Sep 7,2014
(ኢ.ኤም.ኤፍ) የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባል የሆነችው ወይንሸት ሞላ፤ የሙስሊሙን እንቅስቃሴ ለመከታተል አንዋር መስጊድ ሄዳ በነበረበት ወቅት በደህንነት ታፍና፤ በአሰቃቂ ሁኔታ እየተደበደበች መወሰዷን በድረ ገጻችን ላይ ገልጸን ነበር። ከዚያም ሰውነቷ ተጎድቶ እና ደክሞ ፍርድ ቤት ትመላለስ የነበረ መሆኑን በመጨረሻም በዋስ መፈታቷን በወቅቱ ገልጸናል። ከ”ነገረ ኢትዮጵያ” መጽሄት ጋር ያደረገችው ቃለ ምልልስ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታተም በመደረጉ ምክንያት አዘጋጆቹ ቃለ ምልልሱን በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ ለቀውታል። እኛም ይህንኑ ቃለ ምልልስ ለናንተ ልናጋራቹህ ወደድን። ከዚህ በታች አቅርበነዋል።
ወ/ት ወይንሸት ሞላ የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ስትሆን ፓርቲው በሚያደርጋቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል እንደሆነች ይነገርላታል፡፡ ወጣቷ ፖለቲከኛ ወይንሸት ሞላ ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም ለዓመታት የዘለቀው የሙስሊሙ ማህበረሰብ የመብት ጥያቄ አካል የሆነውንና በዕለቱ በአኑዋር መስጊድ የተደረገውን የተቃውሞ ሁኔታ ለማየት በቦታው ተገኝታ እንደነበር ትናገራለች፡፡ ወ/ት ወይንሸት በዕለቱ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ ለ29 ቀናት በእስር ቆይታ በዋስ ተለቅቃለች፤ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ስለጉዳዩ አነጋግሯታል፡፡
ነገረ ኢትዮጵያ፡- አንዋር መስጊድ አካባቢ ተይዘሽ ከታሰርሽ በኋላ ለምን መስጊድ ሄደች የሚሉ አካላት ነበሩ፡፡ ለመሆኑ እንዴትና ለምን ነበር የሄድሽው?
ወይንሸት፡- የሄድኩበት ምክንያት ግልጽ ነው፡፡ በእርግጥ እኔ የሄድኩበትን ብቻ ሳይሆን በተለይ በገዥው ፓርቲ በኩል የሙስሊሙን ማህበረሰብ እንቅስቃሴም ባልሆነ መንገድ ትርጉም እየተሰጠው ነው የሚገኘው፡፡ የሙስሊሙን እንቅስቃሴ እስላማዊ መንግስት ለመመስረት የሚደረግ እንደሆነ አድርገው በተሳሳተ መንገድ ያቀርቡታል፡፡ የእኔንም ከዚህ በተለየ ሁኔታ አይደለም ያቀረቡት፡፡ ምን አልባት የእኔ ይለያል ከተባለ ፖለቲከኛ በመሆኔ ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ ሆኖም እኔም የሄድኩት እንቅስቃሴውን ለማየት ነው፡፡ ይህን ለማየት የሄድኩበት ምክንያት አንደኛ ገዥው ፓርቲ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ሰላማዊ አይደለም ብሎ ስለሚፈርጅ ነው፡፡ ሙስሊሞች ደግሞ እንቅስቃሴው ሰላማዊ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ለህዝብ እንደቆመ እንደ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባልነቴም ሆነ መሪ ለመሆን እንደምትፈልግ አንዲት ሴት ቦታው ላይ ተገኝቼ ነገሮችን ማረጋገጥ ስለነበረብኝ ቦታው ላይ ተገኝቻለሁ፡፡
ነገረ ኢትዮጵያ፡- የተያዝሽበት ሁኔታስ ምን ይመስላል?
ወይንሸት፡- መስጊዱ ፊት ለፊት ባለ አንድ ህንጻ ላይ ሆኜ እንቅስቃሴውን ስከታተል ነው የያዙኝ፡፡ በተለይ ከያዙኝ በኋላ የወሰዱት እርምጃ በጣም ዘግናኝ ነበር፡፡ በድብደባ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰውብኛል፡፡ አጸያፊ የሆነ ስድብ ይሳደቡ ነበር፡፡ መንግስት ነኝ ከሚል አካል የመጣ ሰው እንዲህ ይሳደባል ብሎ ለማመን እስኪከብድ ድረስ ነው የሚሳደቡት፡፡ ለሴት ልጅ ምንም አይነት ክብር የላቸውም፡፡ ሲሳደቡ ኢትዮጵያዊ አይመስሉም ነበር፡፡ የህዝቡን ስነ ልቦና ለመስለብም ይሁን ለሌላ ጉዳይ ግፉ ምን ያህል ጫፍ እንደደረሰ የሚያሳይ ነበር፡፡ ድብደባ የፈጸሙብኝ ደህንነቶች ተደብቀውና እኔን ከተያዙት ሌሎች ሰዎች ለይተው ነበር የሚደበድቡኝ፡፡ እንዳይታዩ መስገጃ ተከናንበው ነበር ይደበድቡኝ የነበረው፡፡ ከሌላው ለይተው ሰማያዊ ፓርቲ መጥቶ ያድንሽ እያሉ ነበር ከበው የደበደቡኝ፡፡ ይህ ፍርሃታቸውን ነው የሚያሳየው፡፡ በሚደበድቡኝ ወቅት ሞባይሌን ይጎረጉሩ ነበር፡፡ በድንገት የአባይ ግድብን ፎቶ አግኝተውት ‹‹ደግሞ አባይ ግድብንም ልታፈነዱ ነው?›› ይሉኝ ነበር፡፡ ሌላስ ተልዕኮሽ ምንድን ነው እያሉ ከፍተኛ ደብደባ አድርሰውብኛል፡፡ የመጣው ሁሉ የሌለ ጥያቄ እየጠየቀ ይሳደባል፡፡ ይደባደባል፡፡
በምርመራ ወቅት መረዳት እንደቻልኩትም እኔን ሙስሊሞቹ የደበደቡኝ ለማስመሰል ነው የፈለጉት፡፡ በደህንነት አካላት ተደበደበች የሚሉትን ነገር ማመን አልፈለጉም፡፡ በዱላና አናቴን ደግሞ በእርግጫ ከደበደቡኝ በኋላ ጥለውኝ ሄዱ፡፡ ደም በጣም ይፈሰኝ ነበር፡፡ ፊቴ ሁሉ በደም ታጥቦ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ ወደ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱኝ፡፡ እዛ ፖሊስ ጣቢያ ቤቱ መቆሚያ መቀመጫ እስኪያጣ ድረስ በተጎጅዎች ተሞልቷል፡፡ እኔ ህክምና ያስፈልገኛል ስላቸው አንዲት ነርስ መጥታ አየችኝና ‹‹ከአቅሜ በላይ ነው ቁስሉ መሰፋት አለባት›› ስትል ደህንነቶቹ ግን ‹‹ይህ የአገር ጉዳይ ነው፡፡ አይሆንም›› ብለው ወደ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱኝ፡፡ ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ ድብደባ የደረሰብኝ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ደሜ እየፈሰሰ ነበር፡፡ እስከዛ ሰዓት ድረስ ቁስሉ አልተሰፋም ነበር፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን በርካታ ሰዎች ተመሳሳይ በደል ተፈጽሞባቸዋል፡፡ በፖለቲከኛ ደረጃ እኔ ብቻ ብሆንም እንፈልጋቸዋለን ያሏቸውን ሰዎች ምንም ህክምና ሳይደረግላቸው ወደ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ነበር የሚልኳቸው፡፡ የራሳቸውንም ሰዎች ሰርጎ ገቦች ናቸው እያሉ የፖሊስ መታወቂያ ስለያዙ ብቻ ተመሳሳይ በደል ተፈጽሞባቸው አብረው ልከዋቸዋል፡፡
ለረዥም ጊዜ ህክምና ባለማግኘቴ እራሴን እየሳትኩ ሄድኩ፡፡ ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ ወደ ራስ ደስታ ሆስፒታል ወሰዱኝ፡፡ ራስ ደስታ ሆስፒታል ላይ የፈጸሙብኝም በጣም የሚያሳዝን ጭካኔ ነበር፡፡ ሐኪሞቹ ቁስሌን ሲያዩ ‹‹ይህ የተፈነከተ ሳይሆን በጩቤ የተወጋ ነው›› እስከማለት ደርሰው ነበር፡፡ ነገር ግን ያንን ያህል ጉዳት ልተኛባቸው ስልሆንኩ ነው መሰለኝ ያለማደንዘዣ ነው የሰፉት፡፡ ውሃ እንኳን የሚሰጠኝ ላገኝ አልቻልኩም፡፡ ጉዳትክን እያዩ ሁሉም ጸጥ ብለው ነው የሚያልፉት፡፡ ቤተሰቦቼ የተሻለ ሐኪም ቤት ይወስዱኛል ብላቸው ሊሰሙኝ አልቻሉም፡፡ ያለ ማደንዘዥ ሲሰፉኝ በጣም እጮህ ነበር፡፡
ነገረ ኢትዮጵያ፡- እንደነገርሽኝ እንደ አንድ ፖለቲከኛ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ጉዳይ ያገባኛል ብለሽ ነው የሄሽው፤ በወቅቱ ምን ታዘብሽ?
ወይንሸት፡- ሙስሊሙ ማህበረሰብ የፈጠረው ችግር የለም፡፡ ሁላችንም እንደሰማነው በእምነታቸው ላይ በሚፈጸምባቸው ጣልቃ ገብነት ትልቅ የተቃውሞ ፕሮግራም አዘጋጅተው ነበር፡፡ ሙስሊሞቹም ያንን ነገር ለመታደም ነው የሄዱት፡፡ በወቅቱ ሙስሊሞቹ ያደረጉት ነገር የለም፡፡ ድንጋይ ወርዋሪዎቹ ደህንነት ነን የሚሉት አካላት ናቸው፡፡ ዘግናኝ ድብደባ ይፈጽሙ የነበሩትም ራሳቸው የደህንነት አካላት ናቸው፡፡ ቀርበህ ስትጠይቃቸው የሚገልጹትም በሙስሊምነታቸው እንደታሰሩ እንጂ ወንጀል ፈጽመው እንዳልሆነ ነው፡፡
በድብደባው በኩል ያለው በጣም ዘግናኝ ነው፡፡ ጦር ሜዳ ነበር የሚመስለው፡፡ ከሰባት ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት መስጊዱ አካባቢ ደብደባ ነበር፡፡ ወደቁ፣ የተፈነከቱና የደሙ እናቶችን፣ ነፍሰ ጥሩዎችን ታያለህ፡፡ ቦታው ላይ ከ2000 በላይ ሰው ተይዟል፡፡ ይህ የተያዘ ሰው ወደ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰደ፡፡ አብዛኛው ለመደብደብ እንዲያመች ወደሚኖርበት አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ነው የተወሰደው፡፡ ከፍተኛ ድብደባ የሚያደርሱባቸውን ሰዎች የሚለዩት የእንቅስቃሴው ደጋፊ ነኝ ብለው በመናገራቸውና በአለባበሳቸው ነው፡፡
መጀመሪያ በተለይ ጦር ኃይሎች አካባቢ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ (መደብደቢያ) የተወሰዱት በጣም የሚያሳዝን ግፍ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ጊዜያዊ ህክምና ከሰጡ በኋላ በኒቃብ፣ በሂጃብና በሌሎች ሀይማኖታዊ አለባበሳቸው እየነጠሉ ወደ ጦር ኃይሎች አካባቢ ወደሚገኘው መደብደቢያ ወሰዷቸው፡፡ ሞባይላቸውንና ሌሎች ንብረታቸውን ተቀምተዋል፡፡ ንብረታቸውን መዝግበው አልነበረም የሚቀበሏቸውና ማንም ንብረቱን ያገኘ የለም፡፡ በጣም በሚያሳዝንና በሚያሳፍር ሁኔታ ኒቃባቸውንና ሌሎች ሙስሊሞች በተለይም ሴቶቹ የሚለብሱትን ልብሶችቻውን እያስወለቁ ነበር የሚደበድቧቸው፡፡ መቼም ሙስሊም ሴቶች እምነቱ በሚፈቅደው መሰረት የሚለብሱትን ልብስ ሲያወልቁ ከውስጥ ምን ሊቀር እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ አብዛኛዎቹ እንዲህ ራቁታቸውን ሆነው ወንድ አይቷቸው የማያዉቁ ለጋ ወጣቶች ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ በደል ከተፈጸመባቸው በኋላ ንብረታቸውን ሳይመልሱላቸው ከሌሊቱ 9 ሰዓት ላይ ለቀቁዋቸው፡፡ ንብረታቸው አይመዘገብም፡፡ በዛና ሰዓት ሴቶቹ ወደየት ሊሄዱ ይችላሉ?
ነገረ ኢትዮጵያ፡- ለብቻሽ ተለይተሸ ከተደበደብሽ ምርመራ ላይም የተለየ ትኩረት ሊኖር እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ምርመራው እንዴት ነበር?
ወይንሸት፡- ዋነኛው የምርመራ አካል ‹‹ተልዕኮ አለሽ ይህን ተልዕኮ ንገሪን›› የሚል ነው፡፡ እንደዛ ጉዳት ደርሶብኝና ቁስሌን ያለ ማደንዘዣ ሰፍተው እስከ ሌሊቱ 9ና 10 ሰዓት ገደማ ምርመራ ላይ ነበርኩ፡፡ እኔ ደግሞ ተልዕኮ እንደሌለኝና ሁኔታውን ለመታዘብ እንደሄድኩ ነበር የምናገረው፡፡ ያው እነሱ ይሳለቃሉ፣ ይዘባበታሉ፡፡ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ድብደባ አልነበረም፡፡ ከዛም በኋላ ቤቴን ፈትሸው መጽሃፍቶችና የዘፈን ሲዲዎችን አግኝተዋል፡፡ ሊፈትሹ የሄዱት ግን ከፍርድ ቤት ፈቃድ አውጥተው የጦር መሳሪያ፣ በራሪ ወረቀቶችና ሁከትና ብጥብጥን የሚያስነሱ ቁሳቁሶች ይገኛል ብለው ነው፡፡ ቤት ያገኙትን ወረቀት መስመር በመስመር እያነበቡ የፈለጉትን ለማግኘት ጥረው ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ መታወቂያና የዘፈን ሲዲዎችን ብቻ ነው የወሰዱት፡፡
ነገረ ኢትዮጵያ፡- በተለይ ወደመጀመሪያው አካባቢ ማንም ታዛቢ ፍርድ ቤት መግባት ባለመቻሉ መከታተል አልተቻለምና የፍርዱ ሂደቱስ እንዴት ነበር?
ወይንሸት፡- የፍርድ ቤቱ ሂደቱ ድራማ ነበር፡፡ ሌላ ምንም መገለጫ የለውም፡፡ በማይመለከተን ነገር ክሱን ወደ ግድያ ለመቀየር ብዙ ብዙ ጥረዋል፡፡ ክሱ ሁከትና ብጥብጥ አስነስተዋል ነው የሚለው፡፡ በህግ መሰረት ሁከትና ብጥብጥ የዋስትና መብት አያስነጥቅም፡፡ እኛም ለፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታችንን ጠይቀናል፡፡ ይህን ስንል ‹‹በእለቱ ዕለት ከፍተኛ አደጋ የደረሰባቸው ሁለት ፖሊሶች አሉ፡፡ የእነዚህ ፖሊሶች የህክምና ውጤት እስኪረጋገጥ ድረስ እነዚህ ልጆች መለቀቅ የለባቸውም›› ብለው ነበር መርማሪዎቹ የሚከራከሩት፡፡ ፍርድ ቤት የቀረብነው 17 ሰዎች የመጣንበትን ምክንያት ተናግረናል፣ የየራሳችን መከራከሪያም አቅርበናል፡፡ መርማሪዎቹ ግን ይከራከሩ የነበሩት ግድያ እንደፈጸምን ነው፡፡ የሞተ ሰው አለ፣ ጥቁር አንበሳ የተኛ ሰው አለ እየተባለ በየ ሳምንቱ የእሱ ውጤት ነበር በመርማሪዎቹ በኩል በመከራከሪያነት ይቀርብና የጊዜ ቀጠሮ ይጠየቅበት የነበረው፡፡ ነገር ግን ሄደው አይጠይቁም፡፡ የሞተ ሰው ኖረም አልኖረም ቦታው ላይ ፖሊስ የከፈለው መስዋዕትነት ይሆናል እንጂ 17ቱም ታሳሪዎች አንድ ጠጠር እስካልወረወርን ድረስ ጥፋተኛ የምንሆንበት አንድም ምክንያት የለም፡፡ ግን ሰው ገድላችኋል ብለው የሚጠይቁት እኛን ነበር፡፡
በተለይ በፖሊስ በኩል የመጨነቅ ስሜት ይታይ ነበር፡፡ በራሳቸው ፈልገው ያደረጉት ነገር እንዳልሆነ ፊታቸው ይናገር ነበር፡፡ እነሱም ህሊናቸው ያውቀዋል፡፡ እንዲያውም እረፍት አጣን እያሉ ያማርሩ ነበር፡፡ በጣም በሚገርም ሁኔታ የአንድ መስጊድ አስተማሪ ኡስታዝ ጭምር ነው የታሰረው፡፡ የጋዜጠኛዋ አዚዛ መሃመድም ቢሆን ተመሳሳይ ነው፡፡ እነሱም እኛን ተከራክረው ጥፋተኛ ለማሰኘት የሚያስችል ምክንያቱም ተነሳሽነቱም አልነበራቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ጭንቀት ይታይባቸው ነበር፡፡ የዋስትና መብቱም የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡ እንድንለቀቅ ተወስኖ አምስትና አስር ደቂቃ ሳይሞላ ነው ወደ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ሄደን ዋስትናችን የታገደው፡፡ እነሱ ሳይሄዱ እዛው ላይ ሆነው ጨርሰውታል ማለት ነው፡፡
በወቅቱ ተመሳሳይ ምክንያት ነበር የሚያቀርቡት፡፡ ሊሞት የተቃረበ ፖሊስ አለ ነበር የሚሉት፡፡ ያው በግድያ ወንጀል ለመክሰስ ነው፡፡ የግድያ ወንጀል ደግሞ የዋስ መብትን አያስፈቅድም፡፡ የዋስ መብታችን ያገደው የይግባኝ ፍርድ ቤት ቀጠሮውን ለአንድ ሳምንት ሲያራዝም መርማሪዎቹ ጉዳት ደርሶበታል የሚሉትን ፖሊስ የህክምና ምርመራ እንዲያመጡ ቢጠይቅም እነሱ ግን ሊያመጡ አልቻሉም፡፡ በሂደቱ መረዳት እንደቻልኩት ፖሊስም ሆነ ፍርድ ቤት በራሳቸው የሚወስኑት ነገር እንደሌለ ነው፡፡ እንዲያው ዳኛው ላይ የተሻለ ነገር ማየት ችያለሁ፡፡ የተወሰነም ቢሆን ትንሽ ነገር ደፍሮ በራሱ ወስኗል፡፡ ፖሊሶቹ ላይ ግን ሙሉ በሙሉ ጭንቀት ይታያል፡፡
በዋስ ይፈቱ ከተባልን በኋላ እስር ቤት ውስጥ ቆይተናል፡፡ ከዚህም የተረዳሁት መንግስት እኛን ማንገላታትና የእስር ጊዜያችን ማስረዘም እንደሚፈልግ ነው፡፡ የመንግስት እጅ ነበረበት፡፡ ፖሊስም ሆነ ዳኛ በራሳቸው መወሰን አልቻሉም፡፡ አስር አይነት ምክንያት ይዘረዝራሉ፡፡
ነገረ ኢትዮጵያ፡- የፖለቲካ ፓርቲ አባል በመሆንሽ የደረሰብሽ የተለየ ነገር ምንድን ነው?
ወይንሸት፡- ከሌሎች በተለየ በተደጋጋሚ ከምርመራ እጠራ ነበር፡፡ አሰልቺና ተደጋጋሚ የሆኑ ነገሮችን ነው የሚጠይቁኝ፡፡ በምርመራው ወቅት የሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ አባል ያልሆኑ ማንነታቸው የማላውቃቸው ሰዎች ነበር የሚመረምሩኝ፡፡ ከመጠን በላይ ተደጋጋሚ ጥያቄ ይጠይቁኝ ነበር፡፡ ካሜራ እየተቀረጽኩ ነበር የሚያናግሩኝ፡፡ ምርመራው ከተከሰስኩበት ነገር ጋር የሚገናኝ አልነበረም፡፡ እኔ የተከስስኩት በሁከትና ብጥብጥ ነው፡፡ እነሱ የሚጠይቁኝ ግን ስለ ሰማያዊ ፓርቲ ነው፡፡ አንዴ ከፓርቲው እንድወጣ ይመክሩኛል፡፡ ለኢህአዴግ እንድሰልልም ሊያግባቡኝ ይሞክራሉ፡፡ መሰደድ የምፍለግ ከሆነ እንደሚመቻችልኝ፣ ከፖለቲካው ወጥቼ በተለይም ከኢህአዴግ ጋር መስራት ከቻልኩ ሀብታም እንደምሆን ሊመክሩኝ ይጥራሉ፡፡ ምርመራውና ክሱ ምንም አይነት ግንኙነት አልነበራቸውም፡፡
ነገረ ኢትዮጵያ፡- የሙስሊሙን ጉዳይ ለመከታተል ስትሄጂ ከገመትሽው በላይ ያልጠበቅሽው ሆኖ ያገኘሽው ነገር ምንድን ነው?
ወይንሸት፡- ሁሉም ነገር ያልጠበኩት ነው፡፡ በወቅቱ ጉዳዩን ለመታዘብ ስሄድ እንደዛ አይነት ችግር ይፈጠራል ብዬ አልገመትኩም፡፡ መንግስትን ተቃውሞው አስፈርቶታል፡፡ ይህ ግልጽ ነው፡፡ ቦታው ላይ የነበረው አድማ በታኝ ፖሊስ፣ በአካባቢው ከነበረው የሙስሊሙ ማህበረሰብ ይበልጥ ነበር፡፡ ያደረሱባቸው ነገርም ያልጠበኩትና አሰቃቂ ነገር ነው፡፡ የሰው ልጅ እንደዛ ይደበደባል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል፡፡ የሙስሊሙን ማህበረሰብ እንቅስቃሴ ሌላ መልክ ለመስጠት እዛው ላይ ድራማ ሲሰሩ ታያለህ፡፡ ለምሳሌ ያህል በጣም ትልቅ ገጀራ ነገር ነው፣ በጨርቅ ነገር ተጠቅልሏል፡፡ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ለብጥብጥ ይዞት የመጣ ለማስመስል ሲሞክሩ በርቀት እመለከት ነበር፡፡ በጣም በርካቶች ሙስሊም በመሆናቸው ብቻ ተደብድበዋል፡፡ በሙስሊም ስም መጠራት ህመም እስኪሆን ድረስ ማለት ነው፡፡ ሆን ተብሎ ጥይት ተነጣጥሮ የተተኮሰባቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ያህል ከ17 የሙስሊሙ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት መካከል አንዱ የሆነው የያሲን ኑሩ ታናሽ ወንድም ፋኢዝ ኑሩን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ፋኢዝ ኑሩ ስግደት ላይ እያለ ጥይት ተተኩሶበት እንደተመታ አብረን ታስረን በነበርንበት ወቅት ለማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ እሱ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ እነሱ ደግሞ የሚጠይቁት ስለወንድሙ ነው፡፡ እየሰገደ ስለነበር ከተመታ በኋላ ነው ያየው፡፡ ህክምናም ልክ እንደ እኔ ‹‹የአገር ጉዳይ ነው›› ተብሎ አልታከመም፡፡ ጥይቷ እስኪፈታ ድረስ አልወጣችም ነበር፡፡ ይህን ያህል ርህራሄ በጎደለው መንገድ ነው አገር እየገዙ የሚገኙት፡፡
አብዛኛዎቹ ሴቶች መስጊድ ውስጥ ነው የነበሩት፡፡ ወንዶቹ ናቸው ውጭ ላይ ይሰግዱ የነበሩት፡፡ በእስልምና እምነት መሰረት በሴቶች መስገጃ ወንድ አይገባም፡፡ መስጊድ ውስጥ የሚገኝን ሰው አውጥቶ መደብደብ ይቅርና መግባት አይፈቀድም፡፡ ነገር ግን አድማ በታኞች ከእነ ጫማቸው ሴቶች የሚሰግዱበት ውስጥ ገብተው ተደባድበዋል፡፡ ሁኔታውን አብረውኝ የታሰሩት ሴቶች እያለቀሱ ነበር የነገሩኝ፡፡ ይህ ዘግናኝና እነሱ እምነት አላቸው ወይ? ብለህ እንድትጠይቅ የሚያስገድድ ነው፡፡ አድማ በታኝ ሴቶች መስገጃ ድረስ ገብቶ ህጻናትን፣ እናቶችንና ነፍሰ ጡሮችን በጭካኔ ሲደበድብ በጣም ያሳዝናል፡፡ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በጣም አዝኗል፡፡
ነገረ ኢትዮጵያ፡- እንደገለጽሽልኝ ከተያዝሽበት ጊዜ ጀምሮ በደል ደርሶብሻል፡፡ ለ29 ቀናትም እስር ቤት ቆይተሻል፡፡ ባልሄድኩ ብለሽ ይጸጽትሻል?
ወይንሸት፡- ጉዳዩን ተገኝቼ በማየቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ለማየት ነው የሄድኩት፡፡ ተይዤ የእስር ቤት አያያዙን ጨምሮ በርካታ ነገሮችን መታዘብ ችያለሁ፡፡ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ የሚፈጸምበትን ግፍና በደል በአካል ተገኝቼ ማየት ችያለሁ፡፡ ደህንነቶቹ በምርመራ ወቅት የሚያደርጉትን ነገር መታዘብ ችያለሁ፡፡ በአስተሳሰብም ደረጃ ጉዳዩን በአንድ ደረጃ ከፍ ብየ እንዳየው ያደረገኝ በመሆኑ ተገኝቼ የሙስሊሙን እንቅስቃሴ በመታዘቤ ምንም አልጸጸተኝም፡፡ እንዲያውም በመገኘቴ ኮርቻለሁ፡፡
ነገረ ኢትዮጵያ፡- አመሰግናለሁ ወይንሸት!
ወይንሸት፡- እኔም አመሰግናለሁ!