‹አሜሪካ የመጣሁት ከቃሊቲ ስለሚሻል ብቻ ነው›› ዳዊት ከበደ (የቀድሞው የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር)
‹‹አሜሪካ የመጣሁት ከቃሊቲ ስለሚሻል ብቻ ነው››
ዳዊት ከበደ
የቀድሞው የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር
በ97 ዓ/ም. በሀገራችን ተከስቶ በነበረው ፖለቲካዊ ቀውስ ሣቢያ ለእስር ከተዳረጉ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወራት እስር በኋላ በሂደት አውራምባ ታይምስ ጋዜጣን በየካቲት ወር 2ዐዐዐ ዓ.ም. አቋቁሞ ማሳተም ጀመረ፡፡ የሲፒጄ የ2ዐ1ዐ የኘሬስ ነፃነት ዓለም አቀፍ ተሸላሚ የነበረው – ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ፡፡ ህዳር 9 ቀን 2ዐዐ3 ዓ/ም. ግን “ይቅርታዬ ተነስቶ እንድታሠር በመወሰኑ ከፍትህ ሚኒስቴር አስተማማኝ ምንጭ መረጃ አገኘሁ” በማለት ከሀገሩ ወደ አሜሪካ መሰደዱ ይታወሳል፡፡
ኤልያስ ገብሩም ለቀድሞው የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ በተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄ በማንሣት ተከታዩን ቃለ-ምልልስ አድርጓል፡፡
አድዋ እንደተወለድክ አውቃለሁ፤ እስቲ ስለትውልድህና ስለልጅነት ህይወትህ ጠቅለል አርገህ ንገረኝ፡፡ አድዋ በመወለድህስ ምን ይሰማሀል?
በቅድሚያ እድሉን ስለሰጣችሁኝ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ያው የተወለድኩት አድዋ
ነው፡፡ ያደግኩት ደግሞ አዲስ አበባ፡፡ አንዳንድ ሰዎች አድዋ መወለዳቸውን ብቻ እንደ ትልቅ ስኬት አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ እኔ ግን አይታየኝም፡፡ ሰው ፈልጎ ባመጣው ነገር ነው መኩራት ያለበት፡፡ እውነትም ፈልጌና መርጬ አድዋ ብወለድ ኖሮ እንደ ስኬት እቆጥረው ነበር፡፡ በተረፈ ከተወለድኩ በኋላ ነው የት እንደተወለድኩ ያወቅኩት፡፡ ስለዚህ አጋጣሚ እኔ የተወለድኩበት አካባቢ የተወለዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያን ለ21 ዓመታት ስለመሩ የዚህ ኩራቱ አይታየኝም፡፡ ከዛ ይልቅ መኩራት ያለብኝ አድዋ ላይ በተሰራው የጥቁር ህዝቦች ታላቅ ታሪክ ነው፡፡ ያ ታሪክ ደግሞ በሌላ የኢትዮጵያ ክፍልም ብወለድ ኖሮ ኩራቱ እኩል ነው የሚሰማኝ፡፡
ጋዜጠኝነትን መቼ ጀመርከው? ወደዚህ ሙያ እንድትገባስ ምክንያት የሆነህ ምንድነው?
ጋዜጠኝነትን መቼ እንደጀመርኩት ከመናገር ይልቅ፤ ለሙያው ትኩረት መስጠት የጀመርኩት ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ መናገሩ ይሻላል፡፡ የጋዜጠኝነት ፍቅር በውስጤ ማደር የጀመረው ገና የአራት አመት ልጅ እያለሁ ጀምሮ ነው፡፡ በወቅቱ ምንም የማውቀው ነገር ባይኖርም አባቴ አንድ አነስተኛ ሬዲዮ ይዞ የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በተመስጦ ሲሰማ በጣም ይገርመኝ ነበር፡፡ እና አስታውሳለሁ፡- በወቅቱ ለእኔ በጣም አስገራሚ የነበረው ‹‹እንዴት ነው የሰው ልጅ በእንደዚህ አይነት ትንሽዬ ነገር ውስጥ ሆኖ (ሬዲዮውን እያየሁ ማለት ነው) ሊያወራ የሚችለው›› የሚለው ነገር ነበር፡፡ ደግሞም በነገሩ ተገርሜ ዝም አልልም” አባቴንም እጠይቀው ነበር፡፡ ታዲያ ሁሌ እሱ በተመስጦ ሲሰማ እኔ ደግሞ ያንኑ ተመሳሳይ ጥያቄ ደጋግሜ እየጠየኩ ሳስቸግረው አንድ ቀን ‹‹ስማ ጋዜጠኞች ናቸው፤ የሚያወሩት እዚህ ውስጥ ገብተው ሳይሆን ሌላ ቦታ ሆነው ነው፡፡ ስለዚህ እንደነሱ መሆን ከፈለክ ትምህርትህን ጠንክረህ ተማር!›› አለኝ፡፡
ከዛ በኋላ በትምህርት ቤት ግጥም ማንበብ፣ የተለያዩ ክበባት ውስጥ መግባት፣ ሚኒ ሚዲያ መሳተፍ ጀመርኩ፡፡ 12ኛ ክፍል ጨርሼ የማትሪክ ውጤት እስኪመጣልኝ ድረስ ባለው የክረምት ወር ከአዲስ አበባ ማስታወቂያ ቢሮ የሦስት ወር የጋዜጠኝነት ስልጠና ወሰድኩ፤ እግረመንገዴንም በአንዳንድ ጋዜጦችና መጽሄቶች ጽሁፍ እንዲወጣልኝ መስጠት ጀመርኩ፡፡ ከዚህ በኋላ የማትሪክ ውጤት መጣ፡፡ የመጣው የማትሪክ ውጤት በመንግስት የትምህርት ተቋም ሊያስገባኝ የሚችል ቢሆንም እኔ ግን ሁሌ የማስበው ጋዜጠኝነት ብቻ ስለነበረ በወቅቱ የጋዜጠኝነት ትምህርት የሚሰጠውን ዩኒቲ ኮሌጅ መርጬ ገባሁ፡፡ እና በዚህ መልኩ ነው ወደ ሙያው የገባሁት፡፡
በጋዜጠኝነት ህይወትህ ውስጥ የገጠመህን ፈተናና ውጣ ውረድ ብትገልጽልን? (ከሐዳር ጋዜጣ ጀምሮ እስከ ፊኒክስ – አሪዞና ድረስ የነበረህን ጉዞ ብትነግረን)
እንግዲህ ፈተና ሲባል ከትልቁ ነው መጀመር ያለብኝ፡፡ እኔ መጀመሪያ ያጋጠመኝ ፈተና ትልቁ ፈተና ነው፡፡ እስኪ አስበው በአንድ የክስ መዝገብ ውስጥ በስድስት የተለያዩ ክሶች መከሰስ ብቻ ሳይሆን” የእያንዳንዱ ክስ ቅጣት ደግሞ እድሜ-ልክ እና ሞት የሚያስፈርድ ሲሆን ምን አይነት ፈተና ብለህ ትጠራዋለህ? የ1997ቱን ፈተና ዱብ እዳ ከማለት ውጪ ምን ትለዋለህ፡፡ ደግሞም ከዛ በፊት ታስሬ አላውቅም፡፡ አንዳንዴ ፕሬስን የመሰለ ተቋም በአንድ አገር ሊኖረው የሚገባው ሚና እጅግ በጣም ትልቅ ቢሆንም” ይህ አይነቱ ተቋም ድምጥማጡ እንዲጠፋ የሚያደርግ ፍጹማዊ ስልጣን በጣም ጥቂት በሆኑ ግለሰቦች እጅ ውስጥ ገብቶ እንዳሻቸው ሲጫወቱበት ታያለህ፡፡ ሙያውና ሙያተኛው የሚተዳደርበት ህግን የሚያረቁት እነሱ፣ ሙያተኛም ተሰብስቦ እስር ቤት እንዲገባና በሞት እንዲቀጣ አቃቤ ህግ ሆነው የሚከራከሩት እነሱ፣ የአለም የፕሬስ ቀን በተከበረ ቁጥርም ይሁን በተለያዩ ኮንፈረንሶች ተገኝተው ‹‹የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ያላቸው የኤዲቶሪያል ነጻነት ለአለም ሁሉ ምሳሌና ትምህርት ይሆናል›› የሚል ስብከት የሚሰብኩትም እነሱ ናቸው፡፡ አየህ ኢንዱስትሪው ኃላፊነት እንዲሰማው ለማድረግ ሁሉንም የሚያስማማ ግልጽ የሆነ ተቋማዊ አደረጃጀትና ሁሉም በእኩል የሚስተናገዱበት ጽኑ መሰረት ያለው የህግ ማዕቀፍ ሊኖር ይገባል፡፡ አለበለዚያ ግለሰቦች እንዳሻቸው በታማኝነት አሊያም በቂም በቀል ውሳኔ የሚያስተላልፉበት፤ በየጀበና ቤቱ ማን ፍቃድ ሊነጠቅ እንደሚገባ፣ ማን መባረር እንዳለበት የሚወስኑበት አገር ነው ያለን፤ ያሳዝናል፡፡
ጥያቄውን በትክክል አልመለስክልንም?
ያው ስለውጣ-ውረድ ነው እየጠየቅከኝ ያለኸው፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ አሪዞና ድረስ ያለውን መንገድና ውጣ-ውረድ መዘርዘር አቅቶኝ አይደለም፡፡ ከዚህ ሁሉ ውጣ-ውረድ እና እንቅፋት በስተጀርባ ያለው መነሻ ምክንያት ምን እንደሆነ ነው መታወቅ ያለበት፡፡ አውራምባ ውስጥ ዘገባዎችን ሚዛናዊ ለማድረግ ምን ያህል ርቀት ስንጓዝ እንደነበር ታውቃለህ፡፡ ያንን እያደረግን ግን የግል ጥላቻ የነበራቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ በመንግስታዊ መዋቅር ውስጥ ያላቸው ‹‹ስልጣን›› ደግሞ የግል ጥላቻቸውን ለማራመድ ምቹ ነበር፡፡ እናም ያላቸውን ኔትወርክ ተጠቅመው ሳንወድ በግዳችን ከጨዋታው እንድንወጣ አደረጉን፡፡ ከኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት እስከ ፍትህ ሚኒስቴር፤ በጉዳይ ፈጻሚነት ከሚያገለግሏቸው የግል ሬዲዮኖች፤ እስከ መንግስታዊው አዲስ ዘመን ድረስ ተረባርበው ስራቸውን ሰሩ፡፡ ከዛ ደግሞ ክራቫታቸውን አሳምረው በኪሳራ እንደዘጋነው ሊሰብኩ አለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ ወጡ፡፡ ስለዚህ የውጣ-ውረዱ ማጠንጠኛ እዚህ ላይ ነው ያለው፡፡
አሁን ባለህበት አገር አሜሪካ ኑሮን እንዴት እየገፋኸው ( እየመራኸው) ነው? ለመሆኑ ምግብ ታበስላለህ?
ማንም እንደሚያውቀው ተገድጄ ነው የወጣሁት፡፡ በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት አሜሪካ የመጣሁት ከቃሊቲ ስለሚሻል ብቻ ነው፡፡ የመንግስት ደጋፊ የሆኑ ወዳጆቻችን እንደሚሉት ሰው የሚሰደደው የተሻለ ኑሮ ለመኖር ነው፡፡ እኔ ያየሁት የተሻለ ኑሮ ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ከሙያዬ ውጪ ሌላ ስራ እንኳን መስራት አልፈልግም፡፡ በመንፈስ ደረጃ ስደትም ሌላ እስር ቤት ነው፡፡ እንደምታውቀው ከአገሬ የወጣሁት በ 2004 ህዳር ወር መጀመሪያ ላይ ነው፡፡ ሁኔታዎች ይሻሻላሉ በሚል ተስፋ እስከ መጋቢት ድረስ የ‹‹አሳይለም›› (የጥገኝነት) ጥያቄዬን አላቀረብኩም ነበር፡፡ በኋላ ግን የግድ የሚዲያ ስራውን ስደት ላይ ሆኜ መቀጠል ስለነበረብኝ ህጋዊ የሆነ ማዕቀፍ ውስጥ ለመግባት ‹‹አሳይለም››(ጥገኝነት) ከመጠየቅ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበረኝም፡፡ ስደት ካከበድከው ይከብዳል” ካቀለልከውም ይቀላል፡፡ ምግብ አበስላለሁ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ሲሰለቸኝ ውጭ እመገባለሁ፡፡
እንደሚታወቀው አሁን ድረ-ገፅ አቋቁመሃል፤ ስራው አንዴት ነው? (ከጋዜጣ ስራ የሚለይበት ነገርስ ምንድን ነው?)
የድረ-ገጽ ስራ ከጋዜጣ ይለያል፡፡ ጋዜጣ በሳምንት አንዴ ነው የሚታተመው፡፡ ድረ-ገጽ ግን በየሰዓቱ የሚፈጠሩ አዳዲስ ነገሮችን እየተከታተልክ ማቅረብ የግድ ይላል፡፡ ሌላ ዌብ ሳይት ቀድሞ ሳያወጣው የመጀመሪያ ለመሆን የምታደርገው ትንቅንቅ ደስ ይላል፡፡ ለምሳሌ ከዌብሳይቶች መካከል የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ህልፈት፤ የአቶ መለስን ዜና እረፍት (ከኢቲቪ ቀጥሎ) ቀድሞ ያወጣው ዌብሳይት አውራምባ ነው፡፡ ለምሳሌ ኦባማ በድጋሚ ተመረጡ ተብሎ በቀጥታ (ላይቭ) ሲነገር በ1 ደቂቃ ከ 15 ሴኮንድ ውስጥ ዜናውን ፖስት በማድረግ አውራምባ የመጀመሪያው ነው፡፡ የእድል ጉዳይ ሆኖ የአውራምባ ድረ-ገጽ በተመረቀ በሁለት ወር ውስጥ ነው ከፍተኛ ጎብኝ ካላቸው አንጋፋ ድረ-ገጾች መካከል አንዱ ለመሆን የበቃው፡፡ የዳያስፖራ የፖለቲካ ሙቀት ከምትገምተው በላይ ነው፡፡ ነገሮችን በኃላፊነት መንፈስ መርምረህ ገለልተኛ የሆኑ አቋሞችና አመለካከቶችን መያዝ ካልቻልክ ፈታኝ ነው፡፡ ልክ አገርቤት ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ መዘገብ የለብህም›› የሚሉ አምባገነኖች እንዳሉ ሁሉ፤ እዚህም በተመሳሳይ መልኩ እኛ የምንፈልገው ነገር ብቻ ነው መቅረብ ያለበት የሚሉ ‹‹የዳያስፖራ ሽመልስ ከማሎች›› አሉ፡፡ ልክ አገር ቤት ጸያፍ ስድብ የሚሳደቡ የሬዲዮ ጣቢያ ባለቤቶች እንዳሉ ሁሉ እዚህም በመልክም በተግባርም እነሱን የሚመስሉ በሌላ ጽንፍ የተሰለፉ የፓልቶክ አድሚኖች አሉ፡፡ ይገርምሀል እንዲሁ ፈርዶብን የአምባገነንነት ችግር የትም ቦታ ነው የሚያጋጥመን፡፡ እጅ ላለመስጠት ቁርጠኛ መሆን ግን ግድ ይላል፡፡
ከዲሲ ወደ ኦሪዞና ግዛት ለምን ሄድክ? (ብዙ ኢትዮጵያውያን ካሉበት መራቁ ለስራህ ጥሩ ነው?)
አዎ! ዲሲ ብዙ ኢትዮጵያዊያን አሉ፡፡ የብዙ ፖለቲከኞችና ቲፎዞዎቻቸው መፈንጫ፤ የብዙ ፍላጎቶች መናኸሪያም ነው፡፡ ብዙ ዝግጅቶች፣ በርካታ ሰላማዊ ሰልፎችና ኮንፈረንሶችም ይከናወንበታል፡፡ ይህ ማለት ግን አገር ቤት ለሚደረገው ትግል አሊያም እንዲመጣ ለምንፈልገው ፖለቲካዊ መቻቻል የሚኖረው ፋይዳ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጽንፍ የያዘ የፖለቲካ አማራጭ አሉታዊ እንጂ አዎንታዊ ውጤት የለውም፡፡ ገና ለገና ነጻነት ያለበት አገር ላይ ነው ያለነው ተብሎ የሚደረገው ልቅ የሆነ የመጠፋፋት ዘመቻ፤ ገና በዳዴ ላይ ላለው የፖለቲካ ባህላችን መራዥ የሆነ ሚና ነው የሚኖረው፡፡
ስለዚህ ከዲሲ ወደ አሪዞና የመጣሁበት ዋናው ምክንያት ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እዚሁ አሪዞና ስቴት ዪኒቨርስቲ ትምህርቴን ለመቀጠል አንዳንድ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች እያሟላሁ ነው፡፡
የዳያስፖራውን ኑሮ፣ ማህበራዊ-ህይወትና፣ ፖለቲካ እንዴት ተመለከትከው? በተለይ ፖለቲካ አራማጆቹ የፅንፈኝነት ደረጃቸውን እንዴት ትገልጸዋለህ? የዳያስፖራ ፖለቲካ ሲባል ሚዲያዎቹንም ይመለከታልና አያይዘህ ብትመልስልኝ፡-
እንደው አለመታደል ሆኖ የፖለቲካ ባህላችን ከ1960ዎቹ ጀምሮ የጽንፍ ፖለቲካ ነው፡፡ የኢህአዴግ ደጋፊዎችም ሆኑ ተቃዋሚዎች በእኩል ደረጃ ሁለት ጫፍ ይዘው ነው ሲጠዛጠዙ የምታያቸው፡፡ ፍልሚያው ደግሞ በኢህአዴግና በተቃዋሚዎች መካከል ብቻ የሚቆምም አይደለም፡፡ አንዱ ተቃዋሚ ሌላውን በወያኔነት ለመፈረጅ ያለው ጥድፊያ ብዙ መጽሐፍ ይወጣዋል፡፡ <የአንድን ሰው የፖለቲካ አቋም ለመፈረጅ ብሄሩን ጠንቅቀህ ማወቅ በቂ ነው> ባዬች ብዙ አሉ፡፡ አንዳንዴ አገር ቤት ያለው እንዴት አይነት ስልጡን ህዝብ ነው ትላለህ፡፡ ሁለቱም ወገን ጋር የምትመለከተው ‹‹እኔ ጋ ካልሆንክ ጠላቴ ነህ›› አይነት አጥፊ ድምዳሜ ነው፡፡
ሚዲያዎቹም የዚህ አይነቱ አሰላለፍ ሰለባዎች ናቸው፡፡ በተለይ እዚህ የምታየው አስቀያሚ ነገር የፖለቲካ ልዩነትን የብሄር ካባ አልብሶ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ያለው ሩጫ ተአምር ነው፡፡ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ‹‹ጸባችን ከስርዓቱ ጋር ነው” ከትግራይ ህዝብ ጋ አይደለም›› ሲል ትሰማውና ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ‹‹አጼ ዮሐንስም እኮ ለአካባቢያቸው ተወላጆች ነበር ስልጣን የሚሰጡት፤ እነ ብርሀነ መስቀልና እነ ተስፋዬ ደበሳይም ለትግራይ የበላይነት ነው ሲታገሉ የኖሩት›› ሲሉ ትሰማቸዋለህ፡፡ ይህ አይነቱ አባባል ‹‹ጸባችን ከህዝቡ ጋር ሳይሆን ከስርአቱ ጋር ነው ለሚለው ፕሮፖጋንዳ እንዴት ግብአት ሊሆን እንደሚችል ግልጽ አይሆንልህም፡፡
እንደሚገባኝ ከሆነ ይህ አይነቱ የፖለቲካ ስትራተጂ ተግባራዊ እንዲሆን የተፈለገው ‹‹ህወሃት በትጥቅ ትግሉ ወቅት ደርግና አማራ አንድ እንደሆኑ አድርጎ ይቀሰቅስ ነበር፤ እናም በዚህ መንገድ ውጤታማ መሆን ችሏል›› በሚል የተሳሳተ ስሌት ምክንያት ይመስለኛል፡፡ ይህ አይነቱ የፖለቲካ ቀመር በ2012 ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር ግን ምንኛ ኋላ ቀር አካሄድ እንደሆነ ለመገንዘብ ዝግጁነቱ የለም፡፡ አንዳንዴ ከአንዳንድ የተቃዋሚ መሪዎች ጋር ሳወራ ‹‹የትግራይ ተወላጆች የጸረ ኢህአዴግ ትግሉን የማይቀላቀሉት ለምንድነው›› የሚል የቁጭት ጥያቄ ሲጠይቁ ይደመጣል፡፡ ነገር ግን ደግሞ እነ ስዬና እነ ገብሩ አስራት አይነት ሰዎች ወደ ተቃዋሚው ጎራ መጥተው ‹‹ተባብረን አንድ ነገር እናድርግ›› የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ የተቃዋሚው ምላሽ ‹‹እናንተም ያው ወያኔዎች ናችሁ›› የሚል ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡ ‹‹ታዲያ እሺ ምን ይደረግ ስትል›› ደግሞ መልስ የለም፡፡
አሁን አቶ መለስ በህይወት የሉም፤ ወደአገርህ ለምን አትመለስም?
ችግሩ እኮ በአቶ መለስ መኖርና አለመኖር የሚፈታ አይደለም፡፡ ከሆነም እናየዋለን፡፡ አውራምባን የማዘጋቱና እኔን የማባረሩ የቤት ስራ የተሰራው ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልህ ይህ አይነቱን ሴራ እንዲያከናውን በተመደበው ቡድን አማካኝነት ነው፡፡ ይህ ቡድን የሚያቀርበው ሪፖርት ደግሞ ከእንደኛ አይነቱ ምስኪን ዜጋ የበለጠ በአቶ መለስ ዘንድ አቅምና ተሰሚነት የነበረው ነው፡፡ አሁንም እንዳለው ይሰማኛል፡፡ ለዚሁ ተብሎ የተዋቀረ የጥፋት ቡድን ነውና፡፡
የአቶ መለስን ህልፈት ስትሰማ ምን ተሰማህ? በቀብራቸው ቀን ተገኝተው ሱዛን ራይስ ተናግረው ነበር፤ ንግግሩን እንዴት አየኸው?
