Thursday, January 22, 2015

50 ዓመት ሙሉ ባንድ ዱላ

January 22,2015
ዮናታን ተስፋዬ
(የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ)
ትናንትና የርዕዮትን ልደት ኢህአዴግ ሊያፈርሰው በሚቅበጠበጥበት የአንድነት ፓርቲ ቢሮ ለማክበር ተገኝተን ነበር ... (በእውነቱ ልደቷን በዛ መልኩ ለማክበር ለደከሙት አዘጋጆች ምስጋና ይገባል) ...
እናላችሁ የርዕዮትን ልደት ስናከብር ከተቀመጥኩበት ወንበር ላይ በሀሳብ ተነስቼ የኋሊት ወደ 50 ዓመታትን አዘገምኩ፡፡ ይህን ሁናቴ የፈጠረው በተለይ በርዕዮት ላይ በማእከላዊ ይፈፀም የነበረውን ግፍ ሳስብ ነበር፡፡ እርግጥ ማዕከላዊን ሳስብ ከርእዮት ሌላ ብዙዎች ባይነ ህሊናዬ ይዞራሉ - ዞን 9 ጦማርያን ደግሞ ልቤን ከነኩት ውስጥ ግንባር ቀደም ናቸው፡፡
በተለይ የዚሁ የዞን 9 ጦማርያን አባላት ስለደረሰባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዘርዘር ባለ መልኩ ለ(ኢ)ሰመጉ በላኩት ሪፖርት ላይ የሰፈረውን የመርማሪዎች የጭካኔ ተግባርና ይፈልጉት የነበረው ነገር የኋሊት ግስጋሴዬን በንጉሱ ዘመን በተፈፀመ አንድ ክስተት ላይ አሳረፈኝ፡፡
ሰሞኑን ‹‹ግዝትና ግዞት›› የተሰኘ በኦላና ዞጋ የተፃፈ መፅሃፍ እያነበብኩ ያገኘኋት ታሪክ ነበረች ማረፊያዬ፡፡ በታሪኩ በ1959 ዓ.ም በብ/ጄነራል ታደሰ ብሩ የተመራው እና በዛው ዓመት ጥቅምት 23 የታቀደውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ የተፈጠረ አንድ ክስተት ነበር፡፡ ይኸውም ህዳር 10 ቀን 1959 ዓ.ም ምሽቱን በሲኒማ አምፒር ሁለት የእጅ ቦምቦች የመፈንዳቱ ነገር ነው፡፡ በእለቱ በተከሰተው ፍንዳታም 14 ሰው ተጎድቶ እንደነበር አዲስ ዘመን በወቅቱ ዘግቦት ነበር፡፡
ይህን ክስተት ተከትሎም ‹ታአምራዊ› በሆነ ምርመራ ሁለት ሰዎች በቁጥጥር ስር ይውላሉ፡፡ መ/አለቃ ማሞ መዘምር እና አቶ ተስፋዬ ደጋጋ፡፡ እዚህ ሁለት ሰዎች እርግጥ ለጄነራል ታደሰ የቅርብ ሰዎች መሆናቸው ስለአያያዛቸው ሁናቴ የሚያስረዳን ነገር ይኖረዋል፡፡ የሆነ ሆኖ እኔን በሀሳብ ያናወዘኝ ለእናንተም ላካፍላችሁ የወደድኩት ጉዳይ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ስለተያዙበት እና ስለምርመራው ነገር ነው፡፡
እስቲ ከመፅሃፉ ይቺን ጀባ ልበላችሁ→
‹‹እንደተያዙም የምርመራው ትኩረት ምን እንደነበር ሲናገሩ፤ ‹‹ከተያዝን በኋላ የተካሄደው ምርመራ ጥቅምት 23 ቀን 1959 ዓ.ም በተደረግው ሙከራ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ቤታችን ከተፈተሸ በኋላ ግን በቤታችን ውስጥ ቦምብ መገኘቱ እና ‘የኦሮሞ ህዝብ ታሪክ’ የተሰኘው በመ/አለቃ ማሞ መዘምር የተዘጋጀ በብዙ መቶ ገፆች ላይ የተፃፈ ረቂቅ መፅሃፍ ስላገኙ ጧት ማታ በድብደባ የሚደረገው ምርመራ በዚሁ ፅሁፍ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ የቦምቡን ነገር የሚያነሱት በኛ እንደተወረወረ አድርገው የፃፉትን እድንፈርም ሲፈልጉ ብቻ ነው፡፡ በዚህ አይነት መ/አለቃ ማሞ መዘምር ብዙ ጊዜ ቦምቡን እንደወረወረ አድርገው በፃፉት ቃል ላይ እንዲፈርም ሞክረው እምቢ ባለ ቁጥር መደብደብና ማጎሳቆል ሆነ፡፡ በምርመራ ጊዜ ስለጥቅምት 23 ሙከራና ስለኦሮሞ ህዝብ ታሪክ መፅሃፍ፤ በፊርማ ጊዜ ግን ስለቦምቡ የመሆኑ ሚስጥር እየዋለ ሲያድር ግልፅ ስለሆነ እውነተኛውን ነገር ፍርድ ቤት በምንቀርብበት ጊዜ ለመግለፅ በማሰብ በፃፉት ነገር ላይ ሁሉ መፈረም ጀመርን፡፡››
ይህን ፅሁፍ ሳነብ አሁን ባለሁበት ዘመን የተፃፈ የጋዜጣ ፅሁፍ እንጂ የምር የታሪክ መፅሃፍ የማነብ ሁሉ መስሎ አልተሰማኝም ነበር፡፡ በዞን 9ጦማርያን፣ በነርዕዮት ፣ በነእስክንድር፣ አብረሃ፣ የሺዋስ . . . የሆነው ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡ አሁም በማዕከላዊ እየተገረፉ ያሉ የነፃነት ታጋዮች ይኸው በድብደባ እመኑልን በሚል ሰብብ መከራቸውን ያያሉ፡፡ ደብዳቢው ይቀየራል ዱላው ግን ያው ነው፡፡ 50 ዓመታት አለፉ - ዘመን ተቀየረ፤ ዛሬም ግን የተለየ አቋም ያለው ሰው ከዱላ እና ስቃይ የሚድንበት ስርዓት አልተፈጠረም፡፡ ‘አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ’ እንዲል ቴዲ - እውነት ነው አዲስ ገራፊ፣ አዲስ ተገራፊ - 50 ዓመት አንድ ዱላ! የዱላ ስርዓት!
እጅግ የሚያሳዝነው ግን ባለንበት መቆም እንኳን አቅቶን ወደ ኋላ የመውረዳችን ነገር ነው፡፡ የዛሬ 50 ዓመት ላይ የነበረው ስርዓት ቢያንስ ስዩመ እግዚአብሔር - ፍፁማዊ መሆኑን አውጆ ያለ መሆኑ ይወስዳቸው የነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ባወግዝም የምረዳበት አይን ግን ከዘመኑ አንፃር ነው(Order of the day)፡፡ ሌላው ጉዳይ ደግሞ በወቅቱ የዚህ አይነት ምርመራ ይደረግባቸው የነበሩት ወንድሞች ስርዓቱን ወቅቱ በሚፈቅደው(በሚያስገድደው) መልኩ በሀይል መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ መንቀሳቀሳቸው የዘውዱ ስርዓቱ ሊበቀላቸው ቢፈልግም ያሳዝን ይሆናል እንጂ አያስገርምም፡፡
በዚህ በኔው ጉደኛ ዘመን ግን እንኳን መፈንቅለ መንግስት ሊያስነሱ ‘የሚፈለገው’ ለውጥ በራሱ ጊዜ ተወስዶና በተጠና መልኩ ይሁን ብለው የሚከራከሩና ቅድሚያ ማህበረሰቡ መንቃት፣ ስለሀገሩ ተጨባጭ ሁናቴም aware መሆን አለበት ብለው ያስተማሩ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን በተመሳሳይ ወይም በከፋ መልኩ መሰቃየታቸው እጅግ የሚያስቆጭ እና ምን ያህል ኋላ ቀር ስርዓት ውስጥ እንዳለን የሚያመላክት ነው፡፡ ምርመራው በዱላ ብቻ ሳይሆን ፍፁም ከሰብዓዊነት ውጪ በሆነና የሰውን ክብር ሆን ተብሎ በማዋረድ የተሞላ መሆኑ፣ ለማሸማቀቅ በስነልቡና ጭምር የሚፈፀመው በደል በራሱ እጅግ እጅግ ያሳምማል፡፡ ያስቆጫል!
እናም ርዕዮት ዛሬ የዚህ ፈላጭ ቆራጭ፣ ዘመኑን ፈፅሞ ያልዋጀ እና ኋላ ቀር ስርዓት ሰለባ ሆና የዛሬ 50 ምናምን ዓመት አባቶቿ የሄዱበትን መንገድ እየሄደች ነው፡፡ በጨለማ ቤት እጥፍጥፍ ብለው የተኙባትን መደብ እሷም ጎኗን አሳርፋበት እያለፈች ነው፡፡ ብዙዎች የዚሁ ሰላባ ሆነዋል፤ እየሆኑም ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ጊዜው ይለወጣል እንጂ ያው አንድ አዙሪት ውስጥ ነን፡፡ ጥቂቶች ሰፊው ህዝብ ላይ የሚያዙበት አዙሪት፡፡ እፍኝ የማይሞሉት ይህን ትልቅ ሀገር ለብቻቸው ሲፈነጩበት ይኸው 50 ዓመት ያለፈው አዙሪት፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ ወደ ትግል የሚገፋ ምን ነገር እንዲመጣ እንጠብቅ? እስከመቼስ ይሆን ጥቂቶች በዚህ መልኩ ዋጋ እየከፈሉ ብዙዎቻችን ዳር ቆመን ከንፈር መጣጭ ሆንን የምንዘልቀው?
አምናለሁ የግፍ ፅዋው ይሞላል! አምናለሁ በመጨረሻም ህዝብ ይነሳል፣ ከፊት ሆኖ የሚመራ መሪም ይኖረናል! ነፃ ሆነን ተፈጥረን ተገዢ የምንሆንበት አንዳች ምክንያት የለም የምንልበት ቀን፣ ሆ ብለን የምንነሳበት ቀን ሩቅ እንደማይሆን ይሰማኛል! ነገ አዲስ ቀን ነው!
‹‹ዳገቱ ላይ አትዛል ጉልበቴ
የተራራው ጫፍ ፍቅር ናት እርስቴ
ቀላል ይሆናል - ቀላል ይሆናል!››
እናቸንፋለን!


No comments: