ከብርሃኑ ተስፋዬ
የሰይጣኑን ሙት ኣመት ለማክበር በሚዘጋጁበት ወቅት ወያኔዎች ሆዳም ዲያስፖራዎችን ወደ ኣዲስ ኣበባ ጋብዘው ቡራ ከረዩ የሚሉበት ሁኔታ ስለገረመኝ ነው ይህን ጽሁፍ ለንባብ የማቀርብላችሁ። በመሆኑን መልካም ንባብ።
መነሻ
በመጀመሪያ የሰው ልጅ ከትውልድ ቀየው ወደ ተለያዩ ቦታ ወይም የኣለም ክፍሎች የሚሰደደው ኣንድም በሃገሩ ባለው የፖሊቲካ፣ የሶሽያልና የኢኮኖሚ ሁኔታ ኣለመመቻቸት ነው ቢባል ማጋነን ኣይሆንም። እውነቱና ሀቁም ይህ ሆኖ ሳለ የተሰደደበት ችግር በሚቀረፍበት ጊዜ ኣንድም በኣካል ኣሊያም በሃሳብ፣ ማቴሪያል፣ ወይም በገንዘብ ለሃገሩ ኣስተዋጾ ያደርጋል። ይህንን ኣይነት ሁኔታ ሊፈጠር የሚችለው ግን በተሰደደበት ወቅት የነበረው የመንግስት ስርኣት ሲቀየር የሚከተላቸው ፖሊሲዎች ዲያይስፖራውን እንደ ኣንድ ኣገር ገንቢ ኣካል ቆጥሮ በእኩልነት ማሳተፍ የቻለ እንደሆነ ነው።
በኣንድ ጥናት እንደሚያሳየው በአሜሪካ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ፣ ጋናና ዚምባዌ ዲያስፖራ አባላት(2010) በ2009 ብቻ የኣመታዊ ምርታቸውን 6.5 ፣ 7.5ና 34.4 በመቶ ወደየሃገሩ ተልኩዋል። ይህም ባንድ በኩል ከዲያስፖራው ወደ ሃገር ከሚገባው የክህሎት፣ የፖሊቲካ፣ የባህልና ሶሺያል ካፒታል በተጨማሪ የተገኘ ነው ቢባል ማጋነን ኣይሆንም።
ይህን በመነሻ ያነሳሁት ለመንደርደሪያ ይሆን እንጅ ዋናው ሃሳቤ ይህን ሃሳብ ይዤ ለመሙዋገት ኣይደለም። ሆኖም የዲያስፖራውን ሃይል ባግባቡ መጠቀም የሚፈልጉ መንግስታት ካሉ ያለውን እምቅ ሃይል ለማመላከት ብቻ ነው።
መረማመጃ
ኣሁን በኣለም ላይ ተበትኖ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ኣንድም የጉጅሌው ሰለባ የነበረ ወይም በነበረው የፖሊቲካ ኣመለካከቱ ሳይደነብር በሃገሩ መኖር ያልቻለ ስብስብ ነው ቢባል ማጋነን ኣይሆንም። ይህን ስል ግን በቅርብ ጊዜ በስወር ለስለላ የተሰማሩ የጉጅሌው ኣባላት የሉም ለማለት ኣይደለም። እነዚህ ግን ኣምላክ ምስጋና ይግባዉና የጉጅሌው መሪ ተብየ በሞተ ማግስት በየድንኩዋኑ ሙሾ ሲወርዱ ስላገኘናቸው እርቃናቸውን ለማስቀረትና መስመራቸው ወዴት እንደሆነ መለየት ተችሉዋል። ከነሱ በተጨማሪ በጉጅሌው ተሳደድን ተገረፍን መብታችን ተገፈፈ ብለው ይጮሁ የነበሩ ሆኖም ትንሽ ትንፋሽ ሲያገኙ ማንነታቸው ገሃድ የወጡ የሆዳም ስብስቦች ኣደባባይ ወጥተዋል። በመሆኑም ነው ባሁኑ ጊዜ ባለም ላይ ከተበተነው ኢትዮጵያዊ ውስጥ ሆዳሞች ብቻ ተለይተው ወደ ሃገር ለበኣል የታደሙት።
ማንም ሰው ወደ ሃገሩ በመሄድ ቤተዘመዱንም ሆነ የተወለደበትን ቀየ ጉዋደኞቹንም ሆነ ሃገሩን መጎብኘት የለበትም የሚል እምነት የለኝም። ሆኖም ግን በውጭ ሃገር ኢትዮጵያዊነት ሲዋረድ ካዋራጆቹ ጋር ኣብሮ የሚጨፍረውን ወያኔን፣ (ሳውድ ኣረቢያ፥ ሊቢያ፥ የመን፥ሌሎች ኣረብ ሃገሮች) መልካም ገጽታ ኣለኝ ብሎ እንዲያናፍስበት የፖሊቲካ መጠቀሚያ ለመሆን ባህር ኣቓርጦ በጎርሻ በሚኖር እናት፣ ኣባት፣ ወንድምና እህት ላይ መሳለቅ ህሊናቢስ መሆን ነው።
ሌላው ኣስገራሚው ደግሞ ትላንት ጎረቤቱና የመንደሩ ገበሬ የተፈናቀለበትንና በረንዳ የተወረወርበትን ቦታ ለዚህ እኩይ ስራ እጅ መንሻነት ውሰድ ሲባል እሽ ብሎ ተቀብሎ የራሱን ፍላጎት ብቻ መመልከቱ ከሆዳምነት የመጨረሻው ሆዳምነቱን የሚያመላክት ነው።
ባሁኑ ወቅት ተሰባስበው የታደሙትን የዲያስፖራ ኣባላት በተናጠል ብንመለከት በውስጣቸው የተሰባሰቡት ኣንድም በወያኔ ድርጎ የራዲዮ ጣቢያ፣ የውይይት መድረክ ኣልያም ወያኔ ከህዝብ በዘረፈው ሀብት መዋእለ ንዋይ ተሰጥቶዋቸው ገበሬውን በማፈናቀል ቦታ የተረከቡ ናቸው። ኣንዳንዶቹም በሚኖሩበት ሃገር መንግስት ድጎማ የሚኖሩና የወር ገቢያቸወ እንኩዋን ድርጅት ለመመስረት ከወር ወር የሚያኖራቸው ኣለመሆኑን እያወቅን በሶስት ወር ሁለት ጊዜ ወደ ሃገር እንዲጉዋዙ የተደረጉ ናቸው።ይሁን እንጅ ይህ ሁኔታ ኣሁን ለምን ኣስፈለገ የሚለው መሰረታዊ ጥያቄን ማንሳት ያስፈልጋል።
ወያኔዎች ኣንድ ኣለመግባባት በመሃከላቸው በሚኖርበት ጊዜም ሆነ በሃገሪቱ ያለው ትግል ትንሽ ጉልበት ያወጣ ከመሰላቸው ጊዜ መግዣ የሚሉት ዘዴ ኣላቸው። ይህንን በ1997ቱም ምርጫ፣ ህዋህት በሚሰነጠቅበት ወቅት፣ ኣርዮስ መሪያቸው በማቀዝቀዣ በነበረበትም ሆነ ኦባማ ለጉብኝት ከመምጣቱ በፊት ያከናወኑዋቸውን ሸረኛ ስራዎች ማስታወስ ግድ ይላል። እነዚህን ነፍሱን ኣይማረዉና ለገሰ ዜናዊ ወጣት በነበረበት ጊዜ ይተኛበት በነበረው መኝታ ቤት ግድግዳ ላይ የዚያን ጊዜ ያስቀመጠውን “procratination is a theft of time” የሚል ኣባባል መቃብር ከመውረዱ በፊት ለወያኔዎቹ ጥሎ መሄዱን ያረጋግጥልኛል።በወቅቱ ይህ ኣባባል ያመለክት የነበረው የፊዳሉን ኣስተዳደር የመሬት ላራሹ መፈክርን ተግባራዊ ኣለማድረግን የሚያመላክት የነበረ ቢሆንም ከዚያ ትምህርት ቤት የተማረውን የከፋፍለው ግዛ ከ17 ኣመት በሁዋላ ተገባራዊ እንዳረገው ሁሉ ይህንንም መቃብር ይዞት ኣለመውረዱ ርዥራዦቹ እየተጠወሙበት ይገኛል።
ወያኔ ባሁኑ ጊዜ ይህ ዘዴ ኣሁን ያፈለገው በተላያዩ የውስጥና የውጭ ችግሮች መሆኑን በሚከተለው ለማሳየት እሞክራለሁ።
1. በሃገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ እየታገሉ ያሉትን ተቃዋሚዎች ለማስመመሰያነት እየተጠቀመበት ያለው ድራማ በምርጫ 2007 እርቃኑን እንዲወጣ ካደረጉት በሁዋላ ወያኔ ከህዝቡ ልብ ብቻ ሳይሆን ኣንዳንድ የራሱ ኣባላት ምን እየተደረገ ነው የሚል ጭምጭምታ መጀመራቸው ብሎም ኣንዳንድ የተቃዋሚ ድርጅት ኣባላት የወደፊቱ የትግል ኣቅጣጫ ምን መምሰል ኣለበት የሚለው ጥያቄ እያጫረባቸው መሆኑን በገሃድ እየተመለከተው በመሆኑ፣
2. በጎረቤት ሃገር ያሉ በሁለገብ ትግል የሚያምኑ ታጋዮች በመሃከላቸው ያለውን መለስተኛ ኣለመግባባት ወደ ጎን ትተው ኣይናቸውን በቀጥታ ወደ ኢላማቸው ለማነጣጠር በጋራ ለመስራት ኣንድ እርምጃ ወደፊት መጉዋዛቸው፣
3. ወያኔ ከኣለም የረድኤት ድርጅቶችና ኣበዳሪዎች ከሚያገኘው የውጭ ምንዛሪ ቀጥሎ ያለው የገቢ ምንጭ ዲያስፖራው ኣንድም ለቤተሰቡ ኣልያም በኢንቨስትመንት መልክ ወደ ሃገር የሚያስገባው ሲሆን ከዚህ ባሻገር ለዚህ ግንባታ ለዚህ ማስፋፊያ በሚል የልመና ኣቁማዳ ይዞ ሊሰበስበው ያቀደው የውጭ ምንዛሪ በትንታግ ታጋዮች በተለያዩ ኣካባቢዎች ሊሳካለት ባለመቻሉ፣
4. በሃገራችን በያመቱ 7.5 ሚሊዮን ገበሬዎች በበጎ ኣዳራጎት (safety net) ድጋፍ ይኖራሉ፣ ሆኖም ሃገሪቱ በምትከተለው ደካማና ያልተጠና የግብርና ፖሊሲ የተነሳ ራሱዋን በምግብ እህል ልትችል የቻለችው በሃይለ ማርያም ደሳለኝ ኣንደበት ብቻ በመሆኑ ባሁኑ ወቅት 4.5 ሚሊዮን ለረሃብ ኣደጋ የተጋለጡ መሆናቸው በኣለም መገናኛ መነገሩ፣
5. በተለያዩ ሜዲያዎች በሃገሪቱ የሚካሄደው የሰብአዊ መብት ረገጣና የህዝቦች ሰቆቃ የየእለት የመወያያ ርእስ በመሆኑና በሌሎችም ምክንያቶች የህዝባችንን የትኩረት ኣቅጣጫ ማስቀየስ በማስፈለጉ የተዘጋጀ ድራማ ነው።
ለዚህ ድራማና ዘፈን ደግሞ ኣጃቢ በማስፈለጉ በዲያስፖራው የተነገሩ መሰረታዊ ባይሆኑም ወቅታዊ ችግሮች በቅመምነት እንዲስተናገዱ ማድረግ ደግሞ ወያኔ የተካነበት መሆኑን ደደቢት ላይ ተነስታ ሳሞራን የጠየቀችው ኣርቲስትን ማጣቀስ ብቻ በቂ ይመስለኛል። በመሆኑም ወያኔ በውስጡ ያሉትን ኣለመግባባቶች ሽፋን መስጠት በመፈለጉና መቶ በመቶ ኣብላጫ ድምጽ ኣግኝቼ ኣሸነፍሁ የሚለውን የ2007 ምርጫ ተከትሎ ሊያዋቅር የሚፈልገውን የክልልና የዞን ምክር ቤት እስኪያዋቅር ድረስ ከምንሰማቸው ነጠላ ዜማዎች ኣንዱ ኣካል እንጅ ዲያስፖራው በጉቦ የተሰጠውን መሬትም ሆነ ንብረት ሸጦ ወደመጣበት እንደሚመለስ ወያኔም ያውቀዋል ዲያስፖራውም የለመደው ነው። ከዚህ ጋር ግን ኣብሮ መታሰብ ያለበት ይህች ዘለል ዘለል እቃ ለማንሳት ነው እንዲሉ የተለየ ቡድን ግን (ትክክለኛ ወያኔዎች) በልጅ ኣመካኝቶ ይበላሉ ኣንጉቶ እንደሚባለዉ ኣባላቶቻቸውን ለመጥቀም የተዘጋጀ መሆኑን ላፍታም መዘንጋት የለብንም።
ማሳረጊያ
ከላይ የጠቀስኩዋቸው መሰረት በማድረግ ሃሳቤን ለማጠቃለል ይረዳኝ ዘንድ ትናንት የሰማሁትን ባለ ፭ ሚሊዮን ባውንድ ኣጉዋጉዋዥ ኣብዛኛዎቻችን ስንሰማ ግር ያለን እንኖራለን ሆኖም በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ብዙ ሚሊዮኖች ቡልጋሪያ ሃንጋሪና ኡክሬይን ድረስ ተጭነው ሄደው የጦር መሳሪያ መገዛቱን ደግሞ እንረሳለን። በመሆኑም ኣሁን የተሰባሰበው የዲያስፖራ ጋጋታ ኣቅጣጫ ማስቀየሻ በመሆኑ እንደኔ ኣመለካከት ምን ቢሰበሰብ መግላሊት ኣይከፍትም ነውና ኣይናችንን ከኩዋሱ ላይ ማድረግ ብቻ ነው የሚጠበቅብን። በመሆኑም ያለን ባለን ሁሉ ትግሉ ኣንድ እርምጃ እንዲሄድ የየራሳችንን ኣስተዋጾ ማድረጉ ወሳኝነት ኣለው።
ኢትዮጵያ በልጆችዋ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች
chillalo@gmail.com