Friday, October 9, 2015

የሕወሓት ሰዎች ዶላርን በሰሜን አሜሪካ በ23 ብር እየመነዘሩ ሃብታቸውን በማሸሽ ላይ መሆናቸው ታወቀ

October 10,2015

የሕወሓት ባለስልጣናት ከሃገር ቤት ሃብታቸውን ለማሸሽ እየጠቀሙበት ያለው ዘዴ የኢትዮጵያን ባንኮች ከመጉዳቱም በላይ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አስፈሪ ዳመና እንደጣለበት ተሰማ:: በአሁኑ ወቅት የሕወሓትና የተላላኪዎቹ ድርጅቶች ባለስልጣናት በሙስና ያከበቱትን ሃብት እያሸሹ ያሉት እዚህ ሰሜን አሜሪካ ወደ ሃገራቸው ዶላር መላክ የሚፈልጉትን በ23 ብር ሃገር ቤት ላይ እንመነዝርላችኋለን በሚል እንደሚቀበሉና በዚህም ጥቁር ገበያ የሕዝብ ሃብት እየሸሸ መሆኑ ተጋልጧል::

በአሁኑ ወቅት በዋሽንግተን ዲሲ; በሲያትል; በዴንቨር; በሚኒያፖሊስ; በአትላንታ; በዳላስ; በቺካጎ; በሂውስተን; በኦሃዮ; በፖርትላንድ; በላስቬጋስ; በካሊፎርኒያ የተለያዩ ከተሞች; በአሪዞና በተዘረጉ ኔትወርኮች ዶላር በጥቁር ገበያ 23 ብር እየተመነዘረ መሆኑ ታውቋል::

የገንዘቡ ዝውውር የሚደረገው ከላይ በተጠቀሱት ከተሞች ባሉ ኔትዎርኮች መካከል ዶላሩን እዚሁ ይሰጡና ሃገር ቤት በግለሰቦች አማካኝነት በ23 ብር ምንዛሬ ይሰጣል:: ዘ-ሐበሻ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድረገጽ ባገኘችው መረጃ መሰረት በዛሬው ዕለት የዶላር ምንዛሬ ዋጋ 20.85 ሲሆን በ23 ብር በጥቁር ገበያ እየሸጠ ይገኛል::

ዶላር በሕገወጥ መንገድ እንዲህ መተላለፉ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ መንግስት ዘንድ ያለውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት የሚያባብሰው መሆኑ እየታወቀ የሕወሓት ሰዎች እንዴት እንዲህ ባለው ሕገወጥ ተግባር ላይ እንደተሰማሩ የሚያስገርም ነው የሚል አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች ከጥቂት ጊዜያት በፊት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ “የኢትዮጵያን መንግስት በኢኮኖሚ ማዳከም ካስፈለገ ከውጭ የሚላኩ ዶላሮች በኢትዮጵያ ባንኮች በኩል መተላለፍ የለባቸውም:: ሕዝቡ ዶላሩ መንግስት እጅ በማይገባበት መልኩ ገንዘቡን ይላክ” ማለታቸውን ይጠቅሳሉ::
ምንጭ ዘ-ሐበሻ

No comments: