November 26/2013
ህዳር ፲፯(አስራ ሰባት )ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም ይህን የተናገሩት ” በክርስትና እና በእስልምና ሃይማኖት ሽፋን የሚካሄደው የፖለቲካ እንቅስቃሴ የመንግስት ቀጣዩ የምርጫ ፈተና” በሚል ርእስ ለኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ባቀረቡት ጽሁፍ ነው።
ኢሳት የሚኒስትሩን ሙሉ ንግግር የያዘ ሰነድ የደረሰው ሲሆን፣ በሰነዱ ግርጌ ላይ ” ለመደበኛ አባላት የማይነገር፣ ለከፍተኛ አመራሮች ብቻ” የሚል ተጽፎበት ይታያል። በዚህ ርእስ ስር ደግሞ ” ቀጣዩ የምክር ቤት አባላት ምርጫ የግንቦት ሰባት እና አክራሪ እስልምና ሀይሎችን የሚያስቀጥሉ አባላት ወንበሩ በኢህአዴግ አባላት ስም ሊነጠቅ ይችላል። ” ብሎአል። ሚኒስትሩ ለዚህ አስተሳሰባቸው የምርጫ 97ትን ሁኔታ እንደማጠቃሻ ተጠቅመዋል። ” የ97 የቅንጅት አሸናፊት አካሄድ ስልት ማለትም የተቃዋሚ አባላት ሁነው በህቡእ ተደራጅተው በኢህአዴግ የአባላትን ካርድ ሙሉ በሙሉ ፓርቲውን ሊጎዱት ይችላሉ” ሲሉ ሚኒስትሩ ጽፈዋል።
ሚኒስትሩ በዚህ ጽሁፋቸው፣ ቅንጅት በ97 ምርጫ ማሸነፉን እንዲሁም የኢህአዴግ አባላት ሆነው ለቅንጅት በውስጥ ይሰሩ የነበሩ ሰዎች እንደነበሩ ጠቅሰዋል። በክርስትና እና በእስልምና ሀይማኖት ሽፋን የሚካሄደውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሚኒሰትሩ በዝርዝር አቅርበዋል።
በክርስትና ሀይማኖት በኩል ” መንግስት በሃይማኖት አባቶች ሹመት ላይ እጁን ያስገባል፤ የዋልድባ ገዳም ተደፈረ፤ አልፎ አልፎ በአጋጣሚ ቤተክርስታያን ባለበት አካባቢ ከድርቅ ጋር ተያይዞ በሚነሳ ቃጠሎ ሆነ ተብሎ እንደተደረገ ማስወራት፤ ይህን የሚያግዝ የውጭ ሚዲያ መኖር ኢሳት በቀዳሚኒት ፣ የደርግ ስርዓት ደጋፊዎች የሆኑት ቪኦኤ በቀጣይነተወ የሚያራግቡት አካሄደ ጉዳዩን ትኩረት እንዲያገኝ ” ማድረጉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የሙስሊሙ እንቅስቃሴንም በተመለከተ ሚኒሰትሩ ሲገልጹ” ከቅንጅት እስከ ህብረት፣ ከቪኦኤ እስከ ቲቪ አፍሪካ፣ ከጀርመን ድምጽ እስከ ቢላል ሬዲዮ፣ ከጅሃዳዊ ሀረካት እስከ ግንቦት ሰባት፣ ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ዓለም አቀፍ እስከ መድረክ እስከ ስደተኛው ሲኖዶስ ያሉ ሀይሎች በተናጠልና በህብረት” ተሳትፈውበታል ብለዋል።
የሙስሊሙ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ፍጥነት በመዳከም ሂደት ውስጥ የገባው በቡድኑ ቀንደኛ መሪዎች ላይ ህጋዊ ስርአቱን ተከትሎ የእስራት እርምጃ ከተወሰደ በሁዋላ ነው ብለዋል።
በሃይማኖት ሽፋን የሚካሄዱ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውለው አድረው እየተጋለጡና እየተዳከሙ መሄዳቸው ባይቀርም ባለፉት ሁለት ዓመታት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን በሀይል ለመፈታተን ከሞከሩት የሁከት ሀይሎች ዋነኞቹ ነበሩ ማለት ይቻላል ብለዋል ሚኒሰትሩ።
“በሃይማኖት ስም የሚካሄደውን ንግድ ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ ረገድ የድህነት መንሰራፋትና የመልካም አስተዳደር እጦት ወይም ጉድለት ተጠቃሽ ናቸው” የሚሉት ዶ/ር ሽፈራው በተለይ ከድህነትና ኋላቀርነት መውጫውን ትክክለኛ መንገድ የሚያመላክት መሪ ድርጅት በሌለበት ፣ በሃይማኖት ሽፋን የሚነግዱ የፖለቲካ ሀይሎች አንዱን በሌላው ላይ ማነሳሳት የፅድቅ መንገድ እንደሆነ አስመስለው በማቅረብ ዜጐችን ወደጥፋት ይመራሉ” ብለዋል።
መሪ ድርጅቱም ኖሮ በአመራርም ሆነ በአባላት ደረጃ በአንድ በኩል ከፀረ ድህነትና ኋላቀርነት ትግሉ ላይ ጽናትና ብቃት ያለው አመራር መስጠት ካልተቻለ፣ በሌላ በኩል ደግም የፓርቲና የመንግስት መሪዎች ስራቸውን ከየትኛውም ሃይማኖት ገለልተኛ በሆነ መንገድና ሁሉን ሃይማኖቶች እኩል በሚያስተናግድ አግባብ ካልፈፀሙ ይኸው ችግር ተባብሶ መቀጠሉ አይቀርም ሲሉ ዶ/ር ሽፈራው አስጠንቅቀዋል።
አሁንም ድህነትና ኋላቀርነት በመኖሩ፣ በፓርቲና በመንግስት አመራራችን የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች በመኖራቸውና የእምነት ጉዳይ ለሚዛናዊ አስተሳሰብ ያለው ተጋላጭነት ዝቅተኛ በመሆኑ አልፎ አልፎ የተካረረ ፍጥጫ እያጋጠመ መሆኑንም ሚኒስተሩ በጽሁፋቸው አብራርተዋል።
ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም ለኢህአዴግ ባለስልጣናት ያቀረቡትን ሙሉ ጽሁፍ በድረገጻችን መመልከት የምትችሉ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
በክርስትና እና በእስልምና ሃይማኖት ሽፋን የሚካሄደው የፖለቲካ እንቅስቃሴ የመንግስት ቀጣዩ የምርጫ ፈተና
ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም
ህዳር 2006 ዓ.ም
አዲስ አበባ
1. በክርስትና ሃይማኖት ሽፋን የሚካሄደው የፖለቲካ እንቅስቃሴና ቀጣይ አዝማሚያዎቹ፣
በክርስትና ሃይማኖት ሽፋን የሚካሄደው እንቅስቃሴ በዋነኛነት ኢትዮጵያ የክርስትና ሃይማኖት የበላይነት ሊኖርባት ይገባል በሚል ኋላቀርና ዘመን የሻረው አስተሳሰብና ሀይል የሚመራ ነው፡፡
በዚህ መሠረት ይህ ኋላቀር ሀይል መነሻና መድረሻውን የክርስትና ሃይማይማኖትን የበላይነት አድርጐ ይህን ሊያረጋግጡልኝ ይችላሉ የሚላቸውን መፈክሮች ጐላ አድርጐ ያሰማል፡፡
በዚህ ረገድ “ኢትዮጵያ የክርስትና ደሴት ነች”፣ “አንድ አገር አንድ ሃይማኖት” የሚሉ መፈክሮቹ የአስተሳሰቡን ጭብጥ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
በዚህ ሀይል አስተሳሰብ መሠረት አገራችን በርካታ ሃይማኖቶችን ያስተናገደችና በማስተናገድ ላይ የምትገኝ አገር መሆኗ ቀርቶ የክርስቲያን ደሴት ብቻ ተደርጋ ትቀርባለች፡፡
እራሱ አንድ አገር አንድ ሃይማኖት የሚለው አስተሳሰብም በተመሳሳይ መልኩ በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሃይማኖት ብቻ እንዳለ ወይም ሊኖር እንደሚገባ የሚሰብክ ኋላቀር የፀረ እኩልነት አስተሳሰብ ነው፡፡
እነዚህ ሀይሎች አንደንዶቹ የሃይማኖት ጉዳይ ህብረተሰቡን በቀላሉ ሊያደናግርልን ይችላል ብለው የሚያምኑ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሀይሎች ሲሆኑ
ከፊሎቹ ደግሞ ከሃይማኖት አኳያ የኦርቶዶክስ እምነት መንግስታዊ ሃይማኖት መሆኑ ቀርቶ ከሌሎች ሃይማኖቶች በእኩልነት የሚታይና የሚከበር መሆኑን ያልተቀበሉ በትላንቱ ዓለም የሚኖሩ ሀይሎች ናቸው፡፡
የፖለቲካ ሀይሎቹ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የክርስትና ሀይማኖትን መጠለያ በማድረግ የተለያዩ ቀስቃሽና ስሜትን የሚኮረኩሩ የፈጠራ አጀንዳዎችን ለማራገብ የሚሞክሩ ናቸው፡፡
ለምሳሌ፡- መንግስት በሃይማኖት አባቶች ሹመት ላይ እጁን ያስገባል፤ የዋልድባ ገዳም ተደፈረ፤ አልፎ አልፎ በአጋጣሚ ቤተክርስታያን ባለበት አካባቢ ከድርቅ ጋር ተያይዞ በሚነሳ ቃጠሎ ሆነ ተብሎ እንደተደረገ ማስወራት፤ ይህን የሚያግዝ የውጭ ሚዲያ መኖር ኢሳት በቀዳሚኒት እና ቪኦኤ /የደርግ ስርዓት ደጋፊዎች/ የሚያራግቡት አካሄደ ጉዳዩን ትኩረት እንዲያገኝ አድርግውታል፡፡ ፤
በራሳቸው ፖለቲካዊ መስፈርት የቤተ ክርስቲያኒቱን መሪዎችና ሀላፊዎች መሾምና መሻር የሚፈልጉ ተቃዋሚ ሀይሎች በተለይም ደግሞ በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚ ሀይሎች የራሳቸውን ሰው አዘጋጅተው ለማስመረጥ ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡
በዛሬማ ሸለቆ አካባቢ የስኳር ልማቱ የሚካሄደው በጣም ዝቅተኛና ቆላ ላይ ሲሆን፤ የዋልድባ ገዳም መሬት ደግም በደጋና ወይናደጋ ቦታዎች ላይ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ በገዳሙና በስኳር ማሳው መካከል ያለውን ከፍተኛ የመልክዓምድር ልዩነት በቅርቡ ለማያውቁ የክርስትና ምዕመናን ሁሉ ገዳሙ ተደፈረ የሚለው ቃል እልህና የቁጣ ስሜት ይፈጥርባቸዋል ብሎ በማመን ሰፊ ዘመቻ ሲካሄድበት ከርሟል፡፡
የዚህ ዘመቻ ፊታውራሪዎች በአሜሪካን ድምጽ ሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ የቀድሞ የኢህአፓዎችና የቅንጅት ትርፍራፊዎች ናቸው፡፡
በአንድ ወቅት በምዕራብ ኢትዮጵያ ጅማ አካባቢ በኻዋርጃ ስም የሚታወቁ አክራሪዎች በክርስቲያኖች ላይ ያደረሱትን ግድያ መጠጊያ በማድረግ “ክርስቲያኖች እየተጨፈጨፉ ነው ስለዚህም አፀፋው ሊመለስ ይገባዋል” በሚል ቅኝት መንቀሳቀስ ጀምረው ነበር፡፡
አልፎ አልፎ እንደምናየውም ከድርቅ ጋር በተያያዘ ምክንያት በሚነሳ ቃጠሎ አንድ ቤተ ክርስትያን ወይም ገዳም ባለበት አካባቢ በአጋጣሚ ቃጠሎ ከተነሳ ይህንኑ ሆን ተብሎና በክርስትና ላይ ጥቃት ለመፈፀም ሲባል እንደተደረገ አስመስሎ የማቅረብ፣
እንዲሁም ለቤተ ክርስትያን መስሪያ ተብሎ ባልተሰጠ ቦታ የቤተክርስትያን ግንባታ መጀመርና ህገ ወጥ ግንባታ እንዲቆም ሲጠየቅ በክርስትና ሃይማኖት ላይ ተዘመተ ብሎ የእኩልነት ጥያቄ ማንሳት አዘውትረው የሚጠቀሙባቸው ስልቶች ናቸው፡፡
ከመንግስትና ድርጅት ሀላፊዎች ውጭ ባሉ የተሳሳተ አስተሳሰብ ባላቸው ዜጐች የሚራመዱት እነዚህ ኋላቀርና ፀረ እኩልነት አስተሳሰቦች እንደተጠበቁ ሆኖ ሃይማኖታዊ አዝማሚያ ባልተለያቸውና በመንግስታዊ ሀፊነትና በእምነታቸው መካከል ያለውን ልዩነት በውል መገንዘብ የተሳናቸው ሀላፊዎች ደግሞ የየራሳቸውን ስህተት ሲሰሩ ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ ወቅታዊና ለፖለቲካ ንግድ የሚያመች እንዲህ አይነት አጀንዳ ሲፈጠር አጋጣሚውን ለመጠቀም ምን ጊዜም ወደ ኋላ አይሉም፡፡
በክርስትና ስምና ሽፋን የሚነግዱ ፖለቲከኞች አነዚህን የመሳሰሉ መሠረተ ቢስ አጀንዳዎችን በመቅረጽና በማራገብ ክርስትና ሃይማኖት ተከብሮና ተቻችሎ በሚኖርባት አዲሲቷ ኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ክብርና ሞገሱን የተገፈፈ አስመስለው ያቀርባሉ፡፡
ለእምነቱ ክብርና ሞገስ የሌላቸው ራሳቸው በሃይማኖቱ ሽፋን የፖለቲካ ንግድ የሚያካሂዱት
ሀይሎች መሆናቸውን ደብቀው መንግስትና ስርዓቱን በመሰረተ ቢስ ወንጀል ይከሳሉ፡፡
2. በእስልምና ሀይማኖት ሽፋን የሚካሄደው የፖለቲካ እንቅስቃሴና ቀጣይ አዝማሚያዎቹ፤
በክርስትና ሀይማኖት ሽፋን ከሚካሄደው እንቅስቃሴ ባልተናነሰ ይልቁንም አልፎ አልፎ በራሱ ባህሪ ከዚያም በከፋ ሁኔታ በእስልምና ሀይማኖት ስም ሚካሄድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚታይ መሆኑ ይታወቃል፡፡
እንቅስቃሴው ውስጥ ውስጡን ሲካሄድ ቆይቶ ከቅርብ አመታት ወዲህ አክራሪነትን ለመታገል እንቅስቃሴ ሲጀመር ነው በግልጽ ፀረ ህገመንግስታዊ መልክ ይዞ መታየት የጀመረው፡፡
ከ20 ዓመታት በፊት በጨቋኙ ስርዓት ይደርስባቸው ከነበረው ግፍና በደል በዲሞክራሲያዊ ትግል ተላቀው የሃይማኖታቸውን እኩልነት ባስከበሩባት አዲሲቷ ኢትዮጵያ የሃይማኖት የበላይነትን በማስፈን ቅኝትና ከሌሎች ሃይማኖት ተከታይ ወንድሞቻቸው ጋር በመቻቻልና በእኩልነት የመኖር እድልን በሚዘጋ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱ አክራሪ ዝንባሌዎች መታየት ጀምረዋል፡፡
እነዚህ አክራሪ እንቅስቃሴዎች በዋኛነት ከሰሜን አፍሪካና ከመካከለኛው ምስራቅ አገሮች አክራሪ ሀይሎች የመነጩ፤ በአንድ በኩል የእስልምናን የበላይነት በአካባያችን ለማስፈን የሚካሄደው እቅድ ማስፈጸሚያ፤ በሌላ በኩል በሃይማኖቱ በሚነግዱ ግለሰቦችና ቡድኖች በሃገሪቱ የተፈጠረውን የእኩልነት ስርዓት በመፃረር የበላይነትን ለማሰፈን የሚካሄደው እንቅስቃሴ መገለጫዎች ናቸው፡፡
በእነዚህ አክራሪ አስተሳሰቦች የሚመሩ ጽንፈኞች መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ በመገንዘብ በሀይማኖት ሽፋን የዜጐችን ሰብዓዊ መብቶች የሚረግጡ በርካታ አስነዋሪ ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡ ነባር መስጊዶችን አቃጥለዋል፣ ነባርና ኢትዮጵያዊ መሠረት አላቸው የሚሏቸውን የሃይማኖት መጽሃፍት አቃጥለዋል፡፡
ይህን በመቃወም ለማስቆም የሞከሩ ዜጐችና የሃይማኖት ትምህርት ቤቶችንና መስጊዶችን የአመራር ቦታዎች በጉልበት ነጥቀዋል፣ ይህን የተቃወሙ ዜጐችን ሁሉ ከቤት ንብረታቸው አፈናቅለዋል፡፡ ይህ ከሞላ ጐደል አክራሪዎቹ በደረሱባቸው ቦታዎች ሁሉ የተካሄደ ነው፡፡
የመጀመሪያው ሙከራ ያነጣጠረው በኢትዮጵያ ያሉ ብዙዎቹ ነባር ሃይማኖቶች ሁሉ መሠረታቸው መካከለኛው ምስራቅ መሆኑ እየታወቀ መንግስት አህባሽ የሚባል ሃይማኖት ከውጭ አመጣብን የሚለው መከራከሪያ ውሃ የማይቋጥር ቢሆንም መንግስት ይህኛውን ወይም ያኛውን ሃይማኖት ከዚህኛው ወይም ከዚያኛው አገር በብድር የሚያመጣበት ምክንያትም ሆነ ሎጂክ አልነበረውም፣ የለውምም፡፡ ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ በውጭ ገንዘብ ድጐማ የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ሀይሎች ባላቸው አቅመ ሁሉ በመታገዝ
መንግስት አህባሽ የሚባል የውጭ እምነት አምጥቶ /በሃጂ አብዲላሂ መምህርነት የተስፋፋውን/ ሙስሊሙን ህብረተሰብ ሊጭንበት እየተንቀሳቀሰ ነው የሚል መሠረተ ቢስ ጉዳዮችን እያመጡ መንግስት በሃይማኖታችን ጉዳይ ጣልቃ ገባ ብለው ሲከሱ ሰንብተዋል፡፡ ቀላል ያልሆነ የህብረተሰብ ክፍል በተለይም ወጣት አደናግረዋል፡፡
የአስተምህሮ መሰረታቸው ብቻ ሳይሆን የየፋይናንስ ምንጫቸውም የውጭ ሀይል ለዚያውም በጣም በቅርቡ የምናውቀው መካከለኛው ምስራቅ በሆነበት ሁኔታ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ ገብነት ለመክሰስ የሚያስችላቸው ሞራላዊ ብቃት እንዴት ሊጐናፀፉ ቻሉ?
ገንዘብን በመጠቀም ነባሩን የሱፊ እምነት ለመገለባበጥ ያደረጉት ጥረትና በተወሰነ ደረጃ ያገኙት ውጤት የልብ ልብ ስለሰጣቸው ብቻ ራሳቸውን ምሉዕ በኩልሄ አገር በቀል ሌላውን ደግሞ መጤ ለማስመሰል እስከመሞከር ደርሰዋል፡፡
ደግነቱ በዚህች ዴሞክራሲያዊት ምድር አገር በቀል መሆን ወይም አለመሆን እምነትን ለማስተማር ቦታ የሌለው መሆኑ እንጅ አገር በቀል ያልሆነ እምነት ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ቦታ ሊኖረው አይገባም ቢባል ማን ይቀራል፤
ነገር ግን አዲሱቱ ኢትዮጵያ የሃይማኖት መለኪያዋ የዜጐች ምርጫ መሆን አለመሆኑ ነው፡፡ መሠረቱ ኢትዮጵያዊ፣ አፍሪካዊ ወይም የሌላ ዓለም መሆን አለመሆኑ አይደለምና ከመካከለኛው ምስራቅ አንዳንድ አገሮች በቅርቡ የገቡትን ሌሎች አስተምህሮዎች ያልከለከለችውን ያክል አህባሽም ሆነ ሌላ አስተምህሮ የዜጐች ምርጫ እስከሆነ ድረስ እንዳይገባ የምትከለክልበት አንዳችም ምክንያት አልነበረም፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ መንግስት ጉዳዩን አቃሎ በመመልከት ሰፊና አጥጋቢ ማብራሪያ ባለመስጠቱ ግን አክራሪዎቹ ፈቃጅና ከልካይ ሆነው አህባሽ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የለበትም የሚል አስተምህሯቸው የብዙዎቹን ወጣት ሙስሊሞች አዕምሮ እንዲበርዝ እድል አገኘ፡፡
ሌላው መጠቀሚያ ሊያደርጉት የሞከሩት እና የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምርጫ ነበር፡፡
መንግስት ከት/ቤቱ የፈለገው ሃይማኖትና ፖለቲካ የተነጣጠሉ መሆናቸውን በመቀበል ከማናቸውም አይነት የፖለቲካ አስተምህሮ በፀዳ አኳኋን ተግባሩን እንዲፈጽም ብቻ ነው፡፡
ተቋሙ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አክብሮ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ለማንም ተጠያቂነት በሌላቸው ወገኖች እየተመራ ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች በራቁና ለአክራሪዎች በተመቹ አጀንዳዎች ተጠምዶ ጊዜውን ሲያሳልፍ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም ይህንኑ መነሻ በማድረግ ድርጅቱ በእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሚመራና ተጠያቂነት ያለበት ተቋም እንዲሆን ተደርጓል፡፡
የሙስሊሙ ማህበረሰብ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤቶችን እንደ አዲስ መርጦ ማደራጀት እንደሚፈልግ ግልጽ ነበር – ከየአቅጣጫው በሚነሱ ጥያቄዎች፡፡ በዚህመ ሠረት ምክር ቤቶቹ በአፋጣኝ በሚካሄድ ምርጫ እንዲዋቀሩ ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ ይህ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ህገ መንግስታዊ መብት በመሆኑ መንግስት ይህንኑ ተቀብሎ፤ ምክር ቤቶቹ ለዚህ የህዝብ ጥያቄ አወንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ ከእርሱ የሚጠበቀውን ምክር ለግሷል፡፡ ምክር ቤቶቹ በአፋጣኝ በሚካሄድ ምርጫ እንዲዋቀሩ የማድረጉን ዴሞክራሲይዊ አሰራርም ደግፏል፡፡
ልክ መንግስት ጣልቃ እንደገባና ያለሙስሊሙ ህዝብ ፍላጐት መራጮች በላዩ ላይ እንደተጫኑበት በማስመሰል ሲቀሰቅሱ ከቆዩ በኋላ ከዚህ ታላቅ የዴሞክራሲ ተግባር አቋርጠው ወጡ፡፡
በውጤቱም ህዝቡ ከአክራሪነት የፀዱ የሚላቸውን ሰዎች መምረጡን አረጋግጧል፡፡ ነገር ግን ይህ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ መካሄዱ ያንገሸገሻቸው አክራሪ ሀይሎች ገና ከምርጫው ዋዜማ ጀምሮ ይህንኑ ለመቃወም ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡
ድምፃችን ይሰማ በማለት አርብ አርብ በአንዋር መስጊድና አልፎ አልፎም በሌሎች መስጊዶች ከመንግስት ጋር በከፍተኛ ደረጃ ሲፋጠጡ ከርመዋል፡፡
ከውጭ ሚዲያዎች ጋር በተቀናጀ አኳኋን በእስልምና ሃይማኖት ላይ ጥቃት የደረሰ በማስመሰል ለማነሳሳት ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡
በፖሊስና ፀጥታ አስከባሪ ሀይሎች ትዕግስት ወደ መካረርና ግጭት እንዳይመራ ተደረገ እንጂ ከሞላ ጐደል ለአንድ ዓመት ተኩል ያክል አክራሪዎቹ መንግስትን ወደ ግጭትና ደም መፋሰስ ለማስገባት ያላደረጉት ጥረት አልነበረም፡፡
በአፍሪካ ህብረት ዓመታዊ ስብሰባ ወቅት ያልተፈቀደ የሚሊዮን ሰዎች ሰልፍ ለማድረግና የአዲስ አበባን መንገዶች በመዘጋጋት አደጋ ለመፍጠር ሙከራ አድርገው ነበር፡፡ እንደዚሁም ባለፈው ክረምት አንድ ሌሊት ላይ ከቢላል መስጊድ በመነሳት አዲስ አበባ ከተማን ለማተራመስ ሞክረው ነበር፡፡
እራሱን ጀሃዳዊ ሃረካት በሚል ስያሜ ለማስተዋወቅ ጥረት ያደረግ ከነበረ የአሸባሪዎች ድርጅት ጋር በመቀናት የአንዋር መስጊዱንም ሆነ ሌሎች መሰል የነውጥ ሙከራዎች በሽፋንነት መጠቀም መርጠው ነበር፡፡
ይህም ሆኖ መንግስት ረጀም ጊዜ ወስዶ ባካሄደው ጥናትና በሰበሰባቸው ማስረጃዎች ላይ በመመስረት በቡድኑ ቀንደኛ መሪዎች ላይ ህጋዊ ስርዓቱን ተከትሎ የእስራት እርምጃ ወስዷል፡፡
ከዚህ ጊዜ በኋላ ነው ንቅናቄው በከፍተኛ ፍጥነት በመዳከም ሂደት ውስጥ የገባው፡፡
በሌላ በኩል ደግም ሃይማኖትን በሽፋንነት ለመጠቀም የሞከረው ይኸው ሀይል በተለይ በውጭ ከሚገኙ ደጋፊዎቹ ጋር በመቀናጀት አሉ የተባሉትን ፀረ ኢትዮጵያ ሚዲያዎች ከመጠቀሙም ባሻገር ከግንቦት 7 እስክ ስደተኛው ሲኖዶስ ባለ የትምክህት ሀይሎች ለመደገፍና ብርቱ ጥረት አድርጓል፡፡ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል ፈሊጥ እርስ በእርስ ተሳስረውና ተደጋግፈው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡
በማጠቃለል ሲታይ በሃይማኖት ሽፋን የሚካሄዱ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውለው አድረው እየተጋለጡና እየተዳከሙ መሄዳቸው ባይቀርም ባለፉት ሁለት ዓመታት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን በሀይል ለመፈታተን ከሞከሩት የሁከት ሀይሎች ዋነኞቹ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡
በሀይማኖት ሽፋን የሚካሄደው እንቅስቃሴ በጽንፈኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጥታ ከተደረገው የነውጥ ማነሳሰት በእጅጉ የላቀ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ምንም እንኳን ነውጠኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከ97 ውድቀታቸው በኋላ በተመሳሳይ ደረጃ ወደሚገለጽ የጐዳና ላይ ነውጥ ለማምራት በከፍተኛ ደረጃ እየተቸገሩ ቢሆኑም በሃይማኖት ሽፋን የሚካሄደውን እንቅስቃሴ በመደገፍና ነዳጅ በማርከፍከፍ ለማቀጣጠል ያደረጉትን ጥረት ጨምሮ የወቅቱ ፀረ ህገ መንግስታዊ ንቅናቄ መገለጫ የሃይማኖት ልባስ ይዞ የሚካሄደው እንቅስቃሴ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በሃይማኖት ሽፋን ለመንቀሳቀስ የተመረጠበትን ዋነኛና ደጋፊ ምክንያቶች መለየትና ከዚህም አኳያ መሠረታዊ መፍትሄ ማበጀት ይገባል፡፡
3. ሃይማኖትን በሽፋንነት ለመጠቀም የተመረጠባቸው ምክንያቶች፣
ሃይማኖትን በሽፋንነት በመጠቀም የፖለቲካ እንቅስቃሴውን ማካሄድ የመረጡት ሀይሎች የተለያየ መጠሪያ ያላቸው ነገር ግን በመሰረቱ የትምክህት ወይም የጠባብነት መፈክሮችን አንግበው ለመፋለም የሞከሩ የፖለቲካ ሀይሎች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡
ከቅንጅት እስከ ህብረት፣ ከቪኦኤ እስከ ቲቪ አፍሪካ፣ ከጀርመን ድምጽ እስከ ቢላል ሬዲዮ፣ ከጀሃዳዊ ሃረካት እስከ ግንቦት ሰባት፣ ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ዓለም አቀፍ እስከ መድረክ እስከ ስደተኛው ሲኖዶስ ወዘተ ያሉ ሀይሎች በተናጠልና በህብረት የተሳተፉበት ነው፡፡
ሁሉም ያነገቡትን ዓላማ በተለያዩ ፀረ ህገ መንግስታዊ ስልቶች በመታገዝ ለማስፈፀም ሞክረው የከሸፈባቸው ሀይሎች ናቸው፡፡
እነዚህ አላማቸውን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ በማራመድ ለስኬት መብቃት ያቃታቸው ድርጅቶችና ሀይሎች ከፍ ሲል እንደተመለከትነው የፖለቲካ ዓላማቸውን በሃይማኖት ሽፋን ማራመድ የመረጡት ይህ ስልት ምን ዓይነት እድል ቢሰጣቸው ነው ብሎ ጥያቄ ማንሳትና ጉዳዩን መመርመር በዚሁ ዙሪያ በቀጣይነት መካሄድ ያለበትን ትግል በትክክል ለመወሰን አስፈላጊ ነው፡፡
በድሃና ኋላቀር ህብረተሰብ ውስጥ በእምነት ጉዳይ ዜጐችን ብዥታ ውሰጥ መክተት ይህን ስልት ለመረጡ ወገኖች በቀላሉ ያለመጋለጥ እድል ያጐናጽፈናል፡፡ ከዚህም አለፍ ሲል ለድል ያበቃናል ብለው ማመናቸው ነው፡፡
የእምነት ጉዳይ ለሚዛናዊ አስተሳሰብ ያለው ተጋላጭነት በተነፃፃሪ አነስተኛ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
በሃይማኖት ለሚመራ ሰው ወደ ማንኛውም ድርጊት ለማምራት ማመን ብቻውን በቂ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
“በእምነትህ የመጣ ነው” ተብሎ የቀረበለትን ጉዳይ ያለማንገራገር ተቀብሎ ወደ ድርጊት ማምራት በብዙ የሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የሚታይ ክስተት ነው፡፡
ስለሆነም ይህ አካሄድ በሃይማኖታቸው ቀናዒ የሆኑ ሰዎች በሃይማኖት ሽፋን የሚራመዱ የፖለቲካ አጀንዳዎች ሰለባ ለማድረግ የተሻለ እድል ይፈጥርልናል በማለት ነው፡፡
በበለፀገው ዓለምም በአሸባሪነትም ሆነ በፀረ አሸባሪነት ጐራ ተሰልፈው የሚፋለሙ ሀይሎች ሃይማኖታዊ ጥሪ በማስተላለፍ የፖለቲካ ዓላማቸውን በሃይማኖት ግጭት መልክ ሲያስኬዱ ማየት የተለመደ ነው፡፡
የትኛውንም ጎራ በመሠረተ ቢስ እምነት ነክ ውንጀላዎች በቀላሉ በስሜት በማነሳሳት ሌላውን እንዲገጥሙ ማድረግ ይቻላል ተብሎ ይታመናል፡፡
በመሆኑም የከሰሩ ፖለቲከኞች ሁሉ ሃይማኖትን በሽፋንነት በመጠቀም መንቀሳቀሳቸው የእምነት ጉዳይ ለሚዛናዊ አስተሳሰብ ያለው ተጋላጭነት በተነፃፃሪ አነስተኛ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
በሃይማኖት ስም የሚካሄደውን ንግድ ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ ረገድ አጋዥ ሚና የሚጫወቱ ችግሮች ደግሞ ይኖራሉ፡፡ በዚህ ረገድ የድህነት መንሰራፋትና የመልካም አስተዳደር እጦት ወይም ጉድለት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በተጨባጭ እንደሚታየው በበለፀገና ሰርቶ የመጠቀም እድል በሰፋበት ማህበረሰብ ውስጥ ለጽንፈኝነት መሠረት የሚሆን ተስፋ መቁረጥ አይገኝም፡፡ ሰርቶ መክበርና ማደግ ስለሚቻል ለተስፋ መቁረጥ ምክንያት የሚሆን ችግር አይኖርም፡፡
መልካም አስተዳደር በሰፈነበት ሁኔታ ዜጐችና ህዝቦች በደስታና በስምምነት ይኖራሉ፡፡ በአንፃሩ ድህነትና ኋላቀርነት በተስፋፋበት ህብረተሰብ ውስጥ ተስፋ መቁረጥ ያይላል፡፡ ዜጐች የምድራዊ ኑሯቸውን ከሲኦል ያልተለየ አድርገው በመውሰድ በሃይማኖት ስም ለሚቀርቧቸው ሃሳዊ መሲሆች ሁሉ አመኔታቸውን ሊሰጡ ይገደዳሉ፡፡ ኢትዩጵያ በመጭው ምርጫ ፈተና ይሆንብናል፡፡
በተለይ ከድህነትና ኋላቀርነት መውጫውን ትክክለኛ መንገድ የሚያመላክት መሪ ድርጅት በሌለበት በሃይማኖት ሽፋን የሚነግዱ የፖለቲካ ሀይሎች አንዱን በሌላው ላይ ማነሳሳት የፅድቅ መንገድ እንደሆነ አስመስለው በማቅረብ ዜጐችን ወደጥፋት ይመራሉ፡፡
መሪ ድርጅቱም ኖሮ በአመራርም ሆነ በአባላት ደረጃ በአንድ በኩል ከፀረ ድህነትና ኋላቀርነት ትግሉ ላይ ጽናትና ብቃት ያለው አመራር መስጠት ካልተቻለ፣ በሌላ በኩል ደግም የፓርቲና የመንግስት መሪዎች ስራቸውን ከየትኛውም ሃይማኖት ገለልተኛ በሆነ መንገድና ሁሉን ሃይማኖቶች እኩል በሚያስተናግድ አግባብ ካልፈፀሙ ይኸው ችግር ተባብሶ መቀጠሉ አይቀርም፡፡
ከዚህ አኳያ ሲታይ ድህነትና ኋላቀርነነት እንዲሁም እነዚህን ለማስወገድ የሚያስችል ብቃት ያለው አመራር እጦት የፖለቲካ ጽንፈኝነትና የሃይማኖት አክራሪነት የሚስፋፋባቸው ለም አፈሮች ብቻ ሳይሆኑ በሃይማኖት ሽፋን የሚነግዱ ፖለቲከኞችም እንደመልካም አጋጣሚ የሚመለከቷቸው ናቸው፡፡
በመሆኑም እነዚህን ችግሮች በመፍታት በሃይማኖት ሽፋን ለሚነግዱ ፖለቲከኞች መንቀሳቀሻ አድማሱን ማጥበብ እጅግ ተፈላጊ ሆኖ ይገኛል፡
IV. በሃይማኖት ሽፋን የሚካሄደውን የፖለቲካ ንግድ በአስተማማኝ ደረጃ ለማሸነፍ ምን እንስራ?
ከፍ ሲል እንደገለጽነው ፈጣንና ህዝብ የሢቀምበት ለውጥና ብዝሃነነትን በአግባባ የማስተናገድ ችሎታተ የያለው ህብረተሰብ በመፈጠሩሪ ምክንያት በሀይማኖት ሽፋንም ሆነ በግላጭ ሲካሄድ የቆየው ጽንፈኛ እንቅስቃሴ የህዝብ ይሁንታን ሊያገኘ ባለመቻሉ ትርጉም ያለው ሁከትና ብጥብጥን ለመቀስቀስ ሳይቻለው ቆይቷል፡፡
ይህ መሠረታዊ ሃቅ አንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም ድህነትና ኋላቀርነት በመኖሩ፣ በፓርቲና በመንግስት አመራራችን የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች በመኖራቸውና የእምነት ጉዳይ ለሚዛናዊ አስተሳሰብ ያለው ተጋላጭነት ዝቅተኛ በመሆኑ አልፎ አልፎ የተካረረ ፍጥጫ የሚያጋጥመን ሆኖ ቆይቷል፡፡
ይህ ፍጥጫ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከሞላ ጐደል ሁሉንም ተፋላሚ ሀይሎች በሁለት ጐራ ከፍሎ ያፋጠጠ ሆኖ ከርሟል፡፡
ምንም እንኳን ችግሩ ለጊዜውም ቢሆን በመንግስት ታጋሽነትና አርቆ አስተዋይነት እንዲሁም በሰላም ወዳዱ ህዝብ ብርቱ ትግል የከሸፈም ቢሆን ለችግሩ መቀስቀስ ምክንያት የሆኑት ጉዳዮች በሙሉ ዛሬም በተጨባጭ ይገኛሉና ይህንን ታሳቢ ያደረገ የመፍትሄ ሃሳብ ማመላከት ተገቢ ይሆናል፡፡
1. ፀረ- ድህነትና ፀረ-ኋላቀርነት ትግላችንን እናፋፍም፣
በድህነት የተጐዳ ህብረተሰብ ሁሌም በምሬት ውስጥ የሚኖርና ከዚህ ችግር የሚያላቅቀው ትክክለኛ አማራጭ ካልቀረበለት በስተቀር በሌሎች ጽንፈኛና መሰረተ ቢስ አማራጮች ሊማለል የሚችል ነው፡፡
በተለይ ደግም በምድራዊው ህይወቱ ያላለፈለትን ህዝብ በሰማይ ቤት ያልፍልሃልና ማንኛውንም ጽንፈኛ አቋም ተግባራዊ አድርግ ለሚሉ አይነት ቅስቀሳዎች ተጋላጭ ይሆናል፡፡
ኋላቀርነትም እንደዚሁ አንድን ህብረተሰብ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር እድል በመንፈግ ለተስፋ መቁረጥና ጽንፈኝነት ሊዳርገው ይችላል፡፡
ምሬቱ የከፋና ተስፍ የቆረጠ ህዝብ ባለበት ሁሉ ጽንፈኝነት ሲስፋፋ የምንመለከተው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ይህ አዲስ ግኝት ሳይሆን ድርጅታችን ቀደም ሲል ጀምሮ የተገነዘብነውና ለመፍትሄውም የታገለለት ጉዳይ ነው፡፡
ድርጅታችንና በርሱም የሚመራው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ድህነትና ኋላቀርነት ጽንፈኝነትንና፣ ፀረ እኩልነት የሆኑ የትምክህትና ጠባብነት አዝማሚያዎችን ወዘተ ሊሸከም የሚችል ለም አፈር መሆኑን ታሳቢ በማድረግ በድህነትና ኋላቀርነት ላይ ጦርነት ካወጀ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡
ፈጣንና ብዙሃኑ ህዝቦች የሚቀጠሙበትን ልማት አስፋፍቷል፡፡
መሠረተ ሰፊና አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ገንብቷል፡፡ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ቀጣይ ትግል አካሂዶ በመስኩ ከፍተኛ ድሎችን አስመዝግቧል፡፡
ይህም በመሆኑ ዛሬ አገራችን ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ በፈጣንና ህዝብ በሚጠቀምበት ዴሞክራሲያዊ የእድገት አቅጣጫ እየገሰገሰች ትገኛለት፡፡
እድገታችን ፈጣንና መሰረተ ሰፊ በመሆኑም የህዝቡን ተስፋ አለምልሟል፡፡
ዴሞክራሲያችን ብዝሃነትን በማወቅና በማክበር ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በህዝቦች መካከል ፍቅርን መከባበርና መቻቻልን አጐልብቷል፡፡
የእርስ በርስ መናቆርና ከዚህም ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችል ተስፋ መቁረጥ መሰረት ተንዷል፡፡ ብዙ አገሮች በቀለም አብዮቶች ሲናጡና ከቀውስ ወደ ቀውስ ሲረማመዱ በአገራችን ሰላምና መረጋጋት እንደሰፈነ የቀጠለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
2. ወጣቱን ከስራ አጥነትና ተስፋ መቁረጥ እንታደግ?
አብዛኛውን ጊዜ በስሜት የሚያነሳሱ ጉዳዮች በቀላሉ ተጽዕኖ የሚያሳርፉት በወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ነው፡፡
በተለይ ወጣቱ ለስራ አጥነት፣ ጥራት ለሌለው ትምህርት፣ ከተደራጀ ፖለቲካዊ ተሳትፎ መገለልና ለመልከም አስተዳደር የሚያመች ሁኔታ ባልገጠመው ወቅት ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ አቀራረቦች በደካማ ጐኑ ለመግባት የተሻለ እድል ያገኛሉ፡፡
በአገራችን በተለይ ከ97 ዓ/ም ድህረ ምርጫ ቀውስ በመማር የወጣቱን የልማትና የተጠቃሚነት፣ የመልካም አስተዳደርና የተሳትፎ ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት ያደረግነውና የተሳካ ውጤት ያገኘነውም በመሰረቱ ለስራ አጥነትና ለተስፋ መቁረጥ የተጋለጠ ወጣት ሊኖርበት የሚችለውን ተጋላጭነት በማስወገድ ንቁ የአገር ገንቢ ለማድረግ ነው፡፡
ወጣቱ ያለበትን የመነሻ ካፒታል ችግር በከፊልና የራሱን ተሳትፎ ባረጋገጠ አኳኋን ልንቀርፍለት፣ የመስሪያና የመሸጫ ቦታዎችን ገንብተን በማቅረብ ለልማታዊ ጥረቱ የተሻለ ሁኔታ ልናመቻችለት ይገባናል፡፡
በገጠርም በግብርናና ከግብርና ውጭ በሚካሄዱ ልማታዊ ሰራዎች ተሳትፎውንና ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ይገባናል፡፡
ከዚህ ጐን ለጐን ወጣቱ ትውልድ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በሚካሄደው ትግል ዋነኛ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ተጠናከሮ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡
ይህ ሲሆን ብቻ ነው ወጣቱ ሚዛናዊ አስተሳሰብ እንዲይዝ ለማድረግ የምናደርገውን አስተምህሮ በቅን ልቦና ተመልክቶ ሊቀበል የሚችለው፡፡
3. የመንግስትና ፓርቲ አመራርን ሃይማኖታዊ ገለልተኝነት እናጠናክር፣
ህዝቡ ለመብቱና ለጥቅሙ የሚያደርገውን ትግል በትክክለኛ መስመር ለመምራት የተነሳው ድርጅታችንም ሆነ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስታችን የብሄርና የሃይማኖት ልዩነት ሳያደርግ አላማውን የተቀበሉና መንግስታዊ ተልዕኮን ለመፈፀም ዝግጁ የሆኑ ታጋዮችንም ያሰባስባል፡፡
ይህም በመሆኑ ድርጅታችንም ሆነ ልማታዊ መንግስታችን የተለያዩ እምነቶች ተከታዮች የሚሳተፉባቸው ተቋማት እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
ይህ መሠረታዊ የግል እምነትን የማክበርና የማስከበር ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ድርጅታዊ አመራርን የማረጋገጥም ሆነ መንግስታዊ አገልግሎትን የመስጠት ጉዳይ ከሃይማኖት /ከራስህም እምነት ጭምር/ ገለልተኛ በሆነ መንገድ መካሄዱን ማረጋገጥ ይገባል፡፡
ዜጐችና የተለያዩ እምነት ተከታዮች ከድርጅት የሚያገኙት አመራርና ከመንግስት የሚያገኙት አገልግሎት በእኩልነት ከሀይማኖት ገለልተኛ በሆነ መንገድ ሊፈፀም ይገባዋል፡፡
በየደረጃው የሚገኙ ሀላፊዎች ከዚህ አኳያ በተጨባጭ ከሚፈፀሙ ገለልተኝነትን ለድርድር ከሚያቀርቡ ስህተቶች መጽዳታቸውን ማረጋገጥ ይገባል፡፡
4. የህገ መንግስታዊና ሚዛናዊ አስተሳሰብ ትምህርትን ማስፋፋት፣
ሆን ብለውና እያወቁ በሀይማኖት ሽፋን የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ጥረት የሚያደርጉ ወገኖችን ከተሳሳተ አቅጣጫቸው በትምህርት መመለስ አይቻልም፡፡
እነዚህ ጥቅማቸውን በጥገኛ ወይም የኪራይ ሰብሳቢ መንገድ ለማሳካት የሚንቀሳቀሱና ለዚህም የቆረጡ ናቸው፡፡
ስለሆነም ተጋልጠው የፖለቲካ ተፅዕኖ የማሳረፍ አቅማቸው እንዲዳከምና የማታ ማታ ደግሞ ተነጥለው ወደ ዳርቻ እንዲገፉ /marginalized/ ማድረግ ብቻ የሚጠይቁ ወይም የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ስለሆነም ስለህገ መንግስታዊና ሚዛናዊ አስተሳሰብ አስተምህሮ ስናነሳ ለእነዚህ እንደማይሆን በመገንዘብ ጭምር ነው፡፡
ህገ መንግስታዊና የሚዛናዊ አስተሳሰብ ትምህርት ከማንም በላይ የሚያስፈልገውና የሚጠቅመው ከልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ተጠቃሚ ለሆኑት ብዙሃን ህዝቦች ነው፡፡
ስለሆነም ለራሳችን ማህበራዊ መሰረቶች በህገ መንግስታዊ ስርዓታችን ላይ ግልጽነት፣ እምነትና ስርዓቱን ከአደጋ የመጠበቅ ቁርጠኝነት እንዲያዳብሩ የሚያግዝ ትምህርት ልንሰጥ ይገባናል፡፡
እያንዳንዱ ዜጋ በማንኛውም ጉዳይ ላይ አቋም ከመውሰዱ በፊት ለምን? ለማንና መቼ? እንዴትና የት? ወዘተ የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን በማንሳት መመርምር እንደሚገባው ማስተማር ይገባናል፡፡
እነዚህን ጥያቄዎች በማንሳት የህዝብንና የአገርን ጥቅም የሚጐዳን ማናቸውም ጉዳይ መቃወም፣ የሚጠቅመን ጉዳይ ደግሞ መደገፈ እንዳሚገባ ማስተማር ይገባል፡፡
ሌላው ሰው አድርጐታል በማለትና በመንጋ ቅኝት በመመራት አቋም መውሰድ እንደማይገባ ይልቁንም አያንዳንዱ ሰው ራሱን ችሎና በህሊናው አመዛዝኖ አቋም መውሰድ እንዳለበት ማስተማር ይገባናል፡፡
በአንድ በኩል ከእያንዳንዱ ሚዛናዊ አቋምና ተግባር በሌላ በኩል ደግሞ ከእያንዲንዱ ሚዛናዊነት የጐደለው አስተሳሰብና ተግባር ተፈላጊውን ትምህርት መስጠትና የሚዛናዊ አስተሳሰብን የበላይነት ማረጋገጥ ይገባናል፡፡
5. በሃይማኖት ሽፋን የሚነግዱትን ሀይሎች በቀጣይነት ማጋለጥና መሰረት ማሳጣት፣
ü እነዚህ ተግባራት በትክክል ከተፈፀሙ አክራሪነትንና ጽንፈኝንት ከማሸነፍ አኳያ ረጅም ርቀት እንደሚወስዱን አያጠያይቅም፡፡ ይህም ሆኖ ብቻቸውን በቂ ናቸው ሊባሉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ በሃይማኖት ሽፋን የሚነግዱ ጽንፈኞችን ሁሉ በማጋለጥ ትግል ሊደገፉ የሚገባቸው ናቸው፡፡ ከዚህ ትግል ውጭ የምናገኛቸው ውጤት ምሉዕነት ሊኖረው የሚችል አይደለም፡፡
ህዝቡ ህይወቱን በሚመለከቱ መሠረታዊ ጉዳያች ላይ ሁሉ ብቁ፣ ዝርዝርና ወቅታዊ መረጃ እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡
የመንግስትን እቅዶችና አፈፃፀም እንዲሁም በአፈፃፀም ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችና መልካም አጋጣሚዎችን የሚመለከት መረጃ ለህዝቡ በፍጥነትና በግልጽ ማቅረብ ይገባናል፡፡
ከዚህ አኳያ በየመስሪያ ቤቱና በየድርጅት ጽ/ቤቱ ያሉትን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊዎች አደረጃጀቶች በብቃት ማንቀሳቀስ ይጠበቅብናል፡፡
ይህን የማጋለጥና መሠረታቸውን የመናድ ስራ እየሰራን አስፈላጊ ሆኖ በተገኘበት ደረጃና መጠን ደግም ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ይገባናል፡፡
እነዚህን በተናጠልና በድምር በመፈፀም በሃይማኖት ሽፋን የሚካሄዱ አፍራሽና አክራሪ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን በተሟላ አኳኋን አይሳነንም፡፡
ለመደበኛ አባላት የማይነገር ፤ ለከፍተኛ አመራሮች ብቻ
ቀጣዩ የምክር ቤት አባላት ምርጫ የግንቦት ሰባት አና አክራሪ እስልምና ሃይሎችን የሚያስቀጥሉ አባላት ወንብሩ በኢህአዴግ አባላት ስም ሊነጠቅ ይችላል፡፡
የ97 የቅንጅት አሸናፊነት አካሄድ ስልት ማለትም የተቃዋሚ አባለት ሁነው በህቡእ ተደረጅተው በኢህአዴግ የአባላትንት ካርድ ሙሉ በሙሉ ፓርቲው ሊጎዱት ይችላሉ፡፡