January 13,2015
በዳንኤል ተፈራ
በዳንኤል ተፈራ
ያሳለፍነው ሳምንት በሕወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ተሰልተው፣ ታስቦባቸው ይፋ ከተደረጉና አሻንጉሊቱ ምርጫ ቦርድ እንዲፈጽመው በህወሃት ሰዎች ቀጭን ትዕዛዝ ተሰጥቶት ገቢራዊ እንዳደረገው የሚጠረጠረው የፖለቲካ ጉዳይ ይፋ የተደረገበት ነበር፡፡ ይሄው ጉዳይ በአይረቤ ሰበብና በምክንያት አልባ ሁነት ግን ዳግም ከቤተ-መንግስት በወጣ ትዕዛዝ በሚመሰል መልኩ አንድነት እና መኢአድ ወደ ምርጫ ፍክክሩ እንዳይገቡ አይን ያወጣና የሰዎችን የስልጣን ብልግና ባጋለጠ መልኩ መግለጫ የሰጡበት ነው፡፡
እንደዚህ ዓመቱ ምርጫ ቦርዱ የተጋለጠበት ጊዜ አለ ብዬ አላምንም፡፡ ይሄው የምርጫ መቆመሪያ ተቋም እንደ ጫጩት ፍፁም ጠቅላላ ጉባዔ አድርገው የሚያውቁ፣ ቢሮም ሆነ ስራ አስፈፃሚ የሌላቸውን ተቃዋሚ ተብዬዎች በጉያው ሸጉጦ በኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ላይ እያላገጠ መሆኑ ሳያንስ የገዥውን ፓርቲ ኃላፊነት የጐደለው ተግባር ተቋቁመው ለሃገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እየደከሙ ያሉ ፓርቲዎችን እየገፉ ያለበት አግባብ ተቋሙን ከምርጫ መቆመሪያ ማዕከልነት ባለፈ ፋይዳ የሌለው፣ በህወሃት/ኢህአዴግ ማንቁርቱ የታነቀና የራሱ ሳንባ የሌለው ምስኪን ተቋም እንደሆነ ለመገንዘብ ይቻላል፡፡
ይሄው የተጨመደደ ቦርድ ተብየ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ገለልተኛነቱ አጠራጣሪ ቢሆንም እንደ ሰሞኑ ገለልተኛ አለመሆኑን በይፋ ያረጋገጠበት ወቅት ያለ አይመስለኝም፡፡ የውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚጠቁሙት ቦርዱ በዋናነት የሚመራው በፕ/ር መርጋ በቃና ሳይሆን በምክትልነት በተቀመጠው የትግራዩ ሰው ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሄር ነው፡፡ ለዚህም ነው በኢህአዴጉ አፈ-ቀላጤ ፍና እና ሌላው ቀላጤ ኢቲቪ በኩል ፓርቲዎችን በህገ ወጥ መንገድ መገፋታቸውን እየገለፀ ያለው፡፡ ሰውየው የቦርዱን ህገ ወጥ ተግባር ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ የሚችል ሰው ነው፡፡ ዶ/ር አዲሱ የፓርቲዎችን የፋይናንስ ክፍፍል ቀመር አዘጋጅቶ ያቀረበ፤ በዚህ ቀመርም በፓርላማ መቀመጫና በክልል ም/ቤት መቀመጫ 55% እንዲይዝ ለማሳመን የጣረ የህወሃት የቁርጥ ቀን ልጅ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም 55% ጠቅልሎ የሚወሰደው ኢህአዴግ ነው፡፡
ቦርዱ ገለልተኛ አይደለም ስንል እንዲሁ በግብታዊነት ሳይሆን ተጨባጭ መከራከሪያዎችን የማቅረብ አቅም ስላለን ነው፡፡ አንድ ወዳጄ የኢትዮጵያውን ምርጫ ቦርድ በማገዝ ከመቆሪያ ተቋምነት መገላገል እንደሚገባ ስነግረው ተስፉ በቆረጠ ስሜት ግን ደግሞ በምፀት ፈገግ ብሎ “ወዳጄ ቦርዱ እኮ ግንባሩን ከመሰረቱ ፓርቲዎች አምስተኛው ፓርቲ ነው፡፡ የሚያስፈልገው ቦርዱን ማገዝ ሳይሆን አፍርሶ እንደገና መስራት ነው፡፡ በታሪክ ከሚጠየቁ ተቋማት ግንባር ቀደሙ ነው፡፡” ነበር ያለኝ፡፡ እውነትም መፍረስ የሚገባው አይረቤ ተቋም ነው፤ ራሱን ነፃ ያላወጣና የምርጫ መቆመሪያ ተቋም እንደሆነ ግብሩ አረጋገጠ፡፡
ቦርዱ ገለልተኛ አይደለም ስንል እንዲሁ በግብታዊነት ሳይሆን ተጨባጭ መከራከሪያዎችን የማቅረብ አቅም ስላለን ነው፡፡ አንድ ወዳጄ የኢትዮጵያውን ምርጫ ቦርድ በማገዝ ከመቆሪያ ተቋምነት መገላገል እንደሚገባ ስነግረው ተስፉ በቆረጠ ስሜት ግን ደግሞ በምፀት ፈገግ ብሎ “ወዳጄ ቦርዱ እኮ ግንባሩን ከመሰረቱ ፓርቲዎች አምስተኛው ፓርቲ ነው፡፡ የሚያስፈልገው ቦርዱን ማገዝ ሳይሆን አፍርሶ እንደገና መስራት ነው፡፡ በታሪክ ከሚጠየቁ ተቋማት ግንባር ቀደሙ ነው፡፡” ነበር ያለኝ፡፡ እውነትም መፍረስ የሚገባው አይረቤ ተቋም ነው፤ ራሱን ነፃ ያላወጣና የምርጫ መቆመሪያ ተቋም እንደሆነ ግብሩ አረጋገጠ፡፡
አንድነት ፓርቲ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኢ/ር ግዛቸው በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ አንድነት በመዋቅሩ በአመራርነት የማያውቃቸው ግለሰቦች ተሰባስበው ኢ/ር ግዛቸውን የተካውን አመራር ህግ የጣሰ ለማስመሰል ጥረት ጀመሩ፡፡ የቦርዱ የፖለቲካ ቁማርም ከዚህ ሁነት ይጀምራል፡፡ አንድነትን አስቀድሞ ከምርጫው ለማስቀረት እነዚህን ተራ ግለሰቦች “ጐሽ፣ ጐሽ” ማለት ጀመሩ፡፡ እነዚህ “አንድነት ነን፣ መርህ ይከበር” የሚሉ ጥቂት ግለሰቦች የተንኮል ፖለቲካው አድራሽ ፈርሶች እንጅ በራሳቸው ምንም አይደሉም፡፡ የእነዚህ አፍራሽ ግለሰቦች ያላቸው ብቃት የሚለካው ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት ባፈነገጠ መልኩ ለመዋሸት የማይሳቀቁ፤ ተልዕኳቸውን ለመፈፀም አይናቸውን በጨው ያጠቡ የዘመናችን ባንዳዎች መሆናቸው ነው፡፡
ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው የመቆመሪያው ተቋም ሳያፍር “አመራር” እያለ የሚጠራው የማነአብ አሰፋ የሚባል የትግራይ ተወላጅ ሲሆን ዕድሜው በሃያዎቹ መጀመሪያ የሚገኝ፣ በተግባሩ ስለሚያፍር በቆብና በጃኬት ራሱን ደብቆ የሚዞር ወጣት ነው፡፡ ይሄ ልጅ አንድነት ቤት ተቀጣሪ ሆኖ ለተወሰኑ ወራት የድርጅት ጉዳይ ተላላኪ ሆኖ ሰርቷል፡፡ አንገት ደፊና አይናፋር በመምሰል የተወነው ትወና አስደናቂ ነው፡፡ የኢህአዴግ ክትትል እንዳላስቀመጠውና ስራ መቀጠር እንኳን እንዳልቻለ እንባ እየተናነቀው ለመናገር የሚችለው ይሄ ወጣት ምርጫ ሲደርስ እንዲፈነዳ ህወሃት አቀባብሎ ያስቀመጠው ፈንጂ እንደሆነ ያወቅነው ቦርዱ “አመራር” እያለ ቢሮው ጐልቶት ስናገኘው ነው፡፡ ወደ ነጥቡ ስንመለስ እነዚህ “አንድነት ነን” የሚሉ በተግባር ግን የአንድነት ወገን ያልሆኑ ስብስቦች ም/ቤቱ በደንቡ መሰረት የተካውን አመራር “ህገ-ወጥ ነው” በማለታቸው ብቻ የምርጫ መቆመሪያው ተቋም በችኮላ አንድ ደብዳቤ ለፓርቲው ፃፈ፡፡ ይሄ የመጀመሪያው ደብዳቤ ኢ/ር ግዛቸውን ፕሬዝዳንት አድርጐ የመረጠውን ጉባኤ ዕውቅና በመንፈግ ዶ/ር ነጋሶን እንደሚያውቅ የሚጠቅስ ነው፡፡ ቦርዱ በችኮላ በየዋህነት የፃፈው ደብዳቤ ለቁማሩ በጆከርነት የሚያገለግሉ ግለሰቦችን ከጨዋታ ውጭ የሚያደርግበት መሆኑን ሲረዳ ምናልባትም አለቃቸው ህወሃት /ኢህአዴግ ለአንድነት ቦርድ የፃፈውን ዝርዝር ደብዳቤ ሲመለከት ለሴራ ፖለቲካ እንደማይመች ሲረዳ በአስቸኳይ ቀይር ብሎት ይመስለኛል፡- “እሱን ደብዳቤ ተውት” ከሚል መልዕክት ጋር ሌላ 3 ነጥቦችን የያዘ ደብዳቤ ላከ፡፡
የመጀመሪያውን ደብዳቤ ተውት ያለበት ምክንያት ለአፍራሽ ተልዕኮ የተዘጋጁ ገልቱ ግለሰቦች ከጨዋታ ውጭ ስለሚሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ግለሰቦች በዶ/ር ነጋሶ የአመራር ዘመን አይታወቁም ወይም የሉም ነበርና፡፡ ባለ ሦስቱ ነጥብ ደብዳቤ ሲመጣ ግን አንድነት የፖለቲካ ዕደንድምታውን በጥንቃቄ ገምግሟል፡፡ ምነው ቢሉ ይሄ ከቦርዱ በስተጀርባ የሚደንስ አካል እንዳለ በመረጋገጡ ነው፡፡ ዳንሰኞቹ ምርጫን ለማስመሰያና ማወናበጃ እንጅ በትክክል ሊጠቀሙበት አይፈልጉም፡፡
የደብዳቤው ሦስት ነጥቦች የሚከተሉት ነበሩ አንደኛው ም/ቤቱ የጠቅላላ ጉባኤ ውክልና እንዳለውና ም/ቤቱ ፕሬዘዳንት መምረጥ እንደሚችል አብራሩ፤ ሁለተኛው የጠ/ጉባኤ ሪፖርት በጊዜ አስገቡና የመጨረሻው የጠቅላላ ጉባኤ የኮረም ቁጥር ግለጹልን የሚል ነበር፡፡ በጣም ቀላልና ተራ ጥያቄ የሚመስል ነበር፡፡ አንድነት በፍጥነት ምላሽ ሰጠ፡፡ የመቆመሪያው ተቋምም የሰጠነውን ምላሽ “በቅንነት” እንደተቀበለው ገልጾ ነገር ግን የጠ/ጉባኤ ቁጥር በደንቡ እንድናካትት የሚጠይቅ ደብዳቤ ፃፈ፡፡ በቅንነት የምትለውን ግን በቅንነት አልተመለከትነውም፡፡ ጉባኤ በፍጥነት መጠራት እንዳለበትና ምርጫ ቦርዱ የጠየቀውን አሟልተን በሙሉ ልብ ወደ ምርጫ መግባት እንደሚገባ በመታመኑ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ የምርጫ ቦርድ ተወካይ ባለበት በስኬት ተጠናቀቀ፡፡
አንድነትም ገዥዎች ባዳፈኑት የፖለቲካ ምህዳር እና ልፍስፍሱ ቦርድ ቢኖርም ህዝቡን አንቀሳቅሽ በ2007 ዓ.ም የአምባገነኑ ስርዓት ፍፃሜ ይሆናል በሚል ፅኑ እምነት ሙሉ ለሙሉ በስራ ተጠመደ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም የህዝብ ታዛቢዎችን ምርጫ በመላ ሀገሪቱ ያሉ ቢሮዎቹን በመዝጋት በንቃት ተከታተለ አጋለጠ፡፡ ህዝቡ የምርጫ ካርድ የሚወስድበትንና በካርዱ ለመጀመሪያ ጊዜ አሸናፊ የሚሆንበትን ስትራቴጂ መንደፍንና ሕዝባዊ ንቅናቄ እንደሚያስፈልግ ይፋ ማድረጉ ተከትሎ የ40 እና 50 ዓመት የመግዛት ህልም ያላቸው “ነፃ አውጭዎች” መንደር ጫጫታና ጭንቀት ፈጠረ፡፡
ይህንን ጭንቀት ለማርገብ አንድነትን ከምርጫ ጫወታ ማስወጣት እንደሚገባ ታመነበት፡፡ ለዚህ ማስፈፀሚያ የመቆመሪያው ተቋም አለ፡፡ በጠቅላላ ጉባኤው ተወካዩን የላከው ቦርዱ ሌላ ታሪካዊ ስህተት ለመስራት ደፈረ፡፡ ከቦርዱ በስተጀርባ ያሉ ዳንሰኞች ማንቁርቱን ስላነቁት ምርጫ አልነበረውም፡፡ ይሄ ተራ ጨዋታ በፋና እና ኢቲቪ ታጅቦ ለህዝብ ቀረ፡፡ ድራማው “የውስጥ ችግሮቻቸውን ካልፈቱ ወደ ምርጫ አይገቡም” የሚል ነው፡፡ የውስጥ ችግር ከማን ጋር? እንዴት? መልስ የላቸውም፡፡ ኢ/ር ግዛቸው በፈቃዳቸው ለቀው ወደ ግል ጉዳያቸው ገብተዋል፡፡ ታዲያ እነዚህ አመራር ተብየዎች እነማን ናቸው? እነዚህ የአንድነት አመራር እንዲደራደራቸውና ችግሩን እንዲፈታ የተጠየቁት ግለሰቦች በፓርቲው የአመራር መዋቅር የማይታወቁ፤ ከየመንገዱ ተለቃቅመው የመጡ ተራ ሰዎች ናቸው፡፡
ህወሃት/ኢህአዴግ በቦርዱ በኩል ይህንን ተራ ድራማ እየሰራ ያለው አንድነት ወደ ምርጫ እንዳይገባ ለመከልከል የወሰነው የፖለቲካ ውሳኔ ስጋ ለማልበስ ነው፡፡ የእርኩም ስጋ፡፡ ሁሉም በሰፈረው ቁና የሚሰፈርበት ቀን እንደሚመጣ ቅንጣት አልጠራጠርም፡፡ እየተካሄደ ያለው ሰላማዊ ትግል ከዚህ ዓይነት ተራ ድራማ በላይም ነው፡፡ ትግሉ የነፃነት የመውጣትና ተደፍቆ የመኖር ነው፡፡ ወደ ምርጫ እንገባለን ስንላቸው በዚህ ደረጃ ተርበትብተዋል፡፡ ምርጫ ቦርድም ያለውድድር ለኢህአዴግ ተጨማሪ የአገዛዝ ዘመን ለመስጠት ዝግጅቱን የጨረሰ ይመስላል፡፡ ይሄ የስርዓቱን የውድቀት ፖለቲካ የሚያሳይ ነው፡፡ የዚች ሀገር ትግል የቦርድ ወይም የሌላ ትግል አይደለም፡፡ ትግሉ በሕዝቡ እጅ ላይ የወደቀበት ታሪካዊ ወቅት ነው፡፡ ታሪካዊ ጊዜ ዴሞክራሲን እናሰፍናለን የሚሉ ሰዎች በግብራቸው ያፈሩበት ታሪክ፡፡ ይህንን በአደባባይ ቆመን የምንናገርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡
2007 ለለውጥ!!!