የሰብዓዊ መብት ተመልካች የሆነው ድርጅት (ሂዩማን ራይትስ ዎች) “ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም” በሚል ርዕስ ያወጣል ተብሎ የተጠበቀውን ዘገባ ማምሻው ላይ ይፋ አድርጓል፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ “ያለ ነጻ ሚዲያ – ምርጫ ወይስ ቁማር?” በሚል ርዕስ ባተመው ዜና ላይ ዘገባው እንደሚወጣ በተናገረው መሠረት ባለ 76 ገጽ ሪፖርቱ በሚዲያ አፈና ዙሪያ ዝርዝርና ወቅታዊ መረጃዎችን አውጥቷል፡፡
ኢህአዴግ በሚያደርስባቸው ስልታዊ አፈና፣ ማስፈራሪያ፣ ህይወት የማጥፋት ዛቻ፣ … ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በትንሹ 22 የሚሆኑ ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንደሚገኙ፤ ከ30 በላይ የሚሆኑ ደግሞ አገር ጥለው መኮብለላቸውን በዘገባው ተጠቁሟል፡፡ እንዲህ ያለው ገለልተኛ ሚዲያን የሚያፍን እና ከሜዳው የሚያስወጣ አሠራር ከወራት በኋላ ይካሄዳል ከሚባለው “ምርጫ” አኳያ የውድድሩን ሜዳ ከማጥበብ አልፎ እንዳይኖር እንደሚያደርገው የዘገባው ሃተታ ያስረዳል፡፡
ድርጅቱ ካወጣው ዘገባ ጋር በተሰራጨው የዜና መግለጫ ላይ የድርጅቱ የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ሌስሊ ለፍኮው ሲናገሩ “በመጪው ግንቦት በሚካሄደው ምርጫ የኢትዮጵያ ሚዲያ ወሳኝ ሚና መጫወት ይችል ነበር፤ ሆኖም ግን ብዙዎቹ ጋዜጠኞች ሊያወጡ የሚፈልጉት ጦማር ወደ እስርቤት እንደሚያስወረውራቸው ስለሚፈሩ” ሙያዊ ተግባራቸው ከመወጣት እንደሚቆጠቡ ተናግረዋል፡፡
ዘገባው ከ70 የሚበልጡ አገር ውስጥና በስደት ከሚገኙ ጋዜጠኞች ጋር ቀጥተኛ ቃለምልልስ በማድረግ የወጣ የአንድ ወገን ሰነድ ሳይሆን ለኢህአዴግ ባለሥልጣናትም ጥያቄዎችን በማቅረብ የሰጡትን ምላሽ ለማመጣጠኛ አቅርቧል፡፡ በመጨረሻም ይበጃሉ ያላቸውን የምክር ሃሳቦች ጠቁሟል፡፡ የመጀመሪያ ጥቆማ ለኢህአዴግ ሲሆን በመቀጠልም የኢህአዴግን ቋት የሚሞሉትን ለጋሽ አገራት በተለይ አሜሪካንና የአውሮጳ አገራትን ተጽዕኖ ማድረግ በሚገባቸው ቦታዎች ላይ ዝምታን ከመምረጥ ይልቅ ተጽዕኖ ማድረግ የሚችሉበት ቦታ የት እንደሆነ አውቀው ስለ ሰብዓዊ መብት መከበር ሲሉ ተግባራቸውን እንዲወጡ የምክር ሃሳቡን ለግሷል፡፡ አፈናውን፣ ዛቻውንና እንግልቱን አምልጠው በጎረቤት አገራት ኬኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ዩጋንዳ የስደት ኑሯቸውን በሚገፉት ጋዜጠኞች ላይ ተጠቃሾቹ አገራት የኢህአዴግ ጓሮ በመሆን የስደተኞቹን መከራ ከማብዛት ይልቅ ተገቢውን ጥበቃና ከለላ በማድረግ እንዲሁም የጥገኝነት ማመልከቻቸውን በአፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ተገቢውን የሰብዓዊ መብት እንክብካቤ ሊያደርጉ እንደሚገባቸው አሳስቧል፡፡
ሙሉ የእንግሊዝኛው ዘገባ
እዚህ ላይ ይገኛል፡፡
ከዘገባው ጋር በተያያዘ የወጣው አጭር ቪዲዮ
እዚህ ላይ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ ያወጣው የማጠቃለያ መግለጫ ክዚህ በታች ሰፍሮዋል፡፡
“ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም”
በኢትዮጵያ የመገናኛ-ብዙሃን ነጻነት ላይ የሚፈፀም የመብት ጥሰት
እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 2015 ዓ.ም.
ማጠቃለያ
የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) እ.ኤ.አ. በ2010 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ 99.6 በመቶ የፓርላማ መቀመጫን ካሸነፈ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን እና መረጃ የማግኘት መብትን በመገደብ በግል መገናኛ-ብዙሃን ላይ እያሳደረ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ አባብሶታል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ቢያንስ 60 ጋዜጠኞች ሃገር ለቀው የተሰደዱ ሲሆን ሌሎች 19 ጋዜጠኞች ደግሞ በእስር ላይ እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡ መንግስት በደርዘኖች የሚቆጠሩ ህትመቶችን ዘግቷል፤ እንዲሁም አብዛኛዎቹን የቴሌቪዥን እና የሬድዮ ስርጭቶች በቁጥጥሩ ስር በማድረግ ኢትዮጵየዊያን የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ጉዳዮችን በተመለከተ ነጻ መረጃ እና ትንታኔ የሚያገኙበትን እድል አጣቧል። በግንቦት 2007 በሚካሄደው ምርጫ መገናኛ-ብዙሃኑ ህዝቡን በወሳኝ ጉዳዮች ላይ በማስተማርም ሆነ መረጃ በመስጠት ረገድ ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይችሉ ነበር፤ እንዲሁም የመከራከሪያ መድረክ በመሆን ሊያገለግሉ ይችሉ ነበር፤ ይሁን እንጂ መንግስት በሃገሪቱ ላለው ብቸኛ የበላይነት የግሉን መገናኛ-ብዙሃን እንደ ስጋት አድርጎ በመውሰድ የግሉን መገናኛ-ብዙሃን፣ ነጻ ጋዜተኝነትን እና ተቺ ትንታኔን ለማጥፋት የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህም የከፋ ውጤት አስከትሏል።
የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ የሆነው የኮሚቴ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ (Committee to protect Journalists) መረጃ እና የሂዩማን ራይትስ ዎች ጥናት እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ከኢራን በመቀጠል በዓለም ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞችን ለስደት የምትዳርግ ሀገር ሆናለች። የመንግስት አካላት አፋኝ ህጎችን መሰረት አድርገው ጋዜጠኞች በየወቅቱ ያሉ ክስተቶችን እና ጉዳዮችን አስመልከተው በሚሰሩት ዘገባ እና ትንታኔ ምክንያት በተደጋጋሚ ክስ ይመሰርቱባቸዋል፤ ፍርድ ቤቶችም ክሱን ተከትለው የጥፋተኝነት ውሳኔ ያስተላልፋሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት እስክንድር ነጋን እና ርዕዮት ዓለሙን የመሰሉ ግለሰቦች በአዲስ አበባ እና በክልሎች የሚገኙ ተለይተው የሚታወቁም ሆነ የማይታወቁ ከደርዘን በላይ የሚሆኑ ጋዜጠኞች እየደረሰባቸው የሚገኘውን ፈተና የሚያሳዩ ምልክቶች ሆነዋል። ጋዜጠኞቹ በርካታ ስጋት ውስጥ የሚገኙ፣ ማስፈራሪያ የሚደርሳቸው፣ አልፎ አልፎም አካላዊ ጥቃት የሚፈጸምባቸው እና ፖለቲካዊ ይዘት ያለው የወንጀል ወይንም የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው ናቸው፡፡ የፍርድ ቤት ክርክራቸው ፍትሃዊ የፍርድ ሂደትን የሚጥሱ አሰራሮች የሚታዩበት ሲሆን ፍርድ ቤቶቹም በያዟቸው ጉዳዮች ላይ የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ገለልተኛ እንዳልሆኑ የሚያሳይ ነው።
በኢትዮጵያ የሚገኙት አብዛኛዎቹ የህትመት መገናኛ-ብዙሃን ከመግስት ጋር የቀረበ ትስስር አላቸው፤ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ከመንግሰት የተለየ አቋም እምብዛም አያንጸባርቁም።የግል የህትመት መገናኛ-ብዙሃን በርካታ ከቁጥጥር ጋር የተያያዙ ችግሮች ያጋጥማቸዋል እንዲሁም በደህንነት ሰራተኞች ተከታታይ ወከባ ይደርስባቸዋል፡፡ መንግስትን የሚተቹ የህትመት ውጤቶች በየጊዜው ይዘጋሉ፣ የበሰለ ትችት የሚያቀርቡ የህትመት ውጤቶችን የሚያትሙ እና የሚያከፋፍሉ አሳታሚዎች እና አከፋፋዮችም ተዘግተዋል፡፡ የመንግስት ፖሊሲዎች ላይ ትችት የሚሰነዝሩ ጋዜጠኞች እና የቤተሰብ አባሎቻቸው ጭምር የጥቃት፣ የመታሰር እና የገቢ ምንጫቸውን የማጣት ዘላቂ ስጋት ላይ ይወድቃሉ፡፡ መንግስት አብዛኛውን የመገናኛ-ብዙሃን ተቆጣጥሮ የሚገኝ ሲሆን የቀሩት ጥቂት የግል መገናኛ-ብዙሃንም በተለይ ለአሳሳቢ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በሚሰጡት ሽፋን ራሳቸው ላይ ቅድመ ምርመራ የሚያደርጉ ያደርጋሉ ይህም እንዘጋለን ከሚል ፍርሃት የመነጨ ነው፡፡
ይህ ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግስት ነጻ ጋዜጠኝነትን እና ትንታኔን ለመቆጣጠር እንዲሁም መረጃ የማግኛ መንገድን ለመገደብ የተጠቀማቸውን ዘዴዎች የሚዘግብ ነው፡፡ ሪፖርቱ ከ70 የሚበልጡ የአሁን እና የቀድሞ ጋዜጠኞችን እና የመገናኛ-ብዙሃን ባለሙያዎችን ቃለ-መጠይቅ በማድረግ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የሚገኝበትን አስከፊ ሁኔታ እና በዚህም ምክንያት ሃሳብን በመግለጽ ነጻነት እና መገናኛ-ብዙሃን ላይ የደረሰውን አሉታዊ ተጽዕኖ ይዘረዝራል፡፡
በስፋት በተዘገቡ ጉዳዮች ላይ ከዓለምዓቀፍ ማህበረሰብ የተሰነዘሩ ውግዘቶች ቢኖሩም የኢትዮጵያ መንግስት ለገለልተኛ የመገናኛ-ብዙሃን ድምጽ ምንም አይነት የመለሳለስ ምልክት አላሳየም፤ እ.ኤ.አ. በ2014 ዓ.ም የግል መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚደርሰው አሉታዊ ተጽዕኖ በእጅጉ ተባብሷል፡፡ አስር ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ክስ የተመሰረተባቸው ጋዜጠኞችን ዝርዝር ተቀላቅለዋል እንዲሁም አምስት መጽሄቶች እና አንድ ጋዜጣ በመንግስት የዛቻ እና የማስፈራሪያ ዘመቻ ከተካሄደባቸው በኋላ እንዲዘጉ ተደርጓል፡፡ ዘመቻው በመንግስት በሚተዳደረው የቴሌቪዥን ጣቢያ የህትመት ውጤቶቹ ሽብርን እንደሚደግፉ አስመስሎ ማቅረብ፣ የህትመት ውጤቶቹን የሚያትሙ ማተሚያ ቤቶችን ማዋከብ፣ በህትመት ውጤቶቹ የማከፋፈል ስራ ላይ የመንግስት ጣልቃ ገብነት፤ እንዲሁም ከደህንነት ባለስልጣናት በርካታ ዛቻዎችን መሰንዘርን ያካትታል፡፡ ይህም በመጨረሻ በደርዘን የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች እና በርካታ የህትመት ውጤቶች ባለቤቶች ሃገር ለቀው እንዲሰደዱ እና ባለቤቶቹ የወንጀል ክስ እንዲመሰረትባቸው በማድረግ ተከናወኗል። ፍርድ ቤቶች ሌላ ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃ ሳይቀርብ መንግስትን የሚተቹ ጽሁፎችን ብቻ መሰረት በማድረግ በሶስት የህትመት ባለቤቶች ላይ በሌሉበት እያንዳንዳቸው ከሶስት አመት የሚበልጥ እስር እንዲቀጡ ወስነውባቸዋል፡፡ የሌሎች የህትመት ባለቤቶች ክስም በሂደት ላይ ነው፡፡
መንግስት ከሚፈፅማቸው ትኩረትን የሚስቡ እስሮች በተጨማሪ መገናኛ-ብዙሃንን ለማዳከም እና ለመዝጋት ሌሎች በርካታ በግልጽ የማይታዩ የእጅ አዙር መንገዶችን ይጠቀማል፡፡ የደህንነት ሰራተኞች በአሳሳቢ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ የሚጽፉ ጋዜጠኞች ላይ ተከታታይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ያደርሱባቸዋል፡፡ እነዚህ ዛቻዎች ብዙውን ጊዜ ከጋዜጠኞቹም አልፎ ወደ ቤተሰባቸው እና ጓደኞቻቸው ድረስ ይዘልቃሉ፡፡ የሚደርስባቸውን ማስፈራሪያ ተቀብለው በሚሰሩት ዘገባ ላይ ቅድመ-ምርመራ የማያካሂዱት በአብዛኛው ክስም ሳይመሰረትባቸው በዘፈቀደ ይታሰራሉ እንዲሁም ተጨማሪ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ይደርሳቸዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ በሚገኙ አካባቢዎች በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ያልተገባ አያያዝ እና ድብደባ የተለመደ ሆኗል፤ በአብዛኛው ጊዜም የወነጀል ክስ ተከትሎ ይመጣል። ብዙዎቹ ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ የግል ጋዜጠኞች በርካታ ጊዜያት እስር ተፈጽሞባቸዋል፤ እንዲሁም ከደህንነት ባለስልጣናት፣ ከገዢው ፓርቲ ካድሬዎች፣ እና ከቀድሞው የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ሚኒስቴር አሁን ደግሞ የመንግስት ኮምዩኒኬይሽን ጉዳዮች ቢሮ ከተባለው መስሪያቤት ባለስልጣናት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዛቻዎችን ተቀብለዋል፡፡
ይህም በመጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በራሳቸው ላይ ቅድመ-ምርመራ በማድረግ የገዥውን ፓርቲ አጀንዳ ከማራገብ ወይንም ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ዘገባ እና እና ትንታኔ ማቅረብ ከመቀጠል አንዱን የመምረጥ ከባድ ፈተና ውስጥ እንዲወድቁ ያደርጋል።
በግለሰብ ጋዜጠኞች ላይ ከሚደርሰው ጥቃት በተጨማሪ የግል መገናኛ-ብዙሃን ባለቤቶች የህትመት ውጤቶቻቸውን የሚያሳትሙባቸውን ማተሚያ ቤቶች ለማዳከም ባለስልጣናቱ የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀማሉ፡፡ በመግስት ስር የሚተዳደረው እና በመደበኛነት ጋዜጦችን የማተም አቅም ያለው ብቸኛ ማተሚያ ቤት የግል ህትመት ውጤቶችን ስራ ያዘገያል ወይንም አይቀበልም፣ በአንድ አጋጣሚ መንግስት በጣም አሳሳቢ ነው ባለው ጉዳይ ላይ ዘገባ ያሳተመን ጋዜጣ 40,000 ኮፒ ህትመት አቃጥሏል፡፡ የደህንነት ሰዎች የግል ህትመት ውጤቶች አከፋፋዮች ላይም የሚያደርጉትን ክትትል እና የሚያደርሱትን ጥቃት ጨምረዋል፡፡ የጋዜጠኞች የመረጃ ምንጮች በተደጋጋሚ ለጥቃት እየተጋለጡ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ለመነጋገር ፍርሃት የሚያድርባቸው ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ ነው።
መንግስት የግል ጋዜጠኞች ማህበር ለማደራጀት የሚደረግን ሙከራ ያግዳል እንዲሁም የግል የህትመት ውጤቶች ያላቸውን ፖለቲካዊ ትስስር በተመለከተ የደህንነት ባለስልጣናት ሰፊ የኋላ ታሪክ ጥናት ያካሂዳሉ፡፡ የመንግስት ወይም የገዥው ፓርቲ ሙሉ ደጋፊ ያልሆኑ የግል ህትመቶች ለሚያቀርቡት የህትመት ፈቃድ አሊያም እድሳት ጥያቄ ባለስልጣናት ምላሽ ለመስጠት ይዘገያሉ፡፡
የድረ-ገጽ መገናኛ ብዙሃንም በተሻለ መልኩ የተያዙ አይደሉም፡፡ በውጭ ሃገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚመሩ በርካታ ጦማሮች እና ድረ-ገጾች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ተደርገዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 ዓ.ም ዞን ዘጠኝ በመባል የሚታወቁት በሃገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ የሚያቀርቡ የጦማሪያን ስብስብ 80 ቀናት ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ከቆዩ በኋላ በጸረ-ሽብር አዋጁ እና የወንጀል ህጉ መሰረት ተከሰዋል፡፡ በቀረበው ክስ መሰረት በክስ ዝርዝር ሰነዱ ከተጠቀሰባቸው ማስረጃ መካከል አንዱ ቴክኒካል ቴክኖሎጂ ኮሌክቲቭ በተባለው በኢንተርኔት ላይ የሚገኝ የግላዊ መረጃዎችን ሚስጥራዊነት ለመጠበቅ የሚረዱ ተግባራትን እና መሳሪያዎችን በሚያቀርበው ዓለም ዓቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የዲጂታል ደህንነት ጥበቃ ስልጠና ወስደዋል የሚል ነው፡ ፡ የዞን ዘጠኝ አባላት መታሰር እና መከሰስ በሃገሪቱ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ላይ የፍርሃት ድባብ ፈጥሮአል።
ይህም ጦማሪዎች እና የኢንተርኔት ላይ ተሟጋቾች በፌስቡክና በመሳሰሉ እና ሌሎች ማህበራዊ ድረ-ገጾች በሚለጥፏቸው ትችቶች ምክንያት ችግር ውስጥ ልንገባ እንችላለን የሚለውን ስጋታቸውን በእጅጉ ከፍ አድርጎታል፡፡
በሬድዮ እና ቴሌቪዥን ስርጭት ላይ ያለውም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የሃገሪቱ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በመንግስት ስር የሚገኙ ሲሆን ገለልተኛ የዜና ዘገባ እና ትንታኔ አይቀርብባቸውም፡፡ ከ80 በመቶ የሚበልጠው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖረው በገጠራማ አካባቢዎች በመሆኑ እና ሬድዮ እስከአሁን ዋናው የዜና እና መረጃ ማግኛ ምንጭ ከመሆኑ አንጻር ይህ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ዘገባ የሚያቀርቡ ጥቂት የግል ሬድዮ ጣቢያዎች ዝግጅቶቻቸውን አየር ላይ ከማስተላለፋቸው ከቀናት በፊት የመንግስት ባለስልጣናት እንደሚገመግሙት እና እንደሚያጸድቁት ለሂውማን ራይትስ ወች ተናግረዋል፡፡ ተቀባይነት ካገኘው ይዘት የሚያፈነግጡ አሰራጮች በመንግስት ባለስልጣናተ የሚፈጸም እስር እና ወከባ ጋር መጋፈጥ ሊኖርባቸው ይችላል።
በርካታ ጋዜጠኞች ከማያቋርጥ የማዋከብ እና የፍርሃት ሕይወት ለመገላገል ሲሉ ከመንግስት ጋር ትስስር ባለው መገናኛ-ብዙሃን ተቀጥረው መስራት ይመርጣሉ፡፡ አንዳንዶች የመንግስት ባለስልጣናትን እስከማያስቆጣ ድረስ ባለው መለያ መስመር ላይ ሆነው ትችቶችን የሚያቀርቡ ሲሆን ሌሎች ደግሞ የመንግስትን የልማት ውጤቶች በማስተዋወቅ እና በማጋነን የመንግስት ፕሮፖጋንዳ አራጋቢዎች ሆነው ይሰራሉ፡፡ በእነዚህ መገናኛ ብዙሃን የኢህአዴግ አባልነት እድገት ለማግኘት የሚጠየቅ መስፈርት ነው፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙት የውጭ መገናኛ ብዙሃን ውሱን ናቸው። የአሜሪካ ድምጽ ቮይስ ኦፍ አሜሪካ (ቪኦኤ) እና የጀርመን ድምጽ ዶቼቬሌ የቴሊቪዥን እና የሬድዮ ሽፋን በመስጠት በርካታ የዲያስፖራ ጣቢያዎችን ተቀላቅለዋል፡፡ ሆኖም የአየር ሞገዳቸውን በማገድ፣ በሰራተኞቻቸው እና የመረጃ ምንጮቻቸው ላይ ዛቻ እና ጥቃት በማድረስ እንዲሁም በቅርቡ ደግሞ የዲያስፖራ መሰረት ያላቸውን ስርጭቶች የሚመለከቱ እና የሚያዳምጡ ግለሶቦችን በማጥቃት እና በማሰር ጭምር መንግስት የሃገር ውስጥ ተከታታዮቻቸውን ለመገደብ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማሕበራት ላይ በደረሰው ጫና ምክንያት በርካታ የሲቪል ማሕበራት ስራ ለማቆም የተገደዱ ሲሆን ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ጥብቅ ገደብ ተጥሎባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ንቁ እና ነጻ የመገናኛ-ብዙሃን ዘርፍ በመንግስት አስተዳደር ላይ ተሳትፎን ለማበርከት እና የሰብዓዊ መብቶች በተሻለ ሁኔታ እንዲከበሩ ለማገዝ ያለውን አስፈላጊነት የበለጠ ያጎላዋል። አለመታደል ሆኖ በፖለቲካ ሁነቶች ላይ ገለልተኛ ሽፋን እና የዜና ትንታኔ ለመስጠት ያለውም ጥቂት ክፍተት እ.ኤ.አ. በ2014 ዓ.ም. የበለጠ ተጣቧል፡፡ ከግንቦት 2007 ምርጫ መቃረብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያዊያን የተለያዩ የፖለቲዊ አተያዮች እና ትንታኔዎችን የሚያገኙበት እድል እየተመናመነ ነው።
በኢትዮጵያ የሚገኙ መገናኛ-ብዙሃን ሁኔታን ለማሻሻል በአጭር እና በረጅም ጊዜ አሁንም ብዙ ሊደረግ ይችላል፡፡ እንደ መጀመሪያ እርምጃ መንግስት ክሶችን በአስቸኳይ በማንሳት የታሰሩ እና የተፈረደባቸው ጋዜጠኞች እና ጦማሪያንን ክስር ሊለቅ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ መሪዎች ንቁ እና ገለልተኛ የመገናኛ ብዙሃን መኖር ለሃገሪቱ እድገት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ እንዲሁም በመጪዎቹ ሳምንታት እና ወራት መንግስት የጸረ-ሽብር ህጉን ጨምሮ ሌሎች መገናኛ ብዙሃኑ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድሩ አፋኝ ህጎችን ማረም አለበት፡፡ የሚወጡ ህጎች እና የሚፈጸሙ ተግባራት የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት እና ዓለምዓቀፍ መለኪያዎች ጋር በሚጣጠም መልኩ መሆኑን ባለስልጣናት ማረጋገጥ አለባቸው፡፡
ምክረ ሃሳቦች
ለኢትዮጵያ መንግስት
- ሁሉንም ክሶች በአስቸኳይ ማንሳት እንዲሁም በወንጀል መቅጫ ህጉ እና በጸረ-ሽብር አዋጁ መሰረት ተከሰው በዘፈቀደ የታሰሩ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን በሙሉ መፍታት።
- የጸረ-ሽብር አዋጁ እና የመገናኛ-ብዙሃን እና የመረጃ ነጻነት አዋጁ መሰረዝ አሊያም በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት እንዲሁም በክልላዊ እና ዓለምዓቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ህጎች ላይ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት መብት ከተቀመጡ መስፈርቶች ጋር በሚጣጣም መልኩ ከፍተኛ መሻሻያ ማደረግ፡፡
- የስም ማጥፋትን የወንጀል ቅጣት እንዲያስከትል ተደርጎ በወንጀል መቅጫ ህጉ አንቀጽ 613 ላይ የተደነገገውን ማሻሻል።
- በህትመት እና ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ላይ መንግስት ያለውን የባለቤትነት ድርሻ መገደብ ፤ እንዲሁም የግል መገናኛ-ብዙሃን ባለቤትነትን የሚገድቡ ጉዳዮችን ለማስቀረት እና ገለልተኛ እና ንቁ መገናኛ-ብዙሃንን ለማበረታታት የሚያስችሉ የህግ እና የፖሊሲ ማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ።
- አዳዲስ የህትመት እና የሬድዮ ስርጭቶች ቁጥጥርና ፈቃድ አሰራር ቀልጣፋ ማድረግ እና ከፖለቲካዊ ይዘት ነጻ ማድረግ። ቁጥጥር አድራጊ ባለስልጣን አካላት ገለልተኛ መሆን አለባቸው፤ እንዲሁም አስተዳደራዊ እና ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው ከመንግስት የደህንነት አካላት አና ከመንግስት ኮምዩኒኬይሽን ጉዳች ቢሮ መለየት አለበት፡፡
- የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ገለልተኛነትን ለማረጋገጥ ማሻሻያዎች ማድረግ።
- የሃገር ውስጥ እና የውጭ ጋዜጠኞች በመላው ሃገሪቱ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብታቸውን የሚገድቡ አሰራሮችን ማስወገድ፣ ይህም ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው ይገኛሉ በሚባሉ አካባቢዎች በነጸነት መንቀሳቀስን እንዲጨምር፣ ፖሊስ እና የደህንነት ሰዎች መገናኛ-ብዙሃን በነጻነት ይንቀሳቀሱ ዘንድ ፈቃድ እንዲሰጡ መመሪያ መስጠት፤ በዛቻ፣ በማስፈራራት እና በማሰር የጋዜጠኞችን እንቅስቃሴ የገደበ ማንኛውም ፖሊስ በያዘው የማዕረግ እርከን ልዩነት ሳይደረግ መቅጣት።
- የፖለቲካ ፓርቲ ፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የጦማሪያን ድረ-ገጾችን ማፈን እና ቅድመ ምርመራ ማድረግን ማቆም እንዲሁም ለወደፊት እንደዚህ አይነት ድረ-ገፆችን ላለማፈን በይፋ ቃል መግባት።
- የሬድዮ እና የቴሌቪዥን አየር ሞገዶችን ማፈን ማቆም ፤ ለወደፊቱም የሬድዮ እና ቴሌቪዥን አየር ሞገዶችን ላለማፈን በይፋ ቃል መግባት።
- አስተያየት የመስጠት እና ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት መብቶችን ለማዳበር እና ለመጠበቅ የሚንቀሳቀሰው የተባበሩት መንግስታት ልዩ ራፖርተር ኢትዮጵያን እንዲጎበኝ እና የግል የህትመት እና የብሮድካስት መገናኛ-ብዙሃን ያሉበትን ሁኔታ እንዲገመግም እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን ሁኔታ እንዲያጠና ግብዣ ማቅረብ።
የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት እና ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ለዓለምዓቀፍ የኢትዮጵያ ለጋሾች
- በዘፈቀደ የታሰሩ እና በወንጀል ህጉ እና በጸረ-ሽብር አዋጁ መሰረት የተከሰሱ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን በሙሉ እንዲፈቱ በይፋ ጥሪ ማቅረብ አና በተናጥል ጫና ማሳደር።
- የጋዜጠኞች የፍርድ ቤት ክርክር ሂደት ዓለምዓቀፍ የፍርድ ሂደት መስፈርቶችን ያሟላ መሆኑን ለማረጋገጥ የፍርድ ሂደት ክትትሉን ማሻሻል እና መጨመር።
- የታሰሩ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን የሚገኙበትን ሁኔታ ለመገምገም እስር ቤቶችን እና ማቆያ ጣቢያዎችን ለመጎብኘት ጥያቄ ማቅረብ።
- ሃሳብን የመግለጽ ነፃነትን የተመለከቱ አሳሳቢ ጉዳዮች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ልማትን እና ደህንነትን እንደሚጎዱ ያላቸውን ስጋት ለመንግስት ባለስልጣናት በይፋ እና በግል መግለፅ።
- ገለልተኛ የጋዜጠኝነት ማህበር የሚፈጠርበትን መንገድ ጨምሮ የኢትዮጵያ መገናኛ-ብዙሃን የሙያ ብቃት እንዲዳብር ድጋፍ ማበርከት፤ ከአዲስ አበባ ውጭ ለሚገኙ ለግል መገናኛ-ብዙሃን ጋዜጠኞች የተለዩ እድሎች መኖራቸውን ማረጋገጥ እና የመገናኛ-ብዙሃን አቅምን ለማሳደግ ያለሙ እንቅስቃሴዎች እንዲካተቱ ልዩ ጥረት ማድረግ።
- ነጻ ጋዜጦች እና ሌላ አይነት ህትመቶች መንግስታዊ ያልሆኑ ወይም በመንግስት ቁጥጥር ስር ያልገቡ ማተሚያ መሳሪያዎችን የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት ድጋፍ ማድረግ።
በመንግስት ለተያዙ እና ከመንግስት ጋር ትስስር ላላቸው ማተሚያ ቤቶች
- ከመንግስት ጋር የተለየ ትስስር ያላቸው ህትመቶች ከሚታተሙበት የጊዜ ሰሌዳ በሚጣጠም መልኩ ሁሉንም ፈቃድ ያላቸው የግል መገናኛ ብዙሃን ህትመቶችን በተገቢው የጊዜ ገደብ እና አግባብ ባለው ሁኔታ በገለልተኝነት ማተም።
በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ የውጭ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን አስተላላፊዎች
- የተለየ አደጋ ያለባቸውን የመረጃ ምንጮች ለመለየት የሚጠቀሙበትን አሰራር ማጠናከር እና አደጋውን ለመቀነስ የሚወስዱትን እርምጃ ማዳበር፤ ይህም የግለሰቡ ማንነት እንዳይታወቅ ማድረግ፣ ማንነታቸውን በተመለከተ ያላቸውን መረጃ ሚስጥራዊ አድርጎ ማስቀመጥ እና ከፍተኛ ታዋቂነት ላላቸው ግለሰቦች ያለውን አደጋ እንዲገነዘቡት ማድረግን ይጨምራል፡፡
ለኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ዩጋንዳ መንግስታት
- ጋዜጠኞች እና ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ጨምሮ ጥገኝነት ጠያቂዎች ለጥገኝነት ማመልከቻቸው በአፋጣኝ ምላሽ መስጠት እና ሊደርስባቸው ከሚችለው ጥቃት ከለላ እንደተሰጣቸው ማረጋገጥ።
- ከጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