Friday, March 25, 2016

ሰበር ዜና! የመለስ ፋውንዴሽን ተዘጋ! – ነፃነት ዘለቀ

March 25,2016
arton390ይህን የመለስን ፋውንዴሽን መዘጋት በሚመለከት “ዜና ላድርገው ወይንስ መጣጥፍ?” ብዬ ብዙ ተጨነቅሁ፡፡ ዜናም ላድርገው መጣጥፍ መቼም እስካሁን የቀደመኝ እንደማይኖር ተስፋ አለኝ፡፡ ወደሰበር ዜናው ላምራ፡፡
የሕዝብ ዋይታ የፈጠረው ዕንባና ያፈሰሰው የንጹሓን ደም ፈጣሪ ዘንድ ጮኸው ባመጡት የጸሎት መልስ ለገሠ ዜናዊ – በፖለቲካዊ የብዕር ስሙ መለስ ዜናዊ – የሚባለው ሽፍታ  የዛሬ አራት ዓመታት ገደማ ከሥሩ ተግነድሶ አይሞቱ አሟሟት መሞቱ የሚታወስ መሆኑን የገለጸልን ይህን ሰበር ዜና ያደረሰን ግለሰብ በመቀጠልም በዚህ ዱርዬ ሀገር አጥፊ ስም ተቋቁሞ የነበረውና ካዛንቺስ አካባቢ የሚገኘው ፋውንዴሽን ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱን ጠቁሟል፡፡
አቶ ነፃነት ዘለቀ የሚባሉ – ባጋጣሚ ሆኖ የዜናውም ዘጋቢ እርሳቸው ናቸው – የአዲስ አበባ ኗሪ ዛሬ መጋቢት 16 ቀን 2008 ዓ.ም – በዕለተ ኪዳነ ምሕረት – ከቤታቸው ወደ ሥራቸው ለመሄድ ዝምቡን እንኳን እሺ የሚልለት ሰው ሳይኖር ኦናውን ተገትሮ በሚውለው በዚያ ፋውንዴሽን አጠገብ ሲያልፉ የተመለከቱት ነገር ከባድ ምልኪያዊ ገጽታ እንዳለው የደረሱበት መሆኑንም አልሸሸጉም፡፡
ዝርዝሩን በተመለከተ እንዲህ በማለት ገልጸዋል – አቶ ነፃነት፡፡ “ዌል፣ እኔ ኖርማሊ ጧት ጧት ወደ ሥራ የምሄደው በዚህ የመለስ ፋውንዴሽን በሚሉት መንገድ አስታክኬ ነው – ብዙም የምታከክ ደግሞ እንዳይመስልህታዲያ፤ እናንት ጋዜጠኞች አንድን ነገር ኤግዛጀሬት እንደምታደርጉና ነገሮችን እንደምታዛቡ አውቃለሁ፡፡ እርግጥ ነው አክቹዋሊ እዚያ አካባቢ ስደርስ ወደፋውንዴሽኑ ማየትን አልወድም፡፡ ሰውዬው በቁሙ ያስጠላኝና የእናቴ ገዳይ ያህል እቆጥረው ስለነበረ በዚያ የማልፈው ደሜ እየተንተከተከ ነው – ዩዥዋሊ፡፡ ዛሬ ግን ለየት ያለ ነገር ታዘብኩና የመኪናየን ፍጥነት በረድ አድርጌ በመስኮት በኩል ስመለከት ከዐድዋ ድልድይ አቅጣጫ የመጣ የሚመስል አንድ ላንድክሩዘር በመናኸሪያ ሆቴል አቅጣጫ በኩል ከሚገኘው የፋውንዴሽኑ ዋና መግቢያ የበሩ ኮለን ጋር በመጋጨት በሩን ዘግቶ ቆሞ አየሁ – በትዕዛዝ በሩን ለመዝጋት የቆረጠ ይመስላል፡፡ ወደግቢው የሚወስደውን መንገድ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ዘግቶታል፡፡ ከሰው በቀር ወደግቢ መኪና አያስገባም – ለነገሩ ከዚያች ውሻ ሴት በስተቀር ሌላ ሰው ማን ሊገባ እንደሚችል አላውቅም – (ውሻ ማለቴን በዜናህ እንዳታቀርበው ታዲያ ፤ እናንተ እኮ አትታመኑም – አደራህን ኤዲት አድርገህ አውጣው ኦኬ?) ብዙ ሰዎችም ዙሪያውን ቆመው ጉድ ጉድ ይላሉ – “ድ” እንደማይጠብቅ አንባቢዎችህን ንገራቸው – አለበለዚያ ምን ድግስ ኖሮ ነው ‹ጉድ ጉድ› (አሁን ‹ድ› ይጠብቃል) የሚሉት እንዳይሉህ፡፡ እንደምገምተው ብዙዎቹ ሳይደሰቱ አልቀሩም፤ ግን በላይ ያዘኑ መስለው ሊፓቸውን ይመጣሉ – ‹እምጵ› እያሉ፡፡ ግጭቱ ከባድ ቢመስልም የተጎዳ ሰው ግን እንደሌለ አንገቴን በመስኮት አስግጌ የጠየቅሁት አንድ ሰው ነግሮኛል፡፡” በማለት ፋውንዴሽኑ ቢያንስ ያ ላንድክሩዘር እሰኪነሳ ድረስ ተዘግቶ እንደሚቆይ አስረድተዋል፡፡
“በዚህ በፋውንዴሽኑ መዘጋት ምን ተሰማዎት?” ተብለው የተጠየቁት አቶ ነፃነት ሲመልሱ “ኦፍ ኮርስ ምንም አልተሰማኝም ልልህ አልችልም፡፡ ግጭቱ ባይደርስ ደስ ይለኛል፡፡ በተለይ ከመጠነኛ የንብረት ዲስትራክሽን ውጭ የሰው ላይፍ ላይ ምንም ሃፕን ያደረገ ነገር ባለመኖሩ ደስ ብሎኛል፡፡ በት ኦን ዚአዘር ሃንድ ላንድ ክሩዘርን የመሰለ ሚጢጢየ ካር ኦር መኪና ኢፍ ዩ ላይክ ሳይሆን የሆነ ዩ ኖው የፋውንዴሽኑን ግቢ ብቻ የሚያህል ሜቴዎሮይድ ቢወድቅበትና ድራሽ አምላኩ ቢጠፋም የምጠላ ፐርሰን አይደለሁም – ኤግዛክትሊይ ኤ ካይንድ ኦፍ ዛት፡፡ ቱ ዩር ሰርፕራይዝ ይሄ ላንድክሩዘር በሩን እንዲህ ልክክ አድርጎ በግጭት ምክንያት መዝጋቱ ኢት ኢዝ ሪሊ ኦሚነስ – ማለቴ ምልኪያዊ ነው፡፡ ይህ ያልተጠበቀ ክስተት ግቢው በቅርቡ እንደሚዘጋና ለሌላ ፍሬያማ ተግባር እንደሚውል ይጠቁማል፡፡ ሶሪ እቸኩላለሁ፡፡ ሌላ ነገር ባትጠይቀኝ ደስ ይለኛል” በማለት ወደ ሥራቸው ለመሄድ ማቆብቆባቸውን በሰውነት እንቅስቃሴያቸው ቢጠቁሙም የያዛቸው ጋዜጠኛ ቀላል ባለመሆኑ “ጥሩ ነው፣ በንግግርዎ ጣልቃ እንግሊዝኛን የሚጠቀሙት ለምንድነው?” ሲል ጠይቋቸዋል፡፡ መልሳቸውም “ሂድና ኢቲቪን ጠይቅ፣ ሂድና ወያኔን ጠይቅ፣ ሂድና በየስብሰባውና በየዐውደ ጥናቱ በእንግሊዝኛና ዐማርኛ ጉራማይሌ በቅጹ ሳያውቅበት እያወለጋገደ የሚንተባተበውን ምሁርና ካድሬ ጠይቅ፣ ሂድና ስሙን ሲጠየቅ ባላስፈላጊ ሁኔታ ሳይቀር ‹አክቹሊ ስሜ ገረመው ነው› የሚል ዓይነት ጉራማይሌ ሠርክ የሚነገርባቸውን ኤፌሞች ጠይቅ፣ ሂድና የተማርኩ ነኝ የሚለውን ዜጋ በሙሉ ጠይቅ፣ ‹የሠራተኞች መጓጓዣ› ማለት አቅቷቸው አይደለም እንዴ ዐማርኛን በመጸየፍ ‹ፐብሊክ ሰርቪስ› የሚል የዐማርኛ ጽሑፍ ሰማያዊ አውቶቡሶች ላይ ለጥፈው የሚያስቁን? እኔስ ታዲያ ከማን አንሳለሁ? ሁ ማይነስ ሁ አንተ!?” በማለት በንዴት መልሰዋል፡፡ አሁን የቸኮልኩት እኔ ጋዜጠኛው ሆንኩ – እርሳቸው እንደሆኑ ሥራቸውንም ረስተው ከኔ ጋር ሲያወሩ ቢውሉ ደስተኛ ይመስላሉ፡፡
በተዋዛ አቀራረብ ላደረስንላችሁ ጮማ ሰበር ዜና ምሥጋና እንደሚገባን በሾርኒ በመጠቆም በሌላ – ከተገኘ – ሰበር ዜና እስክንገናኝ ደህና ዋሉ በማለት የምሰናበታችሁ –
ከመለስ ፋውንዴሽን ቅጽር ግቢ ውጪ የተጠናቀረውን ዜና ያቀረብኩላችሁ ነፃነት ዘለቀ ነኝ ከአዲስ አበባ
ማሳሰቢያ፡- ይህንን ዜና በምስል ማስደገፍ ያልተቻለው በዚያ አካባቢ ፎቶግራፍ ማንሣት ከጤና አኳያ ጎጂ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑን ከይቅርታ ጋር ማሳሰብ እንወዳለን፡፡ ጎመን በጤና፡፡ ለሥራ ያልደረሱ፣ ለምግብ ያላነሱ ልጆችን ቀፍቅፎ ከጅብና ከዓሣማ ጋር አላስፈላጊ ልፊያ ውስጥ መግባት ብልኅነት አይደለም፡፡


No comments: