Saturday, November 14, 2015

በረሀብ ለተጠቁ ወገኖቻችን እንድረስላቸው !!!

November 14, 2015
def-thumbበወቅታዊ ሁኔታ ላይ የአርበኞች ግንቦት 7 የአቋም መግለጫ
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳግም ለአስከፊ ረሀብና ችጋር ተጋልጧል፤ ስፋት ጥልቀቱ በ70ዎቹና 80ዎቹ ከነበሩት ጋር ይስተካከላል ተብሎ ተፈርቷል። ከአሁኑ ሰው በረሀብ መሞት መጀመሩ ከአራትና አምስት ወራት በኋላ የሚመጣውን አደጋ ከባድነት መገመት ያስችላል።
ለአስር ተከታታይ ዓመታት ከአስር በመቶ በላይ ዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገት በማምጣት ዓለምን እየመራን ነው የሚለው ዓይን ያወጣ ውሸት፤ “ድህነትን ተረት እናደርጋለን” የሚለው ጉረኛ መፈክር፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ራድዮ “የህዳሴ ብስራቶች”፣ የአባይ ግድብና የከተማ ባቡር ግንባታ ዜናዎች ለኢትዮጵያዊው አርሶ አደር ቁርስ፣ ምሳና እራት አልሆኑም።
“አድገናል”፣ “ተመንድገናል”፣ “በምግብ ራሳችንን ችለናል” ሲል የከረመው የህወሓት አገዛዝ የረሀቡ ዜና አፈትልኮ ሲወጣ እና የዓለም መገናኛ ብዙሀን መነጋገሪያ ሲሆን የተራበውን ወገናችንን ለማብላት ከመሯሯጥ ይልቅ ተፈጥሮ ላይ ማላከኩን ተያይዞታል። ከዚህ አልፎ ዓመታዊ ድግሶቹ እና ለባለሥልጣናቱ የሚሰጡ ጥቅማጥቅሞች ጉዳይ ከረሀብ በላይ አሳሳቢ በመሆኑ 15 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ በሞት አፋፍ ላይ እያለ የአገሪቱ ሀብት ለድግስና ፈንጠዚያ እንዲሁም ለእያንዳንዱ ባለሥልጣን ቤተመንግሥት አከል መኖሪያ ቤት ማሠሪያ እየዋለ ነው። መቀሌ ላይ ህወሃት 40ኛ ልደቱን ለማክበር ወደ ግማሽ ቢልዮን ብር ባወጣ ማግስት በአማራ ስም ለወያኔ ባርነት የገባው ብአዴን 300 ሚሊዮን ወጪ በማድረግ በረሃብተኛው ሕዝብ አናት ላይ እየጨፈረ ነው:: ይህ የኢትዮጵያን ሕዝብ መናቅ ብቻ ሳይሆን ደግሞ ደጋግሞ ከመግደል የሚቆጠር ወንጀል ነው።
ለመሆኑ የአየር ንብረት መዛባት እየተደጋገመ ለሚመጣ ችጋርና ቸነፈር በቂ ምክንያት ሆኖ ያውቃልን? ለምንድነው ፍትህና ነፃነት በሰፈነባቸው አገሮች ውስጥ ዝናብ ጠፍቶ የእርሻ ምርት ቢቀንስ እንኳን ሰው በረሀብ የማይሞተው? አስከፊ የረሀብ ዜናዎች የሚሰማባቸው አገሮች በሙሉ ነፃነት የታፈነባቸው አገሮች መሆናቸውስ የአጋጣሚ ጉዳይ ነው? ለምንድነው ተደጋግሞ ከሚመጣ የረሀብ አዙሪት መውጣት ያቃተን?
የእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልስ አጭርና ቀጥተኛ ነው። ለችግሮች መፍትሄ መሻት የሚቻለው በነፃነት ማሰብ የሚችል ጭንቅላት ሲኖር ነው። በባርነት ጨለማ ውስጥ ያለ ጭንቅላት ለችግሮች መፍትሄ የማፍለቅ አቅም የለውም። እንዲያውም እንዲህ ዓይነቱ ድኩም ጭንቅላት ችግሮችን ማሸነፍ ሳይሆን ተሸናፊነትን ተቀብሎ ከችግሮች ጋር ተስማምቶና ተወዳጅቶ መኖርን ይመርጣል። ለዚህም ነው የአስተዳደር በደልና ረሀብ ምክንያትና ውጤት ብቻ ሳይሆን እጅና ጓንትም ጭምር የሆኑት።
ነፃነት ያለው ሕዝብ ረሀብን እንደሚያሸነፍ ተደጋግሞ የታየ ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው ረሀብን የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት ውጤት ብቻ አድርጎ ማቅረብ እውነትን መሸፈጥ የሚሆነው። ረሀብ የብልሹ አስተዳደር ውጤት መሆኑ ያፈጠጠ፣ ያገጠጠ ሀቅ ነው። ከረሀብ መገላገያ መንገድም የተበላሸ አስተዳደር ተወግዶ ኃላፊነት የሚሰማው፣ የዜጎች የማሰብ ነፃነት የሚያረጋግጥ ሕዝባዊ አስተዳደር ሲኖር ነው።
አገራችን ኢትዮጵያን የረሀብ ቀጠና ካደረጉ የ24 ዓመታት የወያኔ “የዘርፈህ ብላ” የኢኮኖሚ ፓሊሲ ውጤቶች መካከል አንዳንዱን ለአብነት ያህል መዘርዘር ይቻላል።
1.ገበሬና መሬት ተለያይተዋል። ኢትዮጵያዊያን አርሶ አደሮች መሬት አልባ ሆነዋል። ለም መሬቶች በኢንቨስትመንት ስም ለህወሓት ጉልተኞችና ምስለኔዎቻቸው ታድሏል፤ እነሱ ደግሞ በተራቸው ለባዕዳን ሽጠውታል። ኢትዮጵያዊው አርሶ አደር በሀገሩ ጭሰኝነት እንኳን አጥቶ ለቀን ሠራተኝነትና ልመና ተዳርጓል። በዚህም ምክንያት ገበሬው እንኳንስ ትልቁን የአየር መዛባት ትንሿንም የዋጋ ንረት መቋቋም እስከማይችልበት ደረጃ ተዳክሟል።
2.ዘርን መሠረተ ባደረገ ክልላዊ ድንበር ሳቢያ ኢትዮጵያዊው ጎበዝ አርሶ አደር አንዱ ቦታ ቢከፋ ወደ ተሻለ ቦታ ተዛውሮ ማረስ አልቻለም። ከሰሜን ወደ ደቡብ ከሄደ የአገራችን አርሶ አደር ይልቅ ባህር ተሻግሮ የመጣ ኤንቨርስተር ነኝ ባይ መሬት ማግኘት ይቀለዋል። እንዲያውም ኢትዮጵያዊው ገበሬ በዱላና በጥይት ሲባረር፤ ከባዕድ አገር የመጣው ብድርና ማበረታቻዎች ይሰጠዋል።
3.የህወሓት ባላሥልጣኖችና በየቦታው ያስቀመጧቸው ምስለኔዎቻቸው ራሳቸውን ባለሚሊዮኖች፣ ከፍ ሲልም ባለ ቢሊዮኖች አድርገዋል። እነዚህ በአንድ ጀምበር ከትቢያ የተነሱ ቱጃሮች ከገንዘብ በተጨማሪም የጄኔራልነት፣ የሚኒስቴርነት፣ የክልል ገዢነት፣ እጅግ ቢያንስ የቢሮ ኃላፊነት ሥልጣንን ኪሳቸው ውሰጥ ከተዋል። የመንግሥት ሥልጣንና ሃብት ይኸን ያህል የተቆራኙበት ሥርዓት በኢትዮጵያ ኖሮ አያውቅም። የጥቂቶች ያለአገባብና ያለቅጥ መክበር በአንፃሩ ደግሞ የብሃኑን ሕዝብ መደህየት ረሀብ እጣ ፈንታችን እንዲሆን አድርጓል።
4.በአቋራጭና በፍጥነት ለመክበር አስተማማኙ መንገድ የገዛ ራስ ጥረትና ታታሪነት ሳይሆን ቅጥፈት፣ አጭበርባሪነትና ሎሌነት ማደር መሆኑን የህወሓት አበጋዞች በተግባር እያሳዩ ሠርቶ፣ ለፍቶ ማደግ ሞኝነት እንዲሆን አድርገውታል። በዚህም ምክንያት በባህላችን ውስጥ ኮትኩተው ያሳደጓቸው አድርባይነት፣ ስንፍናና እና ልመና ችግርን የመጋፈጥ አቅማችንን ሰልበውታል።
5.ደኖቻችን ተጨፍጭፈው፣ ለም መሬታችን ተሸርሽሮ በማለቁ የግብርናችን ምርታማነት በእጅጉ ቀንሷል። በህወሓት የአገዛዝ ዘመን የደን ጭፍጨፋና የመሬት መሸርሸር በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል። አገሪቷ በፍጥነት ወደ ምድረበዳነት እየተቀየረች ነው።
6.ኢትዮጵያዊያን ገበሬዎች ድርቅን መቋቋም ስለሚችሉ ሰብሎች ወይም የአስተራረስ ዘዴዎች ማሰብ፣ መመራመርና መፈተሽ አይችሉም። አዲስ ነገር መሞከር “የኢህአዴግ የግብርና ፓሊሲን“ በመቃወም ወንጀል የሚያስቀጣ ተግባር ሆኗል። በዚህም ምክንያት ገበሬው ድርቅን መቋቋሚያ አዳዲስ ዘዴዎች መፈለግ ቀርቶ በተለምዶ የሚያውቃቸውንም መጠቀም አልቻለም።
7.የህወሓት አገዛዝ፣ እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ብዛት ሊቆጣጠር የሚሞክረው ቢሮ ውስጥ ቁጭ ተብሎ በሚደረግ የቁጥር ጨዋታ ነው። አገዛዙ ውጤታማ የስነ ሕዝብ ፓሊሲ የለውም፤ እንኳንስ የቀጣይ ዓመታት የሕዝብ እድገት ምጣኔን ሊቆጣጠር አሁን ያለነው ቁጥራችን ስንት እንደሆነ እንኳን በትክክል ሊነግረን አልቻለም፤ ረሀብ ነው መብዛታችንን እየነገረን ያለው።
አርበኞች ግንቦት 7፡ የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እነዚህና የመሳሰሉት ጭብጦችን በማንሳት የረሀቡ መሠረታዊ ምክንያት የህወሓት አገዛዝ ያሰፈነው ብልሹ አስተዳደር መሆኑን በአንጽዖት ይናገራል። ሕዝባችን በነፃነት ማሰብ፣ መመራመር፣ መፈተሽ ቢችል ኖሮ ረሀብን መከላከያ ብልሃት ማግኘት ባላቃተውም ነበር ብሎ አርበኞች ግንቦት 7 ያምናል። ረሀብን ለማጥፋት ህወሓትን ከሥልጣን ማስወገድ ከምንጊዜውም በላይ ወሳኝ የሆነ ጊዜ ላይ ተደርሶአል ብሎ አርበኖች ግንቦት 7 ያምናል።
ነገር ግን ረሀብ ጊዜ አይሰጥም። የፓለቲካ ሥርዓት ለውጥ በሞት አፋፍ ላይ ላለ ወገናችን መፍትሄ አይሆንም። ስለሆነም ለረሀቡ መሠረታዊ መፍትሄ የሆነውን ትግላችንን ሳንዘነጋ የወገኖቻችንን ሕይወት ለመታገድ የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ ያደርጋል። ሲቪክ ማኅበራት የተራበው ወገናችን የወያኔ መጠቀሚያ ሳይሆን የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚያገኝበት መንገድ እንዲያፈላልጉ እና ወገን ለወገን የሚቆምበትን ዘመቻ እንዲያስተባብሩ ጥሪ ያደርጋል። ለወገኖቻችን የሚላከው እርዳታ ከዚህ በፊት እንደነበረው ሁሉ ወደአገዛዙ ባለሥልጣኖች የግል ኪስ እንዳይፈስ ጥንቃቄ እንዲደረግ ያሳስባል። ለወገኖቻችን ለመድረስ እያንዳንዳችን በግል፤ እንዲሁም በቡድን የተቻለንን ሁሉ እናድርግ።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
ኅዳር 3 ቀን 2008 ዓ.ም.

No comments: