September 6, 2013
ስደተኛው ጋዜጠኛ የቋንቋ ትምህርት ቤቱ የደረሰው አምስት ደቂቃ አርፍዶ ነበር። በትምህርት መጀመሪያው ቀን ማርፈዱ እያሳፈረው ያልተያዘ ወንበር ፈልጎ ተቀመጠ። ክፍት ቦታ ያገኘው አንድ ቻይናዊና አንድ ፓኪስታናዊ የተቀመጡበት ጠረጴዛ ዙርያ ነበር። “ዑመር እባላለሁ” አለው ፓኪስታናዊው። “ጄን” ብሎ እጁን ዘረጋለት ቻይናዊው። “ጌቱ” በማለት ተዋወቃቸው ከደቂቃዎች በኋላ ሌላ ፓኪስታናዊ መጥቶ አብሯቸው ተቀመጠ። በእረፍት ሰሃት ዞር ዞር እያለ እያለ ሲመለከት የትምህርት ቤቱ መግቢያ በር አካባቢ አስር የሚሆኑ ከአፍሪካ የመጡ ስደተኛ ተማሪዎች ለብቻቸው ነጠል ብለው ያወራሉ። ሊቀላቀላቸው ስላልፈለገ ነጠል ብሎ ለብቻው ቆሞ በማስታወሻ ደብተሩ ላይ መሞነጫጨር ጀመረ።
ስደተኛው ጋዜጠኛ የቋንቋ ትምህርት ቤቱ የደረሰው አምስት ደቂቃ አርፍዶ ነበር። በትምህርት መጀመሪያው ቀን ማርፈዱ እያሳፈረው ያልተያዘ ወንበር ፈልጎ ተቀመጠ። ክፍት ቦታ ያገኘው አንድ ቻይናዊና አንድ ፓኪስታናዊ የተቀመጡበት ጠረጴዛ ዙርያ ነበር። “ዑመር እባላለሁ” አለው ፓኪስታናዊው። “ጄን” ብሎ እጁን ዘረጋለት ቻይናዊው። “ጌቱ” በማለት ተዋወቃቸው ከደቂቃዎች በኋላ ሌላ ፓኪስታናዊ መጥቶ አብሯቸው ተቀመጠ። በእረፍት ሰሃት ዞር ዞር እያለ እያለ ሲመለከት የትምህርት ቤቱ መግቢያ በር አካባቢ አስር የሚሆኑ ከአፍሪካ የመጡ ስደተኛ ተማሪዎች ለብቻቸው ነጠል ብለው ያወራሉ። ሊቀላቀላቸው ስላልፈለገ ነጠል ብሎ ለብቻው ቆሞ በማስታወሻ ደብተሩ ላይ መሞነጫጨር ጀመረ።
በተከታታይ ቀናት ራቅ ብሎ ለመታዘብ ሞከረ። ለምን እንደሆነ ባይገባውም አፍሪካውያኑ ለብቻቸው ነጠል ብለው ነው የሚሰባሰቡት። አብሯቸው ነጠል ብሎ መሰብሰቡን አልፈለገውም። ራቅ ብለው ወደቆሙት ፓኪስታናውያንና ቻይናዊ የክፍል ጓደኞቹ ሄዶ ተቀላቀላቸው። ሜክሲኳዊ የክፍል ጓደኛቸው ተጨምሮ እየተቀላለዱ መሳቅ ጀመሩ።
መርማሪው ፖሊስ የጋዜጠኛውን ፋይል በትኩረት እያገላበጠ ይመለከታል። “በቋንቋ ትምህርት ቤት እያለ አብዛኞቹ ጓደኞቹ ፓኪስታናውያን ነበሩ። ለምን ፓኪስታናውያንን በጓደኝነት መረጠ!? ለምንስ በፌስቡክ ገፁ ላይ በአገሩ የሚደረገውን የሙስሊሞች እንቅስቃሴ አብዝቶ ይደግፋል? ለምንስ አብዝቶ የአልጃዚራን ዜና ይከታተላል?” የሚለውን እንዳነበበ “መልስ የሚሻ ጥያቄ” ብሎ ቀና አለ።
ጋዜጠኛው፣ ስልክ አናግሮ እንደጨረሰ ወደ መፅሃፍ መደርደሪያው ሄዶ አንድ መፅሃፍ አንስቶ አልጋው ላይ በጀርባው ወደቀ። መፅሃፍ ቢይዝም የሚያስበው ከደቂቃዎች በፊት ደውላ ስላናገረችው ልጅ ነበር። እንዴት አድርጎ እንደሚረዳት አልገባውም። ስልኩን አንስቶ ደወለላት።
“አግኝቼ ላወራሽ እችላለው?” አለ በአካል አይቷት የማያውቃት ሴት ደውላ ችግሯን ከነገረችው በኋላ የሰማው ነገር ሰላም ቢነሳው።
ተገናኙ።
ያስጨነቃት ታሪኳን ትነግረው ጀመር።
በፓልቶክና በስካይፕ ለተዋወቀችው ሰው ሚስጥሯን ሁሉ ነገረችው። አሳየችው። ችግሩ ጠይም ይሁን ቀይ አለማወቋ ነው። የምታውቀው ነገር ኢትዮጵያዊ መሆኑን ብቻ ነው። እሷ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልዳ ያደገች ኢርትራዊት ነች።
ቅዳሜና እሁድ ምሽት የስነፅሁፍ ውይይት የሚደረግበት የፓልቶክ ግሩፕ ውስጥ እንደሚሳተፍና ስነፅሁፍ ስለምትችል በፓልቶክ ቡድኑ ውስጥ ገብተህ ጓደኛ ብታደርገውና ምን አይነት ሰው እንደሆነ ብትነግረኝ ከዛ ውጪ ምንም አልጠይቅህም ብላ ጠየቀችው።
እምቢ አላላትም። “እሞክራለሁ” አላት እንጂ።
በሌላ ቀን ሌላ ጥያቄ ይዛ መጣች። መጀመርያ “ቀይ ይሁን ጠይም ምን አይነት ሰው እንደሆነ ብቻ ንገረኝ” ነበር ያለችው። ቀጥሎ ግን ጥያቄዋ ወደ “አንዴ አግኝተህው አድራሻውን ብታገኝልኝ አበባ ይዤ እቤቱ ሄጄ” ወደ ማለት ተቀየረ። ሊረዳት እንደሚገባው ቢያውቅም የጥያቄዎችዋ ማደግ እያስፈራው መጣ። ግን እንደሚረዳት ቃል ገብቶላታልና የፓልቶክ ቡድኑ ቋሚ ታዳሚ ሆነ።
ኮምፒውተሩ ላይ አፍጥጦ ቀለማትን እየቀያየረ የቢዝነስ ካርድ ዲዛይን ለማስዋብ ይጥራል። ዲዛይኑን የሚሰራው ለአንዲት ኤርትራዊት ነው። የሚሰራላት በነፃ ነው። በነፃ የሚሰራላት ጀማሪ ነጋዴ ስለሆነች ብዙ ወጪ ይበዛባታል ብሎ ስላሰበ ነው። የቢዝነስ ካርድ ዲዛይን እንዲሰራላት የጠየቀችው ለሌላ ኤርትራዊ የሰራውን የሬስቶራንት የምግብ ዝርዝር የያዘ ዲዛይን ተመልክታ ነው። ለነገሩ ከኤርትራዊው የሬስቶራንት ባለቤት ለሰራበት ገንዘብ አልተቀበለውም። ለእሱም “ወጪ በዝቶብሃል” ነበር ያለው ለሬስቶራንት እድሳት ያወጣውን ወጪ ስለሚያውቅ።
መርማሪው ፖሊስ የጋዜጠኛውን ፋይል እያገላበጠ እየተመለከተ እያለ ጉዳዩን እንዲከታተሉ ካዘዛቸው ፖሊሶች አንዱ ያመጣውን መረጃ ደጋግሞ አነበበው። “አሸባሪው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ኤርትራውያንን የሚጠላም ዘረኛ ነው። ጊዜ ሳንወስድ ከኮሚኒቲው እንዲገለል ማድረግ አለብን። ሌሎችን መበከል የለበትም” ነበር የሚለው መረጃው።
መርማሪው መረጃውን በሚያነብበት ሰሃት ጋዜጠኛው የሰራውን የቢዝነስ ካርድ ዲዛይን ለመስጠት ወደ ኤርትራዊቷ ሱቅ እየሄደ ነበር።
ከኤርትራዊትዋ ችግር ጋር የሚመሳሰል ታሪክ ያገኝ እንደሆነ ኢንተርኔት ላይ መረጃ ሲያፈላልግ አንድ መረጃ አገኘና በግርድፉ ተረጎመው በጋዜጣው ላይ ሊያወጣው። የፅሁፉን ርዕስ “ስሜታዊ ዘማዊነት” አለው።
ስሜታዊ ዘማዊነት አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰተው ወይም አለ የሚባለው አንድ ሰው ከሚስቱ ወይም አንዲት ሴት ከባልዋ ውጪ ሌላን ሰው በወሲባዊ ስሜት ከተመኘችውና/ከተመኛትና/ ልታገኘው ካለመች ነው።
አብዛኛውን ጊዜ ስሜታዊ ዘማዊነት የሚጀምረው ደስተኛ ስላልሆኑበት ትዳርዎ ከሌላ ሰው ጋር/የተቃራኒ ፆታ/ ጋር መወያየት፣ መነጋገር ወይም ምክር መጠየቅ ወይም ብሶትዎትን መተንፈስ በጀመሩ ጊዜ ነው።
ከትዳር አጋርዎ ጋር አተካራ ውስጥ ወይም አለመጣጣም ውስጥ በመግባትዎ ምክንያት ብቻ ላለመግባባታችሁ ምክንያት ስለሆኑት ጉዳዮች ከትዳር አጋርዎ ጋር ከመወያየት ይልቅ ስላጋጠመዎት ችግር ለሌላ ሰው መተንፈስ ይፈልጋሉ። አብዛኛውን ጊዜ በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሊያዋሩት ወይም ችግራቸውን ሊያካፍሉት የሚፈልጉት ሰው አብሯቸው የትዳር አጋራቸውን ሊረግምላቸው ወይም እነሱ ልክ እንደሆኑ ሊነግራቸው ለሚችል ሰው ነው። ነገር ግን ይህ ትልቅ ስህተት ነው።
ትዳርዎ እንዳሰቡት ሳይሆን ሲቀር ወይም በሚመኙት መንገድ መጓዝ ሳይችል ሲቀር ሚስጥራዊ የሚስጥር ተጋሪዎችዎን አጥብቀው እየፈለጓቸው ይሄዳሉ፤ ለምን ቢሉ ያለነሱ ውዳሴያዊ ወይም ሽንገላዊ ቃላት ህይወትዎ ባዶ እንደሆነ ይሰማዎታልና ነው። ለትዳርዎ ጤናማ አለመሆን የእርስዎም ስህተት እንዳለበት የሚሞግቶትን ህሊናዎትን አሸንፈው ፀጥ የሚያስብሉት በሚስጥራዊ ወዳጅዎ የከንቱ ውዳሴ ቃላት ነው:: በዚህም ምክንያት በትዳርዎት ውስጥ የሚያጋጥምዎትን እያንዳንዱን ችግር ሁሉ /ሚስጥር መሆን ይገባቸው የነበሩትን ጨምሮ / ይዘው ለውይይት ወደ ሚስጥራዊ ወዳጆችዎ ይሄዳሉ። እንደነዚህ አይነት ወዳጆች ደግሞ ደጋግመው የሚነግሩዎት አንድ ነገር ነው - የትዳር አጋርዎ እርስዎን የመሰለ ሰው በማግኘቱ ምን ያህል የታደለ እንደሆነ:: ከባሰም እነሱ በእሱ ቦታ ቢሆኑ ኖሮ ስለሚያደርጉት ነገር:: በአብዛኛው ጊዜ እርስዎ በትዳርዎ ውስጥ እንዲኖሩ የሚመኙትንና የነገሩዋቸውን ነገሮች ያደርጉ እንደነበር ይደሰኩሩሎታል። ይህን አይነቱን የቃላት ኳኳታ/ዲስኩር/ ደጋግመው በሰሙና ትዳርዎም እንዳሰቡት ባልሄደ ቁጥር አማካሪዎትን ለፍትፈታዊ ጓደኝነት እየተመኙዋቸው ይሄዳሉ::
ባለንበት ዘመን እንዲህ አይነት ስሜታዊ ዘማዊነት ከሚከሰትባቸው ቦታዎች ወይም መንገዶች አንዱ ኢንተርኔት ነው:: በኢንተርኔት ማለትም በፌስቡክ፣ በስካይፕ፣ ወይም በሌላ መንገዶች በሚፈጠር ጓደኝነት በእየዕለቱ የሚያጋጥም ክስተት ነው- ስሜታዊ ዘማዊነት::
በርካታ ሰዎች በኢንተርኔት ‘ቻት ሩሞች’ ስለተለያዩ ጉዳዮቻቸው ቢወያዩም፣ ስለትዳራቸው መላ ቢጠይቁም፣ ከመጠየቅም አልፈው ከሚስጥራዊ ጓደኛቸው ጋር በስሜታዊ ዝሙት ቀልጠው ቢገኙም በጓደኝነታቸው መሃል ስሜታዊ ዘማዊነት መኖሩን አምነው ለመቀበል ይቸገራሉ:: ስሜታዊ ዘማዊነት በ ‘ፎን ወይም ቪዲዮ ሴክስ’ ይገለፃል። ለዚህም ነው በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ያለፉ በስተመጨረሻ ወደ ፀፀትና ጭንቀት የሚያመሩት።
መቼ ነው ስሜታዊ ዘማዊነት አለ የሚባለው!? ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ነጥቦች በእርስዎና በሚስጥራዊ የሚስጥር ተጋሪዎ መካከል ካለ አይጠራጠሩ በስሜታዊ ዘማዊነት አለም ውስጥ እንዳሉ
- ሚስጥራዊ ጓደኛዎትን በማሰብ በወሲባዊ ስሜት የሚቃጠሉ ከሆነ
- ለሚስጥራዊ ወዳጅዎ ልዩ ስጦታዎችን የሚሰጡ ከሆነ/በተለይ በአካል የምትገናኙ ከሆነ/
- የትዳር አጋርዎን ጭራሽ ቸል ያሉ ከሆነ
- የትዳር አጋርዎን ከሚስጥራዊ ጓደኛዎት ጋር ማነፃፀር ከጀመሩና የሚስጥር ጓደኛዎት የሚሻል መስሎ ከተሰማዎት አይጠራጠሩ በስሜታዊ የዝሙት ባህር ውስጥ ለመስመጥ ብቅ ጥልቅ እያሉ ነው::
ታዲያ ከስሜታዊ ዘማዊነት ለማምለጥ መፍትሄው ምንድን ነው!? መልሱ ቀላል ነው:: በትዳርዎ ውስጥ የሚያጋጥሙዎትን እያንዳንዷን ችግር ጊዜ ሳይሰጡ በመነጋገር ለመፍታት ይሞክሩ:: ከትዳር አጋርዎ ጋር የሚያሳልፉት በቂ ጊዜ ይኑርዎት:: የትዳርዎን ገበና በፍፁም ለውጪ ሰው አይንገሩ:: የግድ መንገር ወይም ማዋየት ከፈለጉም በፍፁም ለተቃራኒ ፆታ አይንገሩ ወይም አያማክሩ/ያ ሰው የቤተሰብዎ አባል እስካልሆነ ድረስ/ ከስሜታዊ ዘማዊነት ለማምለጥ:: በተለይ በተለይ ማንነቱን ለማያውቁትና በኢንተርኔት ለተዋወቁት ሰው ገበናዎን በፍፁም አይንገሩ ሳይሆን ጭራሽ አያስቡት!
መርማሪው ፖሊስ በፋይሉ ላይ “ለኤርትራውያን መረጃው በአስቸኳይ መረጃው ሊሰጣቸው ይገባል። ኤርትራውያንን የሚጠላ ዘረኛ አሸባሪ ጋዜጠኛ መሆኑ ሊነገራቸው ይገባል” በማለት ውሳኔውን ፃፈ።
ይቀጥላል