July 27/2014
ታሪክማ ሊረሳ አይገባም
ታህሣሥ 7 ቀን 1966 ዓ.ም የነጌሌ ጦር አባሎች ለአዛዦቻቸው ላለመታዘዝ ወሰኑ። የምድር ጦር አዛዥ የነበሩት ሌተና ጄኔራል ድረሴ ዱባለ አማፅያኑን እንዲያረጋጉ በታዘዙት መሠረት የመንግሥት ልዑካን ይዘው ታህሣሥ 23ቀን 1966 ዓ.ም ነጌሌ ጦር ሠፈር ገብተው ሠራዊቱን ሲያነጋግሩ የተጠበቀውን መልስ ስላልሰጡ እርሳቸውም ከነተከታዮቻቸው ታገቱ፡፡ በ27/4/66 በአየር ኤታማጆር ሹም በጄኔራል አበራ ወልደማርያም የሚመራ የዓፄው ልዑካን ቡድን ወደ ነጌሌ ተልኮ በመደራደር፣ ታጋቾችን ሊያሰፈታ ቻለ። ነገር ግን ያድማው መነሻ ኢኮኖሚ-ተኮር ቢመስልም፣ አንደምታው በሌሎችም የጦር ኃይሎች ካምፖችም ውስጥ በመዛመቱ ምክንያት፣ መለዮ ለባሹ ለአብዮት ፍንዳታ አጋር ኃይል እንደሚሆን መሠረታዊ ለውጥ ለሚፈልጉ ተራማጅ ኃይሎች የምሥራች ሆኖ በግልፅ ይታይ ነበር።
የነጌለው አድማ የፖለቲካ አጀንዳ ይዞ ደብረ ዘይት የአየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ወደሚገኝበት ብቅ አለና የጎጃሙን ተወላጅ ማስተር ቴክኒሺያን ግርማ ዘለቀን እና በሕቡእ አብረው የተደራጁትን እነ ሲኒየር ቴክኒሽያን አበበ አረጋን፣ እንዲሁም ከጎረቤት የአየር ወለድ ጦር የተባበሩለትን ባለሌላ ማእረጎችን አገኛቸው። እነርሱም ታሪክ ለመሥራት ለአብዮታዊ ተግባር ተነሱ! በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ዘርዘር አድርጌ እንደምገልጸው፣ ጀግናው ግርማ ዘለቀ ከፍተኛ መኮንኖችን አግቶ የአየር ኃይሉን ከተቆጣጠረ በሗላ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር በስልክ በቀጥታ ፖለቲካዊ ድርድር ጀመረና አስደናቂ ወጤት አስገኘ። ባላሌላ ማዕረጎች (non-commissioned officers)፣ አየር ኃይልን የሚያክል አግራዊ ተቁአም ተቆጣጥረው የፖለቲካ ለውጥ ሲያስገኙ በየትም ተነግሮ አያወቅም።
የ“እኛና አብዮቱ” ደራሲ ጠቅላይ ምኒስትር ፍቅረስላሴ ወግደርስ የአየር ኃይል መኮንን ስለነበሩ ይህን ምዕራፍ በመጽሐፈቸው ለምን እንዳላካተቱት በመገረም ለጊዜው በጥያቄ ልለፈው።
ወደሚቀጥለው አርዕስት ከመሸጋገሬ በፊት፣ በሙስና ያልተበከሉ የወያኔ የመከላከያ፣ የደህንነተና የበላይ ከበርቴ አለቆቻቸውን በቀጥር ስር በማወወል የጀገናውን ግርማየ ዘለቀን ምሳሌ በመከተል ሰላማዊ ለውጥ ለማምጣት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እዲያደርጉ መማፀን ከዓላማዬ ውስጥ አንዱ ነው።
ስለዚች ጽሑፍ ዓላማ ጥቂት ልዘርዘር
አብዮቱ በየካቲት ወር 1966 ዓ.ም (18/6/66) ሲፈነዳ፣ ለብዙሀኑ ብሩህ ተስፋ የፈነጠቀ መስሎ ታይቶ ነበር። ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ደም ያላፋሰሰ ሰላማዊ ትግል ሂደቱ፣ “ኢትዮጵያ ትቅደም፣ ያለምንም ደም” በሚል መፈክር ዙሪያ ሕዝቡን አሰልፎ እንደ ነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
በ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት በቀጥታ የተሳተፍነውና በውስጡም ስንጓዝ ያጋጠሙንን ተግደሮቶችና የተከሰቱትን ሁነቶች ለታሪክ ጸሐፊዎች በማስረጃ ማቆየት የዜግነት ሞራላዊ ግዴታ ነው። እግዚአብሔር ረዢም እድሜ ሰጥቶኝ እስከ አሁን ስለአደረሰኝ በአብዮቱ ሂደት ወቅትና በፊት በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ላይ በሀላፊነት ላይ ተመድቤ ሳገለግል፣ ካካበትኩት የሥራ ልምድና በዚያም ሳቢያ በእጄ የገቡትን ሰነዶችና የመዘገብኳቸውን የግል ማስታወሻዎች በመመርኮዝ፣ በኔ አስተያየት ወቅታዊ ናት ብዬ ያመንኩባትን፣ ይህችን አጭር ጽሑፍ ለአንባቢ አቅርቤያለሁ።
ስለሆነም፣
- በ1966ቱ አብዮት መዳራሻና ዋዜማ የዓፄው መንግሥት ወታደሮችና የፖሊስ ሠራዊት ወገናዊነታቸውን ለሕዝብ በማሰየት ዘውዳዊውን አገዛዝ በመገርሰስ ያስመዘገቡትን አኩሪ ታሪክ፣ የወያኔም የመከላከያ ሠራዊት፣ የፈፌዴራል ፖሊስና የብሔራዊ ደህንነት ተቋም አባላት በበኩላቸው በአርአያነት እንዲከተሉ በአጽንኦት መምከር አንዱ ዋና ዓላማዬ ነው።
- የዛሬው የኢትዮጵያ ትውልድ፣ ከ1996 ጀምሮ ላለፉት 40 ዓመታት በእናት ሀገራችንና በህዝቦቿ ላይ ያደረሰው ውድቀት እንዳይደገም ከታሪክ በትክክል ተገንዘቦ ላንዴና ለመጨረሻ የሚደረገውን የነጻነት ዘመቻ እንዲቀላቀል አሳስባለሁ።
- ጀግናው ማስተር ግርማ ዘለቀ እና ቆራጥ የትግል ጓደኞቹ እንደነ ሲኒየር ቴክኒሽያን አበበ አረጋ፣ ማስተር ቴክኒሽያን አየለ ኃይሌ የመሳሰሉትን ይዞና የአየር ወለድ መለዮ ለባሾችን አሰተባብሮ፣ ከሁለቱም ወገን ከፍተኛ መኮንኖችን አግቶ፣ አብዮታዊ የፖለቲካ ጥያቄ ለአፄው መንግሥት ስላቀረበ፣ የ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ኃብተወልድ ካቤኔ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ የስንብት ደብዳቤ ለዓፄው አቅርቦ ደም ሳይፋሰስ በሰላም መሰናበቱንና በልጅ እንዳልካቸው ካቢኔ መተካቱን ላንባብያን ሳስታውስ፣ ምትክ የማይገኝላቸው ጠቅላይ ምኒስትር አክሊሉ ላሳዩት አርቆ አስተዋይነትና የፖለቲካ ብስለት አድናቆቴን እየገለጽኩ ነው።
በ1966ቱ አብዮት የኔን ተሞክሮ በተመለከተ በተለይ ለታሪክ ጸሐፈት የሚሆን አንድ መጽሐፍ ለማዘጋጀት ማቀዴን በዚህ አጋጣሚ እገልጻለሁ። ምክንያቱም፣ ጠቅላይ መምሪያው የሚገኝበት ግዙፍ የደብረ ዘይት አየር ኃይል ጣቢያ፦
- ምሁራን ከአዲስ አበባና ካካባቢዋ እንዲሁም ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ፣ ከአፈሪካና ከእስያ እየመጡ ፣ የተወያዩበት፣ ያስተማሩበት፤
- ፖሊሲና ፕላን የሚዘጋጅበት፤የአብዮቱን ፍንዳታ ተከትሎ ከባድ የውሳኔ ሀሳቦች የፈለቁበት፤
- የአብዮቱን ፍንዳታ ተከትሎ ልዩ ልዩ የፖለቲካ ድርጅቶች አባሎቻቸውን በሕቡእ ለመመልመል የተረባረቡበት፤
