Sunday, February 21, 2016

የፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አዛዦች በአዲስ አበባ ስብሰባ አካሄዱ፡፡ ስብሰባው ያለምንም ውጤት በግጭት ተቋጭቷል

February 21,2016
የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ

የፌደራል ፖሊስ ከፍተኛ አዛዦች በአዲስ አበባ ከየካቲት 9 እስከ 12 2008 ዓ.ም የተሰበሰቡ ሲሆን የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የፀጥታ ሁኔታ እና የአባላት መክዳት እያነሱ ከተወያዩባቸው አጀንዳዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በስብሰባው ላይ የአማራና የኦሮሞ ተወላጅ አዛዦች "እኛ ከእናንተ የተሻለ የትምህርት ደረጃና ልምድ እያለን ሁሉንም ቦታ ጠቅልላችሁ ይዛችሁት ተገቢው ቦታ አልተሰጠንም..." በማለት ህወሓቶችን ልካቸውን ነግረዋቸዋል፡፡
ህወሓቶች በፌደራል ፖሊስ ተቋም ውስጥ ባሰፈኑት ዘረኝነት ምክንያት ሰራዊቱ በመፍረስ ላይ እንደሚገኝ ስብሰባው ላይ በተደጋጋሚ ተወስቷል፡፡ በውይይቱ ላይ ተቃውሟቸውን ያሰሙ የኦሮሞና አማራ ተወላጅ አመራሮች ከህወሓቶች "የእናስራችኋል" ማስፈራሪያ ደርሷቸዋል፡፡
በመጨረሻም ስብሰባው ወደ ለየለት ንትርክና አምባጓሮ በማምራቱ አብዛኞቹ አዛዦች እንዲበተኑ ተደርገው ውይይቱ በጥቂት ዋና፣ ዋና አመራሮች ለተጨማሪ ጊዜ ተካሂዷል፡፡ የፌደራል ፖሊስ አደረጃጀት ሊፈርስ እንደሚችልም ጭምር ጭምጭምታ ተሰምቷል፡፡
በተያያዘ ዜና የሚከዱ የፌደራል ፖሊስ አባላት ቁጥር አሁንም ከቀን ወደ ቀን እየናረ መምጣቱ እየተነገረ ነው፡፡ በጎንደር ብቻ ቢያንስ በቀን 3 የፌደራል ፖሊስ አባላት እንደሚከዱ የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ ዜና ምንጮች ገልፀዋል፡፡

No comments: