October 17,2014
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
በአሁኑ ጊዜ የረዥም ጊዜ አንባቢዎቼ አንደምያውቁት ሁሉ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ያሉኝን ሀሳቦች እና ማሳመኛ የሙገታ ትንታኔዎች ከፍተኛ በሆነ ግልጽነት፣ እርግጠኝነት እና ለየት ባለ አቀራረብ ሁኔታ በእራሴ ቃላት እና ሀረጎች ለመግለፀ አሞከራለሁ፡፡ በዚህ በአሁኑ ትችቴ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት በአመጽ እና በኃይል ከህዝቦች ፍላጎት ውጭ በስልጣን እርካብ ላይ ተፈናጥጦ የሚገኘውን ህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሐት) እየተባለ የሚጠራውን “የለማኝ መንግስት” ገዥ ቡድን የፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍልስፍና መሰረት የሆነውን ጽንሰ ሀሳብ በማስተዋወቅ ውስጣዊ ይዘቱን እና ባህሪያቱን ለመመርመር እሞክራለሁ፡፡
በተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ እና የደቡብ ኤስያ አገሮች ብዙ የመከሰቻ መገለጫዎችን ያካተተ “ልመና” (ወይም ባክሸሽ) የሚባል የተለመደ ባህል አለ፡፡ አንዳንዱ እንደ ኃይማኖታዊ ቀኖና ግዴታ “ምጽዋት በመስጠት” ወይም ደግሞ ለድሆች ልገሳ በማድረግ “ልመናን” መተግበር ይችላል:: ለተሰጠ አግልግሎት ይመጥናል ተብሎ ለባለስልጣን በ ”አጅም” (ኪስ ባዶ አንዳይሆን) የሚሰጥም ክፍያ ተለምዷዊ ድርጊት አለ፡፡ “ልመና” ከዚህም በተጨማሪ የፖለቲካዊ ሙስናን እና የሞራል ዝቅጠትን ባካተተ መልኩ በከፍተኛ የስልጣን እርካብ ላይ ያሉት የመንግስት ባለስልጣኖች ሀብትን በከፍተኛ ደረጃ ለማካበት፣ በዝቅተኛ የስልጣን እርካብ ላይ ያሉት የመንግስት ባለስልጣናት ደግሞ ከእጅ ወደ አፍ ለሆነው አነስተኛ ወርሀዊ ገቢያቸው የኑሮ መደጎሚያ ይሆናል በሚል ስሌት ልዩ “ስጦታ” እና “ሽልማት” የሚጠይቁበት የአሰራር ባህል ነው፡፡
“ለማኝ መንግስት” በሚለው ጽንሰ ሀሳብ በዋናነት ዓለም አቀፍ ምጽዋትን (እርዳታ + ብድር) እና በእርዳታ እና ብድር ስራ ላይ የማጭበርበር ድርጊቶችን በመፈጸም (ህጋዊ የሆኑ ድርጅቶችን ለህገወጥ ተግባር በማዋል) የተለያዩ የሙስና ስልቶችን በመጠቀም እራሳቸውን በስልጣን እርካብ ላይ ለማቆየት የሚፍጨረጨሩትን ገዥ አካሎች እና መንግስታትን ሁኔታ ለመገንዘብ እንዲቻል በማሰብ ነው፡፡ ቀደም ሲል ለማስገንዘብ እንደሞከርኩት የአፍሪካ ከፍተኛው የአምባገነንነት ደረጃ “ዝርፊያ” ነው፡፡ ከዚህ ላይ በግልጽ ሊታወቅ የሚገባው ጉዳይ የለማኝ መንግስት የፖለቲካ ስልጣንን መከታ በማድረግ የመንግስት ባለስልጣኖች እና ለገዥው ስርዓት ታማኝ አገልጋይ እና ሎሌ የሆኑት የተማሩ ሰዎች ስልታዊ በሆነ መልክ የህዝብ ህብትን ወደ ግል ኪሳቸው በማስገባት እና የህዝቡን የግምጃ ቤት ገንዘብ ህገወጥ በሆነ መልኩ ከአገር እንዲወጣ በማድረግ ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉበትን ዘዴ የአፍሪካ የንቅዘት አስተዳደር በሚል ቃል ገልጨው ነበር፡፡
የእኔ የአፍሪካ ለማኝ መንግስት ጽንሰ ሀሳብ የፈለቀው አለቃ (ቺፍ) ኦባፌሚ አወሎዎ በሚባል ታዋቂ ናይጀሪያዊ ብሄራዊ አገር ወዳድ፣ ደራሲ እና ቃልአቀባይ ከድህረ አፍሪካ ነጻነት በኋላ “የለማኝ መንግስታት መነሳሳት” እና የእነዚህን ለማኝ መንግስታት እኩይ ምግባራት ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመቆጣጠር እና ለማስወገድ እንዲቻል ተከታታይነት ባለው መልኩ ጥረት ሲያደርግ እና ምክር ሲሰጥ ከነበረው ስልታዊ አካሄድ ጋር የሚጣጣም እና አብሮ የሚሄድ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1967 4ኛው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጉባኤ ላይ አለቃ አዎ እንዲህ በማለት ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር፣
በአሁኑ ጊዜ አፍሪካ የለማኝ መንግስታት የውድድር አህጉር ሆናለች፡፡ ቀደም ሲል ቅኝ ይገዙን ለነበሩት ገዥዎቻችን ምቹ ድልዳል በመሆን እኛ ግን እርስ በእርሳችን በመመቃቀን እና አንዳችን በአንዳችን ላይ ደባ በመፈጸም ሆን ብለን የእጅ አዙር ቅኝ ገዥዎችን በየግዛቶቻችን እንዲመጡ እየጋበዝን እንደገና በአፍሪካ ምድር ላይ እንዲነግሱ እና የኢኮኖሚ እድሎቻችንን አሳልፈን በመስጠት የእነርሱ ባሪያ በመሆን ላይ እንገኛለን…
…በእርግጥም ያለንን ስልጣን እና የሉዓላዊነት ሽፋን የሚሰጣቸውን ጥሩ አጋጣሚዎች በመጠቀም እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ መርህ የሚሰጠውን የህጋዊነት ማዕቀፍ ስልት እና አካሄድ ከግንዛቤ በማስገባት በገንዘብ ከሚረዱን እርዳታ ሰጭዎች ጋር በመሞዳሞድ ይህንን ድርጊት ልንቀጥልበት እንችላለን፡፡ ሆኖም ግን ዘለቄታ ያለው ሰይጣን በዚሁ ይቀጥላል… እናም ለማኙ በቃኝ ብሎ ፊቱን ካላዞረ በስተቀር የልመና ባህሉ ከማንም ጋር ሳይሆን ከእኛ ጋር ይቆያል፡፡ ብዙ በለመነ ቁጥር የተነሳሽነት ማጣትን፣ ድፍረትን፣ ቁርጠኝነትን እና በእራስ የመተማመን ተግባራትን በማስወገድ የለማኝነት ባህልን በቋሚ ለማኝነት እረድፍ ላይ ተሰልፎ እንዲገኝ ያደርጋል፡፡
ዴሞክራሲ “በህዝቦች እና ለህዝቦች የተቋቋመ ህዝባዊ አስተዳደር” ነው በማለት በማያሻማ መልኩ ተገልጿል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ “የለማኝ አገዛዝ” በእርዳታ ሰጭዎች እና በአበዳሪዎች ለእርዳታ ሰጭዎች እና ለአበዳሪዎች የተቋቋመ የእርዳታ ሰጭዎች እና የአበዳሪዎች መንግስት ነው፡፡ በሌላ አባባል የለማኝ መንግስት በምጽዋት ሰጭዎች ለምጽዋት ተቀባዮች የተቋቋመ የምጽዋት መንግስት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
በኢትዮጵያ በስልጣን እርካብ ላይ ተፈናጥጦ የሚገኘው የህወሐት የለማኝ መንግስት ከአፍሪካ የለማኝ መንግስታት ውስጥ ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ ውድድሩን በአንደኝነት ደራጃ ያጠናቀቀ ቁጥር አንድ የለማኝ መንግስት መሆኑ ከጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ በእርግጥም የህወሐት ገዥ አካል የለማኝ መንግስት በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ የቋሚ ተምሳሌት እና የልዩ ባህሪ የለማኝ መንግስት ስብስብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከአፍሪካ አህጉር ከፍተኛውን የውጭ እርዳታ በመቀበል ላይ የምትገኝ እና ወደፊትም የምትቀበል ሀገር መሆኗየተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በሚገኘው እንደ ኢትዮጵያ የልማት እርዳታ ቡድን/Development Assistant Group Ethiopia ዘገባ ከሆነ እ.ኤ.አ በ2008 ለልማት እርዳታ ተብሎ በእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ የተሰጠው ገንዘብ 3.819 ቢሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን በ2010 ይህ አህዝ 3.525 ዶላር፣ በ2011 ደግሞ 3.563 ቢሊዮን ዶላር ሆኖ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 እንግሊዝ ኢትዮጵያን በሚቀጥሉት 4 ዓመታት ከአፍሪካ አገሮች ሁሉ ታላቋ የልማት እርዳታ ተቀባይ አድርጋ መርጣታለች፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ እ.ኤ.አ በ2005 ለህወሐት የምትሰጠውን የእርዳታ መጠን ከ1.8 ቢሊዮን ገደማ አካባቢ እ.ኤ.አ በ2008 የእርዳታ መጠኑን በከፍተኛ ደረጃ ከፍ በማድረግ ወደ 3.5 ቢሊዮን አድርሳዋለች፡፡
ዓለም አቀፋዊ ለጋሾች እና አበዳሪ ድርጅቶች ግዙፍ የሆነ መጠን ያለው ገንዘብ (ለሰብአዊ፣ ለልማት፣ ለወታደራዊ፣ በመንግስታት መካከል በሚደረግ ለሁለትዮሽ እና በበይነ መንግስታት መካከል በሚደረግ እርዳታ፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚሰጥ እርዳታ፣ ወዘተ) በድጎማ መልክ እና በቀጥታ ገቢ በማድረግ እንደ ኢትዮጵያ ላለው ለማኝ አገዛዝ በመስጠት የእራሳቸውን ስልታዊ እና ጀኦፖለቲካ አጀንዳ ለማስፈጸም ጥረት ደርጋሉ፡፡ የእርዳታ መረባቸውን በመጠቀም በህዝቦች ጫንቃ ላይ በኃይል ተፈናጥጠው ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በእርዳታ እና በብድር በህዝብ ስም የሚሰጣቸውን ገንዘብ እራሳቸውን ለማበልጸግ የሚያውሉትን ጥቂት የወሮበላ ገዥ ስብስብ ነቀርሳዎች ለመቆጣጠር ይጠቀሙበታል፡፡ ለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶች ለማኝ መንግስታትን በመያዝ እንደፈለጉ ለማጦዝ እንዲችሉ ከሚጠቀሙባቸው እኩይ ምግባሮች ውስጥ ለእነርሱ የታዛዥነት አገልግሎት ለሚሰጡ ለማኝ መንግስታት ከፍተኛ የሆነ እርዳታ እና ብድር መስጠት ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ ሶማሊያን እ.ኤ.አ በ2006 ከወረረ በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ ለዚህ ገዥ አካል እ.ኤ.አ በ2005 ከነበረበት 1.8 ቢሊዮን ዶላር በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ በ2008 ወደ 3.5 ቢሊዮን የሚጠጋ ዶላር በእርዳታ መልክ ሰጥታለች፡፡
አንድ የአደንዛዥ ዕጽ ሱስ የተቆራኘው ሰው የአደንዛዥ ዕጽ የሱስ ወጥመድ ቁራኛ እንደሚሆን ሁሉ የህወሐት ለማኝ መንግስትም የእርዳታ የሱስ ቁራኛ ሆኗል፡፡ ያ ገዥ አካል የሚለውን ትዕዛዝ ይከተላል፣ “አገርህ በምን ዓይነት መንገድ እራሷን እንደምትችል ያለውን ስልት አትጠይቅ ይልቁንም ለአገርህ በምን ዓይነት መንገድ በመለመን በምንም ዓይነት መንገድ እራሷን እንዳትችል ለማድረግ ጠይቅ፡፡“ የህወሐት ገዥ አካል አመራሮች እርዳታን እንደ ጥቁር አባይ ምንም መጨረሻ ሳይኖረው እና ምንም ዓይነት ገደብ ሳያስቀምጥ እንደሚፈስሰው ሁሉ እርዳታንም እንደዚሁ “ነጻ ገንዘብ” አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ልመናን የሚያካሂዱ ለማኞች ለዘለቄታው ለማኝ እንደሆኑ ይቀራሉ የሚለውን የአለቃ አዎን ምክር በፍጹም እረስተውታል፡፡ ለህወሐት አመራሮች ዓለም አቀፋዊ እርዳታዎች እና ብድሮች ልክ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ እንደሚዘንብ ሁሉ ለእነርሱም እነዚህ እርዳታዎች እና ብድሮች ወቅቱን ጠብቆ እደሚዘንብ ዝናብ ከምዕራብ አምላክ እንደ መና ከሰማይ እንደሚዘንብ ዝናብ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ አንድ ዓመት አነስተኛ የሆነ የእርዳታ ዝናብ ሲኖር በሌላ ዓመት ደግሞ የተሻለ የእርዳታ ዝናብ ሊኖር ይችላል፡፡ ሆኖም ግን የምዕራብ አምላኮች በምንም ዓይነት መንገድ ቢሆን የእርዳታ ዝናቡን ለህወሐት ለማኝ መንግስት ማዝነቡን ሊያቋርጡ አይችሉም፡፡ በተለምዶው አነጋገር እንደሚባለው አምላክ ጥረት የሚያደርጉትን እና እራሳቸውን የሚረዱትን ሁሉ ይረዳል የሚለው አምላካዊ ቃል እንዳለ ቢሆንም የምዕራብ እርዳታ አምላኮች በቁንጮው ላይ ያሉትን የህወሐት አመራሮች እና በየዓመቱ ከሚሰጧቸው ገንዘብ ውስጥ በግል የሂሳብ አካውንታቸው በማጨቅ ሌላ ተጨማሪ በማሳደድ ላይ ይገኛሉ፣ አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል ነውና ተረቱ፡፡
በገደብ እና ያለምንም ገደብ ለህወሐት ለማኝ መንግስት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የተሰጠው እርዳታ ውጤቱ አውዳሚ ጉዳይ ነው፡፡ የህወሐት ለማኝ መንግስት በምንም ዓይነት መልኩ መልካም አስተዳደርን ወይም ደግሞ መልካም አስተዳደርን ለማምጣት የማስመሰል ስራ እንኳ እንደማይሰራ በነቢብም ሆነ በተግባር አረጋግጧል፡፡ የህወሐት አመራሮች ምንም ይስሩ ወይም አይስሩ የእርዳታ ገንዘቡ በኪሳቸው እንደሚገባ ያውቃሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 ሀገራዊ ድህረ ምርጫ ውዝግብን ተከትሎ የህወሐት አገዛዝ የተቃዋሚ የፖለቲካ አመራሮችን ሁሉንም በሚባል መልኩ፣ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞችን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን፣ እና የሲቪል ማህበረሰብ አመራሮችን ወደ ማጎሪያ እስር ቤቶች እየወሰደ በሚያስርበት ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ የበለጠ በመሸለም በ2005 ሰጥታው የነበረውን 1.8 ቢሊዮን ዶላር በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ እ.ኤ.አ በ2008 ወደ 3.5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ እርዳታ በመስጠት በመርህ ደረጃ ሌት ቀን የምትለፈልፍለትን ባዶ የሰብአዊ መብት ጥበቃ መፈክር በተግባር እንዲደፈጠጥ ለአምባገነኖች በመርዳት ሙሉ ተባባሪነቷን አስመስክራለች፡፡
እንደዚሁም ደግሞ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ተጣብቆ የሚገኘው የህወሐት ለማኝ መንግስት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ምንም ዓይነት ገደብ ሳይጣልበት ከእርዳታ ሰጭ እና አበዳሪ ድርጅቶች ገንዘብ እንደሚቀበል የሚያወዛግብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን አንዳንድ ጊዜ ገደብ በሚጣልበት ጊዜ በምንም ዓይነት ሁኔታ አስገዳጅ አይሆኑም፡፡ በዚህም ምክንት የህወሐት አጧዦች እና ቁልፍ አመራሮች አብዛኛውን ጊዜ በእርዳታ እና በብድር የሚመጣውን ገንዘብ የእነርሱን የዘመድ አዝማድነት ትስስር ለማጠናከር እንዲሁም በስልጣናቸው ለረዥም ጊዜ እንደ መዥገር ተጣብቀው ለመቆየት ይጠቀሙበታል፡፡ ብልጠት በተመላበት መልኩ በእርዳታ እና በብድር የተገኘውን ገንዘብ ወደ በጀታቸው በማዘዋወር በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ለእነርሱ የፖለቲካ ደጋፊዎች የስራ እድል መፍጠር እና የደህንነት መዋቅሩን በማስፋት የፖሊስ እና የወታደራዊ አገልግሎቶች ለማጠናከር ይጠቀሙበታል፡፡ እ.ኤ.አ ኦገስት 2011 የምርመራ ጋዜጠኞች ቢሮ እና ቢቢሲ እንደዘገቡት “የኢትዮጵያ መንግስት በብዙ ሚሊዮን ፓውንድ የሚቆጠረውን ዓለም አቀፋዊ እርዳታ ከታለመለት ዓላማ ውጭ የፖለቲካ ተቀናቃኞቹን ለመቅጣት እና ለማሸማቀቅ ተጠቅሞበታል“ በማለት የሁኔታውን አሳሳቢነት ይፋ አድርገዋል፡፡ የእርዳታ ገንዘብ የመለስ ዜናዊን መንግስት ለማጠናከር እና የተቃዋሚውን ጎራ ለማዳከም በመሳሪያነት የተጠቀመበት መሆኑን ቢሮው አሳማኝ በሆነ መልኩ ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡
በፈጠሩት ግዙፍ የፖለቲካ ማሽን (ፖለቲካ ማሺን) በመጠቀም እና የመራጮችን ድምጽ በመግዛት እና በመስረቅ እ.ኤ.አ በ2010 በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ 99.6 በመቶ አመጣሁ በማለት የድል ከበሮውን ደልቋል፡፡
የህወሐት ለማኝ መንግስት በዓለም አቀፉ ለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶች እራሱን ችሎ መንቀሳቀስ እንዳይችል አበራታች ያልሆኑ ነገሮች ተፈጽመውበታል፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 “የዩኤስ አሜሪካ በአፍሪካ የምታራምደው ፖሊሲ የሞራል ኪሳራ” በሚል ርዕስ ገዥው አካል ከውጭ በሚገኘው እርዳታ በሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ላይ ሙሉ በሙሉ ጥገኛ በመሆኑ በመንግስታት በሚሰጡ ግዙፍ ብድሮች እና የማያቋርጥ የሰብአዊ እርዳታ ለአምባገነኑ ገዥ አካል አሰራር የሚተው ከሆነ በአግባቡ ያልተመራ የኢኮኖሚ መመሰቃቀል፣ አውዳሚ ሙስና እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የሚመጣ ድህነት የሚንሰራፋ ይሆናል፡፡ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የህወሐት ለማኝ መንግስት በለጋሽ እና በአበዳሪ ድርጅቶች ዘንድ ተጠያቂነት ያለበት መሆኑን ሳያስመሰክር የልመና ኮሮጆውን እንደተለመደው በመያዝ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የረኃብ ሰለባ የሆኑ ዜጎችን ለመመገብ በሚል ልመናውን ቀጥሏል፡፡
በዚህም መሰረት ገዥው አካል በህዝቡ ዘንድ ታማኝነትን ፍጹም በሆነ መልኩ አጥቷል፡፡ እ.ኤ.አ በ2008 በደቡብ ኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው ረኃብ አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ ተጠያቂ እንዳልሆነ እና በረኃብ ለተጠቃው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ ደህንነት መጠበቅ ብዙም እንዳላተጨነቀ የሚያመላክት ነበር፡፡ መለስ በወቅቱ ላሳየው ቸልተኝነት እና የአቅም ማነስ ችግር ለቀረበበት ክስ በመከላከል እንዲህ ብሎ ነበር፣ “ያ ጉዳይ በእኛ በኩል ያልተሳካ ነበር፡፡ በእጃችን ላይ ያለውን አስቸኳይ ሁኔታ በውል አልተገነዘብነውም ነበር፡፡ በዚህ የተወሰነ አካባቢ የተጎዱ ህጻናት ገጽታዎች ገዝፈው እስኪወጡ ድረስ የነበረውን ምስቅልቅል ሁኔታ አላወቅንም ነበር፡፡“ የምግብ እህል እጦት ጉዳት የተለመደ እና የማይቀር መሆኑ እየታወቀ እና በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እንደሚከሰት እየታወቀ አንድ ሀገርን የሚመራ መሪ የህጻናቱ አጥንት አንደ ጣረ ሞት እስኪወጣ ድረስ ረኃብ አለመኖሩን እና ዜጎች በረኃቡ አደጋ መጠቃታቸውን አላወቅንም ነበር ማለት በጣም አስደንጋጭ ሁኔታን የሚፈጥር እና ኃላፊነትን እንደመዘንጋት የሚቆጠር እና የሚያስገርም ጉዳይ ነው፡፡ በ2014 የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው ለረኃቡ የለማኙ የህወሐት አገዛዝ ምላሽ ከዚያ የተለየ አልነበረም፡፡ እንዲህ የሚል ነበር፣ “በእጃችን ላይ በጣም የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ተጎጅዎች የነበሩ መሆናቸውን ለመገንዝብ ዘግይተን ነበር…“ በስልጣን ላይ ያለው ገዥ አካል የርኃብ፣ የምግብ እጥረት እና አለመመጣጠን ጥያቄ ዓመት ከዓመት፣ አስርት ዓመት ከአስርት ዓመት ወሳኝነት ባለው መልኩ ማስወገድ ያልቻለው ለምንድን ነው? ለዚህ ምላሹ በስልጣን ላያ ያለው የህወሐት ለማኝ መንግስት ከምዕራብ በሚመጣው እርዳታ እና ብድር ንጉሶች እና ንግስቶች በመሆን እጅግ ከፍተኛ የሆነ ትርፍን የሚያጋብሱበት የመዝረፊያ ስልት ሆኖ ስላገኙት እና በብዙ ሚሊዮን የሚመጣውን ዶላር በልማት ስራ ላይ ማዋል ለእነርሱ ገንዘብ መዝረፊያነት የማይስማማ ሆኖ ስለተገኘ ነው፡፡ ድህነትን ለዘለቄታው ለማጥፋት ለእነርሱ ምናቸው አይደለም ሆኖም ግን ድህነትን ታሪክ እናደርጋለን የሚል ባዶ መፈክር እያሰሙ በህዝብ ላይ ይሳለቃሉ፡፡ ስለሆነም ዓለም አፋዊ እርዳታ መልካም አስተዳደርን የሚያኮሰስ ብቻ አይደለም ሆኖም ግን እራሱ ድህነት ነው፡፡
