March 5/2014
የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት በየዓመቱ የሚያወጣውን የሰብአዊ መብት ሪፖርት ዘንድሮም አውጥቷል። ሪፖርቱ የበርካታ ሀገራትን የሰብአዊ መብት አያያዝ በተመለከተ ያሉትን ጠንካራና ደካማ ጎኖች ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች በመሰብሰብ ያወጣል። በሪፖርቱ ከሚካተቱ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነች።
በዘንድሮው የ2013 የአሜሪካ የስቴት ዲፓርትመንት ሪፖርት በሰብአዊ መብት አያያዝ ጉድለቶች ከተተቹ አገራት ኢትዮጵያ አንዷ ናት። የዘንድሮው ሪፖርት በየዓመቱ ኢትዮጵያ ላይ “ጠንከር” ያለ መልዕክት እንዲያዝ የሚገልፁ አሉ። በሌላ ወገን ሪፖርቱ አምና እና ካቻምና የተንከባለሉ ጉዳዮችን ከማንሳቱ በስተቀር አዲስ ነገር እንደሌለው የሚገልፁም አልጠፉም።
በዚህም ተባለ በዚያ በዘንድሮው የስቴት ዲፓርትመንት ሪፖርት ጎልተው ከታዩ ጉዳዮች መካከል ከእምነት ነፃነት ጋር በተያያዘ የተነሱ ተቃውሞዎችና በመንግስት በኩል የተወሰዱ እርምጃዎችን እንዲሁም ከመንደር ማሰባሰብ (Villagation) ጋር በተገናኘ ዜጎች በግዳጅ ከቦታቸው ተነስተው ወደ ሌላ ቦታ እንዲዛወሩ መደረጋቸውን አትቷል።
ሌሎች መሰረታዊ የሰብአዊ መብትና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አለመከበርን በተመለከተ ቀደም ሲል ከሚወጡ ሪፖርቶች እምብዛም የተለየ አይደለም። በሀገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ መሰረታዊ ችግሮች መኖራቸውን በዚህኛውም ሪፖርት ተጠቅሷል። ምንም እንኳ በመንግስት በኩል የሰብአዊ መበት አያያዝን ለመሻሻል የተለያዩ የድርጊት መርሃግብሮች ቀርጾ እንደሚንቀሳቀስ ቢገልፅም፤ የስቴት ዲፓርትመንት ሪፖርት የሀገሪቱ የሰብአዊ መብት አያያዝ ካለፉት ዓመታት አለመሻሉን አመልክቷል።
በሪፖርቱ መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለፍርድ ቤት መያዝ፣ ሕገ-ወጥ የፖሊስ ብርበራ፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ፍርድ አለማግኘትና የእስረኞች አያያዝ ላይ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ዘርዝረዋል። በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ላይ የሚካሄደው ምርመራና የእስር ቤት አያያዝ ላይ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ችግሮች እንዳሉም አስቀምጧል። በፖሊስ ምርመራ ወቅት አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳቶች መኖራቸውንና ኢሰብአዊነት (Inhuman) የሆኑ አያያዞችንም እንዳሉ አስረድቷል።
የማረሚያ ቤቶች ሁኔታንም በተመለከተ እንዳለፉት ዓመታት ሪፖርትቱ “እጅግ አስቸጋሪ (Harsh)” በሚል ቃል ያስቀመጠው ሲሆን፤ ለታራሚዎችም የሚመደበው ዓመታዊ በጀት ከአምናው ያልተሻለ መሆኑንም ይኸው ሪፖርት ጠቁሟል። እንደ 2013 የስቴት ዲፓርትመንት የሰብአዊ መብት ሪፖርት መሠረት በኢትዮጵያ ውስጥ ለአንድ እስረኛ አማካኝ የቀን ወጪ ስምንት ብር (0.42) ዶላር ብቻ መሆኑንም አስረድቷል። በሪፖርቱ መሠረት ይህ ወጪ የታራሚውን የምግብ የውሃ እና የሕክምናን ወጪ የሚያጠቃልል ነው። በሀገሪቱ በፌዴራል መንግስት የሚተዳደሩ ስድስት እና 120 በክልል የሚተዳደሩ ማረሚያ ቤቶች እንዳሉም ሪፖርቱ ጠቁሟል። ማረሚያ ቤቶቹ ግን በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው ሳይጠቅስ አላለፈም። ከምግብ አቅርቦት ጀምሮ ንፁህ ውሃና የመኝታው አገልግሎት ብዙ የሚቀረው እንደሆነም በሪፖርቱ ላይ ተብራርቷል።
የሲቪል መብቶችንም በተመለከተም ልክ እንዳምናውና ካቻምናው ሪፖርት በዘንድሮውም መሻሻል አለመኖሩን ሪፖርቱ አመልክቷል። በሀገሪቱ በቂ የሆነ የሕትመትም ሆነ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ አለመኖሩን፣ ያሉትም ቢሆን ችግር እንደለባቸው ጠቅሷል።
በተለይ ጋዜጠኞች የመንግስትን ጫና በመፍራት አደገኛ ጉዳዮችን (Sensitive Topics) ለመዘገብም ሆነ ለመመርመር እንደሚፈሩ ጠቅሷል። ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘም በጋዜጠኞች ላይ የተለያዩ ጫናዎች መኖራቸውን አስረድቷል።
የኢንተርኔት ነፃነት (Internet Freedom) በተመለከተም አልፎ አልፎ ፌስቡክ የማኅበራዊ ድረገፅን ጨምሮ በቋሚነት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ የተደረጉ ድረገጾች መኖራቸውን ዘርዝሯል። በተጨማሪም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የአካዳሚክ ነፃነት አለመኖሩንና የትምህርት ሚኒስቴር ለገዢው ፓርቲ ደጋፊዎች የፖስት ግራጁዬት ሥልጠና ቅድሚያ እየሰጠ እንደሆነም አመልክቷል።
የመሰብሰብና የመደራጀት መብትም አሁን ሙሉ በሙሉ አለመከበሩን ያተተው የ2013 የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሪፖርት፤ ባለፈው ዓመት ሰላማዊ ሰልፎች አለአግባብ መከልከላቸውን አንዳንዶቹም በግዳጅ ጊዜና ቦታ በመቀያየር መብታቸው መጣሱን አመልክቷል። በዚህ ረገድ የሰማያዊ ፓርቲን ያጋጠመውን ችግር በምሳሌነት አንስቷል።
ሪፖርቱን ካነበቡት ምህሩን መካከል ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርኸ አንዱ ናቸው። ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በመጀመሪያ ደረጃ የኢትዮጵያውያንን ሰብአዊ መብት ለማክበር ከአሜሪካ መንግስት ይልቅ የኢትዮጵያ መንግስት ሊጨነቅበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ እና ጥያቄው ከአሜሪካ መንግሰት መምጣቱ ተገቢ አለመሆኑን ነው ያስረዱት።
በዚህኛው ሪፖርት ከመንደር ምስረታ ጋር በተገናኘ እና ግድብ በሚገነባበትና ሌሎች ሰፋፊ ልማቶች በሚካሄድበት ቦታ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች ሲነሱ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ነው የመከሩት።
ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር በተመለከተም ማንም ሀገር ፍፁም አለመሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በዚህ ረገድ በወረዳ ሹመኞችና በአካባቢ አስተዳደሮች የሚፈፀም የሰብአዊ መብት ጥሰት በቀላሉ መታለፍ የሌለባቸው መሆኑን ሪፖርቱ ያስገነዝበናል ብለዋል።
የመንደር ምስረታና ከሰፋፊ የእርሻ ልማት መካሄድ እንዳለበት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ይስማማሉ። ሀገሪቱ 70 ሚሊዮን ሔክታር የሚታረስ መሬት እያላት ወንዞቿ በአራቱም አቅጣጫ እየፈሰሱ ባለበት ሁኔታ ከእህል ልመና መውጣት አለባት። ነገር ግን እነዚህ ልማቶች ሲካሄዱ ግን የሰዎች መብት መከበር ላይ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ነው የጠቀሱት። ያም ሆኖ “ተጥሷል” የተባለው ሰብአዊ መብት በትክክል ሪፖርት እንዲደረግ ሂዩማን ራይስ ዎች ጨምሮ ለሁሉም የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ወገኖች በሩ ክፍት መሆን አለበት ብለዋል። በዚህ ረገድ መንግስት የሚደብቀው ነገር አለ ብለው እንደማያምኑ ያስረዱት ዶ/ሩ የማይደበቀውን ሁሉ የምንደብቅ ከሆነም አሉታዊ ውጤት ይኖረዋልም ሲሉ አስረድተዋል። በመጨረሻም የአሜሪካ እርዳታ ሲቀር የሚጎዳው እርዳታ የሚመጣለት ሕዝብ ነው። ዝሆኖች ሲጣሉ ሣሩ ይጎዳል እንደሚባለው የኢትዮጵያ መንግሰት ተቃዋሚዎች ጉዳዩን በአግባቡ ቢያጤኑት ጥሩ ነው ብለዋል።
በሪፖርቱ ላይ በኢትዮጵያ ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብትና የመገናኛ ብዙሃን በነፃ መንቀሳቀስ መብት ላይ ችግሮች የሉም ብሎ ማለት እንደማይቻል የሚጠቅሱት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ “መሻሻል ያለበት ገና ብዙ ነገር አለ” ብለዋል በተለይም ከሚታሰሩ ጋዜጠኞች አንፃር የሚነሳው ጉዳይ ችግር ያለበት መሆኑን ነው ያስረዱት። ሚዲያው እራሱን የሚመራበት የሚዲያ ካውንስልና የስነ ምግባር ደንብ ሊኖረው እንደሚገባም ጠቅሰዋል። በደፈናው ጋዜጠኛ ተበደለ የሚለውን ነገር ለማስቀረት ጠቃሚ መሆኑን፣ ሚዲያውም ነፃነቱን ከመንግስት ከመጠበቅ ይልቅ እራሱን በራሱ እንዲያስከብር የሚዲያ ካውንስልና የስነ-ምግባር ደንብ ሊኖረው እንደሚገባ ጠቁመዋል። መንግስታት ሁልጊዜ ለስልጣናቸው ስለሚሰጉ ሚዲያውን የመጫን ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ነው የጠቀሱት።
ይሁን እንጂ ለሀገር የሚጠቅሙትን ሕዝብ የሚያስተምሩና የሚያነቁትን የሲቪል ማኅበረሰቡ ድምፅ የሚሆኑትን መንግስት በተቻለው መጠን በመደገፍ እንዲያድጉ ማድረግ እንዳለበትም የሚጠቅሱት ዶ/ሩ በዚህ ረገድ መንግስት መሄድ ያለበትን ርቀት ያህል እየሄደ አለመሆኑን ነው የጠቀሱት።
የሲቪል ማኅበረሰብን በተመለከተ በመንግሰት በኩል ሕጉን በተመለከተ መነጋገር አይቻልም የሚለውን ጉዳይ ቆም ብሎ ማየቱ እንደማይከፋ፣ በተለይ ዘጠና አስር የሚለው ድንጋጌ በሕፃናት፣ ሴቶች ደህንነት መብቶች ከፖለቲካ ጋር ተያይዞ መሄዱ ስራዎችን እየገታ እንደሆነ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ጠቅሰዋል። መንግስት እራሱ በከፍተኛ እርዳታና ብድር እየኖረ ባለበት የሲቪል ማኅበራትን የመከልከሉ ተጠየቅ (logic) ግልፅ አይደለም ብለዋል። አዋጁ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሲቪል ማኅበረሰብ እንዲያድግ መደገፉ ተገቢም ተመካሪም እንደሆነ የሚጠቅሱት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ነገር ግን ኢትዮጵያዊ የሆነ የሲቪል ማኅበረሰብን ለመፍጠር ትንሽ ጊዜ የሚጠይቅ ነው ብለዋል። በአሁኑ ወቅት ብዙ ስራ ሊሰሩ የሚችሉ በዓመት እስከ 900 ሚሊዮን ዶላር ይዘው በመምጣት በሺህ የሚቆጠር ፕሮጀክት የሚያንቀሳቅሱና በሺህ ለሚቆጠር ሰው የስራ ዕድል ይፈጠር እንደነበርም አስረድተዋል። አሁን ባለው የአዋጅ አሰራርም 30 በ70 የሚለው አሰራርም እንደገና መታየት ያለበት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሪፖርቱን ካነበቡ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች መካከል የአንድነት ለዲሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው አንዱ ናቸው። በአጠቃላይ መልኩ ሪፖርቱ ጥሩ የሚባል ቢሆንም፤ አንዳንድ የሚቀሩት ነገር እንዳለ ግን ሳይገልፁ አላለፉም።
በኢንጂነር ግዛቸው እምነት የሪፖርቱ ደካማ ጎኖች መካከል በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉልና በደቡብ ክልሎች በተለያየ ምክንያት የሚፈናቀሉ ሰዎች ተገደው ይነሳሉ የሚለውን ኀሳብ ከማጉላት ይልቅ ፈቃደኝነት እንዳላቸው ተደርጎ ቀርቧል። በአንፃሩ ከቀዬአቸው ሲነሱ መሰረታዊ አቅርቦት እንዳልተሟላላቸው የሚመስል ነገር አለው ብለዋል። በዚህ ረገድ ከስቴት ዲፓርትመንት ሪፖርት ይልቅ የኦክላንድ ኢንስቲትዩት፣ ሂዩማን ራይትስዎችና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርቶች የተሻሉ መሆናቸውን አስረድተዋል። በእኛ እምነት ዜጎቻችን ለልማትም ሆነ በሌላ ምክንያት ከቀዬአቸው እንዲነሱ ሲደረግ መሰረታዊ የሰብአዊ መብታቸው እየተጣሰ ነው ብለን እናምናለን ሲሉ ገልፀዋል።
ሌላው በኢንተርኔት አፈና ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ከሚደረጉ በርካታ ድረገጾች መካከል የተዘረዘሩት ጥቂቶቹ ከመሆኑም በላይ ከኢንተርኔት አፈና ጋር በተያያዘ በሪፖርቱ የቀረበው እውነታ ሀገሪቱ ያለችበትን ሙሉ ስዕል እንደማያሳይም ኢንጂነር ግዛቸው ተናግረዋል።
በተጨማሪም የአንድነት ፓርቲ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በሚለው የሕዝብ ንቅናቄ ወቅት በተጨባጭ በፍቼ፣ በባሌና በሌሎች አካባቢዎች በአባላቶቻችን ላይ ድብደባና ሰብአዊ መብት ተጥሷል፣ ፓርቲው ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያደርግ መደረጉን በአግባቡ ያዩት አይመስለኝም ብለዋል። የታሳሪዎችንም ጉዳይ ቢጠቅሱትም ከሕግ አኳያ (Legal Perspective) እንዳልታየም አስረድተዋል። በሪፖርቱ ላይ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎች አላግባብ መታሰራቸውን፣ እንዳይጎበኙ መደረጉን እኛም እነሱም ሁልጊዜ የምንለው ነገር ቢሆንም ከሕግ አንፃር አልታየም ብለዋል።
በሌላ በኩል የስቴት ዲፓርትመንት በየዓመቱ ሪፖርት ማውጣቱ መረጃ ከመስጠት አንፃር ጠቀሜታ ቢኖረውም የመጨረሻው ግብ (end result) ግልፅ አይደለም የሚሉት ኢንጂነር ግዛቸው፤ ቢያንስ ከመንግስት ጋር ገንቢ ዲፕሎማሲ በማካሄድ እንኳ አጠቃላይ ሁኔታውን የማስለወጥ ተነሳሽነት እያየን አይደለም ብለዋል።
“የሀገራችንን ሉአላዊነት ጥሰው በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ ይግቡ ባንልም፤ ሪፖርቱን መነሻ አድርገው ቢያንስ የማሻሻያ እይታ ልናይ ይገባል። ባለፉት አምስት ዓመታት ተመሳሳይ ሪፖርቶች እያየን ነው። ተደጋጋሚነት ያላቸው ናቸው። እና ግባቸው ሪፖርት በየዓመቱ መፃፍ ይመስላል። ይሄ ደግሞ ማንንም አይጠቅምም” ሲሉ ኢንጂነሩ ሪፖርቱን በተመለከተ ያላቸውን ቅሬታ ገልፀዋል።
ከሪፖርቱ መውጣት በመቀጠል እንደተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ምን እንዲደረግ እንደሚፈልጉ ኢንጂነር ግዛቸው ተጠይቀው፤ የሚታይ የሚዳሰስ የዲፕሎማሲ ውይይት በመንግስትና በአሜሪካ መንግስት መካከል እንዲደረግ እንፈልጋለን ብለዋል። ሰዎች ያለ ሕግ ሲታሰሩ፣ ከታሰሩም በኋላ በወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዳይጠየቁ ሲደረግ፣ ዜጎች ሰላማዊ ሰልፍ ሲከለከሉ፣ ፕሬሱ ሲዳክም በዚህ ላይ ቢያንስ ጉዳዩ የሚያሳስባቸው ከሆነ የአሜሪካ መንግስትና የኢትዮጵያ መንግስት ሲነጋገሩ ማየት አለብን። ውጤቱንም ማየት አለብን። የአሜሪካ መንግስት ከዚህ መንግሰት ጋር ወዳጅ መንግስት መሆኑን እንረዳለን። ወዳጅነታቸውን በተሻለ ደረጃ ፍሬያማ ለማድረግ እነዚህ ችግሮች ላይ ሲነጋገሩ ማየት እንሻለን። በውጤቱም እኛ በምናካሂደው እንቅስቃሴ መገለፅ አለበት። በየዓመቱ ሪፖርት ማውጣት ግን ፋይዳው ምንድነው (So what?) ብለዋል።
“በእኛ በኩል እርዳታ ይከልከል የሚለው ጉዳይ በጥሞና መታየት እንዳለበት እናምናለን። በተለይ ለሕዝቡ መሠረታዊ አገልግሎት የሚሰጥ እርዳታ ላይ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። በተለይ በጤና አገልግሎት ላይ ጥሩ ስራ እየሰሩ ነው። ግብርናውንም እያገዙ ነው። በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ መንግስት ማኅበራዊ አገልግሎቱንና ኢኮኖሚውን ወደማገዙ እያዘነበለ ነው። በእኔ እምነት በፖለቲካውም ንቁ ተሳታፊ በመሆን የዴሞክራሲ ሂደቱ የሚሻሻልበትን መንገድ መፈለግ አለባቸው። በእኛ እምነት ዴሞክራሲውና የዴሞክራሲ ተቋማቱ ነፃ አልሆኑም። የፖለቲካ ክንፍ ሆነዋል። የሕዝብ ሚዲያውና የምርጫ መዋቅሩ፣ የፍትህ ስርዓቱ ህይወት እንዲኖራቸው ስለምንፈልግ እንዲሻሻሉ የአሜካ መንግስት መርዳትና ግፊት ማድረግ አለበት። በደፈናው እርዳታ ይቁም የሚለው በጥንቃቄ መታሰብ አለበት። ከዚህ ባሻገር ከሕዝቡ መሠረታዊ ፍላጎት ውጪ በሆኑ እርዳታዎች ላይ ቅድመሁኔታዎችን ማስቀመጥ ይችላሉ። በተለይ ለሚሊተሪው፣ ለፖሊስና ለደህንነቱ የሚሰጡ ድጋፎች ቢያንስ የዴሞክራሲ ሂደቱን ሊያግዙ በሚችሉ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ቢመሰረቱ የተሻለ ነው” ሲሉ ኢንጂነር ግዛቸው አብራርተዋል።
“ከዚህ ውጪ የፀረ-ሸብር ሕጉ፣ የፕሬስ ሕጉና የሲቪል ማኅበረሰብ ሕጎቹ በጥቅሉ የዴሞክራሲ ሂደቱን የሚያፍን የፖለቲካ ዓላማን ይዘው የተነሱ በመሆኑ በምትኩ ዴሞክራሲያዊ ስሜት (Democratic Sense) ሊኖራቸው ይገባል። ሕጎቹ ከተቻለ በሀገሪቱ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ መግባት አለባቸው። አዋጆቹ አሁን ባላቸው ዓላማ የዴሞክራሲ መገንቢያ መሳሪያ ሊሆኑ አይችሉም። አዋጆቹ በአመዛኙ የዴሞክራሲ ስርዓት ማፈኛ ናቸው። ስለሆነም አዋጆቹ ወይ መሻሻል አለባቸው አለበለዚያ መሠረዝ አለባቸው” ሲሉ ኢንጂነር ግዛቸው ኀሳባቸውን አጠቃለዋል።
“ሪፖርቱ ከዓመት ዓመት የተለየ ነገር የለውም አላነበብኩትም። ባነበውም ተመሳሳይ ነው” ያሉት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ፤ “ሪፖርቱ ለእንጀራ ሲባል የሚፃፍ ነው። ይሄንን ሪፖርት ካልፃፉ የማይኖሩ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ” በማለት ሪፖርቱን አጣጥለውታል።
አቶ ጌታቸው እንደ አሳሳቢነት የሚያነሱዋቸው የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተመለከተ እኛም የምንጨነቅበት ጉዳይ ነው። ነገር ግን እነሱ የሚያቀርቡት መንገድ አያስማማንም ብለዋል።
“እንደ ችግር የሚያነሱዋቸው ነገሮች የሚያቀርቡበት መንገድ ጥሩ አይደለም። ዴሞክራሲ የራሳችን ጉዳይ ነው። አሜሪካኖች ስለተጨነቁ አይደለም፤ እኛ ስለዴሞክራሲ የምንጨነቀው። ለራሳችን ስለምናስብ ነው የምንጨነቅበት። ስለዚህ የስቴት ዲፓርትመንት ሪፖርት ከስንፍናም ብዛት የሪፖርቱን አመተምህረት የማይቀይሩበት ጊዜ አለ። እና አንድ አይነትና ተደጋጋሚ ነው። አምና ያወጡት ከዘንድሮው ስለማይሻል ባላነበው እንኳ ምን እንደሚል ልነግርህ እችላለሁ” በማለት ሪፖርቱ አዲስ ነገር እንደሌለው ተናግረዋል።
ሪፖርቱን በአግባቡ እንዲጠናቀርና እውነታው ግልፅ እንዲሆን መንግስት ለሪፖርቱ አቅራቢዎች ምን ያህል በሩን ክፍት አድርጓል ለሚለው ጥያቄ አቶ ጌታቸው ሲመለሱ፤ “እኛ የግልፅነት ችግር የለብንም። እነሱ የእውነት ምርመራ ከፈለጉ በእኛ በኩል ችግር የለብንም። ነገር ግን ተመርምሮ የተሰጣቸውንም በአግባቡ አያቀርቡትም። ለምሳሌ ሞተ የሚሉት ሰው በህይወት አለ ተብለው ተነግሮአቸው በግድ ሞተ ነው የሚሉት። የእነሱ ምኞች እንዲሳካ ግለሰቡን መግደል አይኖርብንም።” ሲሉ በሪፖርቱ ጥራት ላይ አቶ ጌታቸው ያላቸውን ቅሬታ ገልፀዋል።
ሪፖርቱ ወጣም፣ አልወጣም ከአሜሪካ መንግስት ጋር ያለን ግንኙነት በጣም መልካም ነው ያሉት አቶ ጌታቸው በተለይም ስትራቴጂካዊ የጥቅም ጉዳዮች ላይ ችግር የለብንም። አሜሪካ ነፃ ሀገር ስለሆነችም የተለያዩ ተቋማት የተለያየ ኀሳብ ቢያንፀባርቁ የሚገርም አይሆንም ብለዋል።
ሦስቱ አወዛጋቢ ሕጎች ማለትም የፀረ-ሽብር ሕጉ፣ የሲቪል ማኅበረሰብና የፕሬስ ሕጉን በተመለከተም አቶ ጌታቸው ሲመለሱ፤ “የሽብር አዋጁ ሽብርተኞችን እንዲያበረታታ፣ የፕሬስ አዋጁም ሁከትን እንዲያነሳሱ የሚፈልጉ ወገኖችን የበጎ አድራጎት አዋጁ የውጪ ድርጅቶችን ለምሳሌ የናሽናል ኢንዳውመንት ፎር ዴሞክራሲ በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ሂደቱ ውስጥ እንዲፈተፍት ካልፈቀደ ሰብአዊ መብት አይከበርም፣ ዴሞክራሲ አያድግምና ፀረ-ሽብር እንቅስቃሴ አይሳካም የሚል እምነት ያላቸው ሰዎች አሉ። በእርግጥም ሕጉን ለማስቀየር የሚጥሩም አሉ። በእኛ እምነት ሕጎቹን መቀየር የሚያስፈልግ ከሆነ በሂደት ከታለመላቸው ዓላማ አንፃር ያመጡት ስኬት ተመዝኖ የኢትዮጵያ መንግስት በራሱ መንገድ (Organic process) መልሶ የሚያያቸው ይሆናል። ከዚህ ውጪ እነዚህ ሕጎች ላይ ዝርዝር ችግሮችን ይዞ ይሄንን ችግር ይፈጥራል ብሎ ይዞ የሚመጣ የለም። ከዚህ ይልቅ መፈክር ነው የሚያሰሙት። መፈክር በተሰማ ቁጥር መፈክሩን ተከትለን የምንነጉድበት ምክንያት የለም” ሲሉ አቶ ጌታቸው መልሰዋል።