የስነ ስሁፍ ሰው አይደለሁም:: ይህንን ስሁፍ እንድጽፍ ያስገደደኝ ግን በኢትዮጳያ ቴሌቪዝን አየር ሃይልን በተመለከተ የተላለፈው ዜና ነው:: በዚሁ ዜና ላይ ያሁኑ አየር ሃይል ኢንዶክትሪኔሽን ሃላፊ ኮሎኔል አስፋው ማመጫ በ 1983 ሰለነበረው አየር ሃይል ሲያስረዱ ” በ1983 የተረከብነው የደከመ የፈራረሰና የወደቀ አየር ሃይል ነበር”
[i] በማለት እጅግ አስቂኝና ከውነት የራቀ መግለጫ ሰተዋል:: አዲሱ ትውልድ ስለቀደመው አየር ሃይል እውነት ጥቂትም ቢሆን ያውቅ ዘንድና አየር ሃይሉ ምን ይመስል እንደነበር እንዴትስ እጅ እንደሰጠ በጥቂቱ ልጽፍ ወደድኩ::
በመጀመርያ ወያኔ አየር ሃይሉን ሲረከብ ምን እንደሚመስል እንመልከት MiG-23 Flogger Tactical Fighter Jet
1. የውጊያ የስለላና የትራንስፖርት አውሮፕላኖች
ወያኔ ግንቦት 1983 አየር ሃይሉን ሲቆጣጠር አየር ሃይሉ በበርካታ ዘመናዊ አውሮፕላኖች የታጠቀ ነበር:: በውጊያ አውሮፕላኖች ዘርፍ ሚግ 23 : ሚግ 23 ፍሎገር እና ሚግ 21 የተባሉ ሱፐር ሶኒክ የአየር ለአየርና ያየር ለምድር ተዋጊ ጀቶችን ( ሚግ 23 ማክ 3 ነው:: ይህም ማለት ከድምጽ ፍጥነት ሶስት ግዜ ይፈጥን ነበር) የታጠቀ ነበር:: ሚ 24 (ነጮቹ flying tank ይሉታል) እና ሚ 35 የተባሉ ከጠላት ጋር እየተናነቁ መዋጋት የሚችሉ ሄሌኮፕትሮችም የአየር ሃይሉ ንብረቶች ነበሩ:: ሚ 35 ከጠላት የሚተኮስበትን ጸረ አየር ሊከላከልና አቅጣጫ ሊያስቀይር የሚችል እስከ 12 ጸረ ታንክ ሚሳኤሎችን መታጠቅ ይችላል:: በግዜው ( 1970 ዎቹ መጨረሻ) ሚግ 23 ፍሎገርና ሚ 25 ሄሌኮፕተሮችን የታጠቀች የመጀመርያዋ ሰብ ሰሃራ ሀገር ኢትዮጵያ ነበረች::
በትራንስፖርቱም በኩል ወያኔ አየር ሃይሉን ሲረከብ አየር ሃይሉ አንቶኖቭ(Antonov 12,22,260) : ሲ- 130 እና ቲ ዩ( TU) የተባሉ ዘመናዊ የትራንስፖርት አውሮፕላኖች ነበሩት:: አንቶኖቭ ከትራንስፖርት ጠቀሜታው ሌላ በርካታ ቦንቦችን ጭኖ ውጊያ ላይ መሳተፍም የሚችል ሶቪየት ሰራሽ አውሮፕላን ሲሆን ሲ 140 ም ተመሳሳይ አገልግሎትን የሚሰጥ አሜሪካ ሰራሽ አውሮፕላን ነው:: ቲ ዩ የተሰኘው አውሮፕላን ደግሞ የአገሪቱ ርእሰ ብሔር ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማርያም ልዩ የትራንስፖርት ጀት ነው:: ወያኔ የደብረዘይቱን የኢትዮጵያ አየር ሃይል ዋና ቤዝ ሲቆጣጠር በነዚህ ሁሉ የውጊያና የትራንስፖርት አውሮፕላኖች የተደራጀን አየር ሃይል ነበር የተረከበው::
በቁጥር መልኩ ሲተነተን አየር ሃይሉ በጠቅላላው 112 ሚግ 21 ተዋጊ ጀቶች: 37 ሚግ 23 የአየር ለአየርና የአየር ለምድር ተዋጊ ጀቶች: 15 ሚግ 17 : 20 አንቶኖቭ 12: 18 አንቶኖቭ 26 : 5 አንቶኖቭ 22: አስራ ሱኮይ ሰባት ጀቶች: አርባ ሶስት ሚ 8 እና ሰላሳ ሚ 24 ተዋጊ ሄለኮፕተሮች ነበሩት:: ከነዚህ ውስጥ ወያኔ ደብረዘይትን ሲቆጣጠር በርካቶቹን ተረክቧል::
2. አየር መቃወሚያና የስለላ ራዳሮች
ከአየር ሃይሉ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የኢትዮጵያን ያየር ክልል ለመጠበቅ የተቋቋመው ሌላው ክፍል ደግሞ አየር መከላከያ ነበር:: ወያኔ በ 1983 የደብረዘይትን ኤር ቤዝ ሲቆጣጠር አየር መከላከያ እጅግ ዘመናዊ በሆነ ራዳርና ሚሳኤሎች የተደራጀ ነበር:: በተለይ ቮልጋ ፐትቼራና ስትሬላ ( Volga, Petchera, stinger, SAM) የተባሉ በርካታ የአየር መቃወሚያ ሚሳ ኤሎችን የታጠቀ ነበር::ግንቦት 1983 ወያኔ አየር ሃይሉን ሲይዝ ሙሉና የተደራጀ አየየር መከላከያን ነበር የተረከበው:: የሚደንቀው እሰከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ የአየር መቃወሚያ ባለሙያዎች አገሪቷ ላይ ያለ የውጭ ሀገር ጀቶች እንዳይገቡ የሙያ ግዴታቸውን ሲወጡ ነበር:: ወያኔ ሲገባም ሙያቸው ያገሪቱንያየር ድንበርን ማስጠበቅ እንደሆነና ወያኔም ስለአየር መቃወሚያ ሚሳኤሎቹ ግንዛቤ እስኪያገኝ ድረስ ክፍሉን እንዳይበትናቸውና በመሃል የጠላት ሀገር ጀቶች ገበተው ኢትዮጵያን እንዳይጎዷት ለወያኔው የጦር አዛዥ ግንቢት 1983 ወያኔ አየር መከላከያን እንደያዘ ወዲያ እዛው ግቢ ውስጥ ጥያቄ አቅርበውለት ነበር::
3. የጥገገናና የድጋፍ ሰጭ ክፍሎች
ለነዚህ አውሮፕላኖችና ሚሳኤሎች ጥገናና አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ደጋፍ ሰጭ ክፍሎችም ነበሩት:: ተዋጊ ጀቶች : ሄሌኮፕተሮችና ትራንስፖርት አውሮፕላኖች የሚጠገኑበት በርካታ ሃንጋሮች ወያኔ ሲገባ አብሮ የተረከባቸው የአየር ሃይሉ አካላት ናቸው:: እነዚህ የጥገና ሃንጋሮች ወያኔ ገብቶ እስኪረከባቸው ድረስ ሙሉ ነበሩ:: አንዲትም ብሎን እንኳን አልተነካችም ነበር:: ከዚህም ባሻገር የአውሮፕላን ስፔር ፓርቶችን ሞዲፊክ የሚሰሩ አሰደናቂ ማሽን ሾፖችም እና ውድ ወርክ ሾፖችም የአየር ሀይሉ ስውር አካላት ነበሩ:: እጅግ በሚደንቅ ሁኔታ በተለይ ማሽን ሾፕ በርካታ የአውሮፕላን መለዋወጫዎችን በሞዲፊክ ይሰራ ነበር:: ወያኔ በ1983 ሲገባ የተረከበው እነዚህን ሙሉ ሀንጋሮች ጭምር ነበር::
4. የሰው ሃይል ማሰልጠኛ ኮሌጆች
እነዚህን ስራ የሚሰሩ ባለሙያዎንና ተዋጊዎችን የሚሰለጥኑበት የሁለት ድንቅ ኮሌጆችም ባላቤት ነበር – ወያኔ የተረከበው የኢትዮጵያ አየር ሃይል:: የመጀመርያው የበራሪዎች ማሰልጠኛ ኮሌጅ ሲሆን ሁለተኛው በተለምዶ ግራውን ስኩል በመባል የሚታወቀው የግራውን ቴክኒሻን ማሰልጠኛ ኮሌጅ( ground technician college) ነው:: እነዚህ ሁለት ኮሌጆች በጊዜአቸው በአፍሪካ አሉ ከሚባሉ ማሰልጠኛዎች የሚጠቀሱ ነበሩ:: ራሺያና ሌሎች ሀገራት ሰልጥነው የሚመጡ ተማሪዎች እንኳን ስራ ከመጀመራቸው በፊት እነዚህ ኮሌጆች ውስጥ ገበተው መፈተን ነበረባቸው::አየር ሃይሉ በነዚህ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የታነጹ የባለሙያዎችና የተዋጊዎች መናሃርያ ነበር::ወያኔ ሲገባ የተረከበው እነዚህን ኮሌጆች ጭምር ነበር::
5. ማህበራዊ ተቋማትን በተመለከተ
የሰራዊቱን አካላት ለመደገፍ ይረዳ ዘንድ በርካታ ተቋማት በአየር ሃይሉ ውስጥ ነበሩ:: የሰራዊቱ አባላት ከራሳቸው ደሞዝ እየተቆረጠ ስራው የተጀመረ እጅግ ዘመናዊ ሆስፒታል ነበር:: የሰራዊቱን አባላትም ከስውር የገበያ ጥቃት ( የተመረዘ ምግብ ) ለመሰወርና ለመከላከል ኮሚሴሪ በመባል የሚታወቅ የህብረት ስራ ንግድ ማዕከል ነበር:: ይህ ድርጅት የተለያዩ የፍጆታ እቃዎችን ለአየር ሃይሉ አባላት በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ሃላፊነት ተሰጥቶት የሚንቀሳቀስ ራስ አገዝ ( economic cooperative) ሲሆን ሁለት የመዝናኛ ክበቦችም ( ኦፊሰርስ ክለብ እና ኤ ን ሲ ኦ ክበብ) ነበሩት:: በግዜው በከተማው ብቸኛ ፊልም ቤትም የነበረው አየር ሃይሉ ብቻ ነበር:: ያየር ሃይሉ እና አየር ወልድ አባላትም ሲያርፉ ሬሳቸው በከብር የሚያርፍበት እጅግ ያማረና በወታደራዊ ዘቦች የሚጠበቅ የመቃብር ቦታ በደብረ ዘይት ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስትያን ተከልሎ ነበር:: ይም መቃብር የጦሩ የክብር መቃብር ስለነበር ከአየር ሃይልና ከአየር ወለድ ውጭ ማንም አይቀበርበትም ነበር:: ወታረዶችም ተመድበውለት ይጠበቅ ነበር:: እጅግ በጣምም ያማረና ማራኪ ቦታ ነበር::
6. የሰው ሃይል
የሰው ሃይልም ደረጃ አየር ሃይሉ ከ 6 እሰከ ሰባት ሺህ የሚደርሱ ባለሙያዎች ነበሩት:: እነዚህ ባለሙያዎች በአሜሪካ : ሩስያ: ሰሜን ኮርያ : ቼኮስላቫኪያ: እስራ ኤል ወዘተ የሰለጠኑ ብቃት ያልቸው ብሔራዊና አለማቀፋዊ ምሁራን ነበሩ:: ይህም ሰራዊት ወታደራዊ መኮንንኖችንና ሲቪል ባለሙያዎችን ያካተተ ነበር:: በርካቶቹ አባላት የአቪዬሽን መሃንዲሶች: የጥገና ባለሙያዎች : የአየር ላይ intellegence አማካሪዎች ነበሩ::
ወያኔ ሀሜን ሲቆጣጠር ( ሀሜ ሀረር ሜዳ ማለት ሲሆን ደብረዘይት የሚገኘው ያየር ሃይሉ ዋና ጣብያ ሀሜ ይባል ነበር:: ) የተረከበው እነዚህን ሁሉ ነው:: በመቶዎች የሚቆጠሩ የውጊያና የትራስፖርት አውሮፕላኖች: በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳ ኤሎች: ሁለት ትልለቅ ስቴዲየሞች: የአየር ሃይል ቁጠባ ባንክ: ያያር ሃይል ሆስፒታል: ሁለት ዝነኛ ያይር ሃይል ማሰልጠኛ ኮሌጆች : ራዳሮችና ከ ስድስት እሰከ ሳባት ሺህ የሚቆጠሩ ያያር ሃይል ባላሙያዎችን ነበር::
ያሁኑ አየር ሃይል ኢንፎክትሪኔሽን ሃላፊ ኮሎኔል አስፋው ማመጫ ” የተረከብነው አየር ሃይል የተዳከመ የፈራረሰ እና የወደቀ አየር ሃይል ነበር” የሚለው መግለጫ በፍጹም ህሰትና ከውነት የራቀ ነው:: ኮሌኔሉ ወይ አየር ሃይሉን አያውቀውም ነበር ወይ ደግሞ አድር ባይነት ያጠቃው ይመስላል:: እውነትን እውነት ማለት ግን ጅግንነት ነበር:: የሚደንቀው ግን አያር ሃይሉን ያወደመውና የበታተነው ራሱ ወያኔ መሆኑ ነው:: ይሄንንም ያይን እማኝነቴን ከዚህ በታች እገልጸዋለሁ:: በመጀመርያ አየር ሃይል እንዴት ተያዘ?
ኣየር ሃይል እንዴት በሰላም እጁን ሰጠ?
እግረኛው የጦሩ ክፍል እየሸሸ በመጣባቸው ቦታዎች የወያኔን ጉዞ ለመግታት ከፍተኛ ውጊያ ሲያደርግ የነበረው አየር ሃይሉ ነበር:: ይሄን ወያኔ አሳምሮ ያውቀዋል:: በተለይ ሄሌኮፕተሮችና ተዋጊ ጀቶች እጅግ በርካታ ግዜ በመመላለስ ከእግረኛ በከፋ ሁኔታ ተዋግተዋል:: በተለይም ወያኔ ነጻ አወጣሁ በሚላቸውና የኢትዮጵያ ሰራዊት በሌለባቸው ቦታዎች ላይ ብቸኛው ተዋጊ አየር ሃይሉ ነበር::
እንደ አየር ሃይልም እንደ እግረኛም ታች ድረስ በመውረድ ፓይለቶቻችን ሰፊ መስዋትነት ከፍለዋል:: በስተመጨረሻም ወያኔ የደብረ ዘይትን አየር ሃይል ሊይዝ ውጊያ ሲያደርግ ከፍተኛ እልቂት እንደሚደርስ ተፈርቶ ነበር:: ጨፌ ዶንሳ ( ከደብረ ዘይት ወጣ ብሎ የሚገኝ ቦታ ነው) ላይ እጅግ አስከፊና ደም እንደውሃ ያፋሰሰ ውጊያ ከተካሄደ በኋላ የወያኔ ጦር ወደ ኢትዮጵያ አየር ሃይል ዋና ቤዝ ወደ ደብረ ዘይት ሲገባ አየር ሃይሉ በሁለት ሃሳብ ተከፍሎ ነበር::
የመጀመርያው ” የአየር ሃይልን ግቢ እንዲሁ አናሲዝም እስከመጨረሻው እንዋጋለን:” የሚል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ “ደብረ ዘይት ላይና አየር ሃይል ግቢ ውስጥ ባለን መሳርያ ውጊያ ከጀመርን የሚወደመው ሀገሪቷ ለበርካታ ዘመናት የገነባችው አየር ሀይልና በውስጡ ያሉት የአቪዬሽን ባለሙያዎች : መሳርያዎች ይበልጡኑ ደግሞ የደብረ ዘይት ሕዝብ ስለሆነ አየር ሃይሉ ግቢ ውስጥ ባንዋጋ ይሻላል” የሚል ነበር:: በስተመጨረሻም ከተማው ውስጥ እንዳይገቡ ከፍተኛ ውጊያ እንዲደረግና ከተማው ውስጥ ከገቡ ግን በተለይም የአየር ሃይል ግቢ ውስጥ ውጊያ መግጠሙ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ስምምነት ላይ ተደረሰ:: በተለይ አየር ሀይሉ ግቢ ውስጥም የሚከፈተው የጅ በእጅ ውጊያ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ስምምነት ላይ ተደረሰ::
ይህም ምክንያቱ አንደኛ አየር ሀይሉ ውስጥ ተከዝነውና ተከማችተው ያሉት መሳርያዎች ይልቁንም ናፓልና ክላስተር ቦምቦች ቢመቱ ከተማዋ በሙሉ ልትጠፋ ትችላለች የሚል ሲሆን: ሁለተኛው ደግሞ አየር ሀይሉ ግቢ ውስጥ ያሉት በርካታ አገሪቱ በዲፕሎማሲና በከፍተኛ ወጭ ለሃምሳና ስልሳ አመት የገነባቸው ያቪዬሽን ቴክኖሎጂ ይወድማሉ የሚል እሳቤ ስለነበር ነበር:: ይሄንንም ተቋም ሀገሪቱ መልሶ ለመገንባት ሌላ ስልሳ አመት ይፈጅባታል:: በዚህ መሃልም የጠላት አየር ሀይል እንደፈለገው በኢትዮጵያ አየር ክልል ውስጥ ሊፈነጭ ይችላል የሚል ነበር:: ከተማዋን ከውድመት ለመታደግና አየር ሃይሉን ከጥፋት ለመታደግ አየር ሃይል ግቢ ውስጥ ወጊያ እንዳይካሄድ ስምምነት ላይ ተደረሰ:: ደብረ ዘይት ዙርያ በተለይ ጨፌ ዶንሳ : የረር ላይ ከፍተኛ ትንንቅ ተካሄደ:: በውስጥ አዋቂና ባንዳ ይመራ የነበው ወያኔ ግን ሳይታሰብ ሾልኮ ደብረዘይትን ተቆጣጣረ:: አየር ሀይልም እንደቀልድ በሰላም ተያዘ::
አስደናቂውና ወደር የለሹ በቀል _ ወያኔና አየር ሃይሉ
ወያኔ አገረቱን ከተቆጣጠረ በኋላ አየር አየር ሃይሉን ላገሪቷ ጥቅም ይጠቀምበታል የሚል እሳቤ ነበር:: ቢያንስ ፓይለቶቹንና ወታደራዊ መኮንንኖቹን ባይቀበል እንኳን ሲቪል እና የሙያ ሰዎች የሆኑትን አረጊቷ በከፍተኛ ወጭ ያሰለጠነቻቸውን የበረራ መሃንዲሶችና ሌሎች ባለሙያዎችን ይበትናል ተብሎ አልታሰበም ነበር:: ምክንያቱም እነዚህ አካላት አውሮፕላኖችንን ከመጠገን : ስፔር ፓርቶችን ከማምረትና ስለ አቪዬሽን ከማስተማር ውጭ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ውስጥ ምንም ተሳትፎ ያልነበራቸው ንጹህ ሲቪል ባለሙያዎች ነበሩ::
ወያኔ አየር ሀይሉን ያለምንም ውጊያ ከያዘ በኋላ የመጀመርያ ስራው ማፍረስ እና ማፈራረስ ሆነ:: አየር ሃይሉ እንደሀገር ንብረት ሳይሆን በሚገርም ሁኔታ እንደጠላት ጠላት ንብረት ታይቶ ተበዘበዘ:: እጅግ በከባድ ወጭ ተገዝተው የተተከሉ ማሽኖች በሙሉ ከአየር ሃይሉ እየተፈቱ ተጫኑ :: በትልልቅ መኪኖችም እየተጫኑ በሌሊት ይጓዙ ጀመር:: በተለያየ ሀገር ተምረዉ ( ከምስራቁም ከምራቡም ዓለም) ከፍተኛ ያቪዬሽን እውቀት የነበራቸው የበረራ እና የአውሮፕላን ጥገና መምህራን እየታደኑ ጦላይና ብላቴ ታሰሩ:: ቀላል ቁጥር የሌላቸው ባለሙያዎች በጦላይና ብላቴ በረሃ በወባና ኮሌራ አለቁ::ይህም የተደረገው ሆን ተብሎ ነበር:: ጥቂት የማይባሉትንም ፓይለቶች ወያኔ እያደነ አረመኔያዊ በሆነ ሁኔታ ገደላቸው:: በተለይም ባይኔ ያየሁት የኮለኔል ጥላሁን ግድያ የማይረሳ ነበር:: በአየር ሃይሉ ውስጥ የሚገኘውንም የአየር ሃይል ቁጠባ ባንክ በዝርፊያ የተካነው ወያኔና ጀሌዎቹ ዘረፉት:: ያሁሉ ያየር ሃይል አባልና ቤተሰቡ ያለደሞዝና ጡረታ ንብረቱ ተዘርፎ ተበተነ:: ተራው የወያኔ ወታደርም የበርካታ አውሮፕላኖችን መስታውታቸውን በመሰበር እና ውስጣቸው ያሉትን የተለያዩ ሲስተሞችን በስለትና በብረት በጣጠሱት::በድንጋይ አውሮፕላን ማረክን እያሉም ዘፈኑ:: የአየር ሀይሉ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የሚገኙ ልዩ ልዩ የስለላ ሚስጥሮችን : መዛግብትንና የጦሩ መረጃዎችን እንደቀልድ በተኗቸው:: ያየር ሀይሉን ማሰልጠኛ ትምርት ቤቶችና ቤተ መጻህፍት ዘበዙት:: ማንም ተራ ወታደር ቤተ መጻሕፍት ገብቶ መጽሃፍ መዝረጥ እያደረገ ማንደድና እሳት መሞቅ ይችል ነበር:: መጻሕፍቶቹ የሚያወጡት ዋጋ ; የያዙት ቁም ነገር ለነሱ ትርጉም አልነበረውም:: ምናልባትም ጀቶቹ በራሳቸው ድንገት የሚነሱ እየመሰላቸው ይመስላል : በከፍተኛ ወጭ የተገነባውን የአውሮፕላን ማኮብኮቢያ በታንክ ሄዱበት :: ኮሚሴሪው : ክበባቱ: ሆስፒታሉ በሙሉ የጨፍጫፊው አየር እየተባለ ብትንትኑን አወጡት:: አየር ሃልን አፈረስነው እያሉ ደስታቸው ወሰን አጣ:: የሚደንቀው ግን አየር ሃይሉ ግቢ ውስጥ ከወያኔ ጋር አብረው ገብተው በርካታ እቃዎችን እየመረጡ ሲያስጭኑ የነበሩት ሱዳኖችና ወደ ሱዳን መሆኑ ነው::
ነገር ግን የቀድሞው ያየር ሃይል ሰራዊቱ አባላት ወያኔ የቀድሞውን ሰራዊት ባያምን እንኳን የራሱን የሚያምናቸውን ሰው እንኳን አሰልጥኖ የኢትዮጵያን ያየር ክልል ያስጠብቅ ዘንድ በርካታ ተማጽኖዎች ያደረጉለት ነበር:: ያይር ሃይሉን እንዳልሆነ ሆኖ መመዝበር የሰሙት እስር ላይ ያሉ መኮንንኖችም በየግምገማው ወቅታ( ግምገማ እያሉ በየግዜው ይሰበስቡን ነበር) ያሰሙ የነበረው ለቅሶ ለነሱ ሳይሆን ላየር ሃይሉ ነበር:: እነሱን ባያምን እንኳን የኔ የሚላቸውን ሰዎች አሰልጥኖ አገሪቱ አየር ሃይል አልባ እንዳትሆን እንዲያደርጋት ከፍተኛ ተማጽኖ ነበር::
ወያኔ ወደ ልቡ ሲመለስ “የራሴን አየር ሃይል ማሰልጠን አለብኝ ” በማለት አየር ሃይሉን ከማፍረስ እንቅስቃሴው ተገቶ ስለ ስልጠና ማሰብ ጀመረ:: የተወሰኑ የቀድሞ አየር ሃይል አባላትን በመመለስም ስራዎች እንዲጀመሩ ሆነ:: ነገር ግን ወያኔ ለፓይለትነትና ለተዋጊነት እንዲሰለጥኑለት የሚፈልጋቸው ወታደሮች ትንሽ እንኳን ዘመናዊ ትምህርት ያልቀመሱ ለአስራ አምስትና ከዛ በላይ አመት ግዜያቸውን በበረሃ ላይ ያሳለፉ ትምርት ለመቀበል እድሜያቸው የገፋ ስለሆነ ሌላ ችግር ነበር:: ከሁሉም በላይ አሰልጣኞቻቸውንና አስተማሪዎቻቸውን የማይሰሙ እብረተኞች ሰለነበሩ በርካታ አውሮፕላኖች እየተከሰከሱ አለቁ:: በዘጠናዎቹ ብቻ ከ 13 የማያንሱ አውሮፕላኖች ወድቀዋል:: ይሄ ባየር ሃይሉ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ነበር :: በተለይ ሞጆ ገበያ ላይ የተከሰከሰው አወሮፕላን አይረሳም::
የሻቢያ ወረራ
ወያኔና ሻቢያ የጫጉላ የፍቅር ግዜያቸው ሲያልቅ ጦርነት ከፈቱ:: ወያኔም ሻቢያ ወረረችኝ አለ:: በሚያሳዝን ሁኔታ ተራ ፓይለት በተራ አውሮፕላን ትግራይን ያውም የህጻናት ትምርት ቤትን ባሰቃቂ ሁኔታ ደበደበ:: ከጣልያን በኋላ ያየር ክልሏ ተደፍሮ የማታውቀው ኢትዮጵያ ያየር ክልሏ ተደፍሮ በጀት ተደበደበች:: ወያኔ ግራ ገባው:: ሰባት አመት ሙሉ ያለ ደሞዝና ጡረታ በትኖ በረሃብ ሲቆላው ለከረመው ለኢትዮጵያ አየር ሃይል አባላት ጥሪ አቀረበ:: ለባንዲራውና ላገሩ ቃል የገባው ሰራዊት ግን ቂም ይዞ ጥሪውን እምቢ አላለም:: ሁሉንም ይቅር ብሎ በሚገርም ሁኔታ አየር ሀይሉን ድጋሚ አነሳው::
ሲጠቃለል ወያኔ የተረከበው አየር ሃይል የፈረሰ : የወደቀና የደከመ አየር ሃይል አልነበረም::የተረከበው ሙሉና ብቁ የሆነ አየር ሃይልን ነበር:: አየር ሃይሉን እንደጠላት ንብረት ያፈርሰውና ያረሪቱን አቪዬሽን ወደ ኋላ የጎተተው ራሱ ወያኔ ነው:: የአየር ሃይል አባላትን እንደ ሰው ሳይሆን እንደማርያም ጠላት ተጫውቶበታል:: የአየር ሃይል አባላት ገንዘብ ያጠራቅሙበት የነበረውን የቁጠባ ባንክ ዘርፎ የአያር ሃሉን አባላት ንብረትዘርፎ ያየር ሃይሉን አባላት ቤተሰብ በሙሉ ከድህነት በታች በማድረግ ከባድ ወንጀል የፈጸመው ወያኔ ነው:: ስንቱን ምሁር የበተነው ወያኔ ነው:: አየር ሃሉን እንደጠላት ንብረት ሙጥጥ አድርጎ የዘረፈውም ወያኔ እንጂ ሰራዊቱ አንዲት ብሎን እንኳን ሳትጎል ሙሉ አየር ሃይል ነበር ያስረከበው::
እንዲህ አይነት ከባድና አሰቃቂ ውንጀል ፈጽሞም ወረራ ሲመጣና ዳግም ጥሪን ሲያቀርብ የቀድሞው ጦር አባላት እምቢ አላሉም:: ምንም አይነት ቅሬታ ሳይሰማቸው ወደ አየር ሃሉ በመመለስ ወያኔ እንክትክቱን ያወጣውን አየር ሃይል ዳግም አቆሙት:: የሚገርመው ወያኔ ግን 7 up እያለ ያላግጥባቸው ነበር:: ( ከሰባት አመት በኋላ ወደ ስራ ስለተመለሱ):: በመሃልም ያለምክንያት በፈለገው ወቅት እየተነሳ ስንቱን ፓይለቶች ይጨርስ ነበር:: እነ ሻለቃ ዳንኤል ነፍስ ይናገር::
እናም እነ ኮሎኔል አስፋው
ባጭሩ ታሪክን መበረዝና መመራዝ ለማንም አይጠቅምም:: ወያኔ የተረከበው ሙሉና ብቁ የሆነ አየር ሃልን ነው:: አየር ሃይልን እንደጠላት ንብረት የዘረፈውና ያወደመው ራሱ ወያኔ ሲሆን እንደገናም ወያኔ ያወደመውን አየር ሃይል መልሶ ያቋቋመው ያው የጥንቱ አየር ሃይል አባላት መሆናቸው አይዘንጋ:: እውነት እውነት ናት::
በዚህ አጋጣሚ የምፃፍ ችሎታው ያላችሁ ይሰራዊቱ አባላት ለሚመጣው ትውልድ ያለውን እውነት ጽፋችሁ ብታስቀምጡት መልካም ስለሆነ ጥሪዬን አቀርባለሁ