Friday, December 4, 2015

ፈረንሳይ እስከ 160 የሚሆኑ መስጊዶችን ልትዘጋ ነው!

December 4,2015

“ጥላቻ የሚሰብኩ ፈቃድ የሌላቸው መስጊዶች ይዘጋሉ” ኢማም ሃሰን
mosque Paris France
በመጪው ጥቂት ወራቶች ፈረንሳይ እስከ 160 የሚጠጉ መስጊዶችን ለመዝጋት መወሰኗ ተሰማ፡፡ የአገሪቱ ከፍተኛ ኢማም እንዳሉት በሥራ ላይ በዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት ጽንፈኛ አመለካከት የሚያራምዱ የእምነት ቦታዎች መዘጋትአለባቸው፡፡
በኅዳር ወር መጀመሪያ አካባቢ በፓሪስ የተከሰተውን ጥቃት ተከትሎ እስካሁን ጽንፈኛ አቋም አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሦስት መስጊዶች መዘጋታቸውን የአገር አቀፍና የአካባቢ ኢማሞች ለመምረጥ ኃላፊነት የተሰጣቸው ኢማም ሃሰን ኤል-አላዊ ለአልጃዚራ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት በቀጣይ ወራቶች በርካታ መስጊዶች እንደሚዘጉ አስረድተዋል፡፡
“ከአገር ውስጥ ሚኒስቴር ጋር በምናደርገው ውይይት እና ይፋ በሆኑት መረጃዎች መሠረት ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸው፣ ጥላቻን የሚሰብኩ፣ ታክፊሪ ንግግር የሚደረግባቸው ከ100 እስከ 160 መስጊዶች ይዘጋሉ” በማለት ኢማም ሃሰን ተናግረዋል፡፡ ታክፊሪ ንግግር ማለት በእምነቱ ውስጥ ያሉትን ሌሎች ሙስሊሞችን በከሃዲነት የሚነቅፍ ንግግር ነው፡፡ “እንዲህ ዓይነቱ ንግግር ዓለማዊ በሆነችው ፈረንሣይ ብቻ ሳይሆን በእስላማዊ አገራትም ቢሆን መፈቀድ የለበትም” በማለት የመጀመሪያው የእስርቤት ኢማም (ቻፕሊን) ለመሆን የበቁት ሃሰን ኤል አላዊ ተናግረዋል፡፡
franceይህ በፈረንሳይ አገር በቤተ እምነት ላይ የተወሰደ የመጀመሪያው የተባለለት እርምጃ የተወሰደው “አንዳንድ ሕገወጥ ነገሮች በመገኘታቸው” መሆኑን የጠቀሱት ኢማም ድርጊቱ ባለሥልጣናት ማድረግ የሚገባቸው ሕጋዊ እርምጃ ነው ማለታቸውን አልጃዚራ ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ለ130 ሰዎች መሞት ምክንያት የሆኑትን “አሸባሪዎች” በማለት የጠቀሷቸው ኢማም ሃሰን “እነዚህ የሃይማኖት ልብስ የተጎናጸፉ ሌቦችና አደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች ናቸው፤ ነገሩ የአሸባሪዎች ጉዳይ ነው እንጂ ከሙስሊሞች ጋር ምንም ግንኑነት የለውም፤ የሁሉንም ሰው ደኅንነት ማስፈን የመለከተ ነው” በማለት ኢማም ሃሰን በጥቃት አድራሾቹ ላይ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ሌላው ለአልጃዚራ አስተያየታቸውን የሰጡት የአል-ካዋኪቢ ድርጅት ተባባሪ መሥራች የሆኑት የፋርሱ ሙስሊም ፊሊክስ ማርቃርት የመስጊዶቹ መዘጋት እንዳላስደነቃቸው ተናግረዋል፡፡ ይልቁንም በተለያዩ የፈረንሳይ ከተሞች በተካሄዱ እስላማዊ የጸሎት ሥነ ሥርዓቶች ላይ የሰሙት ነገር በእጅጉ እንዳስደነገጣቸው ተናግረዋል፡፡ “እስልምናን ከፖለቲካ ጋር በማያያዝ እስልምናን አስፈሪ የማስደረግ ሥራ በፈረንሳይ መንግሥት እንደሚሠራ አንዳንድ ቦታዎች በይፋ ሲነገር ሰምቻለሁ” ብለዋል፡፡
ሆኖም ግን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ከጥቃቱ በኋላ ፈረንሳይ ሙስሊሞች ላይ ያነጣጠረ የመብት ጥሰት እየፈጸመች መሆኗን ይናገራሉ፡፡ የቤት አሰሳ፣ እስራት፣ ሙስሊሞች ባለቤት የሆኑባቸው ድርጅቶችን የመዝጋት፣ ወዘተ የመብት ጥሰት ተከስቶባቸዋል የተባለባቸው ናቸው፡፡
“በአሁኑ ጊዜ በፈረንሳይ ሙስሊም ሆኖ መኖር ቀላል አይደለም” ያሉት ማርቃርት “በተለይ የፊት መሸፈኛ የሚያደርጉ ሴቶች የመድልዖ ሰለባ ሲሆኑ ለወንዶች ደግሞ ሥራ ማግኘት እጅግ ከባድ ነው” በማለት አስረድተዋል፡፡
በፈረንሳይ ውስጥ በድምሩ 2,600 መስጊዶች ይገኛሉ፡፡

No comments: