Monday, May 18, 2015

ካድሬዎች የምርጫ ካርድ ላይ ንብን እየለጠፉ ለመራጩ እያደሉ ነው

May 18,2015
በጋሞጎፋ ዞን ቁጫና ቦርዳ ወረዳዎች የደኢህዴን/ኢህአዴግ ካድሬዎች የህዝቡን ካርድ እየተቀበሉ የምርጫ ካርዱ ላይ የንብን ምልክት በስቴፕለር በማያያዝ ኢህአዴግን እንዲመርጡ እያስገደዱ እንደሚገኙ በጋጎፋ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ አስተባባሪ አቶ ወንድሙ መኩሪያ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ካድሬዎቹ ህዝቡን 1ለ5 በማደራጀት የንብ ምልክት የተለጠፈበት ካርድ በማደል ‹‹የምትመርጡት ኢህአዴግን ነው›› እያሉ እያስገደዱ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
የዞኑ፣ የወረዳውና የየ ምርጫ ክልሉ ምርጫ አስፈጻሚዎች ካድሬዎቹ የንብ ምክትን የምርጫ ካርዱ ላይ እያያያዙ ኢህአዴግን እንዲመርጡ እያስገደዱ መሆኑን ቢያውቁም ምንም እርምጃ እየወሰዱ አይደለም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በጋሞጎፋ ዞን ቦረዳ ወረዳ ሰማያዊ ፓርቲ እሁድና ቅዳሜን ‹‹የገበያ ቀን ስለሆነ›› በሚል ቅስቀሳ እንዳያደርግ መከልከሉን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡ ‹‹የምርጫ ህጉ የሚለው ቅስቀሳ መደረግ ያለበት ከገበያ 500 ሜትር ርቆ ነው እንጅ በገበያ ቀን ቅስቀሳ አይደረግም አይልም፡፡ እኛን ግን ገበያ በሌለባቸው ቦታዎች ሁሉ እሁድና ቅዳሜ ቅስቀሳ እንዳናደርግ ከልክለውናል›› ብለዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ቅስቀሳ እንዳያደርግ እየከለከሉ የሚገኙት የቦረዳ ወረዳ የፀጥታ አስተዳደር ኃላፊ አቶ ማርካ ማዶ እና የወረዳው ፖሊስ አዛዥ መቶ አለቃ ታምራት ናቸው ብለዋል፡፡

No comments: