January 20,2015
(አስገደ ገ/ስላሴ ከመቀሌ)
በሕወሓት አመራርና አጃቢዎች የተፈበረከው ምርጫ ቦርድ ባለፉት 20 አመታት ለ4 ጊዜ ከፌደራል እስከ ቀበሌ ምርጫ አካሂዷል። ሁሉም ምርጫዎች ግን የዴሞክራሲ መስፈርትን የሚያሟሉ እንዳልነበሩ ዓለም-አቀፍ ታዛቢዎች ጭምር አረጋግጠዋል።
በ2007 ዓ.ም የምርጫ ውድድርም ሕወሓቶች፣ በዚሁ አመት ሃቀኛ ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን ጭራሹን ላለማሳተፍ፣ ለአመታት ያህል የቤት ስራ እየሰሩ ቆይተዋል፡፡ ለዚሁ አላማ ግቡን ለመምታት አስቀድመው እጅግ ብዙ ብቁ ምሁራንን እና ወጣት የፖለቲካ አመራሮችን “ለስልጣናችን አስጊ ናቸው” በማላት በሀሰት ወንጅለው አስረው በማሰቃየት ላይ ይገኛሉ። ብዙ የተቀናቃኝ ፓርቲዎች አባላት ላይም ስጋት ፈጥረዋል፤ ከትምህርትና ከስራም አፈናቅለዋል። ፓርቲዎችን ለመበታተን ብዙ ሰርጎ-ገቦችን በማስረፅ አለመተማመን በመፍጠር፣ እንዲከፋፈሉ ለማድረግ ብዙ ገንዘብ ረጭተዋል።
ተቃናቃኝ ፓርቲዎች፣ ሰርገው ከገቡ ባንዳዎች ውስጣቸውን ለማጥራት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴም ለማሰናከል፤ ምርጫ ቦርዱ ከባንዳዎች ጋር በማበርና በመወገን ሃቀኛ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ስራቸውን እንዳይሰሩ በጭቅጭቅ እየጠመዳቸው ይገኛል።
ለዚሁ ለማስረጃነት የሕወሓት መንግስት የህዝብ ድጋፍ ያላቸው ተቀናቃኝ ፓርቲዎች፤ ህዝብ በስብሰባና በሰላማዊ ሰልፍ ሕዝቡን እንዳያነቁ ከመከልከል አልፎም ብዙ አባላት ተጨፍጭፈው ደማቸው በጎዳና ፈሷል። በአገር ውስጥ ያለውን ሁለ-ገብ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የሚዘግቡ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን፣ፀሃፊዎች፣ አምደኞችና ከያኒያን ታስረዋል ተሰደዋል።
ይሄ ሁሉ አልበቃም ብሎ፣ በዚሁ በምርጫ ዋዜማ አሸንፈው በፓርላማ ከፍተኛ ወንበር ያገኛሉ ያሏቸውን አንድነት እና መኢአድን ከምርጫ ጨዋታው ለማስወጣት፣ ብሎም ለመሰረዝ የተለያዩ ደባዎች እየተፈፀሙ ነው፡፡ ፓርቲዎቹ፣ ምንም ስህተት ሳይኖርባቸው ትዕዛዙን ለመፈፀምና ምክንያታቸውን ለማስጨረስ ተደጋጋሚ ጉባኤ አድርገዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ ጉባኤያቸውን እንዲታዘብ ጠርተውት፣ ሳይመጣ ቀርቶ ፓርቲዎችን ለማባረር ተዘጋጅተዋል ። ይህን ሁሉ ሲል የኢትዮጵያ ህዝብ ገጠር ከተማ ሳይለይ የምርጫ ቦርድን ሴራ ተረድቶት እየተመለከተው ይገኛል። ለውጥ ፈላጊ ነውና።
በሌላ በኩል፣ ምርጫ ቦርድ ህወሓቶች ባዋቀሯቸውና ምንም ተከታይ በሌላቸው፤ ለወደፊትም የህወሓት ተስፈኞች ከመሆን ውጭ ለህዝብና ሀገር ምንም ፋይዳ የሌላቸው ባንዳዎችን ወደፊት በማምጣት ገንዘብ ያገኛል። በሌላ በኩል ግን ጠንካራ ፓርቲዎችን ለማፍረስ ወጥመድ እየፈጠረ ይሰጣል። ምርጫ ቦርድም ሆነ ሕወሓት መረዳት ያለባቸው እነዚህ ፓርቲዎች ከምርጫ ጨዋታ ውጭ ከሆኑ፣ የሕወሓቶች ውድቀት የተቃናቃኝ ፓርቲዎች ድል መሆኑ የማይቀር እንደሆነ መረዳት አለባቸው።
እነዚህ ከምርጫ ጨዋታ ውጭ እንዲወጡ የሚፈለጉ ፓርቲዎች ህወሓት አስቀድሞ የወሰነው ስለሆነ ተደጋጋሚ ጉባኤ ማድረግ አቁመው ህወሓት ከሰራቸው ጥገኛ አጃቢዎቹ (ብቻው ማንጨብጨብ አለበት) የዚህ ኣፈና ውጤት ዳግም ህዝብ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲሄድ ተስፋ እንዲቆርጥ ያደርገዋል፤ ለዚህ ተጠያቂ የሚሆኑት ህወሓትና ምርጫ ቦርድ ይሆናሉ።
ለሕወሓት መሪዎች የምለግሳላቸው ምክር ቢኖር፣ የዘንድሮውን ምርጫ የዓለም-አቀፉን ህብረተሰብ ለማታለልና ለተራ የፖለቲካ ፍጆታ ብለው በሸፍጥ ጊዜያቸው ከማባከን እንዲቆጠቡ ነው፡፡ ሕወሓት፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም፣ ነፃነት ፍትህና መልካም አስተዳደር ሲል ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞችን መፍታት ይኖርበታል፡፡ ሁሉም በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉ ፓርቲዎች፣ ነፍጥ አንስተው በረሃ እስከ ገቡ ሃይሎች ድረስ የሰላም መድረክ ከፍቶ የሰላም ድርድር ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በዚህች አገር ሰላም ሰፍኖ ሁሉም ዜጎች በመቻቻል፣ በመፈቃቀር ስለሀገር ጥቅም ሀሳባቸውን በነፃነት አንሸራሽረው በህዝብ የድምፅና ዳኝነት ትመራ ዘንድ ምህዳሩን ቢያሰፉት የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ራሱ ሕወሓት ጭምር እጅጉን ይጠቀማል። ይህ ካልሆነ ግን ይህች ሀገርና ህዝቦቿ፣ ለከፋ ችግር መጋለጣቸው አይቀሬ ነው። አሁንም መፍትሄው በሕወሓት መሪዎችና አጃቢዎቹ እጅ ነው።
ሕወሓት ምርጫ ቦርድን መሳሪያ አድርጎ፣ በተቃናቃኝ ፓርቲዎች ላይ እያካሄደ ያለውን ሴራ ህዝባችንና አለምም ከወዲሁ ጠንቅቆ አውቆታል።
እግዚአብሔር ለሕወሓት መሪዎች ልብ ይስጥልን። (ምንጭ: ፍኖተ ነጻነት)