Tuesday, March 15, 2016

ቡና ሁነኛውን ደጋፊውን በፌደራል እጅ አጣ

March 15,2016
(ሳተናው) የአዲስ አበባ ስታዲየም ደምበኛ ከሆኑ የቂርቆሱን ልጅ ሽመልስ ጨርቆስን አያጡትም፡፡ቂርቆሶች በርህራሄው በደፋርነቱና ጥቃትን በመጠየፉ ያውቁታል፡፡የድንገተኛው ሞቱ ምክንያትም ይሄው ጥቃትን በሌሎች ሰዎች ላይ ሲደርስም ‹‹እንዴት ተደርጎ››ባይነቱ ነው፡፡
የፌደራል ፖሊስ ልብስ የለበሰ በወጣትነት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ አንዲት ሴትን መንገድ ላይ በማስቆም አብራው እንድትሄድ ይጠይቃታል ልጅቷ ፈቃደኛ አልሆነችም፡፡
የልጅቷንና የፌደራል ፖሊሱን ሁኔታ ሲከታተል የነበረው በቀድሞው ወረዳ 21 ቀበሌ 13 ነዋሪ የነበረው ሽመልስ ፖሊሱን ልጅቷን ያለፍላጎቷ ምንም ሊያደርጋት እንደማይችል በመግለጽ ባይሆን በእርጋታ እንዲያናግራት ለማግባባት ይሞክራል፡፡ፌደራሉ ግን ብቻውን አልነበረምና በተደፈርኩ ባይነት ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ድብደባ ይፈጽሙበታል፡፡ሽመልስ የደረሰበትን ድብደባ መቋቋም ባለመቻሉም ህይወቱ ማለፉ ታውቋል፡፡
ሽመልስ ላይ ግድያ በተፈጸመበት አካባቢም ከሁለት አመት በፊት አንድ ፌደራል ፖሊስ አንዲት ሴተኛ አዳሪን እንዴት ከእኔ ሌላ ወንድ ትይዣለሽ በማለት በጥይት ደብድቦ መግደሉና አብሯት የነበረውን ማቁሰሉ አይዘነጋም፡፡በአካባቢው በሚገኘው ካምፕ የሰፈሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት በቂርቆስ አቅራቢያ በሚገኙ መንደሮች የሚኖሩ ሴቶችን በማስፈራራት ፣የሚያስቸግሯችሁን እናስራለን በማለትና በተለያዩ መንገዶች እንደሚያስቸግሯቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡በወረዳው ለሚገኝ የፖሊስ ጣቢያም ተደጋጋሚ አቤቱታዎች ቢቀርቡም ምንም አይነት ምላሽ ባለመገኘቱ ነዋሪዎች መቸገራቸውን ይገልጻሉ፡፡
በፌደራል ፖሊሶቹ በደረሰበት ድብደባ ህይወቱን ያጣው ሽመልስ ጨርቆስ በዛሬው ዕለት የቀብር ስነስርዓቱ የተፈጸመ ቢሆንም ይህ ዘገባ እስከተሰራ ድረስም በፌደራል ፖሊሶቹ ላይ የተወሰደ ምንም አይነት እርምጃ የለም፡፡
ምንጭ የቂርቆስ ልጆች

No comments: