Saturday, January 31, 2015

አንድነት ታገደ፣ ጽ/ቤቱ ተወረረ ፣ ከዚህ በኋላስ

January 31,2015
ግርማ ካሳ
Girma Kassa's photo.
ይህ ሳምንታ በጣም አሳዛኝ ሳምንት !!!! በዚህ ምርጫ አንጻራዊ መረጋጋትና ብሄራዊ መግባባት መጥቶ ፣ የጋራ የልማት ኮሚሽን ተቋቁሞ በጋራ አባይን እንገነባላን፣ የባቡር መስመሮችን እንዘረጋለን፣ አገራችንን ከዉጭ ኃይሎች ከቻይናዎች ከመሳሰሉ ጥገኝነት እናወጣለን የሚል ተስፋ ነበረኝ።
ሆኖም በዚህ ሳምንት በኃይል፣ በጭካኔ የዚህን ፓርቲ ሕጋዊነት ሕወሃቶች ጨፍልቀዋል። በሐሳብ ማሸነፍ ሲያቅታቸው የኃይልና የጡንቻ እርምጃ ወስደዋል። በጠራራ ጸሃይና በአደባባይ ወንበዴዎችን ሽፎቶች መሆናቸውን አሳይተዋል። የ2007 ምርጫ በደምና በጭካኔ፣ ከመደረጉ ከአራት ወራት በፊት ተጠናቋል።
ፖለቲካዉን ከተቀላቀልኩ ከዘጠና ሰባት ጀምሮ በሰላም ለዉጥ ይመጣል ብዬ ስከራከር እንደነበረ ይታወቃል። ስለሰላማዊ ትግል ብዙ ጽፊያለሁ። አሁንም በሰላማዊ ትግል አምናለሁ። ወደ ጦርነት የሚሉ ወገኖቼ ስሜት ብረዳም፣ ዉሳኔያቸውን ባከብረም፣ የጦርነትን አስከፊነት ከግምት በማስገባት፣ አሁን የሰላማዊ ትግሉን ብቻ ነው የምደገፈው። (ይሄን ስል የትጥቅ ትግል እቃወማለሁ ማለት አይደለም። አለመቃወምና መደገፍ የተለያዩ ነገሮች ናቸው)
የሰላማዊ ትግልን እደግፋለሁ ስል፣ ህጋዊ የሰላማዊ ትግልን ማለቴ አይደለም። ሕጋዊ የሰላማዊ ትግል ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ ሞቷል። ተቀብሯል። የምርጫ ፓርቲ የሚባል ነገር ከአሁን በኋላ የለም። እርግጥ ነው እንደ ሰማያዊ ፓርቲ ያሉ አሉ። እነርሱም ቢሆኑ በዚህ ሁኔት ይቀጥላሉ ብዬ አላስብም። ምናልባትም በአደባባይ የምርጫ ካርዶቻቸውን ቀዳደው ሊያቃጥሉም ይችላሉ። ምርጫዉን ከተሳተፉ የሚያመጡት ለውጥም አይኖርም። ለምን አንድ አስጊ ደረጃ ሲደርሱ በጉልበት መጨፍለቃቸው አይቀሬ ነው።
ትንሽ ላብራራ። ሕጋዊ ስል አገዛዙ ያወጣዉን ሕግ በመከተል የሚደረግ ትግልን ማለቴ ነው። በፈለጉ ጊዜ ሕጋዊነትን ሕግ ወጥ በሆነ መልኩ የሚረግጡ ከሆነ፣ ሕግን ተጠቅመው ዜጎችን የሚያፍኑ ከሆነ፣ እንዴት ተደርጎ ነው ሕጋዊ ትግል የሚደረገው ?
ለሕወሃት ሕግ አልገዛም የሚል የእምቢተንኘት ሰላማዊ ዘመቻና ትግል ነው የሚቀጥለው ምእራፍ። ሰላማዊ፣ የእምቢትኝነት ዘምቻ ስል፣ ጠመንጃ ከማንሳት ዉጭ የሚደረጉ ተግብራት ሁሉ ያጠቃልላል። ሕወሃትን ስናከብረው፣ እርሱ ባወጣው ሕግ ተገዝተን ስንቀሳቀስ፣ የሚጨፈልቀን ከሆነ፣ ታዲያ መብታችንን በራሳችን መንገድ ለምን አናስከበርም ?
ይህ አይነቱ ትግል አንደኛ ጥንቃቄ ይጠይቃል። ሁለተኛ ራስን አጋልጦ መሆን የለበትም። ሶስተኛ የምናደርገውን አስቀድመን እየነገርንና ወያኔዎች እንዲጠነቀቁ እያደረግን አይደለም። አራተኛ ዲሴንትራላይዝ መሆን አለበት። አምስተኛ ዲሲፕሊን እና ተጠያቂነት መኖር አለበት። በስሜት፣ ባልተጠና መልኩ አንድ ነገር አድርገን ብዙ ሰው እንዲጎዳ ማድረግ የለብንም። አንርሳ ለሕዝብ የሚያስብ "ኢትዮጵያው ነኝ" ቢልም ኢትዮጵያው ያልሆነ፣ ከግራዚያኒ የማይተናነስ አገዛዝ ነው ያለን። ስለዚህ በምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ለዜጎቻችን መጠንቀቅ አለብን።ስድስተኛ የምናደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ከተደረጉ በኋላ ለሕዝብ እናሳወቅ። ሰባተኛ ገዢውን ፓርቲ ፍሊትሬት እናድረግና ሚስጥራቸውን እናወጣ። ስምንተኛ ሜዲያ በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ እንደ ኢሳት ያሉ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይገባል። ይጫወታሉምም።
አንድ ነገር ግን ግልጽ ላደርግ። ሕወሃት ይወድቃል። ይሄን እርግጠኛ እንሁን። በዚህ ሳምንት የወሰኑት ዉሳኔ እንደዉም የበለጠ እንድቆርጥና እንድንጨክን ነው ያደረጉን። አሁን አንዱን በር በኃይል ቢዘጉብንም፣ ሌሎች በሮች አሉ። ይህ ስርዓት ከሕዝቡ ጋር የተጣላ ስርዓት ነው። የበሰበሰ ስርዓት ነው።
ዉድ በገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ ያላችሁ ወገኖቼ፡
ነጻነት ከሰማይ አይመጣም። ነጻነትን የምናመጠው እኛው ራሳችን ነን። ሕጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱ የምርጫ ፓርቲዎች ፣ እግዚአብሄር ይባርካቸዉና፣ ተደብድበው፣ ታስረው ትልቅ ዋጋ ከፍለው መድረስ የሚችሉበት ጫፍ ላይ ደርሰዋል። ሕጋዊነታቸው ይኸው ተነጥቀዋል። ከአሁን በኋላ ተራው የእያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን ነው። በራሳችን ተደራጅተን፣ የምንቀሳቀስበት ሰዓት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት ወደፊት እመለስበታለሁ።

No comments: