September 5, 2013
በሀገሬ ሰማይ ስር በሚደረገው የተቃውሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ከኢዴፓ እስከ አንድነት ፓርቲ ድረስ በመሳተፍ ለአስራ ሶስት ዓመታት ያህል የምችለውን አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ፡፡ ይህ ኩነትም የፓርቲዎችን ጓዳ ፈትሼ ግንዛቤ እንዳገኝ ስላመቻቸልኝ፣ በቀጣይ ህዝባችን የፖለቲካና ሰብአዊ መብቶቹ ተከብረው ነፃነቱን እንዳያገኝ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ የማስባቸውን ነጥቦች እንደሚከተለው ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡
1. እንደ ገዥው ፓርቲ፣ ተቃዋሚ ድርጅቶችም ከኋላቀሩ የፖለቲካ ባህላ ለማስጀመር ከመስራት ይልቅ ሳያውቁት ከዘመነ-መሳፍንት የተቀዳውን የፖለቲካ ባህል በተሻለ ተግባራዊ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ዛሬም ይታያሉ፡፡
2. የእስከ ዛሬውን የከሸፈ ሂደት የገመገመና የኢትዮጵያን ህዝብ ለአንዴና ለመጨረሻ ከተጫነበት የጭቆና ቀንበር ለማላቀቅ የሚያስችል በውል የታሰበበትና የተጠና የፖለቲካ ቀመር እጦት በተቀቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ በጉልህ ይንፀባረቃል፡፡
3. የማያምኑበትን መቃወም ተገቢ የሆነውን ያህል የየራሳችንም ህፀፆች ያለርህራሄ ማየት፣ አይቶም ነቅሶ ማውጣት ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን በተቃዋሞ ጎራ ባለነው ፖለቲከኞች ላይ ይህንን የማድረግ ችግር ይታይብናል፡፡ ህፀፆችን ቀድሞ ማየቱ ከሌላ ወገን የሚሰነዘረው ነቀፋ ምክንያቱን ለመረዳት እድል ይሰጣል፡፡ በትችት ከመሰበርም ይታደጋል፡፡
4. ከ1960ዎቹ ጀምሮ የኢትዮጵያ ፓርቲዎች መለያ ከሆኑት አንዱ ‹ግትርነት› መሆኑ አከራካሪ አይመስለኝም፡፡ ይህ ሁኔታ በፓርቲዎች መካከል ብቻ ሳይሆን፣ በራስ ፓርቲ አባላት ውስጥም የሚፈጠሩ ችግሮች ከግትርነት የሚነሱ ናቸው፡፡ ‹‹መሸነፍ››፣ ‹‹ማሸነፍ››፤ ‹‹መንበርከክ››፣ ‹‹ማንበርከክ›› በሚለው የጫወታ ህግ ታስረን በቆምንበት ስንረግጥ በአስከፊው የመከራ ዘመን እንድንቆይ አድርጐናል፡፡ ችግር የመፍቻ ስልትም ሆነ ባህል አላዳበርንም፡፡ እንዲያውም የትግሉ እንቅስቃሴ ከአገዛዙ ጋር መሆኑ ቀርቶ በእኛ መካከል ሆኗል፡፡
5. የተወሰኑ ሰዎች ‹‹በሰላማዊ ትግል›› ውስጥ ቢሆኑም ‹‹በዚህ መንገድ አገዛዙን ታግሎ ማሸነፍ አይቻልም›› የሚል እምነት ስላደረባቸው በግማሽ ልብ የሚያደርጉት ትግል ትርጉም ያለው አስተዋፆ እንዲያበረክቱ አላስቻላቸውም፡፡ ሰላማዊ ትግል ራሱን የቻለ ትልቅ እምነት መስጠትና ስነ-ምግባር ያለው መሆኑን ይዘነጋሉ፡፡
6. አንዳንድ የተቃዋሚው የትግል ጐራን የሚቀላቀሉ ግለሰቦች በስሜት ብቻ በመመራት አባል የሚሆኑበት አገጣሚ ብዙ መሆኑ ለተደራጀ ትግል እንቅፋት ሆኗል፡፡ ይህንን በምሳሌ ለማስረዳት ከአንድ የቀበሌ ካድሬ ጋር ስለተጣሉ ብቻ አባል የሚሆኑ ሰዎች፣ አገዛዙን ለመቀየር የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ከፍሎ ከማሸነፍ ይልቅ እልሃቸው ሲበርድ የውሃ ሽታ ሆነው መቅረታቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
7. አገዛዙ አንዳንድ ጠንካራ አባላትና አመራር ላይ ጥቃት ማድረስ ሲጀምር ተደናግጦ ማፈግፈጉም ሌላ ችግር ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የነፃነት ትግል አልጋ በአልጋ እንደሆነ ከመጠበቅ የሚመነጭ ይመስለኛል፡፡
8. የፓርቲ አባላት ከአመራር እስከ ተራ አባላት፣ ከገጠር እስከ ከተማ ንቃተ-ህሊናቸውን የሚያዳብሩና የርዮተ-ዓለም ትጥቆችን የሚያስታጥቁ ስልጠናዎችንና የውይይት መድረኮችን የመፍጠር ችግርም ተጠቃሽ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ድንገተኛና በቂ ዝግጅት ያልተደረገበት እንቅቅስቃሴ ይደረጋል ውጤቱም አመርቂ አይሆንም፡፡
9. የዓለም አቀፍ ሰላማዊ ትግል ተሞክሮዎችን ከኢትዮጵያ ታሪክ፣ ፖለቲካ፣ ባህል እና ተጨባጭ ወቅታዊ ሁኔታዎች አንፃር ተቃኝተው ተግባራዊ የሚያደርጉበትን ሁኔታ የመፍጠር ችግር ይታያል፡፡
10. የቁርጠኝነት ችግር፡- የአገዛዙ አውራዎች ወጥተው በመገናኛ ብዙሃን ፉከራና ቀረርቶ ሲያሰሙ ተደናግጦ ወደዋሻ መግባትና የትግሉን ሙቀት ማቀዝቀዝም እንዲሁ መፍትሄ የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡
11. በእቅድ የመመራት ችግር፡- በገዥው ፓርቲ ትንኮሳ ወይንም መግለጫ ላይ ተመስርቶ የእሳት አደጋ ስራ መስራት፡፡
12. ተቀባይነት ያለውና ህዝብ በቀላሉ የሚረዳው አስተሳሰብ፣ ታማኒነት ያለው ንግግር የተጨባጭ ተግባር ባለቤት ያለመሆን ችግር፡፡
13. ተጠራጣሪነት፡- አብሮ ታግሎ ለውጤት ለመብቃት መተማመንን መፍጠር የመጀመሪያው ተግባር ሊሆን ሲገባው መተማመን በጎደለበት ሁኔታ ፓርቲዎች አብረው ለመስራት ቢሞክሩም ሩቅ መገዝ አይችሉም፡፡ አሉባልታ ከግልፅነት ይልቅ እድል ይሰጠዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ትግሉ ያለባለቤት ይቀመጣል፡፡
14. መናናቅ፡- ጥቂት ንብረትና ጥቂት አባላት ያሏቸው ፓርቲዎች ከሌሎች ፓርቲዎች በጥቂቱ መሻላቸው ትግሉን ያጠናቀቁ ያህል ይኮፈሳሉ፡፡ በሌላ ወገን ያሉትም ጉድለቶችን በማስተካከል ወደፊት በትጋት ሊፋታ ሲገባ ስራቸውን ትትው መዘላለፍ ውስጥ ይገባሉ፡፡
15. የፓርቲ አመራሮች ታላቅ የመሆን ቅዠት፡- ከዘመነ-መሰፍንት የተቀዳው የፖለቲካ ባህላችን ብዙ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን በማስጎምዠት እንቅልፍ ይነሳናል፡፡ የፕሮግራም ሆነ የአሰራር ልዩነት ሳይኖር ለስልጣን በሚደረግ ፍልሚያ ፓርቲን የሚያህል ተቋም ለሁለት ይከፍሉታል፡፡ በቲኒኒሽ ቢሮዎች ትልልቅ ሽኩቻዎች ይደረጋሉ፡፡ ትልልቅ ስም ያላቸው አመራሮች በጥቃቅን ጉዳይና ከስልጣን ጋር በተያያዙ ችግሮች ተጠልፈው ይወድቃሉ፡፡ የማያበራ ችግርም ይፈጠራል፡፡ ዓላማችን ትልቅነት እንኳ ቢሆን ትልቅ መሆን የሚቻለው በአስተሳሰብና በተግባር ልቆ በመገኘት እንጂ በብልጣ ብልጥነት ሊቀ-መንበር ተብሎ በመሰየም አለመሆኑን ይዘነጉታል፡፡
16. የሰላማዊ ትግልን ባህሪያት የትግል ስልቶችና ግቦቹን በሚገባ አለመተንተን ወይንም ግልብ በሆነ ግንዛቤ ተመስርቶ መንቀሳቀስ፡- ከ1960ዎቹ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ የሀገራችን የፖለቲካ ትግል በሰላማዊ መንገድ ወጣ ገባ እያለም ቢሆን ተሞክሯል፡፡ በኢህአዴግ የ22 ዓመታት አገዛዝም ለቁጥር የሚያታክቱ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን ብለው ቢደራጁም አብዛኛው የትግሉን ባህሪ አለማወቃቸው በትብብር የሚመጣ ውጥን አዘግይተዋል፡፡
17. ትግሉን የህዝብ የማድረግ ችግር፡- በሀገራችን በተደረጉ የሰላማዊ ትግል ሙከራዎች ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚያነሷቸው አጀንዳዎችን የሕዝብ በማድረግ እንዲታገልባቸው ሲያደረጉ አይታይም፡፡ ትግሉ ግብ ሊመታ የሚችለው ህዝቡ በትግሉ ከልብ አምኖ መታገል ሲችል ነው፡፡ ሆኖም ወደ ህዝብ ባለመውረዱ ጥቂት አመራሮች ሲታሰሩ ወይንም ቢሮዎች ሲዘጉ ትግሉም የመዳፈን አዝማሚያ ሲያሳይ አስተውለናል፡፡
18. የተፅኖ ማዕከሎች ያለመኖር፡- ተቃዋሚ ፓርቲዎች እራሳቸው አፈና ውስጥ ሆነው የአፈና ቀንበር ለመስበር የሚሰሩ በመሆናቸው የአቅም ውሱንነቶች አለባቸው፡፡ ስለዚህ ያላቸውን የገንዘብና የሰው ሃይል አብቃቅተው የተሳካ ትግል ማድረግ ይችሉ ዘንድ የተወሰኑ የተፅኖ ማዕከላትን መፍጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ደቡብ ህበረት በ1992 ዓ.ም. ብሔራዊ ምርጫ ሃድያ አካባቢ ያደረገው ተጋድሎ ለተነሳው ሃሳብ ጥሩ ምሳሌ ይመስለኛል፡፡
19. ትኩረት የተነፈገው የፓርቲዎች የገንዘብ የማሰባሰቢያ ስትራቴጂ፡- በገንዘብ አቅርቦት ምክንያት በርካታ እቅዶች ወደተግባር ሳይለወጡ ይቀራሉ፡፡ በየክፍለ ሀገሩ ራሳቸውን ለመስዋዕትነት ያዘጋጁ አባሎቻቸውን ከማዕከል ጋር ግንኙነት እንዲኖራቸው በማድረግ ትግሉን አጠናክሮ ከመግፋት ይልቅ የቢሮ ኪራይ እንዲላክላቸው በመወትወት ጊዜያቸውን ሲያባክኑ ይታያሉ፡፡ በሂደትም እየተሰላቹ ከትግሉ ያፈገፍጋሉ፡፡ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ስትራቴጂ አዘጋጅቶ የገንዘብ ጥያቄን በማያሻማ መልኩ መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ይኽንን ማድረግ ሳይቻል በሰላማዊ ትግል ብዙ ርቀት መሄድ አይቻልም፡፡ የሚኖረው ዕጣ ፈንታ እንደአንዳንዶቹ ፓርቲዎች ጓዝን ጠቅልሎ ቀለብ ለማስፈር ለገዥው ፓርቲ ማደር ነው፡፡
ከሞላ ጎደል የኢትዮጵያን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቀይደው የያዙና ሰላማዊ ትግሉን ወደፊት አላራምድ ካሉ ችግሮች ውስጥ እነዚህ ዋነኞቹ ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ እናም ፓርቲዎቹ በሰላማዊ ትግል የኢትዮጵያን ሕዝብ የነፃነቱ ባለቤት እንዲሆን በሚያስችል መንገድ ለመምራት ከዚህ አንፃር ራሳቸውን ቢፈትሹ የተሻለ ነው፡፡
ይህንን ሀሳብ ከጠባቡ የእስር ክፍሌ የላኩት ፓርቲዎች፣ አመራሮቻቸውና አባላቻቸው እንዲዳከሙ ወይም ተነሳሽነታቸውን አኮስሼ ከጫወታ ለማስወጣት ከመፈለግ ሳይሆን የተሻ አቅምና ስትራቴጂ አዳብረው ለውጤት እንዲበቁ ብሎም የኢትዮጵያን ህዝብ ከአፈና አዙሪት ለማውጣት እንዲችሉ ከልቤ በቅንነት በመመኘት መሆኑን እንደምትረዱኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሌላው መረሳት የሌለበት እውነታ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በተለያዩ የሀላፊነት ደረጃ ባሳለፍኳቸው እስራ ሶስት ዓመታት በፓርቲም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ለታየው ድክመት እኔም ሀላፊነት የምወስድ መሆኔን ነው፡፡ እንዲሁም ካሉብኝ ውሱንነቶች አንፃር አቀራረቤ የጅምላ በመሆኑም ምንም እንኳን በአጠቃላይ የዴሞክራሲ ትግሉ ላይ በተናጠል ለውጥ ማምጣት ባይችሉም ሁልጊዜም የተሻለ የተደራጀ፣ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ አሰረራር የነበራቸው ፓርቲዎች እንደነበሩ አይካድም፡፡ እናም ሁሉንም በአንድ አይነት ደረጃ ማስቀመጥ እንዲመጣ ለምንሻው መሻሻልም በጐ አስተዋፆ እያበረክትም፡፡ በግለሰብ ደረጃ ቢሆን ሁሉንም አንድ ቅርጫት ውስጥ መወርወር ተገቢ አይደለም፡፡ ለስልጣን የማይቋምጡ፣ ቀን ከሌት ሰርተው የማይሰለቹና ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ችግር ቅድሚያ የሚሰጡ (በጣም ጥቂት ቢሆኑም) ግለሰቦች መኖራቸውን በዚህ አጋጣሚ ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡ የዚህ ፅሁፍ አላማም እንዲህ አይነት ግለሰቦች ተበራክተው ወደ ስብስብ ደረጃ እንዲደርሱ ማበረታታት ነው፡፡
የሆነ ሆኖ ከፍ ብዬ ያነሳዋቸው ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በላይ ውል አልባ ያደረጉ ችግሮችን መፍታት ለነገ የማይባል ስራ ነው፡፡ ይህን ዓላማ ከግብ ለማድረስም ከዚህ በታች የምጠቅሳቸው ነጥቦች አስፈላጊ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡
1. በየጊዜው ለምናስመዘገባቸው ለውጦች እውቅና በመስጠት በተገኘው ድልም እየተበረታታን ነፃነት እኛ እስከታገልን ድረስ በተጨባጭ የምናሳካው ግብ መሆኑን ማመን፡፡
2. አገዛዙን ለማሸነፍ ተቀዳሚው ተግባር ራሳችንን ማሸነፍ መሆኑን ተገንዝቦ ህዝብን ከስሜት በፀዳ መልኩ በሀላፊነት ስሜት ማደራጀትና ለውጤት ለማብቃት መስራት፤
3. ሰላማዊ ትግል ለውጤት የሚበቃው በዕውነት፣ በፍቅርና ከዚያም በሚመነጭ ፅናት ላይ ተመስርተን ተግባራዊ ስናደርገው መሆኑን መገንዘብ፤
4. ገዥዎች በአፈ-ሙዝ ስጋን ሊገድሉ ሲያደቡ፣ ክፉ ሃሳባቸውንና ተግባራቸውን በአሳማኝ ምክንያቶችና በተገራ ሰብዕና ላይ ተመስርቶ ለመለወጥ መስራት፡፡
5. ፍርሃትን መግደል፡- ፍርሃትን ማሸነፍ ባልቻልን ቁጥር ሰላማዊ ታጋዮች የመሆን ዕድላችን በዚያው መጠን መቀነሱ አይቀሬ ነው፡፡ የፍርሃት እስረኞች በሆንን ቀጥር አገዛዙ የጭቆና ሰንሰለቱን ለማጥበቅ ስለሚበረታ ፍርሃትን ግዴታ ማሸነፍ ያስፈልጋል፡፡ የአገዛዙን ቁንጮዎችም ሆነ ማንኛውንም ሃላፊ መፍራትና ክብሩን ማዋረድ አያስፈልግም፡፡ ትግሉ የእነርሱ አይነት የህዝብ ጌቶች ለመፍጠር ሳይሆን የህዝብ አገልጋዮችን ለመፍጠር ነውና፡፡
6. ሰላማዊ ትግል ለውጤት የሚበቃው ከበቀልና ግብታዊ ከሆኑ እርምጃዎች እራሳችንን ስናፀዳ ነው፡፡ አላማችን የማንም ክብር የማይደፈርባትና የሁላችንም ሉዓላዊነት የሚከበርባት ልጆቻችንም በኩራት የሚኖሩበትን ሀገር መፍጠር ነው፡፡
7. የአገዛዙ የአፈና እርምጃዎችና በህዝብ ዘንድ ሽብርን ለመንዛት የሚያደርጋቸው የሀሰት ዶሴዎች ለተጨማሪ ትግል መነሳት እንዳለብን የሚያስገነዝቡ እንጂ ፈፅሞ ወደኋላ እንድናይ የሚያደርጉን አለመሆናቸው፡፡
8. በየጊዜው የአቋማችንን፣ የትግል ስልታችንን ትክክለኛነት መፈተሽ በወቅቱም እርምት መውሰድ ወሳኝ ነው፡፡
9. ሁልጊዜም ቢሆን ተሳስተን ገዥዎቻችን መጠላት፣ ለበቀል መዘጋጀትም ሆነ በእነርሱ ላይ በመዛት ወደፊት በሚመጣው ንጋት ስጋት እንዲገባቸው ማድረግ አያስፈልግም፡፡ አይገባምም፡፡
10. አገዛዙ ለህዝብ ፈቃድ ለመገዛት ተነሳሽነት ሲወስድ ማበረታታት እንጂ እንደተዳከመና እንደተንበረከከ እንዲሰማው ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡
11. የኢትዮጵያን ህዝብ ለዘመናት ከስብዕና ሚዛን ያወረደውን የጭቆና ስርዓት መታገል የህይወት ዘመናችን ዓላማ አልፋና ኦሜጋ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በግለሰብ ደረጃ ያሉን ህልሞችና ጥቅሞች ሊሳኩ የሚችሉት ትልቁ ችግራችንን በጋራ ስንፈታ ነው፡፡ ሁለንተናችን አንድ ላይ የተገመደ መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት አይገባንም፡፡
12. በረጅሙ ታሪካችን ተሳክቶ የማያውቀውን የድሎች ሁሉ አውራ ማስመዝገብ የምንችለው ትግሉ የሚጠይቀውን የመስዋዕትነት ደረጃ ከወዲሁ ተረድተን በስነ-ልቦናም ስንዘጋጅ ነው፡፡ ምናልባት አንዳንዶቻችን የትግሉ ፍሬ ተቋዳሾች ለመሆንም እንደርስ ይሆናል፤ መንገዳችን ላይ መታሰርና መንገላታት ብቻ ሳይሆን ሞትም አድፍጦ ሊጠብቀን ይችላል፡፡ ይኽንንም አውቀን በቁርጠኝነት መግፋት ብቻ ነው ያለን አማራጭ፡፡
13. ሁልጊዜም በአቋራጭ እና የትግል አጋሮቻችን መስዋዕት በማድረግ ለውጤት ለመብቃት መሞከር አይገባንም፡፡ ትግላችን ግልፅነትና ንፅህና የተሟላ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ነገ ልንፈጥር የምንመኘውን መልካም ነገር፣ ዛሬ በምናደርገው መልካም ተግባሮች የተሞላ መሆን ማስመስከር አለብንና፡፡
14. የአገዛዙን ባህሪዎችና ‹‹የእግር ቆረጣ›› ስልቶች ቀድሞ በመረዳት የተጠና አፀፋዊ እርምጃ ለመውሰድ አስቀድሞ መዘጋጀትም ያስፈልጋል፡፡
15. በዘረኝነት ወጥመድ ተጠልፎ ላለመውደቅ መጠንቀቁም ተገቢ ይመስለኛል፡፡ አገዘዙ ስልጣን ላይ መቆየት እስከቻለ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ በዘረኝነት ወረርሽኝ ቢጠቀም አንዳች ቅሬታ የሚገባው አይመስልም፡፡ ያዝ ለቀቅ እያደረገ ሲንቀሳቀስ እንደምናየው ስልጣኑን የሚነቀንቅ ከመሰለው የሃይማኖት አሊያም የዘር ግጭት ቀስቅሶ መልሶ እራሱን ግጭት አርጋቢና መፍትሄ ፈላጊ አድርጐ ለማቅረብ ይሞክር ይሆናል፡፡ በእኛ በኩል ሊያዝ የሚገባው ግልፅ አቋም በየትኛውም ዘመን ቢሆን አንዱ ህዝብ ሌላውን ጨቁኖ ባለማወቁ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በየትኛውም ወቅት ቢሆን ኢትዮጵያውያን አማኞች የወንድሞቻቸውን የማምለክ ነፃነት ተጋፍተው አያውቁም፡፡
ሕዝብ በጋራ የአምባገነን መሪዎች የአፈና ሰለባ ነው፡፡ ሰውን በአስተሳሰቡ እንጂ በዘሩ መመዘን የጀመርን ቀን ያን ጊዜ ከሰብዓዊነት ሚዛን እንወጣለን፤ ከስልጣኔ ሃዲድ እንስታለን፡፡ የሰላማዊ ትግል የመጨረሻ ግብ ፍቅር፣ ወንድማማችና አስተማማኝ ነፃነት ሆኖ ሳለ ለዘረኝነት እድል በሰጠን መጠን የትግላችን አላማ ይከሽፋል፡፡ ዘረኝነት ኢሰብዓዊነት ነው፡፡ ዘረኝነት ከትንሽና ክፋት ከተጠናወተው ሰብዕና የሚመነጭ መርዝ ነው፡፡ በዘረኝነት ሰንሰለት ተጠፍንገን ለውጤት ለመብቃት ብንሰራም ፈጣሪም ከእኛ ጋር አይቆምም፤ ዓላማው በሰው ልጆች መካከል ፍቅርና አንድነት እንጂ ጥላቻና መለያየት አይደለም፡፡ ጊዜም ከእኛ ጋር አይተባበርም፡፡ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ እኩልነት፣ ነፃነትና ክብር ከልብ ስንቆም ያን ጊዜ የፈጣሪ ሀያል ክንድ ከእኛ ጋር ይሆናል፡፡
16. ሚስጥራዊነትና ሰላማዊ ትግል ጋብቻ ሊፈፅሙ አይገባም፡፡ የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ ውጤታቸውም ጭምር በይፋ ማወቅ ለሚፈልግ ሁሉ ግልፅ ማድረግ ይገባል፡፡ አገዛዙ እንኳን በሚስጥር የሚደረግ እንቅስቃሴ አግኝቶ በይፋ የሚደረጉ የትግል እንቅስቃሴዎችንም እስካልተመቹት ድረስ አይኑን በጨው ታጥቦ የሽብር ካባ እየደረበ ትግሉን ለማምከን ሲሞክር እያየን ነው፡፡ የአገዛዙ ክፉ ሃሳብና ተግባር እንዳለ ሁኖ ግልፅነት በህዝብና በትግሉ መካከል ያለውን ቁርኝት ያጠብቀዋል፡፡ ህዝቡም የፕሮፓጋንዳ ሰለባ እንዳይሆን ይረደል፡፡ ስለዚህ በምንም አይነት መልኩ ከመጋረጃ ጀርባ የሚደረጉ የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴዎች ሊኖሩ አይገባም፡፡
17. የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴዎች ትኩረት በማዕከል በሚደረግ ዝግጅት ብቻ ሳይሆን በየአካባቢው ያሉ አባላት አጠገባቸው ባሉ አመራሮች አማካኝነት በተጨባጭ ችግሮች፣ በእውቀትና በጥሩ ዝግጅት ላይ የተመሰረቱ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ሲችሉ ለትግሉ ግብዐት ይሆናሉና፡፡ ሌሎች የፓርቲ ቅርንጫፎችም ከእነርሱ ተሞክሮ እንዲወሰዱ ማድርግ በተቻለ መጠንም በየቦታው ያሉ አባላትና ነዋሪው ህዝብ ስለሰላማዊ ትግል ተጨባጭ ትምህርት በመቅሰም እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
18. የሰላማዊ ትግል ፈርጦች የሆኑት ማህተመ ጋንዲና ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር በተለያየ ወቅት የተናገሩትን ተመሳሳይ ይዘት ያለውን ሃሳባቸውን አፅንዎት ሰጥተን ልንወስደው ይገባል፡፡ ማህተመ ጋንዲ ‹‹ማንም ሰው ያለፈቃዱ አንዳች ነገር እንዲያደርግ ምንም አይነት ምድራዊ ሃይል ሊያስገድደው አይችልም፡፡›› ሲሉ፣ ዶ/ር ኪንግም ‹‹እስካልተጐነበስን ድረስ ማንም ሊጋልበን አይችልም፡፡›› ማለቱ ይታወሳል፡፡ ይህ አንድ አይነት መልዕክት የሚያስተላልፈው የሁለቱም የነፃነት ታጋዮች አባባል በየትኛውም ሀገር በጭቆና ቀንበር ስር ለሚማቅቅ ህዝብ የሚሰራ እውነታ ነው፡፡ ስለዚህም ከቆምንለት ህዝባዊ፣ ዴሞክራሲያዊ መንግስት የተመሰረተባት የወንድማማችነት፣ የፍቅርና የነፃነት ማማ የሆነች ሀገር የመገንባት ግባችን ሊመልሰን የሚችል አንዳች ሃይል እንደሌለ ተገንዝበን በፅናትና በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይገባናል፡፡
እንደ መውጫ
ከመተኛት አልፎ እንደ ልብ መንቀሳቀስ በማይቻልበት ጠባብክ የእስር ክፍሌ ሆኜ ጎኔን ወለል ላይ፣ ጆሮዬን ወደምድር አስጠግቼ ልዳበስውና ልጨብጠው የማልችለውን ድምፅ ላደምጥ ሞከርኩ፤ እናም የአለፈው እና የአሁኑን የዘመን ዱካ ከእነአፈ እና ግሳንግሱ እየራቀ ሲሄድ፤ የመጭው ዘመን የነፃነት ድምፅና ጭቆናን የማይቀበል ትውልድ ኮቴ እየቀረበ ሲመጣ ይሰማኛል፡፡ ይህ ድምፅ ዕውን እንዲሆን ጊዜውም እንዲፈጥን፣ አባቶቻችን የዳር ድንበር ነፃነት ለማስከበር እንደዘመቱት እኛም የሰላም፣ የፍቅር፣ የወንድማማችነትና የፅናት ሰይፍ ታጥቀን የመትመም ለነገ የማያድር ሀላፊነት አለብን፡፡
ጉዞአችን ምንም ያህል አዝጋሚና በውጣ ውረድ የተሞላ ቢሆንም የምንወዳትን አዛውንት ሀገራችንን ከዘመናት የስቃይ ፅንሷ ነፃነትን የምትገላገልበት ወቅት ስለመቅረቡ ለሰከንድም አልጠራጥርም፡፡ የሐምሌና ነሐሴ ድቅድቅቅ ጨለማ፣ አጥንት ሰብሮ የሚገባ ብርድ ያኮራመታቸው እፀዋት በመስከረም ወር ከአፅናፍ አፅናፍ በሚዋኘው የብርሃን ጅረት ሁለንተናቸው ተፍታቶ ለአይን የሚማርኩ የተፈጥሮ ፀጋዎች መሆናቸውን በኩራት እንደሚያውጁ ሁሉ፣ ኢትዮጵያውያንም ዕድሜ ጠገቡን የአገዛዝ ቀንበር ከጫንቃችን አውርደን በመጣል፣ ሀገራችን ከዳር ድንበር ነፃነት ጋር ብቻ ተያይዛ የምትጠቀስ አለመሆኗን በተጨባጭ በማረጋገጥ በኩራት በሀገራችን መኖር እንጀምራለን፡፡ ሀገራችን የሰብዓዊ ክብር ማማ የምትሆንበት ዘመን እነሆ እየገሰገሰ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ያ ዘመን በመሬታችን ሲደርስ ‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና…›› የሚለውን የኩኩ ሰብስቤ ዜማ ከተወሰኑ የግጥም ማስተካከያዎች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን ከልብ መዘመራችንም አይቀሬ እንደሆነ አምናለሁ፡፡
አዛውንቷ ሀገራችን የሰብዓዊ ክብር ማማ፣ ‹‹የአፍሪካ ገናና›› ትሆን ዘንድ ነፃነትን በእርጋታ፣ በትዕግስትና አስተዋይነት በተሞላበት ሁኔታ የምናዋልድ ጥበበኛ ሀኪሞ ልንሆን ይገባናል፡፡ ሀገራችን በተለያየ ወቅት ነፃነትን ብታረግዝም ፅንሱን ከእነነፍሱ ለማዋለድ እስከዛሬ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ያልተሳኩ ነፃነትን የማዋለድ ጥረቶችም በባለታሪኳ ሀገራችን ላይ አገዛዙ እረግጦ በመግዛት ለመቀጠል የሚያደርገው የሞት ሽረት ትግል ሲጨመርበት፣ ሀገራችንን ፈፅሞ ወደ ማንመኘው የውድቀት አፋፍ ይዟት እንዳይወርድ ጥብቅ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡ ይኽን ማድረግ ካልቻልን በምክንያት የማንመራ፣ በስሜትና ኋላቀርነት አረንቋ የምንዳክር ልጆቻችን የሚያፍሩብን፣ መጭው ትውልድ የሚወቅሰን አባቶች እንዳንሆን ስጋቴ ፅኑ ነው፡፡
ስለዚህ በድቅድቁ የጭቆና ሌሊት ላይ ለዘላለም የማትጠልቅ የነፃነት ፀሐይ እስትከሰት ትግላችን ሊቀጥል የገባዋል፤ በድቅድቁ የአፈና ሌሊት ጨረቃ ያለማቋረጥ እስክትሰለጥን ጤፍ የሚያስለቅም ጣፋጭ ፍቅር የሚያስኮመኩም፣ ዜጐች ያለአንዳች ስጋት የሚመላለሱበትና የዱር አራዊትም ጭምር ለአደን ያለመከልከል እንዲወጡ የሚያስችል ብርሃኗን በምድራችን ላይ እስክትረጭ ትግላችን ከቀድሞ በበለጠ ደረጃ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፤ ሀገራችን የረጅም ዘመን እርግዝናዋን በሰላም ተገላግከላ የምድር ሁሉ ፈርጥ እስክትባል ድረስ የነፃነትንና የወንድማማችነት ንጋት የተራባችሁ ኢትዮጵየውያን ሁሉ የፍቅርና የፅናት ዝናራችሁን ታጥቃችሁ ትግላችሁን ቀጥሉ፡፡ አዎ! ነፃነት እንደቀትር ብርሃን ፍቅርም እንደሃይለኛ ጅረት የሀገራችን ምድር ሞልቶ ይፍሰስ!! ነፃናት፣ ነፃነት፣ ነፃነት፤ እደግመዋለሁ አሁንም ነፃነት!!!