአንድ ወገን የሚያደላው ፖዘቶቭ ሳይንስ በአሸናፊነት ሰለወጣ፣ የተፈጥሮና የህብረተሰብ ሳይንስ ገለልተኛ መሆናቸው ቀርቶ የአገዛዝ መሳሪያዎች በመሆን ተፈጥሮንና የሰውን ልጅ መሉ በሙሉ ወደ መቆጣጠሪያነት እንዳመሩ ይነግሩናል። በዚህም ምክንያት በታወቁ ፈላስፋዎች መሰረት የእነ ሬኔ ዴካና የኒውተን ፍልስፍናና ሳይንስ በአሸናፊነት መውጣት ተፈጥሮን ሙሉ በሙሉ ተበዝባዥ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን ራሽናል የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ ነጠላ ነገሮችን መተንተኛ ዘዴ ከመሆን አልፎ የሰውን ልጅ ተፈጥሮአዊ የጭንቅላት ባህርዮች፣ ኮመን ሴንስንና በደመ-ነፍስ የማወቅ ችሎታን( Intution) እየገፈተራቸው መጣ። ራሽናሊዝም በካፒታሊዝም ዘመን ወደ ዋጋ ጥቅም(Cost-Benefit) ማስሊያ ዘዴነት ዝቅ በመደረጉ ማንኛውም የምርት እንቅስቃሴና የቴክኖሎጂ ዕድገት ከትርፍና ከዋጋ አንፃር ብቻ የሚታዩና የሚተመኑ ሆኑ። የአገራችንም ምሁራን ችግር ይህንን በተለይም ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ ጀምሮና፣ በ20ኛው ክፍለ-ዘመን ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ሎጂክ የተዋቀረውን አገሮችን በሱ ቁጥጥር ስር ለማድረግ ያስፋፋውን የዘመናዊነት ርዕየተ-ዓለም አለመገንዘብ ነው። ይህ ጉዳይ የኛ አገር ችግር ብቻ ሳይሆን ሶስተኛው ዓለም አገሮች ተብለው የሚጠሩ ሁሉ የገቡበት መቀመቅ ነው።
ይህንን እጅግ አስቸጋሪውን በከበርቴው ዓለም ውስጥ ያለውን የተወሳሰበ ሳይንሳዊ አመለካከት ትቼ ወደ ዶክተር ብርሃኑ የቃለ-መጠይቅ ምልልስ ጋ ስመጣ በእኔ ግምትና ዕምነት በአለፉት አርባ ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የተሳተፉና ያለፉ፣ ዛሬም የሚገኙ ምሁራን ችግር የህብረተሰብአችንን ችግር፣ ዶክተር ብርሃኑ በትክክል እንዳለው ችግራችንን ለመረዳት መጣር ሳይሆን በስሜታዊነት በመታገዘና አንድን ሁኔታ በጥቁርና በነጭ በመሳል የማይሆን ንትርክና ግብግብ ውስጥ መግባት ነው። የዚህ ሁሉ ችግር ምንድነው ?
እነሶክራተስና ፕላቶ የግሪክን የረዥም ጊዜ የስልጣኔና የርስ በርስ ታሪክ ካጠኑ በኋላ የደረሱበት መደመደሚያ፣ ላይ እንዳልኩት በዚያን ጊዜ የነበረው ችግር አርቆ የማሰብ ችግር ጉዳይ ነበር። ስለዚህም በእነሱ ዕምነት ለአንድ ህብረተሰብ ችግር ዋናው መፍትሄ ችግርን መደበቅ ሳይሆን ዲያሌክቲካዊ በሆነ መንገድ ወደ ውጭ አውጥቶ በግልጽ መነጋገር ነው። ለዚህ ደግሞ ትክክለኛ ፍልስፍና ያስፈልጋል። ይህ ዐይነቱ የትግልና ሃሳብን ወደ ውጭ አውጥቶ የመከራከሪያ ዘዴ በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በድራማና በልዩ ልዩ ነገሮች ዙሪያ ክርክርና ማስተማሪያ ዘዴ በመሆነ የሰውን ልጅ ጭንቅላት ማረቂያና ማስተማሪያ ዘዴ እንዲሆን ተደርጓል። በተለይም ሶሎን የተባለው ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ላይ ስልጣንን የተረከበው መሪ በፍልስፍና በመታገዝ ተግባራዊ ያደረገው የፖለቲካ ሪፎርም ግሪክን በጊዜው ከነበረችበት የህብረተሰብ ቀውስ ለጊዜውም ቢሆን ሊያላቅቃትና፣ ከዚያ በኋላ ሺህ በሺህ ለሚቆጠሩ የሂሳብና የፈላስፋ አዋቂዎች መንገዱን እንደከፈተ ታሪክ ያረጋግጣል።
ወደኛው አገር ስንመጣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ህብረተሰብአዊ ችግርን በግልጽ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመጠየቅና ለመከራከር ወይም ደግሞ ለመወያየት የተለመደ መንገድ አልነበረም። ከአክሱም አገዛዝ ጀምሮ አብዮቱ ፈነዳበት እስከተባለበት ጊዜ ድረስ የተዋቀረውን የአገዛዝ ሁኔታ ስንመለክት ህብረተሰብአችን በስራ-ክፍፍል መዳበር፣ በውስጥ ንግድ እንቅስቃሴ መበልጸግ፣ በእደ-ጥበብ ማበብ፣ በከተማዎች ዕድገትና ሰፋ ባለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ የሚገለጽና ጎልቶ የሚታይ ስልጣኔ ስላልነበር አመለካከታችንን በማደበርና ትላልቅ የታሪክ ስራዎችን ለመስራት አላስቻለንም። ከህብረተሰብ ሳይንስም ሆነ ከፍልስፍና ዕውቀት አንፃር ሁኔታ ስንነሳ በአንድ ህብረተስብ ውስጥ የማቴሪያል ሁኔታዎች በሚለወጡበት ጊዜ የሰው ልጅ ህብረተስብአዊ ባህርይን የመውሰድና መስልጠን እየጎለመሱ ይመጣሉ። በዚያውም መጠን በጭንቅላቱ ውስጥ ያሉ የተደበቁ ባህርዮቹ በሙሉ በመዳበር ተፈጥሮን የበለጠ መቃኘት ይጀምራል። ስለራሱም ሆነ ስለሌላው ያለው አስተሳሰብ እየተለወጠ በመምጣት የበለጠ ስብአዊነትን እንዲካን ይደረጋል። በዚያው መጠንም ስለህብረተስብ ዕድገትና አኗኗር እንዲሆም ደግሞ ሰለተፈጥሮ ያለው ግምት ይለወጣል። ከፕላቶ ጀምሮ እስከሺለርና እስከ ማክስ ቬበር ያሉ ስራዎችን ላነበበ የምንገነዘበው የሰው ልጅ በአፈጣጠሩ ማህብራዊና ህብረተስብአዊ ቢሆንም፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በሚዋቀሩ መጥፎ የአገዛዝና የማቴሪያል ሁኔታዎች አስተሳሰቡ ይታፈናል፤ ይበላሻልም። ከዚህ ስንነሳና አያሌ የህብረተሰብ ሳይንስ ጥናቶችን ሳገላብጥና የህብረተስብአችንን ችግር ለማጥናትና ለመረዳት ስቃጣ የኛ ችግር በመሰረቱ ሰፋ ካለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ጉድለት የተነሳና ነገሮች በግልጽ ለመወያየት ያለመቻል ችግርና ፍላጎት ማጣት ነው። ዞሮ ዞሮ ከአርባ ዐመት የአብዮት መዳፈን በኋላም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ዓለም ውስጥ ተቀምጠን እንደዚህ ግራ መጋባት የቻልነውና በቂም በቀል የምንተያየው ያ ፊዩዳላዊ አመለካከት በጭንቅላታችን ውስጥ ስለተቀረጸ ነው።
እንደሚታወቀው ከአብዮቱ በፊትም ሆነ በአብዮቱ አፍላ ዘመን ተራማጅ በሚባሉ ኃይሎች መሀከል ይካሄድ የነበረውን የክርክር ዘዴ ስንመለከት ከአንዳንድ አቀራረቦች በስተቀር አብዛኛው በእንካ ስላንቲሃ ላይ ያተኮረ ነበር። በአብዮቱ ወቅት በተፈጠረው ትርምስ በመጀመሪያው ወቅት ይካሄድ የነበረው ክርክር እንዲዘጋና የጠብመንጃ ትግል ብቻ ነው የሚያዋጣው በማለት ወጣቱን ሁሉ የእርስ በአርስ ጦርነት ውስጥ ማሰማራትና መጨራረስ ሆነ። በሳይንሳዊ መንገድ ከማስተማርና ከማሳመን ይልቅ በተለይም የወጣቱን ጭንቅላት በመጥመድ አርቆ አሳቢነት እንዲወድም ተደረገ። በጊዜው የነበረውም ትግል ስልጣን ለመያዝ ብቻ ስለነበር፣ ሁሉም የደፈጣ ውጊያ ጀመረ። ሳይቀድሙኝ ልቅደም የሚለው አስተሳሰብ በመስፋፋቱ የወጣቱ አስተሳሰብ ተመረዘ። ስልጣን በጠብንጃ ብቻ ነው ሊያዝ የሚችለው፣ አብዮትም ደም በመፍሰስ ብቻ ነው ሊሰምር የሚችለው በማለት የውይይትና የመከራከር ባህል እንዳይዳብር ተደረገ። የተለያዩ ድርጅቶች የየራሳቸውን ካድሬዎች ሲመለምሉ ጋጠወጥነት ተስፋፋ። አብዮቱ ተቀለበሰ ከተባለበት ጊዜና ወታደሩ መሉ በሙሉ ስልጣንን ከጠቀለለ በኋላ ተራማጅ ነኝ የሚለው ኃይል ጊዜ ወስዶ በማጥናትና በመመራመር በጊዜው የተፈጠረውን ችግር ሊረዳ አልቻለም። ያ በዚያን ጊዜ የተፈጠረው የፅንፈኝነትና የመበጥበጥ ባህል ከደማችን ጋር በመዋሃድ በአጠቃላይ ሲታይ በሳይንስ፣ በፍልስፍናና በቲዎሪ ዙሪያ ምንም ዐይነት ጥናት እንዳይካሄድ ታገደ። የቲዎሪንና የሳይንስን ጥያቄ የሚያነሱ በሙሉ እየተሾፈባቸውና ስማቸው እየጎደፈ የትግል መድረክ የሚባለውን እየጣሉ እንዲወጡ ተገደዱ። ይህ ዐይነቱ ሳይንሰ- አልባና ፍልስፍና አልባ ትግል ለጮሌዎችና ለበጥባጮች፣ እንዲሁም ደረታቸውን እየነፉ ሰውን ለሚንቁ በሩን ከፈተላቸው። ህብረተሰብአዊ ለውጥ ካለሳይንስና ካለቴክኖሎጂ እንዲሁም ካለፍልስፍና የሚመጣ የሚመስለው እዚህና እዚያ ፓርቲዎችን በመመስረት ብዙ ወጣቶችን አሳሳተ። ዛሬም ያለው ችግር ይህ ነው። እንዴት አድርጎ አንድን ህብረተሰብ ካለሳይንስና ካለቴክኖሎጂ መለወጥ ይቻላል? አንድ ህብረተሰብ በፍልስፍናና በህብረተሰብ ሳይንስ መነፅር እየታየ ካልተመረመረ እንዴት አድርጎ ችግሩን መረዳት ይቻላል? ይህንን ዐይነቱን ግራ የተጋባ አካሄድ ካልተውንና፣ በተለይም ደግሞ ለጮሌዎችና ለሰላዮች መንገዱን እስካልዘጋን ድረስ በሚቀጥሉት መቶ ዐመታትም የኢትዮጵያ ሁኔታ በፍጹም ሊለወጥ አይችልም። ስለዚህም ዛሬ ከገባንበት አስጨናቂ ሁኔታ ለመውጣት የግዴታ የሙጥኝ ብለን ከያዝነው የትግል ዘዴ መላቀቅ አለብን። ፍልስፍናን፣ ሳይንስንና ሶስይሎጂን ያስቀደመ የምርምር ዘዴ ማስቀደምና ወጣቱን ማስተማር መቻል አለብን። ኢትዮጵያን አድናለሁ የሚል ሁሉ ሀቀኛ ነኝ ብሎ እስካመነ ድረስ ከጭንቅላት ተሃድሶ የትግልና የምርምር ዘዴ ውጭ ሌላ የትግል ዘዴ በፍጹም ሊኖር እንደማይችል መገንዘብ አለበት።
የሀብረተስብአችንን የተወሳሰበ ሁኔታ የመረዳት ችግር!
ወደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ የአንድን ህብረተሰብ ሂደትና ዕድገት በህብረተስብና በተፈጥሮ ሳይንስ ለመረዳት ያለመቻል የግዴታ እየመላለስን በብሄረሰቦች መሀከል ያለ ችግር ወይም ደግሞ አንድ ብሄረስብ ብቻ የፈጠረው ችግር አድርገን እንድንመለከት አድርጎናል። ወደድንም ጠላንም እንኳን በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ብሄረሰቦችም ሆነ ከአንድ እናት የሚወለዱ ህጻናት በአሰተዳደጋቸውና ነገሮችን በመቅሰም ተመሳሳይ ዕድገት ሊኖራቸው አይችልም። በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ አንደኛው ከሌላው ቀድሞ ነገሮችን በመማርም ሆነ በመቅሰም ወይም በቁመት በማደግ ሊቀድመው ይችላል። ወደ ህብረተሰብ ታሪክም ስንመጣ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ በአንድ አካባቢ የሚኖር ህዝብ ወይም ብሄረሰብ ቋንቋን፣ ባህልን፣ ዕደ-ጥበብንና የስራ ክፍፍልን በማዳበር በተፈጥሮ ላይ የተወሰነ የበላይነትን ይቀዳጃል። ከእንስሳ የተሻለ መሆኑን ያረጋግጣል። በዚህ መልክ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አገሮች ቋንቋዎችና ባህሎች በሁሉም አካባቢ ተመጣጣኝ በሆነ መልክ ያደጉበት ሁኔታ የለም። የየአገሮችን ስልጣኔ ታሪክ ስንመለከት ወደ ባህር አካባቢና ለውጭው ዓለም የቀረቡና ክፍት የነበሩ አገሮች ስልጣኔን ቶሎ የመቀዳጀትና የማዳበር ዕድል አግኝተዋል። ለምሳሌ ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛው ክፍለ-ዘመን የመጀመሪያው ዘመናዊ የግሪክ ስልጣኔ በአዮን አካባቢ የዳበረው ከግብጽ ስልጣኔ ጋር የጠበቀ ግኑኝነት ስለነበረውና ከህንድ ጋር በሚመጡ ፍልስፍናዎች በመተዋወቁ ነበር። የሌሎችም አገሮች ታሪክ ይህንን ይመስላል።
የአገራችንን ታሪክ ስንመለከት የስልጣኔው ታሪክ እጅግ የተወሳሰበና ገና ብዙም ያልተጠና እንደሆነ መገንዝብ ይቻላል። ይሁንና ግን የዛሬው የኢትዮጵያ ስልጣኔ ዋናው መሰረት የተጣለው ከአክሱም አገዛዝ ቀደም ብሎ እንደነበርና፣ ከአራተኛው ክፍለ-ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ መልክ እየያዘና የአገዛዝ መዋቅር እየጣለ የመጣ ለመሆኑ ብዙ የታሪክ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። ይህም የሆነበት ምክንያት የሰሜኑ ክፍል ለባህር የቀረበና ከውጭው ዓለም ጋር የጠበቀ ግኑኝነት ስለነበረው ነው ። በዚህም ምክንያት ከአራት ሺህ ዐመት በፊት የግዕዝ ፊደልን ማፍለቅ ሲቻል፣ ይህ ፊደል ከአራተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ስርዓት ባለው መልክ እየተቀነባበረና የመጻፊያና የመነጋገሪያ ዘዴ እየሆነ ይመጣል። በዚያን ጊዜ እንደዚህ ዐይነቱ ፊደልና ቋንቋ ሲዳብር ሌላውን የህብረተሰብ ክፍል ለመጨቆኛ ተብሎ ሳይሆን ማንኛውም ህብረተሰብና የሰው ልጅ እንደሚያደርገው ሁሉ የሰሜኑ የአገራችንም ህዝብ ይህንን ዕድል አገኘ። በዚህም በመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ምድር ውስጥ ከመነጋገሪያ አልፎ እንደመጻፊያ የሚያገለግል የተሟላ ቋንቋ ማዳበር ተቻለ። ከዚህም አልፎ የሙዚቃን ምት በማዳበርና የሙዚቃን መሳሪያ በመስራት እስከተወሰነም ደረጃ ቢሆን ለስልጣኔው ዕምርታ ሰጠው። ስለሆነም በዚያን ጊዜ የነበረውን አገዛዝና ህዝብ በዚህ የስልጣኔ አፍላቂነቱ ልናመስግነው የሚገባን እንጂ እንደጠላት የምናየው አይደለም። ይህንን የምናደርግ ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየአገሮች ውስጥ ፊደልንና ቋንቋን ያዳበሩትንና ያፈለቁትን፣ እንዲሁም ሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠሩትን ግለሰቦች በሙሉ እንደጠላት እያየናቸው ልንፈርድባቸው ነው ማለት ነው። በሌላ አነጋገር በመጀመሪያው ወቅት ስልጣኔዎች ሁሉ የሚፈልቁት ከሰው ልጅ ውስጣዊ ውስጠ-ኃይልና የመስለጠን ፍላጎት የተነሳና፣ እንዲሁም ደግሞ የአካባቢ አመችነትና ከተለያዩ ህዝቦች ጋር በሚደረግው ግኑኝነት አማካይነት እንጂ የመግዣ ወይም የመጨቆኛ መሳሪያ ይሆናሉ ተብለው በማሰብ አይደለም። ይሁንና ግን ታሪክ እንደሚያረጋግጠው የሰው ልጅና ባህሉ ውስጣዊ-ኃይል ስላላቸው በአንድ ቦታ ረግተው የሚቀሩ አይደሉም። እንደባዮሎጂካዊ ክንውን በሁሉም አቅጣጫ በመስፋፋት ሌሎች የህብረተሰቦች ክፍሎችንም ያዳርሳሉ። ይህ ዐይነቱ ህብርተሰብአዊና ባህላዊ ክንዋኔ ይባላል።
አሁንም ወደ ተጨባጩ የኢትዮጵያ ሁኔታ ስንመጣ የአክሱም አገዛዘ በራሱ ውስጣዊ ድክመትና በዮዲትና በቤጃዎች ወረራ፣ እንዲሁም ደግሞ በአረቦች ግፊት የሩቅ ንግድ መሰመሩ ከተዘጋበት በኋላ ይዳከማል። የመጨረሻ ላይም ይወድማል። ርዝራዡ ወደ ደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል በመተላለፍ በዛግዌ ዲይናስቲ ዘመነ መንግስት እንደገና ማበብ ቻለ። የዛግዌ ዲይናስቲ ከወደቀ በኋላ በአስራ አራተኛው ክፍለ-ዘመን የግዕዝ ፊደል እንዳለ በመወሰድና በመሻሻል የአማርኛ መነጋገሪያ ሊሆን ቻለ። ይህ ዐይነቱ የዕድገት ሂደት ሊገታ የማይችል ሁኔታ ነው። አማርኛም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቋንቋና በልዩ ልዩ ባህሎች በመገለጽ መዳበሩ ለጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዕድገት ጠንቅ ሳይሆን ያስተባበረንና መነሻችን ለመሆኑ የማይካድ ነው። ይሁንና ግን በዚህ ዐይነት የህብረተሰብ ዕድገት ታሪክ ውስጥ ሌሎች ብሄረሰቦች ተሳትፎ አላደረጉም የሚል ዕምነት የለኝም። ለምሳሌ የሸማን ስራ፣ የጠላንና የካቲካላን አጠማመቅንና እንዲሁም የጤፍ ዘርን እርባታ ስንመለከት ከየት እንደመጡ፣ ማን እንደጀመራቸውና እንዳስፋፋቸው በግልጽ የሚታወቅ ነገር የለም። ይሁንና ግን እነዚህን የመሳሰሉትና በጠቅላላው የአስተራረስ ባህልና የእርሻ ባህል መዳበርና ልዩ ልዩ ሰብሎች መስፋፋት የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ውጤት ለመሆኑ አይካድም። በሌላ ወገን ግን ከአስራአራተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ከክርስቲያኑ የሰሜኑ ክፍል ወደ ደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል የክርስትናን ሃይማኖትን ለማስፋፋት በሚል እንቅስቃሴና ህብረተስብአዊ ጋብቻ እንደነበር ታሪክ ያረጋግጣል። ይህ እንግዴህ የሆነው አፄ ምኒልክ ወረራ አድርገዋል ከመባሉ ከስደስት መቶ ዐመት በፊት ቀደም ብሎ ነው። በዚህ ዐይነቱ እንቅስቃሴ መሰረት ወደድንም ጠላንም ህብረተሰብአዊ መተሳሰር ሊዳብር ችሏል። አንዳንዶች የኢትዮጵያን ታሪክ ወደ መቶ ዐመት ቀንሰው ለመጻፍና ለማሳመን እንደሚሞክሩት ሳይሆን በተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች መሀከል ያለው መተሳሰርና የባህል ልውውጥ የብዙ መቶ ዐመታት ታሪክን የሚያስቆጥር ነው። በሌሎች አገሮች ህብረ-ብሄር በዚህ መልክ ነው የተዋቀረው። የህብረ-ብሄር ምስረታ እንደቂጣ የሚጠፈጠፍና ወዲያው የሚደርስ ሳይሆን ውጣ ውረድን በማሳለፍ የሚደረግ የአገራዊ ግንባታ ክንዋኔ ነው።
ይህ ዐይነቱ ህብረተስብአዊ እንቅስቃሴና ዕድገት ፈጣን በሆነ የማቴሪያልና የምሁር እንቅስቃሴ ሊታገዝና ሊዳብር አልቻለም። የአገራችን ከአንድ ሺህ ዐመት በላይ ከውጭው ዕድገት ተገልሎ መኖር የውስጥ ዕድገቷን ሊያግደው ችሏል። በዚህም ምክንያት የተነሳ የህብረ-ብሄር ምስረታ በኢትዮጵያ ውስጥ የአውሮፓውን ዐይነት መንገድ ይዞ ሊጓዝ አልቻለም። አገዛዙም ባለበት ውስጣዊ ድክመት የተነሳ ከፊዩዳል ኖርሞች ባለመላቀቁ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ሊኖር የሚገባው መተሳሰርና መጠናከር እዚህና እዚያ በሚነሱ የፊዩዳል ግጭቶች ፈተና ውስጥ ወድቆ ነበር። ይህ ዐይነቱ ፉዩዳላዊ ፍክክርና ፉክቻ በተለይም የአውሮፓው ካፒታሊዝምና ኢምፔሪያሊዝም እያደገ ሲመጣ ልዩ ዐይነት ውስጠ-ኃይል በማግኘት በተወሰነ አካባቢ የሚገኙ ፊዩዳላዊ አገዛዞች ጥንካሪና በሌላኛው ላይ የበላይነትን የመቀዳጀት ዕድል ሰጣቸው። የአፄ ምኒልክ ጉዞና ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ ከዚህ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ በሌላው ወገን ግን አፄ ምኒልክ ሌሎች ከሳቸው በፊት የቀደሙ አገዛዞችን ህልም ነው መጨረሻ ላይ ተግባር ማድረግ የቻሉት። ወረራ እንበላው መስፋፋት በአፄ ምኒልክ አገዛዝ ዘመን ጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ አገር ውስጥ የመጠቃለሉ ሁኔታ የታሪክ ግዴታ ነው። በመሰረቱ አፄ ምኒልክ የአውሮፓ ፍጹም ሞናርኪዎች ከሰሩት የተለየ ስራ አይደለም የሰሩት። የአፄ ምኒልኩ ከአውሮፓው የሚለየው አንደኛ፣ ሰፋ ባለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የተደገፈ አለነበረም። ይህ ደግሞ የሳቸው ጥፋት አልነበረም። በጊዜው የነበረው የአገራችን ተጨባጭ ሁኒታና የዕውቀት ችግር ነፀብራቅ ነው። ሁለተኛ፣ ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓው በሬናሳንስ፣ በሪፎርሚሽንና በኢንላይተንሜንት የጭንቅላት ተሃድሶና የሳይንስ ግኝት ሂደት ውስጥ የማለፍ ዕድል አላጋጠማትም። ሶስተኛ፣ የአፄ ምኒልኩ መስፋፋት ከአውሮፓው ጋር ሲነፃፀር ይህንን ያህልም አረመኔያዊ አይደለም። የአውሮፓው ፊዩዳል ታሪክ ከአገራችን ጋር ሲወዳደር እጅግ የመረረና በጦርነት የታመቀ ለመሆኑ አያሌ የታሪክ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ።
ይሁንና የአፄ ምኒልክ አገዛዝ በተስፋፋበት ቦታ አልገዛም ያሉት ላይ ርምጃዎች ተወስዶባቸዋል። እሳቸው ከሚያውቁት ውጭ አንዳንድ ተገቢ ያልሆኑ ድርጎቶች ተፈጽመው ሊሆን ይችላል። ይሁንና ግን አፄ ምኒልክን እንደወራሪና ህዝብን ጨፍጫፊ አድርጎ መቁጠር ትልቅ የታሪክ ወንጀል ብቻ ሳይሆን፣ የራስንም የታሪክና የባህል ወንጀል ለመሽፈን መጣር ነው። ለምሳሌ ኦሮሞዎች በተስፋፉባቸው ቦታዎች በሙሉ የአማራና የሌሎች ብሄረሰቦችን ወንዶች በመግደለና ብልታቸውን በመቁረጥ ብዙ ግፍ እንደፈጸሙ ይታወቃል። እንዲያውም አፄ ምኒልክ ፈጽመዋል ከተባለው ግፍ ይልቅ የኦርሞዎች መስፋፋት በተለይም በአማራው ብሄረሰብ ላይ ይበልጥ አሰቃቂ ድርጊት እንደፈጸመ የታሪክ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። ይህ ዐይነቱ ድርጊት የጠቅላላው የኦርሞ ብሄረሰብ ድርጊት ነበር ብሎ ግን መወሰድና መፍረድ አይቻልም። ይሁንና ግን ማለት የሚቻለው በጊዜው በኦርሞዎች መስፋፋት የደረሰው ዕልቂት የኦሮሞ ብሄረሰብ ገና በአፍላ ላይ የነበረና ህብረተሰብአዊና ባህላዊ እንዲሁም ሰብአዊ እሴትን ያላዳበረ እንደነበር የሚያረጋግጠው። እንደዚህ ዐይነቱ ከአንድ ብሄረሰብ ግፊትና መስፋፋት የተነሳ በሌሎች ብሄረሰቦች ላይ የሚደረስ አሰቃቂ ድርጊት በግሪክ ዘመን የተለመደ ነበር። ስለዚህም ይህ ዐይነቱ አሰቃቂ ድርጊት የአንድ ብሄረሰብ መለያ አድርጎ መውሰድ ስህተት ነው። ይሁንና ግን እኛ የሰለጠን ነበርን፣ አማራዎች ናቸው የጨፈጨፉን የሚለው ታሪካዊና ሞራላዊ ድጋፍ ሊኖረው በፍጹም አይችልም።
በጊዜው የነበርውን የደቡቡን ክፍል ስንመረምር የምናገኘው መልስ ሁሉም የበለጸገ ወይም በስራ ክፍፍል የዳበረ ህብረተሰብ ወይም ማህበረስብ እንዳልነበራቸው ነው የምንገነዘበው። የሰሜኑም ክፍል ከደቡቡ እምብዛም አይለይም። በፊዩዳል አገዛዝና በክርስትና ሃይማኖች ጭፍን ዕምነት የተነሳ የዕደ-ጥበብና ንግድ ሊዳብሩ አልቻሉም። በዚህም ምክንያት የጠበቀ ህብረተሰብአዊ መተሳሰርና መንሰራሸር(Social Mobility) ሊኖር አልቻለም። ሁኔታውን ጠጋ ብለን በምንመረምርበት ጊዜ በተለይም አንዳንድ የኦሮሞ ኤሊቶች በፈረንጆች እየታገዙ የሚሰጡት ትንተና ፊክሽን ወይም ምንም ሳይንሳዊ ማረጋገጫ የሌለው ሀታት ነው። የኦሮሞ ብሄረሰብ ተሰበጣጥሮ የሚገኝና፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ አልነበረም። አብዛኛውም በከብት እርባታ ይተዳደር ስለነበር፣ ከአስራ ስድስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ኦሮሞዎች ሲንቀሳቀሱ ቀደም ብለው የነበሩ በደቡብ የሚገኙ ነገስታትንና ስልጣኔዎችን እየደመሰሱና እያፈራረሱ ነው ለመጀመሪያ ጊዘ መቀመጥ የቻሉት። ከአፄ ምኒልክ አገዛዝ መስፋፋት በፊት በአስራሰባተኛውና በአስራ ስምንተኛው ክፍለ-ዘመን በኦርሞ ማህበረሰብ ውስጥ በነበረው ዲይናሚዝም ጋዳ የሚባለው ስርዓት በመፈራረስ ላይ ነበር። አንዳንድ የኦሮሞ ኤሊቶች እንደሚሉን ጋዳ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት አልነበረም። ማርክስና ኢንግልስ ዘ እሪጂን እፍ ፕራይቤት ፕሮፖርቲ በሚለው መጽሃፋቸው ለማሳየት እንደሞከሩት በዚያ አካባቢ በነበረው የህብረተሰብ አወቃቀር የተፈጠረ የሚሊታሪ አደረጃጀት ነው ። ይህም ማለት ጋዳ በመደብ ላይ የተመሰረተና በተለይም ሴቶችን ከግል ሀብት ተሳታፊነት ያገለለ ነበር። ከዚህና ከሌሎች የሀብረተሰብ ታሪክ ዕድገት ሁኔታ ስንነሳ 1ኛ) የኦሮሞ ብሄረሰብ በአንድ አገዛዝ ስር የተዋቀረ አልነበረም። 2ኛ) አገዛዝ ወይም ሁሉንም የሚያጠቃልል መንግስት አልነበረውም። ይህም ማለት ሰፋ ያለ የቢሮክራሲና የአድሚኒስትሬሽን አወቃቀር አልነበረውም። 3ኛ) በውስጡም የዳበረ የስራ-ክፍፍል ስላልነበረው የተሳሰረ አልነበረም። እንደሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶችም የኦሮሞ ብሄረሰብም በዝቅተኛ የማቴርያል ዕድገት ሁኔታ ውስጥ የሚኖር ነበር። 4ኛ) የኦሮሞ ብሄረሰብ ቋንቋውን ከመናገር አልፎ የራሱን ፊደል የፈጠረ አይደለም። እንደሚታውቀው ከሚነገር ቋንቋ ባሻገር ለአንድ አገዛዝና ህዝብ የስልጣኔ መግለጫ የሚጻፍ ፊደልም መኖር አለበት። በዚህ ብቻ ስለህዝብና ስለህብረተሰብ ማውራት ይቻላል። 5ኛ) ከዚህ ስንነሳ የኦሮም ብሄረሰብ እንደ ህዝብና እንደ ህብረተሰብ ሊታይ የሚችል አልነበረም። ይህ እንግዴህ ከስሜት ውጭ ከሆነ የህብረተስብና የፍልስፍና ሳይንስ ግምገማ ስንነሳ ነው። ከዚህ ውጭ የሚደረግ ንትርክ መደነቋቆር ብቻ ነው። ስለፍልስፍና፣ ስለተፈጥሮ ሳይንስና ስለህብረተሰብ ሳይንስ በምናወራበት ጊዜ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ እንደሚያሳስበን እንደተማርን ሰዎች ከስሜት ውጭ መውጣትና መወያየት አለበን። በጥቁርና በነጭ እየጻፍን እንደዚህ ተደረግን፣ እንደዚህ ተባልን እያልን ሌላውን የዋሁን ለማሳመን የምናደረገው ሙከራ የመጨረሻ መጨረሻ የስልጣኔውን ጥምና ዕድገት የሚያራዝም ነው ። ወደ ጥፋትም የሚያመራን ነው። የህዝባችንን ሰቆቃ የሚያባብስ ነው። ዛሬ በጥራዝ ነጠቅነትና በአክራሪነት በኢትዮጵያ ላይ የሚዘምተው ጥቂቱ የኦሮሞ ኤሊት ነኝ ባይ በመሰረቱ የኦርሞ ብሄረሰብ ጠላት ብቻ ሳይሆን የጠቅላላውም ጥቁር ህዝብም ጠላት ነው። የሚሰራው ስራ ሁሉ ለነጭ የኦሊጋርኪና ለስለላ ድርጅቶች የሚሰራ ነው የሚያስመስለው። የተወሳሰበውን የአገራችንን ታሪክና በዓለም አቀፍ ደረጃ በግሎባል ካፒታሊዝም የተደረገብንን ግፊትና ዕንቅፋት ከማገናዘብ ይልቅ የነሱን አባባል በማስተጋባት ህዝባችን ስልጣኔ እንዳያገኝ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው። ይህም የሚያሳየው ምንድነው? ለኦሮምያ ነፃነት እታገላለሁ የሚለው ጥቂት ኤሊት የታሪክ፣ የህብረተሰብ፣ የባህልና የፓለቲካ ነቃተ-ህሊናው በጣም ዝቅተኝ ነው ማለት ነው።
ኢምፔሪያሊዝም፣ ወይም ግሎባል ካፒታሊዝምና የብሄረሰብ ጥያቄና ችግር !
ዛሬ አገራችን ስላለችበት የተወሳሰበ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የህብረተሰብ፣ የባህል፣ የብሄረሰብና የአካባቢ ቀውስ ከግሎባል ካፒታሊዝም መስፋፋትና አገሮችን በሱ ቁጥጥር ስር ከማዋል ውጭ ነጥሎ ማየት ትልቅ ስህተት ነው። ቀደም ብለው የነበሩ ምሁራንና ዛሬም ያለነው በከፊል የአገራችን የታሪክና የባህል ውጤት ስንሆን፣ በከፊል ደግሞ የግሎባል ካፒታሊዝም ውጤቶች ነን። ሁሉቱም አስተሳሰቦች ጭንቅላታችንን በመቅረጽ በቅራኔ ዓለም ውስጥ እንድንኖር በማድረግ አንደኛውን ከሌላው ለመለየትና ለመመረጥ የማንችልበት ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን። እንዲያውም ለአገራችን ትልቁ ውድቀት ከ1940ዎቹ በኋላ የተፈጠረው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታና ከግሎባል ካፒታሊዝም ጋር መተሳሰራችን ነው። ለምሳሌ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በፊት ቀደም ብለው ለዕድገት ትግል የጀመሩ አገሮችን ታሪክ ስንመለከት ከውጭው ዓለም ጋር ግኑኝነታቸውን በመቆጠቡና ለዕድገታቸው የሚያስፈልገውን ብቻ በመውሰድ ህብረተሰባቸውን ለመገንባትና ለመጠንከር ችለዋል። ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያና ቻይናን መመልከቱ በቂ ነው።
ያም ሆነ ይህ የግሎባል ካፒታሊዝም በአገራችን ውስጥ መስፋፋት በህብረተሰብአችን ውስጥ የነበሩት አነስተኛ ቅራኔዎችን በማጉላትና በማዳበር ቅራኔው እንዲፈታ ከማድረግ ይልቅ በማባባስ የዛሬው ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ ሊከተን ቻለ። በተለይም ከየብሄረሰቡ ለወጡ ኤሊት ነን ባዮች የተሳሳተ ንቃተ-ህሊና እንዲያዳብሩ በማድረግ ለህብረተሰብ ግንባታ እንቅፋት ወደ መሆን አመሩ። የመጡበትን ብሄረሰብ ምሽግ በማድረግና ለወጣቱና ለታዳጊው ትውልድ ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር የማይጣጣምና የማይረጋገጥ ውሸት በመናገርና በማስፋፋት ጭንቅላቱን በመመረዝ ጥላቻንና ዝቅተኛ ስሜትን አስፋፉ። ስለዚህም ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ከኢትዮጵያዊ ስሜትነት ይልቅ ከዚህኛው ብሄረሰብ ነኝ የመጣሁ ብሎ ጎልምሶ እንዲወጣ አደረገው።
እንደሚታወቀው በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የተዋቀረው አገዛዝ ንቃተ-ህሊናው በጣም ደካማ ስለነበር በህብረተሰብአችንን ውስጥ ማቆጥቆጥ የጀመሩትን አደገኛ ስሜቶችን ፈጣንና በተወሳሰበ የኢኮኖሚ ዕድገትና የከተማ ግንባታ ሊገታቸውና ልዩ መልክ ሊሰጣቸው አልቻለም። የአገዛዙ የኢኮኖሚ መሰረትም በጣም ደካማ ስለነበር ማህበራዊ ብሶቶችን ቀስ በቀስ ሊያሰወግድና የህዝባችንን የኑሮ ሁኔታ ሊያሻሽል አልቻለም። ይሁ ሁኔታና ቀስ በቀስ በጎሎባል ካፒታሊዝም በተፈጠረው የተዘበራረቀ ሁኔታና የተበላሸ ንቃተ-ህሊና የውጭው ዓለም ቀስ በቀስ ገብቶ እንዲፈተፍት አስቻለው።
ባለፉት 22 ዐመታት የተካሄደውን የክልልን ፖሊሲና ኢትዮጵያዊ ስሜትን መዳከም ዝም ብሎ ከሰማይ ዱብ ያሉ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን እንደ ህብረ-ብሄርና እንደ አገር እንዳትኖር፣ ወይም ደግሞ በዘለዓለም የርስ በርስ ትርምስ ውስጥ እንድትኖር ውስጥ ለውስጥ በውጭ ኃይሎች ሲቀነባበርና ጊዜውን ጠብቆ የመጣ ነው። እንደሚታወቀው የምዕራቡ ዓለምና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በአፍሪካ ምድር የተጠናከረችና ህዝቦቿ በመፈቃቀር የሚኖሩባትን አገር አይፈልጉም። በህዝብ ቁጥር በፍጥነት እያደጉ የሚሄዱ እንደ ኢትዮጵያና ናይጄሪያ የመሳሰሉ አገሮች በጣም አደገኛ ስለሆኑ በውስጣዊ ጠላትና በውጭ በመወጠር መዳከም አለባቸው። በተለያዩ ዘዴዎች ህዝቡ እረፍት ማጣትና ኃይሉንና ዕውቀቱን ሰብስቦ አንድ ነፃና የጠነከረ አገር መገንባት የለበትም። በተለይም ከአብዮቱ መፈንዳት ጀምሮ የውስጥ ኃይሎችን መርዳትና ረብሻ እንዲፈጠር ማድረግ፣ በዚያውም መጠን ህዝባዊ መተማመንና መተሳሰር እንዳይኖር ማድረግ የምዕራቡ፣ በተለይም የአሜሪካን ኤምፔሪያሊዝም ዋናው የብጥበጣ ዘዴ ነው። ቀደም ብሎ ከተጠነሰሰልን ስትራቴጂና በአብዮቱ ወቅት ኢትዮጵያን በሁሉም አቅጣጫ ማዳከም ጋር ስናያይዘው ወያኔና ሻቢያ የአሜሪካን ፕሮጀክቶች መሆናቸውን መጠራጠር አይቻልም። በዚህ ዐይነቱ ኢትዮጵያን በብሄረሰብም ሆነ በሃይማኖት የርስ በርስ ትርምስ ውስጥ ለመክተት የተለያዩ ኢትዮጵያውያን ኃይሎችም ተሳትፈውበታል። የዛሬው የኢትዮጵያዊነት ስሜት መገርሰስ የወያኔና የሻቢያ ስራ ብቻ ሳይሆን በቀኝና በግራ ስም የሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያውያን ኃይሎችም ሳያውቁም ሆነ አውቀው የወንጀሉ ተባባሪ ሆነዋል። ዛሬ ያለውም ችግር ስለኢትጵያዊነትና ስለ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ስናወራ ግራ የሚገባን ይህ ዐይነቱ ኢትዮጵያዊነት የፍልስፍናው መሰረት ምን እንደሆነ ስለማናውቅና ትንተናም ስለማይደረግ ነው።
አዚህ ላይ ይህንን በውጭ ኃይሎች የተጠነሰሰልንን ሴራ ተቃዋሚ ነኝ፣ ካለኔ በስተቀር ኢትጵያዊ የለም እያለ እዚህና እዚያ የሚሯሯጠው የቱን ያህል እንደገባው መረዳቱ ከባድ አይደለም። ነገሩን በጥብቅ ለተከታተለ የተቃዋሚውም ሆነ ሌላው ምሁራዊ ኃይል ይህንን ነገር አለመገንዘቡ ብቻ ሳይሆን እንዲነሳበትም አይፈልግም። እንደሚታወቀው ለአንድ ችግር መንስኤው ብቻ ሳይሆን እንዲፋፋም የሚያደርጉትም ነገሮች በደንብ ካልተጠኑና መከላከያና ማጥፊያ ዘዴ ካልተፈለገ ለብሄረሰብ ችግር ቁልፍ መፍትሄ ማግኘት አይቻልም። ስለዚህም ስለብሄረሰብ ችግር መፍትሄ ለመፈለግ በምንጥርበት ጊዜ ችግሩን ሁለንታዊ በሆነ መልክ ማጥናትና በግልጽ መወያየት ለችግሩ መፍትሄ ለማግኘት መንገዱ የተቃና ይሆናል። ችግሩን በተራ የብሄረሰቦችን መብት በማወቅ ይፈታል የሚለው አካሄድ ከህብረ-ብሄር ግንባታና ከጠንካራ ኢኮኖሚ ምስረታ ጋር ሊያያዝ በፍጹም አይችሉም። በመሰረቱ በአገራችን ምድር በዚህ አኳያ ያለው ችግር የብሄረሰብ ችግር ወይም መፍትሄ ያለማግኘት ሳይሆን፣ የአገራችን ኢኮኖሚ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ተመስርቶ ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ ያለመገንባት ችግር ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ የባህላችንና የማህብራዊ ዕድገታችን ቆርቁዞ መቅረት ለብሄረሰብ ችግር መቆጥቆጫ ሊሆን ችሏል።
ከዚህ ስንነሳ ውስጥ ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ህብረተሰብአዊ ድክመት በመጠቀም የዛሬው አገዛዝ በአሜሪካን፣ በእንግሊዝና በአንዳንድ የምዕራብ አገሮች በመታገዝና በማናፈስ ኢትዮጵያዊ ብሄረ-ስሜት እንዳይዳብር ማድረግ ቻለ።። ኢትዮጵያና አማራ ተመሳሳይ ተደርገው በመወሰዳቸው ዘመቻው ሁሉ ኢትዮጵያን በሁሉም አቅጣጫ ማዳከም ሆነ። አገዛዙ ሁሉም ነገር መበወዝ አለበት በሚለው ፍልስፍና ከዚህ አልፎ በመሄድና በግፍ የሚፈስለትን ዕርዳታ በመጠቀም በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተወዳዳሪነት የማይገኝለትን የባህል ውድቀት ውስጥ ከተተን። የግብረ-ሰዶም መስፋፋትና፣ ሴቶች ወደ አረብ አገሮች እየተሸጡ እንዲሄዱ በመደረግና በመደፈር አርግዘው መምጣት ኢትዮጵያዊ ናሽናሊዝም እስከነ አካቴው አንዲጠፋ ለማድረግ የታቀደ ስትራቴጂ ነው። ወደፊት ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን አገር ሳትሆን የአረቦች አገር ትሆናለች ማለት ነው። ይህ ነው የረዥሙ ጊዜ ስትራቴጂና የጊዜው ቦምብ።
ስለሆነም በኛ ምሁራን ዘንድ ያለው ትልቁ ችግር ከገዢው መደብ ንቃተ-ህሊና ማነስና ታሪክን ካለማገናዘብ የተነሳ አገዛዙ በውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር የሚያደረገው አገርን ማፈራረስ ያለመረዳት ችግር ነው። በተለይም የተቃዋሚው ኃይልና በድህረ-ገጾች ላይ የሚጽፈው ምሁር ነኝ ባይ ስለ ህብረተሰብ ግንባታ፣ ስለማህበረሰብ፣ ስለ ባህል፣ ስለ ህብረ-ብሄር ምስረታና ጥንካሪ፣ ሁለንታዊ የሆነ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ግንባታ አስፈላጊነት ስለማይታየው የዓለምን ፖለቲካ በየዋህነት መነጽር ነው የሚመለከታት። እጅግ የተወሳሰበውንና አደገኛ የሆነውን ዓለም የመመልከት ኃይሉ ደካማ ይመስላል። በዚህም ምክንያት የተነሳ የአገራችንን ችግር በራሳችን ኃይልና ዕውቀት ለመቅረፍና አገራችንን በጠንካራ መሰረት ላየ ለመገንባት የሚያበርክተው አስተዋፅዖ ይህንን ያህልም የሚያመረቃና አስተማማኝ አይደለም።
ከዶክተር ብርሃኑ የቃለ-መጠይቅ ስነሳና ስመረምር የአገራችንን የተወሳሰብ ችግር በጥልቀት ማየትና በግልጽ መነጋገር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። የአገራችን የተወሳሰበ ችግር ብልቅና ጥልቅ በሚሉ እግርና እጅ በሌላቸው ፓርቲ ነን ባዮች የሚፈታ አይደለም። የአገራችንን የተወሳሰበ ችግር ለመረዳት፣ እነ ፕላቶ ከክርስቶስ ልደት በፊት በአራተኛው ክፍለ ዘመን በፊት እንዳደረጉት፣ እነዳንቴ በአስራ አራተኛው ክፍለ ዘመን እንዳስተማሩትና የሬናሳንስን በር እንደከፈቱ፣ እነ ሺለር በአስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን እንዳካሄዱት ሰፋ ያለ ምሁራዊና የጭንቅላት ተሃድሶ እንቅስቃሴ በማድረግ ብቻ ነው ሊፈታ የሚችለው። ለዚህ ደግሞ ክፍትና ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል። የራስንም ድክመት መገንዘብ ይጠይቃል
የፖለቲካ አመለካከትና የፖለቲካ ችግር ጉዳይ !
ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ስለፖለቲካ ችግር በሚያወራበት ጊዜ እየደጋገመ የተናገረው፣ ስለ ስልጣን ጥያቄ፣ ስለውክልናና ሰለመንግስት ጥያቄ ነው። እንደውነቱ ከሆነ እነዚህ በራሳቸው ሰፊ ትንተና የሚያስፈልጋቸው ናቸው። አጠር ባለ መልክ ለማቅረብ ልሞክር።
በመጀመሪያ ደረጃ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር የውክልና ችግር ወይም ይወከለኛል የሚለውን የማጣት ችግር አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር እንደሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ችግር የህብረተሰብ ህግ ችግርን የተረዳና፣ እስካሁን ድረስ ሲያስጨንቁኝ የከረሙትን ችግሮች፣ ድህነት፣ መራብ፣ ንጹህ ውሃ ማግኝት፣ ስነ ስርዓት ያለው ቤት፣ የህክምና ጉዳይና የዕውቀት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ሊፈታልኝ የሚችልና ችግሬን የተረዳ ኃይል አለ ወይ? እያለ ሌት ከቀን ይጠይቃል። የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር ባለፉት አርባ አምስት ዐመታት በድህነትና በረሃብ ነው የምታወቀው፣ ስለዚህም ከዚህ ዐይነቱ ውርደት ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ የሚያላቅቀኝን እትዮጵያዊ ኃይል ነው የምመኘው እያለ ነው ሌት ከቀን የሚጸልየው። ስለዚህም ከጎኔ ሆኖ የሚያታሰተመረኝና ችግሬን የሚጋራ፣ እንዲሁም ከኔ በመማር አዲሲቱንና የተከበረች ኢትዮጵያን የሚገነባልኝን ኢትዮጵያዊ ኃይል ነው የምመኝው እያለ ነው ፈጣሪን የሚማፀነው።
ባለፉት 22 ዐመታት የሚደረገውን በተቃዋሚው ሰፈር ያለውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ስንመለከት ሁሉም ይህንን ወይም ያንን የፖለቲካ መስመር እንደሚያራምዱ ነው ሲነግሩን የከረሙት። አንደኛው ሊበራል ዴሞክራት ነኝ፣ ሌላው ደግሞ ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ነኝ በማለት በዚህ ዐይነቱ የፖለቲካ መስመር ለውጥ ለማምጣት እንደሚፈልጉ ነው የሚስብኩት። አሁን ደግሞ ማዕከለኛ የቀኝ መስመር(Centre Right) እናካሂዳለን የሚሉ ብቅ እንዳሉ ሰምተናል። እነዚህና ሌሎችም ይህንን የመሳሰሉትን ስሞች ለምን እንዳንጠለጠሉ ግልጽ ባይሆንም፣ ሁሉም በኢትዮጵያ ምድር የገበያን ኢኮኖሚና የሊበራል ዲሞክራሲ ዕውን እንደሚያደርጉ ነው የሚነግሩን። ይሁንና ግን በዚህ ዐይነቱ የፖለቲካ መስመር የተወሳሰበውን የኢኮኖሚ፣ የማሀበራዊ፣ የባህል፣ የህብረተሰብና የፖለቲካ ምስቅልቅልና ችግር እንዴት ደረጃ በደረጃ ሊፈቱ እንደሚችሉ ሲያብራሩ አይሰማም።
በጥብቅ እንደተከታተልኩት ከሆነ የአብዛኛዎቹ ፓርቲ ነን ባዮች ችግር፣ ይኸኛውን ወይም ያኛውን የፖለቲካ መስመር እንከተለለን ሲሉ፣ 1ኛ) የፖለቲካ መስመራቸውን በአንዳች ፍልስፍና ላይ አልመሰረቱም፣ 2ኛ) ስፋ ያለ የቲዎሪ ትንተና አልሰጡም፣ አይሰጡምም። 3ኛ) አብዛኛዎቹ ድርጅቶች ይህንን ወይም ያንን የፖለቲካ መስመር እንከተላለን ሲሉ፣ በመጀመሪያ ደረጃን በሶሻሊዝም ስም በአገራችን ምድር የተፈጸመውን አስከፊ ድርጊት እንደመቀጣጫ በመውሰድ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከሌሎች አገር ልምድ በመነሳት ነው ይህንን መስመር ልንመርጥ የተገደድነው ነው የሚሉን። ትልቁ የአገራችንም ሆነ የብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ችግር ከአገራቸው ተጨባጭ የማቴሪያል ሁኔታ፣ ከህዝቡ ንቃታ-ህሊና ደረጃና የሳይኮሎጂካል ሜክ አፕ ሁኔታ በመነሳት ሳይሆን በአቦ ሰጡኝ የምዕራቡን ዓለም ለማስደሰት ብለው የሚይዙት አቋም ነው። ይህ ዐይነቱ ተራ ሎጂክና ሳይንስና ቲዎሪን ያላካተተ ወይም በነሱ ላይ ያልተደገፈ የፖለቲካ መስመር የመጨረሻ መጨረሻ ለሌላ ውዝግብና ትርምስ ዳርጎን ነው የሚሄደው።
በመሆኑም የብዙዎችን ፓርቲዎች አካሄድ ስመለከትና ስመረምር እንዴት አድርገን ስልጣን እንይዛለን ከሚለው ስሌት በመነሳት እንጂ፣ በምን ፍልስፍናና ቲዎሪ ብንደገፍ አፍጦ አግጦ የሚታየውን ችግር አስወግደን የጠነከረችና የተከበረች ኢትዮጵያን እንገነባለን የሚለው ትልቁ የታሪክ ፕሮጀክት አይደለም የሚያሳስባቸው። የፖለቲካ ስልጣን ማነህ ባለሳምንት እንደሚባለው አነጋገር አንዱ ለሌላው የሚሰጠውና የሚያስረክበው ጉዳይ ሳይሆን ማንኛውም ለፖለቲካ ስልጣን እታገላለሁ የሚል ሁሉ የአንድን ትውልድ ዕድል ብቻ ሳይሆን እንዴት አድርጌ ታሪካዊ መሰረት በመጣል ለሚቀጥለው ትውልድ ጥሩና ቋሚ ነገር ማስተላለፍ እችላለሁ ብሎ በመነሳት ለታሪክ የሚዘጋጅበት መድረክ ነው።
በእኛም አገር ሆነ በብዙ የሶስተኛው ዓለም ያለው የፖለቲካ አደረጃጀትና የፅንሰ-ሃስብ ግንዛቤ ለብዙዎች ግልጽ የሆነ አይመሰለኝም። በመጀመሪያ ደረጃ ፓለቲካ አንድን አገር ጥበባዊ በሆነ መልክ ማስተዳደር ማለት ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴና ለስልጣን የሚደረገ ትግል ከተራ የፖለቲካ አደረጃጀት የሚያልፍ ነው። ማለትም ለፖለቲካ ስልጣን ትግል ሲደረግ ተራው ህዝብም እያንዳንዱ ፓርቲ ለምን እንደሚታገልና እንዴትስ ቃል-ኪዳን የሚገባውን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ማስረዳት አለበት። በሶስተኛ ደረጃ፣ የፖለቲካ ስልጣን ለጥቂት አዋቂ ነን ለሚሉ ፓርቲዎች የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን ሰፊው ህዝብም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሊሳተፍበት የሚችልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። ለዚህ ደግሞ የግዴታ የህዝቡ ንቃተ-ህሊናና የመጠየቅና የመከራከር ችሎታ በየጊዜው ከፍ እንዲል አስፈላጊው እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው። በአራተኛ ደረጃ፣ ለስልጣን የሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በፓርቲዎች መሀከል ውዝግብ እንዲፈጠር የሚያደርግ ሳይሆን በርዕይ ላይ በመመስረት ቀና አመለካከት ያላቸውን ሁሉ በፖለቲካ ክንዋኔ ውስጥ ሊያሳትፍ የሚችል መሆን አለበት።
ከዚህ ስንነሳ በመጀመሪያ ደረጃ እንዴት ስልጣን መያዝ ይቻላል ብሎ ማውጠንጠን ሳይሆን፣ እንዴት አድርጎ የተሰበጣጠረውን ኃይል በአንድ ለአገር ግንባታ በሚያገለግል ፍልስፍና ዙሪያ ማሰባሰብ ይቻላል በሚለው ላይ ነው መወያየት ያለብን። ይህ ማለት ግን አመራር አያስፈልግም ማለት አይደለም። ጥያቄው የኢትዮጵያ የተወሳሰበ ችግር በውክልና ዲሞክራሲ ሊፈታ እንደማይችል ለማሳየትና፣ ትግላችንም ከዚህ ርቆ በመሄድ ህዝቡንም ሊያሳትፍና ለውይይት ጋብዞ የአገሪቱን ችግር በጋር ለመቅረፍ የሚቻልበትን ዘዴ ለመተለም ነው። ከብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ልምድ እንደምናየው በየአራት ዐመቱ በሚካሄድ ምርጫ የህዝብ ችግር ሲፈታና መረጋጋት ሲኖር አናይም። በብዙ አገሮች ድህነት፣ በስልጣን ላይ ባሉ ኃይሎች መጎሳቆልና መብትን መገፈፍ፣ ብሄራዊ-ነፃነትን ማጣትና የውጭ ኃይሎች ተገዢ መሆን፣ ባጭሩ ውርደትን ነው የምናየው። ስለዚህም ዶክተር ብርሃኑ በትክክል እንዳስቀመጠው ምን ዐይነት ህብረተሰብ ብንመሰርት ነው እኩላዊነትን ማስፈን የምንችለው? በሚለው ላይ መወያየት ያለብን ይመስለኛል።
ይህ ብቻ ሳይሆን የኢትዮያም ሆነ የብዙ አፍሪካ አገሮች ዋናው ችግር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ብሄራዊ ሀብት ለመፍጠር ያለመቻል ብቻ ሳይሆን፣ አብዛኛዎቹ መንግስታትና አገዛዞች አንድ ስርዓት ያለው ህብረተሰብ በምን መልክና እንዴት ጥበባዊ በሆነ መልክ እንደሚዋቀርና እንደሚተሳሰር አለመረዳትና ችሎታ ማነስ ነው። አብዛኛዎቹ አገዛዞች የየአገሮቻቸውን ሀብት ዝም ብለው የሚዘርፉና የሚያዘርፉ፣ ለዚህም መብት የተሰጣቸው የሚመስላቸው፣ ወይም ደግሞ የየአገሮቻቸውን ሀብት የግል ሀብታቸው አድርገው የሚቆጥሩ ናቸው። ስለሆነም ህዝባዊ ሀብት የመፍጠርና ታሪክን የመስራት አቅማቸው በጣም የተዳከመ ነው። ስለዚህም በአገራችንም ሆነ በአብዛኛዎቹ አፍሪካ አገሮች ያለው ማህበራዊና የባህል ቀውስ ከዚህ የሃሳብ ግንዛቤና የዕውቀት ጉድለት የተነሳ ነው። ህዝባዊ ሀብት መፍጠር ካልተቻለ ደግሞ የሚከፋፈል ሀብት ሊኖር አይችልም፤ እኩልነትም አይኖርምም። ከዚህ ስንነሳ መካሄድ ያለበት ትግልና፣ በመሀከላችንም መኖር የሚገባው ውይይትና ክርክር በምን ዐይነት ዘዴ ነው ፈጣን የሆነ ህዝባችንን ከድህነት የሚያላቅቅ የብሄራዊ ሀብት መፍጠሪያ ዘዴ መፈለግ የሚቻለው? እንዴትስ ብናደርግ ነው ከላይ ወደ ታች ሳይሆን ከታች ወደ ላይ የሚገነባ፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ሊያካትት የሚችል የኢኮኖሚ ግንባታ ማካሄድ የሚቻለው? በሚለው ላይ ማትኮሩ ለችግራችን መፍትሄ እንድናገኝለት ይረዳናል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ከአውሮፓም ሆነ ከራሺያና ከቻይና ልምድ እንደምንማራው ዲሲፕሊን በሌለበት፣ የስራ ፍላጎት በመነመነበት፣ መናናቅ በተስፋፋበት፣ ማላገጥና ማሾፍ እንደሙያ በሚያዝብትና፣ በተጨማሪም ደግሞ የተማረው ኃይል ከአገሩ ይልቅ ለውጭ ኃይል የሚሰራና የውጭን ኃይል ትዕዛዝ የሚቀበል ከሆነ ስለ ዕድገትና ድህነትን ስለመቅረፍ ጉዳይ ማውራት በፍጹም አይቻልም።
ስለሆነም በፓርቲዎችም ሆነ በድርጅቶች ዘንድና መሀከል መደረግ ያለበት ትግል እኔ ነኝ የኢትዮጵያን ህዝብ የምወክለው እያሉ ፕሮግራም እየጻፍ ወደ ኤምባሲዎች መሮጥ ሳይሆን፣ ሀቀኛ ነኝ የሚል ሁሉ ፕሮግራም ከመጻፉ በፊት በሃሳብ ዙሪያ ክርክርና ውይይት መክፈት መቻል አለበት። የኢትዮጵያን ሁኔታ በትክክል ለሚያነብ ሰው የአገራችን ችግር በአንድ ፓርቲ ሊፈታና በትከሻው ላይ ሊወድቅ የሚችል አይደለም። የአገራችን ሁኔታ የሁሉንም ኃይል ተሳትፎ ይጠይቃል። ስለዚህም የፓርቲዎች ቁጥር ወደ ሁለትና ወደ ሶስት ብቻ መቀነስ አለበት። ሌላው ወደ ስራ መሰማራት አለበት። ከዚህ በተረፈ የብሄረ-ሰቦችን ሁኔታ ለተመለከተ፣ ችግሩ የኢትዮጵያ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ ኩሎ ኮንታ፣ ወዘተ. ችግር ሳይሆን፣ ከዚህም ከዚያም የተውጣጣው ኤሊት ነኝ ባይ የፈጠረው ችግር ነው። ትላንትና አማራ፣ ዛሬ ደግሞ ትግሬ፣ ነገ ደግሞ እኔ መግዛት አለብኝ በማለት የሚነዛው ከሳይንስና ከፍልስፍና ውጭ የሆነ አጉል አካሄድ ነው። ከዚህም ሆነ ከዚያ ተውጣጣ፣ ይህም ሆነ ያኛው ኃይል ስልጣን ይዞ መሰረታዊ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር እስካልተፈታ ድረስ የብሄረሰቦች ችግር መልስ ሊያገኝ አይችልም። የማንኛውም ህዝብ ጥያቄ በመጀመሪያ ደረጃ የመብላትና የመጠጣት ጉዳይ ነው። ከዚያ በኋላ ነው ስለሰፊው የመብት ጥያቄ መወያየት የሚቻለው። ይህም ቢሆን ከግለሰበአዊና ከህብረተሰብአዊ ነፃነት ውጭ ሊታይ የሚችል መሆን የለበትም። ብሄረሰቦችን በክልል እየከለሉ ነፃ ወጥተሃል፣ ሌላው አይድረስብህ ማለት ደንቁረህ ቅር ማለት ነው። እንደዚህ ዐይነቱ በብሄረሰብ ዙሪያ የሚካሄድ ትግል የተፈጥሮንንም ሆነ የህብረተስብ ሳይንስን ህግ ይፃረራል። በተጨማሪም የብሄረሰቦች ችግር አለ፣ ኢትዮጵያ የብሄረሰቦች እስር ቤት ነች እያሉ ማራባት ታዳጊው ወጣት በማያስፈልግ አስተሳሰብ ጭንቅላቱ በመጠመድ ለዕውቀትና በጋር በመነሳት አገር አንዳይገነባ መንገዱን እንደመዝጋት ይቆጠራል። ከዚህም ባሻገር እያንዳንዱ ብሄረሰብ ባህሉ ቢጠበቅለት፣ በቋንቋው ቢናገር፣ ሌሎችም ነገሮች ተግባራዊ ቢሆኑለት፣ እነዚህ ሁሉ ነገሮች የኑሮውን ሁኔታ እስካላሻሻሉለት ድረስ፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት እስካላደረጉትና፣ ሰፋ ባለ የስራ-ክፍፍል ታግዞ ሰፋ ያለና የተወሳሰበ ህብረተሰብ እስካልመሰረተ ድረስ የአንድ ብሄረሰብ ባህል ተጠበቀ አልተጠበቀ ትርጉም የለውም። በብሄረሰቦች ዙሪያ የሚደረገው ትግልና የብሄረሰብ ርዕይ የመጨረሻ መጨረሻ የየብሄረሶቦችን ኤሊቶች ጥቅም የሚያስጠብቅና የሚጨፍሩበት እንጂ ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅም አይደለም። ፕላቶ ከሁለት ሺህ አራት መቶ ዐመት በፊት እንዳለው በጎሳ አካባቢ መደራጀትና የጎሳ ሶሊዳሪቲ ማሳየት አንድን ህዝብ ለሌላ የርስ በርስ ግጭት መጋበዝ ነው።
በተረፈ ቃለ ምልልሱ ለውይይት የሚያመችና ሁላችንንም የሚጋብዝ ነው። ሁሉም በሙያው የአቅሙን ከወረወረና ከተከራከርን መፍትሄ ማግኘት እንችላለን። በምሁሩ ዘንድ መፈራራት መኖር የለበትም። እያንዳንዳችን በምናምነው ርዕይ ወይም ፍልስፍና፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር በዚህ መንገድ ነው ሊፈታ የሚችለው ብለን ማሳየት መቻል አለብን። ሁሉም በአጠቃላይ ዙሪያ ከመሽከርከር ይልቅ በጥልቀትና በርዕይ ደረጃ የሚያምንበትን ወደ ውጭ አውጥቶ ለማነጋገር ቢሞክር ለችግራችን የተሻለ መፍትሄ ማግኘት እንችላለን። መልካም ንባብ !!
ፈቃዱ በቀለ