June 4/2014
በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ታላቅ የሕዝብ ቅልቅል ተካሂዷል። ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል፦ የአህመድ ግራኝ ወረራ፣ የኦሮሞ ወረራ፣ በዘመነ መሣፍንት የነበሩት የእርስ በእርስ ጦርነቶች፣ ፈፃሜ-ዘመነ መሣፍንትን ያበሠሩት የማዕከላዊ መንግሥትን እንደገና የማዋቀር ጦርነቶች እንዲሁም ሁለቱ የኢጣሊያ ወረራዎች የሚጠቀሱ ናቸው። እነዚያ ጦርነቶች እና የእርስ በእርስ ግጭቶች ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የሕዝብ ክፍል ሕይዎት እንዳሣጡ አይካድም። ያንንም ተከትሎ ከኑሮ አስገዳጅነት እና በአገዛዝ ኃይሎች የበላይነት የያዘው አካል በሚፈጥረው የፖለቲካ አሠላለፍ መለዋወጥ ምክንያት የአንዱ ጎሣ ወይም ነገድ አባሎች በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ የመጥፋት ጉዳት ደርሶባቸዋል። በዚህ ረገድ ከኢትዮጵያ ዋና ዋና ነገዶች እና ጎሣዎች መካከል፦ በምዕራብ ኢትዮጵያ ነዋሪ የነበሩት የጋፋት ነገድ በኦሮሞ ወረራ ሙሉ በሙሉ እንዲጠፉ ሆነዋል ወይም ማንነታቸውን ተገድደው ለውጠው «ኦሮሞዎች» ወይም «ዐማራዎች» ወይም በሌላ ነገድ ስም ይጠራሉ፤ የሜያ ነገድ ተወላጆች ደግሞ በግራኝ አህመድ እና በኋላም ተከትሎ በመጣው በኦሮሞዎች ወረራ ምክንያት ቁጥራቸው በእጅጉ ተመናምኖ ዛሬ በዝዋይ ኃይቅ ውስጥ በሚገኙ ደሴቶች እና አካባቢው ብቻ ተወስነው ይገኛሉ። ጥንት በባሊ (ባሌ) እና ፈጠጋር (አርሲ) ተስፋፍተው ይኖሩ የነበሩት ሐዲያዎች እና ከንባታዎች በኦሮሞዎች ወረራ ተጨፍልቀው «ኦሮሞዎች» ሲባሉ ቀሪ ወገኖቻቸው በደቡብ ምዕራብ ሸዋ በአንድ ጠባብ አካባቢ በተጨናነቀ ሁኔታ እንዲኖሩ ተገድደዋል። ከዚህ በተጨማሪም፦ አርጎባዎች፣ ቀቤናዎች፣ ወርጂዎች፣ አላባዎች፣ ሲዳማዎች፣ ወዘተርፈ በኦሮሞዎች ወረራ ምክንያት ማንነታቸውን እንዲቀይሩ ተገድደዋል፤ ከዚያም አልፎ በጅምላ ተጨፍጭፈዋል። በእናርያ ንጉሥ ግዛት ሥር የነበሩት ጃንጀሮዎች (የም) በኦሮሞ ቆሮዎች (በእነ አባ ጅፋር) በገፍ በባርነት ተፈንግለዋል። የዳውሮ እና የገሙ ሰዎች ደግሞ ግዛታቸውን በኦሮሞ ወራሪዎች ተነጥቀዋል። በመሆኑም የዘመናዊት ኢትዮጵያን የሕዝብ አሠፋፈር ጥንቅር ለውጥ ለመገንዘብ ከአህመድ ግራኝ ወረራ ጀምሮ ማዬቱ ለበለጠ ግንዛቤ ይረዳል።
ግራኝ አህመድ በኢትዮጵያ ላይ ወረራውን የጀመረው የንጉሡ የአፄ ልብነድንግል ሹም እና የደዋሮ (ምዕራብ ሐረርጌ) ገዢ ከነበረው ከአዛዥ ፋኑኤል ጋር በ፲፭፻፲፯ ዓ.ም. ባደረገው ውጊያ ነበር። ግራኝ አህመድ ዘንተራ (ደንቢያ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ጣና ሐይቅ አጠገብ) በአፄ ገላውዲዎስ ሥር ሲዋጉ በነበሩት የፖርቱጋል ወታደሮች የጥይት አረር ተመትቶ በየካቲት ፳፯ ቀን ፲፭፻፴፭ ዓ.ም. እስኪገደል ድረስ ኢትዮጵያን ለ፲፱ ዓመታት ያህል በጦርነት አመሠቃቅሏታል፤ ዜጎቿን ኍልቆ-መሣፍርት ለሌለው ግፍ እና በደል ዳርጓቸዋል። የእርሱን የወረራ ፍፃሜ እግር በእግር ተከትለው የመጡት የኦሮሞ ወራሪዎች ደግሞ ከ፲፭፻፵ዎቹ ጀምረው ከደቡብ ከነጌሌ ቦረና አካባቢ ተነስተው ከፊታቸው የነበረውን የሌላውን ነገድ እና ጎሣ ሕዝብ ዕድሜ እና ፆታ ሣይለዩ በጅምላ እየፈጁ እስከ ትግራይ ድረስ ዘልቀዋል። ኦሮሞዎች አብዛኛውን የኢትዮጵያ ክፍል በተከታታይ ወረራዎች ለመያዝ የፈጀባቸው ጊዜ ከ፫፻ ዓመታት ይበልጣል። ስለዚህ ዛሬ ያለውን የኢትዮጵያን የሕዝብ አሠፋፈር በቅጡ ለመረዳት ያለፈውን የ፩፻፳ ያመታት ብቻ ታሪክ ሣይሆን አህመድ ግራኝ ኢትዮጵያን ከወረረበት ከ፲፭፻፲፯ ዓ.ም. ጀምሮ የነበረውን ሁኔታ መመርመር የግድ ያስፈልጋል። ሆኖም ባለፉት ፵ እና ፶ ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ «መሪዎች ነን» ብለው የተነሱ ልሂቃን የኢትዮጵያን የረዥም ዘመን የታሪክ ጉዞ በ፻ ዓመታት ብቻ በመገደብ በጉንጭ አልፋ ውዝግብ ሕዝብን ሲያተራምሱ ይታያሉ። በተለይም ለዚህ ውዝግብ ቀዳሚዎቹ የትግሬ እና የኦሮሞ ልሂቃን ሲሆኑ እንደ ዋለልኝ መኮንን ዓይነቶቹ ጥራዝ ነጠቅ የዐማራ ልሂቃንም በዚህ ክበብ ውስጥ ይገኙበታል።
ታሪካቸውን በቅጡ ያልተረዱ ጥቂት፣ አክራሪ እና ዘረኛ የሆኑ የኦሮሞ ልሂቃን፣ ከጀርመናውያን የኃይማኖት ሠባኪዎቻቸው የተጋቱትን ለኢትዮጵያዊነት እና ለዐማራ ያላቸውን ጥላቻ እንደበቀቀን ደግመው፣ ደጋግመው ሲጮኹ ይሰማሉ። ለመሆኑ የዚህ አስተሣሰብ ምንጩ ከዬት ነው? በዘመነ ቅኝ አገዛዝ የአፍሪካ ቅርምት ወቅት፣ እንግሊዞች፥ «ግብፅን መቆጣጠር ማለት ቀይ ባሕርን መቆጣጠር ማለት ነው፤ ቀይ ባሕርን መቆጣጠር ማለት ደግሞ መላውን የመካከለኛውን ምሥራቅ መቆጣጠር ነው፤» ብለው በማመን ግብፅን «የገንዘብ ብድር ዕዳን» ሠበብ በማድረግ ከቱርኮች ነጥቀው ቅኝ ግዛታቸው አደረጓት። እንደዚያም ሁሉ፣ የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሠባኪዎች «ቻይናን ስጡን እና እስያ የእኛ ትሆናለች» ብለው ሰላዮቻቸውን በኃይማኖት ሠባኪነት ሽፋን በቻይና አሠማሩ፥ ቻይናም ቀስ በቀስ በምዕራባውያን ተፅዕኖ ሥር ወደቀች። የኦነግ እና የኦሕዴድ የንስሃ አባታቸው የሆነው ጀርመናዊው ሰላይ ዩሓን ክራፍ በበኩሉ «ጋሎችን ስጡን እና መላው የመካከለኛው የአፍሪቃ ክፍል የኛ [የጀርመኖች] ይሆናል፤» በማለት ጀርመን የኦሮሞን ነገድ ተጠቅሞ ምሥራቅን እና መካከለኛውን የአፍሪቃ ክፍል በቅኝ ግዛቱ ሥር የሚያውልበትን መንገድ መጥረጉን እናያለን። ስለሆነም «የነፃ ኦሮሚያ» ዓላማ አራማጆችም «ኦሮሚያ» ከሚባለው አዲስ ወያኔ-ሠራሽ ግዛት ጀምሮ የሚያራግቡት ተግባር ሁሉ፣ በ፲፱ኛው መቶ ክፍለ-ዘመን ሠፊውን የኢትዮጵያ አካል ቆርሶ ለጀርመን የቅኝ ግዛት ለማድረግ የታቀደው ሤራ በዚህ በእኛ ዘመን ታድሶ መቅረቡን መገንዘብ ያስፈልጋል።
ከዚህ በተጨማሪ ዩሓን ክራፍ፣ ጀርመን በአውሮፓ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ የበላይነቱን እንድትይዝ ያለውን ፍላጎት እንደሚከተለው ገልጿል፥ «“ጋሎችን” መያዝ መካከለኛው አፍሪቃን ለመቆጣጠር ከማስቻሉም ሌላ፣ በቀይ ባሕር ዳርቻ የሚገኙትን አገሮችን መያዝ ከንግድ መቆጣጠሪያነት ባሻገር፣ ጀርመን በአውሮጳ ያላትን የበላይነት ማረጋገጥ እና የጀርመንን ሥልጣኔ በዐረቦች ምድር፣ በአበሻ እና በመላው ምሥራቅ አፍሪቃ ማስፋፋት ነው። የጀርመን በምሥራቅ አፍሪቃ መስፋፋት፣ የእስልምና ኃይማኖት በዐረብ ምድር እና በአፍሪቃ ጠረፎች የሚያደርገውን መስፋፋት የሚያዳክም፣ የዐረቦችን የባሪያ ንግድ የሚቀንስ፣ እንዲሁም የምሥራቅ አፍሪቃን ሕዝብ አረመኔነት በክርስትና ሥልጣኔ መዋጋት ነው። ከአበሻ በስተደቡብ ያሉት “ጋሎች” የሠፈሩበት ቦታ ለአውሮጳውያን ሠፋሪዎች ምቹ ቦታ ነው፤» በማለት ጀርመን የኦሮሞዎችን ልብ ከኢትዮጵያዊነት ስሜት በማውጣት ምሥራቅን እና መካከለኛውን አፍሪቃ እንዴት በቁጥጥሩ ሥር ማዋል እንደሚችል «ወንጌላዊው» ክራፍ ምክሩን ለግሷል፤ ምክሩም የመከነ አይመስልም፤ ኦነግን እና መሰል ድርጅቶችን አፍርቷል። ለአብነትም ያህል ለኦነግ መመሥረት እና መጎልበት የስካንዴኔቪያን አገሮች፣ ጀርመኖች እና ሌሎችም የቅኝ ገዢነት ቅዠታቸው ያልለቀቃቸው አውሮጳውያን የሚያደርጉትን ሁሉን-አቀፍ ድጋፍ ልብ ይሏል!
በማስከተልም ዩሓን ክራፍ፣ ከሸዋ በስተደቡብ የሚኖሩት “ጋሎች” ብዛት ያላቸው መሆኑን ገልጦ፣ የእስላሞችን የመሥፋፋት ወረራ ሊመክቱ እንደሚችሉ እና የአፍሪቃ ጀርመኖች ሊሆኑ እንደሚችሉ ዕምነቱን አስረድቷል። ዩሓን ክራፍ ምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪቃ በጀርመን ቁጥጥር ሥር እንዲውል የነደፈው አንዱ ሥልት፣ ሚሽነሪዎችን በወንጌል ማስፋፋት ስም በአካባቢው በማሠማራት፣ የየአገሮቹ ልዩ ልዩ ነገዶች እና ጎሣዎችን ሊለያዩበት እና ሊናቆሩበት የሚችሉበትን ዘዴ ማጥናት፣ እንዲሁም ያገኟቸውን የማናቆሪያ ቀዳዳዎች ማስፋት ነበር። ለዚህም ዩሓን ክራፍ ያቀረበው ኃሣብ፦ «በደቡብ እና በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆችን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ነገዶች በመለዬት፣ በተቃራኒው ተበታትነው ይኖሩ የነበሩትን የኦሮሞ ጎሣዎች አንድ የሚያደርግ አዲስ መጠሪያ ስም በመስጠት፣ በዚህ አዲስ ስም የሚታወቅ የአካባቢ ስም ፈጥሮ፣ ያን አካባቢ ከቀረው የኢትዮጵያ የሚገነጥል ብሔርተኛ ቡድን በጀርመን ሁለንተናዊ ርዳታ ማጠናከር፤» የሚለው ነበር። ለዚህም «“ጋላ” የሚለው ስም ሁሉንም የነገዱን አባሎች አጠቃሎ ለመጥራት አያስችልም» የሚል ምክንያት በመስጠት፣ «ኦርማኒያ» ከሚለው ስም «ኦሮሚያ» የሚል ቃል በማውጣት ጥንት “ጋላ” በመባል የሚታወቀው ነገድ በዚህ እርሱ ባወጣው አዲስ ስም እንዲጠራ እና «ኦሮሚያ» ለሚባል ክልል ነፃ መውጣት እንዲታገል በወንጌል ማስፋፋት ስም አስተማረ፣ ሰበከ። በዚህ መሠረት ዩሓን ክራፍ ራሱ «ኦሮሚያ» ብሎ የሰየመውን የኢትዮጵያ አካል መቆጣጠር ማለት፣ ምሥራቅን እና መካከለኛውን አፍሪቃ መቆጣጠር እንደሆነ በማመን የጀርመን ተስፋፊዎች ዓይናቸውን ኢትዮጵያን በማፍረስ ላይ እንዲያነጣጥሩ ምክር ለገሠ።
የዩሓን ክራፍ እና የመሠሎቹ ምክር በጀርመን ቅኝ ገዢዎች ልብ ውስጥ መስረፁ ማስረጃው ጀርመን በአፍሪቃ አኅጉር ላይ ትከተል በነበረው የቅኝ ግዛት ፖሊሲ ላይ ጉልህ አሻራ አኑሯል። በዚህ ረገድ እስከ ፩ኛው የዓለም ጦርነት ድረስ ጀርመኖች ከምሥራቅ አፍሪቃ፥ ታንዛኒያን፣ ሩዋንዳን እና ብሩንዲን፤ ከምዕራብ አፍሪቃ ቶጎን፣ ከፊል ጋናን እና ካሜሩንን፤ ከደቡባዊ አፍሪቃ ደግሞ ናሚቢያን በቅኝ ግዛትነት በያዙበት ወቅት ከእንግሊዞች፣ ፈረንሣዮች እና ጣሊያኖች በከፋ ሁኔታ ያካሄዱት የከፋፍለህ-ግዛው የቅኝ አገዛዝ አካሄድ አይረሣም። ከሁሉም መዘንጋት የሌለበት አብይ ነጥብ፥ በ፲፱፻፹፮ ዓም በሩዋንዳ በሁቱዎች እና በቱትሲዎች መካከል የደረሠው የዘር ዕልቂት እና በብሩንዲም በየጊዜው በዘር ልዩነት ምክንያት የሚደረገው መተላለቅ ሠንኮፉ በጀርመን ቅኝ ገዢዎች የተተከለ እና በኋላም ጀርመኖቹን በተኩት ቤልጂጎች ዳብሮ በዘመናችን ደግሞ በፈረንሣዮች የተተበተበ የተንኮል ድር ድምር ውጤት መሆኑን ነው። በእኛም አገር በኢትዮጵያ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት በዩሓን ክራፍ መሠሎቹ አመለካከት ተኮትኩተው ያደጉ የኦሮሞ ልሂቃን የሚያቀነቅኑት አስተሣሰብ አለ። ይኼውም፥ የያዙትን የኢትዮጵያዊነት ማንነት ለማስጠበቅ ሣይሆን ለማጣት በሚያስገድድ መልክ በራሣቸው ላይ ዘመቻ ከፍተው፣ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ቀርቶ ለራሳቸው ሊሰሙት የማይፈቅዱትን ጩኸት ሲያሰሙ ይደመጣሉ።
ለመሆኑ ጥቂት የኦሮሞ ልሂቃን ነገዳቸውን “ጋላ”፣ ቋንቋቸውን “ጋልኛ” የሚለውን ዐማሮች እንደሰጡዋቸው አድርገው የሚያቀርቡት ታሪካዊ መሠረት አለው? በመሠረቱ “ጋላ” እና “ጋልኛ” የሚሉትን ስሞች ዐማራው አላወጣቸውም። እንዲያውም የኦሮሞን ታሪክ በስፋት እና በጥልቀት ያጠኑ ሰዎች እንደሚያስገነዝቡት “ጋላ” ማለት እስላምም፣ ክርስቲያንም ያልሆነ ማለት እንደሆነ ያብራራሉ። የቃሉም ምንጭ ሶማሊኛ እንደሆነ ያስገነዝባሉ። በሌላ በኩል “ጋላ” ማለት ግመል ማለት ነው የሚሉም አሉ። ሌሎች ደግሞ “ጋላ” የሚለው ቃል «ገላ» ከሚለው የኦሮሚኛ ግሥ የወጣ መሆኑን እና ትርጉሙም «ወደ ቤታችን መሄድ ፈለግን፣ ወደ ቤታችን ሄድን ወይም ገባን» ማለት እንደሆነ ያስረዳሉ። ይህም ትርጉም ኦሮሞዎች በሶማሌና በባንቱ ጎሣዎች ተገፍተው፣ ከነበሩበት ከምሥራቅ አፍሪቃ የሕንድ ውቅያኖስ ዳርቻዎች ፈልሰው ወደ ደቡብምሥራቅ ኢትዮጵያ ግዛት፥ ወደ ባሌ፣ የተጠጉበትን ዘመን በማውሣት፣ በሰላም ተረጋግተው የሚኖሩበትን ሥፍራ ፈልገው ማግኘታቸውን የሚያመለክት ስያሜ እንደሆነ ብዙዎች በትርጉሙ ይማማሉ። ስለዚህ ጥቂት ዘረኛ የኦሮሞ ልሂቃን «“ጋላ” የሚለውን የስድብ ስያሜ የሰጠን ዐማራው ነው፤» የሚሉት የራሣቸው የማንነት ቀውስ ያስከተለባቸው ግራ መጋባት ከመሆን ውጭ ሌላ አሣማኝ ምክንያት የላቸውም። «ዐማራ ይህንን መጠሪያ ሰጠን» የሚሉትም ውንጀላ ፍፁም መሠረተ-ቢስ ሐሰት ነው። በአንፃሩ «ኦሮሞ» እና «ኦሮሚያ» ለሚሉት መጠሪያዎች የታወቀ ፈጣሪ አላቸው፦ እርሱም አፍቃሬ ቅኝ ገዢዎች የነበረው ጀርመናዊው ዩሓን ክራፍ ነው።
ዩሓን ክራፍ «ጋላ» የሚለውን ቃል ለመቀየር ያነሣሣውን ኃሣብ ሲያስተነትን፦ «ጋላ» የሚለውን ቃል ሲተረጉም «ስደተኛ» ማለት እንደሆነ እና ይህም መጠሪያ በዐረቦች እና በ«አበሾች» የተሰጠ እንደሆነ ይገልፃል። በአንጻሩ እርሱ የፈጠረው «ኦርማ» ወይም «ኦሮማ» ማለት ትርጉሙ «ጎበዝ» ማለት እንደሆነ ያምናል። በእርሱ አባባል «ጋሎች» ለራሣቸው እና ለሚኖሩበት አካባባቢ አጠቃላይ የወል መጠሪያ ስለሌላቸው «ኦርማኒያ» ተብለው እንዲጠሩ ኃሣብ አቅርቧል። ሆኖም ይህንን የዩሓን ክራፍን ኃሣብ የእርሱ-ቢጤ የሆኑ የዘመኑ ሚሽነሪዎች እና ተመራማሪዎች እንኳን አልተቀበሉትም። ለምሣሌም ያህል፦ ኢትዮጵያን ያጠኑ እንደ ዶክተር ቻርለስ ቴ ቢክ ያሉ የመልከዐምድር ተመራማሪዎች፣ ለኦሮሞዎች «ጋላ» የሚለውን ስም የሰጡዋቸው ዐረቦች እና «አበሾች» አለመሆናቸውን እና ስሙ ከራሣቸው ቋንቋ የተገኘ እንደሆነ ይሞግታሉ። ይሁን እንጂ፣ ዕውነቱን ትተው ውሸቱን፣ ሠፊውን ጠልተው ጠባቡን፣ የሚያኮራውን ንቀው የሚያቀልለውን፣ የሚያስከብረውን አውግዘው የሚያዋርደውን፣ የመረጡት ጥቂት «ተማርን ያሉ» የኦሮሞ ልሂቃን፣ የዩሓን ክራፍን ስብከት አምነው ተቀብለው፣ ዐማራን እና ኢትዮጵያን ከምድረ-ገፅ በማጥፋት፣ «ኦሮሚያ» የተባለ አዲስ አገር በመመሥረት እንቅስቃሴ ላይ ከተሠማሩ ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በላይ አድርገዋል። ወራሪ የሆኑትን ኦሮሞዎችን እንደ ተወራሪ በመቁጠር፣ ወያኔም ዮሓን ክራፍ የሰጠውን የአካባቢ መጠሪያ በማፅደቅ፣ ዐማሮችን እና ሌሎችን ኢትዮጵያውያን ከአፅመ-ርስታቸው በማባረር፣ «ኦሮሚያ» የሚል አዲስ ግዛት ፈጥሮላቸዋል።
«እንግዳ ሲሰነብት፣ ባለቤት የሆነ ይመስለዋል፤» የሚሉት አባባል አለ። እንግዶቹ እና ወራሪዎቹ ኦሮሞዎች፣ የነባሮቹን የኢትዮጵያ ነገዶች እና ጎሣዎች ግዛቶች በወረራ ይዘው፣ የገደሉትን ገድለው፣ የሠለቡትን ሠልበው፣ ጡት ቆርጠው ሲያበቁ፣ ተበዳዮቹ «ይህ በደል ተፈፀመብን» ሣይሉ፣ እንዲያውም እነርሱ «ተበደልን» ብለው በወረራ የያዙትን አገር እንገንጥል ይላሉ፣ ነባሮቹን ኢትዮጵያዊ ነገዶች እና ጎሣዎች ያፈናቅላሉ። እነርሱው ነባር የአካባቢ ስሞችን ለውጠው እና በነገዳቸው ስም ቀይረው መያዛቸው እየታወቀ፣ «ዐማራው ስማችን እንድንቀይር አስገደደን፤ ቋንቋችንን፣ ባህላችንን እና የየአካባቢ ስሞችን ለወጠብን» እያሉ ስም ሲያጠፉ ይሰማሉ። ሃቁ ግን የአካባቢ ስሞችን በመለወጥና በራሱ ነገድ ስም በመጥራት የሚታወቀው የኦሮሞ ወራሪ ኃይል ነው። የታሪክ ሠነዶችን ማጣቀስ ካስፈለገም፥ በ፲፮፻ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያን ከጎበኙት እና በአገሪቱም ተቀምጠው የሕዝቡን የአኗኗር ልማድ እና ዘይቤ በቅርበት እያጠኑ የታሪክ መድበሎችን ካበረከቱልን የአውሮፓ ሊቃውንት መካከል ፔድሮ ደ-ኮቪልኻም፣ አባ ፍራንሴስኮ አልቫሬዝ እና ሌሎችም የፖርቱጋል ዜጎች አያሌ ጠቃሚ የታሪክ ማስረጃዎችን ትተውልን አልፈዋል። እንዲሁም አህመድ ግራኝን ተከትሎ የዘመተው፣ እርሱ ባደረጋቸው ወረራዎች ሁሉ የቅርብ ተሣታፊ የነበረው የመናዊው ሺሃብ አድ-ዲን አህመድ ቢን አብድልቃድር ቢን ሣሌም ቢን ዑትማን፣ «ፉቱህ አል-ሓበሻ» በተባለው የታሪክ ድርሣኑ የዚያን ዘመን የኢትዮጵያን የሕዝብ አሠፋፈር ቅጥ በዝርዝር መዝግቦት ይገኛል። በእነዚያ ጽሑፎች ውስጥ «ጋላ» ወይም ኦሮሞ የሚባል ነገድ ዛሬ «ኦሮሚያ» ተብሎ በተከለለው አብዛኛው የኢትዮጵያ ግዛት ስለመኖሩ በአንዱም ጭራሽ አልተጠቀሰም። ስለዚህ የዛሬው ዘመን የኦሮሞ ልሂቃን የጥንት አባቶቻቸው በወረራ የያዙትን ግዛት እንደ አፅመ-ርስት ቆጥረውት ሌላውን ኢትዮጵያዊ ሲያፈናቅሉ ሃግ ሊባሉ ይገባቸዋል። ከኦሮሞ ወረራ በፊት ዛሬ ወለጋ፣ አርሲ፣ ወሎ፣ ኢሉባቡር፣ ወረኢሉ፣ ወረሂመኖ፣ ወዘተርፈ በመባል የሚታወቁት የቦታ (የአካባቢ) ስሞች የሚታወቁት እና የሚጠሩት በሌሎች ስሞች ነበር። የሚከተለውን ሠንጠረዥ እንዲሁም አባሪ ካርታዎችን ፩ እና ፪ ልብ እንበል።
ተራ ቁጥር | ነባር ስም | በኦሮሞዎች የተሰጠው ስም | የትኞቹን አካባቢዎች እንደሚገልጽ | በአካባቢው ነዋሪ የነበሩ ነገድና ጎሳዎች |
ቢዛሞ | ቄለም | ምዕራብ ወለጋ | ጋፋት፣ ዐማራ፣ ሽናሻ፣ ቤንሻንጉል፣ አንፊሎ፣ ሌሎች፣ እንዲሁም የጠፉ ነገዶች እና ጎሣዎች | |
ዳሞት | ሌቃ | ምሥራቅ ወለጋ | ጋፋት፣ ዐማራ፣ ሌሎች፣ እንዲሁም የጠፉ ነገዶች እና ጎሣዎች | |
እናርያ | ኢሉ አባቦራ | ኢሉባቦር | ዐማራ፣ ከፊቾ፣ ሌሎች፣ እንዲሁም የጠፉ ነገዶች እና ጎሣዎች | |
ገሙ | ጂማ | ጂማ | የም (ጃንጀሮ)፣ ገሙ፣ ዳውሮ (ኩሎ)፣ ሌሎች፣ እንዲሁም የጠፉ ነገዶች እና ጎሣዎች | |
ገንዝ | ጅባት እና ሜጫ | ምዕራብ ሸዋ | ጋፋት፣ ዐማራ፣ ሌሎች፣ እንዲሁም የጠፉ ነገዶች እና ጎሣዎች | |
ግራርያ | ሰላሌ | ሰሜን ሸዋ | ጋፋት፣ ዐማራ፣ ሌሎች፣ እንዲሁም የጠፉ ነገዶች እና ጎሣዎች | |
እንደጥና | እንጦጦ፣ ጉለሌ፣ የካ | አዲስ አበባ ዙሪያ | ሜያ፣ ዐማራ፣ ሌሎች፣ እንዲሁም የጠፉ ነገዶች እና ጎሣዎች | |
ኦ(ወ)ይጃ | የረር እና ከረዩ | ምሥራቅ ሸዋ | ሜያ፣ ሐዲያ፣ ዐማራ፣ ከምባታ፣ ሲዳማ፣ ሌሎች፣ እንዲሁም የጠፉ ነገዶች እና ጎሣዎች | |
ፈጠጋር | አርሲ | አርሲ | ሐዲያ፣ ከንባታ፣ ሜያ፣ ዐማራ፣ አዳል (አፋር)፣ ሲዳማ፣ ሌሎች፣ እንዲሁም የጠፉ ነገዶች እና ጎሣዎች | |
ደዋሮ | ጭሮ | ምዕራብ ሐረርጌ | ሐዲያ፣ ከምባታ፣ ዐማራ፤ ሌሎች፣ እንዲሁም የጠፉ ነገዶች እና ጎሣዎች | |
ላኮመልዛ | ወሎ | ደቡብ ወሎ | ዐማራ፤ አዳል (አፋር)፣ አገው፣ ሌሎች፣ እንዲሁም የጠፉ ነገዶች እና ጎሣዎች | |
ቤተ-ጊዮርጊስ | ወረኢሉ | ወረኢሉ | ዐማራ | |
ቤተ-ዐማራ | ወረሂመኖ | ወረሂመኖ | ዐማራ | |
አንጎት | ራያ | ሰሜን ወሎ | ዐማራ፣ አገው፣ አዳል (አፋር) | |
ባሊ | ባሌ | ባሌ | ሐዲያ፣ ከንባታ፣ ሜያ፣ ዐማራ፣ ሲዳማ፣ ሌሎች፣ እንዲሁም የጠፉ ነገዶች እና ጎሣዎች |
ስለዚህ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባን «ፊንፊኔ»፣ ናዝሬትን «አዳማ»፣ ደብረዘይትን «ቢሾፍቱ በሉ» እያሉ ለማስገደድ ለሚሞክሩት ዘመነኞች እኛም፥ ወለጋን ቢዛሞ እና ዳሞት፣ ኢሉባቡርን እናርያ፣ ወሎን ላኮመልዛ፣ አርሲን ፈጠጋር፣ ሐረርጌን ደዋሮ፣ ወዘተርፈ ብለን በጥንቱ ስማቸው የምንጠራ መሆናችንን እንዲያውቁት እንሻለን። ወደፊት ካላረፉም በእንግድነት ከኖሩበት አገር «ውጡ» የምንል መሆኑን ሊያውቁት ይገባል። የኦሮሞ ቀለም-ቀመስ ትውልድ ዐማራን በአውራ ጠላትነት ፈርጆ፣ ክንዱን አስተባብሮ ሊያጠፋው ሲነሣ፣ ዐማራው በተቃራኒው እጁን አጣጥፎ ተቀምጦ ይጠብቀናል ብለው ካሠቡ በእጅጉ ተሣስተዋል። በመሆኑም ለማንኛችንም የሚበጀው እኛ ኢትዮጵያውያን በጠቅላላ አንዳችን ለሌላችን ቀና መተሳሰቡ እንጂ፣ ፍጭው ፈንግጭው ከሆነ ዬትም አንደርስም። እንዲያውም ከኖረው መልካም ባህላችን ውስጥ የቀረንን አብሮ እና ተቻችሎ የመኖር መልካም ባህላችንን እንኳን ለማጣት እንገደዳለን። ስለሆነም ከዚህ ተነስተን «ወደፊት እንዴት እንጓዝ?» የሚለውን ጥያቄ አንስቶ በጋራ በሚደረስበት ውሣኔ የተሻለች ኢትዮጵያን በመገንባቱ ላይ ማተኮሩ ዐዋቂነት ብቻ ሣይሆን ብልኅነትም ነው። በየትኛውም መልኩ የትናንት ኢትዮጵያን ካነሣን፣ በዳዩ «ተበደልኩ» ባዩ፣ ወራሪውም «ተወረርኩ» የሚለው የኦሮሞው ልሂቅ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
ሞረሽ ወገኔ በተለይ በአሁኑ ወቅት ራሱን በኢትዮጵያዊነት ጭንብል ውስጥ ሸፋፍኖ፣ ለጥፋቱ ሁሉ የሩቅ ተመልካች ሆኖ ለሚታዘበው የተማረው የዐማራ ተወላጅ የሚያስተላልፈው ግልፅ መልዕክት አለ፦ ወገናችን ከምድረ-ገፅ እየጠፋ ዝምታው እስከመቼ ነው? «ትውልድ ትውልድን ተክቶ ያልፋል፣ ታሪክም ይመዘገባል» ተብሏልና ዛሬ ለወገኖቻችን ካልደረስን ነገ እያንዳንዳችን የትውልድም፣ የታሪክም ተጠያቂ ከመሆን እንደማንድን መካድ አይቻልም። ስለዚህ በወገኖቻችን በዐማራው ነገድ ተወላጆች ላይ በትግሬ-ወያኔ እና በተባባሪዎቻቸው ላይ የሚደርሰው ሠቆቃ ከዚህ በላይ በዝምታ እና በቸልተኝነት ሊተው ከማይችልበት ምዕራፍ ላይ መድረሱን ተገንዝቦ ለወገን ጥሪ ተጨባጭ የተግባር ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል።
ዐማራን ከፈፅሞ ጥፋት እንታደግ!
ፈለገ-አሥራት የትውልዳችን ቃልኪዳን ነው!
ኢትዮጵያ በታማኝ ልጆቿ መስዋዕትነት እና ትግል ለዘለዓለም ፀንታ ትኖራለች!
ካርታ ፩፦ (ምንጭ፦Tellez, Balthazar, (1710). The Travels of the Jesuits in Ethiopia.)
ካርታ ፪፦ (ምንጭ፦ ፕሮፌሠር ጌታቸው ኃይሌ፣ ፲፱፻፺፭ ዓ.ም.። የአባ ባሕርይ ድርሰቶች፤ ኦሮሞችን ከሚመለከቱ ሌሎች ሰነዶች ጋራ። ገፅ ፲፪።)