Wednesday, April 22, 2015

ወያኔ በሚሞቱትም በሚሰደዱትም ደስተኛና ተጠቃሚ ነው

April 22, 2015
አንዷለም
ወያኔን እንቅልፍ የሚነሳው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያውያን በሰላም ውለው መግባታቸው ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ በሰላም ውሎ ካደረ አንድ ቀን ቀፎው እንደተነካበት ንብ ገንፍሎ ወጥቶ የሚውጠው ይመስለዋል ስለዚህም የጅምላ ሞት፤ስደት፤ እልቂት እንዲኖር ጠንክሮ ይሰራል ሲደርስም ሲበዛ ይደስታል።
የወያኔ ጥቅሞችን ላስረዳ።Ethiopian refugees heading to Yemen
1. ወጣቱ (በወያኔ ቋንቋ አደገኛ ቦዘኔው) አገር ውስጥ ከተቀመጠ በችጋር ተገፍቶ አንድ ቀን መነሳቱና የግፍ ወያኔያዊ አገዛዝን ከምድረ ገጽ ማጥፋቱና የበይ ተመልካችነቱም ሊያበቃ እንደሚችል ወያኔ ጠንቅቆ ያውቃል፤ ስለዚህም ደላላዎቹን በመላ አገሪቱ በማሰማራት፤ በቀላሉ ቀይባህርን ተሻግሮ ሳውዲ አረቢያ በመግባት ቤተሰቦቹን ሀብት በሀብት ማድረግ እንደሚቻል ይሰብካል። በሌላም በኩል በኬንያ አቋርጦ በቀላሉ ደቡብ አፍሪካ መግባትና በአጭር ጊዜ ሚሊዮነር መሆን እንደሚቻል ምሳሌ እየጠቀሱ የወያኔ ደላላዎች ያለመታከት ይሰብካሉ፤ የጉዞ ዶኩመንት የሚያስፈልገውንም በድርጅታዊ አሰራር ያሟላሉ፤ ለዚህም ወላጅ ተበድሮም ቢሆን ይከፍላል። ሌላው የወያኔ ደላላ ደግሞ በሱዳን ተሻግሮ ሊብያን አቋርጦ በአጭር እርቀት የባህር ላይ ጉዞ ጣሊያን መግባት አዲሱ የመክበሪያ ዘዴ መሆኑን ምሳሌ እየጠቀሰ ያስተምራል የሚያሻግሩ ሰዎችም እንዳሉ ጭምር ይናገራል፤ ያመቻቻል። የሊብያው ካልተሳካ ወደእስራኤል መሻገርም አማራጭነቱ በወያኔ ደላሎች በብርቱ ይሰበካል።
ስለዚህም ወጣቱ ከአገር እንዲወጣ ወያኔ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል፡ ቀይ ባህር ሰጠሙ፤ ለአካል ክፍሎቻቸው ሲባል ሲናይ በርሃ ውስጥ ታረዱ፤ አይኤስኤስ አረዳቼው፤ ሜዲትራንያን ባህር ሰጠሙ፤ በታንዛንያና በማላዊ በርሃዎች ውስጥ በኮንቴነር ውስጥ ታፍነው አለቁ በወያኔና ደላላዎቹ ቤት ለዜናም አይበቃም። የድለላውን ከፍለዋል፤ የተበላ እቁብ!!
2. ተሳክቶላቸው ወደሶስተኛ አገር ደርሰው መስራት ከጀመሩ ወጣቶቹ የተበደሩትን ለመክፈልና ቤተሰብም ለመርዳት ገንዘብ መላክ ይጀምራሉ። ወያኔም ዶላር እየተቀበለ እንደፈለገ የሚያትመውን ብር ለቤተሰብ ይሰጣል። አገር ውስጥ ያለው ቤተስብም እንጄራ ድሎት ቢሆንበትም ሩዝም ቀምሶ ነገን ተስፋ እያደረገ ይኖራል።
ስለዚህም ወያኔ አደገኛ ስደትን ያበርታታል።
ምናልባት አንዳንድ የወያኔ ባለስልጣናት በቴሌብዥን ቀርበው ስደትን ሲቃወሙ ሰምታችሁና የልማታዊ መንግስታችንን ስም አጠፋህ ብላችሁ በሽብርተኝነት በሽመልስ ከማል አቃቤ ህግነትና በተከበሩ ዳኛ ልኡል ዳኝነት ልትከሱኝ ላሰባችሁ እበላ ባዮች አንድ ቀላል ጥያቄ ልጠይቃችሁ?
ሁላችንም እንደምናውቀው ወያኔ አንድ ለአምስት በሚለው መጠርነፊያው እያንዳንዱን ሰው 3 ና 4 ጊዜ በቤተሰቡ፤በመስሪያቤቱ፤ በሙያ ማህበሩና በሌላም የጠረነፈው በመሆኑ በእያንዳንዱ ቤትና መስሪያቤት የተተነፈሰው ብቻ ሳይሆን የተላሰውም ለወያኔ በመዋቅሩ መሰረት ሪፖርት ይደረጋል። እመኑኝ ዛሬ ወያኔ ደላላዎቹን ከዛሬ ጀምሮ በውሸት እያተለላችሁ ሰው እንዲሰደድ ማደረጋችሁን አቁሙ ካለ ያኑ ቀን ይቆማል። ይህን ስል ሃይለ ማርያም፤ ደመቀ ወይም አባዱላ እንዲህ አለ ብላችሁ መንግስት ተናገረ የምትሉ ቁጭ በሉ ላሞኛችሁ መሆኑን እዎቁ።
ስለዚህ ወያኔ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ይህ ነገር ይቀጥላል፤ ጎበዝ መሞታችን ካልቀረ በክብር ለአገር በአገራችን መሬት እንሙት።
የሞቱትን አምላክ ያስባቸው፤ ከተመሳሳይ አደጋ ለመዳን ወያኔን ማስዎገድ ብቼኛው መፍትሄ ነው።

No comments: