ግንቦት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከብአዴን እና ከኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚነት በቅርቡ በተካሄዱት ጉባዔዎች የተነሱት የፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ብርሃን ኃይሉ በማረሚያ ቤቶች የሰብዓዊ መብት ጥሰት መኖሩን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ የመብት ጥሰት የለም ሲሉ ተናገሩ።
በዛሬው ዕለት የመ/ቤታቸውን የ9 ወራት ሪፖርት ለፓርላማ ያቀረቡት ሚኒስትሩ አቶ ብርሃን ኃይሉ ከብቸኛው የአንድነት ፓርቲ የፓርላማ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡
...
አቶ ግርማ ባቀረቡት ጥያቄ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው በማረሚያ ቤቶች የሰብዓዊ መብቶች እየተከበሩ መሆኑን በተካሄዱ ጉብኝቶች ማረጋገጣቸውን መጥቀሳቸውን በማስታወስ በጉብኝቱ ምን እንዳገኙ ጠይቀዋቸዋል፡፡ አይይዘውም ባለፈው ቅዳሜ ዕለት የታሰሩ ሰዎችን ለመጠየቅ ወደማረሚያ ቤት ሄደው ተከልክለው መመለሳቸውን በማስታወስ ይህ ፓርላማ እንኳን መጣስ የማይችለውን ሕገመንግስት ማረሚያ ቤት እየጣሰ ነው ሲሉ ምሬት አዘል አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ በማረሚያ ቤቶች ጉብኝታቸው የታራሚዎች መብዛት ጋር ተያይዞ መጨናነቅ መኖሩን፣የመገልገያ ዕቃዎችና እንደንጹህ መጠጥ ውሃ ያሉ የመሰረተ ልማት ችግሮች መኖራቸውን ማስተዋላቸውን እና ይህ ችግር እንዲፈታ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
የማረሚያ ቤቶች ተጠሪነታቸው ለፍትህ ሚኒስቴር ሳይሆን ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሩ በሰብዓዊ መብት አያያዝ በኩል ችግር እንደሌለና፤ አለ እንኳን ቢባል ሕገመንግስት ተጥሶአል ለማለት እንደማይቻልና የተፈጠረ የአሰራር ችግር ካለ ሊስተካከል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
በማረሚያ ቤት በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች፣የፖለቲካ መሪዎች፣የሙስሊሙ ማኀበረሰብ አባላትና ሌሎችም በየጊዜው በሕገመንግስቱ የተረጋገጠው የሰብዓዊ መብቶቻቸው ማለትም በቤተሰቦቻቸውና በወዳጆቻቸው የመጎብኘት፣ ከጠበቆቻቸው ጋር ያለችግር የመገናኘትና ሃሳብ የመለዋወጥ፣ ከሃይማኖት አባቶቻቸው ጋር የመገናኘት መብቶቻቸው በማረሚያ ቤት
ኃላፊዎች በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተና ብዙውን ጊዜ የሚጣስ መሆኑን እየገለጹና በመግለጽ ላይ የሚገኙ ከመሆኑ አንጻር የሚኒስትሩ አባባል ግልጽ ክህደት መሆኑን አንድ ያፓርላማ አባል ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ያቀረቡትን ሪፖርት ተከትሎ ከፓርላማ አባላቱ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል በይቅርታ ከማረሚያ ቤት የሚለቀቁ ሰዎች መስፈርቱን ያሙዋሉት እያሉ ያላሙዋሉት ይለቀቃሉ፣ይህ ለምንድነው በሚል ለተነሳው ጥያቄ ይቅርታ የታራሚው ጉዳይ ሳይሆን መንግስት በራሱ ፍላጎት የሚያደርገው ነው፡፡እንደመብት ሊጠየቅ አይችልም ሲሉ የፓርላማ
አባላቱን ጥያቄ አጣጥለዋል፡፡
በፍትህ ሚ/ር ስር የሚገኘው የይቅርታ ቦርድ ጥያቄው ሲቀርብ የታራሚው ጠባይ፣ለመሻሻል ያለው ፍላጎት ታይቶ በማረሚያ ቤት በጎ አስተያየት ሲቀርብ እንደሚለቀቁ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ይህ የሚኒስትሩ ማብራሪያ ግን በሌላ የፓርላማ አባል ተተችቶአል፡፡ አባሉ በሰጡት አስተያየት ሚኒስትሩ ሲናገሩ ይቅርታ እና አመክሮን መደበላለቃቸውን በመጥቀስ ይቅርታ ልክ እንደአመክሮ ጠባይ የሚመዘንበት አይደለም፡፡ቀደም ሲል የቅንጅት እስረኞች ጠባያቸው ታይቶ አልተፈቱም ሲሉ የሚኒስትሩን ንግግር ተችተዋል፡፡
