Wednesday, August 17, 2016

ጊዜዉ ደረሰ

Augest 17,2016
ፊዳ ቱምሳ
ዕንባ እየተናነቀኝ የዛሬዉ የኦሮሞ ትዉልድ እየከፈለ ያለዉን መስዋዕትነት ከእሱ ጋር ሆኜ ያለመካፈሌ እያንገበገበኝ ተከዝኩ፡፡ የነፃነት ቀን መቃረቡን ሣይ በአንድ በኩል እጅግ ተፅናናሁ፡፡ የነገዉን ነፃነት ሳያዩት ለመጪዉ ትዉልድ የተሰዉትን ጀግኖች በዓይኔ እየዳሰስኩ ኮራሁባቸዉ፡፡ የእነርሱ ደም የፈሰሰዉ በከንቱ እንዳልሆነ ስረዳ በእጅጉ ተፅናናሁ፡፡ በልጅነት ዕድሜአቸዉ ለዚህ ታላቅ መስዋዕትነት ራሳቸዉን መስጠታቸዉ ለትዉልድ መዘከር የሚገባዉ ታሪክ እንደሆነ ያለጥርጥር ከህሊናዬ ጋር ተስማማሁ፡፡ እንደገናም ወደኋላ ሄጄ ያለፍንበትን መንገድ እንድመለከት አዕምሮዬ ሞገተኝና ተጓዝኩ — የህሊና ጉዞ፡፡
Ethiopia, TPLF officials
“Whoever sows injustice will reap calamity.”
ጊዜዉ 1991 ዓ.ም. ነበር፡፡ የነበርኩት ጀርመን አገር በርሊን ከተማ ዉስጥ ነበር፤ በጊዜዉ የኦሮሞ ከተማ!! የወያኔ ሠራዊት ጎጃምን ተሻግሮ ወደ ኦሮሚያ ሲገሰግስ ተቃወምን፣ አወገዝን፤ ቀጥሎም ነቀምት መግባታቸዉን ሲለፍፉ የተቃዉሞ ሰልፍ አዘጋጀን፡፡ የተቃዉሞ ሰልፉ መነሻ ነቀምት ከመግባታቸዉ ጋር የሰጡት መግለጫ ነበር፡፡ መግለጫዉን እንደማስታዉሰዉ “ወተት ጠጣን ጮማ በላን” የሚል እና በዚህ መንገድ ተስተናገድን የሚል መግለጫ ነበር፡፡ ይሄ መግለጫ ወደፊት ለታቀደዉ ብዝበዛና ምዝበራ ሀ ሁ መሆኑን ስለተገነዘብን ነበር ተቃዉሞ ያዘጋጀነዉ፡፡ እናም በተቃዉሞዉ ሰልፍ ላይ የሚሰራጭ ወረቀት እንዲዘጋጅ ተወስኖ አንድ ጓደኛችን ወረቀቱን አዘጋጅቶ አመጣ፡፡ በጽሑፉ ዉስጥ የተቀመጠዉ ምሳሌያዊ መልዕክት ዛሬ ይህን እንድጽፍ አስገደደኝ፡፡
ምሳሌያዊዉ መልዕክት እንዲህ ይላል:- “አንድ በበረሃ የተጎሳቆለ እባብ በጠርሙስ ዉስጥ ያለ ወተት አይቶ ወተቱን ለመስረቅ ዙሪያዉን ተጓዘ፤ አልቻለም፡፡ እናም ጠርሙሱ ዉስጥ ገብቶ ለመጠጣት በዚያ በከሣ አካሉ በጠርሙሱ አፍ ወደ ጠርሙሱ ገባ፤ ወተቱን እየጠጣም ወፈረ፤ ከጠርሙሱ ለመዉጣት የገባበት የጠርሙስ አፍ ከዉፍረቱ የተነሣ አያስወጣዉም፡፡ እናም ሁለት አማራጭ ብቻ ቀረዉ፤ ወይ ወተቱን ተፍቶ መዉጣት ወይ ጠርሙሱ ዉስጥ መሞት፡፡” እናም ያ ጽሑፍ ወያኔ ወደ ኦሮሚያ ገባ፤ ምርጫዉ የዚያ እባብ ምርጫ ብቻ ይሆናል ይላል፡፡ ለወያኔ የያኔዉ መልዕክት ሳትጠራ ወደ ኦሮሚያ አትግባ፤ ኦሮሚያ የራሱ አባት አለዉ፤ ባለቤት አለዉ የሚል ነበር፡፡ ከገባህ ደግሞ ዕጣ ፈንታህ የእባቡ ዕጣ ፈንታ ነዉ፤ ወይ እዚያዉ ትቀበራለህ፣ ወይ በመጣህበት ሁኔታ ወደመጣህበት ትመለሳለህ የሚል ነበር፡፡
ከሃያ-አምስት ዓመት በኋላ ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ ተነስቷል፤ የኦማራ ሕዝብ ተነስቷል፡፡ ወያኔ በእነዚህ ሕዝቦች ተከቦአል፤ እባቡ በጠርሙሱ እንደተከበበዉ፡፡ ወተቱን ጠጥቶ እንደወፈረዉ እባብ ወያኔ ወፍሯል፤ ሀብት ዘርፎአል፣ ተንጠባሯል፡፡ እናም እንደእባቡ ሁሉ ጠርሙሱን ለመስበር ይንፈራገጣል፡፡ ጠርሙሱ ግን አይሰበርም፤ የተጠናከረ የተባበረ ሕዝባዊ ኃይል ነዉና፡፡ ጠርሙሱን የከበቡት የኦሮሞ የአማራና የሌሎች ህዝቦች የነፃነት ሃይሎች ኢሳት አቀጣጥለዋል …. ጠርሙሱም እየጋለ ነው ፤ የወያኔ ምርጫ እንግዲህ እንደ እባቡ ሁሉ የበላዉን ተፍቶ፣ የዘረፈዉን ትቶ መዉጣት፤ አለያም እንደበላ እንደወፈረ መቃጠልና መሞት ነዉ፡፡ መዉጫ ቀዳዳ የለም፡፡ በህፃናት ደም ተጨማልቆ፣ በእናቶች ደም ተጨማልቆ፣ በከበሩ አዛዉንቶች ደም ተጨማልቆ የደም ካሣ ሣይከፍሉ ወዴት ይኬዳል? ይዋል ይደር እንጂ የእባቡ ምሳሌ ጊዜዉ ደረሰ፤ ጠርሙሱም ከተሰባሪ ጠርሙስነት ወደ ብረት ጠርሙስነት ተሸጋገረ፤ እባቡም ተከበበ፡፡ እንደገናም ጊዜዉ ደረሰ፡፡
August 6, 2016 (አመሻሽ)

No comments: