የንቅናቄያችን መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ለኢትዮጵያ ህዝብ ባደረጉት የትግል ጥሪ በ11ኛው ሰዓት ላይ እንደምንገኝ ገልጸዋል ። የ 11ኛው ሰዓት መልዕክት፣ አንደኛ፣ ወደ 12ኛው ሰዓት ወይም ወደ ፍጻሜው እየተቃረብን መሆኑን የሚነገረን ነው። የ11ኛው ሰዓት የትግል ጥሪ የአንድን የትግል ምዕራፍ ለመዝጋት እና አዲስ የትግል ምዕራፍ ለመጀመር የመጨረሻ የሞት ሽረት ትግል የምናደርግበት ጊዜ ላይ መድረሳችንን የሚገልጽ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጥሪው ከትግሉ ፍጻሜ በሁዋላ ስለሚፈጠረው አዲስ ስርዓት ከአሁኑ ማሰብ መጀመር እንዳለብን የሚያነቃን ደወል ነው። 11ኛው ሰዓት ላይ ቆመን ከ12ኛው ሰዓት በሁዋላ ስለሚፈጠረው ነገር መጨነቅ ካልቻልንና በጊዜ ቤታችንን ካላሰናዳን ፣ ከትግሉ ፍጻሜ በሁዋላ ሊገጥሙን የሚችሉትን ተግዳሮቶች በጊዜና ብቃት ባለው መልኩ ለመፍታት መቸገራችን አይቀርም ። አንድ በእድሜ የገፋ ሰው 11ኛው ሰዓት ላይ መሆኑን ሲያውቅ ከህይወቱ ፍጻሜ በሁዋላ ስለሚኖረው ህይወት ማሰላሰሉ ተፈጥሯዊ ነው። የ11ኛው ሰዓት ጥሪም የአንድን አገዛዝ እርጅናና ፍጻሜ የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፣ በቦታው የሚወለደውን አዲስ ስርዓት ምንነትም የሚያሳይ ነው።
የ11ኛው ሰዓት ጥሪ ተደራሾች እነማን ናቸው? የጥሪው ተደራሾች በኢህአዴግ ዙሪያ የተሰባሰቡት እና እነዚህን ስብስቦች በማፍረስ አዲስ ስርዓት ለመገንባት የሚታገሉት የነጻነት ሃይሎች ሁሉ ናቸው። የ11ኛው ስዓት ጥሪ ለወያኔ ገዢዎች መገርጀፋቸውን የሚያረዳ የሞት ጥሪ ደወል ነው፤ ወደማትመለሱበት መቃብር ከመወርወራችሁ በፊት በቀራችሁ የአንድ ሰአት እድሜ አሟሟታችሁን አሳምሩ ብሎ የሚመክር ነው። በተለይ በጣት የሚቆጠሩ የሻገቱ ገዢዎችን ደግፋችሁ የቆማችሁ የመከላከያ፣የፖሊስና የደህነት አባላት አሰላለፋችሁን በጊዜ አስተካክሉ የሚል አርቆ ከማሰብ የመነጨ ምክር ነው ። የ11ኛው ሰዓት ጥሪ የሚመክር ብቻ ሳይሆን የሚያስጠነቅቅም ነው። ይህን የገረጀፈ አገዛዝ ደግፈው የቆሙ ሁሉ በጊዜ ከህዝብ ጋር እንዲታረቁ ይህ ካልሆነ ግን በመጨረሻው ሰዓት ከፍርድ እንደማያመልጡ የሚያስጠነቅቅ ነው። ካለፈው የሚመጣው ይበልጣል፤ ወያኔን ደግፋችሁ የቆማችሁ ሁሉ ያለፈ ጥፋታችሁን ለወደፊት በምትስሩት ስራ እንድትክሱ መልእክት ተላልፎላችሁዋል።
የ1ኛው ሰዓት ጥሪ የነጻነት ሃይሎች በአንድነት እንዲሰባሰቡና ትግሉን እንዲያቀጣጥሉም ያሳስባል። አገዛዙ 11ኛው ሰዓት ላይ ነው ማለት በራሱ ጊዜ ይወድቃል ማለት አይደለም። አገዛዙ ከደሃው በዘረፈው ገንዘብ ኪኒኖችን እየዋጠና ምርኩዞችን እየገዛ እድሜውን ሊያራዝም ይችላል። ከገፋነው በቀላሉ ተሰባብሮ ይወድቃል፤ ዝም ካልነው ግን ድዱ ረግፎም በህይወት መቆየቱና ስቃያችን ማራዘሙ አይቀርም። እኛ በዘር፣ በጾታ፣ በትምህርት ወይም በሌሎች ጥቃቅን ነገሮች ሳንለያይ አንድ ሆነን ይህን የሻገተ አገዛዝ እንድናስወግድ ግልጽ ጥሪ ተላልፏል።
የ11ኛው ሰዓት ጥሪ ያረጀውን ስርዓት ወደ መቃብሩ ከከተትነው በሁዋላ ስለሚፈጠረው አዲስ ስርዓት እንድናስብ የሚመክርም ነው። ዛሬ በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበን እንድንነጋገርና የነገውን ትልም እንድንተልም የሚጠይቅ ነው። አስቀድሞ በጋራ መተለሙ ነገ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ከመቀነሱም በላይ፣ የሻገተውን አገዛዝ በህብበረት ለመጣል ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል። በጭሩ የ11ኛው ሰዓት ጥሪ ወያኔን ተባብሮ ለመቅበር ብቻ ሳይሆን፣ በመቃብሩ ላይ ስለሚተከለው አዲስ ችግኝ ለመነጋገር ጥሪ የሚያቀርብ ነው።
ሁላችንም የ11ኛውን ሰዓት ጥሪ ተቀብለን ተግባራዊ ልናደርገው ይገባል። ድሉ የሁላችንም ነው!
አርበኞች ግንቦት7!