- የአየር የአየር ኃይል ሠራዊት ተሰብስቦ የዘውድ ሥርዓትም ሆነ የወታደራዊ መንግሥት በፍፁም ስለማንፈልግ፣ ሕዘባዊ መንግሥት እንዲቋቋም የውሳኔ ሃሰብ የሰጠበት፤
- የዳበረ ዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት የተከማቹበት፤
- ዘመናዊ ላቦራቶሪዎችና የጥገና ወረክሾፖች የሚገኙበት፣
- ለ34 ለዩ ልዩ ሙያዎች የሥልጠና ፋሲሊቲ የተዘጋጀበት፤
- የንጉሠ ነገሥቱ የከፋፍለህ ግዛው ሥርዓት ተንኮል የተጋለጠባት፤
ስፍራ ነው። በእጩ መኮንንነት ተምሬ የተመረቅሁበት፣ ያስተማርኩበት እስካ ከፍተኛ ደረጃ አዛዥነት የሠራሁበት አመቺ ስፍራ እንደመሆኑ፣ መረጃዎችን ማግኘት ቀላል ስለሆነልኝ መጽሐፉን ለማዘጋጀት በእግዚአብሔር ፍቃድ ሥራዬ እንደማይከብደኝ አምናለሁ።
ከአብዮት ፍንዳታ እስከ ወታደራዊ ደርግ ምሥረታ
አብዮቱ ሊከሰት መዳረሻ ላይ ሕዝባዊው ንቅናቄ እየጎለበተ በመሄዱ መንግሥት ተጨነቀ። ሁኔታውን ለማቀዘቀዝ የአድማ መሪዎች ከጦሩ ውስጥ ጃንሆይ ፊት ቀርበው ይቅርታ እንዲለምኑ መንግሥት መላ መታ። የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንደሚባለው!
ሴራው ግን አልሰራም። ከአየር ኃይል ከኔ ጭምር በርካታ መኮንኖችና ባለሌላ ማዕረጎች፣ እስከዛሬ ግልጽ በልሆነልኝ መመዛኛ ተመርጠን ኢዩቤልዩ ቤተመንግሥት ሄደን ለግርማዊነታቸው ታማኝነታችንን እንድንገልፅና በየቦታው የተፈጠረውን አለመረጋጋት እንድናወግዝ የተሰጠንን መመሪያ ለመተግበር፣ በአውቶቡስ ተሳፍረን ወደ አዲሰ አበባ (ሸገር) ጉዞ ጀመርን። ተልዕኳችን ለሚዲያ ፍጆታ የታለመ ተንኮል በመሆኑና እኛ መጠቀሚያ በመደረጋችን ነገሩ በጣም አናደደን። ወደ አዲስ አበባ እሩ መንገድ እንደተጓዝን፣ በታቀደው ጊዜ ቤተ መንግሥት ላለመድረስ፣ እቃ ረስተናል፣ ዩኒፎርም መቀየር አለብን በሚል ሰበብ ሹፌሩ ወደ ደብረዘይት መኮንንኖች ሠፈር እንዲመለስ በፈጠርነው ዘዴ ጊዜ ለማባከን ተቻለ። ዘግይተን ከቤተመንግሥቱ ስንደረስ፣ አዛዣችን ሜጀር ጄኔራል አበራ ወልደማርያም በንዴት ጦፈው ዋናው በር ላይ ጠበቁን። ሌሎች ሰዓታቸውን ጠብቀው የመጡት የምድር ጦር፣ የብሔራዊ ጦር፣ እና የፖሊስ ሠራዊት ተወካዮች የተፈለገውን የታማኝነትና የአድመኞችን ኩነና መግለጫ ካሰሙ በሗላ ዓፄው ስለአሰናበቷቸው፣ አዛዣችን ምርጫ ስላልነበራቸው በብስጭት ተቆጥተው ወደ ቤተመንግሥቱ ግቢ ሳንገባ ከውጪው አሰናበቱን።
የተፈለገውን ታማኝነት ባላመግለፃችን ረክተን ተመልሰን ደብረ ዘይት ከተማ ስንደርስ፣ ያልጠበቅነው ሁኔታ አጋጠመን። የአየር ኃይልና የአየር ወለድ መለዮ ያጠለቁ ባለሌላ ማዕረጎችና ወታደሮች ተሰባጥረው ባንክ ቤቱን አዘግተው ጥበቃውን ተቆጣጥረውታል። ትላልቅ ሱቆች ተዘግተዋል። ወደቤቴ ሄጄ ምሳዬን ከበላሁ በሗላ በግል መኪናዬ ወደቢሮዬ ሄድኩ።
ማስተር ቴክኒሽያን ግርማ ዘለቀ፣ የአየር ኃይል መሣሪያ ግምጃ ቤት ሀላፊ እንደመሆኑ የመጋዘኑን በር ከፍቶ በውስጡ የሚገኙትን የነብስ ወከፍ መሣሪየዎች ለባለሌላ ማዕረጎች (ቴክኒሽያኖች) ካስታጠቀ በሗላ፣ በርሱ መሪነት በሕቡእ ይንቀሳቀስ የነበረው ቡድን ይፋ ወጣና ደብረ ዘይት የምንገኝ የንጉሠ ነገሥቱ አየር ኃይል ከፍተኛ የአመራር ባለሥልጣናት ታግተን በተለያዩ ስፍራዎች የካቲት 18 ቀን 1966 ዓ.ም ታጎርን፡፡ የጦር ሠፈሩም ባሳሪዎቻችን ቁጥጥር ስር ዋለ። ከሻለቃ ማዕረግ በታች ያሉ መኮንንኖች ያልታገቱ ቢሆንም ምንም ዓይነት መሣሪያ ሳይታጠቁ በግቢው (ካምፕ) ውስጥና ውጪ ይንቀሳቀሱ ነበር።
ከላይ ከተጠቀሰው እገታ በሗላ፣ አጋቾች ዐቢይ የፖለቲካ ለውጥ እንዲደረግ በርካታ ጥያቄዎችን ለመንግሥት አቀረቡ። በዚህ ሂደት ውስጥ ማስተር ቴክኒሽያን ግርማ አልፎ አልፎ ከግርማዊነታቸው ጋር በስልክ እየተገናኘ ለሚያቀረቡለት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ይደራደር ነበር። ለምሳሌ እናንተ በአድማ ላይ እያላችሁ ሱማሊያ የኢትዮጵያን ድምበር አልፋ ብትወር ምን ይደረጋል ብለው ጃንሆይ ሲጠይቁት፣ አድማችንን በቅጽበት አቁመን ወራሪዉን በመግረፍ ይህንን የጋለ ቁጣችንን በጠላት ላይ እናበርዳለን ሲል ማስተር ቴክኒሽያን ግርማ ዘለቀ እንደመለሰላቸው ከእገታ በሰላም ከተለቀቅን በሗላ ለማወቅ ችያለሁ። እውነትም ማ/ቴክኒሽያን ግርማ እንዳለው፤ አብራሪዎች እና ቴክኒሲያኖች ስለአልታገቱ ተዘጋጅተው በተጠንቀቅ ላይ ስለነበሩ ተዋጊ አውሮፕላኖች ከደብረ ዘይት፣ ከድሬዳዋና ከአስመራ አየር ጣቢያዎች በመነሳት፣ ከሶሰተኛው ክፍለ ጦር ጋር በመተባበር ባጭር ጊዜ ውስጥ ውጊያ ለመግጠምና ጠላትን ለማዳሸቅ ይቻል ነበር።
በቁጥጥር ስር የዋልነው ከፍተኛ መኮንኖች በታሰርን በሶስተኛወ ቀን ከያለንበት ተወስደን በባለ ሌላ ማእረጎች ክበብ ምግብ ቤት ምሳ ከበላን በሗላ በአቅራቢያው ከሚገኝ አንድ ሰፊ አዳራሽ ውስጥ እንድንሰበሰብ ተደረገ። ሁለት ባለሌላ ማዕረግ ቴክኒሽያኖች፣ አንዱ ሽጉጥ ሌላው ኦቶማቲክ (ኡዚ) የያዘ ከፊታችን ቆሙ። ዙሪያውን ስመለከት ጥቁር ቱታ የለበሱ ፊታቸው ላይ ቁጣ የሚታይባችው ኦቶማቲክ መሳሪያ የታጠቁ ቴክኒሲያኖች ቆመዋል። ሽጉጥ የያዘው ቴክኒሽያን፣ እምባ እየተናነቀው አስተምራችሁ አሳደጋችሁናል፣ በማህበራዊ ኑሮም ተሳስረናል፣ አበልጆችም የሆን አለን በማለት እርምጃ ለመውሰድ የተገደዱበትን በመግለፅ ላይ እያለ ንግግሩን ሳይጨርስ፣ ከአጠገቡ የቆመው ጓደኛው ከመቅጽበት ሽጉጡን ከጁ ነጠቀውና ድራማው አበቃ። የገረመኝ ነገር ይህ ሁሉ ሲሆን ታጋች መኮንኖች ሁኔታውን ከቁብ አልቆጠነውም፡፡
ድራማው ቢያበቃም እስከዛሬ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን አጭሮ አልፏል። ዕውን ሊረሽኑን ኖሯል? ወይስ መንግሥት የአጋቾችን የፖለቲካ ጥያቄ በአስቸኳይ እንዲመልስ ለማስገደድ? የክብር ዘበኛ አዛዠ ሌተና ጄኔራል አበበ ገመዳ የአየር ኃይልን ጦር ሠፈር በመድፍ ኢላማ ወስጥ አስገብቼዋለሁና ጃንሆይ ከፈቀዱልኝ ልምታው ብለው ፈቃድ ጠይቀው ስለተነፈጉ፣ አጋቾቻችን ሕይዎት ለማጥፋት እርምጃ ከመወሰድ ተቆጥበው ይሆን?
ጃንሆይ ምህረት የማድረጋቸውን ዜና ለማሰማት፣ ምክትል የእልፍኝ አስከልካያቸው ሜጀር ጄኔራል አሰፋ ለማ፣ የመጡ መሆኑን አጋቾቻችን አበሰሩን። ከዚያም ከአየር ኃይል ካምፕ ውጪ ጋራ በሩ ተብሎ በሚጠራው ተራራ አቅጣጫ በሚገኝ ጥቅጥቅ ባለ ቁጥቋጦ በተከበበ ገላጣ ሜዳ ላይ ታጋጆች ከፍተኛ የአየር ኃይል መኮንንኖች ብቻ እንድንኮለኮል ተደረገ። ቀደም ሲል ከኛ ጋር ታግተው የነበሩት የአየር ወለድ ጥቂት መኮንንኖች አልነበሩም። ለምን እንደሆነ እስከ አሁን ይገርመኛል።
ምን ሊመጣ ነው ብለን ስንጠባበቅ፣ የአየር ወለድ አዛዥ ኮሎኔል የዓለምዘውድ ተሰማ፣ በጥይት የተሞላውን ዝናር በወገቡ ዙሪያና ከጀርባው በትከሻው ላይ እስከ ጉልበቱ ድረስ አንዠርንጎ መትረየሱን አንግቦ ከጥቂት አጃቢዎቹ ጋር ከቁጥቋጦ ውስጥ ወጥቶ ኩስትር ብሎ ከታጋቾች ፊት ለፊት ቆመ። ነገሩ ያልጠበቅነው እንደመሆኑ ይህ ወራሪ ከጎረቤታቸን በማን ታዞ ነው የመጣብን ሳንል አልቀረንም።
የኮሎኔል የዓለም ዘውድ ወገናዊነት ከማን ጋር እንደሆነ ገና ንግግሩን ሲጀምር ግልፅ ሆነ። ግርማዊነታቸው ይቅርታ ያደረጉልን መሆኑን አበሰረን። ለሠራዊቱም በወር ሰባት (7) ብር ደሞዝ በዓፄው መልካም ፍቃድና ትእዛዝ ለመከላከያ ሠራዊት የተጨመረ መሆኑን አስታወቀን። ዝምታን ያዘለ ተቃውሞ ለጥቂት ጊዜ ሠፈነ። ከዚያ እጄን አወጣሁና ለመሆኑ ደሀው ገበሬ ከየት አምጥቶ ነው የተባለውን የደሞዝ ጭማሪ የሚከፈለን ብዬ ላነሳሁት ጥያቄ መልሱ በደፈናው ገንዘቡ አለ ከየትም ይገኛል ሆነ። ያሳፍራል! ቀጥሎም ከታገትነው ውስጥ አንዱ ኮሎኔል (ጌታሁን እጀጉ) እኛ ታሳሪ፣ እናንተ አሳሪና መሐሪ የተሆነበት ምክንያት እንቆቅልሽ እንደሆነበት አምርሮ ተናገረ። ለዚህ ጠንካራ ተቃውሞ ኮሎኔል የዘውድዓለም ምላሽ አልሰጠም፤ ታጋቾች ኮሎኔሉን በትዝብትና በንቀት ዓይን ይመለከቱት ነበር። ስብሰባውም በዚህ አበቃና ወደ ሌላ ቦታ ተወሰድን። ምንስ አጥፍተን ነው የጃንሆይ ‘ምህረት’ በአየር ወለድ አዛዠ የሚበሰርልን የሚለው ጥያቄ እስከዘሬ ድረስ በአዕመሮዬ ውስጥ ይመላለሳል።
ከኮሎኔል የዓለምዘውድ አሳፋሪ ድራማ ተላቀን ወደ ካምፓችን እንድንመለስ ተደረገና በአየር ኃይል ሠልጣኞች ክበብ አዳራሽ ውስጥ ተሰበሰብን። መልከ መልካሙ አጅሬ ግርማ ዘለቀ ብቅ ብሎ እፊታችን ቆመ። ማራኪው ቁማናው እንዳለ ሆኖ የሚያማምሩት ትላልቅ ዓይኖቹ እንቅልፍ ከማጣት ምክንያት ይመስለኛል ቀልተዋል። ግርማ፣ ከፊትለፊቱ ለተቀመጥነው ከሻለቃ እስከ ብ/ጄኔራል ማዕረግ ላይ ለምንገኝ ከፍተኛ መኮንኖች፣ ስለታሰርንበት ምክንያት እጅግ የሚመስጥ አጭር ንግግር አደረገ። ከአንድ መሪ የሚጠበቅ በሳልና ድንቅ ንግግሩንም፣ “እኛ በያዘችሁት ሥልጣን ስሩበት ብለን ተነሳን እንጂ ልንነጥቃችሁ አይደለም” በማለት ዘግቶ በሰላም አሰናበተን። ጥሪውና መልእክቱ ወቅታዊውን ሁኔታ ያካተቱ ጥርት ያሉ በመሆናቸው፣ ታጋቾች ትንፍሽ ሳንል አንዳች ጥያቄም ሆነ አስተያየት ሳንሰጥ ወደየቤታችን ሄድን። ተዳክሞ የነበረው የመንግሥት አስተዳደር ባስከተለው በደል ተነሳስተው፣ የምናዛቸው ባለሌላ ማዕረጎች የፖለቲካ ለውጥ ጥያቄ እስኪያነሱ ድረስ እኛስ ከፍተኛ መኮንኖች ምን እንጠብቅ ነበር? በበኩሌ መንፈሳዊ ቅናት ተሰምቶኝ እንደነበር አልክድም። ለውጡንም ሰላማዊ እስከሆነ ድረስ ከልብ ለመደገፍ ወሰንኩ።
መሪ ይወለዳል ወይስ በሥልጠና ይታነፃል? በኔ እምነት ግርማ ዘለቀ ከመሪነት ባሕርዩ ጋር የተወለደ ነው። በየካቲት 1966 አብዮት ያሳየው አመራረና ብስለት ካስገኘው ውጤት ጋር ሲገመገም፣ የመንግሥት ካቤኔ በሰላም ሥልጣኑን ሲለቅ በኢትዮያ ታሪክ የመጀመሪያው ነው።ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየ ዐቢይ ሰላማዊ ለውጥ ነው ለማለት እደፍራለሁ። ለዚህም ድንቅ ክንውን ማስተር ቴከኒሽን ግርማና አብዮታዊ ግብረ-አበሮቹ የሚመሰገኑ ናቸው። ለዚህ አንፀባራቂ ድል፣ ታሪክ ክሬዲቱን ለግርማና ለትግል ጓደኞቹ እንደሚሰጥ ጽኑ ተስፋ አለኝ።
የካቲት 20 ቀን 1966 ዓ.ም፣ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ኃብተወልድ ካቢኔ የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ ለንጉሠ ነገሥቱ በይፋ ያቀረበው ጥያቄ ከፀደቀ በሗላ፣ የዘውድ ምክር ቤት ሌ/ጄኔራል ዐቢይ አበበ እንዲተኩ ቢያሳሰብም እርሳቸው ፈቃደኛ ሁነው ባለመገኘታቸው፣ ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ተሹመው የአክሊሉ ካቢኔ በሰላም ሊተካ ቻለ። የቀድሞው ካቢኔ በሰላም ከሥልጣን መውረድ በምእራባውያን ዲፐሎማቶች ዘንድ እንደ ሰላማዊና ደም ያላፋሰሰ ለውጥ የተወደሰና የተደነቀ መሆኑን አንድ የፈረንሳይ ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ለሥራ ጉዳይ ደብረ ዘይት መጥተው ስለነበር እግረመንገዳቸውን ቢሮዬ ጎራ ብለው እንደነገሩኝ አስታውሳለሁ። ምን ጊዜም ምትክ የማይገኝላቸው፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ደም እንዳይፋሰስ በማሰብ ላሳዩት በሳል አመራርና ሥልጣን ለመልቀቅ ላደረጉት ውሳኔ የላቀ ምሥጋና ይገባቸዋል እላለሁ።
ከእገታ ከተለቀቅን በሗላ፣ ሥነሥርዓትና ወታደራዊ ዲሲፕሊን በማስፈን አመራር መስጠት አንገብጋቢ ጥያቄ ሆነ። የዓፄው ሥርዓት የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲውን መተግበር ቀጥሎበታል። ስለሆነም ከጎረቤታችን ከአየር ወለድ ጦር ጋር መቃቃር ቀጥሏል። ሕዝባዊ እንቅስቃሴውም እያየለ ቀጥሏል። ስለዚህ ተወዳጁ አዛዣችን ብ/ጄኔራል አሰፋ ገብረእግዚ ሠራዊቱን ሰበስበው ምን መደረግ እንዳለብት በእሳቸው መሪነት ሰፊ ውይይት ተካሄደ። እጄን አወጣሁና፣ የሀገር መውደድ የሚለካው በክንዳችን ላይ በለጠፍነው ወይም በትከሻችን ላይ በተሸከምነው ማዕረግ ሳይሆን ከእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ከሚመነጭ ፍቅር ነውና፣ ሕዝባዊ እንቅስቃሴውን በሕቡዕ የምትመሩት ባለሌላ ማዕረጎች በዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ ተመካክራችሁበት አቋማችሁን በፍጥነት ወስናችሁ ውጤቱን ለአዛዣችን አስታውቁ ብዬ ሀሳብ ሰጠሁ። ታዳሚው ባንድ ድምፅ በሀሳቡ ተስማማና ያንኑ ሌሊት መልካም ዜና የሚያበስር ወረቀት ተበትኖ አደረ። ሙሉ ወታደራዊ ዲሲፕሊን ሰፍኖ፣ አዛዥና ታዛዠ ተከባበሮ፣ ሠራዊቱ በአንድነት የአየር ኃይሉን ግዳጅ በስነሥርዓት እንዲወጣ በተበተነው ወረቀት ውስጥ መጻፉ በእረግጥም አስደሰታች ነበር። መለዮ ለባሹ የተነሳለትን አብዮታዊ ዓላማ ሳይዘነጋ፣ እንደተለመደው ጢሙን ተላጭቶ፣ አጎፍሮ የነበረውን ፀጉሩን አሳጥሮ ተስተካክሎ፣ እና ንፁህ የደንብ ልብሱን ለብሶ ግዳጁን ለመወጣት ዝግጁነቱነን በተግባር አረጋገጠ።
ወደ ሌላ አርዕስት ከመሸጋገሬ በፊት ከእገታ ከወጣን በሗላ ስለተወዳጀሁት ጀግና ስለ ግርማ ዘለቀ ጥቂት ልበል።
ከእገታ ከወጣን በሗላ ግርማ ዘለቀ ልክ የታገትን እለት ማታ መኖሬያ ቤቴ ድረስ መጥቶ ቤተሰቤን ለሠፈሩ ጥበቃ እንደተደረገ አረጋግጦላቸው እንደነበር ስለተነገረኝ አድመኞቹ በኔ ላይ ምንም ቅሬታ እንዳልነበራቸው ተሰማኝና ወዳጅነታችን ቀጠለ።
የደርግ አመራር ብቃት ማነስና የሚከተለው የሶሽሊሰት ፍልስፍና ግርማን አላስደሰተውም፡፡ ፍልስፍናው፣ ኢትዮጵያ ለምትገኝበት የፊዉዳል ሥርዓት ፈፅሞ አይሠራም እያለ አጥብቆ ይከራር ስለነበር ከትግል ጓደኞቹም ጋር ሳይቀር ከሶሽያሊስት ርዕዮት አቀንቃኞች ጋር ልዩነት ተፈጠረ።
ደርግ ግርማን የማረሚያ ቤት ሀላፊ አድርጎ በመሾም ከፖለቲካ አርቆት ነበር። አጅሬ ግን ስድቡን አልተቀበለውም፤ ወደ ሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ሄዶ ከፀረ-ደርግ ሐይሎች ጋር ለመቀላቀል ሲጓዝ ጎጃም ውስጥ ዳንግላ ሲደርስ ላስቆሙት ወታደሮች እጁን ላለመስጠት በመታኮስ ገሎ በተኩሱ ልውውጥ እሱም ሞተ። በኔ እምነት፣ አትዮጵያም ጀግና ልጇን አጣች!!!
ፋሺስትን-አርዕድ ሸጋው አርበኛ የብቸናው ተወላጅ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ አራዳ ጨርቅ ተራ አራተኛ ፖሊስ ጣቢያ አጠገብ ሲሰቀል፣ አንቺ ኢትዮጵያ ወንድ አይብቀልብሽ ብሎ መራገሙ ይታወቃል። የጎጃሙን ተወላጅ ጀግናውን ግርማ ዘለቀን ያ እርግማን ደርሶበት ይሆን? ጀግኖችን ከማክበሬ የተነሳ ደጃች በላይ ዘለቀን በተለይ በይፋ በጣም ስለማደንቅ፣ ባለቤቴ የፖለቲካ ሰለባ ይሆናል እያለች ትጨነቅ ነበር። ግርማ ዘለቀ ሲሞት እጅግ በጣም አዘንኩ።
ወያኔን በለስ ቀንቶት፣ በአሜሪካ ሁለንታዊ አጋዥነት፣ በጋዳፊ የጦር መሣሪያዎችን በገፍ አስታጣቂነት፣ በዓረብ ሀገሮች አመርቂ ገንዘብ ለጋሽነት፣ በመንግሥቱ ኃይለማርያም ኮብላይነት ታግዞ እናት ኢትዮጵያን ላለፉት 23 ዓመታት ለመቆጣጠርና በታሪኳ ተመጣጣኝ የማይገኝላቸው ዘግናኝ ሰቆቃዎችን በሕዝቦቿ ላይ በጭካኔ ሊፈፅም ቻለ። ይህን በተመለከተ፣ ሰኔ አንድ ቀን 2006 ዓ.ም ደብረ ማርቆስ ከተማ የተደረገው ጀግንነትና ፖለቲካዊ ብስለትን የተላበሰ አፍቃሬ-ለውጥ ደማቅ ሰልፍ፣ ለጎጃም ሕዝብ ያለኝን አክብሮት አሻቅቦታል። ጀግናው ግርማ ዘለቀና፣ በወያኔ ፓርላማ በተቃዋሚነት ተሰይሞ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ሲሟገት የነበረው አርበኛው ታላቅ ወንደሙ አድማሴ ዘለቀ (እስር ቤት ተዋወቅነናል)፣ ሁለቱም ካሉበት ሆነው ደማቁን ሰልፈ ሲመለከቱ ከፍተኛ ኩራት እንደሚሰማቸው አይጠረጠርም
ማጠቃለያ
የወያኔ መከላከያና የፀጥታ ሠራዊት፣ የማስተር ቴክኒሽያን ግርማ ዘለቀን ምሳሌ ተከትሎ፣ በሙስና የተጨማለቁትንና በቁልፍ የአዛዥነት ቦታ ላይ የተመደቡትን የአንድ አናሳ ብሄረሰብ ከበርቴ ጄኔራሎችንና ኮሎኔሎችን በቁጥጥሩ ስር በማዋል፣ ወገናዊነቱን ግፍ ለደረሰበት የኢትዮጵያ ሕዝብ በማሳየት፣ ታሪክ የመሥራት እድል ሳያመልጠው በፍጥነት ቆራጥ እርምጃ መውሰድ የሚያስመሰግነው ይሆናል።
የክቡር አክሊሉ ኃብተወልድን ምሳሌ በመከተል፣ ክርስቲያኑ የኢሀዴግ ጠቅላይ ሚ/ር፣ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በሕዝባዊ አመፅ የሚጥለቀለቁበትን አይቀሬውን ቀን በማሳብ፣ ሕይዎት ሳይጠፋ፣ ደም ሳይፈስ፣ እና ንብረት ሳይባክን ከተቃዋሚዎች ጋር ቢደራደሩ፣ የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን አለምንም ቅድመ ሁኔታ ቢፈቱና የፖለቲካውን ምህዳር ቢያሰፉ፣ ከአስከፊ ውርደት ይድናሉ። ኢትዮጵያ ሀገራችንን ግን መለኮታዊ ጥበቃ ከውድቀት ያድናታል።
ወያኔ ላለፉት 23 ዓመታት ሲግተን የነበረው የግፍ ጽዋ፣ በቆራጡ አርበኛ በአንዳረጋቸው ፅጌ ታፍኖ መታሰር ሞልቶ መፍሰስ ጀምሯልና የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእንግዲህ ትግዕግሥቱ ተሟጦ አልቋል።ሳይዘገይ መታረም ምርጫው የእሀዴግ ብቻ ነው!!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
rababya@gmail.com