መንግስት ለትውልድ የሚተርፍ የማያልቅ እዳ ውስጥ እየገባ ነው”
መንግሥት የሱቅ ነጋዴ ቢሆን በአንድ ሳምንት ሱቁን ይዘጋ ነበር ትልቁ ሙያ ግሽበቱን ቀንሶ፣ ብሄራዊ ምርቱን አሳድጐ፣ ስራ
አጥነትን መቀነስ ነው የዋጋ ግሽበቱ የቱ ጋ ነው የወረደው ---- ስኳር ላይ ነው? ዘይት ላይ ነው? ጤፍ ላይ? ኢህአዴግ
በቅርቡ ባህርዳር ላይ ባካሄደው ድርጅታዊ ጉባኤው አጠቃላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ እንዳሳሰበው ገልጿል፡፡ በሌላ በኩል የዋጋ
ግሽበት በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መምጣቱን ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ቢሮ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አንዳንድ የኢኮኖሚ
ባለሙያዎች እንደሚሉት ኢህአዴግ ቀደም ሲል የተሰጡትን ሙያዊ ምክሮች አለመስማቱ አሁን በኢኮኖሚው ማሽቆልቆል ዋጋ እያስከፈለው
ነው፡፡ በ97 ምርጫ ቅንጅትን ወክለው በመወዳደር ፓርላማ የገቡትና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ከአገሪቱ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር መለስ
ዜናዊ ጋር ክርክርና ሙግት በመግጠም የሚታወቁት አቶ ተመስገን ዘውዴ፤ በአሁኑ ሰዓት መንግሥት ቀንሷል የሚለው የዋጋ ግሽበትም
እንደተባለው አለመቀነሱን ይናገራሉ፡፡
የአንድነት ፓርቲ የውጭ ጉዳይ ሰብሳቢና የመድረክ ስራ አስፈፃሚ አባል
የሆኑትን አቶ ተመስገን ዘውዴን በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ አድማስ አነጋግሯቸዋል፡፡ ከፓርላማ ከወጡ በኋላ ለምን
ከሚዲያው ጠፉ? ወድጄ አይደለም፡፡ አብዛኛው ሚዲያ በገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ስር ነው ያለው፡፡ ይኼ ደግሞ ሃቁን የሚናገሩ ተቃዋሚ
ፓርቲዎች የሚናገሩት ነገር ለገዢው ፓርቲ ሊዋጥለት ስለማይችል ነገሩን አድበስብሰው ከሚያልፉት ጋር ብቻ ከማቀንቀን ብዬ ነው
የጠፋሁት፡፡ የሚዲያ አማራጭ የለንም፡፡ አሉ የሚባሉትን ነፃና ገለልተኛ የፕሬስ ውጤቶች ገዢው ፓርቲ እንዳይታተሙ በማድረጉ ብዙም
የሚዲያ እድል ስለሌለኝ ነው እንጂ የምናገረው ነገር በማጣት አይደለም፡፡ አሁን ምን እየሠሩ ነው? ከፓርላማው ከወጣሁ በኋላ
በፓርቲዬ “አንድነት” ውስጥ እያገለገልኩ ነው፡፡ የፓርቲው የውጭ ግንኙነት ጉዳይ ኃላፊ ሆኜም እየሰራሁ ነው፡፡
አሁን ያለው ፓርላማ እርሶ ከነበሩበት ፓርላማ አንፃር በሀገሪቱ ወሳኝ
ጉዳዮች ላይ የሚያደርጋቸውን ውይይቶችና የሚያስተላልፋቸውን ውሳኔዎች እንዴት ይገመግሙታል? እኔ በነበርኩበት ፓርላማ ይብዛም
ይነስም 172 የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ነበሩ፡፡ እነዚህ አባላት በሙሉ አቋማቸው ግልፅ ነበር፡፡ እዚያ ውስጥ ያለነው የፓርላማ
አባላት በተለይ እኔ የነበርኩበት የመጀመሪያው ቅንጅት፣ ቀጥሎም አንድነት የህዝብን አንገብጋቢ ጥያቄዎችና የመንግሥትን ፖሊሲ
የመሳሰሉትን አንስተን ወደ ፓርላማው ለማቅረብ ባንችልም በነዚህ ዙሪያ የሚነሱ ሃሳቦችን በቀጥታ በመጋፈጥ ለህዝብ ይጠቅማሉ
ያልናቸውን ሃሳቦች በትክክል ህዝቡ እንዲሰማ አድርገን እናቀርብ ነበር፡፡ አሁን ግን ገዢው ፓርቲ ሙሉ ለሙሉ ፓርላማውን
ስለተቆጣጠረ የሚወጡት አዋጆች የኢትዮጵያን ህዝብ ሰላም፣ ዲሞክራሲያዊ ነፃነት እና የሰብአዊ መብት ጥበቃ ወደ ኋላ የሚጐትቱ
መሆናቸውን ለማሰማት የሚደረጉ ጥረቶች ደካማ ናቸው፡፡
ይሄም ከገዢው ፓርቲ ተፅእኖ የሚመጣ ነው ለማለት እችላለሁ፡፡ ባለፈው ግን
ቁጥራችንም ብዙ ስለነበረ በምትሰጠን ጥቂት ደቂቃ ውስጥ ከፍተኛ የህዝብ ስሜትን ሊይዝ የሚችል ክርክር በፓርላማው ውስጥ በማድረግ
ለህዝቡ ያለንን ታማኝነትና ቆራጥነት ለማሳየት የቻልንበት ሁኔታ ነበር፡፡ አጠቃላይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እየተቀዛቀዘ መሆኑን
መንግሥትም አለማቀፍ ተቋማትም ገልፀዋል፡፡ ምክንያቱ ምን ይሆን? እንግዲህ እዚህ ሀገር አንድ ገዢ ፓርቲ ከማዕከል እስከ ቀበሌ
ፍፁም በሆነ አስተዳደራዊ የበላይነት እያስተዳደረ ነው፡፡ ኢኮኖሚው በሁለት አሃዝ ጨምሯል ሲባል በእርግጥ ጨምሯል ወይ ብለን
ከሦስተኛ ወገን የምናጣራበት መንገድ የለም፡፡ ኢኮኖሚው ላለፉት ሦስትና አራት አመታት እያደገ ነው ሲባል እየሰማን ነው፡፡
የኢኮኖሚ እድገት ዞሮ ዞሮ ተጠቃሚ ማድረግ ያለበት ህብረተሰቡን ነው፡፡ መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን እንደ ምግብ፣ መጠለያና
አልባሳትን ማሟላት አለበት፡፡ የኢኮኖሚ እድገቱም በዚህ ነው የሚታየው፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢኮኖሚው በሁለት አሃዝ አድጓል ሲል እኛ
አልተቀበልንም፡፡ ብሄራዊ ምርት (GDP) ከዓመት ዓመት አድጐ እንኳ ቢሆን ኖሮ የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር የሚጠይቀው ብሄራዊ
ምርቱን ማሳደግና የዋጋ ግሽበቱን መቆጣጠር ነው፡፡
በማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር ሙያ፤ ብሄራዊ ምርት (GDP) ማሳደግ ብቻ
አይደለም ትልቁ ነገር፣ ኢኮኖሚውን እያሳደጉ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ነው፡፡ ትልቁ ነገር ስራ አጥነትን መቀነስ መቻል ነው፡፡
ገዢው ፓርቲ ግን እያየው ያለው ከፖለቲካዊ አንድምታው አንፃር ብቻ ነው፡፡ ብሔራዊ ምርቱ በማደጉ ምክንያት ዜጐች በገቢያቸው
ለመተዳደር አለመቻላቸውን እንደ ቁምነገር አይቆጥረውም፡፡ ግን ትልቁ ቁምነገር እሱ ነው፡፡ የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ሳይቻል
ብሄራዊ ምርት አድጓል ማለት በቀኝ ሰጥቶ በግራ እጅ መቀበል ነው፡፡ ምክንያቱም ዜጐች በዋጋ ግሽበት ምክንያት በገቢያቸው
መተዳደር ካልቻሉ የብሄራዊ ምርት ማደጉ ትርጉም የለውም፡፡ በማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር ሙያ፤ ብሄራዊ ምርት አድጓል ማለት
መንግሥት ወጪውን ሳይቀንስ ብር እያፈሰሰ ነው ማለት ነው፡፡ ትልቁ ሙያ ያለው ግሽበቱን ቀንሶ፣ ብሄራዊ ምርቱን አሳድጐ ስራ
አጥነትን መቀነስ መቻሉ ላይ ነው፡፡ ብሄራዊ ምርቱ በማደጉ ምክንያት ዜጐች ተጠቃሚ ሆነዋል ወይ የሚለው ያልተመለሰ ጥያቄ
ነው፡፡
በምሳሌ ላስረዳ፤ የዛሬ አራት ዓመት አምስት ብር በኪሎ የሚሸጥ ሙዝ ዛሬ
12 ብር ነው፣ በተቃራኒው የዛሬ አራት ዓመት 3ሺህ ብር በወር የሚያገኝ የመንግሥት ተቀጣሪ ዛሬም 3ሺህ ብር እያገኘ ነው፡፡
ታዲያ ይኼ ዜጋ እንዴት ነው ከእድገቱ ተጠቃሚ የሆነው፡፡ የብር የመግዛት አቅሙ መሬት ወድቋል፡፡ መንግሥት ግን ብሄራዊ ምርቱ
አደገ እያለ ነው፡፡ ምን ጥቅም አለው ይሄን ማለቱ? ዜጐች በገቢያቸው መተዳደር ካልቻሉ፣ ሸማቹ ህብረተሰብ በገቢው መተዳደር
ካልቻለ ዋጋ የለውም እያልን ነው፡፡ አሁን የዋጋ ግሽበቱ ወረደ እያሉን ነው፡፡ የቱ ጋ ነው የወረደው? እንደ ኢትዮጵያዊ
የምንመገባቸውን ምግቦች እናውቃቸዋለን፡፡ የሰብል ምግቦች ዋጋ ላይ ነው የተሻሻለው? ስኳር ላይ ነው? ዘይት ላይ ነው? ጤፍ ላይ
ነው? እስቲ የቱ ላይ ነው የወረደው፡፡ ይኼንን በተገቢው መንገድ ማስረዳት አለባቸው፡፡ የዋጋ ግሽበቱ በአይ ኤም ኤፍ የሐምሌ
2004 ዓ.ም መረጃ መሰረት፤ 33 በመቶ ደርሷል ይላል፡፡
አሁን ደግሞ እነሱ ወደ 12.9 በመቶ ዝቅ ብሏል እያሉን ነው፡፡ በጣም
የሚገርም ሂደት ነው፤ የዋጋ ግሽበት ወደ ላይ ለመውጣትም ጊዜ ወስዶ ነው የሚወጣው፡፡ አወጣጡም አወራረዱም የራሱ መንገድ ስላለው
የዋጋ ግሽበቱ በአራት እና አምስት ወር ጊዜ ውስጥ ከ33 በመቶ ወደ 12.9 በመቶ ወረደ ማለት መቶ ኪሎ ሜትር በሰዓት እየበረረ
የሚሄድ መኪና ከመቅፅበት ቆመ እንደማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሌላ የሚያስከተለው ጉዳት አለ፡፡ ወረደ ከተባለ በምን ምክንያት ነው
የወረደው? የወጣውስ በምን ምክንያት ነው? የሚለው ተተንትኖ ሊቀርብ ይገባዋል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ንግግራቸው የሃቅ ነው
ማለት አይቻልም፡፡ ለፖለቲካ ፍጆታ የሚነገር ብቻ ይሆናል፡፡ ዛሬ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በገቢው መተዳደር፣ ልጆቹን
ማስተማር፣ የቤት ወጪውን መሸፈን ባልቻለበት ሁኔታ እንዲህ አይነት የፕሮፓጋንዳ ምላሾች አስገራሚ ናቸው፡፡ ገዢው ፓርቲ የመንገድ
መሰራትና የህንፃዎች መብዛትን ከፍተኛ የልማት ስኬት አድርጐ ነው የሚወስደው፡፡ ሃቁ ግን ይህ አይደለም፡፡
አስቀድሜ እንዳልኩት የህዝቦች የኑሮ ደረጃ የሚለካው በብሄራዊ ምርት
(GPD) እድገት ብቻ አይደለም፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ሂውማን ዴቨሎፕመንት ኢንዴክስ (የሰብዓዊ ልማት መለኪያ) የሚል ሪፖርት
አውጥቷል፡፡ በዚያ መለኪያ መሰረት ኢትዮጵያ ከ178 ሀገሮች 174ኛ ደረጃ ነው የተሰጣት፡፡ የመጨረሻውን ረድፍ ነው የያዘችው፡፡
ይኼ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ እስከ 12 ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ የምግብ ሰቆቃ ያለበት ሀገር ኢኮኖሚው አድጓል ቢባል ትርጉም
የሚሰጥ አይደለም፡፡ አሁን ግን እድገቱ ቀንሷል እያለ ነው መንግሥት፡፡ ይኼ ምንን ነው የሚያመለክተው? እንግዲህ ትክክለኛውን
እንናገር ከተባለ የዋጋ ግሽበት የሚባለውን ኢህአዴግ አልፈጠረውም፡፡ በማንኛውም ኢኮኖሚ ውስጥ የሚያጋጥም ጉዳይ ነው፡፡ የተለያዩ
የኢኮኖሚ “ሳይክሎች” አሉ፡፡ ግሽበት ውስጥ የምንገባው፣ ኢኮኖሚው ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ገንዘብ እየታተመ ወደ ኢኮኖሚው
ሲገባ ነው፡፡ በመሰረቱ ግሽበት ማለት “ጥቂት ምርትን ብዙ ገንዘብ ሲያሳድድ” ማለት ነው፤ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ አሁን ምርቱ
የለም፤ ብዙ ገንዘብ አለ ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው አንድ ዶላር 20 ብር ድረስ እየተመነዘረ ያለው፡፡
እንደዚህ ያሉ የግሽበት ሂደቶች ውስጥ ሲገባ ኃላፊነት የሚሰማው ገዢ ፓርቲ
ሊወስዳቸው የሚገቡት እርምጃዎች አሉ፡፡ አንደኛው የመንግሥት ወጪን መቀነስ ነው፡፡ የመንግስት ወጪ እንዲቀንስ የሚደረግበት
ምክንያት አለው፣ ኢኮኖሚው መሸከም ከሚችለው በላይ የብር ፍሰት ካለ መንግሥት ወጪውን መቀነስ አለበት፡፡ ይሄን ሌሎች ሀገራት
እያደረጉ ያሉት ሞኝ ስለሆኑ አይደለም፤ “ኮንቬንሽናል የማክሮ አስተዳደር” የግዴታ ይሄን ስለሚጠይቅ ነው፡፡ ሌላው የበጀት
ጉድለት እንዲጠብ መደረግ አለበት፡፡ እዚህ ግን የበጀት ጉድለቱ እንዲሰፋ እየተደረገ ነው፡፡ ሌላው ዜጐች ከባንክ የሚያገኙት
የወለድ መጠንና የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ ከፍ እንዲል ይደረጋል፡፡ ምክንያቱም ገንዘብ ከኢኮኖሚው ውስጥ ለመሰብሰብ ይጠቅማል፡፡
ሌሎችም ብዙ መንገዶችም አሉ፤ መንግሥት ይሄን ለማድረግ አይፈልግም፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን እድገቱ ቀነሰ ሲባል ምን ሆኖ ቀነሰ
የሚለውን እናነሳለን፡፡ የመንግሥት ወጪ ቀንሶ አይደለም እንዲያውም እየጨመረ ነው ያለው፡፡ የበጀት ጉድለቱ እየጠበበ ነው?
አይደለም እንደውም እየሰፋ ነው፡፡ የወለድ መጠኑም እየጨመረ አይደለም፣ ብሄራዊ ባንክም ገንዘብ እያተመ ወደ ገበያው ማሰራጨት
አቁሟል ማለትም አይደለም፡፡
ስለዚህ በየትኛውም መንገድ ሚዛን ላይ ሊቀመጥ የሚችል ገለፃ የሌለው ነው፡፡
አሁን ብሄራዊ ምርቱ (GDP) ወርዷል ነው ያሉት፡፡ ቢወርድም እኛ እያየን እንዳለነው የዋጋ ግሽበቱ እየቀነሰ አይደለም፣ የስራ
አጥ ቁጥር እየቀነሰ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ ኢኮኖሚው ከፍተኛ መቀዛቀዝ ውስጥ ገብቷል እያሉን ነው፡፡ ከ11.5 ወደ 8.5 በመቶ
በአራትና በአምስት ወር ጊዜ ውስጥ መውረድ ከፍተኛ ለውጥ ነው፡፡ ኢኮኖሚው የሚመራው በፖለቲካው ስለሆነ የትኛውንም ዓይነት መረጃ
ለመቀበል ያስቸግረናል፡፡ ያኔም የሚናገሩት ችግሮችና መፍትሄዎቹ የተዛቡ ናቸው፤ አሁንም የሚናገሩትና መፍትሄ የሚሉት ነገር
የላቸውም፡፡ ስለዚህ ኢኮኖሚውን በሙያ፣ በግንዛቤ መተንተን ሳይሆን ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ መጠቀም ነው የያዙት፡፡ የኢኮኖሚው
መቀዛቀዝ ምናልባት የገበያ (ግሽበት) መረጋጋት ይፈጥር ይሆን? የኢኮኖሚውን መቀዛቀዝ ከአቶ መለስ ህልፈት ጋር የሚያያይዙትም
አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ? አሁን እኮ የኢኮኖሚም ሆነ የገበያ መረጋጋት የለም፡፡ ሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ እዳ አለባት፣ የብር
የመግዛት አቅም ተዳከሟል፡፡ በዚህ ሁኔታ መረጋጋት የሚታሰብ አይደለም፡፡ ሀገሪቱ መመራት ያለባት በሲስተም እንጂ በሰዎች ማንነት
አይደለም፡፡ በሰዎች ማንነት የሚመራ ኢኮኖሚ አሁን ላለንበት ሁኔታ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ ያለመረጋጋት እና ከሲስተም ውጪ የሆነ
ስራ ነው ውጤቱ፡፡
ኢኮኖሚው በተቀዛቀዘበት፣ ግሽበቱ ባልቀነሰበት ሁኔታ የሀገሪቷ እጣፈንታ ምን
ሊሆን ይችላል? አንድ ጊዜ ፓርላማ እያለሁ ትንቢታዊ የሆነ ነገር ተናግሬ ነበር፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀርመን ውስጥ
የጀርመን መገበያያ ገንዘብ ወርዶ መሬት ስለነካ፣ አንድ ቲማቲምና አንድ ድንች ለመግዛት ጀርመናውያን በከረጢት ሙሉ ብር እየያዙ
ይዞሩ ነበር፡፡ ይኼን ለፓርላማ ስናገር፣ ይኼንና የኛን ሀገር ሁኔታ ምን ያገናኘዋል? የሚል ምላሽ ነበር የቀረበልኝ፡፡ አሁን
እንግዲህ ወደዚያ ደረጃ እየደረስን ነው ማለት ነው፡፡ ግሽበት “ሀ” ብሎ ሲጀምር ነው ኢኮኖሚው ብዙ ማስታገሻ መርፌ መወጋት
ያለበት፡፡ ልማታዊ መንግሥት ነኝ ለሚል የሚቀርቡ መራራ ክኒኖች አሉ፡፡ ከእነዚያ መራራ ክኒኖች አንዱ የምታወጣውን ወጪ ቀንስ
የሚለው ነው፡፡ ያንን መራራ ኪኒን አልውጥም በማለቱ ነው ዛሬ ከዚህ ደረጃ ያደረሰን፡፡ ያንን መራራ ኪኒን ውጦ ወጪውን ቢቀንስና
በጀት ቢያጠብ ኖሮ፣ እዚህ አንደርስም ነበር፡፡ አሁንም እነዚህ የቀበቶ ማጥበቅ ስራዎች ካልተሰሩ የሚገነባው ልማት ዝም ብሎ
ገንዘብ አትሞ ከማፍሰስ ውጪ በምርታማነት ሊገኝ ስለማይችል ኢኮኖሚው ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ ይኼ ላይ ላዩን የተቀባባ
ነገር እየቀጠለ በህዝቡ ላይ ግን የከተማ ድህነት እየጨመረ፣ የመንግሥት ሠራተኛው በገቢው መተደደር እየተቸገረ፣ ምርት እየጠፋ
በሚሄድበት ጊዜ ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እየገባን ነው የምንሄደው፡፡
ገዢው ፓርቲ አሁን አለች የምትባለውን የኢኮኖሚ እድገት ሊያስመዘግብ
የቻለው፣ ከ1997 ዓ.ም በኋላ በወቅቱ “ኦርጅናሉ ቅንጅት” በፈጠረው የሰላማዊ ተቃውሞ ህዝቡ ሌላም አማራጭ አለ ብሎ ማሰቡን
መንግሥት ተገንዝቦ ከእንቅልፉ በመንቃቱ ነው፡፡ አሁንም ግን እድገቱ ተገኘ የተባለው ትውልድን ከፍተኛ የውጭ እዳ ውስጥ
በማስገባት ነው፡፡ አሁን እኮ መንግሥት ለሁለት ወር የሚበቃ የገቢ እቃ ለማስመጣት የሚያስችል ገንዘብ የለውም፡፡ አንዳንድ
ነጋዴዎች ባንክ ውስጥ “ሌተር ኦፍ ክሬዲት” ለመክፈት ቆዩ እየተባሉ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የውጭ እዳው አሳሳቢ ነው፡፡ ለትውልድ
የሚተርፍ ተከፍሎ የማያልቅ እዳ ውስጥ እየገባ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በንግድ ከተሻረከቻቸው ሀገራት ጋር በሙሉ ኢ-ሚዛናዊ በሆነ
የንግድ ሂደት ውስጥ ነው ያለችው፡፡ ሚዛናዊ ወይም ትርፋማ የሆነ የንግድ ጥምርታ የላትም፡፡ ይኼ መንግሥት እኮ የሱቅ ነጋዴ
ቢሆን ኖሮ በአንድ ሳምንት ነው ሱቁን መዝጋት ያለበት፡፡ ምክንያቱም የሚገዛው ከሚሸጠው በእጥፍ የሚበልጥ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ
ገዢ ፓርቲ በዚህ አይነት ሁኔታ ማስተዳደር አይችልም፡፡
ከዚህ ሁኔታ ውስጥ ለመውጣት ደግሞ አንደኛ ለውጭ ግብይት የሚያቀርበውን
ሸቀጥ በአይነት መጨመር አለበት፡፡ ሁለተኛ (Import substitution) የሚባል አለ፡፡ እነዚህ ከውጭ በከፍተኛ ምንዛሬ
ተገዝተው የሚገቡትን ተክተን በራሳችን ልንሰራቸው የምንችላቸው ማለት ነው፡፡ ይሄን ለማድረግ የሚችሉ ስራ ፈጣሪዎችን መንግሥት
ሊያበረታታቸው ይገባል፡፡ ይኼ እየተደረገ አይደለም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ከተቃዋሚ ፓርቲዎችም ጋርም ሆነ ከሌላው ዜጋ ጋር
በመመካከር ችግሮች በዘላቂነት የሚቀረፉበትን መንገድ መፈለግ አለበት፡፡ ኢኮኖሚን መገንባት ይቻላል፤ ጤናማ ኢኮኖሚን ለመገንባት
ግን የተለየ ሙያዊ ብቃት ይጠይቃል፡፡ ጤናማ ኢኮኖሚ የሚባለው የዋጋ ግሽበትን የተቆጣጠረ፣ ስራ አጥነት እንዲቀንስ የሚያደርግና
ብሄራዊ ምርት (GDP) እድገትን የሚያመጣ ነው፡፡ ይሄን ማድረግ ደግሞ ይቻላል፡፡ ከፖለቲካ እይታ ውጪ ብቃቱ ያላቸው ሙያተኞችን
አሳትፎ፣ ጤናማ የኢኮኖሚ እድገትን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ መንግሥት በአሁን ሰዓት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ከድህነት
ወለል በላይ መሆኑንና 30 በመቶው ብቻ በድህነት ውስጥ ያለ መሆኑን እየገለፀ ነው፡፡ እርሶ ይሄን ይቀበሉታል? በመሰረቱ ይኼ
ታማኝነት አለው ወይ? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ገዢው ፓርቲ ብዙ ጊዜ የሚያወጣቸው መረጃዎች ታሽተው ነው እኛ ጋር
የሚደርሱት፡፡
የመረጃ ምንጫችንም ይኸው ገዢው ፓርቲ ብቻ ነው፡፡ ነፃና ገለልተኛ በሆነ
አካል ይህን ማረጋገጥ አንችልም፡፡ እኛ ግን አሁን ባለንበት ሁኔታ መጠየቅ የምንችለው፣ የድህነት መጠኑ ወደ 30 በመቶ ወርዷል
ከተባለ እንዴት ነው ይሄ ነገር የተፈፀመው? የሚለውን ጥያቄ ነው፡፡ የህዝብ ቁጥር ስለቀነሰ ነው? እንግዲህ የህዝብ ቁጥር
በጨመረ ቁጥር ብሄራዊ ምርቱ ለብዙ ህዝብ ነው የሚከፋፈለው፡፡ አሁንም የሚሆነው ፍትሃዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል አለ ነው፡፡ አሁን
ግን የህዝብ ቁጥር አልቀነሰም፤ መረጃዎች የሚያመለክቱት እንደጨመረ ነው፤ ስለዚህ እንዴት ሆኖ ነው ይኼ ድህነት ቅነሳ ሊመጣ
የቻለው? በብሄራዊ ምርት እድገት ነው ከተባለ ደግሞ እድገቱ የከተማ ድህነትን ጨምሯል፡፡ ምክንያቱም የዋጋ ግሽበቱ ትልቁ ቀንበር
የሚያርፈው ድሃው ህብረተሰብ ላይ ነው፡፡ ገቢው የተወሰነና ሊጨምር የማይችል ሆኖ የዋጋ ግሽበቱ ግን በልጦታል፡፡ ስለዚህ የከተማ
ድህነት እየጨመረ ነው ያለው፣ የገጠሩም በተመሳሳይ ነው፡፡ ከህዝቡ 12.5 ሚሊዮን ያህሉ ከግማሽ ሄክታር በታች ይዞታ ያላቸው
ገበሬዎች ናቸው ዝናብ ሲዘንብ ጠብቀው ራሳቸውን መግበው፣ ሌላውን ህብረተሰብ ለመመገብ የሚታትሩት፡፡ ዝናብ ሳይዘንብ ደግሞ
እነሱም ተርበው ህብረተሰቡም ይራባል፡፡
ስለዚህ ከድህነት ወጡ የተባሉት የመሬት ይዞታቸው ጨምሮ ነው? ምርታማ ሆነው
ነው የሚለውን መመለስ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ 12 ሚሊዮን ገበሬዎች በከፍተኛ ድህነት ላይ ነው ያሉት፡፡ በአለም ባንክ ሪፖርት፤
የገቢ ድህነት ያለባቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡ እሱ ብቻ አይደለም፤ የይዞታ ድህነትም አለባቸው፡፡ እነዚህ ገበሬዎች አሁን ላይ
ራሳቸውን የሚያዩት እንደመንግሥት ተቀጣሪ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ያሉበት መሬት መጥበብና ማነስ ብቻ ሳይሆን ያችም ብትሆን
በገዢው ፓርቲ ፈቃድ ስር የዋለች ናት፣ የፖለቲካ ጥገኞች ናቸው፡፡ ስለዚህ በምን ምክንያት ነው እነዚህ ሰዎች ከድህነት የወጡት?
የመሬት ይዞታቸው ጨምሯል፣ የአስተራረስ ዘይቤያቸው ተሻሽሏል፣ የምርት ግብአቶች ተሻሽሎ ነው ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ ቀንሷል
የሚለው ሪፖርት እውነት ከሆነ ደስ ይለን ነበር ግን በአይናችን እያየነው አይደለም፡፡ ምክንያታዊም አይደለም፡፡ የገዢው ፓርቲ
ኃላፊዎች ይሄን ሲናገሩ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ሊያስረዱን ይገባል፡፡ መንግሥት በ2004 የበጀት ዓመት የግብርና ምርቱም
ቀንሷል፤ የታሰበውን ያክል አይደለም የሚል መረጃም አቅርቧል፡፡
የግብርና ምርታማነት ማሽቆልቆሉ ከምን ጋር ነው የተያያዘ ነው? እንግዲህ
እነዚህ ሰዎች በአንድ በኩል የድሃው ቁጥር ቀንሷል እያሉ፣ በሌላ በኩል የግብርና ምርቱ ቀንሷል እያሉን ነው፡፡ ግን ጥያቄው
መሆን ያለበት ይህ ለምን ሆነ የሚለው ነው፡፡ ከግብርና ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ገብተናል? ወደ አገልግሎት ዘርፍ ገብተናል?
እነዚህ ናቸው ሊነሱ የሚገባቸው፡፡ አሁን ምርት ቀንሷል እያሉን ነው፡፡ ምርት በአስገዳጅነት የሚመጣ አይደለም፡፡ በአዋጅም
የሚገኝ አይደለም፡፡ በነፃ ገበያ፣ በፍላጐት፣ በአቅርቦት አርሶ አደሩ የመሬቱ ባለቤት ሲሆን፣ የግል ፍላጐቱ ሲጨምር፣ ራሱን
እንደመንግስት ተቀጣሪ ሳይሆን እንደነፃ ዜጋ መመልከት ሲችል፣ ለራሱ ጥቅም ብሎ መንቀሳቀስ ሲጀምር ነው ምርት የሚጨምረው እንጂ
ምርት በአዋጅ አይጨምርም፡፡ ዜጐች በነፃነት ሲንቀሳቀሱ ብቻ ነው ምርት ሊጨምር የሚችለው፤ በትክክል ነገሩ የገባቸው
አልመሰለኝም፡፡
ገዢው ፓርቲ ለህዝብና ለሀገር የሚበጁ ደንቦችን ማውጣት ነው እንጂ እዚህ ጋ
ስንዴ እዚያ በቆሎ ቀንሱ ብሎ ገበያ ውስጥ ገብቶ የሚያተራምስበት ስርአት እኛ የምናውቀው የለም፡፡ በዚህ መንገድ ደግሞ አንድ
አውራ ገዢ ፓርቲ ከማዕከል እስከ ቀበሌ ያስተዳድራል፡፡ ኢኮኖሚውንም እኔ በምለው መንገድ አስተዳድራለሁ በማለት ወደ ባሰ ችግር
ውስጥ እያስገባን ነው፡፡ አሁን ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የሚሉት ነገር የእሳቸው የአስተዳደር ስራ አይደለም፡፡ በእርግጥ አበዳሪ
ድርጅቶችና ሀገራት እንደሚናገሩት አይነት የገበያ ስርአት የምንመሰርት ከሆነ ይኼ የገበያው ድርሻ ነው፡፡ ይሄን በ18ኛው
ክ/ዘመን ነው አዳም ስሚዝ የተናገረው፡፡ በዚህ ነው የነፃ ገበያ ስርአት የሚተዳደረው እንጂ በአዋጅ አይደለም፡፡ በአዋጅ
ሲተዳደር ነው አሁን ያለበት ቀውስ ውስጥ የምንገባው፡፡ ስኳር በዚህን ያህል ዋጋ ትገዛለህ፣ ጤፍ ከዚህ ቦታ ትገዛለት ሲባል
ችግር አለው፡፡
ከፍተኛ መተራመስ የሚያመጣ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የማይችልበት አዘቅት ውስጥ
የሚያስገባ ነው፡፡ የግብርና ምርታማነት እንደታሰበው አለመሆኑ በአቅርቦት ላይ የሚፈጥረው ተፅእኖ እንዴት ይታያል? ከወራት በፊት
በሰማሁት ሪፖርት የግብርና ምርታችን በ5 በመቶ ጨምሯል ብለው ነበር፡፡ አሁን ምርት ከአይን እየጠፋ በመምጣቱ እንደገና ቀንሷል
እያሉን ነው፡፡ የቀሰነበትን ምክንያትም በትክክል አያውቁትም፡፡ የዛሬ ዓመት ፓርላማ በነበርኩ ጊዜ የዋጋ ግሽበት ምክንያቱ
በጥናት መታወቅ አለበት ብዬ እየጠየቅሁ ነበር፡፡ አሁንም ምርት ጨምሯልም ቀንሷልም ሲሉ ምክንያት የላቸውም፡፡ ከጥቂት ካድሬዎች
የሰሙትን ወሬ እያስተጋቡ ነው፡፡ መሰረታዊ የሆነ የምርምር ውጤት ቢኖራቸው ኖሮ የዛሬ ሁለት ወር በ5 በመቶ ጨምሯል የተባለው
አሁን ቀንሷል ሊባል አይችልም ነበር፡፡
ይሄ የምርት መቀዛቀዝና የገበያ አለመረጋጋት በህዝብ ዘንድ ሰቆቃ ሊያመጣ፣
ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ሊያስከትልና ዜጐችን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ይሄ ገዢ ፓርቲ የማክሮ ኢኮኖሚ
አስተዳደሩን ለመምራት ከፍተኛ ችግር አለበት፡፡ ከፖለቲካ አመለካከት የፀዱ ባለሙያዎች የማግኘት ችግር አለበት፡፡ ከዚያ ውጪ
ይሄንን ነገር ለማየት ካልተቻለ በአብዮታዊ ዲሞክራሲና በአንድ ገዢ ፓርቲ አመለካከት ብቻ ይሄን ሰፊ ሀገርና 90 ሚሊዮን ህዝብ
አረጋግቶ ለመምራት ያስቸግራል፡፡ እርሶ ፓርላማ በነበሩ ጊዜ ስለፊሲካልና ሞኒተሪ ፖሊሲ ደጋግመው ሲናገሩ ይደመጡ ነበር፡፡ ይሄ
ነገር ለአብዛኛው ሰው ግልፅ አይደለም፡፡ ሞኒተርና ፊሲካል ፖሊሲ ማለት ምን ማለት ነው? በእውነት ይሄን ጥያቄ በደንብ ማብራራት
የምፈልገው ጉዳይ ነው፡፡ ባለፈው ጊዜም ሆነ አሁን ያለው የሞኒተሪና ፊስካል ፖሊሲ አመራር በከፍተኛ ሁኔታ ስሜቴን የሚነካኝ
ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ እነዚህን ሃቀኛ በሆነ መንገድ ለማስተዳደር ባለመቻሉ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ የኢኮኖሚ ችግር ላይ
ጥሏል፡፡
ማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር ላይ ችግር የፈጠረውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
ገዢው ፓርቲ በፊሲካል ፖሊሲው ግብር የመጣልና የመሰብሰብ፣ አዲስ ግብር ከፋዮችን ማካተት፣ ፍትሃዊ የሆነ የግብር ስርአት
እንዲኖር ማድረግ… እነዚህ ሁሉ የስራ አስፈፃሚው ኃላፊነቶች ናቸው፡፡ ፊሲካል ፖሊሲ የሚባለው ይሄ ነው፡፡ አንድ ኃላፊነት
የሚሰማው ገዢ ፓርቲ በሚሰበስበው ግብር ይተዳደራል ማለት ነው፡፡ ሁላችንም በገቢያችን መጠን ለመተዳደር እንደምንሞክረው ማለት
ነው፡፡ ከገቢያችን በላይ የምንተዳደር ከሆነ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ በፊሲካል ፖሊሲው ያልሰበሰበውን ወይም ያላመረተውን እየበላ
ያለው ገዢ ፓርቲ ነው፡፡ ይሄ እንዴት ነው የሚገለፀው ከተባለ፣ ወደ 12 ቢሊዮን ዶላር የውጭ እዳ አለበት፣ የበጀት ጉድለቱ
ከገቢው በላይ እየተዳደረ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ የሀገሪቱ ብር የመግዛት አቅም የመጨረሻው ደረጃ ላይ ነው፡፡ ፊሲካል ፖሊሲውን
በተገቢው መምራት ያለበት ገዢው ፓርቲ፣ ይሄን በስርአቱ መምራት ሳይችል ሞኒተሪ ፖሊሲውንም ተቆጣጥሮታል፡፡ ብሄራዊ ባንክ ነፃና
ገለልተኛ ሆኖ ነው ሞኒተሪ ፖሊሲውን መምራት ያለበት፡፡ ያ ማለት ብሄራዊ ባንኩ ወደ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚገባ የገንዘብ መጠንን
ያውቃል፡፡ ዜጐች በቁጠባ ሂሳባቸው ምን ያህል ወለድ ማግኘት እንዳለባቸው ያውቃል፡፡ ያ ዜጐች ያስቀመጡትን ገንዘብ በምን ያህል
ለኢንቨስተሮች ማበደር እንዳለባቸው ያውቃል፡፡
ስለዚህ ከስራ አስፈፃሚውና ከህግ አውጭው ተፅእኖ ነፃ ሆኖ መምራት
አለበት፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ፌዴራል ሪዘርቭ ቦርድ የሚሉት ነገር አለ፡፡ ይኼ ቦርድ በነፃነት ከገዢው ፓርቲና ከህግ አውጪው
ቁጥጥር ውጪ ወደ ኢኮኖሚው የሚገባውንና የሚወጣውን የገንዘብ መጠን - የወለድ መጠን፣ የባንክ ሪዘርቭ መጠንን ቦንድ ሲሸጥ
የሚከፈል የወለድ መጠን… እነዚህን ሁሉ በሞኒተሪ ይቆጣጠራል፡፡ አሁን ይሄን በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ብናመጣው ሁለት ነፃና
ገለልተኛ የሆኑ አካሎች አሉ፡፡ አንዱ ስራ አስፈፃሚው ነው፤ ፊሲካል ፖሊሲውን የሚመራው፡፡ ሌላው ሞኒተር ፖሊሲውን የሚመራው
ብሄራዊ ባንክ ነው ማለት ነወ፡፡ እነዚህ እየተነጋገሩ፣ እየተወያዩ ሚዛናዊና ፍትሃዊ ኢኮኖሚ እንዲኖር ያደርጋሉ ማለት ነው፡፡
አሁን ግን እየሆነ ያለው ጨርሶ ሊጠግብ የማይችለው ስራ አስፈፃሚው፤ ብሄራዊ ባንኩን ብር አትም ይለዋል፣ በራሱ ተፅእኖ ስር
የወደቀ ብሄራዊ ባንክ ደግሞ ደሞዙን የሚከፍለው ማን እንደሆነ ስለሚያውቅ የሚፈልገውን ያክል ያትምለታል፡፡ ኢኮኖሚው ግን ያንን
ሊሸከም አይችልም፡፡
ስለዚህ ማነው ዋጋ እየከፈለ ያለው? ስንል የኢትዮጵያ ሸማቹ ህዝብ ነው፡፡
እንግዲህ በግልፅ ለማስቀመጥ ፊሲካል ፖሊሲ የምንለው፣ የግብር አሰባሰብና አጠቃቀም ሲሆን ሞኒተሪ ፖሊሲ የምንለው የብሄራዊ
ባንኩን ተግባራት የሚያመላክት ነው፡፡ የግብር አሰባሰቡን ማስፋት አለበት ሲባል እንዴት ነው? አሁን ከትናንሽ ነጋዴዎች ላይ
ሳይቀር ታክስና ግብር እየተሰበሰበ ነው… እንግዲህ የእኔም ፓርቲ ቢሆን ስልጣን ሲይዝ ግብር ማስከፈሉ አይቀርም፡፡ ግብር ለልማት
ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡ አስፈላጊም ነው፡፡ ዜጐች ፍትሃዊ የሆነ ግብር መክፈላቸው የሚደገፍ ነው፡፡ አሁን ችግር እየሆነ
ያለው የተሰበሰበው ግብር ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለልማት እየዋለ ነው? የሚለው ነው፡፡ ግን እንደዚህ አይነት የግሽበት አጋጣሚ
ውስጥ ስንኖር ገዢው ፓርቲ ግብር የሚከፍሉትን ብቻ ከፍተኛ ተፅእኖ ውስጥ እንዲወድቁ ማድረግ ሳይሆን የማይከፍሉት እንዲከፍሉ
መረቡን ማስፋት ነው ያለበት፡፡
ሁሉም የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ማድረግ ነው ያለበት እንጂ የተወሰኑ
የህብረተሰብ ክፍሎችን እንዲጐዱና ለመኖር እንዳይችሉ ማድረግ አይደለም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ህዝቡ እያማረረ ያለው ይሄንን
ነው፡፡ ፍትሃዊ ባልሆነ ሁኔታ ግብር ተጣለብን ነው ምሬቱ፡፡ ይሄ ደግሞ ግልፅ በሆነ መንገድ የግብር አጣጣልና አሰባሰብ ሊታይ
ይገባል ወደሚለው ይወስደናል፡፡ ድብቅ መሆን የለበትም፡፡ ሌላው ይሄ ገዢ ፓርቲ ማፅዳት ያለበት ሙስናን ነው፡፡ በተለይ ከዚህ
ከግብርና ከሌሎች ነገሮች ጋር በተያያዘ ዛሬ ከፍተኛ ሙስና እየተፈፀመ ነው፡፡ በ2009 እ.ኤ.አ ወደ 15 ቢሊዮን ዶላር ከዚች
ደካማ ሀገር ወደ ውጭ ወጥቷል የሚል ሪፖርት ቀርቦ ነበር፡፡ ይሄ የገዢው ፓርቲ ባለስልጣኖች ሊያፀዱት የሚገባ ተግባር ነው፡፡
እነሱ የሚነግሩን እዚህ ቦታ የ5 ሺህ ብር ሙስና ተፈፅሟል የሚለውን ነው፡፡ እኛ ግን ማወቅ የምንፈልገው ትላልቆቹን አሳዎች
ነው፡፡ ከተማ ውስጥ ያሉት የገዢው ፓርቲ ትላልቅ ባለስልጣኖች ምን እያደረጉ እንዳለ ህብረተሰቡ ያውቃል፤ የማን ህንፃ እንደሆነ፣
የትኛው የገዢው ፓርቲ አመራር ቦታ እንደሆነ ያውቃል፡፡ ስለዚህ ቤቱን የማፅዳት ስራ ከራሱ መጀመር አለበት፡፡
ምንጭ አዲስ
አድማስ