በአቶ መለስ ህልፈት አዝኛለሁ፡፡ ለምን አዘንክ የሚለኝ ሰው ካለ በሱም ጭምር አዝናለሁ፡፡ አቶ በረከት ስምኦን ህልፈታቸውን በተመለከተ በይፋ ሲናገሩ ‹‹21 ዓመት ሙሉ ያለ እረፍት ሲሰሩ..ወዘተ›› ብለዋል፡፡ አዎ! በረከት ያሉት እውነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአገር ቤትና በውጭ መለስን የሚተካ ሰው አጥታ አንድ ሰው እሰኪሞት ድረስ እንዲመራት ሲደረግ ያሳዝናል፡፡ አቶ መለስ ምንም ጥያቄ የለውም አዋቂ ናቸው፡፡ እንኳን አቶ መለስ አልበርት አንስታይንም 21 ዓመት ሙሉ አንድን አገር በብቃት መምራት አይችልም፡፡ አሜሪካዊያን ከስምንት አመት በላይ አንድ ሰው እንዲመራቸው የማይፈልጉት ለምንድነው? በቃ አንድ ሰው በሙሉ አቅምና ኃይል (ፓሽን) ውጤታማ (ፐሮዳክቲቭ) ሆኖ አገርን መምራት የሚችለው ለትንሽ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ወደ ኢህአዴግ ስንመጣ ለፖለቲካ መቻቻል በሩ ዝግ ነው፡፡ እሱ ብቻ ነው ለአገር የሚያስበው” ሌላው አገር አጥፊ ነው፡፡ ይህ የተሳሳተ የፖለቲካ ባህላችን ለጤናችን እንኳን ተገቢውን ጊዜ እንዳንሰጥ እያደረገን ነው፡፡ መለስ ብዙ ሰው አልቅሶ እንደቀበራቸው አውቃለሁ፡፡ ሁሉም ሰው ግን አልቅሶ አልቀበራቸውም፡፡ ያ ግን እንዲሆን ማድረግ ይችሉ ነበር” እድልም ነበራቸው፡፡
የሱዛን ራይስን ንግግር በተመለከተ በወቅቱ አንድ አርቲክል ጽፌ ነበር፡፡ መለስ ሱዛን ራይስ እንደገለጽዋቸው አይነት ሰው ቢሆኑ ኖሮ በሱዛን ራይስ አገር ላይ በጥገኝነት ተቀምጨ የሱዛን ራይስን ንግግር በቴሌቭዥን አልመለከተውም ነበር፡፡ መቅረጸ-ድምጼን ይዤ መስቀል አደባባይ ሆኜ ነበር የምመለከታቸው፡፡ እውነትም መለስ ‹ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው መሪ> <<ወርልድ ክላስ ሊደር›› ቢሆኑ ኖሮ እኔም እስክንድርም በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተገኝተን አልቅሰን እንሸኛቸው ነበር፡፡ ያ ግን አልሆነም፡፡ ለምን አልሆነም? ካልከኝ መለስ ሱዛን እንደገለጽዋቸው አይነት አይደሉማ!
አንዳንድ ወገኖች እዚሁ ሆነህ የሚከፈለውን ሁሉ መስዕዋትነት መክፈል እንደነበረብህ ይገልጻሉ፡፡ ምን ትላለህ ስለዚህ ጉዳይ?
በመጀመሪያ ጥያቄውን አታድበስብሰው! ‹‹እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች በበቂ ሁኔታ አልታሰሩም” የእነ እስክንድር መታሰር በቂ ስላልሆነ አንተም መጨመር ነበረብህ›› ማለት ነው ጥያቄው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ 80 ሚሊዮን ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች ቀላሉን ጥያቄ ከመጠየቅ ከባዱንም ኃላፊነት ቢጋሩ መልካም ነው፡፡ ሌላው እንዲታሰር የምንጓጓውን ያህል የታሰሩትን ለማስፈታት ምን ጥረት አድርገናል ለመሆኑ? እስከ መቼ ነው ዋጋ የሚከፍሉልንን ሰዎች በመብራት እየፈለግን የምንኖረው? ሁሌ ተመሳሳይ ሰዎች ብቻ እየታሰሩ በይቅርታ እየወጡ እንደገና እየታሰሩ እንዲኖሩልን የምንፈልገውስ እስከመቼ ነው? ለእንደዚህ አይነቱ ነገር ዝግጁ ካልሆንን እንዲታሰሩ የምንፈልጋቸው ሰዎች ታስረው ነው የሚቀሩት፡፡ ለታሰሩ ሰዎች አንድ ነገር ማድረግ የማንችል ከሆነና ‹‹እከሌ ለምን ታስሮ አልቀረም›› ለማለት ከሆነ እንቅልፍ የምናጣው፤ ጭካኔአችን የሰው ልጅ ሳይሆን የእንስሳ ጭካኔ ነው፡፡
እኔ በግሌ ለእንደ ተመስገን አይነቱ አክብሮት አለኝ፡፡ ተመስገን ሁለት አመት ታስሮ በይቅርታ ቢፈታና ከዛ በኋላ ‹‹ይቅርታህ ሊነሳ ነው›› የሚል መረጃ ቢደርሰው እና አገር ጥሎ ቢወጣ ‹‹ተመስገን ለምን አልታሰረም›› ብዬ አገር ይያዝልኝ አልልም፡፡
አዲስ መፅሐፍ እየፃፍክ እንደሆነ ሰምተናል፡፡ መቼ እንጠብቀው? ምንስ ነገሮችን አካቷል?
መጽሐፉን ጽፌ የጨረስኩት ባለፈው ነሐሴ ነው፡፡ ነገር ግን ከጠ/ሚኒስትሩ ህልፈት ጋር በተያያዘ ያኔ የነበረው የፖለቲካ ድባብ መጽሀፉን ገበያ ላይ ለማዋል አስቸጋሪ ስለሆነ ከማቆየት ውጪ አማራጭ አልነበረኝም፡፡ አሁን ሁኔታዎች ስለተረጋጉ ከዛ በኋላ የተፈጠሩ አዳዲስ ነገሮችንም ጭምር አካትቼ እንደ አዲስ ለመከለስ ተገድጃለሁ፡፡ አሁን እያለቀ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንደ እግዚአብሄር ፍቃድ በሁለት ወር ውስጥ ይፋ ይሆናል፡፡ ይዘቱን በተመለከተ፡- አጠቃላይ ፕሬሱ ያለፈበትን ውጣ-ውረድ ከራሴ ልምድ ጋር በማዛመድ እቃኘዋለሁ፡፡ ከፕሬስ ነጻነት አንጻር የአቶ መለስ ሚና ምን እንደነበረም ትዝብቴን አሰፍራለሁ፡፡ እንዴት ከአገር እንደወጣሁ፣ የነበሩት ፈታኝ ሁኔታዎች ምን ይመስሉ እንደነበር ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
ከሀገር ከወጣህ በኋላ የተጻፉ መፅሀፍትን እንዴት አየሃቸው?
እኔ ከተሰደድኩ በኋላ የወጡት መጽሐፎች የአቶ በረከት ስምኦን (በወቅቱ ሪቪው ሰርቼበታለሁ)፤ የኮ/ል መንግስቱ ኃይለማሪያምና የጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ከዚሁ ከዳያስፖራ፤ የተመስገን ደሳለኝና የወሰንሰገድ ገብረኪዳንን አንብቤአቸዋለሁ፡፡ ሌላ ስለ አዲስ አበባ የዝሙት ህይወት እና የመሳሰሉት ነገሮች የሚተርክ መጽሐፍ ደግሞ ‹‹የአውራምባ ታይምስ ሎጎ ተለጥፎበት ወጥቷል›› የሚል ነገር ሰምቻለሁ፤አላየሁትም፡፡ እንደዚህ አይነት ይዘት ባለው መጽሐፍ ላይ የአውራምባን ሎጎ ማስቀመጥ ለምን እንዳስፈለገ እስከ ዛሬ ድረስ አልገባኝም፡፡ እስኪ አጣራለሁ፡፡
እስቲ ደግሞ በቅርቡ ባለህበት አሜሪካ ስለተካሄደው ምርጫ ትንሽ በለን፡፡ ከአገራችን ምርጫ ጋር ስታስተያየው (ማነፃፀሩ አዳጋች ቢሆንም) እንደ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኝነትህ ምን ተሰማህ? በነበርክበት ኦሪዞና ግዛትስ የነበረው የምርጫ ሂደት ምን ይመስላል?
የአሜሪካ ምርጫን በደንብ ተከታትየዋለሁ፡፡ ኦባማ በድጋሚ መመረጡ ብዙ ኢትዮጵያዊያንን አስደስቷል፡፡ ሁሌም የአሜሪካ ምርጫ ስትከታተል የሚያስቀናህ ነገር በእጩዎቹ መካከል ያለው መከባበር ነው፡፡ በተለይ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ አንዱ ለሌላው የሚያስተላልፈው የእንኳን ደስ ያለህ መግለጫ ደስ ይላል፡፡ በተለይ ሚዲያዎቹ ያላቸው ነጻነት ይገርምሀል፡፡ ‹‹ሲ ኤን ኤን›› እና ‹‹ፎክስ››ን ጨምሮ በርካታ ሚዲያዎች በራሳቸው መንገድ የተለያዩ መረጃዎችን መሰረት አድርገው ማን እንዳሸነፈ አስቀድመው ይፋ ያደርጋሉ፡፡ እኛ አገር ግን ምርጫ ቦርድ ይፋ ከማድረጉ በፊት እንዲህ አይነቱን የሚዲያ ትንበያ ይፋ ማድረግ አይፈቀድም፡፡ በእርግጥ በአገራችን እንዲህ አይነቱን ትንበያ ለመስራት የቴክኖሎጂ እጥረትና የአቅም ውሱንነት ቢኖርም በጊዜ ሂደት ግን የማይቻልበት ምክንያት የለም፡፡ በአዋጅ መከልከሉ ግን ተገቢ አይደለም፡፡ እኔ ያለሁበት አሪዞና ‹‹ሬድ ስቴት›› ነው፡፡ ማለትም ሪፐብሊካኖች ናቸው ሁሌ የሚያሸንፉት፡፡ ለምሳሌ ከአራት አመት በፊት ከኦባማ ጋር የቀረቡት ጆ ማኬይን የዚህ አካባቢ ሰው ናቸው፡፡
አዲሱ የአቶ ኃ/ማርያም አስተዳደር በፕሬስ ጉዳዮች ላይ ለውጥ ያመጣል ብለህ ትጠብቃለህ?
እኔ ሁሌም ተስፈኛ ነኝ፡፡ አቶ ኃይለማሪያም እዚህ ለተባበሩት መንግስታት ስብሰባ የመጡ ጊዜ ለእንግሊዝኛው ቪ ኦ ኤ የሰጡትን ቃለምልልስ ሰምቼዋለሁ፡፡ ፓርላማም ላይ የተናገሩት ነገር ተመሳሳይ ነው፡፡ ትንሽ ራሳቸውን መሆን የቻሉ አይመስለኝም፡፡ ፓርላማ ላይ ከእጅ እንቅስቃሴያቸው ጀምሮ አነጋገራቸው፣ በምላሾቻቸው ላይ የሰነዘሯቸው ማስጠንቀቂያዎችና ዘለፋዎች ተገቢ ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን ተስፈኛ ነኝ፡፡ ከ38 ዓመት በኋላ እምነት ያለው ሰው ወደ መሪነት ቦታ መምጣቱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ እግዚአብሄር ይርዳቸው!
ከኢትዮጵያ በመሰደድህ ምን ያጣኸው ነገር አለ? (የሚቆጭህ፣ የሚናፍቅህ፣ የሚፀፅትህ ነገር አለ?)
ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ስደት ላይ ስትሆን ቁጭት፣ ናፍቆትና ጸጸት ሁሌም ይኖራል፡፡ እኔ ማድረግ የምችለውን ሁሉ አድርጌአለሁ፡፡ ባልወጣና ባልሰደድ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ግን ምን ታረገዋለህ” ከዚህ በፊት እንደገለጽኩት ህይወት መቀጠል አለበት፡፡
የባልደረባህ የጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ከስዊድን ጋዜጠኞች ጋር በይቅርታ ያለመፈታት ጉዳይን እንዴት አየኸው?
የውብሸት ጉዳይ ብሄራዊ ክብርን የሚፈታተን ነገር ነው፡፡ ከስዊድኖቹ ጋር እንደሚፈታ ሙሉ እምነት ነበረኝ፡፡ እኩል ነው የይቅርታ ሰነዱን የፈረመው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከፕ/ር ኤፍሬም ይስሐቅ ጋር ተነጋግሬአለሁ፡፡ አጥጋቢ ምላሽ አልሰጡኝም እንጂ፡፡ አለም አቀፉ ሚዲያ የሚጮኸው ለስዊድኖቹ ስለነበር የኢትዮጵያ የይቅርታ ህግ ከኢትዮጵያዊያን ይልቅ የውጭ ዜጎችን ተጠቃሚ ሊያደርግ ግድ ነበር፡፡ ትንሽ ግራ የሚያጋባው ውብሸትም ስዊድናዊያኑም ሲታሰሩ አቶ መለስ የነጭ እና የጥቁር ደም እኩል ነው ብለው ነበር በፓርላማ፡፡ ተመርጠው ሲፈቱ ግን እኩል እንዳልሆነ አረጋግጠናል፡፡ ለዚህም ነው ስዊድኖቹ በተፈቱ በማግስቱ ‹‹አድሏዊውና አሳፋሪው ይቅርታ›› ብዬ አርቲክል ለመጻፍ የተገደድኩት፡፡ ለነገሩ ውብሸት የተበደለው ባሰሩት ሰዎች ብቻ አይደለም፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ባይሆንልኝም አገር ቤትም ውጭም ያለው ሚዲያ ሆን ብሎ ረስቶታል፡፡ ከታሰረበት ጉዳይ ቀጥተኛ የሆነ ትስስር አላቸው የሚባሉ ዌብሳይቶች እንኳን አንድ ነገር ትንፍሽ ለማለት አልፈቀዱም፡፡ በሌላ በኩል አገር ቤት ያሉ ሚዲያዎችም እንደዛው፡፡ አንድ የሚዲያ ተቋም የራሱን ባልደረባ ብቻ እየመረጠ ማግዘፍና ማጀገን የለበትም፡፡ እስርቤት ስለነበርኩ የሚዲያ ሽፋን ስታገኝና ሳታገኝ የሚሰማህ ብርታት እኩል እንዳልሆነ አውቀዋለሁ፡፡
በቅርቡ የተካፈልክበት ስብሰባ በ (National Endowment for Democracy) የተዘጋጀው ላይ ፅሁፍ አቅርበህ ነበር? ስለስብሰባው ምንነትና ዓላማ ብታብራራልን?
ናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ እዚህ ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኝ የአሜሪካዊያን አለም አቀፍ የጥናትና ምርምር ተቋም ነው፡፡ የፌሎውሽፕ ፕሮግራምም ይሰጣል፡፡ እንደምታወቀው ወ/ሪት ብርቱካን ለአንድ አመት ገደማ የቆየችው በዚሁ ተቋም ውስጥ ነው፡፡ ይህ ተቋም ባለፈው ጥቅምት “Toward a Democratic Ethiopia” በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል የሚል አለምአቀፍ ኮንፈረንስ አካሂዶ ነበር፡፡
ውይይቱ በሦስት ፓነል የተከፋፈለ ነው፡- የመጀመሪያው የፕሬስ ነጻነትና የሲቪክ ድርጅቶች እንቅስቃሴ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወጡት አዋጆች ምን ተጽእኖ አላቸው በሚል ርዕስ የቀረበ ነው፡፡ እኔ (በፕሬስ ነጻነት)፣ ወ/ሮ ማህደር ጳውሎስ (በሲቪክ ድርጅቶች) እንዲሁም የሂዩማን ራይትስ ዎች የዋሺንግተን ዲሲ ተጠሪ ሳራ ሞርጋን (በአዋጆቹ ዙሪያ) ጥናታዊ ጽሁፎቻችንን አቅርበናል፡፡ ቀጥሎ ደግሞ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የሚከተለው ፖሊሲ ምን እንደሚመስል አምባሳደር ዴቪድ ሺን እና ፕ/ር ቴሬንስ ሊዮንስ በመጨረሻ ደግሞ የስቴት ዲፓርትመት አሲስታንት ሴክሬታሪ እንዲሁም ሌላው የዩኤስ ኮንግረስ ተወካይ በተከታታይ ጽሁፎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ከኛ ከጽሁፍ አቅራቢዎቹ ውጪ በዚሁ ስብሰባ ላይ አቶ ስዬ አብርሀ፣ አቶ ገብሩ አስራት፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና እንዲሁም በዋሺንግተን ዲ.ሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተወካይ የስብሰባው ታዳሚዎች ሆነው ፕሮግራሙን ተከታትለዋል፡፡
አንተ ያቀረብከው ይዘቱ ምን ይመስላል፤ የኤምባሲው ተወካይስ ማን ናቸው? ምንስ አሉ?
እኔ ያቀረብኩት አጠቃላይ ሚዲያው አሁን ያለበትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ከስብሰባው ከሁለት ሳምንት በፊት በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ላይ ተገኝተው የመናገር ነጻነትን በተመለከተ በጣም ድንቅ የሆነ ንግግር አድርገው ነበር፡፡ እኔ ለንግግሬ መነሻ ያደረኩት ኦባማ ያደረጉትን ንግግር በማስታወስ ነው፡፡ ኦባማ ያሉት ‹‹ሰዎች በሚያራምዱት አመለካከት ምክንያት እስር ቤት መግባት የለባቸውም፡፡ እዚህ አሜሪካ በርካታ ፕሬሶች እኔን ሲያብጠለጥሉ ይውላሉ፡፡ እኔ የአሜሪካ ፕሬዚደንትና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነኝ ብዬ ግን ምንም የማረገው ነገር የለም፡፡ እንደውም በህገ መንግስታችን የተረጋገጠውን መብት ተግባራዊ በማድረጋቸው ይበልጥ ደስ ነው የሚለኝ›› ነበር ያሉት ኦባማ፡፡ ይህንን መነሻ አድርጌ የእስክንድርን፣ የርዕዮትንና የውብሸትን ሁኔታ በንጽጽር ለማስቀመጥ ሞክሬአለሁ፡፡ ያው አምባሳደር ዴቪድ ሼን ሁሌም …ዴሞክራሲ እኮ ሂደት ነው ምናምን የሚሉት ነገር አለ…እኔ ደግሞ ‹‹አምባሳደር ዴቪድ ሺን፣ እርስዎ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር እያሉ ስንት ጋዜጦች ነበሩ? አሁንስ ስንት አሉ? ሂደት ማለት ይሄ ነው? ሂደት ማለት እንደዚህ ከሆነ፤ ወደተሳሳተ አቅጣጫ የሚወስድ ሂደት ላይ ነው ያለነው፤ ‹‹እኤአ እዚሁ በዋሺንግተን ዲሲ ተገናኝተን ስናወራ ቢያንስ እኮ እነ አውራምባ ይታተማሉ ብለው ተከራክረውኝ ነበር፤ ዛሬ ግን እነ አውራምባም አይታተሙም፡፡ ይኼ ነው ሂደት? ባለፈው አመት የእርስዎ ዌብሳይት ሳይቀር ኢትዮጵያ ውስጥ እንደተዘጋ ነግረውኝ ነበር” እንዴት ነው ይህንን ማስታረቅ የሚቻለው?›› አልኳቸው፡፡ በጣም የሚያስቀው ነገር ዌብሳይታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ተዘግቶ እንደነበረና ከአቶ ኃይለማሪያም ጋር ተነጋግረው እንዳስከፈቱት ነገሩኝ፡፡ ከኢትዮጵያ ኢምባሲ አቶ ዋሕድ በላይ ናቸው የተገኙት፡፡ አጋጣሚ የእኔ ጽሁፍ ቀርቦ ቤቱ ለጥያቄና መልስ ክፍት ሲሆን አቶ ዋሕድ ተነስተው የኔ ጽሁፍ የደርግ አመለካከት እንደሚንጸባረቅበት ተናገሩ፡፡ እኔ ደግሞ ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ የዘጠኝ አመት ልጅ እንደነበርኩ ተናግሬ በአዳራሹ የነበሩ ታዳሚዎችን ትንሽ ፈገግ አሰኘኋቸው፡፡ በነገራችን ላይ ከዛ በኋላ ከአቶ ዋህድ ጋር አድራሻ ተለዋውጠን ኢንተርቪው ሁሉ እንደሚሰጡኝ ቃል ገብተውልኛል፡፡
አገሬ መጥቼ ተወዳጇን አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ዳግም አሳትማለሁ ብለህ ታስባለህ?
ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሌላው ቢቀር ቢያንስ ዌብሳይቴን ኢትዮጵያ ሆኜ ብሰራው እንዴት ደስ ይለኛል መሰለህ፡፡ ግን በጣም የሚያሳዝነው ነገር እንደዛ አይነት ሆደ ሰፊነት ኢህአዴግ ጋ የለም፡፡ ይገርምሃል ዌብሳይቱ የተመረቀው ሜይ 05/2012 እንግዶች በተገኙበት በዋሺንግተን ዲ.ሲ ነው፡፡ በተጠቀሰው ቀን ተመርቆ በማግስቱ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ተዘግቷል፡፡ ‹‹አውራምባ ታይምስ በኪሳራ ነው የተዘጋው፤ እኛ ጫና አላሳደርንም›› ያሉት ኃላፊዎች የአውራምባ ዌብሳይትን ግን ከ24 ሰዓታት በላይ ሊታገሱት አልፈቀዱም፡፡ ቢያንስ ይዘቱ ምን ይመስላል? ተብሎ እንኳን ዳሰሳ ለማድረግ አይሞከርም? እና እንዲህ እንዲህ አይነቱን ስመለከት ትንሽ ተስፋዬን ያደበዝዘዋል፡፡ ግን ይሁን እስኪ…………..