March 3, 2015
ከግርማ በቀለ ( የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት ሊቀመንበር)1.መግቢያ፡-
በምርጫ ቦርድ ኦፊሺያል ዌብ ሳይት ላይ ስለ ኢ/ር ይልቃል ‹‹የአመክንዮ ክሽፈት›› የተለጠፈ አንድ መግለጫ ይሁን ማብራሪያ ፣ ማስፈራሪያ ይሁን ማስተማሪያ መሆኑ ያለየለት/ወይም ለመለየት የሚስቸግር እንዲያው በጥቅሉ ቦርዱ ራሱን ከኢ/ር ይልቃል ጋር እያወዳደረ ወይም እልህ የገባ ወይም በፈጠራ ወንጀል ለመጥለፍ እየተዘጋጀ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ጽሁፍ ይነበባል፡፡ የጽሁፉን ይዘት በሚመለከት አጭር አስተያየት የምንሰጥበት ሆኖ አንባቢ ሲያነብ እነዚህን ጥያቄዎች በአዕምሮው ይዞ ቢሆን የዚህን አስተያየት መነሻ ምክንያትና አመክንዮ የመረዳት መንገዱን ያቀልለታል፡፡ እነዚህም– በይዘቱ ላይ የሚነሱ ሌሎች መከራከሪያዎች ቀርተው ጽሁፉ በምርጫ ቦርድ ኦፊሺያል ዌብ ሳይት ላይ በመውጣቱ ብቻ ፡- ለቦርዱ ይህን ግለሰብን/ያውም የፓርቲ መሪን/ በስም መስደብና መወንጀል የሀገሪቱ ህግ ይፈቅድለታልን/የሚፈቅድለት ህግ አለን ወይስ ቦርዱ ከህግ በላይ/ ‹‹የባለሥልጣን ዶሮ›› ስለሆነ ጠያቂ የለኝም በሚል ያደረገው ነው? በተሻሻለው የምርጫ ህግ አንቀጽ 5 ላይ ለቦርድ ከተቀመጠው ዓላማ /ገለልተኝነት፣ ኢ-አድሎኣዊነት…./ አይጋጭምን? አንቀጽ 7 ላይ ለቦርድ ከተቀመጠው ተግባርና ኃላፊነት የወጣ አይደለምን?
ጽሁፉ በመነሻው ላይ የቦርዱን ያላሰለሰ ጥረትና የሚጠበቀውን ውጤት ሲገልጽ ‹‹…ከእንከን የፀዳ ሆኖ እንዲጠናቀቅ…››ይላል፡፡ ጸሃፊው የቦርዱ ሰብሳቢ በአደባባይ/ሸራተን/ ‹‹እንከንየለሽ/ከእንከን የጸዳ/ ምርጫ በዓለማችን የለም ›› ያሉትንና ሁሉንም/ቢያንስ ከእኔ ኃሳብ የሚስማማ/ የሚያስማማ ንግግር አልሰማም ወይስ ምርጫ 2007 በዓለም ታይቶ የማይታወቅና በ‹‹ ጊነስ ቡክ››የሚመዘገብ ታሪክ ለማስመዝገብ ግብ ማስቀመጡን የቦርዱ ሰብሳቢ አልሰሙም ማለት ነው?
እዚህ ላይ አንድ ጉዳይ ጠቅሶ ማለፍ የጽሁፌን ዓላማ ግልጽ ያደርገዋል፡፡ ይህም ይህን የምጽፈው ለኢ/ር ይልቃል ጥብቅና ለመቆም (በራሳቸው አይደለም በአገራቸውና በዜጎች የሚፈጸመውን ህገወጥ ተግባር ለመመከት ያላቸውን ብቃት አስመስክረዋልና የእኔ ድጋፍ አያስፈልጋቸውም በሚል) አይደለም፤ ይልቁንም በአመክንዮ ስም የሚደረገውን ከአመክንዮ የወጣ ጽሁፍ ዝም ብሎ ማለፍ ተገቢ ሆኖ ስላላገኘሁበትና ከጽሁፉ በተቃራኒ በቦርዱ የተደረገውንና በቀጣይም ‹‹ሠይጣን ለማሳቻ ከመጽኃፍ ቅዱስ ይጠቅሳል›› እንዲሉ መሆኑን ለማሳየት/ለማጋለጥ ነው፤ ምን ያልተጋለጠ አለና በከንቱ ትደክማለህ ካልተባልኩ በቀር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሳይሆን ባልተናነሰ በጽሁፉ የተነሳው ጉዳይ በግልና እንደ ድርጅት መሪ በቀጥታ የሚመለከተኝ በመሆኑና በተነሳው ጉዳይ ሂደትና ውጤት በቀጥታና በተዘዋዋሪ የተጎዳሁ በመሆኑ ነው፡፡
እዚህ ላይ አንድ ጉዳይ ጠቅሶ ማለፍ የጽሁፌን ዓላማ ግልጽ ያደርገዋል፡፡ ይህም ይህን የምጽፈው ለኢ/ር ይልቃል ጥብቅና ለመቆም (በራሳቸው አይደለም በአገራቸውና በዜጎች የሚፈጸመውን ህገወጥ ተግባር ለመመከት ያላቸውን ብቃት አስመስክረዋልና የእኔ ድጋፍ አያስፈልጋቸውም በሚል) አይደለም፤ ይልቁንም በአመክንዮ ስም የሚደረገውን ከአመክንዮ የወጣ ጽሁፍ ዝም ብሎ ማለፍ ተገቢ ሆኖ ስላላገኘሁበትና ከጽሁፉ በተቃራኒ በቦርዱ የተደረገውንና በቀጣይም ‹‹ሠይጣን ለማሳቻ ከመጽኃፍ ቅዱስ ይጠቅሳል›› እንዲሉ መሆኑን ለማሳየት/ለማጋለጥ ነው፤ ምን ያልተጋለጠ አለና በከንቱ ትደክማለህ ካልተባልኩ በቀር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሳይሆን ባልተናነሰ በጽሁፉ የተነሳው ጉዳይ በግልና እንደ ድርጅት መሪ በቀጥታ የሚመለከተኝ በመሆኑና በተነሳው ጉዳይ ሂደትና ውጤት በቀጥታና በተዘዋዋሪ የተጎዳሁ በመሆኑ ነው፡፡
የጥያቄዎችን መልስና ስለ ጽሁፉ ዓላማ ያነሳሁትን በዚሁ ልግታና በ‹‹ምርጫ ቦርድ›› ጽሁፍ ላይ ወደ ተነሱት የአመክንዮ ክሽፈት ነጥቦች እናምራ፡፡
2. የተነሱ የአመክንዮ ክሽፈት ነጥቦች፤
2.1. ክሹፍ አመክንዮ 1 ላይ–
ይህ ላይ የቀረበውን የጽሁፉን ይዘት ስናጠቃል ‹‹ህግ መቃወም አይችልም›› የሚል አንድምታ እንዳለው እንመለከታለን፡፡ የተደራጁ ዜጎቸ ቀርቶ አንድ ዜጋ እንኳ በህጋዊና ሰላማዊ መንገድ አንድን አዋጅና ህግ አይደለም፣ህገ መንግስቱን መቃወም፣ የሚቃወመውንም ለመቀየር/እንዲቀየር መታገል ይችላል፤ ይህ ህገ መንግስታዊ መብት ነው፡፡ ህገ መንግስቱም ሆነ አዋጆች/ህጎች የፈጣሪ ቃል አይደሉምና ሊተቹ አይደለም ሊቀየሩ እንደሚችሉ ስለሚታወቅ ህገ መንግስቱን የማሻሻያ ስርዓት በህገ መንግስቱ በግልጽ ሰፍሯል፡፡ የኢትዮጵያ የምርጫ ህግና የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጆች መሻሻላቸው ወደፊትም ሊሻሻሉ የሚችሉ መሆናቸው የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው፤ በመሆኑም ጉድለትን መተቸት፣መቃወም፣ የማይቻልም ወንጀልም አይደለምና ባለ አመክንዮው ጸሃፊ/ቦርዱ ይህንን ከየት እንዳመጣው አልገለጸምና አመክንዮኣዊነቱን ባዶ ያስቀረዋል፡፡
ሌላው በጽሁፉ የተነሳው ጉዳይ የኢ/ር ይልቃልን ኃሳብ ‹‹…የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ህጋዊ ሰውነት የሚገዳደር…›› በማለት የቀረበው ነው፡፡ ይህ ኢንጂነሩ ‹‹ህጋዊ ሰውነታቸውን ለተገዳደሩኣቸው›› ፓርቲዎች በመቆርቆር የተነሳ ኃሳብ ከሆነ በአንድ በኩል እውነትም ቦርዱ ለፓርቲዎች ዋስ ጠበቃ እየሆነ ነውና መጪው ጊዜ ከቦርዱ ጋር ለፓርቲዎች ‹‹ብሩህ›› መሆኑን ያሳያልና እሰዬው እንበል፤ በሌላ በኩል እንዲያውም በተቃራኒው ህጋዊ ሰውነታቸውን ኢንጂነሩ ለተገዳደሩባቸውና ቦርዱ ዋስ ጠበቃ ለሚሆንላቸው ፓርቲዎች ‹‹መብታቸውን የማያውቁ፣የራሳቸውን መብት ማስጠበቅ የማይችሉ፣ ደካሞች፣…›› የሚል መልዕክት የሚያስተላልፍና ለመብታችሁ እድንቆምላችሁና መጪው ጊዜ ከእኔ ጋር ብሩህ እንዲሆንላችሁ ከጎኔ ተሰለፉ ጥሪ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አመክንዮውን የበለጠ ባዶ የሚያስቀረው ጸሃፊው/ቦርዱ ስለፓርቲዎች ህጋዊ ሰውነት የተቆረቆረው በምርጫ አዋጁ የተቀመጠለትን ተግባር ተከትሎ ከኦሕዲኅና 9 ፓርቲዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች መልስ ባልሰጠበት መሆኑ ነው፡፡
ግልጽ ላድርገው–ከቦርዱ ዓላማ፣አሰራርና እየፈጸመ ያለውን ከታች በ2.1.3. ስር በተጠቀሰው የምርጫ ህግ አንቀጽ 12 የቦርድ አባላት ስነ ምግባር ቁጥር 1፣2፣5፣እና አንቀጽ 38 መሰረት እንመልከተው፡- ከላይ ጸሃፊው/ቦርዱ ለፓርቲዎች ህጋዊ ሰውነት ተቆርቋሪነቱን የገለጸው በምን ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ነው ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ የሚከተለው ነው፡፡
2.1.1. ቦርዱ ኦሕዲኅ አመራሩና አባላቱ በምርጫ 2007 በ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ምልክት›› እንዲወዳደሩ የፈቀደበትን ምክንያትና መነሻ የሚያብራራና ይህም በቦርዱ የጸደቀ መሆኑን የሚያሳይ ደብዳቤ (በቁጥር-ኦህዲኅ/0017/07፣በቀን ጥር 30/07 ) በቦርዱ ሳይታይ በጽ/ቤቱ ምክትል ኃላፊ ተጽፎ ሲሰራጭ ለኦህዲኅ ያልደረሰ ህገወጥ የጓሮ በር መልስ በሰጡበት፣ ይህንንም በመቃወም ለቦርዱ በድጋሚ ለቀረበው ይህ የም/ኃላፊው ደብዳቤ እንዲሻር በኦሕዲኀ የተጻፈ ደብዳቤ (በቁጥር-ኦህዲኅ/0017/07፣በቀን የካቲት 10/07 ) የውኃ ሽታ ሆኖ በቀረበትና በዚህም ሰማያዊ ፓርቲ ያቀረባቸው የኦሕዲኅ አመራርና አባላት አቤቱታ ሳይቀርብባቸው በምርጫ የጊዜ ሰሌዳው መሰረት የዕጩ ምዝገባው በ04/06/07 ከተጠናቀቀ ሳምንት በኋላ በ11/04/07 በስልክ ትዕዛዝሙሉ በሙሉ ከዕጩነት በተሰረዙበት፤
2.1.2. በተመሳሳይ የቦርዱ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ የ9ኙ ፓርቲዎችን ህጋዊ ሰውነት በመካድ በ‹‹ትብብር ለዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ/ትብብር›› በቅንጅት ለመስራት ያቀረቡትን ጥያቄ (በመንገድ ቁጥር በቀን 21/02/ 2007 ዓ.ም. ወጪ የሆነ ደብዳቤ) ከህግ አግባብ ውጪ አፍነው ለማስቀረት በተደጋጋሚ የሄዱበትን አሰራር በመቃወም ለቦርዱ ሰብሳቢ ላቀረቡት ደብዳቤ መልስ ባለመስጠቱ የ‹‹ትብብሩ››አባላት የጋራ እንቅስቃሴኣቸውን ለማቆም በተገደደቡት፤
2.1.3. በተቃራኒው ሌሎች 9ኙ ፓርቲዎች (አሁን በጋራ በመስራት ላይ ያሉት- የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር) ደግሞ የጋራ ተግባራትን በጋራ ለመስራት ‹‹የስነ ምግባር ህጉ አንቀጽ 3 (የተፈጻሚነት ወሰን) ቁጥር 1 ( ይህ አዋጅ- በማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ፣የግል ዕጩ ተወዳዳሪ፣እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅንጅት፣ ግንባር፣ ጥምረት፣ ወይም ንቅናቄ…ተፈጻሚ ይሆናል)፣አንቀጽ 38 ላይ (‹‹ማንኛውም ህግ ወይም አሰራር በዚህ አዋጅ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡››) በሚልበት በህጋዊ ሰውነታቸው በሚመነጨው መብታቸው ላይ ቆመው በጋራ ለመስራት (ጥምረት ይሁን ንቅናቄ ዕውቅና/ሰርቲፊኬት ቦርዱን የሚጠየቁበት ህግ በሌለበት) የተስማሙ፣ ነገር ግን ለዚህ የቦርዱን ዕውቅና ያልጠየቁ (ቦርዱ ዕውቅና/ሰርቲፊኬት የሚጠየቀው በቅንጅት፣ በግንባር ለመስራት ወይም ለመዋሃድ ብቻ ሆኖ ባለበት) ለ9ኙ ፓርቲዎች ዕውቅና/ ሰርቲፊኬት አልሰጠሁም በሚል ‹‹…ሰማያዊ አስተባብራለሁ…›› እያለ… በሚወነጅልበትና የድርጅቶችን ህልውና ከተቋቋመበት ዓላማ በተቃራኒ ራሱ እየካደ፣ ይህ ኃላፊነትና ተግባር ከማይጠበቅበት እንዲያውም የራሱን ዓላማና ፓርቲ ከሌላው የሚሻልበትን/የሚበልጥበትን ማሳየት የማያስጠይቀው ወገን /ሰማያዊ/ ላይ ጣት መጠንቆል፤ አመክንያኣዊ ነውን?
ከላይ እንዳልነው መልሶቹንና ፍርዱን ለአንባቢ፣ ለኢትዮጵያዊያን በመተው፣ይህንንም መዝግበን ወደ ቀጣዩ የጸሃፊው/ቦርዱ ‹‹የአመክንዮ ክሽፈት›› ትንታኔ እንለፍ፡፡
2.2. ክሹፍ አመክንዮ 2 ላይ –
ይህም ከላይ ከተጠቀሰው ብዙም የተለየ አይደለም፤ ህጉን ‹‹አይነኬና አይጠየቄ›› ከማድረግ ባለፈ በዓላማ ደረጃም አነሳሱ ባዶ ውንጀላ በማቅረብ የማስፈራሪያ ፣ሲያልፍም በመሰረተ ቢስ ክስ ለመጥለፍ እየተደረገ ያለውን ዝግጅት አብሪ ጥይት ነው ማለት ይቻላል፡፡ እስቲ ማሳያዎቹን ጠቅለል አድርገን እንመልከት፡፡
በዚህ ክፍል የቀረበውን የጽሁፉን ይዘት የ‹‹ከስነ ምግባር ደንቡ ጋር የሚያላትማቸዉ ስለመሆኑ ልብ ያሉት አይመስሉም ወይም የህግ ጥሰቱን የስራቸዉ አንድ አካል አድርገዉታል ማለት ነዉ፡፡›› በማለት የተገለጸው ያጠቃልለዋል ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ ጸሃፊው/ቦርዱ ‹‹አይነኬና አይጠየቄ›› ባደረጓቸው ህጎች (የመተቸትና መጠየቅ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ ተቀብለናቸው) አንጻር እንመልከት፡፡
በዚህ ክፍል የቀረበውን የጽሁፉን ይዘት የ‹‹ከስነ ምግባር ደንቡ ጋር የሚያላትማቸዉ ስለመሆኑ ልብ ያሉት አይመስሉም ወይም የህግ ጥሰቱን የስራቸዉ አንድ አካል አድርገዉታል ማለት ነዉ፡፡›› በማለት የተገለጸው ያጠቃልለዋል ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ ጸሃፊው/ቦርዱ ‹‹አይነኬና አይጠየቄ›› ባደረጓቸው ህጎች (የመተቸትና መጠየቅ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ ተቀብለናቸው) አንጻር እንመልከት፡፡
ይህን እስኪ የምርጫ ህግ አንቀጽ 12 (የቦርድ አባላት ስነ ምግባር) ቁጥር 1.(በነጻነት፣ ገለልተኝነትና ቅን ልቡና ማገልገል)፣ ቁ.2 (በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የቱንም ወገን ያለመቃወም ወይም ያለመደገፍ)፣ቁ.5 (በማንኛውም ሁኔታ የቦርዱን ወይም የአባሉን ተኣማኒነት፣ገለልተኝነትና ነጻነት ከሚጎዳ ወይም ከሚያጎድፍ ማንኛውም ተግባር መቆጠብ)፣ አለበት ከሚለው አንጻር እንዳሰው ፡፡
2.2.1. ከዚህ አንጻር የሥነ ምግባር ደንቡ ዝግጅት የቀረቡት (በሂደት/አዘገጃጀት/ እና ይዘት/) ጥያቄዎች ሳይመለሱ የጸደቀን የስነ ምግባር ህግን፣ያውም በዝግጅቱ ወቅት ያልነበረ ፓርቲን መቃወም አይችልም የሚል ክስ ማቅረብ አመክንዮ መነሻ ከየት የመጣ ነው/ወይም አመክንዮኣዊ ነውን?
2.2.2. የምርጫ ህጉስ ቢሆን በፓርቲዎች ዕጣ አወጣጥስ የዕጩዎች በፓርቲ አመራር ያላቸውን ደረጃ፣ የፓርቲው አደረጃጀት/ብሄራዊ ወይም ክልላዊ/፣ ዕጩዎችን ያቀረቡ ፓርቲዎች በምርጫው ያላቸው ተሳትፎ/ያቀረቡት ዕጩዎች ብዛት/፣ የፓርቲዎች በአገራዊ ፖለቲካው ያላቸው እንቅስቃሴ/ተሳትፎ-የቢሮ ብዛት፣ለህዝብ ተደራሽነት/… ባለማካተቱ ጉድለት አለበት ማለት አይቻልም የሚል አመክንዮስ ከየት የመጣ ነው/ወይም አመክንዮኣዊ ነውን?
2.2.3. ለመሆኑ ቦርዱ ራሱ የሥነ ምግባር ህጉን፣ያውቀዋል፣ እየተገበረ ነውን? ለዚህ ጥቄ መነሻ ማሳያዎች -
የምርጫ ህጉ አንቀጽ 8 (የቦርዱ ሰብሳቢ ስልጣንና ተግባር) ቁጥር 4 ላይ ‹‹የፖለቲካ ድርጅቶችን የጋራ መድረክ በሰብሳቢነት ይመራል›› ይላል፡፡ የሥነ ምግባር ህጉ ደግሞ የጋራ መድረክ ሰብሳቢ ማን እንደሆነ አንድም ቦታ አይገልጽም፣ይህን በሁለት አዋጆች መካከል መናበብ በሌለበት ሁኔታ ባልተጻፈ ህግ በዘፈቀደ የሚከወነውን አፈጻጸም አይነኬ ማድረግ ነውን አመክንያዊነት?
ቦርዱስ በምርጫ ህጉ በአንቀጽ 7 ቁጥር 9 ላይ (‹‹የፖለቲካ ድርጅቶችን የጋራ መድረክ የማደራጀትና ማስተባበር) የተጣለበትን ኃላፊነት እየተወጣ ነውን?
2.2.4. የስነ ምግባር ደንቡን ከኢህአዴግ ጋር ያረቀቀው/ያዘጋጀው…መኢአድ በጋራ ምክር ቤት ተሳትፎ ማድረግ ባቆመበት/እምነት ባጣበት/ ህጉ ሲወጣ ላልነበረው ለሰማያዊ ፓርቲ መሪ አይነኬ ማድረግ ነውን አመክንያዊነት?
የሚሉትን ስንመለከት ጸሃፊው/ቦርዱ ከላይ በምርጫ ህጉ ቀ 12 በቦርዱ ላይ የተጣለበትን ሥነ ምግባር የተከተለ አሰራር ባልተከተለበት፣ነጻነቱ፣ገለልተኝነቱ… ተኣማኒነቱ ከጥያቄ ውስጥ ወድቆ ባለበት፣በአዋጅ የተሰጠውን ተግባር ባላከናወነበት…በሌላው ያውም በግለሰብ ላይ ይህን ዓይነት ጽሁፍ መጻፍና በዌብሳይቱ ላይ መለጠፍ እንደምን ህጋዊና ምክንያታዊ ያደርገዋል፣በምን የሞራል መሰረት በአመክንዮ ለመከራከር ያስችለዋል? መልሱንና ፍርዱን ለአንባቢና ለባለቤቱ መራጭ ህዝብ እንተወውና ወደ ቀጣዩ እንሸጋገር፡፡
2.3. ክሹፍ አመክንዮ 3 ላይ፡-
በዚህ ክፍል ውስጥ በጽኁፉ ‹‹…. 23 ተጠቋሚ እጩዎችን አቅርበዋል፡፡ይሁንና ከእነዚህ መካከል ሁለቱ የአንድነትና የኦሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኀብረት አመራሮች በመሆናቸዉና ህገ ወጥ በሆነ መንገድ በሰማያዊ ፓርቲ ጥላ ስር (በ9 ኙ ፓርቲዎች ትብብር ስም )ለመወዳደር የተመዘገቡ በመሆናቸዉ እንዲሰረዙ ሆኗል፡፡ ›› የሚለውን እናገኛለን፡፡
ይህ ደግሞ የባሰበትና ጆሮ ደፍኖ/ይዞ በህግ አምላክ እያሉ የሚያስጮህ በቅጥፈትና ክህደት የተሞላ ነው፣ እንዴት የሚለውን አብረን እንመልከት፤
2.3.1. ጽሁፉ ‹‹….(በ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ስም) በመመዝገባቸው እንዲሰረዙ ሆኗል›› ያለው በ9ኙ ትብብር ስም የቀረበ ዕጩ በመላ አገሪቱ ባሉት ምርጫ ክልሎች ቢታሰስ በማይገኝበት በመሆኑ ትዝብት ላይ የሚጥል ነው፤/በዚህ ላይ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ኢትዮምህዳር የካቲት 18/07 ቅጽ2 ቁጥር 96 እትም እና Fortune Vol 15 No 773, Feb 22/15/ ይመልከቱ፤
2.3.2. ቦርዱ ‹‹…አመራሮች በመሆናቸዉና ህገ ወጥ በሆነ መንገድ በሰማያዊ ፓርቲ ጥላ ስር…›› ይላል በሌላ በኩል የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር አባል የሆነው መኢዴፓ ሊቀመንበርና የትብብሩ የፋይናንስ ኃላፊ አቶ ኑሪ ሙዲስር ደግሞ የሰማያዊ ፓርቲ ዕጩ ሆነው ተመዝግበዋል፡፡ ይህ የዕጩ ምዝገባው በህግ ሳይሆን በዘፈቀደና በምርጫ ቦርድ በጎ ፈቃድ ወይም በድርብ መመዘኛ/Double Standard/ የተመራ መሆኑን በግልጽ ያሳያል፡፡
2.3.3. ይህን በሚመለከት ኦህዲኅ ከላይ በ2.1.1. ሥር የተገለጹትን ሁለት ደብዳቤዎች አቅርቦ መልስ ባላገኘበት በጓሮ በር ትዕዛዝ አመራሩና አባላቱ ከዕጩ ምዝገባ ቀን በኋላ በስልክ በተሰጠ ትዕዛዝ በተሰረዙበት፤ እውነት ውስጥ የሆነው ነው አመክኒዮኣዊነት?
እንግዲህ በዚህ መልክ የተሰራውን/ጸሃፊው/ ወይም የሰራውን /ቦርዱ/ ነው ክሹፍ አመክንዮ እና ህገወጥ እየተባለ የተፈረጀው፡፡ ፍርዱን ለአንባቢ ትተን የያዝነውን ጉዳይ እናጠቃለው፡፡
3. ማጠቃለያ፡-
3.1. ውሉ የጠፋበት/ የቦርድ መግለጫ ይሁን የቦርድ ሠራተኛ አስተያየት/ የክስ ማቀበያና ፈሪ ከተገኘም ማስፈራሪያ ጽሁፍ መሆኑ፤ ይህን አቶ ወንድሙ በአየር ሰዓት ድልደላ ላይ ሰማያዊ ላቀረበውን ጥያቄና ተቃውሞ ምላሽ ከዚህ ቀደም የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ አስታውሰው ‹‹በቀጣይ ከእንዲህ ዓይነቱ ተግባር የማይቆጠብ ከሆነ ቦርዱ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል›› ካሉት ጋር ሲታይ፤
3.2. በጽሁፉ ማብቂያ ላይ ‹‹እንደ አጠቃላይ ኢ/ር ይልቃል በምርጫዉ ሂደት ላይ ጭቃ ይለጥፉ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ መድረኮችን ረግጦ መዉጣት፣ በኢ-ተገቢ ዘለፋ መጀገን እና የሀገሪቱን የምርጫና የስነምግባር ደንቡን የሚገዳደር ተግባር በመፈጸም መጀገን የሚያስከፍለዉን ዋጋ ካለማወቅ ወይም ለማወቅ ካለመሻት መነሾ ባደረገ መልኩ እየገፉበት ነዉ፡፡›› የሚለውን ስንመለከት፤
3.3. ከላይ የቀረቡትን ጥያቄዎችና በተጨባጭ መረጃዎች የተደገፉ ማሳያዎችን እና የተጠቀሱትን የህግ አንቀጾች ከጽሁፉ ይዘት ጋር ስናገናዝብ፤
የጽሁፉ መልዕክትና ይዘት ወገናዊነት ግልጽ መሆኑ ቀርቶ ይህ ዓይነቱ በአንድ የፖለቲካ አመራር ላይ ያነጣጠረ ጽሁፍ በቦርዱ ዌብሳይት መውጣቱ በራሱ የቦርዱን ገለልተኝነት አጠያያቂ ከማድረግ አልፎ ህገወጥና የሚስጠይቅ ያደርገዋል ወይም ያስጠይቀው ‹‹ነበር›› ብሎ ማጠቃለል ይቻላል፡፡
ሆኖም ምርጫ ቦርድ የሚመካበት አለውና ድርጊቱም ‹‹እስመ አልቦ ነገር ዘይሳነው ለምርጫ ቦርድ›› እየሆነ ነውና አይደለም ኢ/ር ይልቃልን፣ ፓርቲንም ከሁለት ወንጀለኞች በህግበተሰጠው መብትና ኃላፊነት መሰረት በመዳኘት ሳይሆን በራሱ መንገድ የተሻለውን በመምረጥ የፈለገውን ማድረግ እንደሚችል አሳይቶናልና በአመክኒዮኣዊ ክርክር ከመድከም ወደ አቋሙ ቢገባ መልካም ይሆናል ፣ያሊያ ጽሁፉ ጠረን ‹‹ አያ ጅቦ ሳታመካኝ ብላኝ›› የሚያስብል ነው፡፡
እንዲያው በማብቂያው ላይ ቢሆንም ለጽሁፌ ማዋዣ እንዲሆን ጠርጥረን ብናበቃስ–ይሄው ጽሁፍ በፋና ብሮድካስት ዌብሳይትም መለጠፉን፣እና ከዚህ በፊት በፋና ም/ሥራአስኪያጅና ኢ/ር ይልቃል ‹‹ሞጋች›› ፕሮግራም ላይ የነበረውንና ከፋና ‹፣ጠፍቶበት/በስህተት ሳይቀዳ ቀርቶ›› በኢሳት በሰማነው ክርክር ያስመዘገቡትን ‹‹ማርክ/ነጥብ›› ለመዘኑ ሰዎች ምርጫ ቦርድና ፋና ሬዲዮ እንደማይጠየቀው የኢህአዴግና አጋሮቹ ግንኙነት የ ‹‹አጋርነት›› ውል ተፈራረሙ ብሎ መጠርጠር በምርጫ ህጉም ሆነ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ያስጠይቅ ይሆን?
በመጨረሻም ማሳሰቢያ
የቦርዱ ሰብሳቢ እንዳሉት እንከን የለሽ ምርጫ ለማድረግ እንኳን እኛ እነርሱም አልደረሱምና በእኛ አገርም እየሆነ ያለውን ሁላችንም- እኛም፣ ቦርዱም፣ መንግስትም/ገዢው ፓርቲም፣ ህዝቡም ያውቀዋልና በመስተዋት ቤት ውስጥ ያለ ድንጋይ ለመወርወር ቀዳሚ መሆን ተገቢ አይደለም፤ ከነዚህ ሁሉ በላይ ህዝብ ያውቃል፣ይታዘባል፤ በጊዜውም ይፈርዳል፡፡ ማንም ምን ይበልም ለማድረግ ይፈልግም፣ያድርግም– የእኛ የማይናወጥ አቋም – ትግላችን ህገ መንግስታዊ መብታችን ላይ የተመሰረተ፣በሰላማዊና ህጋዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ የሚጓዝ በመሆኑ ማንም ዜጋ ከህግ ባሻገር የኅሊና ፣ከሥልጣን በላይ የዜግነት ግዴታና የታሪክ ተጠያቂነት አለበት፤ ይህን የዘላቂ ሰላምና ልማት ወደ ዲሞክራሲ ሥርዓት የሚያደርስ የትብብሩን አካታችና ባለው ላይ መገንባት ምርጫው ያደረገ አካሄድ የመጥለፍ ሳይሆን የማበረታታት የሞራል ግዴታ እንዳለበት ማስተዋል ለሁላችንም- ለዜጎችም ለአገራችንም- ጠቃሚ መሆኑን በማሳሰብ አበቃለሁ፡፡
አንድ ሙስሊም ወዳጄ የነገረኝን ውስጤ የቀረ የታላቅ ኃይማኖት መሪ አስተምህሮ ለመዝጊያ ልጠቀመው ‹‹መልካምነት የተወደደ/በጣም ጥሩ/ ነው፤ መልካም ሆኖ መልካም ማድረግ ደግሞ የበለጠ የተወደደ/እጅግ በጣም ጥሩ/ ነው››፡፡ ለዚህ እንድበቃ ማስተዋሉን ተችረን በቸር አሰንብቶን በቸር ያገናኘን በሚል መልካም ምኞት መለያየት መልካም ነው፡፡ እስከዚያው መልካም ሆነን መልካም መልካሙን እያሰብንና እየሰራን እንድንቆይ ፈቃዱ ይሁን፡፡