Thursday, January 15, 2015

ሰማያዊ ቲሸርት የለበሱ ወጣቶች ከስላሴ በዓል ላይ ተባረሩ

january 15,2015
• ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ‹የፈራ ይመለስ› የሚል ቲሸርት አስለብሶ ሲበጠብጠኝ ሰንብቷል፡፡›› የየካ ክፍለ ከተማ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ
• ‹‹ገዥው ፓርቲ ጥላውን የማያምንበት ደረጃ ላይ ደርሷል!›› አቶ ዮናታን ተስፋዬ
ዛሬ ጥር 7/2007 ዓ.ም የዓመቱን የስላሴ በዓል ለማክበር አራት ኪሎ የሚገኘው ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን የተገኙ ወጣቶች ሰማያዊ ቲሸርት በመልበሳቸው በፖሊስ እንደተባረሩ የአይን እማኞች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ፖሊስ ‹‹ያመነ፣ የተጠመቀ ይድናል!›› የሚል ሰማያዊ ቲሸርት የለበሱትን ወጣቶች ቲሸርቱን እንዲያወልቁ ሲጠይቅ ወጣቶቹ አናወልቅም በማለታቸው ከበዓሉ ማባረሩን እማኞቹ ገልጸዋል፡፡ ከተባረሩት ወጣቶች መካከል አብዛኛዎቹ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚገቡትንና የሚወጡትን አማኞች በማስተባበር ላይ እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን የተባረሩት ወጣቶች ይታሰሩ አይታሰሩ የታወቀ ነገር የለም፡፡
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የመጡ ከፍተኛ ኃላፊዎች ለጥምቀት በዓል ሰማያዊ ቲሸርት ያዘጋጁትን የጃንሜዳ አካባቢው የጥምቀት በዓል አስተባባሪዎች፣ ያዘጋጁት ሰማያዊ ቲሸርት በዓሉ ላይ እንዳይለበስ በተደጋጋሚ እያስጠነቀቁ እንደሚገኙ ምንጮች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ በፖሊሶችና በደህንነቶች ተደጋጋሚ ጫናም ለጃንሜዳ አካባቢ ወጣቶች የተዘጋጀው ሰማያዊ ቲሸርትና ‹‹ያመነ፤ የተጠመቀ ይድናል›› የሚለውን ጥቅስ በነጭ ቲሸርት እና በሌላ ጥቅስ እንድንቀይር ተገደናል ብለዋል፡፡ በአንጻሩ የፈረንሳይና ቤላ አካባቢ ወጣቶች ሰማያዊ ቲሸርቱን እንዲቀይሩ ጫና ቢደርስባቸው አንቀይርም በሚል አቋማቸው መጽናታቸው ታውቋል፡፡
በተመሳሳይ ጥር 6 የአዲስ አበባ መስሪያ ቤቶችና ወረዳዎች ኮሚኒኬሽን ኃላፊዎች አዲስ አበባ መዘጋጃ ቤት ባደረጉት ስብሰባ የየካ ክፍለ ከተማ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ፈረንሳይ ሌጋሲዮን አካባቢ ‹የፈራ ይመለስ› የሚል ሰማያዊ ቲሸርት አስለብሶ ሲበጠብጠኝ ሰንብቷል፡፡›› ሲል ሪፖርት ማቅረቡን የስብሰባው ተሳታፊዎች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
ስለ ጉዳዩ ያነጋገርናቸው የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ‹‹ደህንነት፣ ፖሊሶችና ካድሬዎች እያንዳንዱን የህዝብ እንቅስቃሴ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር በማገናኘት ወቀሳ የሚያቀርቡት ህዝብ ውስጥ ብሶት እንዳለ፣ ሰማያዊም የህዝብን ብሶት እንደሚያሳማ ስለሚያውቁ፣ ከምንም በላይ ገዥው ፓርቲ የራሱን ጥላ የማያምንበት ደረጃ ላይ ስለደረሰ ነው›› ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ባነሱባቸው ጊዜያት ሁሉ ገዥው ፓርቲ ሰማያዊ ፓርቲን ‹‹የሙስሊም ፓርቲ ነው›› በሚል ሀሰተኛ ወሬ ሲያሰራጭ እንደነበርና ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በሰጠው የ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ስልጠና ሰማያዊ ፓርቲን ሲወቅስ እንደከረመ ያስታወሱት ኃላፊው አሁንም ፓርቲውን ከእያንዳንዱ የህዝብ እንቅስቃሴ ጋር እያገናኘ ቢበረግግ አያስገርምም ብለዋል፡፡
semayawi

No comments: