ከሣምንት በፊት የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን የሚመለከት አንድ መግለጫ አውጥቷል። በዚህ መግለጫው፣ አንዳርጋቸው ጽጌ ለአንድ ዓመት ሙሉ መሠረታዊ የሆኑ የታሳሪዎች መብት እንኳን ተነፍጎት ባልታወቀ እስር ቤት የሚገኝ መሆኑ እና በእንግሊዝ ባለሥልጣናትና በቤተሰቦቻቸው እንዲጠየቅ፣ ቋሚ የቆንስላና የህግ ምክር እንዲያገኝ በተደጋጋሚ የቀረበው ጥያቄ በወያኔ አገዛዝ ውድቅ መደረጉ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው መልካም ግንኙነት የሚያሻክር መሆኑ ከወትሮው ጠንከር ባሉ ቃላት ገልጿል። አዲስ አበባ የሚገኘው የብሪታኒያ አምባሳደርም እንደዚሁ ከተለመደው ዲፕሎማሲያዊ ለስላሳነት ወጣ ያለ ያለ መግለጫ አዲስ አበባ ውስጥ ለሚታተመው ሪፓርተር ጋዜጣ ሰጥቷል። እነዚህ የሰሞኑ የእንግሊዝ መንግሥት መግለጫዎች በቀና የሚታዩ ቢሆንም የብሪታኒያ መንግሥት ማድረግ ይገባው ከነበረው እና ማድረግ ከሚችለው አንፃር ሲታይ ብዙ ይቀረዋል። የአውሮፓ ኅብረት የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ በተደጋጋሚ አንስቷል። የተባበሩት መንግሥታትም የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አያያዝ ጉዳይ ምርመራ እንዲደረግበት እንቅስቃሴ ጀምሯል። ከላይ የተዘረዘሩት ኩነቶች፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ያለሟቋረጥ የሚያደርጉት ውትወታ ውጤት እያመጣ መሆኑ ያሳያል። ይህ ጥረት ለወደፊቱም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ “አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አስልጥኖ አሰማርቷችኋል” ተብለው እንደተለመደው በሀሰት የተከሰሱ ወገኖቻችን “አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚገኙ መከላከያ ምስክር እንዲሆኑን ይታዘዝልን“ ብለው ሲጠይቁ ዳኛ ተብየው “የት እንደሚገኙ የማይታወቁ ሰውን በመከላከያ ምስክርነት ማቅረብ ይከብዳል” ብሎ ሲናገር ተደምጧል። አቶ አንዳርጋቸው ለምስክርነት ይቅረብ አይቅረብ ብይን ሊሰጥበት ቀጠሮ ተይዟል።
አርበኞች ግንቦት 7፡ የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የነፃነት አርበኛው የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የእስር አያያዝ ሁኔታ ዓለም ዓቀፍ የዲፕሎማሲ አጀንዳ በሆነበት በዚህ ወቅት በህወሓት አገዛዝ በተሾመ ዳኛ “የት እንደሚገኙ የማይታወቁ” መባሉ አሳሳቢ ጉዳይ አድርጎ ይመለከተዋል። አርበኞች ግንቦት 7፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የተከሳሾች፣ የአቃቤ ህጉና የዳኛው ምልልስ ለተባበሩት መንግሥታት፣ ለአውሮፓ ኅብረትና ለእንግሊዝ መንግሥት እንዲደርስ እንዲያደርጉም ያሳስባል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ብቻ ሳይሆን በህወሓት እስርቤቶችና ከእስር ቤቶች ውጭ ባልታውቁ ቦታዎች ታስረው እየተሰቃዩ የሚገኙ ወገኖቻችን ሁሉ እና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃ የሚወጣው፣ ኢትዮጵያዊያን በሚያደርጉት ሁለገብ ትግል ነው ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 ያምናል። ስለሆነም ራሳችንን፣ ወገኖቻችንና አገራችን ነፃ ለማውጣት የምናደርገው ትግል ማጠናከር ግዴታችን ነው። እኛ ራሳችን እንጂ ማንም ነፃነታችንን አያጎናጽፈልንም።
ይህ እንዳለ ሆኖ ግን የህወሓትን እኩይ ተግባራት በዓለም አደባባዮች ማጋለጥ፤ የህወሓት አገዛዝን ወዳጅ ማሳጣት እና በእስር ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን ደህነት የሚያሻሽሉ ተጽዕኖዎችን መፍጠር እጅግ አስፈላጊ ተግባር በመሆኑ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፣ በህወሓት እጅ ለወደቁ ወገኖቻችን ድጋፍ የሚያሰሙትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!