ባለፉት 9 ወራት 2 ሺ 958 የይቅርታ ጥያቄዎች ቀርበው 2 ሺ 149 ያህሉ በይቅርታ መለቀቃቸውን ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡
“የፍርድ ሂደቱ ሲጠናቀቅ ጋዜጣዊ መግለጫ እንሠጣለን” - ከጀማነሽ ጋር የታሰሩ አባት
በተለያዩ የመድረክ ቴያትሮች፣ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ድራማዎች በተለይም “ገመና” በተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ የእናትነት ገፀ - ባህሪን ተላብሳ በመተወን የምትታወቀው አርቲስት ጀማነሽ ሰለሞን ታሰረች፡፡ አርቲስቷ ማክሰኞ ማታ ተይዛ አራት ኪሎ የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ከታሰረች በኋላ ረቡዕ አመሻሽ ላይ ወደ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ መዛወሯንና ከእርሷ ጋር ሌላ አንዲት ሴትና ሁለት ወንዶች መታሰራቸውን በስፍራው ተገኝተን አረጋግጠናል፡፡ አርቲስት ጀማነሽና አብረዋት የታሰሩት ግለሰቦች ሃሙስ እለት አፍንጮ በር መንገድ አዲስ አበባ ሬስቶራንት አካባቢ በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጀ ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው የታየ ሲሆን የፊታችን በድጋሚ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፡፡
አርቲስቷንና አብረዋት የታሰሩትን ሰዎች ለመጠየቅ ወደ ስፍራው ከመጡ ግለሰቦች ለመረዳት እንደቻልነው፤ አርቲስቷና አብረዋት ያሉት ሰዎች የታሰሩት “ማህበረ ስላሴ ዘ ደቂቀ ኤልያስ” ከተባለው ማህበራቸውና ከሀይማኖት ጉዳይ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ጠቁመው ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ከአርቲስቷ ጋር የታሰሩት አንድ የሃይማኖት አባት፤ ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ በመሆኑ ከፍርድ ሂደቱ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ፣ አሁን ምንም አይነት ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ነግረውናል፡፡ አርቲስት ጀማነሽን ሊጠይቋት የመጡ ሰዎችን ለማነጋገር ስትወጣ በተመለከትናት ጊዜ በፈገግታ የታጀበች ሲሆን ጠያቂዎቿ “እንዴት ነሽ ተመቸሽ?” ብለው ሲጠይቋት “እግዚአብሔር ያለበት ቦታ ሁሉ ምቹ ነው” ስትል ምላሽ ሰጥታለች፡፡ አርቲስቷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ተዋህዶ” በሚል ሃይማኖት ውስጥ ተሣታፊ በመሆን አነጋጋሪ ሆና መቆየቷ የሚታወስ ነው፡፡
ወረዳ ዘጠኝ ፖሊስ ጣቢያ በተገኘን ጊዜ የሃይማኖቱ ተከታዮች የሚለብሱት የቀስተደመና ቀለማት ያሉት ነጠላ አጣፍታ፣ ፀጉሯንም የቀስተ ደመና ቀለም ዙሪያውን ባቀለመው ሻሽ አስራለች፡፡ ማህበረ ስላሴ ዘ ደቂቀ ኤልያስ “የኢትዮጵያን ትንሣኤ ሊያረጋግጥ ሃያል ባለስልጣን ነብዩ ኤልያስ ከብሔረ ህያዋን ጳጉሜ 1/2003 ዓ.ም ወደ ምድር መጥቶ በመካከላችን ይገኛል፣ ኦርቶዶክስ የሚባለው የሃይማኖት ስም ስህተት ነው ተዋህዶ ነው መባል ያለበት፣ ሰንበት ቅዳሜ ብቻ ነው፣ መለበስ ያለበት እግዚአብሔር ለኖህ ቃል ኪዳን የገባበትን ቀስተ ደመና ቀለማት ያካተተ ጥለት ያላቸው ነጭ አልባሳት ናቸው” የሚሉትን የተለያዩ ጉባኤዎችን እያዘጋጀ የሚያስተምር ማህበር መሆኑን ያነጋገርናቸው የማህበሩ አባላት ገልፀውልናል፡፡
በተለያዩ ገዳማትም የሀይማኖቱ አራማጆች እንደሚገኙና እንደሚያስተምሩ ያገኘናቸው የሃይማኖቱ ተከታዮች ነግረውናል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ከፖሊስ መረጃ ለማግኘት ጥረት ብናደርግም፣ ከመምሪያው የተፃፈ ፈቃድ ያስፈልጋል በሚል የወረዳው ፖሊስ መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