Tuesday, June 2, 2015

የመንግስትና የፖሊስን መልካም ስም አጥፍተዋል የተባሉ ወጣቶች ተፈረደባቸው

June 2,2015
 ኢሳት ዜና :-አይ ኤስ የተባለው አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያውያን ላይ የወሰደውን ዘግናኝ እርምጃ ለማውገዝ በተጠራ ሰልፍ ላይ የመንግስትንና የፖሊስን ስም አጥፍተዋል የተባሉ ወጣቶች በእስርና በገንዘብ ተቀጥተዋል።

አስማማው ወልዴ፣ የማነ ወርቅነህ፣ ስንታየሁ ታሪኩ፣ ያሲን ቃሲምና ይግረማቸው አበበ ሚያዚያ 14 ቀን 2007 ዓም ጠ/.ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ጠ/ሚኒስትሩን መሳደባቸውን በክሱ ላይ ተገልጿል።

አስማማው ወልዴና የማነ ወርቅነህ በመስቀል አደባባይ አድርገው ወደ ቤተመንግስት ሲያልፉ የመንግስትን ስም የሚያጠፉ ቃሎችን በመጠቀም መሳደባቸውን ክሱ በተጨማሪ ያስረዳል።
ፍርድ ቤቱ ወጣቶቹ መንግስትን መሳደባቸውን ማረጋገጡን በመግለጽ፣ ስንታየሁ ታሪኩ፣ ያሲን ቃሲምና ይግረማቸው አበበ በ4 ዓመት ጽኑ እስራት ፣ አስማማው ወልዴና የማነህ ወርቅነህ ደግሞ 500 ብር እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል።

በተመሳሳይ ዜናም ናትናኤል ያለምዘውድ በእለቱ ሁከትና ብጥብጥ ፈጥሯል በሚል በ 3 ዓመት ከ3 ወር እስር እንዲቀጣ ፍርድ ቤት ወስኖበታል። ተመሳሳይ ክስ የተመሰረተባቸው ማቲያስ መኩሪያ፣ ብሌን መስፍን፣ ተዋቸው ዳምጤና መሳይ የተባለ ሌላ ወጣት መከላከያ ምስክር ለማቅረብ ለሰኔ 4 መቀጠራቸውን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል። እነ ማቲያስ ‹‹ሰልፉ ላይ ሀሰተኛ ወሬ በማውራት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተናገሩ በነበረበት ወቅት ወደ ፖሊስ ድንጋይ በመወርወር፣ ህዝቡን አትነሳም ወይ በማለት” ለመቀስቀስ ሞክረዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

በተመሳሳይ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተናገሩ በነበረበት ወቅት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንጋይ በመወርወር ሰልፉን አውካችኋል›› የተባሉ ሌሎች አምስት ወጣቶች ለሰኔ 4 የመከላከያ ምስክር እንዲያቀርቡ መቀጠራቸውን ጋዜጣው አክሎ ዘግቧል። አይ ኤስን ድርጊት ለማውገዝ የወጡ የአዲስ አበባ ወጣቶች በኢህአዴግ መንግስት ላይ ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ እንደነበር ይታወቃል። በኢትዮጵያ የመንግስትን ስም ማጥፋትና መንግስትን መሳደብ በህግ ያስጠይቃል።

No comments: