Friday, August 30, 2013

August 30, 2013
ከኢትዮጵያዊ ሙስሊም

እዚህ አሜሪካ ከዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የሚሰራጨው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ራዲዮ ጣቢያ በቅርቡ የሙስሊም ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት ነፃነትና መብትን የማስከበር ሰላማዊ ትግልን ከ‹ፖለቲካዊ እስልምና› ጋር ለማያያዝ የሚቃጣ “የራዲዮ ዝግጅት” አቅርቧል፡፡ ዝግጅቱ ዊኪሊክስ በተሰኘው ድረ‑ገፅ አምና ይፋ የተደረጉ የስቴት ዲፓርትመንት ምሥጢራዊ ሰነዶችንና ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ከተከሰቱ ግጭቶች ጋር የተያያዙ የድምፅ ግብዓቶችን በመጠቀም ወቅታዊውን የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሃይማኖት ነፃነትን የማስከበር ሰላማዊ ትግል ከ‹ፖለቲካዊ እስልምና› ጋር በማያያዝ ጭቃ ለመቀባት፣ ብሎም ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖችን ግንዛቤ ለማዛባት ይሞክራል፡፡
ይህ ጽሑፍ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን እየተነዛና እየተሰበከ ባለው ጥላቻና ግጭትን የመቀስቀስ ዓላማ ያዘለ ፕሮፖጋንዳ አኳያ፣ ወቅታዊውን የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሃይማኖት ነፃነትን የማስከበር ሰላማዊ ትግል በአጭሩ በማስቃኘትና፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥትና አጫፋሪዎቹ እያካሄዱ ያሉትን ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ያለመ ዕኩይ ዘመቻ አደገኛነት በማመላከት ዓላማ የተዘጋጀ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ራዲዮ ያቀረበውን ዝግጅት አሉታዊነት በድፍኑ ከመተቸት ይልቅ፣ በዝግጅቱ ይዘት ላይ ያተኮረ ሰፋ ያለ ሒስ ማቅረብ አስፈላጊ ይመስለናል፡፡ እናም በዚህ ጽሑፍ የራዲዮ ጣቢያው ባቀረበው ዝግጅት ይዘት ጥቂት አንኳር ጉዳዮች ላይ በማተኮር የጣብያውን አሳዛኝና አሳፋሪ ሥራ ለማስቃኘት እንሞክራለን፡፡
ምሥጢራዊ ሰነዶችና ይፋ የመውጣታቸው ፖለቲካዊ አንድምታ
የዳያስፖራው ራዲዮ “በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እስልምና እየተስፋፋ ነው” የሚል ክስ ያቀርባል፡፡ ለዚህ ክሱ ካቀረባቸው ማስረጃዎች መካከል ‹ዊኪሊክስ› የተሰኘው የዊሊያም አሳንጅ ድረ‑ገፅ ይፋ ያደረጋቸውን ከስቴት ዲፓርትመንት ያፈተለኩ ምሥጢራዊ ሰነዶች ይገኙበታል፡፡ እንደ ማስረጃ በተጠቀሱት ‹ዊኪሊክስ› ይፋ ያደረጋቸው ሰነዶች ይዘት ላይ ከማተታችን በፊት ግን፣ የእነዚህ ሰነዶች ከስቴት ዲፓርትመንት ዳታቤዝ ተሠርቆ በ‹ዊኪሊክስ› ድረ‑ገፅ ይፋ የመደረጉን ፖለቲካዊ አንድምታዎች መመልከት ተገቢ ይመስለናል፡፡
እንደሚታወቀው፣ ማንኛውም መንግሥት በ“ጥብቅ ምስጢር”ነት የሚይዛቸው ጉዳዮች ይኖሩታል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰነዶች “ጥብቅ ምስጢር” (CLASSIFIED) በሚል ተፈርጀው በጥንቃቄ ይቀመጣሉ፡፡ በመንግሥት ሥራ ላይ አንድን ጉዳይ “ጥብቅ ምስጢር” የሚያደርጉ ተቀባይነት ያላቸው ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል አንዳንድ ጉዳዮች/ሰነዶች በ“ጥብቅ ምስጢር”ነት የሚይያዙት ይፋ ቢሆኑ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተቃውሞን ሊያስነሱ፣ ጠንካራ ትችትና ውግዘት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ስለሚታወቅ ነው፡፡ በ“ጥብቅ ምስጢር”ነት የሚያዙ ጉዳዮች/ሰነዶች ይፋ መውጣት ብሄራዊ እና/ወይም ዓለምአቀፍ ሕግን መሠረት ያደረገ ተጠያቂነትን ሊያስከትል፣ ወይም ደግሞ እንደ ይዘቱ በአገራት ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥ የሆኑ ኦፊሴላዊ የ“ጥብቅ ምስጢር” ሰነዶች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር ከደረሱ፣ እንደሁኔታው በምሥጢር ሊካሄዱ የታቀዱ መርኃ‑ግብሮችን ሊያሰናክሉም ይችላሉ፡፡
በብዙ አጋጣሚዎች መንግሥታት፣ ይበልጡኑም በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ ያሉ ፖለቲከኞች ዕውን ሊያደርጉ የሚሹትና በአደባባይ ለህዝብ የሚናገሩት ፍፁም ለየቅል ሊሆን ይችላል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ የአንድን መንግሥት ተግባራት እውነተኛ መግፍዔ (Motive) ለማወቅ፣ አልያም የቅርብ ግምት ለመስጠት የሚቻለው በጥልቅ ፖለቲካዊ ትንተና ነው፡፡ … በዓለምአቀፍ የቴሌቪዥን ኔትወርኮች ዘወትር እንደምናየው፣ የአንድን መንግሥት እርምጃዎች፣ ውሳኔዎች ወይ የአቋም ለውጦች ከተለያዩ ማዕዘናት በመዳሰስ በይፋ ያልተነገሩ ብዙ መረጃዎችን የሚሰጡት የፖለቲካ ተንታኞች ናቸው፡፡ ግና ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በ“ጥብቅ ምስጢር”ነት የተያዘ የመንግሥት ሰነድ ድንገት ሾልኮ ቢወጣስ? ይህ ሲሆን፣ የፖለቲካ ተንታኙን የዙርያ‑ገብ ትንተና ድካም በመቀነስ፣ በቀላሉ ወደ እውነተኛው የጉዳዩ ምንነት ያደርሳል፡፡ በ“ጥብቅ ምስጢር”ነት የተያዘ የመንግሥት ሰነድ ይፋ መውጣት እንደ ጉዳዩ የክብደት ደረጃ አንድን መንግሥት በከፍተኛ ኃፍረት አልያም ቅሌት ውስጥ ሊከተውም ይችላል፡፡
በዚህ ማዕቀፍ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ራዲዮ ጣቢያ ባቀረበው ዝግጅት በስፋት ያጣቀሳቸውን በ‹ዊኪሊክስ› ይፋ የተደረጉ የስቴት ዲፓርትመንት “ምስጢራዊ ሰነዶች” በምን መልኩ ለዕኩይ ዓላማ እንደዋሉ ስናይ በጣም እንገረማለን፡፡ … እናዝናለንም፡፡
ዊኪሊክስ” ማንን እና ምንን ነው ያጋለጠው?
በመሠረቱ፣ ዊኪሊክስ ይፋ ያደረጋቸው የስቴት ዲፓርትመንት “ምሥጢራዊ ሰነዶች” በአሁኑ ወቅት ሙስሊም ኢትዮጵያውያን እያካሄዱ ከሚገኙት ሕገ‑መንግሥታዊ የሃይማኖት ነፃነትን የማስከበር ትግል ጋር ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ግንኙነት የላቸውም፡፡ በአንጻሩ ግን “ምሥጢራዊ ሰነዶቹ” የኢሕአዴግ መንግሥት ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሃይማኖት ነፃነት ላይ የከፈተው ግብታዊነት የሚታይበት “የጥሰት ዘመቻ”፣ የአሜሪካ መንግሥት “አሳስቦኛል” ከሚለው አንድ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ሳይኖረው እንዳልቀረ ይጠቁማሉ፡፡ ሰነዶቹ ከምንም በላይ ዛሬ የኢሕአዴግ መንግሥት ከህዝበ‑ሙስሊሙ ጋር የተፋጠጠበት ጉዳይ፣ በኢትዮጵያዊ ዓይን የታየ ሳይሆን፣ በአሜሪካ መንግሥት ዓይን የታየ፣ በአሜሪካዊኛ የተተነተነ፣ በአሜሪካ ልዩ ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ የተቃኘ መሆኑን ነው በግልፅ የሚያሳዩት፡፡ … ይህ ሆኖ ሳለ፣ የዳያስፖራ ራዲዮ ጣቢያ፣ የአሜሪካ መንግሥት በራሱ ምክንያት ምሥጢር አድርጎ ሊይዝ ይፈልገው የነበረውን ይህን ሰነድ በማጣቀስ፣ ወቅታዊውን የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሃይማኖት መብትን የማስከበር ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማጠልሸት ዓላማ አውሎታል፡፡ ይህ በአንድ በኩል በጣም የሚያስቅና የጣቢያውን ብስለት-የለሽነት የሚያሳይ ሲኾን፣ በሌላ በኩል ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የፍትኅና የነፃነት ተሟጋቾች (አክቲቪስቶች) ከአንድ ዓመት በፊት በፌስቡክ ላይ እንደነገሩ ነካክተው ያለፉትን ነገር ዛሬ ጠበቅ አድርገን እንድንመለስበት የጋበዘ በመሆኑ የሚመሰገን ነው፡፡
እስከምናውቀው ድረስ፣ ዊኪሊክስ ይፋ ያደረጋቸው አዲስ አበባ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ ስቴት ዲፓርትመንት የተላለፉ “ምሥጢራዊ ሰነዶች” በቁጥር ሦስት ሲኾኑ፣ ሦስቱም እ.አ.አ በኦገስት 2009 (በኢት. አቆጣጠር በነሐሤ 2001) የተዘጋጁ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰነዶች፣ የኢሕአዴግ መንግሥት በኢት. አቆጣጠር በሐምሌ 2003 በይፋ የጀመረው የአህባሽ አስተምህሮን በህዝበ‑ሙስሊሙ ላይ የመጫን መርኃ‑ግብር፣ ከዚያ ሁለት ዓመታት ቀደም ብሎ የአሜሪካ መንግሥት በዊኪሊክስ ላይ ባንፀባረቀው በጥልቀት ያልተተነተነ ስጋት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ነው ያጋለጡት፡፡ … እነዚህ “ምሥጢራዊ” የነበሩ ሰነዶች በይዘታቸው በአሁኑ ወቅት የኢህአዴግ መንግሥት በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ እያካሄደ የሚገኘው የአገሪቱን ሕገ‑መንግሥት የሚጻረር (የሃይማኖት ነፃነትን የመገደብ) መርኃ‑ግብር በእውነትና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ከመሆን ይልቅ፣ የአሜሪካ መንግሥት ከራሱ ዕይታ ያንፀባረቀው፣ ኢሕአዴግ በጥልቀት ሳያጠናውና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሙስሊም ዜጎቹ (ቢያንስ ከሚያምናቸው ሙስሊም ምሁራን) ጋር ሳይማከርበት ዓይኑን ጨፍኖ በግብታዊነት ሊያስፈጽም የተቀበለው የቤት ሥራ መሆኑን ነው በግልፅ የሚያሳዩት፡፡ ዊኪሊክስ ምሥጢራዊ ሰነዱን ይፋ ባያደርግ ኖሮ፣ የአሜሪካ መንግሥት እ.አ.አ እስከ 2019 (በኢት. አቆጣጠር እስከ ነሐሤ 2011) ድረስ ይህንን ሐቅ በምሥጢር ሊይዘው ነበር የፈለገው፡፡ ምናልባት ሰነዱን ምሥጢር ማድረግ የተፈለገው ተግባሩ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደመግባት ሊቆጠር ይችላል ከሚል ስጋት በመነጨ ሊሆን ይችላል፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራው ራዲዮ “እኛ” በተሰኘ ፕሮግራሙ፣ በዊኪሊክስ ይፋ በመደረጋቸው የአሜሪካ መንግሥትና ኢሕአዴግ የተጋለጡባቸውን እኒህኑ በምሥጢር ተይዘው የነበሩ ሰነዶች ዋቢ በማድረግ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በሃይማኖታዊ ነፃነታቸው ላይ የተቃጣውን ጥሰት በመቃወም የሚያካሂዱትን ሰላማዊ ትግል ሊያጠለሽ ይሟሟታል፡፡ የራዲዮ ጣቢያው ዝግጅት ከአገረ‑አሜሪካ ለሚገኝ ዳረጎት ሲሉ የ“አክራሪነት”ን ነጋሪት እየጎሰሙ ሙስሊሙን ዜጋ ቁም ስቅል የሚያሳዩት ገዢዎቻችን የተጋለጡበትን “የአደባባይ ምሥጢር” እየተረከ፣ በአገሪቱ ሕገ‑መንግሥት ስለተደነገገው የሃይማኖት ነፃነታቸው መከበር የሚጮሁ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን በ‘ፖለቲካዊ እስልምና’ አስፋፊነት በመወንጀል ሊያሸማቅቅ ይሞክራል፡፡ በሌላም በኩል፣ የሙስሊም ኢትዮጵያውያንን ሕጋዊ፣ ፍትኃዊና ሰላማዊ ጥያቄ ደግፈው የቆሙ ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖቻችንን ግንዛቤ ለማዛባትና የሙስሊም ወገኖቻቸውን ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል በጥርጣሬ እንዲመለከቱት ለማድረግ ይተጋል፡፡ በዚህ ብቻ ግን አያበቃም፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት በአገራችን አንድ ክፍል በተከሰተ የማንም አዕምሮ የማይቀበለው ግጭት ላይ የደረሱ ጥፋቶችን፣ ስሜት በሚኮረኩሩ የድምፅ ግብዓቶች አጅቦ በማቅረብ፣ ሙስሊም ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን በሙስሊም ወገኖቻቸው ላይ ጥላቻና ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው የሚገፋፋ መሠሪ ፕሮፖጋንዳ ይነዛል፡፡ እግረ መንገዱንም፣ ወቅታዊውን የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ሰላማዊ የመብት ትግል ስውር ዓላማ ያለው ለማስመሰል ዳር ዳር ይላል፡፡
በቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ያማሞቶ አማካይነት የተዘጋጀውና ዊኪሊክስ ይፋ ያደረገው የመጀመርያው ሰነድ ‹‹GROWING WAHABI INFLUENCE IN ETHIOPIA: AMHARA›› የሚል ርዕስ አለው፡፡ ሰነዱ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የህዝብ ጉዳዮች ክፍል (Public Affairs Section) ኃላፊዎች በአማራ ክልል፣ ደሴ አቅራቢያ በሚገኙ የገጠር ወረዳዎች (እ.አ.አ. ከጁን 3‑5፣ 2010) ባካሄዱት የሦስት ቀናት ቅኝት ላይ ተመሥርቶ የተዘጋጀ ነው፡፡ የኤምባሲው ባልደረቦች ይህን ቅኝት ያካሄዱት ከአንድ የዞን መሥተዳድር ኃላፊ ጋር መሆኑም በሰነዱ ላይ ተጠቁሟል፡፡ …
ሰነዱ በአማራ ክልል ‹ወሃቢያ› የተባለው የእስልምና አስተምህሮት እየተስፋፋ መሆኑን፣ በገጠር ከተሞች በርካታ መስጊዶች ከኩዌት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በተገኘ ፈንድ መታነፃቸውን፣ የኤምባሲው ኃላፊዎች በጎበኟቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሙስሊም ሴቶች ሃይማኖታዊ አለባበስ በመከተል ፊታቸውን እንደሚሸፍኑ፣ ወንዶች ደግሞ ሱሬያቸውን እንደሚያሳጥሩ፣ ፂማቸውን ግን እንደማያሳድጉ ወዘተ. ይጠቃቅሳል፡፡ በተጨማሪም፣ የወሃቢያ አስተምህሮ የነቢዩ ሙሐመድን ልደት (መውሊድ) ማክበርን ስለሚቃወም፣ በዚህ ረገድ በወሃቢ አስተምህሮና በሱፊ አስተምሀሮ ተከታዮች መካከል፣ በተለይ የሱፊ እስልምና ተከታዮች መውሊድን በሚያከብሩበት የጀማ ንጉስ መስጂድ አካባቢ ከዚያ ቀደም ባለ ጊዜ ሁኔታው ወደ ግጭት አምርቶ እንደነበረ ይገልፃል፡፡ አክሎም የሱፊ እስልምና ተከታዮች የመውሊድ በአልን ለሚያከብሩበት የጀማ ንጉስ መስጂድ እድሳት በማድረግ ባህላዊ ቅርሱን ስለመጠበቅ አስፈላጊነት ያወሳል፡፡ ለዚህም አሜሪካ ከአምባሳደሩ የባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ፈንድ ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳላት ይጠቁማል፡፡ [http://wikileaks.org/cable/2009/07/09ADDISABABA1672.html#]
ሰነዱ የኤምባሲው የስራ ኃላፊዎች ለሦስት ቀናት ባካሄዱት ቅኝት፣ ከአካባቢው መስተዳድር የሥራ ኃላፊ እንዲሁም ከወቅቱ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) በተገኘ መረጃ ላይ ተመሥርቶ፣ በኢትዮጵያ የወሃቢ አስተምህሮ መስፋፋት ለዘመናት የቆየው የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች የመቻቻል ዕሴት አደጋ እንደተደቀነበት ይጠቅሳል፡፡ ሰነዱ በገፅ 3 [8.(C)] በዚህ ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ምክር ቤቱን ሲጠቅስ እንዲህ ይላል፡‑
the IASC continues to be very concerned about growing Wahabi influence in Ethiopia. The newly appointed Council is decidedly anti-Wahabi and speaks openly of their concern about Wahabi missionaries and their destabilizing influence in Ethiopia.
ሰነዱ በገፅ 4 (13.(C)) ላይ ደግሞ የመጅሊሱን ኃላፊዎች ዋቢ በማድረግ በወቅቱ (እ.አ.አ. በ2010) መጅሊሱ ከወሃቢ አስተምህሮ ተከታዮች እንደፀዳ ይጠቅሳል፡፡
13. (C) In a shift from past practice, the IASC is now completely purged of Wahabi members. […] the Council members acknowledged that the Council is now all Sufi and in their public statements they repeatedly make reference to Ethiopia’s tradition of religious tolerance and co-existence with the Christian communities.
በተጨማሪም በዚሁ ገፅ ላይ፣ የእስልምና ምክር ቤቱ [የአመራር] አባላት በመንግሥት እንደሚሾሙ በግልፅ ይናገራል፡‑
As the Ethiopian government appoints the members of the Islamic Council, it is clear that the GoE shares this concern about growing Wahabi influence and is supporting moderate Muslim leaders in trying to counter that influence.
እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ቁም ነገር የመላው ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የጋራ ተቋም እንደሆነ በሚታሰበውና ለረዥም ጊዜያት የሱፊና የሰለፊ አስተምህሮ ተከታዮች በጋራ ሲያስተዳድሩት በኖረው መጅሊስ ላይ፣ በዚህ ወቅት (እ.አ.አ. በ2010) መንግሥት ሙሉ በሙሉ የአህባሽ አስተምህሮ ተከታዮችን የሾመ መሆኑ ነው፡፡ የአህባሽ አስተምህሮ፣ ከሰለፊ አስተምህሮ ጋር የከረረ ተቃርኖ እንዳለው የሚታወቅ ሲኾን፣ በሰለፊ አስተምህሮ ተከታዮች ላይም እጅግ የመረረ ጥላቻ ያንፀባርቃል፡፡ ከዚህ በላይ በጠቀስነው የዊኪሊክስ ሰነድ ላይ እንደተመለከተው፣ መንግሥት በጠቅላይ ምክር ቤቱ ላይ የአህባሽ አስምህሮ ተከታዮችን የሾመው ለዘብተኛ ሙስሊሞችን በመደገፍና የወሃቢን ተፅዕኖ ለመቋቋም ነው ተብሏል፡፡ ይህም ‹‹እርምጃው የወሃቢ አስተምህሮ በሃይማኖቶች የመቻቻል እሴት ላይ ደቅኖታል የሚባለውን ስጋት የማስወገድ ዓላማ ያለው ነው›› የሚል አንድምታ አለው፡፡ ነገር ግን እውን ሐቁ ያ ነዉን? የወሃቢ አስተምህሮ ደቅኖታል የተባለውን ስጋት የማስወገጃው መንገድስ ይህ ነውን? ብለን ስንጠይቅና … መሬት ላይ ያለውን ሐቅ ስንፈትሽ የምናገኘው ምላሽ ይህንን አያረጋግጥልንም፡፡ [ለዚህ አባባላችን ዋቢ የሚሆኑ ተግባራዊ ምሳሌዎችን ወደኋላ ላይ እናቀርባለን፡፡]
ዊኪሊክስ ይፋ ባደረጋቸው ሰነዶች ላይ፣ የአሜሪካ መንግሥት የሱፊ ስርዓተ‑አምልኮ የሚከናወንባቸውን ጥንታዊ መስጂዶችና የቅዱሳን የመቃብር ሥፍራዎችን ጠብቆ በማቆየት ዓላማ መሠራት አለባቸው ብሎ የሚያምናቸው ተግባራት ተጠቅሰዋል፡፡ … የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ በተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል ፀንቶ የኖረው የመቻቻል ባህል በዘላቂነት ይቀጥል ዘንድ የራሱን ጥረት ለማድረግ በመሻቱ ሊመሰገን እንጂ ሊወቀስ አይገባውም፡፡ ነገር ግን፣ እንዲህ ዓይነቱ ጥረት፣ የቱንም ያህል ቀና ቢሆን እንኳ፣ ጉዳዩን እጅግ በቅርበትና በጥልቀት መመርመር የሚጠይቅ መሆኑ አይካድም፡፡ ከዚያም በላይ ግን፣ የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን ማኅበረሰብ፣ ከማኅበረሰቡም ተደማጭነት ያላቸውን የእምነቱ መሪዎች ወይም የሃይማኖቱን ሊቃውንት ባላካተተ መልኩ ሲካሄድ የሚፈለገውን አዎንታዊ ውጤት ያመጣል የሚል እምነት የለንም፡፡ በየትኛውም የሃይማኖት ማኅበረሰብ ውስጥ ከእምነት‑ተኮር አስተሳሰብ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ልዩነቶች ሊፈጥሩ የሚችሉትን አላስፈላጊ ፍጥጫና ይህም ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ውጤት በማስቀረት ጥረት ውስጥ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የሃይማኖት ማኅበረሰብ እና ተደማጭ መሪዎቹ ያላቸው ሚና በምንም የሚተካ አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የወሃቢያ መስፋፋትም ሆነ ከሱፊያ አስተሳሰብ ተከታዮች ጋር ያሉ ልዩነቶችንና ከልዩነቶቹ ሊመነጩ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ውጥረቶችን በዘላቂነት ለመፍታትም የጉዳዩ ባለቤቶችን የመፍትኄ አካል በማድረግ ፈንታ የችግር ምንጭ አድርጎ ማሰብ ትክክለኛ ነው ብለን አናምንም፡፡
ወሃቢያ እንደ ስጋት …
ለመሆኑ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ነው የሚለውን የ‹ወሃቢ› አስተምህሮ ከምን አኳያ ነው እንደ ስጋት የተመለከተው? … ይህ ስጋት በመሬት ላይ ያለ ነውን? ካለስ ስጋቱን የማስወገጃው መንገድ ምንድን ነው? … ሙስሊም ኢትዮጵያውያንስ ይህን ስጋት በማስወገድ ረገድ ያላቸው አቋምና አስተሳሰብ ምን ይመስላል? … በተግባርስ ይህን ስጋት ለማስወገድ ምን አድርገዋል? … ‘ዊኪሊክስ’ ይፋ ያደረጋቸውን “ምስጢራዊ ሰነዶች” መነሻ አድርጎ ስለ ‘ፖለቲካዊ እስልምና በኢትዮጵያ’ ሀተታ ያቀረበው የዳያስፖራ ራዲዮ እነዚህን ቁልፍ ጥያቄዎች አልጠየቀም፡፡ ባለመጠየቁም በኢትዮጵያ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ አላየም፡፡ ከዚያ ይልቅ፣ ሰነዱን ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን እያካሄዱ ያሉትን ሃይማኖታዊ ነፃነትን የማስከበር ሰላማዊ ትግል ጥላሸት ለመቀባት ዓላማ አውሎታል፡፡
በእኛ እምነት በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ የሚንፀባረቁ የጽንፈኝነት ዝንባሌዎችን ማረቅ የሚቻለው ትምህርትና እውቀትን በማስፋፋት ብቻ ነው፡፡ በዚህም መንፈስ በኢትዮጵያ ሙስሊም ማኅበረሰብ ውስጥ የአገሪቱ ሙስሊሞች የጋራ ተቋም ከሚሰኘው መጅሊስ ይልቅ የሃይማኖቱ ምሁራን በርካታ አዎንታዊ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ ከአስተምህሮ ልዩነቶች የሚመነጩ ውጥረቶችን ከማስወገድ አኳያም አንዱን ወገን በጽንፈኝነት ፈርጆ የማሳደድን አማራጭ ከሚያራምደው የመንግሥትና የመንግሥታዊው መጅሊስ መንገድ ይልቅ፣ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ አንጋፋ የሃይማኖት ሊቃውንት በጥልቅና በሳል ውይይቶች አማካይነት ኅብረተሰቡን ወደጋራ መግባባት ለማምጣት በርካታ አዎንታዊ ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ2000/2001 የተለያዩ አስተምህሮ የሚከተሉ አንጋፋ የሙስሊም ሊቃውንት፣ በሱፊው በኩል በሸኽ ዑመር ኢድሪስ መሪነት፣ በሰለፊ በኩል ደግሞ በዶ/ር ጀይላን መሪነት፣ ይህን በመሰሉ ጉዳዮች ላይ ተከታታይ የሆኑ በሳል ውይይቶችን በማድረግ ከመግባባት ላይ ደርሰው፣ የአንድነት ጉባዔ ለማካሄድ የመጨረሻ ዝግጅት እያካሄዱ ነበር፡፡ ይህን መሰል ታላቅ አዎንታዊ እርምጃ ከኢትዮጵያ በቀር በሌሎች ሙስሊሞች በሚበዙባቸው አገራት እንኳ መካሄዱ ያጠራጥራል፡፡ ግና ይህ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የተለየ አዎንታዊ ተግባር በህዝብ ባልተመረጠው የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮችም ሆነ በመንግሥት ዘንድ በበጎ ዓይን አልታየም፡፡ እናም መንግሥት እና ምክር ቤቱ ይህንን ሰላምና አንድነትን የማምጣት ዓላማ የነበረውን ሂደት ሆን ብለው አስተጓጉለውታል፡፡ ከቶ ይህ ለአገር እና ለህዝቦች ሰላም የማሰብ ተግባር ነውን? መልሱን ቅን ልቦና ላላቸው ወገኖች ኅሊና ትተነዋል፡፡
በሙስሊሙ ኅብረተሰብ መካከል የሚፈጠሩ የሃይማኖት አስተምህሮን መሠረት ያደረጉ ማናቸውም ችግሮች ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በራሱ ሊፈታቸው የሚገባ፣ የውስጥ ጉዳዮቹ ናቸው፡፡ የጋራ ተቋማችን በምንለው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ላይ በመንግሥት የተሾሙ አመራሮች ይህንን የማድረግ ኃላፊነታቸውን አለመወጣታቸው ሳያንስ፤ ጭራሽ በዚህ መንፈስ ይካሄዱ የነበሩ የሙስሊም ሊቃውንት ውይይቶችን ማሰናከላቸው እየታወቀ፣ የኢሕአዴግ መንግሥትን እና በእርሱ ሹማምንት የሚመራውን መጅሊስ ፀረ‑አክራሪ፣ ህዝበ ሙስሊሙን ግን የፖለቲካዊ እስልምና አስፋፊ አድርጎ ለመሳል የሚደረገው ሙከራ በጣም የሚያሳዝን እና የሚያስተዛዝብ ነው፡፡
ስለ እኛ ማን ይናገር …
ዊኪሊክስ ይፋ ያደረጋቸው የስቴት ዲፓርትመንት የ2010 ሰነዶችን ዋቢ በማድረግ በዳያስፖራ ራዲዮ በ‘ፖለቲካዊ እስልምና’ ዙርያ በቀረበው ዝግጅት ላይ የምናቀርበው ሌላው ዐብይ ሒስ፣ ለኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ስለ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ማንነትና ምንነት ማን ነው የሚነግራቸው በሚል ጥያቄ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በእኛ እምነት ሙስሊም ላልሆኑ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ስለ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ማንነትና ምንነት በሦስተኛ ወገን ሊነገራቸው አይገባም፡፡ መንግሥታችን የገዛ ዜጎቹን፣ ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖቻችንም ለዘመናት አብረናቸው የኖርን ሙስሊም ወገኖቻቸውን በውጭ መንግሥት ዕይታ፣ ግንዛቤ፣ አረዳድና አስተሳሰብ ላይ ተመሥርተው ሊያዩን ይገባል ብለንም በፍፁም አናምንም፡፡ በእኛ እምነት ይህ ለዘመናት አብሮ በመኖር ያጎለበትነውን ተዋድዶ፣ ተፋቅሮና ተከባብሮ የመኖር ታላቅ እሴት ትርጉም‑አልባ የሚያደርግ የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡ …
**********
በኢትዮጵያ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በህዝብ ሀብት የሚንቀሳቀሱትና ሙሉ በሙሉ በኢሕአዴግ ቁጥጥር ሥር ያሉት መገናኛ ብዙኃን፣ እንዲሁም ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት አንስቶ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ያሉ የኢሕአዴግ ካድሬዎች፣ “ወሃቢ!” የሚለውን ስያሜ ህዝብን፣ በተለይም ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖቻችንን የሚያስፈራሩበት ጭራቅ አድርገውታል፡፡ … ከኩዌት መንግሥት በተገኘ የገንዘብ እርዳታ መስጊዶች መገንባታቸው አልያም አሮጌ መስጊዶች መታደሳቸው የወሃቢ እምነት መስፋፋቱን ይገልጻል ብሎ መደምደም የሚቻል አይመስለንም፡፡ በአዲስ አበባ ፒያሳ አቅራቢያ የሚገኘው ኑር (በተለምዶ በኒ) መስጂድ ከኩዌት በጎ አድራጊዎች በተገኘ የገንዘብ እርዳታ ነው ፈርሶ በአዲስ መልክ የተገነባው፡፡ ነገር ግን መስጂዱ የአንድ የተለየ አስተምህሮ ማስፋፊያ አይደለም፡፡
በምሥጢራዊ ሰነዱ ላይ ባህላዊ ወረራ በማስፋፋት የተጠቀሰችው ሳዑዲ አረቢያ፣ ከኢትዮጵያም በላቀ መልኩ ለዩናይትድ ስቴትስ ወዳጅ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ምናልባትም ሰነዱን ምስጢራዊ (Classified) ተብሎ እንዲፈረጅ ካደረጉት ነጥቦች አንዱ፣ “የሳዑዲ ባህላዊ ኢምፔሪያሊዝም” ‘ያሳስበኛል’ የሚለው የአሜሪካ መንግሥት በባህላዊ ኢምፔሪያሊዝም አስፋፊነቷ ከሚያማት አገር ጋር ባለው ወዳጅነት አኳያ ሰነዱ በሚያንፀባርቀው ተቃርኖ ላይ የተመሠረተ ይመስለናል፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላምና ፀጥታ ለምን ያሳስባታል አንልም፡፡ ነገር ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለቀጣናውም ሆነ በይበልጥም ለአገራችንና ለመላው ህዝቧ ሰላም፣ ዕድገትና ብልፅግና ያለን መቆርቆር ከዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የበለጠ እንጂ ያነሰ እንዳልሆነ ማንም ሊዘነጋው አይገባም፡፡ የአገራችን ሰላም፣ ፀጥታና ደኅንነት ቢረጋገጥ፣ ከሌሎች ወገኖቻችን ጋር የእነዚህ ዕሴቶች ትሩፋት በሆነው ዕድገትና ብልፅግና ተጠቃሚዎቹ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችም ነን፡፡ በአንፃሩ፣ የእነዚህ ዕሴቶች መጓደል ከሌሎች ወገኖቻችን ጋር ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችንም ጭምር ነው የሚጎዳው፡፡
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሃይማኖታችን ኢስላም የአገራችንን ሰላም የሚያውክ የየትኛውም የውጭ ኃይል መሣርያ እንዲሆን የምንፈቅድ ዜጎች አይደለንም፡፡ ነገር ግን በተለምዷዊ አሉታዊ ዕይታ፣ ሃይማኖታችን ኢስላምም ሆነ ተከታዮቹ ሙስሊሞች በድፍኑና በጭፍኑ የችግር ምንጮች ተደርገን መታሰብንም አንቀበልም፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከሃይማኖታችን ጋር ተያይዞ ለሚነሳ፣ ወይም ይነሳል ተብሎ ለሚታሰብ ማንኛውም ችግር የመፍትኄ አካል እንጂ የችግር ምንጭ አይደለንም፡፡ እዚህ ላይ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ እ.አ.አ ጁን 4 ቀን 2009 በካይሮ ዩኒቨርሲቲ፣ ግብፅ፣ ተገኝተው ለሙስሊሙ ዓለም ከደረጉት ታሪካዊ ንግግር ላይ መጥቀስ እንወዳለን፡‑ “ኢስላም ነውጠኛ ጽንፈኝነትን ለመዋጋት በሚደረገው ትግል ሰላምን እውን ለማድረግ የሚያግዝ አጋር እንጂ፣ ከቶም የችግሩ አካል አይደለም፡፡”
ፕሬዚደንት ኦባማ በዚሁ የካይሮ ታሪካዊ ንግግራቸው፣ “አንድን ንፁህ ነፍስ የገደለ፣ መላውን የሰው ልጅ እንደገደለ ነው፡፡ አንድን ንፁህ ነፍስ በግፍ ከመገደል ያዳነ መላውን የሰው ልጅ ያዳነ ያህል ነው” የሚለውን ቁርአናዊ ቃል ጠቅሰውታል፡፡ ይህ ቁርአናዊ ቃል ምንጊዜም ህያው ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በዚሁ መድረክ ላይ እንደተናገሩትም፣ “ከአንድ ቢሊዮን የሚበልጡ ተከታዮች ያሉትን ዘመናትን ያስቆጠረ እምነት ከጥቂቶች ጠባብ እና በጥላቻ ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ እጅግ የገዘፈ” የመሆኑ እውነታ ከቶውንም ሊዘነጋ አይገባም፡፡
የዊኪሊክስ ሰነዶች ይፋ ያደረጋቸው አዎንታዊ ነጥቦች
በዊኪሊክስ ላይ ይፋ ከተደረገውና የአሜሪካ መንግሥት፣ በአዲስ አበባው ኤምባሲው አማካይነት ካስተላለፈው መልዕክት ውስጥ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሃይማኖታዊ ትውፊቶችና ቁሳዊ ቅርሶችን ከጥፋት ለመታደግ አስቦ ያከናወናቸው ተግባራት ተጠቅሰዋል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በዚህ የአሜሪካ መንግሥት ተግባር በጣም ደስተኞች ከመሆናችንም በላይ ምስጋናችንም ከፍተኛ ነው፡፡ በእርግጥም፣ ጠንካራ የሃይማኖት ተቋም ቢኖረን ኖሮ፣ ይህ በእኛው ተቋም ሊፈፀም ይገባው የነበረ እጅግ ትልቅ ተግባር ነበር፡፡ እኛ ልንሠራው ይገባን የነበረውን ሥራ የአሜሪካ መንግሥት በራሱ ተነሳሽነት ስላከናወነልን እጅግ ትልቅ ውለታ እንደዋለልን ሳናወሳ አናልፍም፡፡
**************
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በላይኛው የሥልጣን እርከን ላይ ካሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት እስከ ወረዳ ያሉ የኢህአዴግ ካድሬዎች አለአንዳች እፍረት እኛን ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ስለ ሱፊያ እና ሰለፊያ ሊያስተምሩን ይገዳደራሉ፡፡ ካድሬ ጋዜጠኞችና የፌደራል ፖሊስም በመግለጫዎቻቸው፣ “ታላቁ መሪ” የተጠነቀቁትን ያህል እንኳ ሳይጠነቀቁ፣ “የወሃቢያ/ሰለፊያ ምንደኞች” እያሉ በአደባባይ አፋቸውን ይከፍቱብናል፡፡ ከቶውኑ እነዚህ ስያሜዎች ዊኪሊክስ ይፋ ካደረጋቸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምሥጢራዊ ሰነዶች የተለቃቀሙ አይደሉምን?! ለመጀመርያ ጊዜ ከሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አንደበት የተሰሙት “ነባሩ” እና “አዲሱ እስልምና” የሚሉ ስያሜዎችስ ከወዴት ተቃረሙና ነው እኛን ለመወንጀል ዊኪሊክስ የሚጠቀሰው?! … እኛማ ዊኪሊክስን እናመሰግነዋለን! ምክንያቱም፣ የተመሰገነው ዊሊያም አሳንጅ የኢሕአዴግ መንግሥትን በሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በመግባት፣ በህዝብ‑ሙስሊሙ ተቋም ላይ ሹማምንቱን እንደሚያስቀምጥ ነውና ያጋለጠልን! …
የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት “የሳዑዲ ባህላዊ ወረራ” ሲል የጠራውን ይህን መሰሉን ተግባር ለመቀናቀን የወሰደው ለኢስላማዊ ቅርሶችና ታሪካዊ እሴቶች ጥበቃ እገዛ የማድረግ ባህላዊ መርኃ‑ግብር የሚደገፍ ቢሆንም፣ የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን ህዝበ‑ሙስሊም ባሳተፈ መልኩ የተካሄደ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ኤምባሲው በህዝብ ካልተመረጠው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራር ጋር በመተባበር ያከናወናቸው የቅርስ ጥበቃና ተሃድሶ ተግባራት ብዙዎችን ከጀርባው ሌላ ዕኩይ ዓላማ ያዘለ ሳይሆን አይቀርም ወደሚል ጥርጣሬ ገፍቷቸዋል፡፡
የኢሕአዴግ መንግሥት፣ የቴልአቪቭ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሐጋይ ኤርሊች፣ ከሌላ አንድ ምሁር ጋር በጣምራ የሠሩትን ጥናት፣ እንዲሁም ምናልባት የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ዶ/ር ዴቪድ ሺን በተለያዩ አጋጣሚዎች የሰጧቸውን የግል አስተያየቶች ዋቢ በማድረግ ይመስላል፣ አለ ብሎ የሚያስበውን የወሃቢያ አክራሪነት ለመቋቋም የአህባሽ አስተምህሮን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣትን እንደመፍትኄ አድርጎ ወስዶታል፡፡ መንግሥት ከወሃቢያ አስተምህሮ ሊመነጭ ይችላል ብሎ የሚያስበውን የ“አክራሪነት” ስጋት ለመቋቋም፣ ከላይ በተጠቀሱት ምሁራን “ለዘብተኛ” ተብሎ የተሞካሸውን ሊባኖስ‑ወለድ አስተምህሮ በህዝበ‑ሙስሊሙ ላይ ለመጫን የህዝበ‑ሙስሊሙን የጋራ ሃይማኖታዊ ተቋም (መጅሊስን) መሣሪያ ለማድረግ በመሻት በተቋሙ ላይ የአህባሽ አስተምህሮ ተከታዮችን ሾሟል፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ፣ በ2003 መገባደጃ ላይ የኢሕአዴግ መንግሥት “አክራሪነትን መዋጋት” በሚል ምክንያት፣ በዋነኛነትም የወሃቢያ አስተምህሮን ዒላማ በማድረግ የወሰዳቸው እርምጃዎችና፣ ይበልጡንም በህዝበ‑ሙስሊሙ ላይ የአህባሽን አስተምህሮ ለመጫን የተደረገው ሙከራ ከላይ የተጠቀሰውን ጥርጣሬ በማጠናከር እነሆ ሁለት ዓመታት ሊደፍን ለተቃረበው የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የተቃውሞ እንቅስቃሴ መነሻ ሆኗል፡፡ መንግሥት ይህን ድርጊት በመፈፀም ከጣሰው ሕገ‑መንግሥት ባሻገር የህዝበ‑ሙስሊሙን የጋራ ተቋም ለአንድ እንግዳ አስተምህሮ ተከታዮች አሳልፎ በመስጠት የወሰደው እርምጃ በአገራችን በአስተምህሮ ላይ የተመሠረተ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ውጥረት ከመፍጠር በቀር ምንም ያመጣው አዎንታዊ ውጤት የለም፡፡ …
ላለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አጥብቀው እየተቃወሙ ያሉት እነዚህን የተሳሳቱ የችግር አፈታት መንገዶች ነው፡፡ የእኛ ሁኖ ሳለ የእኛ ያልሆነው የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ይህን የተሳሳተ የችግር አፈታት ከማረም ይልቅ፣ የተሳሳተው አካሄድ ዋነኛ ተዋናይ በመሆኑ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የተቃውሞ እንቅስቃሴ በዋነኝነት ይህን ተቋም እውነተኛ የህዝበ ሙስሊሙ ተቋም በማድረግ ላይ ለማተኮር ተገዷል፡፡ በኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ዓመታት እየተካሄደ በሚገኘው የህዝበ‑ሙስሊሙ ሰላማዊ ትግል የተነሱት ቁልፍ ጥያቄዎች በግልፅ የሚያመለክቱትም ይህንኑ ሐቅ ነው፡፡ ሰላማዊ ትግሉ በጠራ ግንዛቤና ግብ ላይ የተመሠረተ፣ በመላው ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚካሄድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ በአገራችን ሕገ‑መንግሥት በሠፈሩት የሃይማኖት ነፃነት ድንጋጌዎች ላይ እየተቃጡ ያሉ የመንግሥት ጥሰቶች እንዲቆሙ በግልፅ የሚጠይቅ እንጂ፣ ከቶውንም በሌላ እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ ዕኩይ ነገር ያለመና የተለመ አይደለም፡፡ ነገር ግን፣ ይህንን ህዝባዊ፣ ሕጋዊ እና ፍትኃዊ ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ብልህነት መሆኑን ያልተረዳው የኢሕአዴግ መንግሥት፣ የህዝበ‑ሙስሊሙን ጥያቄዎች ላለመመለስ በወሰደው፣ በእኛ እምነት ፍፁም የተሳሳተ ፖለቲካዊ ውሳኔ ምክንያት፣ የፕሮፖጋንዳ አውታሮችን በመጠቀም ጉዳዩን ወዳልተፈለገ እና አደገኛ ወደሆነ አቅጣጫ እየለጠጠው ይገኛል፡፡ ከእነዚህ አደገኛ አካሄዶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው በአገራችን ለረዥም ዘመናት በሰላምና በፍቅር አብሮ የመኖር እሴትን ባጎለበቱት የእስልምና እና የክርስትና ተከታይ ህዝቦች መካከል የእርስ በርስ ጥርጣሬና ግጭትን የመፍጠር ዕኩይ ስትራቴጂው ተጠቃሽ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ዲያስፖራ የራዲዮ ጣቢያዎች ዊኪሊክስን ዋቢ በማድረግ የቀረቡት ዝግጅቶች ይህንን ዕኩይ ዓላማ ከመመገብ ውጪ ለኢትዮጵያ ህዝቦች በሰላም እና በፍቅር መኖር የሚያበረክቱት አንዳችም አዎንታዊ አስተዋጽዖ ይኖራል ብለን አናምንም፡፡ በሰነዶቹ ላይ የተጠቀሱትን የአሜሪካ መንግሥት ፖለቲካዊ ምሥጢራት ልክ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ከክርስትያን ወገኖቻቸው የደበቁት ምሥጢር አስመስሎ ለማቅረብ መሞከር እጅግ በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ ከዚህ በላቀ የሚያሳዝነው ግን በዚሁ የራዲዮ ዝግጅት ጥቅም ላይ የዋሉት ምንጫቸው የማይታወቅ የድምፅ ግብዓቶች ናቸው፡፡ ከዓመታት በፊት በውሱን አካባቢዎች ከተከሰቱ ግጭቶች ውስጥ ስሜት ኮርኳሪ ድምፆችን እንደ በግብዓትነት ተጠቅሞ የሰዎችን ስሜት መኮርኮርም፣ ለአገር ሰላም ተቆርቋሪነትን ያሳያል ብለን አናምንም፡፡
ውድ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ራዲዮ “ጋዜጠኞች” እና የኢሕአዴግ የፕሮፖጋንዳ ድረ‑ገፆች ሆይ! ስለምን ተወናብዳችሁ የኢትዮጵያ ህዝብን ለማወናበድ ትሟሟታላችሁ?! እውን ተወናብዶ ህዝብን በማወናበድ አገር ይቀናል ብላችሁ ታስባላችሁን?! … እውነት እንላችኋለን፣ የምትጓዙበት መንገድ ደግ አይደለም፡፡ ግዴላችሁም አድምጡን፣ … እንደምናየው ደግ ነገርን አላለማችሁም፡፡ … ከመጎራበትም በላይ አንድ ግርግዳ ተጋርተው ለአያሌ ዓመታት በሰላምና በፍቅር በኖሩ ህዝቦች መካከል የጥላቻና የቁርሾ እሳትን ለመጫር የምትተጉት ከቶ ለዚህች አገር ምን ብትመኙላት እንደሆነ ሊገባን አልቻለም፡፡… እመኑን፣ ፍፁም በተሳሳተ መንገድ ላይ እየሄዳችሁ ነው፡፡ ግዴላችሁም ይህንን የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ግሣፄ ከልቦናችሁ ሁናችሁ አድምጡት፡፡ … ወደ አቅላችሁ ብትመለሱ መልካም ነው፡፡ … ወደ አቅላችሁ ተመለሱና እንደማመጥ፡፡ … በሰላም መብታችንን በጠየቅን እየደረሰብን ያለው መገፋት ፈጽሞ ለርካሽ ፕሮፖጋንዳ ተንበርክከን የያዝነውን ሐቅ እንድንለቅ አያደርገንም፡፡ ይህንን ብታውቁት መልካም ነው፡፡ … ከእኛ ይልቅ እናንተ ፅንፍ ሄዳችኋል፡፡ … ግዴለም ዓይኖቻችሁን ክፈቱ፡፡
መልዕክታችንን ከፕሬዚደንት ኦባማ የካይሮ ንግግር በመጥቀስ እንደምድመው፡‑
“የግንኙነታችን ውል በልዩነቶቻችን ላይ እስከተመሠረተ ድረስ፣ ከሰላም ይልቅ ጥላቻን ለሚዘሩት፣ እንዲሁም መላ ሕዝቦቻችን ፍትኅና ብልጽግናን ያገኙ ዘንድ አስፈላጊ የሆነውን የትብብር መንፈስ ከማጎልበት ይልቅ የግጭትን ጎዳና መጥረግ ለሚሹት (ጽንፈኞች) ሁነኛ አቅም እንፈጥርላቸዋለን (የልብ ልብ እንሰጣቸዋለን)፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የጥርጣሬና የቅራኔ ዑደት ማብቃት አለበት፡፡”

Thursday, August 29, 2013

ወታደራዊ ትጥቅማ ምረቻ ፋብሪካ በቃጠሎ ጉዳት ደረሰበት

ሃሴ ፳፫(ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

 ኢሳት ዜና :- ዛሬ በተነሳ የእሳት አደጋ ቃጠሎ በመከላከያ ሚኒስትር የትጥቅና ወታደራዊ ልብስ ስፌት ፋብሪካ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የአይን እማኞች ለኢሳት አስታወቁ፡፡
ከአዳማ ከተማ ወደ ወንጂ በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኘው ወታደራዊ የልብስ ስፌት ፋብሪካ ላይ በደረሰው የእሳት አደጋ በፋብሪካው ላይ ከፍተኛ የንብረት ጉዳት መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በ18 ሚሊዮን ብር ወጪ በቅርቡ የተገነባው ፋብሪካው የተለያዩ ወታደራዊ ዩኒፎርሞችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ ሲሆን የደረሰው አደጋ መንስኤ ሊታወቅ አልቻለም፡፡
በፋብሪካው ላይ የደረሰውን ቃጠሎ ለማጥፋት ከአዳማ ከተማ የእሳት ማጥፊያ ባለመኖሩ ደብረ ዘይት ከሚገኘው አየር ሀይል እሳት ማጥፊያ እስከሚደርስ ድረስ የተነሳውን እሳት ማጥፋት አለመቻሉን የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
ለአንድ ሰዓት ያህል በቆየው የእሳት አደጋ ግምታቸው ከፍተኛ የሆነ ማሽኖች ላይ ጉዳት እንደደረሰ የታወቀ ሲሆን ከአራት ቀናት በፊት መንግስት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የገዛቸው ማሽኖች በፋብሪካው ገብተው እንደነበረ ታውቋል፡፡

ፓሊስ የሰማያዊ ፓርቲ አመራርን ነገ ሊያነጋግር ነው

ነሃሴ ፳፫(ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰማያዊ ፓርቲ የፊታችን እሁድ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ፓሊስ የፓርቲውን አመራሮች በመጥራት ለነገ ሊያነጋግራቸው ቀጠሮ መያዙን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ፡፡
ፓርቲው በበኩሉ ሊካሄድ የታቀደውን የተቃውሞ ሰልፍ በምንም አስገዳጅ ሁኔታ ሊሰርዝ እንደማይችል በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የፓርቲው አመራሮች ተናግረዋል፡፡
ምንጮች ለኢሳት እንደገለጹት ከሆነ የአዲስ አበባ ፖሊስ ነገ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ የሰማያዊ ፓርቲ ፀሐፊን፣ ሊቀመንበሩንና የሰልፍ አስተባባሪዎችን ለማነጋገር ጥሪ እንዳቀረበላቸው ታውቋል፡፡
በፀጥታ ዙሪያ ልናነጋግራችሁ እንፈልጋለን የሚለው የፖሊስ መጥሪያ ፓርቲው የእሁዱን ስብሰባ እንዲሰርዝ ለማግባባት ያለመ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ፓርቲያቸው የእሁዱን ስብሰባ ለማካሄድ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ እንደሆነ ተናግረው፤ ምንም አስገዳጅ ሁኔታ ከያዙት አቋም እንደማያስቆማቸው ለኢሳት ተናግረዋል፡፡
በታሪክ፣ በሞራልም ሆነ በህግ ተጠያቂ የሚያስደርገን ነገር ስለሌለ ሰላማዊ ሰልፉ የማይቀር መሆኑን የፓርቲው አመራር ተናግረዋል፡፡
በትላንትናው እለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና የስብሰባ ማህበራት ፍቃድ ጽ/ቤት የፓርቲውን ሰልፍ ህገወጥ ነው ማለቱን አስመልክቶ የተጠየቁት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ‹ሕጋዊ ወይም ህገ ወጥ› የሚባል ሰልፍ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡
የፓርቲው የሰልፍ አስተባባሪ ዝግጅት ክፍል ለእሁድ ሰልፍ የሚያደርገው ዝግጅት ከገዥው ፓርቲ የተለያየ ወከባ እየደረሰበት እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
መብራት በተደጋጋሚ የመጥፋት ተግባርና በመኪና ቅስቀሳ ለማድረግ የተደረገ እንቅስቃሴ በፀጥታ ሀይሎች ጫና እየተደረገበት እንደሆነ ፓርቲው አስታውቋል፡፡
የኢህአዴግ አባላት ቤት ለቤት በመሄድ ህዝቡ ለእሁድ የሀይማኖቶች ጉባኤ ሰልፍ እንዲወጣ ቅስቀሳ ማድረግ ላይ እንደሚገኙ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
መንግስት እያስተባበረ የሚገኘው የሀይማኖቶች ጉባኤ ሰልፍ ህዝቡ አክራሪነትን እና ጽንፈኝነትን ለማውገዝ በሚል የተጠራ ቢሆንም እየተካሄደ ያለውን የሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ሌላ አቅጣጫ ለማስያዝ ያለመ እንደሆነ የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
ሁለት ቀን ብቻ የቀረው የእሁዱ የመንግስትና የሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ በሀገሪቱ የፖለቲካ አካሄድ ከብዙ ዓመታት በኋላ ያጋጠመ ክስተት ተደርጎ ታይቷል፡

Hailemariam warns opposition again

ESAT News  August 28, 2013
 Prime Minister Hailemariam Dessalegn has once again warned Ethiopian opposition parties during a speech he made in the government organised conference under the  theme of the promotion of religious culture of tolerance, respect of the constitution and coexistence opened on Tuesday at the African Union Conference Hall in Addis Ababa.
Hailemariam said “if some opposition do not stop supporting the activities of some extremists and terrorists, the government will take measures according to the constitution”.
He warned that his government will take measures on all that make anti peace activities and crushing the activities of“forces of destruction” will also continue.
Addressing the Conference, the new Patriarch of the EthiopianOrthodoxTewahedoChurch, Abune Mathias, said that all anti-peace activities need to be condemned. President of the Ethiopian Islamic Affairs Supreme Council, Sheik Kiyar Mohamed, has on his part said the culture of tolerance has to be passed down to generations.
ESAT’s reporter said that the speech of the Prime Minister revealed the government has not regretted its violent actions on Muslim protesters and is even ready to take more forceful actions. He also said that the option of talking to the imprisoned leaders of the “Let our Voice be Heard” Movement or settling it peacefully has not been raised during the Conference.
ESAT’s reporter also said the aim of the conference is to gain support from both religious leaders for the violent actions it took and will take.
Various other government officials and guests spoke during the event.

“በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” እንዳይሆን እንጠንቀቅ

ቢከፍቱት ተልባ የሆነውና ላይ ላዩን ሲያዩት ልማት የሚመስለው የወያኔ ኢኮኖሚ “ልማትና እድገት” የገንዘብ ካፒታል የሚያገኘው እንደሌሎቹ በእድት እንደሚገሰግሱ ታዳጊ አገሮች የእንዱስትሪ ሸቀጥ አምርቶ ለአለም ገቢያ አቅርቦና ሽጦ አይደለም። ተሰራ የተባለው ብልጭልጭ ነገር ሁሉ የሚሰራው የድህነት ጌቶች “Lords of Poverty” በሆኑት አለም አቀፍ ተቋሞችና ሀገሮች በሚገኝ እርዳታ ነው። ወያኔ እራሱ በፈጠሩ ችግር ተሰዶ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊም ለወዳጅ ዘመድ የሚልከው የውጭ ምንዛሬም ሌላው የወያኔ የገንዘብ ምንጭ ነው። በዚህ ላይ የሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብት የሆነውን ለም መሬት በገፍ ለባዕድና ለሀገር ውስጥ የወያኔ ቤተኞች በመቸብቸብ የሚገኝ ገንዘብ አለ። መቼም ኢትዮጵያዊው በገዛ ሀገሩ የኩርማን መሬት ባለርስትና መብቱ ከተነጠቀ ቆይቷል። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ባለርሰተቹ ወያኔና ጉጅሌዎቹ ብቻ ናቸው።
የሀገሪቱ የገንዘብ ሀብት ብዙ ጊዜ የሚገባው ከግርጌው በተቀደደ ቋት ውስጥ ስለሆነ ለዘላቂ ልማትም ሆነ ገንዘቡን ለሚቀራመቱት ወያኔዎች በቂ አልሆነም።
ይህንን ቀዳዳ ቋት ለመሙላት ወያኔ ሰሞኑን የፈጠረው ዘዴ ህዝቡን የቤት ባለቤት ላደርግህ ስላሰብኩ አስቀድመህ ገንዘብህን አምጣ የሚል ዘዴ ነው። ሃያ-ሰማኒያ አርባ-ስልሳ ወዘተ የሚል ዘዴ ተገኝቷል። ይህ አርባ ስልሳና ሃያ ሰማንያ የሚሉት ፈሊጥ የኢትኦጵያ ደሃ ህዝብ ነገ ያልፍልኛል እያለ ሆዱን ቋጥሮና አንጀቱን አስሮ ያፈራትን ገንዘብ እንዲሰጣቸው የታለመ የጮሌዎች የገንዘብ መሰብሰቢያ ዘዴ ነዉ።
በተለይ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል ተብሎ የታመነበት 40/60 የሚባል ዘዴ በየኢምባሲው በወረቀት ላይ በተሰሩ ቆንጆ የቤትና የኮንዶሚኒየም ንድፎች አሸብርቆ መጥቷል።
ይህችን የጭልፊት ኢኮኖሚ ማየት የተሳናቸው የዋህ ኢትዮጵያውያን በየባዕድ ሀገሩ ለፍተው ያፈሯትን ጥሪት ይዘው በየኢምባሲው ለምዝገባ ሲጋፉ ማየት እጅግ በጣም ያሳዝናል። ብዙ ኢትዮጵያውያን ይህንን የዝርፊያ ኢኮኖሚ የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ በሚል ፈሊጥም የገቡበት አሉ። ራሳቸውንም ሀገራቸውንም እያዘረፉ መሆኑ የገባቸው አይመስልም። ወያኔ ይልቁንም የገቢያው መድራት ስላስጎመጀው ለውጭ ነዋሪ ያዘጋጀውን 40/60 አቁሞ የተሻለ ጥቅም የሚያስገኝ መንገድ እያሰላ ነው።
ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ይህን የድቡሽት ላይ ቤት እንሰራለን ብለው ያሰቡ ወገኖች ሁሉ የወያኔን ቀዳዳ ኪስ ከመሙላታቸው በፊት ጥቅሙን፤ ጉዳቱንና ትርጉሙን አገላብጠው እንዲያዩ ይመክራል። በተለይ በወያኔ ስር በሚገኝ ንብረት ያልፍልኛል ብለው በስደት ኑሮ ያፈሩትን ገንዘብ የነጻነታቸዉ መያዣ ተደርጎ ለባሰ ውርደት እንዳይዳርጋቸው ግንቦት ሰባት ወገናዊ ምክሩን ይመክራል።
ቤት አልባ ሆኖ በየመንገዱ ላይና በየደሳሳ ጎጆዉ ታጉሮ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ወገናችን በየዕለቱ እየጨመረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ከነሱ እየተዘረፈ በሚሸጥ ንብረት ሀብት ለማፍራት መሞከር ለህሊናም የሚቀፍ ነው።
የወያኔ የቤት ስራ ፕሮጀክት ገንዘብ መልቀሚያና ጥቂት ባለሟሎቻቸውን መጥቀሚያ እንጂ ለዚህ ሁሉ የውጭ ነዋሪ የሚደርስም አይደለም። ወያኔ አስቀድሞ ከወለድ ነጻ የሆነ ገንዘብ ከሰበሰበ በኋላ ገንዘቡን ተጠቅሞ ከአምስትና አስር አመት በኋላ ቤቱንም ገንዘቡንም ማግኘት ላይቻል ይቻላል። ወያኔም ተጠያቂነትን የማይወድ አገዛዝ መሆኑን ካሁኑ አለመገንዘብም ራስን ጨፍኖ ለመሞኘት መፍቀድ ነው።
የወያኔ 40/60 ገንዘብ መሰብሰቢያ እንጂ ህዝብ መጥቀሚያ አይደለም። ወያኔዎች ሊጠቅሟቸው የሚፈልጉ ዜጎችን ከፈለጉ በየጎዳናው ላይ ያገኟቸዋል ለምን እነሱን አየረዷቸዉም?
በተለይ በውጪ የምንኖር ኢትዮጵያውያን በፍጹም ድህነትና የወያኔ ዝርፊያ ተዋርዶ የሚኖረውን ህዝባችንን እያየን የዚህ ግፈኛ መንግስት መሳሪያ ከመሆን አልፈን ራሳችንንም ለተዋራጅነት እንዳንዳረግ እንጠንቀቅ!
ድል ለኢትዮጵያ ሀዝብ!!

በብሔርተኝነት ስም ታሪክንና የኢትዮጵዊነትን መንፈስ ማጣጣል ተቀባይነት የለውም

August 29, 2013
በፍቅር ለይኩን

በአንድ ወቅት በደቡብ አፍሪካዊቷ ከተማ በኬፕታውን የሚኖር አንድ በንግድ ሥራ የሚተዳደር  ኢትዮጵያዊ ጎልማሳ አንድ አሳዛኝ ገጠመኙን እንዲህ አጫውቶኝ ነበር፡፡ ይህን ታሪኩን ያካፈለኝ ኢትዮጵያዊ ጎልማሳ የሥራ ቦታው ላይ ከአንድ ከኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ጋር በተነሳ ጠብ በተፈጠረ ግጭት የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የሆነው ጓደኛውን አንድ የፊቱን ጥርሱን በቦክስ ያወልቀዋል፡፡ የጥርሱን መውለቅ የሰሙ የዚህ ሰው ጓደኞችም ተሰባስበው ይህን ሰው ካልገደልን በማለት ሲጋበዙ ነገሩ በሰላም ያልቅ ዘንድ አንዳንድ የሚያውቋቸው ሰዎች ለሽምግልና ጣልቃ ይገባሉ፡፡

በሽምግልና ድርድር ላይ እያሉም የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የሆነው ጓደኛውን ጥርስ ያወለቀው ሰው የአያቱ ስም የኦሮሞ ስም ሆኖ ይገኛል፡፡ እነዛም በእንዴት ተደፍረን፣ ይህን ሰው ካልገደልን በማለት ሲዝቱ የነበሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችም፣ ይኽ ሰው ለካ ወገናችን ነው በማለት ለበቀል ያነሱትን ሰይፋቸውን ወደ ሰገባው ይመልሳሉ፡፡ ሐሳባቸውን በመቀየር ጉዳዩ በሰላም ተቋጭቶ፣ በሃያ ሺሕ የደቡብ አፍሪካ ራንድ ካሳ ክፍያ እንዲጠናቀቅ ተስማምተው እርቅ ማውረዳቸውንና አያቴ ስም የኦሮሞ ስም በመሆኑ ከጉድ ወጣሁ ሲል በግርምት መንፈስ ሆኖ ገጠመኙን አጫወተኝ፡፡

ይህ ሰው እስከዛች ቀን ድረስ ስለ አያቱ ኦሮሞነትም ሆነ ስለመጣበት ብሔር ወይም ጎሳና ማንነት በቅጡ አስቦ ወይም ትዝ ብሎት እንደማያውቅና ይህ ገጠመኙ ግን ከሚኮራበት ከኢትዮጵያዊነት ማንነቱ ባሻገርም ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ስለሰኟት ሕዝቦቿ ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነትና ቅርስ ለማጥናት የማንቂያ ደወል ሆነኝ ሲል ነግሮኛል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ሰው በተለያዩ ጊዜያት ወደ ደቡብ አፍሪካ በስደት የገቡና ኖሮአቸውን በዛው ያደረጉ የኦሮሞ ተወላጆች ለደቡብ አፍሪካ መንግሥት የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄ በሚያቀርቡበት ወቅት የተፈጠረውን እሰጥ አገባም እንዲህ ጨምሮ ተርኮልኛል፡:

የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ሆኑ ስደተኞች ለፖለቲካ ጥገኝነት ብቁ የሚያደርጋቸውን ቅፅ በሚሞሉበት አጋጣሚ አብዛኛው የኦሮሞ ተወላጆች ዜግነት ወይም አገር በሚለው ክፍት ቦታ ላይ ‹‹ኦሮሚያ›› በማለት በመሙላታቸው የደቡብ አፍሪካ ‹‹ሆም አፌር ቢሮ›› የሥራ ባልደረቦች እኛ ‹‹ኦሮሚያ›› የሚባል አገር አናውቅም በማለታቸው በተነሳ ክርክር፣ እነዚህ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የሆኑ የፖለቲካ ጥገኝነት ፈላጊዎች፣ ‹‹ኦሮሚያ በቀድሞዋ አቢሲኒያ በአሁኗ ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ስር ምትማቅቅ አገር ናት፡፡›› በማለት በማስረዳት ዜግነት በሚለው ክፍት ቦታ ላይ ‹‹ኦሮሚያ›› የሚለው ማንነታቸው እንዲሞላላቸው ቢጠይቁም ተቀባይነት በማጣታቸው እየጎመዘዛቸው ቢሆንም የማያምኑበትን የኢትዮጵያዊ ዜግነት በክፍት ቦታው ላይ ይሞሉ እንደነበር ይህ ሰው ጨምሮ ነግሮኛል፡፡

ይህንና ይህን የመሳሰሉ ብሔርን ማእከል ያደረጉ አሳዛኝ ገጠመኞች በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ አገር ተደጋግመው የሚከሰቱ መሆናቸው ደጋግምን ያየነውና የሰማነው እውነታ ነው፡፡ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በአውስትራሊያና በደቡብ አፍሪካ ዛሬ ዛሬ በትግሬ፣ በአማራ፣ በኦሮሞ … ወዘተ ስምና ማንነት የራሳቸውን ወሰን ወስነውና አጥር ከልልው የሚኖሩና ይህና ያ ብሔር በእኔና በዚህ ብሔር ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል፣ ግፍና ጭቆና አድርሶብናል በሚል የየራሳቸውን የጭቆና ታሪክና የተጋድሎ ገድል ጽፈውና አጽፈው ያሉ፣ ከዚህም የተነሳ ደግሞ ለበቀል የሚፈላለጉና በጎሪጥ የሚተያዩ ሕዝቦች ኢትዮጵያ በምትባለው ምድር ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው፡፡

ይህን ከላይ በመግቢያችን የገለጽኩትን አሳዛኝ ገጠመኝ ወይም ታሪክ ለዚህ ጹሑፍ መግቢያ ይሆነኝ ዘንድ የመረጥኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ስለ ኢትዮጵያዊነትና ኦሮሙማ (ኦሮሞ ናሽናሊዝም) በተመለከተ ‹‹በገዳ ዶት ኮም›› እና በሌሎች በተለያዩ ድረ ገጾች ሰፋ ያለ ውይይትና ክርክር ተደርጎ ነበር፡፡ በዚህ ከስምንት የማያንሱ ማእከላቸውን አውሮፓና አሜሪካ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና የኦሮሞ ምሁራን ባደረጉት ውይይትና ክርክር ከተሳተፉት ፖለቲከኞችና የኦሮሞ ምሁራን መካከል ዶ/ር በያን አሶቦና ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ይኸው የኢትዮጵያዊነትና የኦሮሙማ ሙግትም የፓል ቶክ ዋና የመወያያ ርዕስ ሆኖ ነበር፡፡ ይህ ውይይትና ክርክር ገና ሳይበርድና ሳይቋጭ ነበር በዛው ሰሞን ወጣቱ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና ተንታኝ ጃዋር ሙሐመድ ከአልጄዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ለዓመታት በዘለቀው የኦሮሞ ጥያቄ፣ የነፃነት ትግል ታሪክ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ትንታኔ የሰጠው፡፡ ጃዋር I am First Oromo. Ethiopia is imposed on me የሚለው አቋሙን ግልጽ ካደረገ በኋላ የኦሮሞን ታሪክና የኦሮሞን የዓመታት ጥያቄ በተመለከተ የፖለቲካ ተንታኙን የጃዋርን ትንታኔና አቋም በመቃወምም ይሁን በመደገፍ የተለያዩ ሐሳቦች መንሸራሸር ጀመሩ፣ አሁንም ድረስም እየተንሸራሸሩ ነው፡፡

ባለፉት ሰሞናትም በተለያዩ በይነ መረቦችና በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይም የጃዋርን ሐሳብ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች በየበኩላቸው አቋማቸውን ለመግለጽ ሞክረዋል፡፡ አንዳንዶችም ስድብ ቀረሽ በሚመስል ጨዋነትና ቅንነት በጎደለው መንፈስ ጃዋር ባነሳው ሐሳብ ላይ የውይይት መድረኩን የሚያጠለሹና የሚበርዙ እሳቤዎችን ከስድብ፣ ከዛቻና ከማስፈራሪያ ጭምር ሲያዘንቡም ታዝበናል፡፡ ከዚህ ውጪ ደግሞ ሰብአዊ ፍቅር፣ ጨዋነትና ቅንነት በተሞላበት መንፈስ ከኦሮሞም ይሁን ከሌላ ብሔር ተወላጆች ዘንድ፣ ሚዛናዊ የሆነ፣ ከጭፍን ጥላቻና ከበቀል ስሜት በጸዳ መንፈስ  ሐሳባቸውንና አቋማቸው የገለጹም ጥቂት ጸሐፊዎችና ተንታኞችም ብቅ ብቅ ብለው ነበር፡፡

እኔም በዚሁ ሰሞነኛ በሆነው የኦሮሞ ሕዝብን ታሪክና ጥያቄ በተመለከተ ለኦሮሞ ሕዝብ ነፃነትና መብት ቆመናል በሚሉ አንዳንድ የኦሮሞ ምሁራንና ፖለቲከኞች ዘንድ በኦሮሙማ (በኦሮሞ ናሽናሊዝም)፣ በኢትዮጵያ ታሪክና በኢትዮጵያዊነት ላይ በሚያነሷቸው አንኳር ሐሳቦችና በሚያራመዱት አቋሞቻቸው ዙሪያ ላይ ጥቂት የመወያያ ሐሳቦችን ለማጫር ወደድኩ፡፡

በእርግጥ ይህ ለውይይት ማጫሪያ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ አጭር ጽሑፍ የኦሮሞ ተወላጅ ምሁራንና ፖለቲከኞችን፣ አሊያም ደግሞ በኦሮሞ ሕዝብ ስም ተቋቋመው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ታሪክና በኢትዮጵያዊነት ላይ ያላቸውን አቋማቸውንና ለኦሮሞ ሕዝብ አለን ስለሚሉት የትግል አቅጣጫዎቻቸውን ለመተንተን፣ ለመተቸትና ለመገምገም አይደለም አነሳሱ፡፡ ይህን ለማድረግ እንሞክር ቢባል እንኳን በእነዚህ ጥቂት ገጾች ለመሞከር የሚታሰብ አይሆንም፡፡

ለዚህም እንደ ዋና ሆነው ከሚነሱት ዐበይት ምክንያቶች መካከል ደግሞ በኦሮሞ ሕዝብ ስም እየተንቀሳቀሱ ያሉ በዓላማም በአቋምም የተለያዩ ፓርቲዎች መኖራቸው፡፡ እንዲሁም እነዚሁ ፓርቲዎችም የኦሮሞን ሕዝብን ታሪክና ጥያቄ  በተመለከተ የሚያራምዷቸው አቋሞችና ጥያቄዎች ‹‹ከባርነት ወይም ነፃነት›› ወይም ደግሞ ‹‹ከአቢሲኒያ/ከዛሬዋ ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነፃ የመውጣት ጥያቄ ነው፡፡›› ከሚለው ፖለቲካዊ አቋም አንስቶ በተለያዩ የኦሮሞ ተወላጅ ምሁራንና ፖለቲከኞች ዘንድ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ባሉ የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ፣ ባህል፣ እምነትና ቅርስ አኳያ ያሉት አመለካከቶችና ትንታኔዎች መንገዳቸው የየቅል መሆኑን ነገርዬውን ቀላል አያደርገውም ብዬ ስለምገምት ነው፡፡

ለአብነትም ያህል የኦሮሞን ብሔርተኝነት በእጅጉ ያራምዱና ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ የነጻነት ጥያቄ ነው፡፡›› ሲሉ የነበሩ አንዳንድ የኦሮሞ ምሁራንና ፖለቲከኞች በጊዜ ሂደት ኦሮሞ በኢትዮጵያ በቆዳ ስፋት ትልቁና የሕዝቡም ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ውስጥ ግዙፍ ሆነ ቦታ ሊሰጠው ይገባል፣ የኦሮሚፋም በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት ፖለቲካ አሥተዳደር ውስጥ የፌዴራል መንግሥቱ  ቋንቋ መሆን የሚችልበት መንገድ ሊታሰብብት ይገባዋል፣ የሚሉ የተለሳለሱ አቋሞችን የሚያራምዱ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ፖለቲከኞችም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብቅ ብቅ ማለታቸውንም ታዝበናል፡፡
ስለሆነም በዚህ ጽሑፍ የኦሮሞን ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነት፣ የኦሮሞን የመብት ጥያቄና ትግል ተመለከተ በፊትም ሆነ በተለይም ደግሞ ከሰሞኑን የፖለቲካ ተንታኙ ጃዋር ሙሐመድ ባነሳው የኢትዮጵያዊነትና የኦሮሙማ አንኳር እሳቤዎች ላይ ተመርኩዤ ጥቂት ነገሮችን ለማለት ወደድኩ፡፡

እንደሚታወቀው ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት ውስጥ የእከሌ ብሔር ወይም ጎሳ በዚህኛው ብሔር ወይም ጎሳ ላይ ለፈጸመው በደልና ጭቆና በሚል ያልተወራረዱና ጊዜ እየጠበቁ ቦግ እልም የሚሉ ምሬቶችን፣ ቁጣዎችንና የበቀል ሰይፎችን በተለያዩ የአገራችን ክልሎች መከሰታቸውን ታዝበናል፡፡ ይህን እኩይ የሆነ የበቀል ሒሳብ በማወራረድ የተጠመዱ አንዳንድ ፓርቲዎች፣ ፖለቲከኞችና ግለሰቦችም ሆን ብለውና ያልተገባ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግበስበስ ሲባል እውነታን በማጣመም በሚጻፏቸውና በሚያጽፏቸው የተዛቡ የታሪክ ድርሳናትና ገድሎቻቸው፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ትናንትና ያልነበረ ዛሬም የሌለ ቅዠት ወይም ሕልም ነው እስኪባል ድረስ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በርካታ ትንታኔዎቻቸውን ሰምተናል፣ የዳጎሱ ጥናታዊ ጽሑፎቻቸውንም አስነብበውናል፡፡
በዚህ እነዚሁ የብሔር ፖለቲካ ጽንፈኞች፣ በቀልን ሰባኪዎች፣ የብሔራዊ መግባባትና እርቅ ተቀዋሚዎች በተጻፉ የተዛቡ ታሪኮችና ያልተወራረዱ የበቀል ሒሳቦች ክፉ ስብከት የተነሣም ለዘመናት ተዋደውና ተከባብረው፣ በጋብቻና በአምቻ ተሳስረው፣ እኔ ትብስ አንተ ትብስ ብለው የኖሩ ሕዝቦች የተሳሰሩበትን የአንድነት ድርና ማግ ለመበጠስ ሲባል የተደረጉ አያሌ ዘመቻዎችንም በዘመናችን በሐዘንና በግርምት ሆነን አስተውለናል፡፡

ዛሬም ድረስ ለኦሮሞ ሕዝብ መፍትሔው የእኔ የፖለቲካ አቅጣጫ ነው የሚሉ በርካታ የኦሮሞ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች በአገር ውስጥና በውጭ አገር ሆነው ለኦሮሞ ሕዝብ ይጠቅማል በሚሉት መንገድ የራሳቸውን አቋም በማራመድ ይጻፋሉ፣ ይወያያሉ፣ ይከራከራሉ፣ ይሟገታሉም፡፡

ይሁን እንጂ እስካሁኗ ቅጽበት ለኦሮሞ ሕዝብ ነፃነት፣ መብትና ጥቅም ቆመናል በሚሉት በበርካታ የኦሮሞ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንንም ሆነ ፓርቲዎች ዘንድ ቢያንስ ባለፉት ሁለት ዐሥርተ ዓመታት የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክና ጥያቄ በማስተጋባትና በመፍትሔ አቅጣጫዎችም ዙሪያ በሚያራምዱት አቋማቸው እርስ በርሳቸው የተለያዩና የተከፋፈሉ መሆናቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች ዐይተናል፡፡ በዋነኝነት የኦሮሞ ሕዝብን ጥያቄ ለመፍታት ከእኔ ወዲያ ለአሳር በማለት ሲምል ሲገዘት የነበረው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በዕድሜ የሚያክለውና የሚስተካከለው ባይኖርም ዛሬም ድረስ በተለያዩ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ውስብስብ ችግሮች ተተብትቦ እየዳከረ ያለ ፓርቲ መሆኑን የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
በተጨማሪም ባለፉት ዓመታት በፓርቲው አመራሮቹ መካከል በተፈጠረ ልዩነትና ውዝግብ የፓርቲው ህልውና አበቃለት እስኪባል ድረስ የነበረውና አሁንም በያዝ ለቀቅ በፓርቲው ውስጥ የሚነሱት ወጀብና ዐውሎ ንፋሶች ዛሬም ድረስ ገና መፍትሔና መቋጫ ያገኙ አይመስሉም፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው፣ ነፃነትን የማወጅ፣ ሉዓላዊነትን የማስከበር፣ የማንነት፣ የታሪክና ፖለቲካ ጥያቄ ነው፣ በማለት ጽንፈኛ አቋሙን በሚያራምደው ኦነግና ደጋፊዎቹ ዘንድ ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በሸዋው ንጉሥ በምኒልክ ሰይፍ ተቀጥቅጦ በአማራ ታሪክና ማንነት ላይ የተገነባ ነው የሚለው መከራከሪያቸው አሁንም ድረስ በአቋም ደረጃ በግልጽ የሚንጸባረቅ ነው፡፡

ወጣቱ የፖለቲካ ምሁርና ተንታኝ ጃዋር ሙሐመድም ይህንኑ ሐሳብ በመድገም እንዲህ ብሎአል፡- ‹‹ … ኢትዮጵያን የመሠረታት የሦስትዮሽ ጦርነት ግብግብ ነው፡፡ በአማራው፣ በኦሮሞው፣ በትግሬው ግብግብ ውስጥ ወደ መጨረሻ ላይ በአመራር ስር የበላይነቱን የያዘው አማራው ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ አሁን የምናያት ኢትዮጵያ ማንነቷ በአማራ ባሕላዊ ሥርጭትና  በአማራ ፖለቲካ የተገነባች ነች፡፡ … የኢትዮጵያ አገራዊ ማንነት የምንለውም የአማራ ባህላዊ ማንነት ነው፡፡›› ሲል ከኢትዮጵያ ታላቅ ሥልጣኔ፣ ታሪክና ከኢትዮጵያዊነት መንፈስ ወይም ማንነት ጋር የሚጣረስ ድምዳሜን ሰጥቶአል፡፡

ይህ ዓይነቱ ትንታኔ የኢትዮጵያን ታሪክ በአግባቡ ያለመረዳት ቀውስ ወይም ደግሞ ሆን ብሎ  የታሪክ እውነታን የማዛባት ዘመቻ ነው የሚመስለው፡፡ ኢትዮጵያ የምትባለው ምድርና ሕዝቦቿ ትናንትና ከመቶ ዓመት በፊት ምኒልክና ተከታዮቹ በኃይልና በሰይፍ በሚፈልጓት ቅርፅና ይዘት ቀጥቅጠው የፈጠሯት እንጂ የሚለው መከራከሪያ ሐሳብ በምንም መንገድ ውኃ ሊያነሳ የሚችል ሐሳብ አይመስለኝም፡፡ ይህ ዓይነቱ አመለካከት ከሺሕ ዓመታት በፊት ጀምሮ በገናና ሥልጣኔዋና ታሪኳ በዓለም መድረክ ስሟ ገኖ የወጣውን፣ ከአፍሪካ አልፎ በሰሜን አሜሪካና በካረቢያን በባርነትና በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ተይዘው ሲማቅቁ ለነበሩ ሕዝቦች የነፃነት ምድር፣ የጥቁር ሕዝቦች ተስፋ ‹‹የጥቁር ሕዝቦች የከነዓን ምድር›› በሚል በሰቀቀንና በናፍቆት ሲያስቧትና ሲዘክሯት የኖረችውን ኢትዮጵያን ህልውና የመካድ ያህል የሚቆጠር ይመስለኛል፡፡

ኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የነፃነት ተምሳሌት፣ የአንድነትና የፍቅር ኪዳን ሆኖ በብዙዎች ልብ ውስጥ ሲንቀለቀልና ለዘመናት ሲያበራ የኖረ እውነት መሆኑን መካድ አንችልም፡፡ ከአፍሪካ አስከ አሜሪካ፣ ካረቢያና ጃማይካ ይህ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ በእውቁ የነፃነት ታጋይ በእነ ማርከስ ጋርቬይ፣ በሬጌው ንጉሥ በእነ ቦብ ማርሌይ፣ በእነ ፒተር ቶሽ፣ በአፍሪካውያኑ የነፃነት አባቶች፣ በእነ ጆሞ ኬንያታ፣ በንኩርማ፣ በማንዴላና በበርካታ የነፃነት ታጋዮች ዘንድ የሞራልና ወኔ ስንቅ ሆኖ ያገለገለ፣ ክቡር ታሪክ፣ ሕያው አሻራና ቅርስ መሆኑን መዘንጋት ከታሪክ ሐቅ ጋር መጣላት ነው የሚሆነው፡፡

በተጨማሪም ለዚህችው በሺሕ ዘመናት ገናና ሥልጣኔዋ፣ ነፃነቷ፣ ታሪኳና ሉዓላዊነቷ ሲሉ በዐድዋ ጦር ግንባር ከወራሪው የአውሮጳ ኃይል ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ለሕዝቦቿም ነፃነት ዋጋ የከፈሉትን የኦሮሞ ተወላጆቹን የእነ ባልቻ አባ ነፍሶን፣ የእነ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪን፣ የእነ ራስ አበበ አረጋይን፣ አውሮጳ ምድር ድረስ ዘልቆ በሮማ አደባባይ የኢትዮጵያውያንን አይበገሬነትና ለነፃነታቸው ቀናኢ ሕዝብ መሆናቸውን ያሳየውን የአብዲሳ አጋንና የበርካታ እልፍ የሚሆኑ የኦሮሞ ልጆችን ለሰው ልጆች ነፃነት የፈሰሰ ደምና መሥዋዕትነት ማራከስ ነው የሚሆነው፡፡

ከሰሞኑን የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩና አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕ/ር መረራ ጉዲና፡- ‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች፡- ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢህአዴግ›› በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፋቸውም በዓድዋው ጦርነት ከየትኛውም ሕዝብ ይልቅ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ጦር አዝማቾችና ጀግኖች ታላቅ መሥዋዕትነት መክፈላቸውን በመግለጽ የዓድዋ ድል የምኒልክን ቅኝ ግዛት ዘመቻ ያጠናከረ ዓውደ ግንባር ነው የሚለውን ሐሳብ አጣጥለው በመከራከር ጽፈዋል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ታላቅነትና አይበገሬነት በኦሎምፒክ መድረክ ከፍ ያደረጉ አበበ በቂላ፣ ዋሚ ቢራቱ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ደራርቱ ቱሉ … እነዚህ ሁሉ በሮጡበት መድረክ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ብሔርና ሃይማኖት ሳይለዩ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ አብረው ሮጠዋል፣ ስለ ኢትዮጵያ ክብርና ድልም አብረው አምጠዋል፣ ተጨንቀዋል፡፡ በባርሴሎና ኦሎምፒክ መድረክ አበባችን ደራርቱ ቱሉ በአሥር ሺሕ ሜትር የመጀመሪያቱ አፍሪካዊት ሴት ወርቅ ሜዳሊስት በሆነችበት ድሏ የአገሯ ብሔራዊ መዝሙርና ሰንደቅ ዓላማ በስፔን ሰማይ ላይ ሲናኝና ከፍ ብሎ ሲታይ በጉንጯ ላይ ኮለል ብሎ የፈሰሰውን ዕንባዋን የታዘብን ሁሉ፣ በኢትዮጵያዊነት ኩራትና አይበገሬነት መንፈስ አብረናት በደስታ ሲቃ አንብተናል፣ መሬት ስመናል፡፡

ይህን ታሪክ በወርቅ ቀለም የጻፈውን የበርካታ ኦሮሞ ጀግኖችን ገድልና ለኢትዮጵያዊነት የተከፈለ መሥዋዕትነትን ማቃለልና ታሪክን ማዛባት ጤነኛ አካሄድ አይደለም፡፡ በዘመናችን ኦሮሙማን/የኦሮሞን ብሔርተኝነት በእጅጉ የሚሰብኩና የሚያራግቡ ሰዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ኦሮሙማን ወይም የኦሮሞ ብሔርተኝነነትን ለመገንባት ሲሉ የኢትዮጵያን የሺሕ ዘመናት ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ቅርስና የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ ማጣጣልና መንኳሰስ ጤነኛ አካሄድ አይመስለኝም፡፡

ኢትዮጵያዊነት እንደ ኮሶ ተበጥብጦ በግድ እያነገፈገፈን የተጋትነው፣ እየቀፈፈንና እየኮሰኮሰን የተደረበብን ማንነት ብለው ለሚከራከሩ ሰዎች በእርግጥም በግድ ሳይወዱ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ተቀበሉ ብሎ ማስገደድ እንደማይቻል አሳምሬ አውቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊ ለመሆን ያለመፈለግ መብታቸውንም በግሌ አከብራለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ታሪክን በማዛባት ጥቁር ሕዝቦች፣ መላው አፍሪካና በአጠቃላይ ነፃነትን አፍቃሪ የሆኑ ሕዝቦች ልብ ውስጥ ትልቅ ዋጋና ክብር ያለውን የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ ማራከስ፣ በኢትዮጵያና በሕዝቦቿን ታሪክ፣ ቅርስና ማንነት ላይ መዘባበት ጤነኛ አካሄድ እንዳልሆነ አሁንም በድጋሚ አስረግጬ ለመናገር እወዳለሁ፡፡

ከሰባት የሕወሓት የልኡካን ቡድን አባላት ሶስቱ በአሜሪካ ጥገኝነት ጠይቀዋል::

August 29, 2013

ከሰባት የሕወሓት የልኡካን ቡድን አባላት ሶስቱ በአሜሪካ ጥገኝነት ጠይቀዋል:: “የመለስ ፋውንዴሽን፣ የአባይ ግድብና የ40/60 የቤቶች ግንባታ ገንዘብ አዋጡ” ሕወሐት ባለስልጣናት የአሜሪካ ቆይታ፤ የከዱ አሉ (ከኢየሩሳሌም አርአያ) በአባይ ወልዱ የሚመራውና ሰባት ከፍተኛ የሕወሐት ባለስልጣናት የተካተቱበት ቡድን በአሜሪካ አራት ከተሞች ባካሄደው ስብሰባ በተለይ በላስቬጋስ ጠንካራ ተቃውሞ እንደገጠመው በስፍራው የተገኙ ምንጮች አስታወቁ። ቡድኑ በዋሽንግተን ኢትዮጲያ ኤምባሲ በጀመረውና በመቀጠል በላስቬጋስ፣ ሲያትልና ካሊፎርኒያ ከተሞች ባካሄደው ስብሰባ “አላማ” አድርጎ የያዛቸው ጉዳዮች እንደነበሩ የጠቆሙት ምንጮች፣ እነሱም፥ “የመለስ ፋውንዴሽን፣ የአባይ ግድብና የ40/60 የቤቶች ግንባታ.” ሲሆኑ፣ ለነዚህ ማስፈፀሚያ “ገንዘብ አዋጡ” የሚለው ዋናው ግብ እንደነበር አስረድተዋል።
በተለይ ደግሞ « በትግራይ ተወላጁ ዘንድ ሕወሐት የለም፣ ተከፋፍሏል፣ ተዳክሟል፣ ፓርቲው ሰው የለውም፤» የሚለውን እራሱ ቡድኑ በማንሳት ለገዛ ጥያቄው መልስ ሲሰጥ « ሕወሐት አሁንም ሃይል አለው፤ አልተዳከመም» በማለት አድራጊ- ፈጣሪ በመሆን ስልጣኑን በበላይነት ተቆጣጥሮ እንደያዘና ቡድኑ የመጣውም “አይዟችሁ” ለማለት እንደሆነ መገለፁን በቅርብ የተከታተሉት ምንጮች አስታውቀዋል። ቡድኑ በተጨማሪም ፥ « ልማት አልምተናል፤ ትግራይ እየለማ ነው፤ ህዝቡን ተጠቃሚ እያደረገነው ነው» ከማለቱ ባሻገር « በትግራይ ተወላጁ ላይ አደጋ ተደቅኗል፤ የሙስሊሙ፣ የትምክህተኞችና የሽብርተኞች አደገኛ እንቅስቃሴ እያንዣበበ መሆኑን፣…የተደቀነብህን አደጋ ከጎናችን ሆነህ ተከላከል፤ ያለበለዚያ ግን ሊያጠፉህ ነው፤» ሲሉ መናገራቸውን የገለፁት ምንጮች አክለውም፣ « አባላት የሆናችሁ ተወደደም ተጠላ መሬትና መኖሪያ ቤት እንሰጣችኋለን፤ ለዚህም ከእኛ ጎን መሰለፍ አለባችሁ» በማለት ሊሸነግሉ መሞከራቸውን ጠቁመዋል። ከዋሽንግተን ስብሰባ (ለሁለት ተከፍሎ ነው የተካሄደው) በኋላ ወደ ሶስቱ ከተሞች ተከፋፍለው እንደሄዱ ሲታወቅ፥ ሲያትል አቶ ብርሃነ ማረት፣ እንዲሁም ላስቬስጋስ አባይ ወልዱና ተክለወይኒ አሰፋ መሄዳቸው ታውቋል።
በተለይ በላስቬጋስ ጠንካራ ተቃውሞ የገጠማቸው እነአባይ ስብሰባው ከቀኑ 2፡00 ሰዓት ይጀመራል ተብሎ ከአራት ሰዓት በኋላ ዘግይቶ አመሻሽ ላይ መጀመሩን ምንጮች ገልፀዋል። ስብሰባው ሲጀመር ከላይ የተገለፁትን ጉዳዮች ያደመጠው ተሰብሳቢ ተከታዮቹን ጥያቄ አቀረበ፤ « ዴሞክራሲ አለ ትላላችሁ፣ ነገር ግን ዴሞክራሲ የለም፤ በሃሳብ የሚቃወማችሁን ታስራላችሁ፣ ታንገላታላችሁ፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ ታካሂዳላችሁ፤ ከእናንተ የተለየ ሃሳብ ያለውን ትፈራላችሁ፤ ለምንድነው ይህን ሁሉ የምታደርጉት?....በማ.ረ.ት.(ማህበር ረድኤት ትግራይ) በትግራይ ሕዝብ ስም የምትሰበስቡትን ገንዘብ ለአራጣ ብድር እና ለፖለቲካ መጠቀሚያ በመሳሪያነት እያዋላችሁት ነው። ለምን?....ትእምት (ኤፈርት) ማነው ባለቤቱ?..በማን ነው የሚመራው?..ማነው የሚቆጣጠረው?..ለመሆኑ ኦዲት ተደርጎ ያውቃል ወይ?..እነማናቸው እየተጠቀሙበት ያለው?» የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ጥያቄዎች እንደነበሩ ምንጮቹ የጠቆሙ ሲሆን፣ አባይ ወልዱ « እኔ አልመልስም፣ ተ/ወይኒ መልስ ይስጥበት» ቢሉም ነገር ግን ግልፅና አግባብ ያለው ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ወደ ማመናጨቅና ቁጣ ያመሩት ተ/ወይኒ በዚህ ድርጊታቸው በርካታ ተሰብሳቢዎችን እንዳሳዘኑ አስረድተዋል።
በዚህ የተበሳጨው ተሰብሳቢ « ጥያቄያችን አልተመለሰም» በማለቱና ሁከትና ያለመደማመጥ በማየሉ ስብሰባው እንዲቋረጥ መደረጉን የጠቆሙት ምንጮች፣ የጥያቄና ተቃውሞው መብዛት ያስደነገጣቸው ባለስልጣናቱ የመረጡት ማምለጫ በላስቬጋስ ተወካያቸው በሆነውና መድረክ ሲመራ በነበረው አቶ ተወልደ በኩል፥ « አዳራሹን የተከራየንበት ሰአት አብቅቷል፤ ስለዚህም ስብሰባው አብቅቷል » በማለት በአስቂኝ ሰበብ መቋረጡን አያይዘው ገልፀዋል። እነአባይ ከአዳራሹ ሲወጡ ቀድሞ ውጭ ሆኖ ይጠብቃቸው በነበረው ተሰብሳቢ ውግዘትና ስድብ እንደደረሰባቸው ያስታወቁት ምንጮች « ሌባ..ሌባ…ሙሰኞች..» የሚሉ ተቃውሞዎች ጎላ ብለው እንደተሰሙ አመልክተዋል።
ስብሰባዎቹን የታዘቡ ወገኖች በሰጡት አስተያየት እንዲህ ብለዋል፤ « በአንድ በኩል ልማት እያካሄድን ነው፤ እያሉና ገንዘብ እየጠየቁ በሌላ በኩል “ትግራዋይ አደጋ ተደቅኖብሃል፣ ከጎናችን ሆነህ ተከላከል፤” ማለት እርስ በርሱ የሚጋጭና ድጋፍ የማግኛ የፖለቲካ የፖለቲካ ቁማር ነው። ያልተጠየቁትን የፓርቲውን ህልውና (ስለ ሕወሐት) አንስቶ መነገሩም አስገራሚና አጠያያቂ ነው።» ሲሉ ትዝብታቸውን የጀመሩት እነዚህ ወገኖች በማያያዝም፥ « እነዚህ ሰባት ባለስልጣናት ወደ አሜሪካ የመጡት ከነዘመዶቻቸው፣ ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ሲሆን፣ ባለስልጣናቱ የመንግስት ወኪሎች እንደመሆናቸው - በማን ገንዝብ ነው የሚንቀሳቀሱት?..የሚለው መጠየቅ አለበት። በሕዝብ ገንዝብ እየተንፈላሰሱ እንደሆነ ግልፅ ነው።
የትግራይ ተወላጁን ብቻ ለይተው ስብሰባ የሚጠሩት ለምንድነው?...በእርግጥ ስላሰቡለት ነው?...የሚሉት ሲፈተሹ .መልሱ በጭራሽ አይደለም ነው። አላማቸውና ትኩረት የሰጡት የትግራይ ተወላጁን እየተንከባከቡት እንደሆነና ተጠቃሚ መሆኑን ለማሳየት በመፈለግ፣ እግረ-መንገዳቸውን ከቀሪው ኢትዮጲያዊ ወገኑ ጋር በመነጠል..ድጋፍ ለማግኘትና በውስጣቸው የተፈጠረውን ቀውስ በዚህ በኩል ቀዳዳውን ለመድፈን የሚደረግ የስልጣን እድሜ ማራዘሚያ ስልት ነው። ..ደግሞስ ሕወሐት “አጋር” ከሚላቸው ብ.አ.ዴ.ን፣ ኦ.ህ.ዴ.ድ.፣ ደቡብ ሕዝቦች ተለይቶ፣ በሕዝብ ገንዘብ ስብሰባ የሚጠራበትና ያሻውን የሚያደርግበት አግባብ ምንድነው?..የሚለው ከዚህ ጋር መታየት ያለብት ነው። ፖለቲካዊ ፍጆታና ማንአለብኝነት በፓርቲው በመነገሱ እንደሆነ ደግሞ ግልፅ ነው።» ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ አሜሪካ ከመጡት ሰባት የሕወሐት ባለስልጣናት መካከል- ማለትም አባይ ወልዱ፣ ብርሃነ ኪ/ማሪያም፣ ተ/ወይኒ አሰፋና ዳንኤል አሰፋ በዋነኛነት ሲጠቀሱ፣ ከሰባቱ ሶስቱ ስብሰባውን ሳያካሂዱ ከቡድኑ ተገንጥለው በአሜሪካ መቅረታቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል። ቤተሰቦቻቸውን ይዘው (ልጆቻቸውን ጭምር) በመምጣት አሜሪካ ጥገኝነት ጠይቀው መቅረትን የመረጡት ባለስልጣናት ውስጥ የሕወሐት ማ/ኮሚቴ አባላት እንዳሉ ያረጋገጡት ምንጮች

የእኛ “መንግስት” (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ)

August 29, 2013

“በእያንዳንዱም መንግስት የሚያድሩ ብዙ ልዩ ልዩ ነገዶች ይኖሩ ይሆናል፡፡ ስለ ሆነ መንግስት አንዱን ነገድ አጥቅቶ ሌላውን ነገድ ለመጥቀም ሥራው አይደለም፡፡ አስተካክለን ካሰብን ዘንድ መንግስት መቆሙ ለሕዝቡ ሁሉ ጥቅም ነው፡፡ ጥረቱም ህዝቡን ሁሉ በትክክል ለመጥቀም ያልሆነ መንግስት ሊቆም አይችልም፡፡ ለአንዱ ነገድ ወይም ለጥቂት ሰዎች ብቻ ማድላት ለመንግስት የሚገባ ሥራው አይደለም” ይህንን መግቢያ የወሰድኩት በልዑል የኢትዮጵያ መንግስት አልጋ ወራሽ ተፈሪመኮንን ማተሚያ ቤት የካቲት 1 ቀን 1917 ዓ.ም ከታተመው የነጋ ድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ‹‹መንግስትና የሕዝብ አስተዳደር›› መፅሀፍ ነው፤ ዛሬም ያለንበትን ዘመን ይዋጃልና፤ በተለይ ስለ‹‹ነገድ›› የተጠቀሰውን አርቀን ሰቅለን፣ ‹‹ለጥቂት ሰዎች ብቻ ማድላት›› የምትለዋን ሀረግ በወጉ ካጤንናት ለጊዜያችን በልክ የተሰፋች መሆኗን ለመረዳት አስቸጋሪ አይደለም፡፡Journalist Temasegan Dasaleg
እናም የስርዓቱን የአስተዳደር ዘይቤ ያለፍርሃት አደባባይ ካዋልነው የቀድሞ ገዥዎቻችን የተጓዙበትን ጎዳና እየተከተለ መሆኑን ለመተንተን የምሁራንን ጥናት መጠበቅ ግድ አይለም፤ ምክንያቱም ለዓመታት የተመለከትነው እውነታ የሚነግረን የአመራሩን እና በዙሪያው የሠፈሩ የጥቅም ተጋሪ ግለሰቦችን ብልፅግና ታሳቢ ያደረገ፣ ከታግሎ መጣል ህግ የተቀዳ፣ የራስ ሀገርንና የራስ ሕዝብን በምርኮ ያስገበረ ፖለቲካ መንበሩን ነው፤ ገብር፣ ገብር፣ ገብር…!!
ዛሬ መንገድ ዳር ረሀብ አዙሮ የጣለው ወንድምህ ስቃይ እንደ ጥላ የሚከተልህ፤ ህፃናት በትምህርት ገበታቸው ላይ በጠኔ ተሸንፈው መመልከቱ የሰርክ አሳዛኝ ክስተት የሆነብህ ከሰው ሰራሽ ችጋር፣ ከሰው ሰራሽ የቀዬ ፍንቀላ፣ ከሰው ሰራሽ እርዛት… የመነጨ መርገምት እንጂ የሰማይ ቁጣ አይምሰልህ፤ እመነኝ መለስም ሆነ ተተኪዎቹ ስኬት አድርገው የሚሰብኩትም ይህንን ነው፤ ‹ሀገር አቀናን!› የሚሉትም ይህንን ነው፤ ሰሞኑን የሚያሰለቹህ ተረኛ ምሁራንም ‹‹ትምህርትና ጤናን በተመለከተ መለስ ‹እልል› የሚያስብል ሥራ ሰርቷል›› የሚሉህ ጣራና ግድግዳ እየቆጠሩ ነው፤ ይህ አይነቱ መደዴ ሙገሳም ለፕሮፓጋንዳ የሚሆን ሪፖርት ለማዘጋጀት ከሚረዳ ቁጥር የዘለለ አበርክቶ አንደማይኖረው አትዘንጋ፡፡
እውነት እውነት እልሀለሁ፡- ይህ የሆነበት ብቸኛው ምክንያት መንግስት በስልጣን ላይ ስለሚቆይበትመንገድ ብቻ መጨነቅን ግዴታው በማድረጉ ነው፤ ይህንን ለመረዳትም እያገባደድን ባለው ክረምት የመንግስት ትኩረት በምን ላይ አንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃን ጨርፌ ላሳይህ፡፡
ክረምቱ እንዲህ እየተገባደደ ነው፡- የእስልምና እምነት ተከታዮች መንግስት በሃይማኖታቸው ጣልቃ መግባቱን በመቃወም እና የታሰሩ ኮሚቴዎቻቸው እንዲፈቱ በመጠየቅ እያደረጉ ያለውን ትግል በሰላማዊ መንገድ አጠንክረው ሲቀጥሉ፤በተቃራኒው ‹‹ፀጥታ አስከባሪዎች›› አንዳንዴ በጥይት፣ አንዳንዴ በአስለቃሽ ጢስ፣ አንዳንዴ በማጋዝ…ምላሽ ሲሰጡ…
በርግጥ መንግስት ከኃይል እርምጃው በተጨማሪ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎችን (በምን አግባብቶ ወይም በምን አስፈራርቶ እንደሆነ ባይታወቅም) ወደ አደባባይ በማስወጣት መብት ጠያቂዎቹን ከ‹‹አክራሪ››ነት እና ‹‹ወሃቢዝም››ነት ጋር አያይዘው የውግዘት በረዶ እንዲያዘንቡባቸው እያደረገ ነው፡፡ ኢቲቪም ይህንን ኩነት እየተከታተለ ማራገቡን ቀጥሎበታል፤ ‹‹የቲፒ ከተማ ነዋሪዎች ‹አክራሪዎችን አወገዙ››፤ ‹‹በደቡብ ወሎ ኩታ በር ዞን አንድነት ፓርቲ ህገ-ወጥ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሰልፍ ተካሄደ››፤ ‹‹የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ‹የሼሁ ግድያ ድራማ አይደለም› አሉ፣ ‹የሼህ ኑሩ ኢልም ነው፣ የአሸባሪዎች ብር ነውም›ብለዋል››፤‹‹የመርሀቤቴ ነዋሪዎች ፅንፈኞችን በመቃወም የአቋም መግለጫ አወጡ››፤…
ክረምቱ እንዲህ እየተገባደደ ነው፡- አንድነት ፓርቲ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የ‹‹ፀረ-ሽብር ሕጉ›› እንዲሰረዝና የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ እና የአዳራሽ ስብሰባዎችን እያካሄደ ነው፤ መንግስትም አንዳንዴ የአፀፋ የድጋፍ ሰልፍ ሲያካሄድ፤አንዳንዴ የአዳራሽ ስብሰባዎች ከመካሄዳቸው አስቀድሞ ‹መጋኛ› ሲሆንባቸው፤ አንዳንዴም የአስተባባሪዎቹን መኪና ጎማ ሲያፈነዳ፤ አንዳንዴም አዳራሽ ከልክሎ ሲያደናቅፋቸው… መዋሉ ፋታ የነሳው ይመስላል፤ በወላይታ የተጠራውን የአዳራሽ ስብሰባም ‹በጠቅላይ ሚኒስትሩ የትውልድ ቦታ እንዴት ተደርጎ!›› ያሉ ካድሬዎች የአንድነት ሰዎችን አዋክበው ስብሰባውን አክሽፈዋል፤
ክረምቱእንዲህእየተገባደደነው፡-ገዥው ፓርቲ ‹የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ አንደኛ ሙት ዓመት አከብራለሁ› በሚል መላ ኢትዮጵያን ችግኝ መትከያ፣ መላ ዜጎቿን ደግሞ ወደ አርሶ አደርነት በአስማት የቀየራቸው አስመስሏቸዋል፤ቴሊቪዥንና ራዲዮንም አስፈላጊነታቸው በየመንደሩ ችግኝ መተከሉን እየተከታተሉ መዘገብ ብቻ እስኪመስል ድረስ እንዲህ ሲሉ ጀምበር ወጥታ ትጠልቃለች፡- ‹‹የላይ አርማጮህ ነዋሪዎች ችግኝ ተከሉ››፣ ‹‹በመቀሌ ከተማ ‹ዘመቻ መለስ› በሚል የችግኝ ተከላ ተካሄደ››፣ ‹‹አቃቂ ኮረብታ ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ችግኝ በኦሮሚያ ፌደራል ፖሊስ አባላት ተተከለ፤ ቦታውም ‹መለስዜናዊ ኮረብታ› ተብሎ ተሰይሟል››፣ ‹‹በምዕራብ ሀረርጌ አስራ ሰባት ሚሊዮን፣ በወልበራ አስራ አራት ሚሊዮን ችግኝተ ተክሏል››፣ ‹‹በመንዝ ላሎ ወረዳ ተቆጥሮ የማያልቅ ችግኝ ተከላ ተደርጓል››፣ ‹‹የብአዴን አመራርና ካድሬ በባህር ዳር ከተማ በቢሊዮን የሚቆጠር ችግኝ ተከሉ፤ በፕሮግራሙ ላይ ጓድ አዲሱ ለገሰ ‹ችግኝ የምንተክለው አገሪቱ በአረንጓዴው ልማት በአለማችን ማግኘት የሚገባትን ቦታ እንድታገኝ ለማድረግ ነው› ሲል፣ ጓድ በረከት ስምዖን ደግሞ ‹ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአለማችን በአንድ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ችግኝ እየተከሉ ያሉባት ብቸኛ ሀገር ናት› ብሏል››፤‹‹ዝክረ መለስ 1ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ ከሐምሌ አስራ አምስት ቀን ጀምሮ ሁሉም ቀበሌዎች በስሙ ‹ፓርክ› ሰይመው ችግኝ ተከላ እያካሄዱ›› መሆኑን ደግሞ የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ መግለፁን የአማራ ክልል ብዙሃን መገናኛ ዘግቧል፤ ‹‹በወልቂጤ ከተማ በተደረገው ችግኝ ተከላ ላይም አንዲት ወጣት ‹መለስ ለሴቶች የተለየ አመለካከት ነበረው›› ማለቷም በዘገባው ተጠቅሷል፤ …ማን ነበር የመለስ ራዕይ ‹ችግኝ መትከል ነው› ያለው? …ኢህአዴግ ይሆን?
ከዚሁ ጎን ለጎን (አሁንም ሙት ዓመቱን ለማሰብ) በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የእግር ጉዞ ተደርጓል፣ የሻማ ማብራት ስነ-ስርዓትም ተካሄዷል፤መነሻውን መቀሌ፣ መድረሻውን አዲስ አበባ ያደረገ ‹‹የመለስ ቱር አረንጓዴ ልማት›› የብስክሌት ውድድርም ሊጠናቀቅ ገና አንድ ሳምንት ይቀረዋል፤ በብሄራዊና ሀይማኖታዊ በዓላት ቀንለሃያ አንድ ጊዜ ይሰማ የነበረው የመድፍ ድምፅም፣ የመለስን አንደኛ ሙት ዓመት ለማብሰር ተተኩሷል፤ …በግድ አልቅሱ፣ በግድ ተዝካር አውጡ፣ በግድ ችግኝ ትከሉ፣ በግድ ተወያዩ፣ በግድ አደባባይ ውጡ፣ በግድ የፎቶ ግራፍ ኤግዚቢሽን ጎብኙ፣ በግድ.. ክረምቱ እንዲህ እየተገባደደ ነው፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ እና የትምህርት ሚኒስትሩ ሽፈራው ሽጉጤ ከአንድ ሺህ ሰባት መቶ በላይ ለሚሆኑ የዩኒቨርስቲ ከፍተኛ መምህራን ‹የአቅም ግንባታ ስልጠና› እየሰጡ ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምሁራኖቹን ማሰልጠን ያስፈለገበት ምክንያት ‹‹ብቃት ያለው ምርጥ የተማረ ኃይል ለማፍራት››መሆኑን ቢነግርህ አይግረምህ፤ ይህ ኢትዮጵያ ነውና የዐዋቂነት ማረጋገጫው መማር፣ ማንበብ፣ መመራመር… አይደለም፣ የፖለቲካውን ኃይል መያዝ እንጂ፤ ‹ስልጣን ላለው ሁሉምሚስጥረ-ጥበብይገለፅለታል› እንዲል አብዮታዊ ዲሞክራሲ መለስ ዜናዊም በሁሉም መስክ ‹አስተማሪ› ነበር፤ የህግ ባለሙያዎችን ሰብስቦ የሀገሪቱን ወንጀለኛ መቅጫ ህግ ትርጓሜ ሲተነትን ደጋግመህ ሰምተኸዋል፤ በቀጣዩ ቀን ደግሞ ለግብርና ባለሙያዎች ከውሃ ማቆር እስከ በላብራቶሪ የሚዳቀል ምርጥ ዘር ድረስ ባሉጉዳዮችዙሪያ የሁለት ቀን ማብራሪያ መስጠቱን ታስታውሳለህ፤ እመነኝ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትርም ይህንኑ ነው እያደረገ ያለው፤ የሆነ ሆኖ ኃ/ማርያም ለምሁራኖች ከሙያቸው ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ጭምር በሰጣቸው ስልጠና ላይ እንዲህ የሚል ጥያቄ ቀርቦለት ነበር ‹‹የኢንዱስትሪዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖሩ፣ በክፍል ውስጥ የምናስተምረውን ንድፈ ሃሳብ በተግባር ለማሳየት እንቅፋት ሆኖብናል››፤ በርግጥጠቅላይ ሚንስትሩ‹‹መፍትሄ››ያለውን የተናገረው ብዙም ሳይጨነቅ ‹‹እኔ ኢንዱስትሪን ‹ዲፋይን› የማደርገው ግብርናም ኢንዱስትሪ ነው ብዬ ነው››በማለት ነበር፤…ግና!ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል በተጨባጭ አላብራራም፡፡ለምሳሌ ህክምና የሚያጠና ተማሪ በምን መልኩ በሞፈርና ቀንበር የተግባር ልምምድ ማድረግ እንደሚችል፤ወይም ፖለቲካ ሳይንስ የሚያጠና ተማሪ የተግባር ልምምዱን በግብርና ኢንዱስትሪ እንዴት ሊወጣው እንደሚችል? ማለቴ ነው፡፡
ለዓመታት በርካታ ምሁራን ብቃት አልባ ተማሪዎች እንደ ሰማይ ከዋክብት የመብዛታቸው መንስኤን ከትምህርት ፖለሲው ጋር የሚያነፃፅሩበትን ሀቲት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ባገኘው የሀገር መሪነት ስልጣን ገልብጦ በዩንቨርስቲ ቆይታው መምህራኖቹ የነበሩትንም ጭምር ‹‹አቅም አንሷችኋልና-እገነባችኋለሁ›› ሲል ከመስማት የከፋ እንደ ሀገር ክሽፈት የለም (በነገራችን ላይ ከወራት በፊት ለኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በረከት ስምዖን፣ ቴውድሮስ አዳህኖም፣ ሶፍያን አህመድ በአጠቃላይ ሁሉም የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት አንድ ህንዳዊ ፕሮፌሰር በኢህአዴግ ጽ/ቤት ‹‹ልማታዊ መንግስት›› እንዴት ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ሲተነትንላቸው፣ እነርሱም ደብተርና እስክርቢቶ ይዘው በንቃት ሲከታተሉ የቴሌቪዥ ዋና ዜና ሆኖ የቀረበበትን ምክንያት ዛሬም ድረስ ሊገለፅልኝ አልቻለም፤ በተለይም ፕሮፈሰር እንድርያስ እሸቴ ‹‹በቃሉ የፀና…›› በሚል ርዕስ መለስን አስመልክቶ በተዘጋጀ ዶክመንተሪ ፊልም ላይ ‹‹በዓለማችን ለመጀመሪያ ጊዜ ልማታዊ ስርዓተ መንግስት ‹ዴሞክራሲያዊ ሊሆን ይችላል፤ መሆንም አለበት› ብሎ በአደባባይ የተከራከረው እኔ እስከማውቀው ድረስ መለስ ነበር›› ማለቱን፣ ተተኪዎቹ ፍልስፍናውን ገና እየተማሩት ከመሆኑ አንፃር ስናየውሀገራችን ያለችበት ሁኔታ ጉዞው ወዴት ነው? ያስብላል፡፡ …ከቶስ በተማሪ ፖለቲከኛ የሚተዳደር ሕዝብ ከኢትዮጵያ በቀር ወዴት ይኖራል?)
ክረምቱ እንዲህ እየተገባደደ ነው፡- የህዳሴውን ግድብ ከዳር ለማድረስ በቂ ገንዘብ ስላልተገኘ ተደጋጋሚ የቦንድ ሽያጭ እየተካሄደ ነው፤ አንዳንድ የመንግስት ሰራተኞችም በካድሬ ባልደረቦቻቸው ጫና በድጋሚ ቦንድ ለመግዛት መወሰናቸው ተሰምቷል፤ በርግጥ ከፍተኛ የኢህአዴግ የአመራር አባላት በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቦንድ እንዲገዙ ለመቀስቀስ የአዘጋጇቸው ስብሰባዎች ‹‹ቅድሚያ የዜጎች መብት ይከበር›› ባሉ የሀገራችን ልጆች መክሸፉም የክረምቱ የመንግስት ዋና ሥራ ነው፤ ክረምቱ እንዲህ እየተገባደደ ነው፡- በነቢብ የኢትዮጵያ፣ በገቢር የገዥው ፓርቲ የግል ንብረት የሆነው ቴሌቪዥን ጣቢያ ባለፉት ሶስት ወር ብቻ ከሃያ በላይ ‹‹ዶክመንተሪ ፊልም›› አሳይቷል (ገና ይቀጥላልም) በርዕሳቸው እንደሚከተለው እንዘርዝራቸው፡- ‹‹ኢፍቲን›› በሶማሊያ ላይ የሚያጠነጥን፣ ‹‹የጥቁር ህዝቦች ልሳን (መለስ በአፍሪካ)››፣ ‹‹ከፓን አፍሪካ እስከ አፍሪካ ህዳሴ›› የጠቅላይ ሚንስትር መለስን ህይወት የሚዳስስ፣ ‹‹ዘመነ አፍሪካ››፣ ‹‹የአፍሪካ ልሳን-መለስ››፣ ‹‹መለስ ማን ነው?››፣ ‹‹ሀገሬ-ቤቴ››፣ ‹‹ባለራዕዮቹ›› ስራ ፈጠራ ላይ የሚያተኩር፣ ‹‹ደውል›› እና ‹‹ደውል 2›› ህገወጥ-የሰዎች ዝውውርን በተመለከተ (በተለያያ ጊዜ የተላለፉ)፣ ‹‹የዲያስፖራ የልማት እንቅስቃሴ››፣ የካርታ ስራ ድርጅትን በተመለከተ፣ ‹‹የጥልቅ አስተሳሰብ ባለቤት›› በፕ/ር እንድርያስ እሸቴ ህይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን፣ ምድር ባቡር ኮርፕሬሽንን በተመለከተ፣ ‹‹ያልተለመደ ጉብኝት›› የአዲስ አበባ አስተዳደር የአምስት ዓመት የመንግስት ግንባታዎችን በተመለከተ፣ ‹‹ሼህ ኑር ለምን ሞቱ?›› የደሴውን ሼህ ኑር ይማምን ግድያ በተመለከተ፣ ‹‹የተስፋ ስንቅ››፣‹‹በቃሉ የፀና›› በድህረ መለስ ላይ የሚያተኩር፣ ‹‹ያልተጠኑ ገፆች›› በመለስ ዜናዊ ህይወት ዙሪያ (በርግጥ በዚህ ፊልም እህቱ ጠላ፣ ወንድሙ አንባሻ በመሸጥ መተዳደራቸውን በምስልም በድምፅም ማቅረቡ ምን የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ተፈልጎ እንደሆነ ለማወቅ ግራ ያጋባል፤ …ምናልባት እንዲያ እየዘረፈ ለቤተሰቦቹ ‹ሶልዲን› የማይሰጥ ‹ቆነቋና› ነበር ለማለት ይሆን? ወይስ ለአዜብ መስፍን ‹የወር ቀለባችንን እንቸገራለን› የአንድ ሰሞን ማስተዛዘኛ ምስክር ፍለጋ ነው?
በጥቅሉ ለኢህአዴግ ሕዝብን የማስተዳደር፣ ሀገርን የመምራት መገለጫ ይህ ነው፤ ሌላ አይደለም፤ ግና! ለዘመናት ያልተመለሱ ጥያቄዎቻችን ዛሬም መጮኻቸውን አላቋረጡምና እነሆ እንዲህ ቀጥለዋል፡- ሀገር ማስተዳደር ‹መለስ ጀግና ነበር› እያሉ ማሰልቸት ነውን? የመንግስትስ ስራ (ግዴታ) ምንድር ነው? ሀገሪቱን ‹‹መለስ-ፓርክ›› ወደሚል ስያሜ ከመቀየራችሁ በፊት፣ ለጤፍ ዋጋ አለቅጥ መናር ምክንያቱን ስለምን መመርመር ተሳናቸው? ሀገሪቱን በ‹አራጣ› እንደያዘ ስግብግብ ነጋዴ በሚሊዮኖች ህይወት ላይ የማይሞላ ‹ሳፋ› ደቅኖ አዋጣ፣ ግዛ፣ ክፈል፣ ገብር… እያለ የሚያስጨንቀው ማን ነው? ስለመለስ ‹የሃሳብ ምጡቅነት› መስካሪ ምሁራኖቻችን ለጎዳና ኑሮ የተዳረጉ ኢትዮጵያውያን ስንት ሚሊዮን እንደደረሱ እና እልፍ አላፍት ታዳጊዎቻችን በሴተኛ አዳሪነት እንደተሰማሩ የምትነግሩን መቼ ነው?እንዲህ የመሆኑ ምክንያትስ በማን ይሆን? ‹የሁለት ዲጂቱ›ዕድገት ሸክምን የማለዘብ አቅም ከሌለውፋይዳው ምንድር ነው? ‹ሳቅ ትዝታ› ስለሆነባቸው ጎጆዎች ለምን አትነግሩንም? መለስ ‹ያለመለማት› ኢትዮጵያ ወዴት ትሆን? ‹ፖለቲካ› ማለትስ ይህ ነውን? …ነጋ ድራስ ገ/ህይወት እንዳሉት ‹‹…መንግስት መቆሙ ለሕዝቡ ሁሉ ጥቅም ነው፡፡ ጥረቱም ህዝቡን ሁሉ በትክክል ለመጥቀም ያልሆነ መንግስት ሊቆም አይችልም፡፡›› የመተራረሚያው ጊዜም በጣም ያለፈ ይመስለኛል፡፡ አገዛዙን ‹እንደ መንግስት› መቀበሉም እንዲሁ፡፡

Wednesday, August 28, 2013

የዱርየው ወያኔ መንግሥት የውሸት አምራች ፋብሪካዎች ይዘጉ

August 28, 2013

ተሾመ ደባለቄ
‘የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያድርቅ’ ሲል የሀገሬ ሰው ሀገር ያወቀውን ፀሐይ የሞቀውን ሌባ ጨዋ ለማስመሰል የሚያጋጋው ውሸት ሲያሰለች ነው። እንደዚሁም መንግሥት ነኝ ተባዩ ወያኔም የውሸት ጋጋታው ሰውን አሰልችቶት እውነትም ቢናገር እነኳን የሚያምነው አጥቶ ሙጥኝ የያዛቸው መዋቅሮች ‘ውሸታም’’ ና  ‘ሌባ’ የሚል ስም አትረፈዋል።
woyane propaganda machine
ውርደት ያተረፈው ወያኔ የውሸት ጋጋታው አልበቃ ብሎት ለምን እውነት ተነገረ ብሎ ድርጅት መዘጋት ባልደረቦችን ማሳደድ፣ ማሰርና  እስከመግደል ደረጃ ደርሷል። በራሱ ውሸት ያበደው ወያኔ በአካባቢው ከሚያጎበድዱለት ጉጅሌዎቹ መሃል አብደሃል በሙስና ተዘፍዝፈሃል የሚለው ጠፍቶ እንደመሸበት ሰካራም ቤቱ ጠፍቶት በየሰዉ ቤት እያንኳኳ በራሱ ውሸት ተሸብሮ ህዘብን ማሸበሩን ቀጥሎበታል።
በመሰረታዊ ውሸት ላይ የተመሰረተው ወያኔ ‘ድንጋዩ ዳቦ ነው’ ብላችሁ ተቀበሉ እያለ መከራውን ሲያይ አዝለውት የሚዞሩት ጉጅሌዎቹ የውሸቱ ሸክም በዝቶባቸው  ሲዘላበዱና  በህዘብ መሳለቂያ ሲሆኑ ማየት ያሳፍራልም ያሳዝናል።
በዕውነቱ ውሸቱ በዝቶ የራሱ ነፍስ ፈጥሮ ወያኔን ማስተዳደር ከጀመረ ሰንብቷል ማለት ሀሰት አይሆንም። ይህ ከመሰረቱ በውሸት የተገነባው መንግስት ነኝ ባዩ ቡድን ወደሃላ መመለስ ስለማይችል የባሰ እያበደ ይሄዳል አንጂ እውነትን ለመቀበል ችሎታም አቅምም ሊኖረው አይቻልም። ስለሆነም እራሱን ወጥመድ ውስጥ አግብቶ ለማምለጥ ሲፈራገጥ ወገን እያቆሰለና አገር አያደማ መሆኑ ሊያስገርመን አይገባም።
ሆዳቸውን በውሸት የሞሉት ጉጅሌዎቹም ቢሆኑ ሆድን ከእውነት መርጠው እየቃዡ ምላሰቸው ተቆላልፋል። እውነት መናገርም የሚያጎርሳቸውን እጅ መንከስ ስለሆነባቸው እውነት የሚናገረውን መናከስ የሚረዳቸው መስሏቸው ሲዘላብዱ በህዘብና በሀገር ሲያፌዙ ይገኛሉ።
የቸገረው እርጉዝ ያገባል እንደሚባለው ቀንደኛው የውሸት መሪ ካለፈ ጀምሮ ውሸቱን ማስተዳደር አቅቷቸው ያዙኝ ልቀቁኝ እያሉ ሲዘባርቁ ለተመለከታቸው አብደው ሊያሳብዱ የተነሱ እንደሆኑ ግልጽ ነው። በእርግጥኝነት ሊባል የሚቻለው እብድ ማበዱን ካላመነ ጤነኛ ነኝ ብሎ እራሱን ስለሚያሳምን በእብዶች መሀል አንድ ጤነኛ ቢኖር እንኳን እንደ እብድ ስለሚቆጠር ያበዱትን ባልደረቦቹን ሊረዳቸው አይችልም።
የብዙሃን መገናኛ ላይ ያሰፈሰፉት ካድሬዎችን ብናስተውል የወያኔ ውሸት የራሱን ነፍስ እንዳላው ያረጋግጥልናል። እነዚህ የብዙሃን መገናኛ ተባዮች የውሸት ፋቢሪካ ሆነው በሶስት ፓኬጅ እያሸጉ ውሸትን ሊሸጡ ሲሯሯጡ ይታያሉ።
አንደኛው ፋብሪካ የውሸቱ ጥሬ ዘር የሚያመርተው በወያኔ የሚተዳደሩት መዋቅሮች ሲሆን የውሸት ምሶሶና በምንጭነት ፊት ቀዳሚ ሲሆን የህዋዓት ዋና መሳሪያ ነው። ሆኖም መንግሥት ነኝ የሚለው ወያኔ ስለተቆጣጠራቸው የሚያምናቸው አጥተው ወንዝ እንደሚያከራትተው ግንድ ይወዛወዛሉ።
በሁለተኛ ደረጃ ያሉት የውሽት ፋብሪካዎች ወያኔ በካድሬዎቹ ያደራጃቸው መዋቅሮችና የብዙሃን መገናኛዎች (በተለይም በስደት ላይ ያለውን ወገን ለማወናበድ) የተዋቀሩ ናቸው። እነኝህ መዋቅሮች በወያኔ ጥሬ ወሸትና ገንዘብ የሚታገዙ ስለሆኑ አላማችው በግል ስም ወያኔ በመንግሥት ስም መሸጥ ያቃተውን ውሸት ዳግም ማሸግና መሸጥ ነው። እነዚህ ግለሰቦች ወያኔ ከመጣ ጀምሮ ማንነታቸው የማይታወቅ (ጎሬላዎች) ናቸው። ከተጋለጡት መሃል የአይጋ-ፎረም ባለቤት ኢሳያስ አፅብሃ  ከሳኖዜ ካሊፎሪኒያና የትግራይ-ነት ባለቤት ሚካኤል አባይ ከዴንቨር ኮለራዶ ይገኙበታል።
በሶስተኛ ደረጃ ያሉት የውሸት ፋብሪካዎች ደግሞ በነጻ ፕሬስ ስም የሚነግዱ መዋቅሮች ሲሆኑ እነሱም በሁለት ይከፈላሉ። አንዱ በወያኔና ባልደረቦቹ የሚተዳደሩ የውስጥ ሚስጥረና ድጋፍ ያለቸውና ዜጋ ለማወናበድ የተደራጁ የብዙሃን መገናኛ መዋቕሮች ናቸው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በተቃዋሚ ስም የተደራጁ አስመሳይ መዋቅሮች ናቸው። የሁለቱም አላማ አንድ ቢሆንም የውሸትን ማሸግና መሸጥ መንገዳቸው ይለያያል። ነገር ግን ሁለትም የወያኔን ሥርዓት በተወሰነ ደረጃ ይገስጻሉ ግን አላማቸው ወያኔን ማቆየት ስለሆነ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ እነዳይነኩ የታዘዙ ይመስላሉ። ሁሉቱም ከውጭ ሚዲያ የመጣን ወያኔን የሚያሞግስ ዜና አያመልጣቸውም ወይን ይፈጥራሉ። ሁለቱም ህዘብ ላይ የሚደርሰውን ግፍና ዘረፋ  ለመሸፈንና ለማደናገር ዘመቻ ላይ የተሰማሩ ናቸው። ሁሉቱም በጋዜጣ ስም አሰመስለው የፐሮፖጋነዳ  ሥራ ለመስራት ውስጥ ለውስጥ የተደራጁ የሥርዓቱ  ጉጅሌዎች ናቸው።
በውሸት ላይ የተሰማሩት የወያኔ ባልደረባና አስመሳይ ጋዜጠኞች ሥራዓቱ እየፈራረሰ ሲመጣ የሚያደርጉት ስለጠፋባቸው ወያኔን ለማዳን ያላቸው ብቻ ምርጫ የእስላም አሸባሪ መጣባችሁ እያሉ ማስፈፈራራት አዲሱ ሞያቸው ሆኗል። እሱንም ጉዳይ በተለያየ የውሸት ማቀነባበር መንገድ እያዘጋጁ ህዘብን በማተራመስና ለወያኔ ጊዜ ሊገዙለት እየጣሩ ነው።
ለምሳሌ ቀንደኛዎቹ የወያኔ የዜና መዋቅሮች የውሸት ቲያትር እያሰሩ ሲያሰራጩ በግል የዜና መዋቀር ስም የሚቀሳቀሱት ደግሞ ቲያትሩን እውነት ለማስመሰል የውጭ አከራሪዎችን ዜና በማነፈስ ህዘብን ቢያንስ እንዲጠራጠር አልያም እንዲያምን ይጥራሉ። ከዚህ በፊትም በአማራው ህብረተሰብ ላይ ያወረዱበት የውሸት ዘመቻ ስኪ ሆነ ብለው ስለሚያምኑ በእስልም ተከታዮች ወገኖቻችን ላይ እየመከሩት መሆኑ በግልጽ ይታያል።
ወገንም የነፃ ብዙሃን መገናኛዎችም የፖሎቲካና የሲቪክ መዋቅሮችን እነኚህን የውሸት ፋበሪካዎችንና የሚያንቀሳቅሷቸውን የውሸት መልክተኞች ማወቅ ማጋለጥና ከዛም አልፎም ማዘጋትና ተጠያቂ ማድርግ ግድ ይላል።
ትግሉ ማንንም ግለሰብንና ቡድን የውሸት ፋበሪካ ሰለባ እንዳይሆን የመከታተልና የመቅታት ዋናው ስራው መሆን ይኖርበታል። የወያኔ ሥርዓት እየገማ በመጣ ቁጥር ባልደረቦቹ እያባሱ መግማታቸው አይቀሬ ስለሆነ እያናዳንዱ ዜጋ እነኝህን የውሸት መልክተኞች መከታተል ሀላፊነት አለበት። የውሸት ፋብሪካ መዘጋትና ሥራ አስኪያጂዎች መቅጣት የዲሞክራሲ ትግል ዋናው ምሶሶ ስለሆነ ፋብሪካዎቹም ሆነ ሥራአስኪያጆቹ ዕውነት ያመርታሉ ማለት የህልም እነጀራና ሞኝነት ነው።
የኢትኦጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ከመጣ ጀምሮ እንቅልፍ የነሳቸው የወያኔ ካደሬዎችና ተጠቃሚዎች የገዢውን ቡድን ውሸት እያሰራጩ ኢሳትን  የሚያጋልጠውን እውነት ሊነኩት አቅቷቸው አይናቸውን ጨፍነው ጆሯቸውን ደፍነው ቅዠት ውስጥ እንዳሉ እራሳቸው ይመሰክራሉ።  ኢሳት አንዱ ትልቁ ሥራው እንኝህን የወያኔን ውሸት ፋብሪካና ቸርቻሪ ባለቤቶችን ለህዘብ ማጋለጥና ማንነታቸውን ህዝብ እንዲያውቃቸው ማድረግ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነቱን በቶሎ የሚጎናፀፈውና የወደፊት ሰላምና ብልጽግና የሚያገኘው የውሸት ፋብሪካዎች ሲዘጉና የእውነት ፋብሪካዎች ሲስፋፉ ነው።  ይህ መሰረታዊ መፍቴህ የውሸት ፋበሪካ ባለቤቶችን እያሳበዳቸው ጨርቃቸውን ጥለው እየሮጡ እነዳሉ ግልጽ እየሆኑ መጥተዋል። ሆኖም በቂ ትኩረት ተሰጥቶት ስላልተሰራ ተደብቀው ውሸትን ማምረትና መቸርቸር ሥራቸውን ቀጥለዋል።  በድርጅት ከመስራት በግለሰብ መሥራት የባህል ድክመት ብዙዎቹን የነፃ ሚዲያዎችን ያዳከመና የውሸት ፋብሪካዎችን እድል ከፍቶላቸዋል ማለት ይቻላል።
የውሸት ፋብሪካዎችን ለማዘጋት ባለቤቶቹንም ለመቅጣት እንዘጋጅ እንደራጅ
ድል ለኢትዮጵያ ህዘብ

በመጪው እሁድ በአዲስ አበባ ሰማያዊ ፓርቲ እና ኢህአዴግ በየፊናቸው ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተከትሎ አዝማሚያው ወደ ውጥረት እያመራ መሆኑን ታዛቢዎች ገለጹ።

ነሃሴ ፳፩(ሃያ አንድ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰማያዊ ፓርቲ ቀደም ካሉት ጊዜያት ጀምሮ ለነሐሴ 26 ቀን 2013 ዓመተምህረት ሰልፍ እንደሚጠራ አስታውቆ የቅስቀሳ ሥራ መሥራት በጀመረበት ጊዜ፤ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ሰሞኑን  በዚያው ቀን ሰልፍ ለማድረግ ጥሪ ማቅረቡ ያታወቃል።
በተለይ በኢህአዴግ የሰልፍ ጥሪ  የሴትና ወጣት ማህበራት፣የመንግስት ሠራተኞች፣ የሀይማኖት ተቋማትና  ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጭምር በግዳጅ እንዲወጡ መታዘዛቸው፤ ሁኔታውን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ይወስደዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ሰማያዊ ፓርቲ፤የ አፍሪካ መሪዎች አዲስ አበባ ላይ በተሰበሰቡበት ወቅት ሰልፍ ለማድረግ  ወስኖ ሳለ፤  የአዲስ አበባ መስተዳድር የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ ክፍል ፤ወቅቱ የመሪዎች ስብሰባ ከመሆኑ አንፃር በዕለቱ በቂ ሀይል እንደሌለውና ሰልፉን ለሳምንት እንዲያሸጋግሩ በጠየቀው መሰረት፤ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፉን ማሸጋገሩ ይታወሳል።
ይሁንና ያን ውሳኔ ያሳለፈው የመስተዳድሩ የሰልፍ ፈቃድ ክፍል ፤ ኢህአዴግ-ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ ሊያደርግ ባቀደበት ተመሣሳይ ቀንና ከተማ ውስጥ ሰልፍ ለማድግ ሢነሳ ምንም አለማለቱ ታዛቢዎችን አስገርሟል።
ኢህአዴግ-የሸህ ኑሩን ሞት ተከትሎ በሌሎች ክልሎች እንዳደረገው ሁሉ በአዲስ አበባ ሊያደርገው በተዘጋጀው ሰልፍም የሙስሊሞችን የመብት ይከበር እንቅስቃሴ ከሽብርተኝነትና ከጽንፈኝነት ጋር በማያያዝ በሰልፈኛው ለማስወገዝ መዘጋጀቱ ታውቋል።
ከዚህም ሌላ የገዥው ፓርቲ ተቃዋሚዎች ሰልፍ በሚወጡበት ዕለት -ኢህአዴግ የከተማዋን ነዋሪዎች በግዳጅ “እኔን ደግፋችሁ ውጡ”ማለቱ፤ በህብረተሰቡ ዘንድ አላስፈላጊ መቃቃርን፣ መወጋገዝንና መለያዬትን  ለመፍጠር በማሰብ  ጭምር ነው የሚሉ አስተያየቶችም እየተሰነዘሩ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ  መንግስት  የጠራውን ሰልፍ እንዲሰረዝ ሰማያዊ ፓርቲ ጠየቀ።
ፓርቲው፦”መንግሥት ለተፈጠረው ችግር በአስቸኳይ ማስተካከያ እንዲያደርግ እንጠይቃለን!!”በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ፤ ሰማያዊ  ፓርቲ ግንቦት 25/2ዐዐ5 ዓ/ም. ታላቅ ህዝባዊ ተቃውሞ ሰልፍ በተሳካ ሁኔታ ማድረጉን አስታውሶ፦” መንግሥት ላቀረብናቸው ጥያቄዎች በሦስት ወር ውስጥ መልስ የማይሠጥ ከሆነ በተጠናከረና በተደራጀ መልኩ ጥያቄያችንን በድጋሚ በህዝባዊ ተቃውሞ ሰልፍ እንደምናቀርብ በግንቦት 25/2ዐዐ5 ዓ/ም. በተደረገው ሠልፍ ላይ ለህዝብ ቃል በገባነው መሠረት ነሃሴ 26/2ዐዐ5 ዓ/ም. በድጋሚ ሰልፍ ጠርተን አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረግን መሆኑን ለህዝብ በልዩ ልዩ መገናኛ ዘዴዎች ገልፀናል” ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ለሰልፉ በሰላም መጠናቀቅ አስፈላጊው ትብብር እንዲደረግልን አዋጁ በሚጠይቀው መሠረት ለአዲስ አበባ መስተዳድር ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማስታወቂያ ክፍል ጉዳዩን እንዲያውቀው አድርገናል ብሏል-ሰማያዊ ፓርቲ።
ይሁን እንጂ ፓርቲያችን የተቃውሞ ሰልፍ በጠራበት ግዜና ቦታ ላይ በሌላ አካል ሰልፉ መጠራቱን በትናንትናው ዕለት ነሀሴ 20 ቀን 2005 ዓ.ም በመንግሥት ቴሌቪዥን ዜና ሰምተናል ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ከዚህም በላይ  የመንግሥትን መዋቅር በመጠቀም  ዜጐች በዚህ ሰልፍ ይገኙ ዘንድ  በግድ እንዲፈርሙ እየተደረገ መሆኑን ከአዲስ አበባ ኗሪዎች አረጋግጠናል ሲል አትቷል።
ሰማያዊ ፓርቲ አስፈላጊውን የህግ ቅድመ ሁኔታ አሟልቶ ነሐሴ 26/2ዐዐ5 ዓ/ም በመስቀል አደባባይ የጠራውን የተቃውሞ ሰልፍ ለህዝብ ያሳወቀና አስፈላጊውን ዝግጅት ያጠናቀቀ በመሆኑም፤ ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ በጠራበት ቀንና ሠዓት በሌሎች አካላት የተጠራው ሰልፍ ከመረጃ እጥረት ከሆነ እንዲሠረዝ እንጠይቃለን ሲልም  ኢህአዴግ የጠራውን ሰልፍ እንዲሰርዝ  ጠይቋ ል።
ሰማያዊ ፓርቲ በማያያዝም፦”ይህ ካልሆነ ግን ሰማያዊ ፓርቲ በህጋዊ መብቱ የሚያደርገውን የተቃውሞ ሰልፍ ሆን ብሎ ለመረበሽና አቅጣጫውን ለማስቀየስና በዜጐች መካከል ግጭት ለመፍጠር የታቀደ ስለሆነ ለሚፈጠረው ችግር ተጠያቂ መንግሥት መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብና የሚመለከታቸው አካላት እንዲያውቁት በአፅንዖት እንገልፃለን፡፡” በማለት አሣስቧል።

የግንቦት7 አባላት ናቸው የተባሉ ሰዎች ክስ ተመሰረተባቸው

ነሃሴ ፳፩(ሃያ አንድ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከተለያዩ የአማራ አካባቢዎች ተያዙ የተባሉ 10 ሰዎች ዛሬ በአቃቂ 4ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።
ዘመኑ ካሴ ከተባለው ሰው በስተቀር ሌሎች 9ኙ ተከሳሾች ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን ለህዳር 2 ቀን፣2006 ዓ/ም ቀጠሮ ተሰጥቶአቸዋል።
ፍርድ ቤት ከቀረቡት መካከል የባህርዳር ከተማና ዙሪያዋ ነዋሪዎች የሆኑት አሸናፊ አካሉ፣ ደህናሁን ቤዛ፣ ምንዳየ ለማ፣ አንሙት የኔዋስ፣ ሳለኝ አሰፋ ፣ የክልሉ የማረሚያ ቤት ረዳት ምክትል ኢንስፔክተር ሙሉየ ማናየ ፣ ጸጋው ካሳ ፣ የአለም አካሉና ሙሉ ሲሳይ ይገኙበታል።
በግለሰቦች ላይ የተመሰረተው ክስ አሸባሪ ከሆነው ግንቦት 7 ጋር ግንኙነት በመፍጠር ጥቃት ለማድረስ ተንቀሳቅሰዋል ሚል ነው።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የግንቦት7 ሊ/መንበር ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ መንግስት መብቱን የጠየቀውን ሁሉ ግንቦት 7 እያለ መወንጀሉ የተለመደ ባህሪው ነው ብለዋል
ገዢው ፓርቲ በመጪው እሁድ በሀይማኖት ጉዳይ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራቱን በተመለከተ ምን አስተያየት አለዎት የተባሉት ዶ/ር ብርሀኑ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ህዝቡን በሀይማኖት ለማጋጨት ላቀደው እቅድ በተመለደ ትእግስቱ እንዲያከሽፈው ጠይቀዋል።

የኢህአዴግ ስውር ሴራ በሮቤ ከተማ ተጋለጠ!!!

ሐገሪቷን የሚያስተዳድራት ማነው? የባሌ ሮቤ ሰላማዊ ሰልፍ ለምን ተደናቀፈ? ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ ማብራሪያ የሚሊየኖች ድምፅ ለነፃነት ንቅናቄ በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት የነፃነት ድምፅ ማስተጋባት ከጀመረ እንሆ ዛሬ ስልሳሰባተኛ(67) ቀኑን ይዟል። ፓርቲያችን በእዚህ ታላቅ ሕዝባዊ የነፃነት ንቅናቄ መሪር የሆነ ውድ ዋጋ እየከፈለ ድምፅ አልባ ለሆኑትሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን ድምፅ በመሆኑ ታላቅ ደስታ ይሰማዋል።

 ላለፋት ስምንት ዓመታት ሰቆቃ እና ግፍ በገዢዎቻችን ሲፈፀምበት የኖረው የገጠሩም ሆነ የከተማው ታላቁ ህዝባችን‘አንድነት ፓርቲአችን አስትንፋሳችን’ በማለት አንድነት ፓርቲ ባመቻቸለት ህዝባዊ ስብሰባዎች እና ሠላማዊ ሠልፎች በነቂስበመውጣት የታፈነ ብሶቱን በግልፅ በአደባባይ ላይ በማሰማቱ ኢህአዴግ እና ህዝቡ ዛሬም ድረስ ተለያይተው እንዳሉ አንድነት ፓርቲበማያወላዳ ሁኔታ በሚሊዮኖች ድምፅ ንቅናቄ በህዝባችን መሀል በመገኘት አረጋግጧል። 

ኢህአዴግ የቀረው በውሸት እና በሴራ የተሞላ የቅጥፈት ፕሮፖጋንዳ ብቻ መሆኑን ይበልጥ ያረጋገጠልን የባሌ ዞንአስተዳደር እና የሮቤ ከተማ አስተዳደር ያዘጋጁት በሀገር ሽማግሌዎች ስም የተቀነባበረው የእናደራድራችሁ አሳፋሪ ድራማለኦህዴድም ሆነ ለኢህአዴግ ታላቅ ውድቀት ነው።

አንድነት ፓርቲ በባሌ ሮቤ ከተማ ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ህጉ በሚያዘው መሰረት ነሐሴ 13/2005 የሰላማዊ ሰልፍማሳወቂያ ደብዳቤ ለከተማዋ አስተዳደር አስገባ። ጉዳዩን የሚከታተሉት የፓርቲው ተወካዮች ደብዳቤው ከገባ ከ48 ሠዓት በኋላ ወደመደበኛ ቅስቀሳቸው መግባት እንደሚችሉ ህጉ እንደሚፈቅድላቸው የተረዱት የፓርቲያችን ትንታግ ታጋዮች ጊዜ ሳያባክኑየተዘጋጀውን የቅስቀሳ በራሪ ወረቀት በከተማ ውስጥ ማሰራጨት ጀመሩ።

ሁኔታውን በቅርብ ሲከታተሉት የነበሩት የፌደራል መንግስት እና የክልሉ መንግስት ከሮቤ ከተማ አስተዳደር ጋርበመቀናጀት አንድነት ፓርቲ ላይ ያጠመዱት ሴራ ለመተግበር የከተማው ከንቲባ አቶ አብዱል ላጥፍ ነሓሴ 13/2005 ለገባላቸውየፓርቲው ደብዳቤ መልስ ያሉትን ነሓሴ 13/2005 ቀን እንደ ተፃፈ ተደርጎ ፓርቲው አላማ ያሉትን ዘርዝረው ነሓሴ 17/2005 ዓ.ምደብዳቤ ለፓርቲው ተወካዮች ሰጡ። የተባሉትን ሰበቦች እና ምክንያቶችን በሙሉ አሟልቶ ፓርቲው የእዚያኑ ዕለት በደብዳቤ ምላሽቢሰጥም የከተማው አስተዳደር ባለስልጣኖች ከንቲባውም ጭምር ቢሮአቸውን ዘግተው ጠፉ። መዝገብቤትም ለማስገባትየተደረገው ጥረት በመዝገብ ቤት ሰራተኞች እምቢ ባይነት ሳይሳካ ቀረ። የአምባ ገነኑን የኢህአድግ ባለስልጣኖችን ነውረኛ ስራቀድሞ የሚያውቀው የአንድነት ፓርቲ የተዘጋጀውን ደብዳቤ በሪኮማንዴ በፓስታ ቤት በኩል አንዲደርሳቸው በማድረግ ምንምመፈናፈኛ ሰበብ እንዳያገኙ አደረገ።

ግራ የገባቸው የከተማው አስተዳዳሪዎች ተሰባስበው ከላይ በተሰጣቸው ትእዛዝ መሰረት አንድነትን የማጥቅያ ሌላ ሴራተጠቅመው መጥታችሁ የሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያውን ቅፅ ሙሉ በማለት ለተወካዮቻችን ጥሪ አደረጉ። የፓርቲው ተወካዮችስራቸውን እየሰሩ ቅፁን የሚሞሉ እና የሚፈርሙ አባላትን በመመደብ ተወካይ ብቻ ወደ ወስተዳድሩ ፅ/ቤት ላኩ። የጠበቃቸው ግንየተቀናጀ ሴራ ነው። አንድነት ፓርቲን በህግ የሚያስጠይቅ እንዲሁም ያዘጋጁትን የሀይል ርምጃ ህጋዊ የሚያደርግ፤ ደብዳቤ ካስገባን48 ሰዓታት ባነሰ ጊዜ ሰልፍ እወጣለሁ ብሎ ፓርቲው ነሓሴ 17/2005 ደብዳቤ እንዳስገባ ተደርጎ ይህንኑ ቀን የጠቀሰ ቅፅአዘጋጅተው የአንድነትን ተወካዮች አንዲፈርሙ ተጠየቁ። ቀድሞውኑ ሴራው የገባው የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር በሰጠውመመርያ መሰረት ቅፁ ላይ የምንፈርመው ደብዳቤአችንን ያስገባንበትን ነሐሴ 13/2005 ቀን ከጠቀሰ ብቻ ነው በማለት የአንድነትተወካዮች አንፈርምም አሉ።

አንድነት ፓርቲን በጉልበትም በህግም ለማኮላሸት ኢህአድግ ያዘጋጀውን ሴራ በጥበብ ማክሸፍ ተቻለ። ኢህአዴግ ለሌላሴራ ማቀንቀኑን ወድያውኑ ተያያዘው።

የፓርቲው ቀስቃሽ ቡድን በ50‚000 የሚገመት በራሪ ወረቀት መበተኑን እና ከ5‚000 በላይ ፖስተር በእለቱ በመለጠፍየፓርቲውን መልእክት ለታፈነው የሮቤ ከተማ ህዝብ አደረሰ። በሁለት መኪና መጠነኛ ቅስቀሳ ካደረገ ከ 1፡00 ሰዓት በኋላመኪናዎቹ ከነቀስቃሽ ቡድኑ ከነሀሴ 18/2005 እስከ እሁድ ነሀሴ 19/2005 ድረስ በታጣቂዎች ከቆሙበት አንዳይንቀሳቀሱ ታገቱ።የትራፊክ ፖሊሶችም መኪናዎቻችንን በማገት ያለቆቻቸውን ትዕዛዝ ተግባራዊ አደረጉ። በዚህ መሀል ነው በሽማግሌ ስምያደራጃቸውን 15 የሚሆኑ የኦህዴድ ካድሬዎች “ነገ የሚከሰተው ደም መፋሰስ አሳስቦን ነው የመጣነው እናወያያችሁ” በማለትከምሽቱ 1፡30 ባረፍንበተ ሆቴል ተሰባስበው የመጡት። ለሀገር ሽማግሌ ክብር የሚሰጠው አንድነት ፓርቲ ሽማግሌዎች የተላኩበትንዝርዝር መልእክት ካዳመጠ በኋላ የእሁዱን ሰላማዊ ሰልፍ በምንም ተአምር እንደማንሰርዘው፤ ይልቁንም የከተማው መስተዳድርለፖሊስ የሀይል እርምጃ ውሰዱ ብሎ ያስተላለፈውን መመሪያ እንዲስብና ህገመንግስቱን እንዲያከብር ሽማግሌዎቹ ምክራቸውንለገዢው ፓርቲ ባለ ስልጣኖች እንዲለግሱ መልእክት በመንገር ውይይቱ ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት ተጠናቀቀ። 

በኢህአድግ የተለመደቀመር የቅስቀሳ ጊዜያችንን በጉልበት እና በማስመሰል ለመስረቅ የተደረገውን የተለመደ ቅንብር አንድነት ፓርቲ ቀድሞ የሚያውቀውጉዳይ በመሆኑ ሁለት ተደራዳሪዎችን ብቻ በመመደቡ ሌላው ግብረኃይል ሳይዘናጋ የቅስቀሳ ወረቀቱን በማሰራጨቱ ኢህአዴግያሰበውን አንድነትን የመነጠል ሴራ ሳይሳካለት ቀርቷል።

እነዚያው የሀገር ሽማግሌዎች የተባሉ ግለሰቦች “መስተዳድሩ አሁን ሊያነጋግራችሁ ዝግጁ ነው። ቢሮ ድረስ ኑ እናተወያዩ” በማለት በሰላማዊ ሰልፉ ቀን እሁድ ከጥዋቱ 1፡00 ሰዓት እኛን ቀጥረውን በሰዓቱ ስንደርስ የኦሆዴድ ባለስልጣኖች ግንየጠዋቱ የቅስቀሳ ስዓታችንን ለመስረቅ ከጠዋቱ 1፡40 በሁለት ኮብራ መኪና እና ታርጋ በሌላት በአንድ መኪና በደህንነት ባለስልጣኖች ታጅበው መጡ።
ውይይቱ በዞኑ ም/አስተዳዳሪ አቶ ሰሎሞን አወያይነት የከተማው ከንቲባ፣ የኦሆዴድ ተጠሪ የኮምኒኬሽን ኃላፊ ሌሎችምከ15 ያላነሱ ባለ ስልጣኖች እንዲሁም በርካታ የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ሦስት የመንግስት ካሜራዎች ተጠምደው ውይይቱተጀመረ።

የሽማግሌ ካባ የለበሱት የኦሆዴድ ካድሬ የሆኑት የሀገር ሽማግሌዎች ተወካይ ነኝ ያሉት ግለሰብ ውይይቱን በንግግርሲጀምሩ “እናንተ የነፍጠኛን ስርዓት ልታመጡብን ነው። እኛን ሳታነጋግሩ ሳንፈቅድላችሁ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንዴትአሰባችሁ? አሁንም ይህንን ሰላማዊ ሰልፍ አታደርጓትም። የሮቤ ህዝብ እኛን ዎክሎናል መንግስት እንኳን ቢፈቅድላችሁ እኛሽማግሌዎች አይደረግም ብለናል አቁሙ” በማለት የተጫኑትን ዉሳኔ በሚደንቅ ሁኔታ አስተላለፉ። በእዚያው መድረክየኢህአዴግ/ኦህዴድ ማንነት እና ጭንብል ለዓለም ህዝብ ተጋለጠ። አንድነት ፓርቲም ይህንን ከላይ እስከታች ባሉ ባለስልጣኖችየተቀነባበረውን ድራማ በካሜራ ቀርፆ ያስቀረ በመሆኑ በእጃችን የሚገኘውን የውይይቱን ይዘት የያዘውን ቨድዮ እንድትመለከቱበአክብሮት  እየጋበዝን አንድነት ፓርቲ የኢህአዴግን እውነተኛ ገፅታ በመረጃ ማጋለጡን  አጠናክሮ ዛሬም ነገም ይቀጥላል።

በሮቤ ከተማ ለቅስቀሳ የተላከው ቡድን በመስተዳድሩ ባለስልጣናት ትእዛዝ ከምሽቱ 4፡00 ስዓት አልጋ ከያዙበትታይታኒክ ሆቴል በግፍ ተባረው፤ የያዙትን ቦርሳ እንኳን ከመኝታ ክፍላችው ሳያወጡ በግፍ አውላላ ሜዳ ላይ ወንጀልእንዲፈፀምባቻው የከተማው መስተዳድር የፍፀመውን መንግስታዊ ውንብድና ፓርቲአችን በዝምታ የሚያልፈው ጉዳይ አይደለም።የመኪና ሹፊሮቻችንን በውድቅት ሌሊት ጭንብል ባጠለቁ ከ 20 በላይ ታጣቂዎችን በማሰማራት በማስወረር በጉልበት ክፍላቸውውስጥ በመግባት ስለተፈፀመው ወንጀል አንድነት ፓርቲ በህግ የሚጠይቅ ሲሆን ታላቁ የሮቤ ከተማ ነዋሪ ህዝብ መብቱንለማስከበር ያደረገውን ትንቅንቅ አንድነት ፓርቲ ከልብ ያደንቃል። ምስጋናውንም በእዚህ አጋጣሚ ያቀርባል።

ድል ለታፈነው የኢትዮጵያ ህዝብ!!!

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ
ነሐሴ 21 ቀን 2005 .
አዲስ አባባ¾

 (ምንጭ፡- ሰንደቅጋዜጣ 9ኛ ዓመት ቁጥር 416 ረቡዕ ነሐሴ 22/2005)