የዓለም ባንክ፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ሌሎች የምዕራብ አገሮች ለጋሽ ድርጅቶች የህወሐትን ለማኝ ገዥ አካል ከውጭ እርዳታ እና ብድር የገንዘብ ትሩፋት ለማግኘት ከሚሰራበት ሁኔታ ወጥቶ በትክክለኛው መንገድ መስራት እንዲችል አጽንኦ በመስጠት አስጠንቅቀውታል፡፡ ባለፈው ሳምንት ገዥው አካል ዓለም አቀፍ የቦንድ ገበያዎችን ለማግኘት እንደሚፈልግ አሳውቆ ነበር፡፡ የህወሐት አገዛዝ ለሩብ ከፍለ ዘመናት ያህል ከውጭ እርዳታ እና ብድር በመቀበል በህዝቦች ስም የሚመጣውን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማጋበሻ ሲያደርገው ቆይቷል እናም አሁን ደግሞ ሌላ የገንዘብ መለመኛ አማራጭ መንገዶችን በመፈለግ ላይ ይገኛል፡፡ የህወሐት የገንዘብ ሚኒስቴር እንዲህ በማለት አውጇል፣ “በዴሴምበር ሁለተኛው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ ሁለት ሳምንታት እና በጃኗሪ የመጀመሪያ ሳምንታት ለዓለም አቀፍ የካፒታል ገበያ የሚቀርብበት ነው፡፡ መሰረተ ልማትን ለማሻሻል ቦንዶች የእቅዱ አንድ አካል በመሆን አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡“
ከ23 ዓመታት በኋላ በሚያስደንቅ ሁኔታ የሕወሐት ገዥ አካል የገንዘብ ገበያ/Capital market ያለ መሆኑን በድንገት ደረሰበት!! በጣም ይደንቃል !! የህወሐት ገዥ አካል እንደዚህ ያለ የገንዘብ ማግኛ ዘዴ መኖሩን ከዚህ ቀደም ፈጽሞ የማያውቀው ስለነበር ህገወጥ በሆነ መልኩ በዩናይትድ ስቴትስ በቁርጥርጭ ገንዘብ ለኢትዮጵያ ዲያስፖራ የቦንድ ሽያጭ በማቅረብ 5,250 ሜጋዋት የሚሆን አቅም ያለውን ታላቁ የህደሴ (ከንቱ ዉዳሴ) ግድብ እያለ ሌት ቀን የሚደሰኩርለትን በአባይ ወንዝ ላይ ለመገደብ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከዲያስፖራው ሊገኝ የሚችለው ገንዘብ ለለማኙ ገዥ አካል ክስ መሙያ ሆና ቀርታለች ። ከዲያስፖራው ገንዘብ የማግኘቱን ጥረት ያላቆሙ መሆናቸውን የምናውቅ መሆኑን አንዲገነዘቡ የህወሐት ገዥ አካል በአሁኑ ጊዜ ከህዝብ ጋር ያለውን የመድረክ ላይ ግንኙነት ዘመቻ በማጠናከር ዓለም አቀፍ የገንዘብ ገበያዎችን ለመድረስ በመኳተን ላይ ይገኛል፡፡ እንደዚሁም ለአስርት ዓመታት ያህል ህገወጥ በሆነ የገንዘብ ዝውውር ግዙፍ የሆነ ገንዘብ ከኢትዮጵያ እንዲወጣ አድርጓል፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ/Global Financial Integrity የተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት እንዲህ የሚል ዘገባ አውጥቶ ነበር፣ “እ.ኤ.አ በ2000 እና በ2009 ዓመታት መካከል ኢትዮጵያ 11.7 ቢሊዮን ዶላር በህገወጥ መልክ ከአገር እንዲወጣ አድርጋለች፡፡“ እስቲ እንግዲህ አስቡት ወደ 12 ቢሊዮን የሚሆን ገንዘብ በህገወጥ መልክ ከአገር እንዲወጣ ባይደረግ እና በቀጥታ ለሀገሪቱ የልማት ፕሮግራም የሚውል ቢሆን ኖሮ ምን ያህል የኢትዮጵያን የልማት ስራ ወደፊት ሊያራምድ ይችል እንደነበር!!!
በኢትዮጵ ያለው የለማኝ መንግስት የሚያስፈልገውን በጀት (በአንድ ዓመት ውስጥ ሊሰበስብ እና ሊያወጣ ያቀደውን) ለማግኘት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ጥገኝነቱን ያደረገው ከለጋሽ እና ከአበዳሪ ድርጅቶች ከሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ ነው፡፡ የዓለም የኢኮኖሚ እና የልማት ትብብር ድርጅት/Organization for Economic Cooperation and Development የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት እንዳወጣው ዘገባ ዩናይትድ ስቴትስ፣ እንግሊዝ፣ እና የዓለም ባንክ (ሌሎች የአውሮፓ ወይም ደግሞ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገሮችን ሳይጨምር) ከ50-60 በመቶ የሚሆነውን የህወሐትን ለማኝ መንግስት ሀገራዊ ዓመታዊ በጀት ለበርካታ ዓመታት ባለማቋረጥ ሲሸፍኑ የቆዩ ናቸው፡፡ ዳምቢሳ ሞዮ የሞተ እርዳታ/Dead Aid በሚለው መጽሐፏ በግልጽ እንዳስቀመጠቸው የህወሐት ገዥ አካል ዋነኛው የገቢ (በጀት) የመገኛ ምንጩ የውጭ እርዳታ ሲሆን እጅግ በጣም ግዙፍ እና 97 በመቶ የሚሆነውን በጀት የሚያገኘው ከዚሁ ከውጭ እርዳታ ነው በማለት አጠቃላዋለች፡፡
የበጀት ድጋፍ የሚለው የእርዳታ አሰጣጥ ዘዴ ለልማት እርዳታ በማለት ብዙ ለጋሽ አገሮች ለድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ በሚል ስልት ለበርካታ ታዳጊ አገሮች በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች እርዳታውን ለመስጠት የመረጡት የእርዳታ አሰጣጥ ዘዴ ነው፡፡ “የበጀት ድጋፍ” (በጀት ሰፖርት) የሚለው የእርዳታ አሰጣጥ ዓይነት እ.ኤ.አ በ1989 በዓለም አቀፍ የግንዘብ ድርጅት፣ በዓለም ባንክ፣ እና በአሜሪካ የገንዘብ መምሪያ የዋሽንግተን ስምምነት/Washington Consensus በሚል የተቋቋመ እና በቀውስ ውስጥ ያሉ ሀገሮች ኢኮኖሚያቸው እንዲያንሰራራ እና እንዲረጋጋ በሚል እሳቤ ሀገሮቹን በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ እና የሀገር ውስጥ የስራ ፈጣሪዎች እንዲነቃቁ እና እንዲነሳሱ ተብሎ የተቀየሰ መጥፎ እና የኒዮሊበራል ጭራቃዊ አሰራር እና ለእነርሱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲስማማ ተብሎ የተዘጋጀ ባዶ ተስፋ ነው፡፡ (በአንድ መጽሐፍ ውስጥ ባለ አንድ ጽሑፍ ላይ የጸረ ኒዮሊበራል አራማጅ በሆኑት ጆይ ስቲግልዝ ባቀረቡት ትችት ላይ መለስ እንዲህ ብሎ ነበር፣ “የኒዮሊበራል ፍልስፍና ያለቀለት ጉዳይ ነው፣ የአፍሪካን ተሀድሶ ሊያመጣ አይችልም፡፡ ስለሆነም የአፍሪካን ተሀድሶ ለማምጣት እና እንደገና የአፍሪካ መነሳሳት እንዲመጣ ከተፈለገ ሌላ አይነት አካሄድ መምጣት አለበት“)
“በዋሽንግተኑ ስምምነት” መቃብር ላይ ሌባ መንግስታት ከእርዳታ ሰጭ እና አበዳሪ ድርጅቶች ጥያቄ እና ፍላጎት ከስምምነት እግረ ሙቅ እስራት ነጻ በማድረግ እራሳቸው ሊጠለሉበት የሚችል የበጀት ድጋፍ የሚል ዛፍ አደገ፡፡ በበጀት ድጋፍ እርዳታ እና አበዳሪ ድርጅቶች የእርዳታ እና የብድር ቅድመ ሁኔታዎችን መጫን አይችሉም ወይም ደግሞ እርዳታውን ወይም ብድሩን ከሚቀበለው አገር የተለየ የፖሊሲ አካሄድ እንዲከተል የሚል ማስገደጃ ነገር የለውም፡፡ ከዚያ ይልቅ ከእርዳታ እና ብድር ተጠቃሚው አገር የልማት ፖሊሲ እና እስትራቴጅ እንዲሁም ድህነት ቅነሳ ፕሮግራሞች ጋር ሊስማሙ የሚችሉ ስልቶችን መርጠው ይገባሉ፡፡ በቀላሉ ግልጽ ለማድረግ የበጀት ድጋፍ እርዳታ እና ብድር ተቀባይ አገሮች ያሉትን የሌባ መንግስታት እና በሙስና የበከቱ መሪዎችን ከህዝብ ተጠያቂነት እና ግልጸኝነት በመከላከል ተንሰራፍቶ የሚገኘውን ሙስና ለመደበቅ ጥበብ የተሞላበት የአካሄድ ስልት ነው፡፡
እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 2009 አቶ መለስ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የበጀት ድጋፍ በማድረግ የኢትዮጵያን የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንዲረዱ ለዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጥሪ አቀረበ፡፡ የእርሱ ተግባራዊ ሊሆን የማይችል እና ከሚገባው በላይ የተለጠጠው የእድገት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በአብዛኛው በበጀት ድጋፍ በውጭ የልማት እርዳታ ላይ የተንጠለጠለ እ.ኤ.አ በ2015 ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የታቀደ የድንብርብር ዕቅድ ነው (2015 መቸ እንደሆነ ልብ ይሏል!)፡፡ መለስ በተጨባጭ በተግባር ለማይገለጸው እና በቋፍ ላይ ለተንጠለጠለው ስሜታዊ ዕቅድ ግዙፍ የሆነ የመሰረተ ልማት ግንባታ እና መጠነ ሰፊ የሆኑ የግብርና ልማት ምርቶችን በማምረት ኢትዮጵያ የመካከለኛ ገቢ ካለቸው አገሮች ጋር እኩል ትሰለፋለች የሚል የተወዣበረ አስተሳሰብን ይዞ ነው የድንብርብር ጉዞ ሲጓዝ የነበረው፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት/United States Agency for International Development ከ2011- 2015 ባዘጋጀው አገራዊ የልማት ትብብር ሰነዱ ላይ እንዲህ የሚል ግልጽ መልዕክት አስፍሮ ይገኛል፣ “ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ወደተረጋጋ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በማምራት ጠንካራ መሰረት ያላቸው የማህበራዊ አገልግሎቶች እና የተመጣጠነ የህዝብ እድገት በማስመዝገብ ወደ አዲስ ምዕራፍ ሽግግር ታደርጋለች፡፡“ ይላል! ማለት ቀላል ነገር ነውና፡፡ አሁን ላይ ሆነን የተተነበየለትን የጊዜ ቀመር ስናሰላው 2015 ለመድረስ ሁለት ድፍን ሙሉ ወራት ብቻ ይቀሩናል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ 2016 ለመድረስ ድፍን አንድ ዓመት ይቀረናል፡፡ እናም ኢትዮጵያ ከዓለም ከመጨረሻዎቹ ደኃ አገሮች ሁለተኛ እንደሆነች ጉዞዋን ቀጥላለች!!! የታየ ለውጥ አለ ከተባለ በህዝብ ሀብት በሚተዳደረው የመገናኛ ብዙሀን ሌት ቀን እንደ መልካም ነገር የሚነዛው ባዶ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ብቻ ነው!
ልማታዊ መንግስት ከሌባ መንግስት ጋር ሲነጻጸር፣
እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 25/2014 ፕሬዚዳንት ኦባማ እንዲህ ብለው ነበር፣ “ከዓለም በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ ካሉ አገሮች አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ እየሆነ ካለው ሌላ የተሻለ የእድገት ምሳሌ ሊሆን የሚችል በአፍሪካ አይገኝም፡፡“ የፕሬዚዳንቱ ንግግር በየትኛውም ትክክለኛ በሆነ መረጃ ላይ ተመስርቶ የተሰጠ አይደለም፣ ሆኖም ግን ይህ ድርጊት አሳዛኝ ነው፣ ምክንያቱም አሁን በህይወት በሌለው በመለስ ዜናዊ ዕኩይ የብልጣብልጥነት ዘዴ ተፈብርኮ የተነዛውን የቅጥፈት ቁጥር እና ባዶ የምርቃና ትንተና እንዳለ በመውሰድ የታላቋ አገር የአሜሪካ መሪ ሆነው እንደበቀቀን እንዳለ መድገማቸው አሳፋሪ ነገር ነው፡፡
ባለፉት አስርት ዓመታት መለስ ዜናዊ እና ደቀመዝሙሮቹ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎች አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ልማታዊ መንግስታቸው በተከለው ጥበብ የተሞላበት አካሄድ በኢትዮጵያ ላይ እስከ አሁን ታይቶ የማይታወቅ እድገት እንደተመዘገበ በሞኖፖል በተቆጣጠሩት የመገኛ ብዙህን ሌት ቀን ድንፋታቸውን ያሰሙ ነበር፣ አሁንም በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡ እ.ኤ.አ ማርች 2009 መለስ የውሸት ፈገግታ በተቀላቀለበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ12.8 በመቶ ያድጋል በማለት ትንበያ ሰጥቶ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተባሉት አጫፋሪዎቹ እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶ ነበር፣ “በዚህ ዓመት 10.1 በመቶ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት የምናስመዘግብ ሲሆን የዋጋ ግሽበት ግን ወደ 3.9 በመቶ ይወርዳል፡፡“ እንደዚህ ዓይነቶቹ ከመጠን በላይ የተጋነኑ የድንፋታ ንግግሮች በተለያዩ በዓለም አቀፍ ተቋማት ዘንድ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ስለሚታዩ እና ስለሚመዘኑ እርባና የለሽ በመሆን ከቁጥር የሚገቡ አይሆኑም፡፡ የዓለም የልማት ማዕከል/Center for Global Development እ.ኤ.አ በ2010 ባወጣው ዘገባ መሰረት እ.ኤ.አ ከ1996 – 2008 ድረስ አማካይ ዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገቱ 4.1 በመቶ እንደነበር ጠቁሟል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የወቅቱን የዓለም ሁኔታ ከግምት በማስገባት እ.ኤ.አ በ2009 ኢትዮጵያ 6 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ልታስመዘግብ እንደምትችል ትንበያ ሰጥቶ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ኖቬምበር 2007 ዘ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት እንዲህ የሚል ዘገባ አውጥቶ ነበር፣ “የኢትዮጵያ መንግስት ከ2003/04 ጀምሮ በየዓመቱ ኢኮኖሚው በሚያስደንቅ ሁኔታ በ10 በመቶ አድጓል የሚል መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ሆኖም ግን ትክክለኛው የእድገት መጣኔ ከ5-6 በመቶ አካባቢ ነው፡፡ ይህም የእድገት መጣኔ ከሰሀራ በታች ካሉ አገሮች አማካይ የኢኮኖሚ እድገት በጣም በትንሹ ከፍ ሊል ይችላል“ ብሏል፡፡ ይኸው ዘ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት ማርች 2012 ባወጣው ዘገባ የመለስን የቅጥፈት የኢኮኖሚ እድገት ድንፋታ በማስመልከት እንዲህ የሚል ማጠቃለያ ሰጥቶ ነበር፣ “የኢትዮጵያ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት አቶ መለስ ዜናዊ የተነበዩት ባለሁለት አሀዝ የኢኮኖሚ እድገት ተምኔታዊ ይመስላል“
“የመለስ ዜናዊ የውሸት የኢኮኖሚ እድገት” በሚል ርዕስ አዘጋጅቸው በነበረው ትችቴ ላይ ከጥርጣሬ በላይ በግልጽ ትንታኔ የሰጠሁበት ስለነበረ መለስ የተቀቀሉ የስታቲስቲክስ ቁጥሮችን እያወጣ በእጅጉ የተሳሳተ መረጃ ይሰጥ እንደነበር አጠያያቂ ጉዳይ አይደለም፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 ጥቂት የእርሱ የስታቲስቲክስ ቁጥሮች ስህተት እንደነበረባቸው ለማመን በሚያስመስል መልኩ የአካሄድ አቅጣጫውን ቀየር አድርጎ እንዲህ ብሎ ነበር፣ ”የኢኮኖሚ እድገቱ አሀዝ ትክክለኛነት አከራካሪ ሆኗል፡፡ እናም እኛው እርስ በእርሳችን እና ከልማት አጋሮቻችን ጋር መንግስታችንን ጨምሮ ቀጣይነት ባለው መልኩ ጥቂት በሆኑ አሀዛዊ መረጃዎች ላይ ውይይት አድርገናል፡፡ ሆኖም ግን ዋናው ጉዳይ ማንም ሊያስተባብለው የማይችለው ኢኮኖሚያችን ከነበረበት በጣም ዝቅተኛ የእድገት ደረጃ በመነሳት ባለፉት ስምንት፣ አስር እና ከዚያ በላይ በሆኑ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ወደ ሆነ የእድገት ደረጃ ተሸጋግሯል“ ነበር ያለው፡፡ እንዲህ አይነቱን አካሄድ ቤንጃሚን ዲስራሊ በሚገባ ተመልክተውት ኖሮ እንዲህ ነበር ያሉት፣ “ቅጥፈቶች አሉ፣ ነጭ ቅጥፈቶች እና አሀዞች/ቁጥሮች ቅጥፈቶች ።“
የመለስ በእራሱ አስተሳሰብ እና አካሄድ አይነት የፈጠረው ልማታዊ መንግስት ሲመረመር በእርግጠኝነት በስስ መጋረጃ የተሸፈነ የኒዮ ሶሻሊስት ርዕዮት ዓለምን ካባ በማጥለቅ ከኒዮሊበራል ርዕዮት ዓለም በተቃራኒው በመቆም ድምጹን ከፍ አድርጎ በመጮህ ከወዲያ ወዲህ እያምታታ በመኖር የዘረፋ ከረጢቱን ለመሙላት የሚናውዝ የሌቦች መንግስት ነው፡፡ በኢራስመስ ዩኒቨርስቲ ባላጠናቀቀው የሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያ የማሟያ ጹሁፍ ላይ መለስ የኒዮሊበራል ርዕዮት ዓለምን እንዲህ በማለት ኮንኖታል፣ “የኒዮሊበራል መንግስት እንደ አዳኝ አጥቂ አውሬ ነው፡፡ በጨለማ ውስጥ ሆኖ የሚመለከት መንግስት ነው“ በማለት ገልጾታል፣ “በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ተሳትፎ እጅግ የቀነሰ መንግስት“፡፡ መለስ ሙግቱን በመቀጠል የኒዮሊበራል መንግስት መዋቅራዊ አቅመቢስነት እንዳለበት ተቁሞ ይህ መንግስታዊ ፍልስፍና “የቀለበት አዙሪቱን እና የድህነት ወጥመድን ሊያሸንፍ እና ሊበጣጥስ አይችልም” ብሏል፡፡
ከአጥቂ/አዳኝ እና በጨለማ ውስጥ ከሚመለከት የኒዮሊበራል መንግስት በተቃራኒ በኩል ያለውን የእርሱን ልማታዊ መንግስት ደግሞ መለስ እንዲህ የሚል የመሞገቻ ዳህራ አቅርቧል፣ “ልማታዊ መንግስት ልማትን የሚያስበው በመጀመሪያ ደረጃ እንደ የፖለቲካ ሂደት ሆኖ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ሂደት በቀጣይነት የሚመጡ ናቸው፡፡“ የመለስ ልማታዊ መንግስት የልማት ሂደቱን ያቅዳል፣ ያደረጃል፣ ተግባራዊ ያደርጋል፣ ይገመግማል፣ ከዚያም አጠቃላይ ሂደቱን ይቆጣጠራል፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነት [የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አብዛኛውን ጊዜ ግለሰቦች፣ ወይም ደግሞ ቡድኖች፣ በሌሎች ግብር ከፋዮች ወይም ደግሞ ተጠቃሚዎች አለያም ሌሎች ግለሰቦች ኪሳራ በየተለየ መልኩ ኢኮኖሚያዊ ውድድር በማድረግ መንግስት በሌሎች ላይ ግብር እንዲጥል፣ ከእራሱ ማዕከላዊ ግምጃ ቤት ወጭ እያደረገ እንዲሰራ እና የቁጥጥር ፖሊሲዎችን እያወጣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን በመቆጣጠር ለእነርሱ የገንዘብ ወይም ሌሎች ልዩ ጥቅማጥቅሞች የሚያስገኝ የአሰራር ሂደት ነው በማለት ይገልጹታል] ባህሪን ለማጥፋት የተሟላ አቅም ያለው ብቸኛው መንግስታዊ ተቋም ልማታዊ መንግስት ነው ይላል መለስ፡፡ በመለስ የኢኮኖሚ ፍልስፍና መሰረት የግል ዘርፉ በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃዎች ላይ ቋሚ ተመልካች ነው እናም ምንም ዓይነት የተነሳሽነት ስሜት የማያሳይ አጋር እንኳ ያልሆነ ኢኮኖሚውን በብቸኝነት ተቆጣጥሮ ለሚያዝዝበት ለልማታዊ መንግስት ታማኝ ታዛዥ ነው፡፡ መለስ እንዲህ ይላል፣ “ልማታዊ መንግስት ከሌለ አብዛኞቹ ወይም ደግሞ እነዚህ ሁሉም በመልማት ላይ ያሉ አገሮች በድህነት ወጥመድ ውሰጥ በመያዝ ወደ ድህነት አራንቋ ውሰጥ በመዘፈቅ የስራ እና የንግድ እንቅስቃሴውን የሚያራምዱት ስራ ፈጣሪዎች እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍል መደቦች ሊፈጠሩ አይችሉም“ ይላል፡፡ የመለስ “የልማታዊ መንግስት” ፍልስፍና በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ያሉትን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት ታምራዊ መፍትሄ በመስጠት እድገትን ማምጣት ይቻላል በሚል የፍልስፍና ዳህራ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡
“የመለስ ዜናዊ የውሸት ኢኮኖሚክስ” በሚል ርዕስ ባዘጋጀሁት ትችቴ ላይ የሚከተለውን ማብራሪያ አስፍሬ ነበር፣ “የአቶ መለስ ‘የእድገት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ’ (የልማታዊ መንግስት መሰረት የሆነው ዋልታ እና ማገር) ሊኖሩን የሚገቡ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው የፍላጎት ዝርዝሮች ከመሆን ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡ ለኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ራዕይ በመንደፍ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የጎለበተባት፣ መልካም አስተዳደር እና ማሕበራዊ ፍትህ የሰፈነባት አገርን ለመፍጠር ዕቅድ የያዘ ነው፡፡ እንደዚሁም ደግሞ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀም ዘመናዊ እና ምርታማ የሆነ የግብርና ዘርፍ እና ምርታማ የሆነ የኢንዱስትሪ ዘርፍ በመመስረት እና በአጠቃላይ መልኩ ዘመናዊ ኢኮኖሚ በመገንባት የዜጎችን የነፍስ ወከፍ ገቢ ከፍ በማድረግ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ካላቸው ገቢ ጋር እኩል እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ፈጣን፣ ቀጣይነት እና ሁሉንም ዜጎች እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት እንደ ዋና የማስፈጸሚያ ምሰሶዎች ተደርገው የተያዙት ግብርናን እንደ ዋነኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ምንጭ ማድረግ፣ ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ላይ ገንቢ የሆነ ሚና እንዲጫወት አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ማማቻቸት፣ መሰረተ ልማትን እና ማህበራዊ ልማትን ማስፋፋት፣ የማስፈጸም አቅምን ማጎልበት እና መልካም አስተዳደር በየደረጃው እንዲጎለብት እና ስር እንዲሰድ ማድረግ፣ ለሴቶች እና ወጣቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት እንዲጠናከሩ እና ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል“ በማለት ከፍተኛ የሆነ ድንፋታ ተደርጓል፡፡
ሆኖም ግን እነዚህ ባዶ የምጣኔ ሀብት መፈክሮች፣ በሚያሰለች ሁኔታ ተደጋግመው የሚነገሩ አባባሎች፣ ባበለስልጣኖች እየተፈበረኩ የሚነገሩ አዳዲስ ቃላት እና ሀረጎች፣ እንዲሁም ታዋቂነት ያላቸው የዲስኩር ማጣፈጫ አባባሎች በየጊዜው እየተዥጎደጎዱ የሚባሉ እና የሚነገሩ ቢሆንም የአቶ መለስ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንደሚደሰኮርለት ተጨባጭነት ያለው ውጤት ከማምጣት እና ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ከማስገኘት ይልቅ ምጣኔ ሀብታዊ ሀፍረት ተከናንቧል፡፡ የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አሳፋሪ ከሆነ ልማታዊ መንግስቱም ከዚህ የተለየ ዕጣ ፈንታ የለውም! እ.ኤ.አ በ2009 በበርሊን ከተማ በሚካሄደ በአንደ በከፍተኛ የስልጣን ደረጃ ላይ ባሉ የምዕራብ ለጋሽ ሀገሮች የፖሊሲ አውጭዎች ስብሰባ ላይ አንድ የጀርመን የዲፕሎማት ሰው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ችግሮች ዋና መሰረት “የመለስ ደካማ የሆነ የምጣኔ ሀብት ግንዛቤ መኖር ነው” ብለው ነበር፡፡ (ውይ የሚያሳዝን ነገር ነው! የጀርመኑ ዲፕሎማት ያልተገነዘቡት እና ያልተረዱት ጉዳይ አለ፣ ይኸውም መለስ የማስተርስ ዲግሪውን ከኢራስመስ ዩኒቨርስቲ በምጣኔ ሀብት ሊያገኝ ትንሽ ሲቀረው ነበር የከሸፈው፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ በ1991 ኦፕን ዩኒቨርስቲ እየተባለ (ኮሮስፖንደንስ ኮርስ) በሚጠራው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን እንዳጠና እና (ከእርሱ ክፍል አንደኛ በመውጣት እንደተመረቀ) በውል ሳያጤኑት ቀርተው ይመስለኛል፡፡)
መለስ የልማታዊ መንግስትን የአመራር ቀጣይነት (አምባገነንነት) ለማሳመን በጣም ረዥም ርቀት ተጉዟል፣ ምክንያቱም የፖሊሲ ቀጣይነት አስፈላጊነት ያለ በመሆኑ ነው ብሏል፡፡ ልማታዊ ፖሊሲ አንድን ደኃ አገር በአንድ በተወሰነ የምርጫ የጊዜ ገደብ ውስጥ በሚደረግ ጥረት ወደበለጸጉት አገሮች ተርታ ለማሸጋገር ያለው አቅም አስተማማኝ አይደለም፡፡ ቀጣይነት ያለው እና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ ከተፈለገ የፖሊሲ ቀጣይነት መኖር አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ባለበት አገር ላይ የፖሊሲ ቀጣይነት መኖር ሊወገድ የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡ ልማትን የበለጠ ሊጎዳው የሚችለው ነገር የፖለቲካ ሰዎች ከአንድ የምርጫ የጊዜ ገደብ በኋላ አዛልቀው ለማየት አለመቻላቸው ነው፡፡ ስለሆነም ልማታዊ መንግስት ለረዥም ጊዜ በስልጣን ላይ ለመቆየት እና ስኬታማ የሆኑ የልማት ፕሮግራሞችን ለማካሄድ እንዲችል ከተፈለገ የዴሞክራሲያዊ ስብዕናን መላበስ አይጠበቅበትም የሚል መሞገቻ አቅርቧል፡፡ በሌላ አባባል የልማታዊ መንግስት ዋና መገለጫ ኢዴሞክራሲያዊ መሆን ነው የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
የግል ዘርፉ ሙሉ ለሙለ “ለልማታዊ መንግስቱ” እጅ መስጠት አለበት ምክንያቱም በመልማት ላይ ባለ አገር ያ መንግስት ብቻ ነው የተረጋጋ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ከዚህም ጋር ተያይዞ ልማታዊ ጥሪ የሚያደርገው… ልማታዊ መንግስት የግል ዘርፉን ተዋናዮች የሚያከናውኗቸው ተግባሮች ልማታዊ ወይም ደግሞ ክራይ ሰብሳቢ መሆን ባለመሆናቸው ላይ መሰረት በማድረግ ለመሸለም እና ለመቅጣት ችሎታው እና ፍላጎቱ እንዲኖረው የግድ ይላል፡፡ በማጠቃለያውም መለስ የሚከተሉትን አስደንጋጭ የሆኑ ሆኖም ግን በከፍተኛ ደረጃ ለእራስ ጥቅም የቆሙ ነገሮችን አስቀምጧል፣
ለልማታዊ መንግስት ምቹ የሆኑ ነገሮች በሌሉበት ጊዜ የተረጋጋ ዴሞክራሲ ብቅ እንዲል ማሰብ በእርግጠኝነት በጣም ሩቅ ነው፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ምቹ የሆኑ ነገሮች ባሉበት እና ለዴሞክራሲ መስፈን ግን ዋስትና በሌለበት ሁኔታ በእርግጠኝነት የልማታዊ እና የዴሞክራሲያዊ መንግስት የመኖር ዕድል ብቅ ይላል፡፡ በዚህም መሰረት በመጨረሻ በደኃ ሀገር የተረጋጋ ዴሞክራሲ የመኖር ዕድሎች ከልማታዊ መንግስት ብቅ ማለት እና ከእርሱ ጋር አብሮ ከሚሄደው ፈጣን ልማት ጋር በእጅጉ የተዛመዱ እና የተቆራኙ ሆነው ይገኛሉ፡፡
በግልጽ ለማስቀመጥ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት፣ ልማት፣ ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር፣ የሰብአዊ መብት ጥበቃ፣ ወዘተ ለማስመዝገብ የምትችለው ለልማታዊ መንግስት ርዕዮት ዓለም እራሱን በጽናት ያቆመ እና በአንድ ሰው አመራር ስር በተዋቀረ በአንድ ዘላለማዊ በሆነ በማይለወጥ የፖለቲካ ፓርቲ ስትመራ ብቻ እና ብቻ ነው፡፡ ይህ በየትኛውም መደበኛ በሆነ ሙያው በሚጠይቀው የትምህርት ክፍል ገብቶ ሳይማር እራሱን አዋቂ አድርጎ ከሚያቀርብ እብሪተኛ ሰው የሚመጣ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ልዩ እና ቆንጆ ህልዮት ነው!
መለስ እራሱን የተዋጣለት የምጣኔ ሀብት ባለሙያ እና ለሁሉም ነገር አለሁ የሚያስብል ባለብዙ ዘርፍ የዕውቀት ባለቤት እንዲሆን ይመኛል፡፡ በወጣትነት ዘመኑ ጫካ በነበረበት ጊዜ አሁን ከተጣለው የማርክሳውያን የፖለቲካል ኢኮኖሚ ህልዮት ጋር በመጣበቅ መለስ (እንዲሁም ደቀመዝሙሮቹ) ስልጣንን ከተቆናጠጡ በኋላ ስብዕናውን ከፍ አድርጎ በመኮፈስ በኢትዮጵያ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ እና የልማታዊ መንግስት ዋና መሀንዲስ እና ቀማሪ በማድረግ በየአደባባዩ ዲስኩሮቹን በማቅረብ እራሱን ሰየመ፡፡ ሊታመን በማይችል መልኩ መለስ ወይም የእርሱ አታላይ እረዳቶቹ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን እና የልማታዊ መንግስትን ህልዮት እንዲቀምሩ እና ወደ ተግባር እንደዲያሸጋግሩ እድሉን ወስደው ነበር፡፡ ያንን ለመተግበር ከመሞከር ይልቅ ለምጽዋት እጆቻቸውን እና መዳፎቻቸውን በመዘርጋት በቀጥታ ወደ ሃብታሞቹ በሮች ለምጽዋት የሚሄዱባቸውን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ የዓለም ባንክ እና የምዕራቡ ዓለም መንግስታት ኤምባሲዎች ኒዮሊበራል እያሉ የስድብ ናዳቸውን ማዥጎድደጎድ መረጡ፡፡ “ገንዘብ፣ ጉቦ፣ በጣም አስገራሚ ነገር ነው!!!“
ታላቁ ቅጥፈት በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ልማታዊ መንግስት፣
ታላቁ የታሪክ ፕሮፓጋንዳ ሰው እንዲህ ብሎ ነበር፣ “ውሸት በዋሸህ ቁጥር እና ያንን ውሸት እየደጋገምክ ባቀረብከው ጊዜ በእርግጠኝነት ሰዎች እውነት አድርገው ይወስዱታል፡፡“ ያ ታላቅ ውሸት በዓለም ታላቅ መሪ እየተደጋጋመ በሚቀርብበት ጊዜ ያ ታላቅ ውሸት ታላቅ እውነታ ሊኖረው የሚያስችል እቅም ይኖረዋለ፡፡ ሆኖም ግን “ውሸት የፈለገውን ያህል ትልቅ ቢሆንም እውነት ሊሆን አይችልም፣ ስህተት ትክክል ሊሆን አይችልም እንደዚሁም ሰይጣናዊ ስራ በታላላቆቹ እና በኃይለኞቹ በተደጋጋሚ የሚፈጸም በመሆኑ ምክንያት ወይም ደግሞ በአብዛኛው ህዝብ ተቀባይነት በማግኘቱ ብቻ በምንም ዓይነት መለኪያ ቢሆን ደግነትን ሊጎናጸፍ አይችልም፡፡“
እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 25/2014 ፕሬዚዳንት ኦባማ በኢትዮጵያ ካለው ገዥ የልዑካን ቡድን ጋር በዋሽንግተን በተገናኙ እና ንግግሮቻቸውን ባደረጉ ጊዜ በሚያሳዝን ሁኔታ ይቅርታ ሊደረግላቸው የማይችሉ መግለጫዎችን ሰጥተዋል፡፡ እንዲህ ብለዋል፣
… በዓለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትን ከሚያስመዘግቡ አገሮች መካከል አንዷ የሆነችው እና በአፍሪካ አንጸባራቂ የእድገት ስኬቶችን እና እመርታዎችን እያሳየች ካለቸው ኢትዮጵያ ውጭ ሌላ የተሻለ አገር በምሳሌነት መጥቀስ አደጋች ይሆናል፡፡
በእውነቱ በአንድ ወቅት ህዝቦቿን ለመመገብ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበረች ሀገር በአሁኑ ጊዜ ግን መጠነ ሰፊ የሆነ እድገትን ስታስመዝግብ ተመልክተናል፡፡ በአህጉሩ በግብርና ምርት የመሪነቱን ቦታ መያዝ ብቻ ሳይሆን እንዲያውም በቅርብ ጊዜ ውስጥ የግብርና ምርት ውጤቶችን ብቻ ሳይሆን ኃይልንም ወደ ውጭ አገር እንደምትልክ ይታመናል፣ ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለው እድገት ለዚህ እውን መሆን ዋና መሰረት ነው፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ፕሬዚዳንት በቀላሉ በማረጋገጥ ሊደረስበት የሚችልን እውነታ በተሳሳተ መረጃ ላይ መሰረት በማድረግ ለጉዳዩ ትኩረት ሳይሰጡ ጉዳዩን ለህዝብ ይፋ ማድረጋቸው አሳፋሪ ነገር ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ መግለጫውን ከመስጠታቸው ሶስት ወራት በፊት የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ/United States Agency for International Development እ.ኤ.አ ኦገስት 15/2014 ያቀረበው ዘገባ የፕሬዚዳንቱን መግለጫ ሙሉ በሙሉ ይቃረናል፡፡
ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ነው ቢባልም ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ ደኃ አገሮች መካከል አንዷ ሆና ቀጥላለች፡፡ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ የምግብ እጥረት እና አስከፊ የሆነ የምግብ ዋስትና እጦት በተለይም በገጠሩ ህዝብ እና አነስተኛ ይዞታ ባላቸው አርሶ አደሮች ላይ የበረታ ሆኖ ይታያል፡፡
በኢትዮጵያ ከሚገኙ እድሜያቸው ከ5 ዓመታት በታች ካሉ ልጆች መካከል በግምት 44 በመቶ የሚሆኑት ከፍተኛ ለሆነ አስከፊ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት አለባቸው ወይም ደግሞ ከእድሚያቸው ጋር ሊመጣጠን በማይችል መልኩ የቀጨጩ ናቸው፡፡ ይህ የተመጣጠነ ምግብ ያለማግኘት ችግር ሊመለስ የማይችል የክህሎት እና የአካል ብቃት ማነስን ያስከትላል፡፡ እንደ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዘገባ ከሆነ የረዥም ጊዜ አስከፊ የሆነ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት የሚያስከትለው ውጤት የኢትዮጵያን መንግስት በግምት በየዓመቱ የአጠቃላይ ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ምርትን 16.5 በመቶ ያህል ወጭ እንዲያወጣ ያስገድደዋል፡፡
የህወሐት አገዛዝ እንደሚለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በየዓመቱ በ10 በመቶ እያደገ የመጣ ከሆነ ሆኖም ግን በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ምክንያት በየዓመቱ በግምት 16.5 በመቶ ያህል ዋጋ ያለውን ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ምርት የሚያሳጣ ከሆነ ሀገሪቱ በኢኮኖሚ አደገች ማለት ይቻላልን? ይህ ሁኔታ አላይስ “በሚያሳይ መስታወት” በሌዊስ ካሮል ከተማ ከንግስቲቱ ጋር ያደረገችውን ንግግር እንዳስታውስ አደረገኝ፡፡ ንግግሩ እንዲህ የሚል ነበር፣ “መሞከር ምንም ጥቅም የለውም፣ ማንም የማይሆኑ ነገሮችን ማመን ስለማይቻል“ አለች አላይስ ንዴት በተቀላቀለበት ሁኔታ፡፡ ንግስቲቱ አላይስን እንዲህ በማለት አረመቻት፣ “ብዙም ልምድ የለሽም ለማለት እችላለሁ፡፡ እኔ በአንች የእደሜ ጣሪያ ላይ በነበርኩበት ጊዜ ሁልጊዜ በቀን ለግማሽ ሰዓት አደርገው ነበር፡፡ ለምን መሰለሽ፣ አንዳንድ ጊዜ ከቁርስ በፊት ስድስት ያህል የማይሆኑ የማይታመኑ ነገሮችን አስብ ስለነበር ነው“ አለቻት፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ስለህወሐት ለማኝ ገዥ አካል ከቁርስ በፊት ቢያንስ ስድስት የማይሆኑ የማይታመኑ ነገሮችን ማሰብ ግድ ይሆንብናል፡፡
እስከ አሁን ድረስ ለበርካታ ዓመታት መለስ እና ደቀመዝሙሮቹ ስለ ፕሮዳክቲቭ ሴፍቲ ኔት ፕሮግራም/Productive Safety Net Program (በውጭ እርዳታ የበጀት ድጋፍ አገኛከሁ በሚል ስሌት) የምርት እህል እጥረትን በማስወገድ እና የቤተሰብን እና የህብረተሰቡን ቋሚ ሀብት በመንከባከብ የምግብ እርዳታ ጥገኛ መሆንን ማቆም ይቻላል የሚል ቅስቀሳ ያደርጉ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ኦክቶበር በ2011 መለስ ለፓርቲው ታማኞች እንዲህ ብሏቸው ነበር፣ “የተትረፈረፈ ምርት ሊያስገኝ የሚያስችል የዕቀድ ዘዴ አዘጋጅተናል፣ እናም እ.ኤ.አ በ2015 ምንም ዓይነት የምግብ እርዳታ ሳያስፈልገን እራሳችንን መመገብ እንችላለን፡፡ የእርሱ የተተረፈረፈ ምርት የማምረት ዕቅድ ሊሳካ ይችል የነበረው ለም እና ዋና የምርት ማስገኛ የነበረውን በሚሊዮኖች ሄክታር የሚቆጠር ለም መሬት በረዥም ጊዜ ኪራይ እና በርካሽ ዋጋ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች እየተባሉ ለሚጠሩ እና ምርቱን እያመረቱ ወደ ውጭ እያወጡ በመሸጥ ትርፍ ከማግበስበስ ውጭ ሌላ ዓላማ ለሌላቸው የውጭ ዜጎች (መሬት ተቀራማቾች) በሊዝ መሸጥ ነበር፡፡“ የተባበሩት መንግስታት ቅርንጫፍ የሆነው እና ረኃብን ማስወገድ እና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ዓላማው አድርጎ የሚንቀሳቀሰው እንደ ትልቁ የሰብአዊ መብት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዘገባ ከሆነ እ.ኤ.አ በ2014 ለረሀብ ሰለባ የተጋለጡ 2.7 ሚሊዮን ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን/ት የምግብ እህል እርዳታ ያቀረበ ሲሆን ለ6.5 ሚሊዮን ለሚሆኑ ለምግብ እህል እጥረት እና ልዩ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አደጋ ተጋላጭ ለሆኑ የትምህርት ቤት ልጆች፣ አርሶ አደሮች፣ ከኤች አይቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎች፣ እናቶች፣ ህጻናት፣ ተረጂ ስደተኞች እና ሌሎችን ለመርዳት እቅድ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ በ2012 የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎት 3.76 ሚሊዮን ለሚሆን ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ፣ በ2011 ደግሞ ቁጥሩ በመጨመር ለ4.5 ሚሊዮን ህዝብ፣ በ2010 ደግሞ ለ5 ሚሊዮን እና በ2009 ቁጥሩ በመጨመር 6 ሚሊዮን ሲሆን በ2008 በከፍተኛ ደረጃ ከፍ በማለት ለ34 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን/ት (የአገሪቱን 40 በመቶ የሚሆነው) ለከፋ ርኃብ ተጋልጦ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ የምግብ እርዳታ የሚተዳደረው እና የሚመራው በዋናነት በሶስት የውጭ ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች (ምግብ ለተራቡ/Food for Hungry፣ የህጻናት አድን ድርጅት/Save the Children የካቶሊክ እርዳታ አገልግሎቶች/Catholic Relief Services በአንድ የሀገር ውስጥ ባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ማለትም ማህበረ ረድኤት ትግራይ/Relief Society of Tigray አማካይነት ነው፡፡ ማህበረ ረድኤት ትግራይ/ማረት እራሱን የህወሐት የሰብአዊ እርዳታ ክንፍ አድርጎ ይቆጥራል፡፡ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት “የበጎ አድራጎት እና ማህበራት አዋጅ” እየተባለ የሚጠራው አዋጅ ከወጣ በኋላ እ.ኤ.አ በ2010 የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ በኢትዮጵያ በመንቀሳቀስ ላይ የነበሩት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር ቀደም ሲል ከነበረበት ከ4,600 ወደ 1,400 ዝቅ ብሎ ነበር፡፡ አብቸኛዎቹ በሀገር ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ የተፈቀደላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የህወሐት ቅርንጫፎች ወይም ደግሞ በግል ወይም በድርጅት ከህወሐት ጋር አጋርነት የመሰረቱ እና ከድርጅቱ ጋር ዝምድና ያላቸው ብቻ ነበሩ፡፡ ህወሐት የውጭ እርዳታን የእራሱ ቅርንጫፍ በሆነው በህወሐት/ማረት አማካይነት ያስተዳድራል፡፡ በቀላል አነጋገር የህወሐት ገዥ አካል ለልማት እርዳታ በሚል ለምኖ የሚያገኘውን የልማት እርዳታ ከዓላማው ውጭ እና በእራሱ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅቱ አማካይነት በህገወጥ መንገድ የገዥውን መደብ አመራሮች እና አባላት ያበለጽጋል፡፡ ከዚህ አንጻር ሲገመገም ይህ ድርጊት የለማኝ መንግስት መገለጫ ባህሪ ነው፡፡
የለማኝ መንግስት አወዳደቅ በኢትዮጵያ፡ ኃብታም ለማኞች በመለመን ድህነትን ሊያጠፉ እና የኢኮኖሚ ልማትን ሊያመጡ ይችላሉን?
ከዚህ ቀደም ሲል አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ የአፍሪካ ለማኞች አለቃ ነው የሚል ጽሁፍ ጽፌ ነበር፡፡ ይህንን መግለጫ ከተንኮል ወይም ደግሞ ለሰውየው ክብር ካለመስጠት አልነበረም የተናገርሁት፣ ሆኖም ግን በተጫባጭመረጃላይበመመስረት እንጅ፡፡ እ.ኤ.አ ኤፕሪል 2012 መለስ ቻይና ደይሊ ለተባለው ጋዜጣ እንዲህ የሚል ቃል ሰጥቶ ነበር፣ “እውነታውእናዋናውነገርይህንንየአፍሪካውያንን/ትንየመሰብሰቢያአዳራሽእንዲገነባቻይናውያንን/ትንየጠየቁአፍሪካውያን/ትናቸው፡፡ ይህንን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለመገንባት የጠየቁት ቻይናውያን/ት አይደሉም፣ እኛ ነን የጠየቅነው፡፡ እንዲገነቡልን ጠየቅናቸው እናም ተስማሙ፣ ከዚያም አጠናቅቀው አስረከቡን፣ ይህንን የምንተችበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለንም፡፡“ ቻይናውያን/ት ህንጻውን ለመገንባት 200 ሚሊዮን ዶላር ወጭ በማድረግ የግንባታ ስራውን አጠናቅቀው የአፍሪካ ህብረት የስብሰባ አዳራሽን አስረክበዋል፡፡
በቀላል አነጋገር አፍሪካውያን/ት እራሳቸው የእራሳቸው አሻራ ያረፈበትን ህንጻ በአፍሪካውያን የህንጻ ግንባታ ገንዘብ መስራት ይችሉ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በሚለመን ወይም ደግሞ ከሰው ኪስ ከሚወጣ ገንዘብ መስራት እየተቻለ ለምን ተብሎ ከእራስ ኪስ ይውጣ? በቁስል ላይ እንጨት እንዲሉ በብር የተሰራው የወለሉ ንጣፍ እና በዋናነት የአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ዋና ዳህራ የሆነው ንጣፍ በሚያስደነግጥ ሁኔታ የተገለበጠ ግዙፍ የለማኝ ቦርጭን ይመስላል፡፡ ለዚያም ነው “የአፍሪካ ለማኞች የመሰብሰቢያ አዳራሽ” በሚል ርዕስ በንዴት ተነሳስች ትችቴን ለመጻፍ የተገደድኩት፡፡ የመለስ ልማታዊ መንግስት እና የደቀመዝሙሮቹ ትርፍ እና ኪሳራ ስሌት መሰረት ያደረገው በአንድ ዓይነት አመክንዮ በተንጠለጠለ ምርኩዝ ነው፡ በእራስ መንገድ በመለመን የኢኮኖሚ ልማት እና እድገት ማምጣት እየቻልክ ኢኮኖሚውን በእራስህ ጥረት እና ጥሪት ለማሳደግ ለምን ትደክማለህ?
የሞተ እርዳታ/Dead Aid በሚል ርዕሰ በተጻፈው መጻሐፏ ዳምቢሳ ሞዮ በእርዳታ እና በብድር ስም ከምዕራቡ እና ከሌሎች በኢንዱስትሪ ከበለጸጉት አገሮች ወደ አፍሪካ የሚላከው እና የሚመጣው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ደህነትን ለመቀነስ እና እድገትን ለማምጣት እገዛ አድርጓል፡፡ በእርዳታ እና በብድር በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር የሚገኝ ቢሆንም እንኳ በአፍሪካ የድህነት የክስተት እና ጥልቀት ደረጃ እየጨመረ የመጣ ሲሆን የኢኮኖሚ እድገት ግን እየቀነሰ መጥቷል፡፡ የአፍሪካ አገሮች (ገዥዎች) የአገር ውስጥ ኢኮኖሚዎችን ሊያበላሽ እና ለሙስና መስፋፋት ዋና የመፈልፈያ ምንጭ ሚሆነው እርዳታ ላይ በሱስ ተጠምደው በቁራኛ ተይዘዋል፡፡ ሞዮ ማንም አገር ቢሆን የውጭ እርዳታን በመቀበል ያደገ የለም የሚል ድምዳሜ ሰጥታለች፡፡ እንዲህ በማለትም ትሞግታለች፣ “እርዳታ በአፍሪካ አህጉር ምንም ዓይነት የስራ ዕድል ፈጥሮ አያውቅም፡፡“ እርዳታ በአፍሪካ የፈጠረው ነገር ቢኖር ዜጎችን ሰነፍ ማድረግ እና የአፍሪካ መሪዎች ከስልጣናቸው የማይነቃነቁ ችካሎች መሆን እና እንዲያውም የበለጠ ሰነፎች እና የማይነቃነቁ መንግስታት ይሆናሉ ብላለች፡፡ ሞዮ ሙገታዋን በመቀጠል አፍሪካውያን/ት እርዳታ እና ምጽዋት አይፈልጉም፣ ይልቁንም ኢኮኖሚው እንዲያድግ እና ድህነት እንዲቀነስ ንግድ፣ የውጭ ኢንቨስትመንቶች፣ የካፒታል ገበያዎች፣ ሬሚታንሶች፣ ማይክሮ ፋይናንስ ይፈልጋሉ፡፡ በገፍ በሚመጣ እና ማቋረጫ በሌለው መልኩ የሚገኝ የውጭ እርዳታን ሳይቀበሉ በእራሳቸው ጥረት ብቻ የተሳካ ልማትን ያመጡ አገሮች በማለት ደቡብ አፍሪካን፣ ቦትስዋናን፣ ቻይናን፣ ብራዚልን እና ህንድን በምሳሌነት ጠቅሳለች፡፡ ለሞዮ አፍሪካውያን/ት ስራ መፈለግ እና ስራ ፈጣሪ መሆን ይፈልጋሉ፣ እናም ተስፋዋን በፍጥነት በሚያድጉ አፍሪካውይን/ት ወጣቶች ላይ አድርጋለች፡፡
ሞዮ ሁሉንም እርዳታ አልተቃወመችም፡፡ የተፈጥሮ እና ሌሎች አደጋዎችን ከማስታረቅ አንጻር በመገምገም ለሰብአዊ እርዳታ ተቃውሞ የላትም፡፡ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚሰጡ እርዳታዎች በዋናነት በጣም አስቸጋሪ ለሆኑ መዋቅራዊ ችግሮች ስለሆኑ የታሰሩ እርዳታዎች ናቸው የሚል ሀሳብ አላት፡፡ የእርሷ ተቃውሞ ያነጣጠረው ከምዕራብ መንግስታት እና ከበርካታ በይነ መንግስታት ከሚመጣ እና በአፍሪካ መንግስታት እና ገዥዎች በሚባክነው በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ላይ ነው፡፡ የምዕራብ እርዳታ እና ብድሮች ሙስናን ያቀጣጥላሉ፣ የአፍሪካ መንግስታት ትምህርትን እና ጤናን ለማዳረስ እንዲሁም የህብረተሱብን ደህንነት በመጠበቅ እረገድ እና ሌሎችን ከውጭ መጥተው የእነርሱን ስራ እዲሰሩላቸው በመፍቀድ እረገድ ኃላፊነቶቻቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ ያደርጋሉ፣ አፍሪካውያን/ት ካለውጭ እርዳታ ወይም ከውጭ እርዳታ ጋር የተያያዙ ድጋፎች ሳይደረጉ በእራሳቸው ጥረት ማደግ እንዳለባቸው የማይካድ ሀቅ ነው፡፡
የውጭ እርዳታን እና የውጭ እርዳታ መር የአፍሪካ ልማትን ውሸትነት እና ታሪክ ለማስተባበል ሞዮ ከፍተኛ ክፍያ የሚያስገኙ ስራዎች በሆኑላቸው እና የውጭ እርዳታ ለአፍሪካ ልማት እንደ ተሸከርካሪ ፔንዱለም እንደሚያፋጥን እምነት ባላቸው በዓለም አቀፍ የድህነት ወትዋቾች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ትችት ቀርቦባታል፡፡ የዓለም ቢሊኒየር የሆኑት ቢል ጌት የሞዮን መጽሐፍ ሰይጣናዊነትን የሚያራምድ በማለት ፈርጀውታል፡፡ ሞዮ እንዲህ በማለት ምላሽ ሰጥታለች፣ “የእኔ መጽሐፍ ሰይጣናዊነትን ይቀሰቅሳል ማለት ወይም ደግሞ በእኔ የሙስና እሴት ስርዓት ላይ ከፍተኛ የሆነ ትችት ማቅረብ ሁለቱም አግባብነት የሌላቸው እና ክብርን የሚቀንሱ ናቸው“ ብላለች፡፡ የፈገውን ያህል መረጃ ቢቀርብ የደማውን ልብ ሊያሽር እና ሊያሳምን የሚችል ነገር ሊኖር እንደማይችል ግንዛቤ ወስዳለች፡፡ የነብይነት ባህሪን ተላብሶ የውጭ እርዳታ ድህነትን ለመቀነስ መፍትሄ ነው የሚለውን ይልቁንስ የውጭ እርዳታ ድህነትን ለመቀነስ መፍትሄ አይደለም የሚለው ግንዛቤ ሊይዝ እንደሚገባ የማሳመኛ ነጥቦቿን አቅርባለች፡፡
እ.ኤ.አ በ2004 ዩኤስ ኤአይዲ የምግብ ቀውስ አዙሪትን መስበር፡ በኢትዮጵያ ረሀብን መከላከል በሚል ርዕስ ሲዲሲኢስ/CDCS እንዲታተም አድርጓል፡፡ ያ ዘገባ እንዲህ የሚል መግለጫን አካቷል፣
ኢትዮጵያ፣ ጎረቤቶቿ እና የልማት አጋሮቿ የአሁኑን እና የወደፊቱን የኢትዮጵያ ትውልድ የጤንነት እና የኢኮኖሚ ሁኔታ በመጉዳት ወሳኝ ሚና የሚጫወቱትን ረኃብ፣ ድህነት እና በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የምግብ እጥረት ቀውስ መስበር ተስኗቸዋል፡፡ ይህንን ፈተና ስኬታማ በሆነ መልኩ ለማለፍ የኢትዮጵያን አመራር፣ ጽናት፣ እና ለለውጥ ዝግጁ መሆንን ይጠይቃል፡፡ በኢትዮጵያ ስኬታማነት ላይ መረጃ ማቅረብ አሳማኝ እና ግልጽ ነው፡፡ ሀገሪቱ ከአጠቃላይ የአፍሪካ አገራት በተለይም ደግሞ ከምስራቅ አፍሪካ አገሮች በተነጻጻነት ስትታይ ላለፉት በርካታ ዓመታት ስኬታማ ያልሆነ አፈጻጸም ስታስመዘግብ ቆይታለች፡፡ …የኢኮኖሚው ደካማ አፈጻጻም በድርቁ ምክንያት አይደለም ሆኖም ግን ይህ የመነጨው ቀጣይነት ላለው ጊዜ በቆየው በአገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ችግር ምክንያት ነው፡፡ ይህም መገለጫው በመንግስት እና በግል ዘርፉ ዝቅተኛ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት እና ኢንቨስትመነት እድገት መጣኔ መኖር፣ ዝቅተኛ የማስፈጸም አቅም እና ዝቅተኛ የሆነ የግብርና እና ግብርና ያልሆነ እድገት፡፡ በተራው ደግሞ ደካማ የኢኮኖሚ አፈጻጻም ወደ ከፋ የማህበራዊ የቀውስ ደረጃ ይመራል፣ ይህም በበኩሉ በቋፍ ያለ መንገስትን ፈጥሯል…
እ.ኤ.አ በ2014 የህወሐት ለማኝ መንግስት እና የልማት አጋሮቹ እየባሰ የመጣውን ረሀብ፣ ድህነት፣ እና በየጊዜው የሚከሰተውን የምግብ ቀውስ አዙሪት ቀለበት መስበር አልቻሉም፡፡ ያ ሊካድ የማይችል ሀቅ ነው!!!
ለማኝ መንግስት ለደኃ ሀገር?
የፈረንሳይ ፈላስፋ እና የዲፕሎማት ሰው የነበሩት ጆሴፍ ማይስትር እንዲህ ብለው ነበር፣ “እያንዳንዱ አገር ሊያገኝ የሚገባውን መንግስት ያገኛል፡፡“ ያ ማለት ደኃ ኢትዮጵያውያን/ት ለማኝ መንግስት ሊያገኙ ይገባቸዋል ማለት ነውን?
ብዙውን ጊዜ በማይስትር መርሆዎች እገረማለሁ፡፡ በትክክለኛው መንገድ ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎች ባሉበት አገር ድምጽ ሰጭዎች ማንን መምረጥ እንዳለባቸው ኃላፊነቱ እና ጥንቃቄው የወደቀው በእነርሱ ላይ ነው፡፡ ያ ሳይሆን ቀርቶ አቅም የሌለውን እና በሙስና የበከተውን ባለስልጣን ቢመርጡ የደካማ ምርጫቸውን ውጤት ተመራጩን ከተቀመጠበት የሰልጣን ወንበር ላይ እራሱን በስልጣን ቦታው ላይ ለበርካታ አስርት ዓመታት ሰይሞ ያስቀመጠ እና ስልጣኑን እና ኃይሉን በመጠቀም እና ምርጫን ሰርቆ ገዥ አካል ቢሆን ምን ሊደረግ ይችላል? እነዚህ ዜጎች እራሱን በላያቸው ላይ ኮፍሶ ስለተቀመጠ ይገባቸዋል ሊባሉ ይችላሉን?
እ.ኤ.አ ሜይ 2015 ኢትዮጵያውያን/ት የማይገባቸውን ገዥ አካል ያገኛሉ፣ እናም እንደገና እነሱ የሚፈልጉትን ዓይነት መንግስት ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ይሳናቸዋል፣ ፍጹም በሆነ መልክ ይሳናቸዋል፡፡ በሕወሐት እራሱ እና በህወሐት እራሱ መካከል ያለ ምርጫ ይቀርብላቸዋል፡፡ በመጨረሻም ቢያንስ 99.6 በመቶ ልዩነት በማግኘት ሌባውን ህወሐት ገዥ አካል ያገኛሉ፡፡
እ.ኤ.አ ጁላይ 2012 “ኢትዮጵያ በቦንድ እርዳታ ላይ” በሚል ርዕስ ተችት አቅርቤ ነበር፡፡ በዚያ ትችት ላይ ባርነት በአንድ ኃይል መያዝ ወይም ደግሞ በአንድ በውጭ ኃይል ስር ወይም ቁጥጥር ስር መዋል ማለት ነው፡፡ ህዝቦች ከፍላጎታቸው ውጭ በግዴታ በባርነት ስር እንዲሆኑ በሚገደዱበት ጊዜ በባርነት ትስስር ውስጥ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በእዳ በተያዙ ጊዜ ደግሞ በእዳ ባርነት የተያዙ ይሆናሉ፡፡ በእርዳታ ሰበብ በተያዙ ጊዜ በእርዳታ ባርነት ቁጥጥር ስር ይውላሉ ማለት ነው፡፡
አፍሪካውያን/ት እ.ኤ.አ በ196ዎቹ ነጻ ከመውጣታቸው በፊት አፍሪካውያን/ት በቅኝ ግዛት የባርነት ቀንበር ስር ነበር፡፡ የዓለም አቀፍ እርዳታ የሱስ ቁራኛ የአፍሪካን የቅኝ ግዛት ባርነት ወደ የእጅ አዙር የቅኝ ግዛት ባርነት አሸጋገረው፡፡ ኢትዮጵያውያን/ት በ21ኛው ክፍል ዘመን ሁለተኛው አስርት ዓመታት ውስጥ በእርዳታ የባርነት የአሸዋ ማጥ ውስጥ በመስመጥ እና በጣም በመስመጥ በባርነት ተይዘው ይቀራሉ ብሎ መከራከር በእውነቱ አመክኖያዊ ሊሆን ይችላልን?
ምናልባት ሸክስፒር ስለኢትዮጵያ ድሆች ስሜትን የሚያነሳሳ ሀሳብ ይኖረዋል፡፡
ዓለም የአንተ ጓደኛ አይደለችም፣ እንዲሁም የዓለም ህግ፣
ዓለም አንተን ለማበልጸግ ትዕግስት አይኖረውም፣
ስለሆነም ደኃ አትሁን፣ ከሆንክም ስበረው…
“ለማኝ ከለማኝነቱ ማምለጥ ካልቻለ እና ከልመና ባህሉ ሊመለስ በማይችል መልኩ ፊቱን ካላዞረ ለዘላለሙ ለማኝ ሆኖ ይቀራል፡፡ ብዙ በለመነ ቁጥር ተነሳሽነት፣ ድፍረት፣ ወደፊት የማለት እና በእራስ የመተማመን የለማኝነት ባህሪያትን ያጎለብታል፡፡” አለቃ ኦባፌሚ አወሎዎ
(ይቀጥላል…)
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ጥቅመት 4 ቀን 2007 ዓ.ም