Friday, January 16, 2015

ሰበር ዜና – ፈረንሳይ ሌጋሲዮን በኢቦላ በሽታ ስጋት ተወጥራለች

January 16,2015
ነገረ ኢትዮጵያ
• ከ10 በላይ ሰዎች ከህዝብ ጋር እንዳይገናኙ በፖሊስ ታግተዋል

ሴራሊዮን ውስጥ በአንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ ሲሰራ ቆይቶ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ ህይወቱ ያለፈውና
በሽታው ኢቦላ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ የደም ናሙናው ወደ ውጭ ለምርመራ የተላከው ኢትዮጵያው ጋር ግንኙነት አለው የተባለው የአምቡላንስ ሰራተኛና ከእሱ ጋር ተገናኝተዋል የተባሉ ሌሎች 10 ያህል ሰዎች የሚኖሩበት ፈረንሳይ ሌጋሲዮን አካባቢ የሚገኝ ግቢ በፖሊስ ተከቦ ነዋሪዎች ከህዝብ ጋር እንዳይገናኙ ተደርገዋል፡፡

ኢሳያስ የተባለና ህይወቱ ያለፈውን ኢትዮጵያዊ በአምቡላንስ ሲያመላልስ የነበር ወጣት ፈረንሳይ ሌጋሲዮን በተለምዶ ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተከራይቶ የሚኖር ሲሆን እሱን ጨምሮ ከእሱ ጋር የሚኖሩት እህቱና ባለቤቱ እንዲሁም ተከራይቶ በሚኖርበት ግቢ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ከ10 በላይ ሰዎች ከህዝብ እንዳይገናኙ በፖሊስ ታግተዋል፡፡ ግቢው በፖሊስ ተከቦ ሰው ከግቢው እንዳይወጣና ወደ ግቢው እንዳይገባ መከልከሉን ተከትሎ ፈረንሳይ ሌጋሲዮን አካባቢ የሚኖረው ህዝብ በኢቦላ በሽታ ስጋት ተወጥሯል፡፡

የጤና ባለሙያዎችና ፖሊሶች ኢሳያስ የተባለው ግለሰብ ሟቹን በአምቡላንስ ሲያመላልስ እንደነበር ከትናንት ጠዋት ጀምረው ቢያረጋግጡም እስከ ትናንት ከቀኑ ሰባት ሰዓት ድረስ ከሰው ጋር እንዳይገናኝ ሳይከለክሉት ቆይተዋል ተብሏል፡፡ የአምቡላንስ ሾፌሩ በሚኖርበት ግቢ ውስጥ ከ20 በላይ ሰዎች የሚኖሩ ቢሆንም 10 ያህሉ ግለሰቦች ብቻ ከግቢ እንዳይወጡ የተከለከሉት ዛሬ ጠዋት ነው ተብሏል፡፡ ሆኖም ከግቢው ውጭ ከኢሳያስ ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ግለሰቦች ላይ ምንም አይነት ክትትል ያልተደረገ ሲሆን ግቢው ውስጥ ከሚኖሩት መካከልም በጠዋት በስራና በሌሎች ምክንያች የወጡ ግለሰቦችም ተመልሰው ወደ ግቢ እንዳይገቡ ከመከልከላቸው ውጭ ክትትል እየተደረገላቸው እንዳልሆነ ታውቋል፡፡

የአምቡላንስ ሾፌሩና ከእሱ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉበት ግለሰቦች የሚኖሩበት ግቢ በርከት ባሉ ፖሊሶችና የደህንነት ሰራተኞች
መከበቡን ተከትሎ ስጋት የገባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተሰባስበው ስለ በሽታው እየተወያዩ አስተውለናል፡፡ ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎችም የአንቡላንስ ሾፌሩ ከበርካታ ሰዎች ጋር ግንኙነት የነበረው መሆኑ፣ እንዲሁም ግቢው ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችም ከግቢ ውጭ የሚገኙ በመሆኑ በሽታው ከተከሰተ ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱም አስጊ እንደሆነ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ በፖሊስና ደህንነት ከበባ ብቻ አንድ ግቢ ውስጥ ተከሰተ የተባለውን ጉዳይ በአግባቡ መያዝ አለመቻሉን ጠቅሰውም ‹‹መንግስት ዝግጅት ሳያደርግ ዜጎችን መላኩ ትክክል አልነበረም፡፡›› ሲሉ ተችተዋል፡፡

በፖሊስ ከታገቱት መካከል በስልክ አግኝተን ያነጋገርናቸው ሰዎች ደህንነቶች ‹‹ይህ የአገር ሚስጥር በመሆኑ ለማንም እንዳትናገሩ፡፡›› ብለው እንዳስጠነቀቋቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ፖሊስና ደህንነቶች ሰው እንዳይወጣና እንዳይገባ በመከልከላቸው እስካሁን ምግብ እንዳልገባላቸውና ‹‹የሟቹ የደም ናሙና ነገ እስኪመጣ ድረስ ከግቢ መውጣት አትችሉም፡፡ ሌሎች ሰዎችም ወደ ግቢ መግባት አይችሉም፡፡ እስከነገ ለማንም መረጃ ባለመስጠት ተባበሩን፡፡›› እንደተባሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ ግቢውን በከበበት ወቅት የግቢው ነዋሪዎች ‹‹ችግር ካለ ባለሙያ መጥቶ ያረጋግጥ፡፡ ፖሊስ ለምን ያግተናል?›› በሚል ከግቢው እንወጣለን በማለታቸው ጭቅጭቅ ተፈጥሮ እንደነበርም የአይን እማኞች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

No comments: