Monday, October 6, 2014

የሕወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በ23 ዓመት ጉዞው ያፈራቸው ጄኔራል መኮንኖች ከወታደራዊ አመራር ሳይንስ ትምህርት እና ስልጠና አንፃር ሲመዘኑ/ በግንቦት 7 የወታደራዊ ጉዳዮች ቡድን የተዘጋጀ ጥናታዊ ፅሁፍ ክፍል 1

October 6, 2014

የሕወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በ23 ዓመት ው ያፈራቸው

ጄኔራል መኮንኖች

 ከወታደራዊ አመራር ይንስ ትምህርት እና ስልጠና አን

ሲመዘኑ

በግንቦት  የወታደራዊ ጉዳዮች ቡድን

የተዘጋጀ ጥናታዊ ፅሁፍ

ክፍል 1

መስከረም 2007 ዓ..

የርዕስ ማውጫ

መግቢያ. 2
1…… የወታደርዊ አመራር ምንነትና ዋና ዋና የአመራር እርከኖች፤. 3
2…… የወታደራዊ አመራር የስልጠና እርከኖችና ወደ ወታደራዊ የትምህርት አካዳሚዎች መግቢያ መስፈርቶች.. 3
2.1. ወታደራዊ አካዳሚ፡ 4
2.2. ሰታፍ ኮሌጅ.. 4
2.3. የአዛዥነት እና የመምሪያ መኮንንነት አካዳሚ… 5
2.4 የጦር ኋይሎች ዋር ኮሌጅ(Armed Forces War College) 6
3…… የመኮንኖች የማዕረግ ዕድገት ሂደት.. 7
4…… የጄነራል መኮንንነት የማዕረግ ዕድገት.. 8
5…… የቀድሞው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አመራሮች የሥልጠና ሂደት፤. 10
6…… የአሁኑ  የሀገር መከላከያ መኮንኖች ከወታደራዊ አመራር ሳይንስና ጥበብ አንፃር. 11
7…… ማጠቃለያ. 13
8…… አባሪ ሰነድ- ፩ (Annex-1) 15
የሕወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በ23 ዓመት ጉዞው  ያፈራቸው ጄኔራል መኮንኖች
ከወታደራዊ አመራር ሳይንስ ትምህርት እና ስልጠና አንፃር ሲመዘኑ

መግቢያ

የኢትዮጵያ ሠራዊት በዘመናዊ መልክ ከተቋቋመበት ከ1927 ጀምሮ  እስክ 1983 ዓ/ም ድረስ ጊዜው በሚጠይቀው ወታደራዊ ሳይንስ የተማሩ፣  ዘመናዊ ክህሎትንና  ሥንምግባርን የተላበሱ እና  በተግባር የተፈተነ ጀግና  የምድር ጦር፣ የባህር ኃይልና የአየር ሃይል ሠራዊትና መሪዎችን  ለማፍራት የቻለ ነበር::  በሂደቱም ሰራዊቱን  ፈታኝ በሆኑ የተለያዬ አውደ ፍልሚያዎች መርተው ለድል ያበቁ ከፍተኛ ወታደራዊ ምሁራንና መኮንኖችን አፍርቶ ማለፉ የሚታወስ ነው::  የማእረግ አሰጣጡም እንዳሁኑ ዘርን መሰረት በማድረግ ሳይሆን የትምህርት ዝግጅትን፣ ወታደራዊ ዲስፕሊንና ሥነምግባርን እንዲሁም በእየእርከኑ ያሳየው ብቃትና ተገቢውን የመቆያ ጊዜ መፈፀሙ ተረጋግጦ፤ ይህንን እንዲያስፈፅም በተዋቀረ ገለልተኛ አካል አቅራቢነት በሀገሪቱ መሪዎች ሹመት ሲሰጥ ኖሯል።
ቀደም ሲል በተገለፀው የማዕረግ እድገት አሰጣጥ ሂደት መሠረት በአጠቃላይ ከ1927 እስክ 1983 ሀገሪቱ 293 ጄኔራሎችን አፍርታ ነበር። በሌላ መልኩ ወያኔ የመንግሥት ሥልጣን ከወሰደበት ከ1983 ጀምሮ ዘርንና ታማኝነትን በቻ መሰረት በማደረግ ለ130  የቀድሞ ሽምቅ ተዋጊ መሪዎቹ ከብርጋዲየር እስከ ሙሉ ጄኔራልነት ማዕረግ አድሎአቸዋል። ከትምህርት ዝግጅት አንፃር 97 በመቶ (126ቱ) የሚሆኑት መደበኛ የወታደራዊ ሳይንስ እውቀትና ከህሎት የሌላቸው ሲሆን ቀሪዎቹ 3 በመቶ የሚሆኑት ተገቢውን የወታደራዊ ሳይንስ የተማሩና በቂ ሙያዊ ክህሎትን ያዳበሩ አራት የቀድሞ ጦር አባላት ብቻ ነበሩ (አሁን ሦስቱ በጡረታ ሲገለሉ አንዱ በፖለቲካ ጉዳይ የተባረሩ ናቸው)። በአጠቃላይ ከነዚህ 130 ጄነራሎች ውስጥ 67ቱ የሆኑ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የሕወሓት አባላት ናቸው።
የዚህ ፅሁፍ አጠቃላይ ዓላማ ባለፉት 23 ዓመታት የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ያፈራቸውን ጄኔራል መኮንኖች ከወታደራዊ ሳይንስና ሙያዊ ክህሎት አንፃር መፈተሽና መገምገም ነው። በዚህም መሰረት ይህን መግቢያ (Introduction) ጨምሮ
1ኛ፡ የወታደራዊ አመራር ምንነት እና ዋና ዋና የጦር  አመራር እርከኖች፣
2ኛ፡ የወታደራዊ አመራር የስልጠና እርከኖችና ወደ ወታደራዊ የትምህርት አካዳሚዎች የመግቢያ መስፈርቶች፣
3ኛ፡ የመኮንኖች የማዕረግ እድገት፣
4ኛ፡ የጄኔራል መኮንኖች የማዕረግ እድገት፣
5ኛ፡ የቀድሞው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አመራሮች ትምህርትና የሥልጠና ሂደት፣
6ኛ፡ አሁን ያለው የጦር ሃይል መኮንኖች የአመራር ሥልጠናና ብቃት፣
7ኛ፡ ማጠቃለያ ሲሆኑ ከዚህ እንደሚከተለው በቅደም ተከተል ይቀርባሉ።

1.    የወታደራዊ አመራር ምንነትና ዋና ዋና የአመራር እርከኖች

ወታደራዊ አመራር በተፈጥሮው የሳይንስንና የጥበብን (both Science and Art) ዘርፍ አጣምሮ የያዘና የተከበረ የሙያ መስክ ነው። ይህም በመሆኑ ማንኛውም የጦር ኃይል አባል በአመራር ቦታ ላይ ከመቀመጡ በፊት ዘመኑ የሚጠይቀውን ለየሥልጣን እርከኑ ተገቢ የሆነውን ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ በመማርና እና ስልጠና በመውሰድ (Military Education and Training) በአጥጋቢ ሁኔታ ማጠናቀቅ ይጠበቅበታል።
የወታደራዊ አመራር (Military Leadership) ትምህርትና ሙያዊ ስልጠናውም በወታደራዊ የአመራር ንድፈ ሀሳብ ፣ ስትራቴጅና ታክቲክ ትምህርትና የተግባር  ሥልጠናን የሚያካትት ሆኖ መደራጀት ይኖርበታል።
በጦር ሀይሎች ውስጥ አመራር የሚሰጡ የአመራር አካላት በሁለት ዋና ዋና ደረጃዎች ይከፈላሉ:: እነሱም:-
1.1.   የበታች ሹም (Non Commissioned Officer/NCO)
1.2.  መኮንኖች ናቸው (Commissioned Officers) ናቸው::
የበታች ሹም (Non Commissioned Officer/NCO)፦ የሚባሉት ሰራዊቱን በቅርብ የሚቆጣጠሩ፣ የሚያደራጁ፣ የሚያሰለጥኑ፣ የሚመሩትን ሀይል ለውጊያ የሚያዘጋጁ ከፍተኛ ሀላፊነት ያለባቸው የሰራዊቱ የጀርባ አጥንት ሆነው የሚያገለግሉ መሪዎች ናቸው:: በሰራዊቱ ውስጥ በግንባር መስመር ከበላይ አካል የሚሰጣቸውን ትእዛዝ ተቀብለው በተዋረዱ የሚያዙ የሚያዋጉ እና በየትኛውም የሰራዊቱ ጠቅላይ መምሪያ ውስጥ የስታፍ ስራዎችን በኃላፊነት የሚሰሩ ናቸው:: የአመራር ብቃታቸውንም ለማጎልበትም የወታደራዊ የአመራር ስልጠናም ይወስዳሉ:: በአጠቃላይ የበታች ሹሞች በተዋጊው ሰራዊትና በአመራር መኮንኖች መካከል እንደ ድልድይ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው::
መኮንን (Commissioned Officer/CO) ፦የሚባለው የወታደራዊ አመራር ጥበብን እና የወታደራዊ ስልት ስልጠናን ወስዶ በምድር ጦር፣ በአየር ሀይል (Pilot Officer) በባህር ኃይል (Ensign) በምክትል መቶ አለቃነት ማዕረግ የተመረቀ(ች) ወይም ከዚያ በላይ እስከ ከፍተኛ ፊልድ ማርሻል ማዕረግ የደረሰ ሁሉ መኮንን ይባላል:: ስልጠና ያልወሰደ ግን መኮንን አይባልም፡፡ አንድ መኮንን በህግ የተሰጠውን ማዕረግና ሀላፊነት ከተቀበለ በኋላ በተመደበበት የጦር ክፍል የሚመራቸውን ክፍሎች ወይም ኃይሎች  በትዕዛዝ፣ በማነቃቃት እና በማግባባት ግዳጃቸውን እንዲፈጽሙ ተጽዕኖ የማድረግ ሀላፊነት አለበት::

2.   የወታደራዊ አመራር የስልጠና እርከኖችና ወደ ወታደራዊ የትምህርት አካዳሚዎች መግቢያ መስፈርቶች

ማንኛውም የሠራዊቱ አባል መኮንን ለመሆን ከዚህ እንደሚከተለው በተዘረዘሩት መሠረታዊ  የመኮንኖች የአመራር ሳይንስና ጥበብ ሥልጠና ተቋማትና እርከኖች ውስጥ በመግባት ተገቢውን እውቀትና ክህሎት በማዳበር የሚሰጠውን የተግባርና የንድፈ ኃሳብ መመዘኛ በጥሩ ሁኔታ ማለፍና መመረቅ ይኖርበታል።የወታደራዊ አመራር የስልጠና እርከኖችም የሚከተሉት ናቸው፦
2.1.   የእጩ መኮንኖች መሰረታዊ የአመራር ስልጠና
2.2.  የስታፍ ኮሌጅ
2.3.  የአዛዥነትና የመምሪያ መኮንንነት
2.4. የጦር ኮሌጅ ናቸው::

2.1. ወታደራዊ አካዳሚ፡

ይህ አካዳሚ የዕጩ መኮንኖች ማሰልጠኛ ሲሆን ተቋሙ እንደ የሀገሩ እና አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ በጦር ኃይሎች ውስጥ እጩ መኮንኖችን መልምሎ ወታደራዊ የአመራር ጥበብና ሳይንስ በማስተማር ሠራዊቱን ለመምራት እና ለማገልገል የሚያዘጋጅና አጥጋቢ ውጤት ያመጡትን  አስመርቆ ወደ ተለያዩ የሠራዊቱ ክፍሎች እንዲሰማሩ የሚያስችል ተቋም ነው፡፡ ወደ አካዳሚው የእጩ መኮንነት ኮርስ መግባት የሚቻለው ከዚህ የሚከተሉት መስፈርቶች ተሟልተው ሲገኝ ብቻ ነው፡፡
ሀ. እድሜያቸው 17 እስክ 23 ዓመት የሆነ (የሆነች)፣
ለ. የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን በሚገባ ያጠናቀቁ ሆነው በትምህርት ቤት ቆይታቸው ወቅት ከክፍል ወደ ክፍል በሚሸጋገሩበት ጊዜ በክፍል ውጤት ደረጃቸው ከ1ኛ እስከ 5ኛ የወጡ፣
ሐ. ከፍተኛ የትምህርት ተቋም/ኮሌጅ በዲፕሎማ በጥሩ ሁኔታ የተመረቁ፣
መ. ከዩኒቨርሲቲ የአንደኛ ወይም የሁለተኛ ዓመት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ፣
ሠ. ከሰራዊቱ ውስጥ ከበታች ሹማምንት ውሰጥ ፲ አለቃ እና ከዛ በላይ ሆነው በአካዳሚ እውቀታቸውና ወታደራዊ አመራር ብቃታቸው የተረጋገጠላቸው፡;
ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን መስፈርቶች አሟልተው የተመለመሉ እጩ መኮንኖችም በአካዳሚው ውስጥ ከሦስት እስከ አራት ዓመት ለሚሆን ጊዜ  የአካዳሚክ፣ የወታደራዊ ስልቶች፣ መሰረታዊ የአመራር ሳይንስና ጥበብ፣ የአካል ብቃት፣ የሞራል እና የስነ ምግባር ትምህርቶችና የተግባር ሥልጠናዎችን በመማር የብቃት መመዘኛ ፈተናዎችን በአጥጋቢ ሁኔታ ሲያሟሉ እንዲመረቁ ይደረጋሉ፡፡ የብቃት ደረጃ የሚለካባቸው መስፈርቶችም፦ የአካዳሚ ብቃት 55% ፤ የወታደራዊ ብቃት 30% እና የአካል ጥንካሬና የአትሌቲክስ ብቃት 15% ይይዛሉ፡፡ ኮርሱን ሲጨርሱና በምዘናው አጥጋቢ ውጤት ሲያመጡ በመጀመሪ ደረጃ የሳይንስ (Bachelor of Science / B.Sc) ዲግሪና በምክትል መቶ አለቃነት ማዕረግ  ይመረቃሉ፡፡ በአጠቃላይ አካዳሚው ተመራቂ መኮንኖችን በቆይታቸው ወቅት በሠራዊቱ ውስጥ የአንድ የመቶ ጦር (ኃይል) ለማዘዝ የሚያስችላቸውን  ወታደራዊ የአመራር ጥበብ ትምህርት እና የአካዳሚክስ እውቀት በሚገባ ታጥቀው እንዲወጡና በብቃት እንዲያገለግላሉ ያስችላቸዋል፡፡

2.2. ሰታፍ ኮሌጅ

ስታፍ ኮሌጅ ማለት የመካከለኛ መኮንኖች የአመራር ሳይንስና ጥበብ የሚማሩበት ተቋም ነው፡፡ በዚህ ኮሌጅ ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት የወታደራዊ አመራር ትምህርት፣ የአስተዳደር እና የስታፍ መምሪያ መኮንንነት ተግባር እና ሀላፊነት፣ የወታደራዊ ሥነምግባር፣ የወታደራዊ ሙያ ፖሊሲ እና የአካል ብቃት ትምህርቶች ይሰጣሉ፡፡ በኮሌጁም ውስጥ በሁለት ደረጃ የተከፈሉ ሥልጠናዎች ማለትም ጁኒየር እና ሲኒየር ኮርሶች ይሰጣሉ። ወደ እዚህ ኮሌጁ ለመግባት የግድ ማሟላት የሚገባቸው መሰፈርቶች በሲኒየር የሻምበልነት ወይም በሻለቃነት ማዕረግ ሰራዊቱ ውስጥ ግዳጅን መወጣትና  ማገልገል ናቸው፡፡
ሀ. የጁኒየር ኮርስ፡ ይህ ኮርስ ሲኒየር የሆኑና የሻምበል ማዕረግ ያላቸው መኮንኖች ገብተው የሚማሩበት ፕሮግራም ነው። የሚሰጠውም የኮርስ ይዘት የወታደራዊ አመራር እና የስታፍ መኮንንነት ተግባራትን፣ የወታደራዊ ሥልቶችን እና የአካል ብቃት ሥልጠናን ያካተተ ነው፡፡ ኮርሱም የሚፈጀው ጊዜ ሃያ ሳምንት ሲሆን ኮርሱንም ሲጨርሱ የሻምበል አዛዥ ወይም በሻለቃ መምሪያ ውስጥ በስታፍ መኮንንነት የኃላፊነት ቦታ ይሰራሉ፡፡
ለ. የሲኒየር ኮርስ፡ ይህ ኮርስ ጁኒየር የሆኑ የሻለቃ ማዕረግ ያላቸው መኮንኖች የሚሳተፉበት ኮርስ ነው፡፡ ትምህርትና የሥልጠናውም ይዘት ወታደራዊ የአመራር ሳይንስና ጥበብ፣ የወታደራዊ ሥልጠናዎች፣ የአስተዳደር እና የሎጂስቲክ ትምህርቶች፣ የስታፍ መኮንንነት ተግባር እና ኋላፊነት እና የአካል ብቃት ሥልጠናዎችን ያካትታል፡፡ የኮርሱም የቆይታ ጊዜ አንድ ዓመት ነው፡፡
መኮንኖቹ ኮርሱን ሲጨርሱ የሻለቃ አዛዥ ወይም በብርጌድ መምሪያ ውስጥ የስታፍ መኮንን ሆነው ያገለግላሉ፡፡ በአጠቃላይ የስታፍ ኮሌጅ ሥልጠና የጨረሱ መኮንኖች የሚሰጣቸው የትምህርት ማስረጃ  ዲፕሎማ ነው፡፡

2.3. የአዛዥነት እና የመምሪያ መኮንንነት አካዳሚ

ይህ አካዳሚ ሲኒየር ሻለቃዎች እና ሌ/ኮሌኔሎች በመቀበል ለከፍተኛ አመራር ሰጭነት  የሚያስተምር ተቋም ነው፡፡ ወደ አካዳሚው የመግቢያ መስፈርቱም  የጁኒየር እና የሲኒየር ስታፍ ኮሌጅ ኮርሱን ካጠናቀቁ መኮንኖች ውስጥ በአመራር ስጭነታቸውና በስነምግባራቸው የሚመረጡ ይሆናል፡፡ ኮርሱም በዋነኝነት  በወታደራዊ የአመራር ጥበብ፣ ፍልስፍና፣ በወታደራዊ ታሪክ፣ በወታደራዊ ሥልቶች፣ እና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት እና የአካል ብቃት ትምህርቶች ያተኮረ ሆኖ ከ10-12 ወራት የሚሆን ጊዜን ይፈጃል፡፡ ኮርሱን አጠናቅቆ ለመጨረስ እንዲያስችላቸው  የመመረቂያ ጥናታዊ ፅሁፎችን አዘጋጀቶ ማቅረብና አጥጋቢ ውጤት ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ መኮንኖቹም ትምህርታቸውን ሲጨርሱ በወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ የማስተርስ (Master of Military Arts and Sciences) ዲግሪ ይሰጣቸዋል፡፡ ከሥልጠናው በኋላም የሥራ ኋላፊነታቸውም የሻለቃ ወይም የብርጌድ አዛዥ ወይም በክ/ጦር (በዕዝ) መምሪያ ውስጥ የመምሪያ መኮንን በመሆን ያገለግላሉ፡፡ መኮንኖቹ ከተመረቁና በያዙት ማዕረግ የተወሰነ አገልግሎት ከሰጡ በኋላ በዚሁ አካዳሚ ውስጥ እንደገና ሁለት ኮርሶችን ይወስዳሉ፡፡
እነዚህም፦
ሀ/ ከፍተኛ ወታደራዊ ጥናትና
ለ/ የዕዝ አዛዥነት
እነዚህ ኮርሶች በዋናነት የሚያተኩሩት በወታደራዊ ስትራቴትጂክ ጉዳዮች እና የዕዝ አዛዥነት ንድፈ ሀሳብ ላይ ነው፡፡ ኮርሱንም ሲጨርሱ የወታደራዊ ዕቅድ ነዳፊዎች (Strategic Military Planners) ሆነው ይመደባሉ፡፡

2.4 የጦር ኋይሎች የጦር ኮሌጅ (Armed Forces War College)

ይህ ተቋም  በወታደራዊ የሥልጠና እርከን ውስጥ የመጨረሻው የስትራቴጂክ አመራር ሥልጠና (Strategic Leadership Training) የሚሰጥበት የጥናት እና የምርምር ማዕከል ነው፡፡ በዚህ ተቋም ውስጥ የኮርሱ ተሳታፊዎች የሚሆኑት በምድር ኋይል፣ በአየር ኋይል፣ እና በባህር ኋይል ውስጥ ስትራቴጂክ አመራር (Strategic Level Leaders) እየሰጡ ከሚገኙት እና   ከከፍተኛ ስቪል የመንግስት ባለስልጣናት ውስጥ ቢያንስ ማስተርስ ዲግሪ ያላቸውን ፖሊሲና እስትራቴጂ አውጪ ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉትን በመቀበል ለከፍተኛ የሥልጣን ቦታ እና ሀላፊነት የሚያዘጋጅ የፖሊሲ እና የስትራቴጂ ጥናት እና ምርምር ተቋም ነው፡፡
እንደ ተለያዩ ሀገሮች ተጨባጭ ሁኔታ በጦር ሀይሎቻቸው ውስጥ እራሳቸውን የቻሉ የምድር ሀይል የጦር ኮሌጅ፣ የአየር ሀይል የጦር ኮሌጅ እና የባህር ሀይል የጦር ኮሌጅ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ሆኖም በወታደራዊ የሥልጠና እርከን መሰረት ሁሉም ሀይሎች አመራር መኮንኖቻቸውን በየራሳቸው የጦር ኮሌጅ ትምህርታቸውን ካስጨረሱ በኋላ ወደ ዋናው የጦር ኃይሎች የጦር ኮሌጅ ገብተው እንዲሠለጥኑ ያደርጋሉ፡፡
ወደ ጦር ኋይሎች የጦር ኮሌጅ ለመግባት በቅድሚያ መሟላት ያለበት፦
  1. የአዛዥነትና የመምሪያ መኮንንነት ኮርስን መጨረስ፣
  2. በጦር ኃሎች የጦር ኮሌጅ የሚሰጠውን ኮርስ መጨረስ፣
  3. በሠራዊቱ ውስጥ በአመራር ሰጭነት ከ 22 ዓመት በላይ ማገለገል፣
  4. በወታደራዊ ሥነምግባር ምንም ችግር የሌለበትና፣
  5. የአካል ብቃቱ በሀኪም የተረጋገጠ መሆን ይኖርበታል፡;
ከላይ የተጠቀሱት መሠረታዊ መስፈርቶች እንደተጠበቁ ሆነው ወደ ጦር ኋይሎች የጦር ኮሌጅ የሚገቡት ለብርጋዲየር ጄኔራልነት የሚታጩ ስለሆነ በምድር ኃይል በሙሉ ኮሎኔል ማዕረግ በአየር ኋይል ተመጣጣኝ በሆነው Group Captain እና በባህር ሀይል ደግሞ ካፒቴን (Captain) በአጠቃላይ ሁሉም በኮሎኔል ማዕረግ ደረጃ ሆነው በማገልገል ያሉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
የኮርሱም ተሳታፊዎች መጠንም 75 በመቶ ከጦር ኋይሎች ከሦስቱም ኃይሎች ተመጣጣኝ ቁጥር ያላቸው ከፍተኛ መኮንኖችን እና 25 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከሲቪል የመንግስት ባለስልጣናት፣ ከሀገር ውስጥ ጉዳይ፣ (በአሁኑ የፌደራል ጉዳዮች)  እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ተመርጠው እንዲሣተፉ ይደረጋል፡፡ ኮርሱም የሚያተኩርባቸው ርዕሰ ጉዳዮችም የስታራቴጂክ አመራር ጥበብ፣ የብሔራዊ ደህንነት ስትራቴጂ ጥናት (National Security Strategy)፣ የግጭት ማስወገድ ጥናቶች (Conflic Resolution Research)፣ የህብረት ጥምር ውጊያ ፍልስፍና (War Games) እንዲሁም የጥናት እና ምርምር ንድፈ ሀሳብ ትምህርት የሚሰጥበት ማዕከል ነው፡፡ መኮንኖቹ ትምህርቱን ሲጨርሱም በስትራቴጂ ጥናት የማስተርስ ዲግሪ (Master Degree in Strategic Studies) ደረጃ  ይመረቃሉ፡፡ በጦር ኋይሎች ውስጥም የኮር ወይም የዕዝ አዛዥ ወይም በሀገር መከላከያ ጠቅላይ መምሪያ የመምሪያ መኮንነት የሥራ ኋላፊ ሆነው እንዲሠሩ ይደረጋል። በጦር ሀይሎች የጦር ኮሌጅ ውስጥ ትምህርታቸውን ጨርሰው የተመረቁ መኮንኖች ምንም አይነት የዲሲፕሊን ችግር ሪከርድ የሌለባቸው ከሆነ በቀጥታ የብርጋዴር ጄኔራልነት ማዕረግ ይሰጣቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ከላይ የተቀመጠው  መሠረታዊ የሆነው የመኮንኖች የአመራር ጥበብ ስልጠና ሂደት ከዕጩ መኮንነት ኮርስ እስከ ጦር ኮሌጅ የሚዘልቅና መንገዱም ሌላ አቋራጭ  የሌለው ረዥም እና አስቸጋሪ ውጣ ውረድ የበዛበት መሆኑን ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ ይህንን ረጅም መንገድ ያለፉ መኮንኖች ሁሉ የተሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት የተወጡ ስለመሆናቸው ያለፉት ታላላቅ አውደ ውጊያዎች(በምስራቅና በሰሜን ኢተዮጵያ) ምስክርና ማስረጃዎች ናቸው፡፡

3.    የመኮንኖች የማዕረግ ዕድገት ሂደት

የመኮንኖች የማዕረግ ዕድገት መነሻውም ሆነ መድረሻው ወታደራዊ ትምህርትና ሥልጠና ነው፡፡ የወታደራዊ አመራር ሳይንስ ጥበብ ደግሞ ለመኮንነት ማዕረግና ዕድገት የማዕዘን መሰረተ ድንጋይ ሲሆን በአጠቃላይ የመኮንነት የማዕረግ  ዕድገት በሥልጠና እየታገዘ የሚከናወን ቀጣይነት ያለው ሂደት  ነው፡፡ መኮንን ለመሆን በቅድሚያ የዕጩ መኮንንነት ኮርስ ወስዶ በሚገባ ማጠናቀቅን ይጠይቃል። የአንድ መኮንን የመጀመሪያው ማዕረግም በምድር ሀይል ምክትል መቶ አለቃ (Second Lieutenant) በአየር ሀይል ፓይለት መኮንን (Pilot Officer) በባህር ሀይል ደግሞ ኢንሳይን (EnSign ) ይባላል፡፡ ምክትል መቶ አለቃ ሆኖ የተመረቀ መኮንን ወደ ሚቀጥለው የማዕረግ ዕድገት ለማለፍ የግል ሪፖርቱ ተገምግሞ ምንም ዓይነት የዲሲፕሊን ችግር ከሌለበት በምድር ሀይል ሙሉ መቶ አለቃ (Lieutenant) በአየር ሀይል በራሪ መኮንን (Flying Officer) በባህር ሀይል ምክትል ሊዩተናንት (Sub – Lieutenant) ይሆናል ፡፡ በሙሉ መቶ አለቃ ማዕረግ ደግሞ አምስት ዓመት ካገለገለ በኋላ የሻምበልነት ማዕረግ ያገኛል፤ በሻምበል ማዕረግ ደግሞ አራት ዓመት ማገልገል አለበት፡፡ በአራት ዓመት የቆይታ ወቅትም የስታፍ ኮሌጅ ኮርሱን ካጠናቀቀና በቆይታ ጊዜ ውስጥ ያስመዘገበው የወታደራዊ ዲሲፕሊን እና የሙያ ብቃቱ ተረጋግጦ በበቂ ሁኔታ ከአለፈ የሻለቃነት ማዕረግ ዕድገት ይሰጠዋል፡፡
በሻለቃ ማዕረግ የቆይታ ጊዜ አራት ዓመት ሲሆን  በአራት ዓመት ውስጥም የአዛዥነትና የመምሪያ መኮንንነት ኮርስ ይወስዳል፡፡ የሻለቃ የማዕረግ ቆይታውን ሲጨርስ በሠራዊቱ ሕገ ደንብ መሰረት በዋንኛነት የወታደራዊ ዲሲፕሊኑ፣ የአመራር ብቃቱ፣ በተዋረድ የወሰደው የወታደራዊ አመራር ስልጠና እና በቆይታው ጊዜ ባስመዘገበው ሪፖርት ተመስርቶ ይገመገምና ወደ ሚቀጥለው የማዕረግ ዕድገት የሚያልፍ ከሆነ የሌ/ኮሎኔል ማዕረግ ይሰጠዋል፡፡ የሌ/ኮሎኔል ማዕረግ ቆይታ አራት ዓመት ሲሆን በአራት ዓመት ቆይታው ወቅት የሚወስዳቸው ኮርሶች የአዛዥነትና የመምሪያ መኮንንነት ኮርስ እንዲሁም የምድር ኃይል ወይም የአየር ኃይል የጦር ኮሌጅ የአመራር ጥበብ ሥልጠናን ወስዶ ከጨረሰና በቆይታ ጊዜውም ውስጥ ምንም ዓይነት የዲሲፕሊን ችግር ከሌለበት የሙሉ ኮሎኔልነት ማዕረግ እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡
ከሙሉ ኮሎኔልነት ማዕረግ ወደ ቀጣዩ ማዕረግ ለማደግ ቢያንስ የአራት ዓመት የቆይታ ጊዜ ያስፈልጋል ፡፡ በአራት ዓመት የቆይታ ጊዜ ውስጥም የጦር ኃይሎች የጦር ኮሌጅ በመግባት የስትራቴጂክ የአመራር ጥበብ መውሰደና መመረቅ ይኖርበታል:: ኮርሱንም ከጨረሰ በኋላ በቀጥታ የወሰደው የአመራር ሥልጠና እርከን፣ የአመራር ብቃቱ እና አጠቃላይ የ22 ዓመት የአገልግሎት የቆይታ ሪፖርት ተገምግሞ ከአለፈ የብ/ጄነራልነት የማዕረግ ዕድገት ይሰጠዋል፡፡ ትክክለኛ የመኮንኖች የማዕረግ እድገት አሰጣጥ ሂደትና ይዘት ከላይ በተጠቀሰው የትምህርት፣ የስልጠና፣ የሥነምግባር አፈፃፀም ግምገማ  ውጤትን መሠረት ባደረገ መንገድ የሚከናወነው ብቻ ነው፡፡

4.    የጄነራል መኮንንነት የማዕረግ ዕድገት

የጄነራል የመኮንነት የማዕረግ ዕድገት መሰረታዊ የትምህርትና ሥልጠና ዝግጁነቶች እንደተጠበቁ ሆኖ በየሀገሩ ተጨባጭ ሁኔታ  መሰረት  ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ ያህል በአሜሪካ የጦር ኋይሎች ውስጥ የጄነራልነት ሹመት በፕሬዘዳንቱ አቅራቢነት በህግ መወሰኛው ምክር ቤት ይጸድቃል፡፡ በሌሎች ሀገሮች ግን የጄነራልነት ሹመት የሚካሄደው በመከላከያ ሚኒስቴር በሚቋቋመው የማዕረግ ዕድገት ቦርድ ወይም በመከላከያ ካውንስል በተቋቋመው በሰራዊቱ ህገ ደንብ መሠረት መመዘኛውን ያሟሉ ተመርጠው ለሀገሪቷ ፕሬዘዳንት ቀርቦ ይጸድቃል፡፡
የጄነራል መኮንንነት ማዕረግ ከፍተኛው የወታደራዊ ማዕረግ እርከን ሲሆን በጦር ኋይሎች ( በምድር ኃይል፣ በአየር ኃይል እና በባህር ኃይል) ከፍተኛውን ኃይል የሚመሩ ወይም የሚያዙ፣ ሠራዊቱን የሚያደራጁ፣ የሠራዊቱን ህግ ደንብ የሚያወጡ፣ ሠራዊቱ የሚዋጋበትን የጦርነት ህግ እና ሠራዊቱ የሚሰለጥንበትን የሥልጠና ፖሊሲ፣ የወታደራዊ ዶክትሪን እና ስትራቴጂ የሚቀርጹ፤ በአካዳሚም ሆነ በወታደራዊ ሳይንስ እና ጥበብ የተካኑ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው የጦር ኃየሎች ጄነራል መኮንኖች ናቸው፡፡
ሰንጠረዥ-ሀ፦ የጄነራል መኮንኖች የማዕረ አጠራር በተለያዩ የጦር ኃይል ክፍሎች
ተ.ቁ
በምድረ ኃይል
በአየር ኃይል
በባህር ኃይል
1
Brigadier GeneralAir CommodoreCommodore
2
Major GeneralAir Vice MarshalRear Admiral
3
Lieutenant GeneralAir MarshalVice Admiral
4
Full GeneralAir Chief MarshalAdmiral
5
Marshal or Field MarshalMarshal Air ForcesAdmiral of the fleet

ሀ. ብርጋዴር ጄነራል፡ ይህ ማዕረግ ከሙሉ ኮሎኔል ቀጥሎ የሚሰጥ ሲሆን የጄነራል መኮንኖች የመጀመሪያ ማዕረግ ነው፡፡ ከሙሉ ኮሎኔልነት ወደ ብርጋዴር ጄነራልነት ለመሸጋገር መመዘኛዎቹ፡
1)    በኮሎኔልነት ማዕረግ የአገልግሎት ዘመን፣
2)   የወታደራዊ የአመራር ጥበብ በተዋረድ የወሰደ፣
3)   በአገልግሎት ዘመኑ ያሳየው ዲሲፕሊን፣
4)   የወታደራዊ አመራር ብቃቱ እና ልምዱ፣
5)   በብ/ጄነራልነት ማዕረግ ሊሰራበት የሚችልበት የሥራ ቦታ ክፍት ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡
ብርጋዲር ጄነራል ማዕረግ ያለው መኮንን በጦር ኃይሎች የብርጌድ ወይም የክፍለ ጦሩ አዛዥ እንዲሁም የኮር እስታፍ ይሆናል፡፡ በያዘው ማዕረግም ከሁለት እስከ አራት ዓመት ያገለግላል፤ የጡረታ ጊዜውም በያዘው ማዕረግ አምስት ዓመት ከቆየና 30 ዓመት የአገልግሎት ዘመን ከሞላው ጡረታ ይወጣል፡፡ የጡረታ የዕድሜ ጣራውም 62 ዓመት ይሆናል፡፡
ለ.ሜጀር ጄነራል፡ ይህ ማዕረግ ከብ/ጀኔራል ማዕረግ ቀጥሎ ያለ ባለ ሁለት ኮከብ ማዕረግ ነው፡፡ ከብ/ጀ ወደ ሜ/ጀኔራል የማዕረግ ዕድገት ለመሸጋገር በቅድሚያ ፡-
  • ክፍት የስራቦታ መኖሩ (Number of Open Positions) ፣
  • በአመራር ብቃት የፈጸማቸው ግዳጆች፣
  • በወታደራዊ ሥነ ምግባር ምንም ችግር የሌለበት፣
  • የአመራር የሥልጠና እርከን በተዋረድ የወሰደ፣
  • የአገልግሎት የቆይታ ጊዜውን (Years of Services) የጨረሰ መሆኑ መታየት ይኖርበታል።
መኮንኑ ሜ/ጀኔራል ከሆነ በኋላ የሥራ ኃላፊነቱም የክፍለ ጦር ወይም የዕዝ አዛዥ ወይም በጦር ኃይሎች ጠቅላይ መምሪያ ውስጥ የመምሪያ መኮንን ሆኖ መሥራት ነው፡፡ በያዘው ማዕረግም እስከ አምስት ዓመት ከአገለገለ በኋላ ወይም 35 ዓመት በጦር ኃይሎች ውስጥ አገልግሎት ከሰጠ ጡረታ ይወጣል፡፡ የጡረታ ዕድሜውም 62 ዓመት ነው፡፡ ከዕድሜው ጣራ ውጭ በተለየ ሁኔታ በሥራ አስፈላጊነት አራት ዓመት በተጨማሪ የመስራት አማራጭ አለው፡፡ እድሜውም እስከ 64 ዓመት ሊዘልቅ ይችላል፡፡
 ሐ. ሊዩተናንት ጄኔራል፡ ይህ ማዕረግ በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ባለ ሦስት ኮከብ ከፍተኛ የጀኔራልነት ማዕረግ እርከን ነው፡፡ አንድ መኮንን ወደ ሌ/ጀኔራልነት ማዕረግ ከመድረሱ በፊት በጦር ኃይሎች ውስጥ በአመራር ከ 20 ዓመት ያልበለጠ አገልግሎት መስጠት አለበት፤ ከሜ/ ጀኔራል ማዕረግ ወደ ሌ/ጄነራል ማዕረግ ለመሸጋገር መሟላት ያለበት የአመራር ብቃቱ፣ በያዘው ማዕረግ የቆይታው ጊዜ፣ በወታደራዊ ሥነ-ምግባር ምንም አይነት ችግር የሌለበት፣ የአመራር የሥልጠና እርከኖችን ያለፈ፣ እና ክፍት የሥራ ቦታ መኖሩ ናቸው፡፡ ሌ/ጀኔራል ከሆነ በኋላ የሥራ ኃላፊነቱም የኮር ወይም የግንባር ወይም የህብረት የጥምር ጦር አዛዥ እና በሀገር መከላከያ ጠቅላይ መምሪያ፣ የመምሪያ መኮንን ሆኖ ማገልገል ነው፡፡ መኮንኑ በያዘው ማዕረግ ቢያንስ ሦስት ዓመት ማገልገል አለበት ነገር ግን በያዘው ማዕረግ አምስት ዓመት ከአገለገለ እና በጦር ሀይሎች ውስጥም 40 ዓመት ካገለገለ በጡረታ ይገለላል፤ የዕድሜ ጣሪያውም 62 ዓመት ይሆናል፡፡

መ. ጄኔራል፡ ይህ ማዕረግ ከሌ/ጄነራል ቀጥሎ ከፊልድ ማርሻል  ዝቅ ያለ ባለ አራት ኮከብ ማዕረግ ሲሆን በጦር ኃይሎች ማዕረግ አሰጣጥም ከፍተኛው የሹመት እርከን ነው፡፡ ከሌ/ጀኔራልነት ወደ ሙሉ ጀኔራልነት የማዕረግ እድገት ለመሸጋገር በቅድሚያ ክፍት የስራ ቦታ ሲኖር፣ በጦር ሀይሎች ውስጥም 20-23 ዓመት ያገለገለ፣ የአመራር ብቃት እና ልምዱ ስኬታማ የሆነ፣ በወታደራዊ ሥነ ምግባሩም ምንም ዓይነት እንከን የሌለበት፣ ለአመራርነት የሚሰጠውን ከፍተኛ የሳይንስና የጥበብ ሥልጠና እርከኖችን በተዋረድ የጨረሰ መሆን ይኖርበታል፡፡ የሙሉ ጀኔራል የኋላፊነት ቦታም በጦር ኃይሎች ውስጥ የምድር ጦር ወይም የአየር ኃይል አዛዥ ወይም የህብረት ዕዝ አዛዥ ወይም የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ወይም የጦር ኃይሎች አዛዥ ሆኖ መሥራትን ያጠቃልላል፡፡ በያዘው ማዕረግ ቢያንስ አምስት ዓመት ያገለገለ ሆኖ በጦር ሀይሎች ውስጥ ያበረከተው የአገልግሎት ጣራ  40 ዓመት ከሞላ ጡረታ ይወጣል፡፡ የዕድሜ ጣሪያውም 64 ዓመት ይሆናል፡፡
የአንድ ሀገር የጦር ኃይል (የምድርኃይል፣ የአየር ኃይል፣ የባህር ኃይል) ከዚህ በታች በተጠቀሱት  ሦስት አይነት የአመራር ደረጃዎች  ማለትም፦
  1. በቀጥተኛ የግንባር መስመር አመራር መኮንኖች
  2. በከፍተኛ አመራር መኮንኖችና
  3. በስትራቴጂክ አመራር መኮንኖች የተደራጀ መሆን ይኖርበታል፡፡
በሰራዊቱ ውስጥ ጄነራል መኮንኖች የሆኑ ሁሉ የሥትራቴጂክ አመራር አካል ናቸው፡፡ አንድ መኮንን የብ/ጄነራል ማዕረግ ለመድረስ 22 ዓመት ማገልገል አለበት ከዚህ ውስጥ ከ7-8 ዓመታት ያለው ጊዜ የወታደራዊ የአመራር ጥበብ ሳይንስ የሚቀስምበት የዕውቀት ጉዞ መንገድ ነው፡፡
በአጠቃላይ የጄነራል መኮንኖች የወታደራዊ አመራር ጥበብ ሥልጠና መነሻው መሰረታዊ ከሆነው ከዕጩ መኮንንነት የሥልጠና እርከን ተነስቶ እስከ መጨረሻው የፖሊሲ እና ስትራቴጂ ትንተና ጥናት እና ምርምር ተቋም እስከ ሆነው የጦር ኮሌጅ ድረስ ይዘልቃል፡፡ የአመራር የሥልጠና እርከኖችን ያላለፈ ጄኔራል የተሟላ ተክለ ሰውነት እንደሌለው ይታሰባል ወይም ይቆጠራል፡፡

5.    የቀድሞው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አመራሮች የሥልጠና ሂደት፤

በሀገራችን የመከላከያ ሠራዊት ታሪክ ውስጥ የወታደራዊ ትምህርትና ሥልጠና ከፍተኛ ቦታ እና ትኩረት ነበረው፡፡ በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት የነበረው የመከላለከያ ሚኒስቴር ሁለት የጦር አካዳሚ ትምህርት ቤቶች ነበሩት፡፡ እነዚህም የሐረር ጦር አካዳሚና የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በትንሽ ዓመት ቆይታ የተቋቋመ በርካታ ብርቅዬ የጦር መኮንኖችን በጥራት ያስመረቀ ተቋም ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ ከ1ኛ ኮርሰ እስከ 54ኛ ኮርስ ድረስ መኮንኖችን ያስመረቀ ቢሆንም በደርግ ጊዜ በነበረው የርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የማሰልጠን ሥራውን ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ማካሄድ ተስኖት ነበር፡፡
የሐረር ጦር አካዳሚ እ.ኤ.አ 1957 ከተቋቋመ አንስቶ እስከ ተዘጋበት 1977 ድረስ በርካታ መኮንኖችን አስመርቋል። አካዳሚው ለጎረቤት ሀገሮች ጭምር መኮንኖችን ያሰለጥን ነበር፤ ሁለቱም የጦር ትምህርት ቤቶች አለም ዓቀፍ የአመራር ስልጠና መመዘኛ ስታንዳርድን በጠበቀ መልኩ ተደራጅተው ብዙ አመራሮችን አሰልጥነው በማስመረቅ ለሃገሪቱ አበርክተዋል፡፡ ከእነዚህ የጦር አካዳሚ ት/ቤቶች ከተመረቁ መኮንኖች ውስጥ ከምክትል መቶ አለቃነት  እስከ ሌ/ጀኔራልነት ማዕረግ የደረሱ ይገኙበታል፡፡እነዚህ ጄኔራል መኮንኖች በወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ የተካኑና በሥነምግባር የታነፁ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የተማሩ ከፍተኛ ብቃት እና ችሎታ ያላቸው ሀገራቸውን በወታደራዊ መስክ ያስጠሩ ብርቅዬ የኢትዮጵያ የሀገር መመኪያ ልጆች ነበሩ፡፡ የሐረር ጦር አካዳሚ  ከ1ኛ ኮርስ እስከ 21ኛ ኮርስ ድረስ በማስተማር አስመርቋል፡፡
በወቅቱ የነበሩት የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ጦር ኃይሎች የመከላከያ ሥልጠና ፖሊሲ በሚያዘው መሠረት ወታደራዊ የአመራር ጥበብና ሳይንስ በተገቢው ሁኔታ ከዕጩ መኮንን ሥልጠና እስከ ስታፍ ኮሌጅ ድረስ የዘለቁ 293 ጄነራል መኮንኖች ነበሩት(ሰንጠረዥ-ለን ይመልከቱ)።
ሰንጠረዥ–ለ፦ በሦስቱም መንግሥታት የተሾሙ ጄነራል መኮንኖች (1927–2007 ዓ/ም)
.
የማ ደረጃ
1927 እስከ 1983
ከ1983 ጀምሮ
ጠቅላላ ድምር
 ኃይለሥላሴ
ርግ
ህወሓት/ ኢህአዴግ
1
ጄኔራል
0
0
1
1
2
ሌ/ጄኔራል
15
3
6
24
3
ሜ/ጄኔራል
6
32
24
62
4
ብ/ጄኔራል
63
174
99
336
ጠቅላላ ድምር
84
209
130
423
በአጠቃላይ እነዚህ ጄኔራል መኮንኖች በዚህ ጽሁፍ ዋና አካል ላይ የተቀመጡትን የወታደራዊ አመራር ሥልጠና እርከኖች ይዘት እና ሂደት አሟልተው የተመረቁና በተግባር በጦር ሜዳ ውሎአቸውም አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡ እንደነበሩ ድርሳናቸው ያስረዳል፡፡

6.    የአሁኑ  የሀገር መከላከያ መኮንኖች ከወታደራዊ አመራር ሳይንስና ጥበብ አንፃር

የዛሬው የሕወሓት ሰራዊት ከሽምቅ ተዋጊነት በቀጥታ መደበኛ የሀገሪቱ ሠራዊት እንዲሆን በምድር ሀይልና በአየር ሀይል ተከፋፍሎ  እንዲደራጀ የተደረገ ሲሆን ሠራዊቱን እንዲመሩ የተመደቡት የበታች ሹሞችና መኮንኖች በሙሉ በምንም ዓይነት ወታደራዊ የአመራር ስልጠና ውስጥ ሳያልፉና ከወታደራዊ ሙያ ሳይንስና  ሕግጋት ውጭ በዘርና በፖለቲካ ወገንተኝነት ላይ በመመሥረት ማዕረግ በጅምላ የተሰጣቸው ናቸው:: ይህ ደግሞ በሀገሪቷ መጥፎ የታሪክ ጠባሳ እየጣለ ይገኛል።
በወታደራዊ የአመራር ስልጠና ታሪክ ያለምንም የአመራር ስልጠና የጄነራል መኮንነት ማዕረግ የሰጠች የመጀመሪያ አፍሪካዊት አገር ኢትዮጵያ ነች:: ሕወሓት/ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ከ1983 ጀምሮ እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ ለ130 አባሎቹ (ለዝርዘሩ አባሪ ፩ን ይመልከቱ)  የጄኔራል መኮንነት ማዕረግ የሰጠ ሲሆን 97 በመቶ የሚሆኑት ተሿሚዎችም በምንም ዓይነት የወታደራዊ አመራር ሳይንስና ጥበብ ስልጠና ውስጥ ያላለፉ ናቸው። ወደ 52 በመቶ (67ቱ) የጄኔራል መኮንንነት ቦታም የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የህወሓት አባላት ተቆጣጥረውታል (ሰንጠረዥ-ሐን እና ሥዕል-አንድን ይመልከቱ)::
በአጠቃላይ ከላይ በሥዕሉና በሠንጠረዡ እንደተመለከትነው፤ ሂደቱ የሀገሪቱን የወታደራዊ ስልጠና ገጽታን ከማበላሸቱም በላይ መጥፎ የታሪክ ጠባሳ እየጣለ ይገኛል:: በሚገርም ሁኔታ የሀገር መከላከያ የስትራቴጂክ አመራር እንዲሰጡ በህዋሓት የተሾሙ ጄነራል መኮንኖች  መሰረታዊ የሆነውን የአመራር ስልጠና እንኳን ያልወሰዱ እና የአካዳሚክስ እውቀታቸው በጣም ዝቅተኛና በአብዛኛው ከ5ኛና ከ9ኛ ክፍል ያላለፈ መሆኑን የግል ሕይወት ታሪካቸው ያሳያል።
አንድን ሠራዊት ለመምራትም ሆነ ለማሰልጠን ቀድሞ ሰልጥኖ መገኝት ጥያቄ ውስጥ ሊገባና ሊጣስ የማይችል መርህ ነው:: የህወሓት መንግስት ከፈጸመው አስከፊ ወንጀል አንዱ ምንም ዓይነት የወታደራዊ አመራር ትምህርትና ስልጠና ሳያገኙ ጄነራል ብሎ በመሰዬም ሠራዊት እንዲመሩ ማድረጉ ነው:: የአሁኑ ጄኔራል መኮንኖች በአካዳሚክስም ሆነ በወታደራዊ ሳይንስና የአመራር ጥበብ ድህነት የተጎዱ፣ ጫካ በነበሩበት ወቅት መደበኛ ባልሆነ የሽምቅ ውጊያ ዕውቀት ብቻ ተኮፍሰው የኖሩ አሁንም በዚያው መንገድ የሚጓዙ ናቸው::
የህወሓት ጄነራል መኮንኖች  ስለወታደራዊ አመራር ጥበብ ስልጠና ምንነትና ይዘት እንዲሁም  ሂደት  ምን እንደሆነ ግንዛቤ የሌላቸውና የማወቅ ፍላጎት የሌላቸው ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት በአስተርጓሚ እንዲማሩ ተሞክሮ ነገር ግን ሳይሳካ መቅረቱ በተጨባጭ የሚታወቅ ነው፡፡ ምክንያቱም “አሁን እኛ ጄነራል መኮንኖች ስለሆንን አንማርም ምን ያደርግልናል” በሚል ነበር።  በአሁኑ ወቅት ሠራዊቱ እየተመራ ያለው በእነዚህ ዓይነት ሰዎች ነው! የሚገያስርመው ነገር በሚመሩት ሰራዊት ወስጥ የሚገኙ የመካከለኛ እና የዝቅተኛ አመራር መኮንኖች በወታደራዊ የአመራር ስልጠና ንድፈ ሀሳብም (Theory) ሆነ ተግባራዊ ስራዎች አለቆቻቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ይበልጧቸዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት እድሉ ቢሰጣቸው እነዚህን ጄኔራሎች በብቃት መልሰው ሊመሯቸው የሚችሉ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የወታደራዊ ሳይንስ ንድፈ ሀሳብ (theory) እንደሚያሳየው አንድ ወታደር መኮንን የሚባለው የአመራር ጥበብ በመውሰድ በተገቢ ሁኔታ ካጠናቀቀ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ንድፈ ሀሳብ  አንፃር ለህወሓት ጄኔራል መኮንኖች ምን ስም ቢሰጣቸው ይመጥናቸዋል? የበታች ሹም ቢባሉ፣ ለበታች ሹምነት ማዕረግ የሚያበቃውን የአመራር ስልጠና አልወሰዱም፡፡ ከበታች ሹም ቀጥሎ ወደታች ያለው ማዕረግ ቢሰጣቸው ደግሞ እሱንም እንኳን ለማሟላት መደበኛ የሆነውን መሠረታዊ የወታደራዊ  ስልጠናም አልወሰዱም፡፡ በዚህ ነባራቂ ሐቅ በመንተራስ ከተራ ወታደር በስተቀር ሊሰጣቸው የሚችል ምንም ዓይነት መጠሪያ ስም የለም፡፡ ሕወሓቶች ጫካ እያሉም ሆነ አሁን የሚጠራሩበት “ተጋዳላይ እከሌ” “ወዲ እከሌ” የሚለው መጠራሪያቸው የሚመጥናቸው ይመስላል፡፡ ለምሳሌ ሌ/ጄነራል ብለው የሾሙትን ከፍተኛ መኮንን ወዲ ወረዳ እያሉ ይጠራሉ፡፡ ይህ ባጠቃላይ ሲታይ ሠራዊቱ የአንድ መደበኛ ሠራዊት አካልነት ባህሪም ሆነ ተግባር አይታይበትም።
የህወሓት ጄኔራል መኮንኖች የወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ፣ ዕውቀትና አመራር አናሳና ደካማነት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በተጨባጭ በግልጽ የተከሰተበት የታሪክ አጋጣሚ ታይቶ አልፏል:: ይህ ጦርነት እልፍ አዕላፍ የሆኑ የደሃው ኢትዮጵያዊውያን/ት ልጆች ህይወት የተቀጠፈበትና የሀገሪቷ አንጡራ ሀብት የወደመበት አስከፊ ጦርነት ነበር:: ለዚህ ደግሞ ተጠያቂዎቹ:-
1ኛ፡ የሕወሓት ከፍተኛው አመራር እና
2ኛ፡ የህወሐት ስትራቴጂክ አመራር ሰጭ ጄኔራሎች ናቸው
ከላይ የተጠቀሱት የሕወሓት ጄኔራል መኮንኖች  የወታደራዊ ትምህርትና ስልጠና ሳይወስዱ ወይንም ሳይቀስሙ ሠራዊቱን እንዲመሩ በመደረጋቸው ከፍተኛ ጉዳትና አደጋ ደርሷል:: ይህ ሁኔታ ጥቅጥቅ ባለ ጨለማ ውስጥ መኪና ያለመብራት መንዳት ወይም መኪናን ያለመሪ ለመንዳት እንደሚደረግ ሙከራ ያህል ይቆጠራል::
በአጠቃላይ የመኮንኖች የወታደራዊ አመራር ጥበብ ሥልጠና ምንነትና ይዘት እንዲሁም ሂደቱን እና የመኮንኖች የማዕረግ ዕድገት አሰጣጥ መነሻውም ሆነ መድረሻው የወታደራዊ ትምህርትና ስልጠና መሆኑን በሚገባ ከተጨባጭ ሁኔታ ጋር አይተናል፡፡

2.    ማጠቃለያ

ይህ ጥናታዊ ፅሁፍ በአጠቃላይ የወታደራዊ ትምህርት እና ስልጠና ይዘትና ሂደት ምን እንደሚመስልና  አሁን ያለውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚመሩትን ጄኔራል መኮንኖችን  ዓለም ከደረሰበትና  ተቀባይነት ካለው የወታደራዊ ትምህርትና ስልጠና ስታንዳርድ እንፃር የሙያ ብቃት ደረጃቸውን በመመዘንና በመተንተን  በጥልቀት ለመዳሰስ ሙከራ አደርጓል። የወታደራዊ ሳይንስና የአመራር ጥበብ ሥልጠና በተዋረድ ከመሰረታዊ ሥልጠና ወደ ቀጣዩ ስልጠና እንዴት እንደሚሸጋገርና እንደሚገባ፣ ሥልጠናው የሚያካትታቸው የትምህርት ዓይነቶች ፣ ከሥልጠናም በኋላም በኃላፊነት ሊመሩት የሚችሉት ኃይልና የወታደር ብዛት፣ የሥልጠናው የቆይታ ጊዜ፣ እንዲሁም ሥልጠናውን ሲጨርሱ የሚሰጠው የትምህርት ማስረጃ እና ከተወሰነ አገልግሎት በኋላ ከአንዱ የአመራር ሥልጠና ወደ ሌላው የአመራር ሥልጠና እርከን እንዴት እንደሚሸጋገሩ ሥዕላዊ በሆነ መለኩ በማቅረብ ሳይንሳዊ የሆነ የአመራር ሥልጠና ሂደት ዋነኛው እና ትልቁ መንገድ መሆኑን ያመለክታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ አንድ ጀኔራል መኮንን በሚያዝዘው  ኃይል ውሰጥ ለየእርከኑ አመራር ሰጭ ሊሆኑ  የሚገባቸውን ማዕረጋቸውን፣ የኃላፊነት ቦታና ሠራዊቱ የሚዋጋበትን የጦርነት ህግ፣ ሰራዊቱ የሚሰለጥንበትን የስልጠና ፖሊሲ፣ የወታደራዊ ዶክትሪንና ስትራቴጂ  መቅረጽ መቻል ያለበት መሆኑን ያስረዳል:: አሁን መሬት ላይ ያለው ሐቅ የሚያሳየው ግን ተሿሚዎቹ ክህሎቱ እና ችሎታው የሌላቸው በመሆኑ ከላይ የተዘረዘሩትን አንድ ብቃቱ የተረጋገጠለት ጀኔራል መኮንን ሊፈፅማቸው የሚገባ ተግባራት በብቃት ማከናወን እንደማይችሉ ጥናቱ ያስረዳል:: የእነሱ ዶክትሪንና ስትራቴጂ ቀረጻ መሬት ወረራ ፣ ዝርፊያ፣ ምዝበራ፣ አፈናና ዜጎችን በውጭ ሀገራት ሳይቀር እንዴት መጥለፍ እንደሚቻል ያተኮረ ላቅ ያለ ተንኮል ብቻ ነው:: በአንድ ወቅት ሟች ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጄነራል መኮንኖቹን ሲገመግሙ ያስቀመጡትን ድምዳሜ በመጥቀስ ፅሁፍን እናበቃለን። “እናንተ በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴም ሆነ በደርግ ዘመነ መንግስት ከነበሩት ጄኔራል መኮንኖች ጋር ስትነፃጸሩ የሰማይና የምድር ያህል ትራራቃላችሁ:: የእናንተ ችሎታ አንድ ሻለቃ  ወይም 400 መቶ ሰው ያለው ሀይል ከማዘዝ  ያለፈ አይደለም!’’
በመጨረሻም ከዚህ በታች በተቀመጠው አባሪ ሰነድ ሰንጠረዥ ፩፤ ሕወሓት/ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ከ1983 ዓ.ም. አንስቶ እስካሁን ድረስ የጦር ኃይሉ የተዋቀረው በአንድ ብሔር (በትግራይተወላጆች) የበላይነት፣ ያለአንዳች የወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ ሥልጠና መሆኑን ማንም ሊያስተባብለው በማይችል መልኩ ጥሬ ሐቁ ተቀምጧል። ይህ በራሱ ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለምን በዚህ አሳዛኝ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና፣ የማኅበረሰባዊ ዝቅጠት ላይ እንደምትገኝ ቁልጭ አድርገው ከሚያሳዩት ተግዳሮቶች (Factors) አንዱ ሊሆን ይችላል።

3.    አባሪ ሰነድ- ፩ (Annex-1)



የወያኔው ወመኔዎች መንግስት የደህንነት ቡድን በድጋሚ በአዲስ መልክ ተዋቀረ

Oktober 5,2014
ምንሊክ ሳልሳዊ
የቀድሞው መዋቅር ከተቃዋሚ ሃይሎችና ለሚዲያዎች የመረጃ ክፍተት ፈጥሮላቸዋል።
– የዲያስፖራውና የተቃዋሚዎች ትግል ፍሬ ማፍራቱ የደህንነት ተቋሙን አደፍርሶታል።…
– የተጀመረው ፍሬያማ ትግል እያደገ መሄዱ መጪውን ጊዜ ለወያኔ ጨለማ አድርጎበታል።
የተቃዋሚ ሃይሎች እና የዲያስፖራው ህዝባዊ ተቃውሞ በርትቶ እና ገኖ መውጣት፣በፓርቲው ውስጥ የሚነሱ ጥያቄዎች ፣የካድሬዎች እንቢተኝነት፣ የውጪ ሃይሎች ጫና፣ የህዝብ እሮሮ እና አቤቱታ አጣብቂኝ ውስጥ የከተቱት ወያኔ የሃገሪቱን እና የሕዝቡን አንጡረ ሃብት ስድሳ ከመቶውን ካለምንም እውቅና በዘፈቀደኝነት ለደህንነት እና ለስለላ ተግባር የመደቡት ከፍተኛ የሕወሃት አመራሮች የሚመራ የደህንነት ቡድን በአገሪቱ በአዲስ መልክ እንደገና መዋቀሩን ምንጮች አስታውቀዋል።
ኢሕአዴግ ውስጥ በተነሳው የብሩህ ተስፋ ክሽፈት የመጣ በባለስልጣናቱ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ድንጋጤ መከሰቱን ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ ውጥረት አመራሮችን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷቸዋል። ባለፉት 23 አመታት በህዝብ እና በሃገር ላይ የተደረገው ከፍተኛ የሆነ በደል እና ዘረፋ በሕዝቡ ዘንድ ጥርስ እንዳስነከሰባቸው እና መጪው ጊዜ ይጨልምብናል ብለው ከፍተኛ ስጋት ስላደረባቸው በአራት ቡድኖች የተከፋፈለ በሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች የሚመራ እና በመላው ሃገሪቱ የተበተነ የድህንነት እና የስለላ ሃይል ማሰማራታቸው ታውቋል።
tplf-rotten-apple-245x300በከፍተኛ የሕወሃት አመራሮች የሚመራ የደህንነት ቡድን በአገሪቱ በአዲስ መዋቅር ዳግም የተዋቀረው በየአከባቢው ከመንደር እና ቀበሌ ጀምሮ እስከ ከተሞች የገጠር ወረዳዎች ዘልቆ በመግባት በወያኔ ላይ ደባ ይሰራሉ ይፈጸማሉ ይመከራሉ የተባሉ እያንዳንዱን የዜጎች እንቅስቃሴዎች ሪፖርቶችን በትጋት በመሰብሰብ ወደ መሃል አገር በመላክ መታፈን ያለባቸው መገደል ያለባቸው ደብዛቸው መጥፋት ያለባቸውን ሰዎች በተመለከተ ከበላይ በሚተላለፍለት ትእዛዝ መሰረት መፈጸም ዋናው ስራው ነው።
ወያኔ የሚጠራው መጪው ምርጫ ሕዝቡ በ1997 እንዳደረገው አሁንም እንዲሁ ቂሙን በካርድ ይገልጽብናል በማለት የሚሰጋው ወያኔ መጪውን ምርጫ ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን ተቃውሞ ከፍተኛ የሆነ የሃይል እርምጃ በመጠቀም ለማክሸፍ የሚያስችለው በየትኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ሊሆን እንደሚችል ስለላውን ተያይዞታል፤በፓርቲው ውስጥ የሚነሱ ጥያቄዎች የካድሬዎች እንቢተኝነት የውጪ ሃይሎች ጫና የህዝብ እሮሮ እና አቤቱታ አጣብቂኝ ውስጥ የከተቱት ወያኔ ማጣፊያው አጥሮት የሃገሪቱን ግማሽ በጀት የሚሆነውን ለደህንነት እና ለስለላ ተግብር በማዋል ከፍተኛ የሆነ አደጋ በሃገር ላይ አውጆ ሕዝብን እያሸበረ ይገኛል።

Sunday, October 5, 2014

ሰልጣኙንም አሰልጣኙንም ያንገሸገሻቸዉ ሥልጠና

Oktober 5,2014

አባትና የ10ኛ ክፍል ተማሪ ልጁ አምርረዉ ሲጨቃጨቁ እናት ትደርስና . . . . እባክሽ ልጄ አባትሽ የሚልሽን ለምን አትሰሚም ብላ ልጇን ትቆጣታለች። ልጅት ከተቀመጠችበት ትነሳና ምነዉ እማዬ ምኑን ነዉ የምሰማዉ፤ አባዬኮ እሱ እራሱ የማያዉቀዉን ነገር ላሳይሽ እያለኝ ነዉ ብላ ንግግሯን ሳትጨርስ በቁጣዉ ብዛት ፊቱ እንደ ፊኛ ያበጠዉ አበቷ ካንቺ ማወቅ ዬኔ አለማወቅ ይሻላል፤ ይልቅ የምልሽን ስሚ ብሎ ጮኸባት። ወጣቷ ተማሪ ወላጅ አበቷ ከስምንተኛ ክፍል በላይ ዘልቀዉ እንዳልተማሩ ብታዉቅም ለግዜዉ ማድረግ የምትችለዉ ምንም ነገር አልነበረምና እሽ አባዬ ብላ አባቷን መስማት ጀመረች። ይህ የአባትና የልጅ ስሚኝ አልሰማም ጭቅጭቅ ባለፉት ሁለት ወራት መሀይሞቹ የወያኔ ካድረዎችና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በየስልጠና አዳራሹ ያደረጉትን ፍጥጫ አስታወሰኝ። ይህ አብዛኛዉን ዕድሜያቸዉን ትምህርት በመማር በሳለፉት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና በወጉ ስምንተኛ ክፍልን ባላጠናቀቁ የወያኔ ካድሬዎች መካከል በክረምቱ ወራት ተጀምሮ አሁን ድረስ የዘለቀዉ የ”አሰለጥናለሁ አታሰለጥንም” ትንግርታዊ ድራማ ወያኔ አስካሁን ከሰራቸዉ ድራማዎች በአይነቱ ለየት ያለ ድራማ ነዉ።
የወያኔ ምርጫዎች ምንም አይነት ዉድድር የማይታይባቸዉ ማንም ተወዳደረ ማንም ወያኔ ብቻ የሚያሸንፍባቸዉና ምርጫዎቹ ከመካሄዳቸዉ በፊት የት ቦታ እነማን ማሸነፍ እንዳለበቸዉ ተወስኖ ያለቀላቸዉ የለበጣ ምርጫዎች ናቸዉ። ወያኔ ግን “ሌባ ላመሉ ዳቦ ይልሳል” እንደሚባለዉ ምርጫዉ በቀረበ ቁጥር የሚያክለፈልፍ በሽታ ይይዘዋል። ኢትዮጵያ ዉስጥ በ1997ና በ2002 ዓም የተደረጉትን ምርጫዎችና እርግጠኞች ነን አሁንም በ2007 ዓም የሚደረገዉን ምርጫ የሚለያያቸዉ ነገር ቢኖር በእያንዳንዱ ምርጫ መኸል የአምስት አመት ልዩነት መኖሩ ነዉ እንጂ የምርጫዉን ዝግጅት፤ ሂደትና ዉጤት በተመለከተ ይህ ነዉ ተብሎ ሊነገር የሚችል ልዩነት የለም። ሁሉም ምርጫዎች የሚካሄዱት ወያኔ የምርጫ ተቋሞች፤ ሜድያዉንና ፍርድ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ በሚቆጣጠርበት ሁኔታ ዉስጥ ነዉ። በዚህ ላይ ቅድመ ምርጫዎችን የሚቆጣጠረዉ፤ በምርጫዉ ብቸኛ ተወዳዳሪ የሆነዉና ህዝብ የሰጠዉን ድምጽ የሚቆጥረዉ ወያኔ እራሱ ነዉ። ይህም ሁሉ ሆኖ ወያኔ ከሱ ዉጭ ማንም ምርጫዉን እንደማያሸንፍ በልቡ እያወቀ አምስት አመት እየቆጠረ የሚመጣዉ ምርጫ በቀረበ ቁጥር ግርግር መፍጠር ይወዳል። በ1997 በተደረገዉ ምርጫ ማንም አያሸንፈኝም ብሎ ሜድያዉንና የፖለቲካ ምህዳሩን ትንሽም ቢሆን ለቀቅ አድርጎ የነበረዉ ወያኔ በ2002 ዓም ይጋፉኛል ብሎ የጠረጠራቸዉን ሁሉ ማሰር፤ መደብደብና እንቅስቃሴያቸዉን መግታት ጀመረ። አሁን በ2007 ዓም ደግሞ ገና በግንቦት ወር ለሚካሄደዉ ምርጫ የኢትዮጵያን ወጣት ካልተቆጣጠርኩ በሚል ትልቅ ዘመቻ ጀምሮ በከፍተኛ በሁለተኛ ደረጃና ዩኒቨርሲቲ ዉስጥ የሚገኙትን የአገሪቱ ወጣቶች በሥልጠና ሰበብ ወያኔያዊ የፖለቲካ ጠበል እያጠመቃቸዉ ነዉ።
ብዙ ኢትዮጵያዊያን ወያኔን ዘረኛ ነዉ፤ ጎጠኛ ነዉ፤ ነብሰ ገዳይ ነዉ ይሉታል። አዎ እነዚህ ሁሉ የወያኔን ማንነትና ምንነት በትክክል የሚያሳዩ ቃላት ናቸዉ። ወያኔ ግን ከእነዚህ ዉጭ ሌሎች ብዙ መገለጫዎች አሉት፤ ለምሳሌ ወያኔ መዋሻት የማይሰለቸዉ ዉሸታም ነዉ፤ ዕኩይ ነዉ፤ ጨካኝና የለየለት መብት ረጋጭም ነዉ። እነዚህ የወያኔ ባህሪያት ሁሉ ያናድዱናል ወይም ያስቆጡናል እንጂ አይገርሙንም ወይም እየኮረኮሩ አያስቁንም። ጉደኛዉ ወያኔ የሚገርሙና የሚያስቁ ባህሪያትም አሉት። ወያኔ የቁጥር ጨዋታ ይወዳል፤ በተለይ ከቁጥርና ከቁጥርም በዛ ካለ ቁጥር ጋር ለየት ያለ ፍቅር አለዉ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ የአገር ዉስጥ ምርት ከዉጭም ከዉስጥም ተገፍቶ 5% ከጨመረ ወያኔ የሚነግረን 10% አደገ ብሎ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ የትምህርት ጥራት ተንኮታኩቶ ከመዉደቁ የተነሳ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀዉ ወደ ስራ አለም በሚገቡ ተማሪዎችና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን ጨርሰዉ ኮሌጅ በሚገቡ ተማሪዎች መካከል ያለዉ ልዩነት ትንሽ ነዉ፤ ወያኔ ግን በኔ ዘመነ መንግስት የዩኒቨርሲቲዉ ብዛት ብቻ ሳይሆን ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ተማሪዎች ብዛት ከ300% በላይ አደገ እያለ ይፏልላል። ካለፈዉ ሐምሌ ወር ጀምሮ ያለፍላጎታቸዉና ያለፈቃዳቸዉ በግድ ወደ ሥልጠና ማዕከላት እየገቡ የወያኔን ርካሽ ፕሮፓጋንዳ እንዲጋቱ የሚገደዱ ወጣቶችም ጉዳይ ይህንኑ ወያኔ ከቁጥርና ከብዛት ጋር የተጠናወተዉን ፍቅር የሚያሳይ ነዉ። ይህ ወያኔ በየክልሉ ሥልጠና ብሎ የጀመረዉ ቧልት የሰልጣኛቹን እዉቀት የሚያዳብር አይደለም ወይም ለአገራችን ለኢትዮጵያም በምንም መልኩ የሚጠቅም አይደለም። የሥልጠናዉ ብቸኛ አላማና ጥቅም በወጣቱ ላይ ተፅዕኖ በማሳደር የወያኔን አባላት ማብዛት ነዉ። ወያኔ ድርጅታዊ የፓርቲ ስራዎችን የሚሰራዉ መንግስታዊ ተቋሞችን በመጠቀም ከመንግስት ካዝና በሚወጣ ገንዘብ ነዉና እሱን የሚያስደስተዉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አባላት አሉት ተብሎ መነገሩ ነዉ እንጂ እነዚህ አባላት ታማኝ ይሁኑ አይሁኑ ወይም ድርጅታዊ ስራ ይስሩ አይስሩ ለወያኔ ጉዳዩ አይደለም።
ወያኔ በዕረፍት ላይ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ከያሉበት በግድ አስመጥቶ ሥልጠና እንዲወስዱ ለማድረግ የወሰዳቸዉ እርምጃዎች ሁሉ በወያኔና በተማሪዎቹ መካከል ያለዉን ሰፊ የፖለቲካ ልዩነት አጉልቶ ከማዉጣቱ ባሻገር ይህ ሳይጀመር የከሸፈዉ ስልጠና ለወያኔ ምንም የፈየደዉ ፋይዳ የለም። እንዳዉም አብዛኛዉ ተማሪ የወያኔ መሪዎችን አንገት የሚያስደፋ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ሥልጠና የሚያስፈልገዉ ለተማሪዎቹ ሳይሆን ለራሳቸዉ ለአሰልጣኝ ነን ባዮቹ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። በብዙዎቹ የስልጠና አዳራሾች የወያኔ ካድሬዎች ተማሪዎቹ የሚጠይቁትን ጥያቄ መመለስ አለመቻላቸዉ ብቻ ሳይሆን ካድሬዎቹ በሚጠየቁት ጥያቄ እየተበሳጩ ጥርሳቸዉን ሲነክሱ ታይተዋል። በእርግጥም ጎንደር ዉስጥ የነበረዉን ጄኔሬተር ነቅላችሁ ዬት አደረሳችሁት ከሚል አፋጣጭ ጥያቄ ጀምሮ አንዳርጋቸዉ ጽጌን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን በጠየቁ ተማሪዎች ላይ አሰልጣኝ ካድሬዎች “ከእናንተ ጋር በኋላ እንገናኛለን” እያሉ ሲዝቱ ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያ ትናንትም ዛሬም ካለ ለጋሽ አገሮች ዕርዳታ መንፈቅ መዝለቅ የማትችል ደሃ አገር ናት፤ ሆኖም የወያኔ መሪዎችና ቤተሰቦቻቸዉ የሚዘርፉትን ገንዘብና አላግባብ የሚያባክኑትን የአገር ሃብት የተመለከተ ማንም ሰዉ ድርጊታቸዉ ከደሃዋ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በፍጹም እንደማይገናኝ ለመገንዘብ ግዜ አይፈጅበትም። ወያኔ ገነባሁ ብሎ የሚያፈርሳቸዉንና በየስብሰባዉና በየጉባኤዉ ከሚያባክነዉ ግዙፍ የአገር ኃብት ዉጭ ከሰሞኑ ምንም አገራዊ ጥቅም በሌለዉና ሠልጣኞቹ አንፈልግም ብለዉ ለተዉት ሥልጠና የሚያባክነዉ የህዝብና የአገር ገንዘብ እጅግ በጣም ብዙ ነዉ። ለምሳሌ ለአሰልጣኝ ካድሬዎች ከሚወጣዉ የትርንፖርትና የዉሎ አበል ዉጭ ለእያንዳንዱ ሰልጣኝ ተማሪ በቀን የሚከፈለዉ ሃምሳ ብር ቁጥራቸዉ ከ600 ሺ በላይ በሆኑ ሰልጣኝ ተማሪዎች ልክ ሲሰላ እጅግ በጣም ብዙ ገንዘብ ነዉ።
ለመሆኑ ዜጎች የሚላስና የሚቀመስ አጥተዉ በሚራቡበት አገር፤ ወጣቶች ስራ ፍለጋ ያደጉበትን መንደር ጥለዉ ባሕር እየተሻገሩ በሚሰደዱበት አገርና የገንብዘብ እጥረት እየተባለ ብዙ ፕሮጀክቶች በሚታጠፉበት አገር ወያኔ ከየት እያመጣ ነዉ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እየከፈለ ምንም እርባና የሌለዉ የፖለቲካ ሥልጠና ሥልጠናዉ በፍጹም ለማያስፈልገዉ የህብረተሰብ ክፍል የሚሰጠዉ? ደግሞስ ከዉጭ አገር ምንጮች ምንም አይነት የገንዝብ እርዳታ እንዳያገኙ በህግ የተከለከሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የስራ ማስኬጃ ወጪያቸዉን መሸፈን አቅቷቸዉ በሚንገዳገዱበት አገር ምን ቢደረግ ነዉ ወያኔ የራሱን ፓርቲ ስራዎች በመንግስትና በህዝብ ገንዘብ የሚያሰራዉ?
የወያኔና የገንዝብ ጉዳይ ከተነሳ እነዚህ ጉደኞች ቢነገር ቢነገር የማያልቅ ከገንዘብ ጋር የተቆራኘ ብዙ የቆሸሸ ታረክ አላቸዉ። ከሰሞኑ ኢትዮጵያ ዉስጥ የአገሪቱን የአየር ሞገዶች ከዳር እስከ ዳር ያጨናነቀዉ ከዚሁ ከወያኔ የረጂም ግዜ ቆሻሻ ታሪክ ጋር የተያያዘዉ የገንዘብ ጉዳይ ነዉ። ከሰሞኑ የኢትዮጵያን ባንኮች፤ ትላልቅ መደብሮችና ዘመናዊ የመገበያያ አዳራሾች በብዙ መቶ ሚሊዮኖች በሚቆጠር ሀሰተኛ ገንዘብ ተጨናንቀዋል። ይህ ማን፤ መቼ፤ ከየትና እንዴት እንዳሰራጨዉ የማይታወቅ የሀሰተኛ ገንዝብ ዝርጭት ኢትዮጵያ ዉስጥ እያንዳንዱን ሰዉ እያነጋገረ ነዉ። የወያኔ ፖሊሶች ከየባንኩና ከየገበያ አዳራሹ በየቀኑ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ሀሰተኛ የብር ኖቶች እየሰበሰቡ መሆናቸዉን ቢናገሩም ከዚህ ሀሰተና ገንዘብ ስርጭት በስተጀርባ የማን እጅ እንዳለበት ግን ምንም የተነፈሱት ነገር የለም። እንደዚህ ብዛት ያለዉ ሀሰተኛ የገንዘብ ኖት ደግሞ አቅምና እዉቀት በሌላቸዉ ተራ ወንጀለኞች የሚሞከር ወንጀል አይደለም። ለዚህም ይመስላል ብዙ ኢትዮጵያዉያን በዚህ ሀሰተኛ ገንዘብ ስርጭት ዉስጥ ያለምንም ጥርጥር የወያኔ ባለስልጣኖች እጅ አለበት ብለዉ በድፍረት አፋቸዉን ሞልተዉ የሚናገሩት። መቼም መሬት ቆፍሮ ቦምብ እየቀበረ በተቃዋሚዎች የሚያሳብበዉና በፈንጂ ህዝባዊ ተቋሞችን እያፈረሰ ሽብርተኛ ብሎ በፈረጃቸዉ ድርጅቶች ላይ ጣቱን የሚቀስረዉ ወያኔ የደረሰበትን ከፍተኛ የገንዘብ ጉድለት ለመሙላት ሀሰተኛ ገንዘብ አሰራጭቶ ሊያጠፋቸዉ በሚፈልጋቸዉ ሰዎችና ቡድኖች ላይ አያመካኝም ማለት አይቻልም። ለሁሉም የወያኔ ነገር አንቺዉ ታመጪዉ አንቺዉ ታሮጪዉ ነዉና ይህ የሀሰተኛ ገንዘብ ስርጭት የራሱ የወያኔ ስራ እንደሆነ ከራሱ ዉስጥ አዋቂ ምንጮች የምንሰማበት ግዜ ሩቅ አይደለም። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዉያንን የሙጥኝ ብሎ ተጣብቆ የሚያሰቃያቸዉ የዋጋ ንረት መሠረታዊ መንስኤዉ መለስ ዜናዊ በህይወት ከነበረበት ግዜ ጀምሮ ከአገሪቱ የማምረት አቅም በላይ በሆነ መልኩ በገፍ እየታተመ ወደ ኤኮኖሚዉ ዉስጥ እንዲገባ የተደረገዉ የገንዘብ አቅርቦት ነዉ። ይህ ዘንድሮ ስሙን ቀይሮ “ሀሰተኛ የገንዝብ ስርጭት” ተብሎ አገራችንን የሚያምሳት በሽታም የዚሁ የተለመደ ወያኔ እያተመ የሚያሰራጨዉ የገንዘብ አቅርቦት ችግር አካል ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለዉም። አለዚያማ ወያኔ በነጋ በጠባ ሚሊዮንና ቢሊዮን እያለ የሚያባክነዉ ገንዘብ ከዬት ይመጣል?
ስልጠና በየትኛዉም ማህበረሰብ ዉስጥ የእዉቀትና የልምድ ልዉዉጥ ለማድረግ የሚረዳ ጠቃሚ ተግባር ነዉ፤ ሆኖም ስልጠና ሲባል አላማ፤ አትኩረትና ግብ ኖሮት በተወሰነ ቡድን ወይም ቡድኖች ላይ የሚያነጣጥር የእዉቀትና ልምድ መቀባበያ መሳሪያ ነዉ እንጂ እንዳዉ በጅምላ የአንድ አገር ህዝብ እንዳለ ተመሳሳይ ስልጠና ይዉስድ እየተባለ የሚደገስ የጨረባ ተዝካር አይደለም። ደግሞም ስልጠና አሰልጣኝና ሰልጣኝ ተግባብተዉና ሁለቱም ሚናቸዉን ወድደዉና ፈቅደዉ የሚካሄድ የጋራ እንቅስቃሴ ነዉ እንጂ ሠልጣኝ አልሰልጥንም ካለና አሰልጣኝ ደግሞ ጥያቄ የጠየቀዉን ሁሉ “ቆይ ጠብቀኝ” እያለ የሚዝትበት ከሆነ ነገሩ ሥልጠና መሆኑ ቀርቶ ጦርነት ይሆናል። ለመሆኑ ወያኔ የአገሪቱን ወጣቶች ሥልጠና ብሎ ሰብስቦ ምንድነዉ የሚላቸዉ? መልሱ ቀላል ነዉ። ከብዙዎቹ ሰልጣኞች አንደበት በግልጽ እንደሰማነዉ፤ የወያኔ ካድሬዎች በየስልጠናዉ አዳራሽ የሚናገሩት በሚቀጥለዉ ምርጫ ኢህአዴግን ካልመረጣችሁ የወደፊት ዕድላችሁ ይጨልማል፤ ከሐይማኖት አክራሪዎች እራሳችሁን አጽዱ ወይም ከሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር እንዳትተባበሩ እያሉ ነዉ። ወያኔ በስልጣን ላይ በቆየባቸዉ አመታት ህይወቱ እንደ ሐምሌ ጨለማ የጨለመበት የኢትዮጵያ ወጣት ግን በየስልጠና አዳራሹ በተደጋጋሚ የሚጠይቀዉ እነሱ ሽብርተኛ ብለዉ ያሰሯቸዉን ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ባስቸኳይ እንዲፈቱና ወያኔዎችን እራሳቸዉን በሐይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አትግቡ እያለ ነዉ።
ባለፈዉ የአዲስ አመት ዋዜማ ምሽት የግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊ/መንበር ለኢትዮጵያ ወጣቶች ኑና ለነጻነት፤ ለፍትህና ለእኩልነት አብረን እንታገል የሚል አገራዊ ጥሪ አድረገዋል። በየዘመኑ ለወገኖቹ መብትና ነጻነት መከበር ሽንጡን ገትሮ የታገለዉ የኢትዮጵያ ወጣት የነጻነት መሪዉ ያቀረበለትን የፍትህና የእኩልነት ትግል ጥሪ ረግጦ ከወያኔ ጋር በተላላኪነት ከሚያስተሳስረዉ ሥልጠና ጋር በፍጹም እንደማይተባበር ሁላችንም እርግጠኞች ነን። ዛሬ ዕድሜዉ ከ35 አመት በታች የሆነ ኢትዮጵያዊ ወጣት አብዛኛዉን ዕድሜዉን በወያኔ ስርዐት ዉስጥ የኖረ ወጣት ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ የዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ወጣት ወንድሙ፤ ዘመዱ ወይም የቅርብ ጓደኛዉ በወያኔ ነብሰ ገዳዮች ሲገደሉ በአይኑ እየተመለከተ ያደገ ወጣት ነዉ። ይህ ወጣት የወያኔ በደልና ግፍ የሚነገረዉ ወጣት ሳይሆን ይህንን በደልና ግፍ ለማቆም ቆርጦ የተነሳ ወጣት ነዉ። ይህ ወጣት ወያኔ ሥልጠና እያለ የሚፈጥርለትን አጋጣሚ ሁሉ እየተጠቀመ እራሱንና ወገኖቹን ነጻ ያወጣል እንጂ በሥልጠና ስም ከወያኔ በሚመጣለት ኮቶቶ እጅና እግሩን አስሮ የወያኔ ባሪያ ሆኖ አይኖርም። ለዚህ ቆራጥና አርቆ አስተዋይ ለሆነ ወጣት ያለን መልዕክት አይዞህ፤ በርታ፤ ጽና በድል የምንገናኝበትና የአገራችን ባለቤት የምንሆንበት ቀን ቅርብ ነዉ የሚል ወገናዊ መልዕክት ነዉ።

ከጋምቤላ ክልል ሜጢ የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ወደ አዲስ አበባ ከመጡት ውስጥ ስምንቱ ታስረዋል።

Oktober 5,2014
- መኢአድ በመጪው ሰኞ አለም አቀፍ ጋዜጣዊ መግለጫ እሰጣለሁ አለ።
- የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተፈናቃዮችን እየተመላለሱ በሰብአዊነት በመርዳት እና በማጽናናት ላይ ናቸው።
- የአዲስ አበባ ሆስፒታሎች ተጎጂዎችን ለማጉላላት ያደረጉት ሙከራ በመኢአድ አባላት ጥ
ረት ክሽፏል።
- የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ተፈናቃዮቹን እንዲጎበኙ መኢአድ ጥሪውን አቅርቧል።


ባለፉት ሳምንታት በምእራብ ኢትዮጵያ በጋምቤላ ክልል በሚጤ ከተማ ከመሬት ቅርሚያ ጋር በተያያዘ በወያኔ ካድሬዎች ቀስቃሽነት ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ የተደረጉ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ችግር ውስጥ በቴፒ የሚገኙ ሲሆን የተወሰኑት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በመኢአድ ቢሮ ውስጥ ተጠልለው የተጎዱት በመታከም ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።

ወደ አዲስ አበባ ከደረሱት ተፈናቃዮች እና ተጎጂዎች መካክል መኢአድ ቢሮ ሳይደርሱ ከመንገድ ላይ ታፍነው የተወሰዱ ስምንት ተፈናቃዮች በስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ ጉዳዩን የሚከታተሉ የጉዳዩ ባለቤቶች በሰጡት መረጃ የታወቀ ሲሆን ሁኔታውን ለማረጋገጥ ተሞክሮ ፖሊስ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። እንዲሁም ሲፈናቀሉ ጉዳት የደረሰባቸው አዲስ አበባ የደረሱ ተጎጂዎች ህክምና እንዲያገኙ ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ ውጣ ውረድ በሆስፒታሎች የደረሰባቸው ሲሆን የቀበሌ መታወቂያ ወይንም የተፈናቀሉ መሆኑን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ከክልሉ አምጡ በማለት ለማጉላላት የተደረገው ጥረት በመኢአድ አባላት ብርቱ ጥረት መክሸፉ ሲታወቅ ተጎጂዎቹ ህክምና እንዲያገኙ ተደርጓውል።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መኢአድ ባደረገው ጥሪ መሰረት አስፈላጊዎን ሰብአዊ እርዳታ እያደረጉ ሲሆን አሁንም የህዝቡን እርዳታ እና አጋርነት ለተጎጂዎቹ በተከታታይነት እንዲቀጥል እንዲሁም የሃገር ቢት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተጎጂዎችን በመጎብኘት አጋርነታቸውን እንዲያረጋግጡ በድጋሚ መኢአድ ጥሪ አቅርቧል። በመጭው ሰኞ አለም አቀፍ ጋዜጣዊ መግለጫ በቢሮው እንደሚሰጥ ያስታወቀው መኢአድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እያደረጉ ያሉትን ሰብአዊ እርዳታ እና መጽናናት በማድነቅ በዚህ እንዲቀጥሉ የሰብአዊነት ጥሪውን አቅርቧል።
ምንሊክ ሳልሳዊ