Thursday, December 3, 2015

ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአቶ አንዳርጋቸው ላይ የቀረበውን ይግባኝ ውድቅ አደረገ

December 3,2015
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌደራል አቃቤ ህግ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ምስክር ሆነው እንዳይቀርቡ ያቀረበውን ይግባኝ ዛሬ ህዳር 23/2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት ውድቅ አደርጎታል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በእነ ዘመነ ካሴ መዝገብ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ድረስ ለተጠቀሱት ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ ተጠይቆ የነበር ቢሆንም ማረሚያ ቤቱ በተደጋጋሚ ሳያቀርባቸው ቀርቷል፡፡
አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ምስክርነት በተጠሩበት ወቅት የፌደራል አቃቤ ህግ አቶ አንዳርጋቸው በእነ ጀኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ እና በእነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ መዝገብ ላይ ክስ ቀርቦባቸው በእድሜ ልክና በሞት እንዲቀጡ ተወስኖባቸው የህዝባዊ መብታቸው የተሻረ በመሆኑ በምስክርነት ሊቀርቡ እንደማይችሉ መቃወሚያ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁንና ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ አቶ አንዳርጋቸው እንዲቀርቡላቸው የጠየቁት ለዋስት አሊያም ልዩ አዋቂ ምስክር ሆነው ሳይሆን ነበሩበት የተባለውን ጉዳይ ለመናገር በመሆኑ ለምስክርነት ሊቀርቡ ይገባል በሚል የፌደራል አቃቤ ህግ ያቀረበውን ተቃውሞ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
የልደታ ፍርድ ቤት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሀምሌ 13/2007 ዓ.ም ቀርበው ምስክርነት እንዲሰጡ ከወሰነ በኋላ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ‹‹ትዕዛዝ አልደረሰኝም፣ የተፃፈው ለቃሊቲ ሳይሆን ለአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት የሚል ነው›› እና ሌሎችም ምክንያቶች በማቅረብ በተደጋጋሚ አቶ አንዳርጋቸውን ሳያቀርብ ቀርቷል፡፡ በስተመጨረሻም ጥቅምት 12/2008 ዓ.ም ማረሚያ ቤቱ አቶ አንዳርጋቸው ቃሊቲ እንደሌሉ በደብዳቤ አሳውቋል፡፡ በእነ ዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ከተከሰሱት መካከል አቶ ደናሁን ቤዛ (3ኛ ተከሳሽ)፣ አቶ ምንዳዬ ጥላሁን (4ኛ ተከሳሽ) ውጭ ያሉት የፍትህ ሂደቱ እየተጓተተባባቸው በመሆኑ የአንዳርጋቸው ፅጌ ምስክርነት ቀርቶ በሌሎች መረጃዎች ውሳኔ እንዲሰጥላቸው ሲጠይቁ ሁለቱ ተከሳሾች ግን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ሊመሰክሩላቸው እንደሚገባ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡
በዚህም መሰረት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለፀረ ሽብር ግብረ ኃይልና አቶ አንዳርጋቸውን ጠይቀውታል ለተባሉት የብሪታኒያ አምባሳደር ደብዳቤ መፃፋቸው ይታወቃል፡፡ ይሁንና ተከሳሾቹ ለሶስቱ አካላት ደብዳቤውን በፃፉበት ማግስት የፌደራል አቃቤ ህግ ከወራት በፊት ለልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ መመስከር አይገባቸውም ብሎ አቅርቦት የነበረውን መከራከሪያ መሰረት በማድረግ አቶ አንዳርጋቸው ምስክር እንዳይሆኑ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቆ ነበር፡፡
የአቃቤ ህግን ይግባኝ ያየው ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ዛሬ ህዳር 23/2008 ዓ.ም በዋለው ችሎት ‹‹አንድ ሰው ለምስክርነት ይቅረብ አይቅረብ በሚል ይግባኝ ሊጠየቅበት አይገባም፡፡ ካስፈለገ ግለሰቡ የሰጡት ምስክረነት መረጃው ተመዝኖ የሚሰጠው ፍርድ ላይ ይግባኝ ሊባል ይችላል፡፡ እኛም ጉዳዩን ለማጣራት ምስክርነቱ እንዲቋረጥ አድርገን የነበር ቢሆንም አሁን ግን እንዲቀጥል ወስነናል፡፡ የአቃቤ ህግን ይግባኝም አልተቀበልነውም›› ሲል ይግባኙን ውድቅ አድርጓል፡፡ አቃቤ ህግ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ምስክር መሆን የለባቸውም ብሎ ያቀረበው ክርክር በፍርድ ቤት ውድቅ ሲሆንበት ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
በእነ ዘመነ ካሴ መዝገብ ከተከሰሱት በተጨማሪ በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ ከተከሰሱት መካከል 1ኛ ተከሳሽ አቶ ዘላለም ወርቃገኘሁ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በመከላከያ ምስክርነት ጠርቷቸዋል፡፡ በሌሎች የክስ መዝገቦች ከአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ተገናኝታችኋል የተባሉ ተከሳሾችም አቶ አንዳርጋቸውን የመከላከያ ምስክር አድርገው ሊጠሯቸው እንደሚችሉ የነገረ ኢትዮጵያ ምንጮች ገልፀዋል፡፡

No comments: