Monday, March 7, 2016

የመለስ ዜናዊ ራእይ

March 7,2016
መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ ማን ነው?
Ethiopia's Prime Minister Meles Zenawi stands behind a transparent bullet-proof screen as he addresses supporters of the Ethiopian People's Revolutionary Democratic Front (EPRDF) party at the Meskel Square in Addis Ababa, May 25, 2010. Zenawi urged the international community on Tuesday to respect his landslide election win and said foreign forces could not overturn the outcome and blood should not be shed. REUTERS/Thomas Mukoya (ETHIOPIA - Tags: ELECTIONS POLITICS)
መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ የጠላት ጠላት ደመኛ ጠላት ነው። ከአባቱ፣ ከእናቱና ከአያቶቹ የወረሰው በኢትዮጵያና በሕዝቧ ላይ የፈጸመው ግፍ፤ የሃገር ማፍረስ ድርጊት በታሪክ የማይረሳ ነው። እሱ ብቻ ሳይሆን የህወሓት አመራርንም ይጨምራል። የስም ዝርዝራቸውን በተለያዩት ጽሁፎቼና ከዚህ በላይም ስላካተትኳቸው እንሱን መመልከትና ማመሳከር ይቻላል።
የመለስ ዜናዊ ራእይ በኢትዮጵያ ልማት፣ እድገት፣ ዲሞክራሲ ማለትስ ምን ማለት ነው? በእርሱ አመራር ለ21 ዓመታት ኢትዮጵያ በልማትና በዲሞክራሲ አብባለች የሚሉት የህወሓት ደጋፊዎችና አጋር ድርጅት ተብለው የሚጠሩት ጸረ-ሕዝብና ጸረ-ኢትዮጵያ ስብስብ ብቻ ናቸው። ብዙ ለሆዳቸው ያደሩም አሉባቸው። ነገሩ የተጋላቢጦሽ ነው። መለስ ዜናዊ የሚመራው ህወሓትና አመራሩ በተፈጥሮው ጸረ-ሕዝብና ጸረ-ዲሞክራሲ ነው። ህወሓት አፈጣጠሩ አምባገነን እና ፋሽስት፣ እንዲሁም ጸረ-ዲሞክራሲ ሆኖ ያደገ ከመቅጽበት የልማት፣ እድገትና ዲሞክራሲ አራማጅ ሊሆን አይችልም። ጎባጣና ጠማማ ሆኖ ያደገ ባህር ዛፍ ተቃንቶ ለኤሌክትሪክ ምሰሶ ወይም ለቤት መስሪያ ማገር ልታደርገው አትችለም። በምሳር ቆራርጦ ማገዶ ከማድረግ ውጪ። ህወሓትን በዚህ አይነት ልንመለከተው ይገባል። ስለሆነም የመለስ ዜናዊ ራእይ ጸረ-ሕዝብ፣ ጸረ-ልማት፣ ጸረ-እድገት፣ ጸረ-ዲሞክራሲ ነው። መለስና ግብረአበሮቹ በዘር ማጥፋት ወንጀል የተሰማሩ፣ በሙስና የሕዝብና የሃገር ሃብት የዘረፉ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ በፋሽስት መዋቅራቸው ያሰቃዩና የገደሉ ናቸው። እንደዚህ ያለ ጨቋኝና ፋሽስት መንግስት ልማታዊ ሊሆን አይችልም።
መለስ ዜናዊና ህወሓት ለኢትዮጵያና ሕዝቧ ምን ናቸው? በመለስ ዜናዊና በስብሃት ነጋ የሚመራው ፋሽስት ፓርቲ፣ ኢትዮጵያን ከግንቦት ወር 1983 ጀምሮ ከተቆጣጠሩ ወዲህ ኢትዮጵያና ሕዝቧ በወያኔ ሀውሓት ቅኝ አገዛዝ የወደቀችበት ወቅት ሆኖ፣ እነሆ ቅኝ ገዢው ህወሓት በሃገራችን አረመኔያዊ ድርጊት እየፈጸመ ይገኛል። በመለስ ዜናዊ የአገዛዝ ዘመን የኢትዮጵያ ሉአላዊንት ፈርሷል። ጥንታዊና ታሪካዊ የቀይ ባሕር ወደቦቿን አጥታለች። ሕዝብ በዘሩ እየታየ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል። ስለዚህ መለስ ዜናዊና ህወሓት እንዲሁም አመራሩ የኢትዮጵያ ደመኛ ጠላት ናቸው።
መለስ ዜናዊ የወታደራዊ ሳይንስና ስትራተጂ ባለ ራእይ ይባላል። ይህ አነጋገር ደረቅ ውሸት ነው። መለስ ዜናዊን የሚያውቁና አብረውት በትግሉ የነበሩ ታጋዮች የማይቀበሉት ጉዳይ ነው። የህወሓት መንጋ በምን ዓይነት የውሸት አዘቅት ውስጥ እንደሰመጠ በግልጽ የሚያሳይ ነው። መለስ ዜናዊ ከትግሉ መጀመሪያ አንስቶ ለብዙ ዓመታት አብረን ተጉዘናል። በጣም የሚተማመንብን ጓደኞቹ ተክሉ ሃዋዝና እኔ ገ/መድህን አርአያ ነበርን። በሚገባ ስለምናውቀው የወታደራዊ ስታርቴጂስት አልነበረም። እውቀቱም ችሎታውም ፈጽሞ አልነበረውም። ሃቁ ይህ ነው።
“ጅብ በማያውቁት ሃገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ” እንዳለው ዓይነት ነው። መለስ ዜናዊ ከፈሪነቱ የተነሳ በተለያዩ ጦርነቶች ፈርቶ የሸሸ፣ በህወሓት ታሪክ ውስጥ በፈሪነቱ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘ ግለሰብ ነው። ከሸሸባቸው ጦርነቶች ለአብነት፤
  1. በ1969 ከአድዋ ኦፐሬሽን ጦርነቱ እንደተጀመረ ፈርቶ የሸሸ፣
  2. በ1970 ከአዲ ደእሮ ፈርቶ የሸሸ፣
  3. በ1971 መጀመሪያ ላይ ከማይቅነጠል ውጊያ ፈርቶ የሸሸ፣
  4. በ1971 ህዳር ወር ከፈረስ ማይ ጦርነት ፈርቶ የሸሸ፣
  5. ሰኔ ወር 1971 ከሃገረ-ሰላም ውጊያ ታመምኩ ብሎ መሬት ላይ ሲንከባለል በበቅሎ ተጭኖ እንዲምለስ የተደረገው  ናቸው። በምስክርነት የሰራዊቱ የጦር አዛዥ አረጋዊ በርሄ የሚያውቀው ጉዳይ ነው።
በህወሓት ውስጥ ማንም ታጋይና አመራር የሚያውቀው ሃቅ አለ። ወታደራዊ እቅድና ስትራቴጂ የነደፈው ጥናት እያደረገ ወታደረአዊ ስትራተጂ ወታደራዊ ታክቲክ የአሸዋ ገባታ ለረጅም አመታት ጥናት በማካሄድ የጻፈና ያዘጋጀ ብቸኛው አረጋዊ በርሄ ነው። ለሁሉም ወታደራዊ አመራር ስየ አብርሃ፣ ሃየሎም አርአያ ወዘተ. አስተምሮ ያሳደጋቸው አረጋዊ በርሄ ነው። ስየ አብርሃ ይሁን ሌላው የሚኩራሩበት ውሸት ነው። ወያኔ ህወሓት እስከ አሁን የሚጠቀሙበት ወታደራዊ ጉዞ በአረጋዊ በርሄ የተዘጋጀ እንጂ መለስ ዜናዊ እስከ እለተ ሞቱ ድረስ ወታደራዊ ሳይንስ ይሁን ስትራተጂ የጤፍ ቅንጣት የምታክል እውቀት አልነበረውም። ሁሉም የሚዋሸው ለሆዱ፣ ለጥቅሙና የሙስና ዘርፊያውን በስፋት ለመቀጠል ስለሚፈልግ የሚመታው የውሸት ነጋሪት ነው።
ግደይ ዘርአጽዮን ከህወሓት ወጥቶ ወደ ስደት ሲሄድ በህቡር ገብረኪዳን መሪነት ተክለወይን አሰፋ፣ ተሻለ ደብረጽዮንን ጨምሮ ተፈትሾ የያዘውን ሰነዶች ሁሉ፣ ብጣሽ ወረቀት ሳትቀር፣ ጠራርገው በመውሰድ ባዶ እጁን ሱዳን ገባ።
አረጋዊ በርሄ፣ ህቡር ገ/ኪዳን፣ ስብሃት ነጋ፣ አርከበ እቁባይ ሁነው ለብዙ ዓመታት ሲያካሂዱት የነበረውን ወታደራዊ ጥናትና ስትራተጂ የአሸዋ ገበታ፤ በትልልቅ ወረቀቶች ላይ በሰእል መልክ የተዘጋጁ ጠቅላላ ወታደራዊ መጻሕፍት ብጣሽ ወረቀት ሳትቀር በሁለት የማዳበሪያ ከረጢት ሞልተው የወረሱትን በታጋዮች አሸክመው ለመለስ ዜናዊ አስረከቡት። ‘በሰው ደንደስ በርበሬ ተወደሰ’ እንደተባለው፣ መለስ ዜናዊ ባልሰራውና በማያውቀው ወታደራዊ ስትራተጂ የአሸዋ ገበታ ንድፈ ሃሳብና አረጋዊ በርሄ ደክሞ ያዘጋጀው ነው። አሁን ወያኔ የሚጠቀምበት ወታደራዊ አካሄድ የአረጋዊ በርሄ ሥራና ጥናት ነው። ባልሰራኸው፣ በማታውቀው ጥበብ የራስህ አስመስለህ መጠቀም ያስንቃል፣ ያዋርዳል። ስለዚህ መለስና የህወሓት መንጋ ውሸታምና በምን ዓይነት ድቅድቅ የውሸት ጨለማ እንደተዘፈቁና ማንነታቸውን እንዲያውቁ ይህንን የጽሑፍ ሰነድ እዚህ ላይ ያንብቡ። (ፎቶ: መለስ ዜናዊ ጥይት ማይበሳው ብርጭቆ ቤት ውስጥ በመስቀል አደባባይ ንግግር ሲያደርጉ – REUTERS/Thomas Mukoya)
ገብረመድህን አርአያ

No comments: