(ገለታው ዘለቀ)
ኣንድ ጊዜ ኣባባ ተስፋየ ከዚያ ከሚያምርባቸው የ ልጆች ክፍለ ጊዜ ዝግጅታቸው ጠፉብኝና ኸረ የት ገቡ? ብየ ኣንዱን ጠየኩ።
“ኣልሰማህም እንዴ ?”
በፍጹም ምን ሆኑ? ደንገጥ ብየ እንደገና ጠየኩ።
ያ ሰው እየሳቀ “ባለፈው ጊዜ ኣዲሱ ኣመት የሰላምና የእርቅ ያድርግልን ብለው በመናገራቸው የመንግስት ሰዎች ማን ሲጣላ ኣዩ? ብለው ኣባረሩዋቸው እኮ!” ሲለኝ ለደቂቃዎች እንደዚያ የሳቅኩበት ጊዜ ትዝ ኣይለኝም። የሁለታችንም ሳቅ ካለቀ በሁዋላ እውነተኛው ስሜት ሲመጣ ደሞ ያስለቅሳችሁዋል። ነገሩ እውነት መሆን ኣለመሆኑን ኣጥብቄ ኣልጠየኩም፣ ለነገሩ ከዚያ ቀን በሁዋላም ከብዙ ሰው ይህንኑ ሰማሁ። ነገሩ በትክክል ሆነም ኣልሆነም ያ ሁሉ ሰው መንግስት እንደዚያ ሊያደርግ ይችላል ብሎ ማሰቡ ራሱ ነገሩ መሆኑን ኣለያም ሊሆን መቻሉን ያሳያል። በዚያች ኣገር ምን የማይሆን ኣለና።
በዚህ ስደነቅ ስደመም ደሞ ኣንዴ እንዲህ ሆነላችሁ። እንዲሁ ኣንድ ሻይ ቤት ተቀምጨ ወጪ ወራጁን እማትራለሁ። በመሃል ኣንድ ሰው ሳምሶናይት የሚባለውን ቦርሳ ጠልጠል ኣርጎ ገባና ወዲያ ወዲህ ካየ በሁዋላ የኔን ጠረንጴዛ ተጋርቶ ለመቀመጥ በትህትና ጠየቀኝ። ወንበሩን ሳብኩለት። እንደኔው ሻይ በሎሚ ኣዞ ቁጭ ኣለ። ጥቂት ቆየት ካለ በሁዋላ ያቺን ቦርሳውን ከፈተና ኣንዲት ጋዜጣ ኣውጥቶ ዘረጋጋና ማንበብ ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ሁለት ሰዎች ወደ ሻይ ቤቱ ገቡና ከኛ መቀመጫ ትይዩ ተሰየሙ። ኣንዱ የቀኝ እግሩን ቀጥ ኣርጎ ዘርግቶ ነበር የተቀመጠው። በሁዋላ ኬክ ሊመርጡ ሲነሱ እንደሚያነክስ ሳይ እግሩ ኣርቴፊሻል መሰለኝና ኣለ ኣይደለም ኣሳዘነኝ። የሚጠጣውን እየጠጡ ኬካቸውን እየበሉ ያወካሉ። እኔና ከፊቴ ያለው ሰውየ ግን ጸጥ ብለናል። ትንሽ እንደቆየ ያቺን ጋዜጣውን በሽንጡዋ ሸመለለና ወደ ቦርሳው ከተተ። ደሞ ወዲያው ኣጨበጨበና ሂሳብ ከፈለ።
እኔም እስካሁን ባናወራም ኣብርን ለትንሽ ሰኣትም ቢሆን ባንድ ጠረንጴዛ በልተን ጠጥተናል ዝም ኣይባልም ብየ ነው መሰለኝ ቻው ለማለት ምንም ኣልቀረኝም።በመሃል ያ ያነክሳል ያልኩዋችሁ ሰውየ ድንገት ወደኛ ዞረና
“ምን ኣልክ ኣንተ? ምን ኣልክ? ድገመው እንጂ…… ልብ በሉ… ሰዎች ልብ ኣርጉ.. ምን ኣልክ ኣንተ?…” እያለ ይጮሃል። ሁላችንም ተደናገጥን። ያ ከኔ ጋር ጠረንጴዛ ተጋርቶ የነበረው ሳምሶናይቱን እንዳንጠለጠለ “ኸረ እኔ ምንም ኣልወጣኝም ጌታየ ምን ነካዎት” ይላል ኣስር ጊዜ። ከዚያ ከሚያነክሰው ጋር ያለው ሰውየም ኣብሮ ያጫፍራል። በሁዋላ ይሄ ከኔጋር የነበረው ሰው መንጨቅ ብሎ ሲወጣ ሁለቱም ተከተሉትና ጭቅጭቁ ከውጭ ቀጠለ።
ያው መቼም ሃይ ሃይ ማለት ያገር ባህል ነውና ወደ ውጭ ወጥቼ ኸረ እሱ ምንም ኣላለም ፣ ምንም ሲል ኣልሰማሁትም ተረጋጉ እያልኩ ለመምከር መቼም ያቅሜን ሞከርኩ።
ያ የሚያነክሰው እንባው ሁሉ የመጣ ይመስላል። ይገርማል ዋሽቶ የሚያለቅስ ሰው ቢገጥማችሁ ምን ትላላችሁ?
“እንዴት ትሰድበኛለህ……” እያለ ሲሙዋገት ጓደኛውን ጠጋ ብዬ እናገላግላቸው እባክህ ምን ኣለ? ምንም ኣላልም እኮ ኣልኩት።
“የለም የለም እኔ ራሴ ሰማሁት እኮ ወራዳ ነው ሽባ ብሎ ሰደበው እኮ”
ደነገጥኩና መቼ? ብየ ጠየኩ::
ወደዚህኛው ሰውየ ዞሬ ትተዋወቃላችሁ እንዴብዬ ጠየኩ::
“በፍጹም ኣንተዋወቅም ኣለ” ግራ የተጋባው ባለ ሳምሶናይቱ ፈጠን ብሎ
“ሂሳብ ከከፈለ በሁዋላ ድምጹን ከፍ ኣርጎ እኮ ነው የሰደበው”
በውነት ግራ ግብት ኣለኝ። ሁዋላ ላይ ይሄ የሚያናግረኝ ሰው ስልኩን ኣወጣና ኣንድ ሁለት ቁጥሮችን ነካካና ወደዛ ዞር ብሎ ጥቂት ኣወራ መሰለኝ። ወዲያው እንደተመለሰ ኣንድ ፖሊስ መጣና ያንን ባለ ሳምሶናይት
“ቅደም ኣለው።
”
በዚህ ጊዜ ወደ ፖሊሱ ጠጋ ብዬ ምንም እኮ ኣላለም እኔ እዚህ ነበርኩ
ምንድነው ችግሩ ለማለት ሞከርኩ። ፖሊሱ በግንባሩ ጥሩ ኣርጎ ገረፈና ኣስቆመኝ። ባለ ሳምሶናይቱ እንዲሁ “ምን ኣጠፋሁ” እንዳለ ይነዱት ጀመር። ሁኔታው ገርሞኝ ነበርና ባጭር ርቀት መከተል ጀመርኩ። የሚገርማችሁ ያ ቅድም ቀኝ እግሩን ይጎትት የነበረው “ሽባ” ተብየ ተሰድቢያለሁ የሚለው ሰውየ ኣሁን በግራው ማንከስ መጀመሩን ትኩር ብዬ ኣስተዋልኩና የሆነ ነገር እየሆነ እንደሆነ ገባኝ። ብዙም ሳልርቅ ወደ ሁዋላየ ሂሳቤን ለመክፈል ተመለስኩ። ወደ ሻይ ቤቱ በር ስቃረብ ኣንዱ “ወሰዱት ኣይደል?” ኣለኝ:: ኣዎ ወሰዱት ኣልኩና ግን ምንም ኣለማጥፋቱን ኣስረግጨ ነገርኩት። ጥቂት ኣየኝና “ወንድሜ ተጠንቀቅ ከዚህ ከሚያነክሰው ጋር ያለው ሰውየ የነሱ ጆሮ ነው የተለያየ ልብስ እየለበሰ ሲሰልል ነው የሚውለው ተነቅቶበታል” ኣለኝ። እኔም ወዲያው ጠርጥሬ ስለነበረ ገባኝ። እንግዲህ ያን ሰው በዚህ ርካሽ ስራቸው ኣወናጅለው የሆነ ነገር ኣርገውታል ማለት ነው።
ባለፈው ጊዜ ግራዚያኒን ለመቃወም ሰልፍ ወጥተው ከነበሩት መካከል ኣንዱ በኢሳት ቴሌቪዥን ኢንተርቪው ተደርጎለት ሲናገር ልብ ይነካል። ሲቪል እየለበሱ መገናኛ እየያዙ እንዴት የስነ ልቡና ጫና እየፈጠሩ እንደሆነ ገለጸ። ኑሮ ኣይደለም የምንኖረው ኣለ። ያሳዝናል። ሃሳብን መግለጽ ጥቂት ኣስተያየት መሰንዘር በስነ ልቡናና በኣካል የሚያስቀጣ ነገር የሆነባት ሃገር ናት ኢትዮጵያ።
መነሻየኮ ስለ እስክንድር ነጋ ነው። ይህን ያመጣሁት በእንዲህ ባለ ኣገር፣ እስክንድርን የመሰለ ፖሊሲ የሚያመነጭ፣ የሰባዊ መብት እንዲከበር ለማድረግ የሚታገል ሰው ስንት ስነ ልቦናዊ ቅጣት እንደሚቀበል ለመገመት እንዲያስችለን ነው ።
እስክንድር የታሰረበትን ምክንያት ኣለም ኣውቆታል። እስክንድር የታሰረው በውስጡ ያለው የእኩልነትና የፍትህ ራእይ እንቅልፍ ኣልሰጥ ስላላቸው ነው። ያንን በገቢ ኣለመመጣጠን የሚሰቃየውን ህዝብ እህል በልቶ እኩልነት ሰፍኖ ማየት የሚፈልግ ሰው መሆኑ ነው የ እስክንድር ሃጢያቱ።እስክንድር ቅንና ርህሩህ ነው። የጻፋቸው ጽሁፎች ዋቢዎች ናቸው። የሱ ወንጀል መምከሩ፣ ኣቅጣጫ ማሳየቱ ብቻ ነው።
የነ ርእዮት ኣለሙም ወንጀል ይሄው ነው። መናገር፣ መምከራቸው ነው ወንጀላቸው።
ግን እውነት ሊሞት ይችላል። መሞት ብቻ ኣይደለም ሊቀበርም ይችላል። ግን ደሞ እውነት መቃብር ፈንቅሎም የመነሳት ሃይል ኣለው። መንግስት ይህን መረዳት ኣለበት።
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ
geletawzeleke@gmail.com