ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጅብ እንደሆነ አድርጎ ያስባል፡፡ ይታያቹህ! ከየትኛውም ሀገር ሕዝብ በተለየ መልኩ ታጋሹን፣ ቅኑን፣ ቅዱሱን፣ ስስት ስግብግብነት የሌለበትን፣ አስተዋዩን፣ እሱ እየተቸገረ እየተራበ እነሱን ያጠገበውን ያደለበውን ቸር ምስኪን ሕዝብ ጅብ ነው ብሎ ማሰቡ አይደንቃቹህም? ምን ይደረግ ድንቁርና ተጭኗቸው ይሄን አስከፊ ድንቁርናቸውን ገንዘባችን ብለው አጥብቀው ይዘውት በየት በኩል አስተውለው ይሄንን ማንነቱን ይረዱለት? እናም ጅብ ነው ብለው በማሰባቸው አሕያ እየፈለጉ እሱን በመጠጋት በእሱ በመከለል ሲዎጉት ቆይተዋ ሰሞኑንም በሰፊው ይሄንን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ወያኔ በዚህ በያዝነው በታሕሳስ ወር 2007ዓ.ም. ከታዋቂ ሰዎችና “ከከያኔያን (Artists)” ለ ሕዝብ ለሕዝብ አቅንኦተ ግንኙነት (Public diplomacy) እና ሕዝብን ለመደለል ተልእኮ በቻለው መጠን እሽ ያሉትን ከያሉበት ሰብስቦ ሁለት ቡድን አዋቅሮ አንዱን ወደ ግብጽ አንዱን ደግሞ የሕወሀት መሪዎች ለትግል አነሣስቶ ወኔ ከሰነቀላቸው ከኢሐፓ እየተነጠሉ ወጥተው ሕወሀትን የመሠረቱበትን 40ኛ ዓመት የምሥረታ በዓላቸውን ምክንያት በማድረግ “የትግራይ ሕዝብ ትግል” ሲሉ በሐሰት የሚጠሩትን ትግል ለመዘከር ወደ ደደቢት በረሀ ልኮ ወይም ሰዶ ነበር፡፡
በእርግጥ ግን ይሄ የሕወሀት ስኬት የትግራይ ሕዝብ አስተዋጽኦ ብቻ ነው? ወያኔዎች እየዋሹና የማይፈጽሙትን ወይም ያልፈጸሙትን ቃል እየገቡ የአማራ ገበሬዎችን አታለው ስንቅ ከመስፈር መረጃ እስከማቀበል፣ ፊት ለፊት እንዲጋፈጡ ተደርገው የመጀመሪያውን ጥይት ቀማሽ እንዲሆኑ ፈንጅ ማምከኛ እንዲሆኑ የተደረጉ ልጆቹን አብረው እንዲታገሉ ከመስጠት እስከ በጉልበቱ በገንዘቡ መደገፍ ከዚያም አልፎ በደርግ ሠራዊት ላይ ፊቱን በማዞርና በመውጋት ሁለንተናዊ ድጋፍ ከአማራ ገበሬ ባያገኙና የአማራ ገበሬ እንደ ጠላት ቢያያቸው ባያቀርባቸው ባያምናቸው ባይደግፋቸው ኖሮ ተከዜን አይሻገሩ እንደነበር ጠንቅቀው እያወቁ እዚህ ለመድረሳቸው ተመስጋኙ ተወዳሹ የትግራይን ሕዝብ ብቻ ሲያደርጉ እንደሰው ውለታ ይዟቸው ትንሽ እንኳን ስቅጥጥ አይላቸውም፡፡
በተደጋጋሚ በቴሌቪዥን (በምርአየ ኩነት) እየቀረበ እንዳያቹህት የወያኔ ባለሥልጣናት ከአማራ ገበሬዎች ጋር ምን ያህል በቅርበት በአካል ገጽ ለገጽ እንደሚተዋወቁ፣ በትግል ወቅት ያደረጉላቸውን ውለታ እንዳይረሱና የገቡትንም ቃል እንዲፈጽሙ ሲጠይቁ ሲያሳስቡ በተገጋጋሚ ተመልክታቹሀል፡፡ እንግዲህ ትውውቃቸውና ቅርርባቸው የዚህን ያህል ነበር፡፡ እንዴት አድርገው አታለው ያንን ሁሉ ድጋፍ ያገኙ እንደነበር ይሄ በቂ መረጃ ይመስለኛል፡፡ እነሱ ግን ቃላቸውን ጠብቀው እናደርግልሀለን ይሉት የነበረውን ሊያደርጉለት ይቅርና ውለታውን ከመርሳትምና ከመካድም አልፈው ጭራሽም ሊያጠፉት በሰይጣናዊ ሸር ሌት ተቀን ያሴሩበታል ይዶልቱበታል በተግባርም ይፈጽሙበታል፡፡ እንዴ! ደግፈን ተዋግተን ለዚህ ያበቃነው ጭራሽ ሊያጠፋን ተነሣብን? ብሎ ተነሥቶ እንዳይቀብራቸውም ሀገሪቱን ከተቆጣጠሩ ማግስት ጀምሮ “እንግዲህ ሀገር ሰላም ሆኗል ለትንንሹ ነገርም እኔ አለሁ እኔ እጠብቃቹሀለሁ” እያለ በየጊዜው በዘመቻ መሣሪያውን አስፈትተው ወስደውበታል፡፡ መጨረሻ ላይም ደብቀህ ያስቀረኸው አለ እያሉ እየቀጠቀጡ ሥራ የሚሠራበት ገጀራ እንኳን ሳይቀር ሰብስበው ወስደውበታል፡፡ ይሄንን ካደረጉ በኋላ ነው እንግዲህ ምንም እንደማያመጣ ሲያውቁ አናቱ ላይ ፍጢጥ ብለው ሊጨማለቁበት በነፍስ በሥጋው ሊጫወቱበት የቻሉት፡፡ ታዲያ በምኑ ይውጋቸው? እንጅ የዋሁ ወገኔ እንዲህ መቀለጃ መጫወቻ ይሆን ነበር? ሽሩድነታቸውን አያቹህት? ግን ሰዎች ናቸው ትላላቹህ? እኔ እኮ ልቡሳነ ሥጋ አጋንንት እንጅ ሰዎች ናቸው ብየ አላምንም፡፡
ወያኔ በእነኝህ ሁለት ቡድኖች ያቀፋቸውን ሰዎች በተለይም በ “ከያኔያኑ” ቡድን በርካቶችን በተለይም ለወያኔ ባለማጎብደድ የሚታወቁትን ከያኔያን እነሱን ለፖለቲካዊ ዓላማው የሕዝብ ግንኙነት (Public relation) ትርፍ መጠቀሚያ ለማድረግ እንዲካተቱ ለማድረግ ያልፈነቀለው ድንጋይ ያላቀረበው የመደለያ ዓይነት ይሄም አልሆን ሲል ያልሞከረው የማስፈራሪያና ማዋከቢያ ዓይነት አልነበረም፡፡ የውርደቱ ውርደት በፊቱኑ ከጣላቸውና ካንበረከካቸው ካዋረዳቸው በስተቀር አዲስ ምርኮ አዲስ ሰለባ መጣል ሳይችል ቀርቷል፡፡ እነኝህን በሁለቱም ቡድን ያሰባሰባቸውን ግን የተለያየ መደለያና ጥቅማጥቅም በማቅረብ ደልሎ በእነዚህ ሁለት ቡድኖች አካቶ ለተልእኮው ተጠቅሞባቸዋል እየተጠቀመባቸውም ይገኛል ገናም ይጠቀምባቸዋል፡፡ አብዛኞቹም እንኳን ተጠይቀው በር እያንኳኩ በመልከስከስ የሚታወቁ በመሆናቸው ጭራሽ እንድች እንድች ዓይነት ነገር ስትኖርማ አጋጣሚውን ለመጠቀም እየተጋፉ እየተሸቀዳደሙ ከወያኔ እግር ስር በመልከስከስና ሕዝብን በማስጠቃት በማሳዘን የሚታወቁ በመሆናቸው እየተጋፉ እየተራኮቱ ነበር የታደሙት፡፡
ሕዝብ ለሕዝብ እንዲኖር ለሚፈለገው ዝምድና ለአቅንኦተ ግኑኝነት (diplomacy) ወደ ግብጽ ከተላከው ቡድን አንዷ ለምን እንደሔደች ስትናገር ምን አለች “መቸም በማንኛችንም ዘንድ የቱንም ያህል የፖለቲካና የአስተሳሰብ ልዩነት ቢኖርም በዐባይ ጉዳይ ላይ ግን አስተሳሰባችን አንድ በመሆኑና የተለየ አቋም ያለው ባለመኖሩ በዚህ መሠረት ነው የሔድኩት” ስትል ተናገረች፡፡ ሲጀመር ያለችው ነገር የተሳሳተ ነው፡፡ ነገሩን ለስሕተቷ እንዲመች ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር ከተጨባጭ እውነታዎችና ሥጋቶች አንጻር የዐባይ ግድብ በወያኔ እጅ መገደቡን የማይፈልጉ የሚቃወሙ በርካታ ዜጎች እንዳሉ ይታወቃልና፡፡ አንዱም እኔ ነኝ፡፡
ታስታውሱ እንደሆን ከዓመት በፊት “በዘመነ ወያኔ ዐባይ ቢገደብ የነዳጅ ዘይት ቢገኝ ለሀገራችን በረከት ወይስ መርገም?” በሚል ርእስ ሰፊ ትንታኔና መረጃ የያዘ ጽሑፍ አቅርቤ ነበር፡፡ እስካሁን በወያኔ እጅ ከተሠሩ እንደ የመንገድ፣ የቴሌኮሚውኒኬሽን፣ የመብራት ኃይል አቅርቦትና ስርጭት የመሳሰሉት የመሠረተ ልማት ሥራዎች በሙስና ቡጥቦጣ ምክንያት አደገኛ አስደንጋጭና አሳሳቢ በግልጽ የሚታዩ ከባባድ የጥራት ችግሮች፣ የአቅም ውስንነት ሊፈጥረው ከሚችለው የጥራትና ተያያዥ ችግሮች፣ የወያኔ በተፈጥሮው ጠባብና ለኢትዮጵያ እንደ ኢትዮጵያነቷ ለሕዝቧም እንደሕዝብ ክብርና ፍቅር የሌለውና ይሄንንም ከበፊት ጀምሮ በተለያዩ የክህደት ድርጊቶቹ በተደጋጋሚ አድርጎት ያሳየ ያረጋገጠ ከመሆኑ እንዲህ ዓይነት የሀገር ፍቅር፣ ቁርጠኝነት፣ ጽናት፣ ትጋት፣ ንጽሕና፣ ቅንነት፣ ሕብረት፣ አንድነት፣ በሙሉ ተነሣሽነት ፈቃደኝነትና ወኔ የሕዝብን ፍላጎት እምነት አቅምና ድጋፍ መታጠቅን የሚፈልግንና የሚጠይቅን ግዙፍ የልማት ሥራ ቀርጾ የመገንባት ሞራላዊ (ቅስማዊ) እና መንፈሳዊ አቅምና ብቃት የሌለው በመሆኑ፣ በእንዲህ እንዲህ ዓይነት ችግሮች ተተብትቦ ግድቡ ቢጠናቀቅም “የሰብአዊ መብቶችን አክብር” ከሚል አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ ጋር በሚያገኘው የእርዳታ ገንዘብ የዚህን ያህል ጨክኖብን የቀጠቀጠን የቀፈደደን የደቆሰን ያንገላታን የገደለን ያሳደደን አውሬና አንባገነን አገዛዝ ቅድመ ሁኔታ የሌለበትን የራሱን የገቢ ምንጪ ቢያገኝ በሀገርና በሕዝብ ላይ ሊፈጥረው ከሚችለው ጭንቅ ችግር አንጻር ግድቡ ተጠናቆ ገቢ ማስገኘት ቢጀምር የወያኔን ጨካኝ ጡንቻ አፈርጥሞ ሕዝብን ለከፋ አደጋ መዳረግ እንጅ ሀገርንና ሕዝቧን የሚጠቅም ባለመሆኑ በእነዚህና በሌሎችም ተጨባጭ ሥጋቶችና ችግሮች ምክንያት ይሄ በወያኔ እጅ እየተሠራ ያለ የግድብ ሥራ ሀገርንና ሕዝብን የሚጎዳ እንጅ በፍጹም የሚጠቅም ካለመሆኑ አንጻር የዚህን የግድብ ሥራ እንደማልደግፍ እንደምቃወም ገልጨ ነበር፡፡ አብዛኛው ሕዝባችንም በተለያዩ ነውሮቹ ምክንያት ፈጽሞ እምነት በማይጥልበት በወያኔ መሠራቱን በመቃወም ይሄንን የኔን ሥጋትና ሐሳብ የሚጋራ ነው፡፡
እነዚህ የሕዝብ ግንኙነት አቅኝ (Public diplomat) ተብየዎች ሻል ሻል ያለ ደረጃ ላይ እንደመገኘታቸው የጥቅም ነገር ሆኖባቸው ነው እንጅ ይሄ ይጠፋቸዋል ብየ አልገምትም ነገር ግን ተደልየ ነው ጥቅም ፈልጌ ነው ላለማለት “የፈለገውን ያህል ልዩነት ቢኖረንም ይሄንን የዐባይ ግድብ ሥራውን የሚቃወም የለም” በሚል ብልጠት መሰል የሐሰት ምክንያት ራሳቸውን ለመከለል ሞከሩ፡፡
ወደ ከያኔያኑ (አርቲስቶች) ስመለስ በእርግጥ ሰዎቹ የከያኔን ሰብእና የያዙ ባለመሆናቸው ማለትም “የቱንም ያህል ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆን ለእውነትና ለፍትሕ መረጋገጥ፣ ለሕዝብ መብቶች መጠበቅ፣ ለሀገር ጥቅሞችና እሴቶች መጠበቅና መከበር ጽናትን ታጥቀው በሥነ-ኪን ሥራዎች (በተውኔት፣ በሙዚቃ ወይም ዘፈን፣ በግጥም፣ በመጽሐፍ ድርሰት ወዘተ.) ታማኝና ጠበቃ የመሆንን ሰብእና የያዙ” ባለመሆናቸውና ለሆዳቸው ያደሩ እንደ እንስሳ ያለሆዳቸው ምንም ነገር የማያውቁ የማይታያቸው፣ ሕሊናቸውን የሸጡ፣ እራሳቸውን ያዋረዱ፣ ማሰብ የተሳናቸው፣ ምን ይሉኝን የማያውቁ፣ ያልበሰሉ እንጭጮች፣ ርካሾች፣ ነውረኞች፣ በመሆናቸው እነሱን ከያኔያን ብሎ መጥራት ቢከብድም ወይም የማይቻል ቢሆንም በዚያ አርቲስቶች (ከያኔያን) በተባለው ቡድን የተካተቱ ጥቂት ግለሰቦች በጉብኝታቸው መጨረሻ ላይ ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ከዚያች ቀን ጀምሮ ከሕወሀት ጎን መቆማችንን እናረጋግጣለን! በማለት ለሀገራቸውና ሕዝቧ ከወያኔ ጋር በማበር በጠላትነት መነሣታቸውን አረጋግጠዋ፡፡ እንደምገምተውም ወያኔ ከያኔያን ተብየዎችን ይሄንን ቃል እንዲገቡ ያደረጋቸው “እነሱ ካሉ ሕዝቡ ይሰማል” ከሚል የጅል ሐሳቡ በመጪው ምርጫ በካድሬነት ሕዝብን በመቀስቀስ እንዲያገለግሉት በማሰብ ነው፡፡ ከያኔያን ተብየዎቹ ይሄንን ያውቁ ይሆን? ወያኔ ይህ ድርጊቱ እንኳን ድጋፍ ሊያስገኝለት ሐዝብን ይባስ እንደሚያስቆጣ እልህ ውስጥ እንደሚከት የሚማር ጭንቅላት የለውም እንጅ ከዚህ ቀደም ሞክረው ካስከተለባቸው መጥፎ ውጤት መማር በቻሉ ነበር፡፡
አቶ ስብሐት ነጋም ትዕዛዝ አዘል በሆነ ቃል ከያኔያኑን “በጉብኝታቸው የተገለጸላቸውን የሕወሀትን ወይም የወያኔን ትግል ተግባር እንቅስቃሴ ዓላማ በጥበብ ሥራዎቻቸው እየገለጹ ለሕዝብ ማስተዋወቅ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል፡፡ ከያኔያኑም ይሔንን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡ ችግሩ ለማን ነው የሚያቀርቡት? የሚለው ነው፡፡ ወይስ ወያኔ ሕዝቡን እያስገደደ አድምጡ ሊል ነው?
እዚህ ላይ አንድ ልንዘነጋው የማይገባን ነገር ቢኖር በዚህ ቡድን እንዲካተቱ የተደረጉ የቲያትር (ተውኔት) ቤቶች ሠራተኞች ከያኔያን የመንግሥት ሠራተኞች እንደመሆናቸው በዚህ ጉብኝት ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል በተደረጉ ሌሎች ዝግጅቶችም በግዳጅ እንዲሳተፉ ሲደረግ ቆይተዋል፡፡ አንሳተፍም ያሉትን ደግሞ አገዛዙ የሥራ ዋስትናቸውን እንዲያጡ ወይም እንዲባረሩ ሲያደርጋቸው ቆይተቷል፡፡ ይሄ ችግር በእነሱ ብቻ ያለ አይደለም አጠቃላይ በመንግሥት ሠራተኛው ሁሉ እንጅ፡፡
ከዚህ አንጻር እነዚህ የቲያትር ቤቶች ሠራተኞች ይሄ ችግራቸው ግንዛቤ ውስጥ ሊገባላቸው የሚገባ ይመስለኛል፡፡ የፈለገው ይምጣ እራሴን አላረክስም በማለታቸው ተባረው ለችጋር የተዳረጉ ኩሩ ቆራጥ ባለ ሕሊና ጀግና ወገኖች እንዳሉ ሁሉ ልጆቸን ምን ላደርጋቸው ነው? እንዴትስ ብየ እኖራለሁ? ብለው አማራጭ ከማጣት አንጻር አጣብቂኝ ውስጥ የሚገቡ ሳይወዱ ሳይፈልጉ ሕሊናቸው ሳይፈቅድላቸው ውስጣቸው እየተቃጠለ እንባቸውን ወደ አምላካቸው እያፈሰሱ ችግር ላይ ላለመውደቅ የወያኔን ፈቃድ የሚፈጽሙ ወገኖቻችንም አሉ፡፡ ሁሉም ግን ማን ምን እንደሆነ ማለትም ተገዶ አማራጭ በማጣት እንዲያ ያደረገውንና አማራጭ ሳያጣ የሚበላው ሳያጣ ለማይሞላ ሆዱ ሲል እየተስበደበደ ወያኔ ከጠየቀውም በላይ የወያኔን ፈቃድ በመፈጸም ሕዝብን የሚያበግነው የሚያስጠቃውና ወያኔን የሚያገለግለው ማን እንደሆነ ከሕዝብ የተሠወረ አይደለምና በዚያ መልክ የሚታዩ ይሆናል፡፡ ይሄ እንግዲህ ነጻነቴን ክብሬን ሰብእናየን ሕሊናየን ማንነቴን የሚል ዜጋ ሁሉ የግድ የሚከፍለው ዋጋ ነው፡፡ ይሄንን ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ወገኖች ጥቂቶች አይደሉም፡፡ በእኔ ላይ የደረሰው የኑሮ መመሰቃቀልም አንዱ ማሳያ ነው፡፡ እስር እንግልት በደል ቢያጋጥምም ለችግር መዳረግ ቢከሰትም ሆድ ይራብ ይጠማል እንጅ ሕሊና ግን ይጠግባል ይረሰርሳል ይረካል ይለመልማል፡፡ እንደ እንስሳ ሆኘ ለሀገሬና ለሕዝቤ ጠላት ሆኘ በልቸ ሆዴ ከሚጠግብ ሰው የሰው ልጅነቴን አረጋግጨ ለሀገሬና ለሕዝቤ ህልውና እየታገልኩ ሆዴ ተርቦ ሕሊናየ ቢጠግብ ሽ ጊዜ እመርጣለሁ ስለሆነም አደረኩት፡፡ ቅንጣትም አልጸጸትም ከዚህም በላይ በቅርብ ጊዜ እንደሚደፉኝ ነግረውኛል ይሄም ቢሆን በሀገሬ በሕዝቤና በሃይማኖቴ ስም ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡ ሕዝቡ ቆርጦ እኔንና እኔን የመሰሉ ሰዎችን ቢመስልና መድፈር ቢችል ይደርስብኛል ብለን በየግል የምንፈራው ነገር አንዱም ሳይደርስብን እራሳችንን ነጻ ማውጣት በቻልን ነበር፡፡
እዚህ ላይ አንድ ሊነሣ የሚገባው ጥያቄ “ለመሆኑ ግን ወያኔ የመንግሥት መዋቅር በመጠቀም የመንግሥት ሠራተኞችን እያስገደደ የሕወሀትን ዓላማና ሥራን የማስፈጸም የማሠራት መብት አለው ወይ?” የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ መልሱ ቀላልና ግልጽ ነው ሕገ ወጥና ከአንባገነናዊ ማንነታቸው በመነሣት የሚፈጽሙት ግፍ ነው የሚለው ነው፡፡ ይሄንን እያደረጉት ያሉት የገዛ ሕገ መንግሥታቸውን በመጣስ በመጻረር በመተላለፍ ነው፡፡ ወያኔ በሕገ መንግሥቱ ሌላው ቀርቶ እንኳን በተቃውሞ እንቅስቃሴ ሳይሳተፉ ከተቃዋሚም ከወያኔም ሳይሆኑ ገለልተኛ ሆነው ይቅርና በተቃውሞው ጎራ ውስጥ ተሰልፈው የነቃ ተሳትፎ እያደረጉም እንኳን ቢሆን ያለአንዳች የሥራ ዋስትናን የማጣት ሥጋትና ችግር የመንግሥት ሥራቸውን በነጻነት እየሠሩ መኖር እንደሚችሉ አረጋግጦ ባለበት ሁኔታ ነው እንዲህ ዓይነቱን ሕገ ወጥና ነውረኛ ቆሻሻ ተግባር እየፈጸመ ያለው፡፡ የመንግሥት ሠራተኛው ይሄንን መብቱን እያወቀም ነው መብቱ ቢሆንም መብቱን ማስጠበቅ የሚችልበት ቁርጠኝነት ጽናት ሕብረትና አንድነት ስለሌለው መፍጠር ስላልቻለ ወያኔ እንደፈለገ እየተጨማለቀበት ያለው፡፡
ወገን ሆይ! ተዋርደሀል እኮ! ተንቀሀል እኮ! በቁምህ ቀብረውሀል እኮ! መቸ ነው በቃ! የምትለው? እየከፋ መጣብህ እንጅ እየተሻለ እየተማረ እየተመከረ እየሠለጠነ እኮ አይደለም የመጣው፡፡ ታግሰህ ያሳለፍከው ጊዜ የከፈልከው ዋጋ ሁሉ እኮ ምንም ጥቅም ፋይዳ ሳያስገኝልህ ከንቱ መሥዋዕትነት ሆኖ እኮ ነው የቀረው፡፡ ከዚህም በኋላ ልታገስ ብትል በመታገስ እየከፈልክ ያለውን ከንቱ መሥዋዕትነት የማይጠቅም ዋጋ ሕይዎትህን ያመረው ያከፋው ካልሆነ በቀር ምንም እኮ የሚጠቅምህ የሚረባህ የሚለውጥልህ ነገር የለም፡፡ ኧረ በቃ! በል? ኧረ ውርደትህ ይሰማህ? ኧረ መናቅህ ያንገብግብህ? የገዛ እንጀራህን እንዲህ ተዋርደህ ተንቀህ ተበሻቅጠህ እየተቃጠልክ እያረርክ ከወያኔ እጅ መብላት አለብህ እንዴ? ወያኔ እኮ የራስህን የሀገርህን ገንዘብ ሳይሆን ልክ ከኪሱ አውጥቶ በችሮታው እንደሚሰጥህ እንደሚከፍልህ አድርጎ እኮ ነው እንድታስብ ያደረገህ፡፡
ወያኔ በወረቀትና በብዙኃን መገናኛው ሌላ እያወራ በተግባር ግን ፍጹም የዚያን ተቃራኒ እየሠራ እንዲህ አድርጎ ሲጫወትብህ ዝም ብለህ ተንከርፍፈህ ታየዋለህ? ማንን ነው የምትጠብቀው? ማን ከየት መጥቶ ላንተ መሥዋዕትነት ከፍሎልህ ነጻ እንዲያወጣህ ነው የምትጠብቀው? ኧረ ተው ከከንቱና ባዶ ምኞትህ ውጣና ሕልምና ምኞትህን ተጨባጭ አድርገህ ለራስህ ደራሽ እራስህ መሆንህን አውቀህ በጊዜ አንድ ነገር አድርግና እፎይ በል? ተው በዘገየህ ቁጥር ነጻ ልትሆን የምትችልበትን ዕድል እያጠበብክ እንዳይቻል እያደረክ ነውና ያለኸው ከቶም ወደማትወጣው አዘቅት ውስጥ ጠልቀህ ከመግባትህ በፊት ሆ! ብለህ ተነሥና አሜከላህን ነቅለህ ጣለው? ራስህን ነጻ አውጣ? እየተሰደድክ ሳታልቅ በገዛ ሀገርህ ሆነህ ያገርህ የእንጀራህ ባለቤት ሁን? ነጻ ሆኖ በነጻነት ማሰብ፣ መናገር፣ መሥራት፣ መውጣት መግባት፣ እፎይ! ብሎ መተንፈስ አይናፍቅህም? እንደዚህ መሆን አያስጎመጅህም? ባርነት አልሰለቸህም? ያውም በወያኔ! ሥነ-ሥርዓት ሥነ-ምግባር ግብረ-ገብ በማያውቀው ባለጌ ስድ ቆሻሻ ነውረኛ ደንቆሮ ጠባብ ጎጠኛ ቡድን?
የሆነ ቦታ ላይ እንቢ ማለት ካልቻልክ እኮ የዘለዓለም ባሪያው ሆነህ መቅረትህ እኮ ነው! ለልጆችህ የተሻለች ሀገር የተሻለ ሕይዎት እንዲኖራቸው አትፈልግም? እየከፋ የሚሔደውን የዚህን ቆሻሻ ወራዳ አገዛዝ ልታወርሳቸው ነው የምትፈልገው? ኧረ እባክህ ተነሥ? ኧረ ስለምትወደው ነገር ሁሉ ብለህ መጫወቻ መቀለጃ አትሁን በቃ! በል???
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!